የደከመን መርገጥ ሳይሆን የደከመን ማገዝ ነው ትክክል – (ምላሽ ለአቶ ይገረም አለሙ)- ግርማ ካሳ

 

ይገረም አለሙ የተባሉ ጸሃፊ “ድርድሩ” በሚል ያቀረቡትን ጽሁፍ  ዘሃበሻ ላይ አነበብኩ። እኝህ ሰው ከሚጦምሩትና ከሚጽፉት ዉጭ ማን እንደሆኑ፣ አገር ቤት ይኑሩ፣ ዉጭ አገር፣ በእዉነተኛ ስማቸው ይጻፉ፣ በብእር ስም ብዙ የማውቀው ነገር የለም። ሆኖም ባቀረቡት ሐሳብ ዙሪያ እኔም የተሰማኝን አንዳንድ ምላሾሽ፣ በአክብሮት መስጠት ፈለኩ።

“ድርድር በእነማን መካከል፣ ድርድር እንዴትና በምን ሁኔታ? ወዘተ የሚሉት ጥያቄዎች መመለስ የሚችል አስተያየት መጻፉ፣ ልምድ ማካፈሉ ነበር የሚበጀው፡፡ እኔ ይህን ለማድረግ የሚበቃ እውቀትም ልምድም የለኝም፡፡ ፍረጃና ውንጀላ ላይ በመሮጥም ሆነ ጭፍን ድጋፍ በመስጠት  ደግሞ አላምንም፣ በዚህ መካከል ሆኜ ስለ ድርድሩ የተሰማኝን  ልበል፡” ሲሉ ነው የጀመሩት ጽሁፋቸው። ሆኖም ግን እንዳለ ጽሁፋቸው፣ እንኳን ለድርዱሩ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን ሊያቀርቡ ቀርቶ፣ ጭራሽ ፍረጃና ወገዛ የሞላበት፣  “ድርድሩ መደረግ የለበትም” የሚል አቋም ያንጸባረቀ ጽሁፍ ነው።

አቶ ይገረም “ወያኔ የድርድር ጥሪ ያቀረበው በመላ ሀገሪቱ በተለይ ደግሞ በኦሮምያና በአማራ ክልሎች በተቀጣጠለው የህዝብ ቁጣና እንቢተኝነት በደረሰበት ድንጋጤ መሆኑን ወያኔዎችም ቢሆን የሚክዱት አይመስለኝም፡” ሲሉ የጻፉት ትክክለኛ አባባል ነው። በኦሮሚያና በአማራው ክልል የተከሰተው ተቃዉሞ ድንጋጤ ዉስጥ ከመክተትም ባለፈ፣ በዉስጣቸው ከፍተኛ የሆነ መከፋፈልን ነው የፈጠረው። በተለይም በብአዴን እና በሕወሃት መካከል ብዙዎች ያልተረዱት ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ነው ያለው። የብአዴን መካከለኛና ታችኛው አመራሮች ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል የሕወሃት የበላይነት መቆም አለበት ብለው የቆረጡና የተነሱ ናቸው።

አቶ ይገረም ድርድሩ የሕዝብ ትግል ዉጤት መሆኑን ከገለጹበት አባባል በስተቀር ግን፣ ሌሎች ያሰፈሯቸው ነጥቦች በድርዱሩ ላይ ከወዲሁ ዜጎች ጨለምተኛ አመለካካት እንዲኖራቸው የሚገፋፉ፣  ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ ፣ በመፍትሄ ላይ ሳይሆን ብሶት በማሰማት ላይ ያተኮሩ ደካም ነጥቦች እንደሆኑ ነው ለማየት የቻልኩት።

እኝህ ሰው በተለይም ተቃዋሚዎችን የገለጹበት አገላለጽ ከማስገረም አልፎ አስቆኛል። “ይቅርታ ይደረግልኝና የድርድሩ ተካፋይ የተባሉትን ፓርቲ ብሎ ለመጥራት አንደበቴ፣ ለመጻፍ ጣቶቼ እሽ አይሉኝም፡፡ ምክንያቴ ደግሞ ለድርጅቶቹ ወይንም ለመሪዎቹ ጥላቻ ኖሮኝ ሳይሆን ፓርቲ ለመባል የማይበቁ በመሆናቸው ነው” ይሉናል አቶ ይገረም። እርግጥ ነው ተቃዋሚዎች ጠንካራ ናቸው ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ ነው። እርግጥ ነው በተቃዋሚዎች ዉስጥ በየትኛውም ድርጅት ችግሮች እንዳሉ ችግሮች አሉ።  ሆኖም ግን ድርጅቶቹ የሚጠናከሩበትን መንገድ ከመፈለግና በዚያም ረገድ ሐሳቦችን ከመስጠት በዚህ መልኩ ፣ በትንሹም ቢሆን ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ወገኖችን እንቅስቃሴ ማሳነስና ዜሮ ማስገባት፣ በግሌ ሃላፊነት የጎደለው አድርጌ ነው የምወስደው።

በነገራችን ላይ አቶ አቶ ይገረም ተቃዋሚዎች ሲሉ ሁሉንም ጨፍልቀው ማየትቸው ራሱ አንዱ ትልቁ ድክመታቸው ነው። ሰማያዊ ፓርቲ፣ መኢአድ፣ መድረክና ኢዴፓ አሉ። እነዚህ አራት ድርጅቶች ሕዝብን እንወክላለን ያሉበት ሁኔታ የለም። ሊሉም አይችሉም። ሆኖም ግን የሕዝብን ጥያቄ ግን እንደ ድርጅት ማቅረብ ይችላሉ። ያንንም ነው እያደረጉ ያሉት። የእስረኞች መፈታት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መቆም፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛ እንዲሆኑ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ….የመሳስለኡት የሕዝብ ጥያቄ አይደሉም እንዴ ?

በአገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎች በከባድ ሁኔታ ውስጥም ሆነው ከፍተኛ አስተዋጾ ያደረጉ መሆናቸውን አቶ ይገረም፣ አዉቀው ላለማመን ካልፈለጉ በስተቀር፣  ያጡታል ብዬ አላስብም። ለምሳሌ ሁለት ምሳሌዎች ልጥቀስ፡

በአማራው ክልል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ከመደረጉ፣ ከአንድም ሁለት አመታት በፊት በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በደብረ ማርቆስ፣ በደሴ በመሳሰሉ ቦታዎች ሕዝቡን ለማደራጀትና  ለማንቀሳቀስ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ ሥራ ሲሰራ እንደነበረ አገር ሁሉ የሚያወቀው ነው። የአንድነት ፓርቲ በምርጫ 2007 ወቅት ከ547  የፓርላም ወረዳዎች በ508 ተወዳዳሪዎች አሰልፎ ፣ በሰላሳ አራት ዞኖች ጽ/ቤት ከፍቶ በምርጫው ጠንካራ ፓርቲ ሆኖ ለመውጣት ዝግጁ የነበረ ፓርቲ ነበር። (ከአንድነት ቀጥሎ የብዙ ድርጅቶች ስብሰብ የሆነው መድረክ 270 ብቻ ነበር ያሰለፈው)   በድርጅቱ ዉስጥ ችግር የነበረ ቢሆንም፣ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ችግሩን ፈቶ፣ አዲስ አመራር መርጦ የተንቀሳቀሰ ፣ ከፓርቲው ምስረታ ጀመሮ አራት ሊቀመናብርትን ያስተናገደ የአንድ ሰው መፈንጫ ያልሆነ ዘመናዊ ፓርቲ ነበር። ብርሃንን ሰላምን ጨመሮ የግል ማተሚያ ቤቶች የአንድነት ልሳኖችን፣ ጋዜጦችን ፣ በደህንነቶች ትእዛዝ አናወጣም ቢሉም ፣ ፓርቲው የራሱ ማተሚያ ማሽን እና የራሱ ጀኔሬተር በመግዛት በሳምንት ሁለት ጋዜጦችን (ፍኖተ ነጻነት እና የሚሊዮኒች ድምጽ ) እያተመ ለሕዝብ ያቀርብ ነበር። በተለያዩ የአገሪቱ ጉዳዮች ዙሪያ አማራጭ ሐሳቦችን ያዘለ ዳንዲ የሚባል መጽሔት፣  በኦሮሚያ ላለው ማህበረሰብ በአፋን ኦርሞ ቶኩማ በቢሊሱማ በሚል ጋዜጣ መረጃዎች እንዲደርሰው ለማድረግ ዝግጁትን ጨርሶ ነበር።

አንድነት ጠንካራ ሆኖ በመውጣቱ ነው ሕወሃት የፖለቲካ ዉሳኔ፣ ጉልበቱና ጠመንጃው ስላላለው የወሰነው።  በድርጅቱ መድረክ ለሊቀመንበርነት ተወዳድሮ አንድ ድምጽ ብቻ (የራሱን ድምጽ) ያገኘውንና ለኑሮ ደሞዝ የሚፈልዉን ደካማ ግለሰብ በመጠቀም፣ ምርጫ ቦርድ አንድነት ሕጋዊ ሰርተፊኬቱን እንዲያጣ አደረገ። እዉነታው ይሄ ሆኖ እያለ፣  አቶ ይገረም ግን በጭራሽ የማይገናኝ ነጥቦች በማገናኘት፣ የተሳሳተና በእዉነት ላይ ያልተመሰረተ፣ ግን እርሳቸው ትክክል ነው ያሉትን ለመሸጥ ሲሉ ፓርቲዎችን ሲያሳንሱ ነው የሚታዩት። “ፓርቲዎች የሚፈርሱት በራሳቸው አባላት ነው” ብለው በጻፉት ጽሁፍ ላይ ከጥቂት ሳምንታት በፊት፡

ንድነት ህመሙ የጀመረው ሊቀመንበሩ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ስትታሰር ነው፡፡ መድሀኒት የሚፈልግለት አይደለም በሽታውን የሚያውቅለት ጠፍቶ ለአምስት አመታት ከተሰቃየ በኋላ በሀገር ቤትም በውጪም የሚኖሩ  ከአመራር እስከ አባል የነበሩ  የግዛቸው ነኝ፣ የበላይ ነኝ በማለት በፈጠሩት የሥልጣን ሽኩቻ በሽታው ተባብሶ ግብአተ መሬቱ ተፈጸመ፡፡ በመቃብሩ ላይ የቆመው ትእግስቱ አዎሉም በየግዜው በሹመት ላይ ሹመት ሲሰጡት የነበረ ሰው ነው፡፡ ታዲያ ለአንድነት ሞት ቀዳሚው ተጠያቂ ወያኔ ወይንስ የሥልጣን ጥም ያናወዛቸው የአንድነት አመራሮችና የዲያስፖራ ብር ያናወዛቸው አጃቢዎቻቸው” ሲሉ እኝህ ሰው፣ የአንድነት ፓርቲ ከምርጫ 2007 የነበረዉን ጉልህ ተሳትፎ በመናቅ፣ በሚሊዮሞች ድምጽ የተሰሩ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ወደ ጎን በማድረግ ፣ አንድነት ከጨዋታ ዉጭ እንዲሆን 90% ድርሻው የወያኔ እንደሆነ እያወቁ በዚህ መልኩ ለተቃዋሚዎች መዳከም ወያኔ የለበትም ማለታቸው በራሱ አጠያያቂ ነው። በነገራችን ላይ የአንድነት ፓርቲ ሕጋዊ ሰርተፊኬቱን ቢነጠቅ፣ አባላቱና ደጋፊዎቹ ግን አሁን በትግል ዉስጥ ናቸው። የተወሰኑይ እንደ መኢአድ እና ሰማያዊ ተቀላልቀለውም እየታገሉ ናቸው። ወያኔ ሰርተፊኬቱን ቢነጥቅም፣ አባላቱን ደጋፊዎች፣ የአንድነት የለዉጥ ሃይል አሁንም አለ።

አቶ ይገረም፣ ትንሽ የነበረዉን ሁኔታ ይረዱ ዘንድ ከጥቂት አመታት በፊት፣ ከብዙ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች መካከል፣  በአማራው ክልል በባህር ዳር የተደረገን አንድ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲመለከቱ ልጋብዛቸው እፈልጋለሁ። የእምቢተኝነት መንፈስ፣ ለመብት የመቆም ስሜት፣ ድፍረት፣አገራዊ ወኔ እንዲኖር የአንድነት ፓርቲና የሚሊዮኖች ድምጽ ንቅናቀ የነበረዉን አስተዋጾ ለማየት ይረዳቸዋል።

ሌላው የሰማያዊ ፓርቲን በተመለከተ ነው።ሰማያዊ ፓርት ከተመሰረተ ጀምሮ ለትግሉ ብዙ አስተዋጾ ያደረገ ፓርቲ ነው። በፓርቲው ውስጥ እንደ ማንም ድርጅት ልዩነቶች ይኖራሉ። ሆኖም ፓርቲው ከግለሰቦች ይልቅ በድርጅቱ ያሉ ተቋማት ጠንካራ እንደሆኑ ያስመሰከረ ድርጅት ሆኗል። አገዛዙ ልክ እንደ አንድነት ፓርቲ፣  ጠንካራ የሰማያዊ አመራሮች በሽብርተኝነት ክስ አስሮ አሰቃይቷል። እያሰቃየም ነው። የድርጅቱ የአሁኑ ሊቀመነበር ወደ 2 አመት ገደማ በወህኒ የተሰቃዩ ናቸው። እንደ ዮናታን ተስፋዬ ያሉ አንጋፋ ታጋዮችም በአሁኑ ወቅት በወህኒ ነው የሚገኙት። ሰማያዊ በከባድ ሁኔታ ዉስጥ ሆኖም ግን በከፍተኛ ተነሳሽነት ለትግል የተዘጋጀ ድርጅት ነው።

ይሀን ስል በፓርቲዎች ዉስጥ “ችግር አልነበረም፣ ድካም አልነበረም” ማለቴ አይደለም። ሆኖም ግን አቶ ይገረም ለማቅረብ እንደሞከሩት፣ አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች ምንም እንዳልሰሩ፣ “ስማቸውን መጥቀስ እስከማፈር ድረስ” የማይረቡ እንደሆኑ አድርጎ ማቅረብ ግን ፣ ያውም የሚረባ የሚሉትን ሳያሳዩን እና ሳያመላከቱን የደከመ፣ የሽንፈት፣ ጨለምተኛ ፖለቲካ ነው።

 

አቶ ይገረም በድርድሩ ዙሪያ ሲጽፉ  አሁንም በተስፋ መቆረጥ ውስጥ ተሞልተው ነው። ወያኔዎች የሚደራደሩት ጊዜ ለመግዛትና የአለም አቀፍ ድጋፍ እንዳይቀርባቸው ነው ከሚል ነው በሚል፣ ከድርድሩ ምንም ነገር እንደማይገኝ ነው የገለጹልን። ተቃዋሚዎችም ፓርላማ ለመግባትና ጥቅም ለማግኘት ብለው እንደሚደራደሩም አይናቸውን በጨው አጥበው ነው የጻፉት። አንደኛ የተቃዋሚ መሪዎች ጥቅም ቢፈልጉ ኖሮ አገዛዙን ተቀላቅለው ፣ ወያኔ ሆነው፣ ይሄን ጊዜ ሃብት በሃብት ይሆኑ ነበር። ሁለተኛ የምእራባዊያን መንግስታት ሁኔታም የመረዳት ችግር ያለባቸው መሰለኝ። ያን ቢረዱ ኖሮ ምእራባዉያን  ለሰብአዊ መብትና ለዲሞክራሲ ሳይሆን ለጥቅማቸው ብቻ የቆሙ እንደሆኑ ያወቁ ነበር።  ወያኔ ድርድር አደረገ አላደረገ ፣ ጥቅማቸውን እስካስጠበቀላቸው ድረስ የውጭ ድጋፍ እንደማይለየው  ይረዱ ነበር። “የዲፕሎማሲ ድጋፍ ቆመ” ያሉትን አቶ ይገረም፣ ስህተት ነው። አልቆመም። “ቆመ” ካሉ መረጃዎች ያቅረቡና ይከራከሩ።

ወያኔ ለድርድሩ የቀረበው እርሳቸው እንዳሉት በሕዝብ ተገዶ ነው። በሕዝብ ብቻ ሳይሆን በድርጅቱ ውስጥ ባሉ መካከለኛና አነስተኛ አመራሮች ግፊት ነው። አሁን ያለው አገዛዙ ከ5 ወይም 10 አመታት በፊት የነበረው አይደለም።በመሆኑም ይህ ድርድር በአንጻራዊነት የፖለቲክ ምህዳሩን እንዲሰፋ ሊረዳ ይችላል። ያም ባይሆን እንኳን  ያ እንዲሆን ሙከራ ማድረጉና መታገሉ አስፈላጊ ነው። አቶ ይገረም፣ አሁንም እላለሁ፣  ሌላ አማራጭ ሳያሳዩን ፣ ትንሽ ቢሆን የተሻለ ነገር እንዲመጣ ወደ ድርድር የመገባቱን ሂደት ማሳነሳቸው፣ ማጣጣላቸው ተገቢ አይደለም።

በግሌ የዞን ዘጠኝ ጦማሪ አቤል ዋቤላ እንዳለው “አገር የሚገነባው በድርድር ነው” የሚል እምነት አለኝ። ከአሁን ለአሁን ትላንት አልተሳካምና ዛሬ መሞከር የለበትም የሚለው አነጋገር ፣  የትም አያስኬድም። ይልቅ ይሄ ድርድር ትንሽም ቢሆን ፍሬ እንዲያፈራ የድርሻችንን መወጣት ነው የሚጠበቅብን።

አሁንም ደግሜ የምለው አገር  ቤት ያሉ ተቃዋሚዎች እንደ ማንም ድርጅት በውስጣቸው ችግሮች ይኖራሉ። ሆኖም ግን በዋናነት በገዢው ፓርቲ በኩል የደረሰባቸዉን የሚደርስባቸው ግፍና መከራ በጣም የከፋው። እዉነቱ ያ ሆኖ እያለ፣ እነርሱ ከማገዝና ከመደገፍ፣ እነርሱ ከድካማቸው እንዲወጡ የድርሻችንን ከማድረግ ፣ ወያኔ በነርሱ ላይ የሚያደርሰው ጫና ሳያንሳ እኛ ደግሞ “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው” እንደሚባለው፣ እነዚህ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ላይ ጠጠር መወርወር ዘመናዊ ፖለቲካ አይደለም። ተቃዋሚዎች መተቸት ፣ መወቀስ አለባቸው። መሪዎቻቸው ተጠያቂ መሆን አለባቸው። ሆኖም ትችታችንን ወቀሳችን ፈረንጆች constructive  criticism ( ገንቢ ትችት) መሆን አለበት እንጂ  destructive criticism  (አፍራሽ ትችት) መሆን የለበትም። የአቶ ይገረም ጽሁፍ በኔ እይታ destructive የሆነ ትችት ነው።

“እኔም ጥያቄ አለኝ እነርሱ የሚሉትንና የሚያደርጉትን ነው መከተል ያለብን ወይንስ ትክክል የምንለውን? “ ነው ሲሉ በመጠየቅ ጽሁፋቸው ያጠቃላሉ አቶ ይገረም። ትክክል የሆነውን ነው መከተል ያለብን የሚል መልስ ነው ያለኝ። ሆኖም እርሳቸው የሚቃወሙት፣ ችግርን በዉይይት መፍታት ትክክል ብቻ ሳይሆን የሰለጠነ ፖለቲካ ነው። ከላይ ጠቅሼዋለሁ የዞን ዘጠኝ ጦማሪ እንዳለው አገር የሚገነባው በድርድር ነው። ትክክል ሳይሆን ትክክል የተበላን ትክክል እንዲሆን መስራትና መድከም ያ ትክክል ነው። አቶ ይገረም እንደሚያደረጉት፣ ዜጎች ተስፋ ማስቆረጥ፣ የደከመዉን ደካማ ነው ብሎ መረጋገጥ ትክክል አይደለም። የደከመውን ማንሳትን ማበረታታት፣ የተሳሳተዉን እንዲታረም መምከርና መዉቀስ  ያ   ትክክል ነው።  የአቶ ይገረም ችግር ትክክል ያልሆነውን ያለመከተል ሳይሆን ትክክል የሆነውን ነገር አለመከተላቸው ነው።

(ይሄ ጽሁፍ የተጻፈው ምሉ በሙሉ አቶ ይገረም ባቀረቧቸው ሐሳቦች ዙሪያ ነው። በርሳቸው ላይ ምን እንደሆኑ ባላወቅም ችግር የለኝም። እርሳቸው ወደ ግለሰብ እንካ ሰላምቲያ ሳይገቡ በቀርቡ ሐሳቦች ዙሪያ ምላሽ የሚሰጡ ከሆነ እጠብቃለሁ)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s