ሸፍጠኛው ጥያቄ ! ኢትዮጵያዊው ማን ነው?- ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

 

ኢትዮጵያዊው ማን ነው? ፤ ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው?

እጅግ ይገርማል ይደንቃል ፤ ኢትዮጵያዊነት ምን እንደሆነ

ኢትዮጵያዊውም ማን እንደሆን ፤ አጠራጥሮ ደመነ?

የኢትዮጵያዊው ኢትዮጵያዊነት ፤ ማንነቱና ምንነቱ

ደብዝዞ እስኪያምታታ ፤ አስቸገረ መለየቱ ?

ለዚህም ተዳርሰናላ ፤ ጭራሽ ጥያቄ እስኪያስነሣ?

መሬት ሲያረጅ ምን ያበቅላል ፤ ይሉት ደርሷላ አበሳ

ኢትዮጵያዊው ማን ነው? ፤ ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው?

ኢትዮጵያዊነት ሲጎዳ ፤ ሲሸረሸር በነፋስ ሲታይ

ሲገፈተር ሲሽቀነጠር ፤ ሲወድቅ አደጋ ላይ

የተፈጠረ ጥያቄ ፤ የሀገር ፍቅርን አግላይ

ሀገር በቀል እሴቶችን ፤ ያለርሕራሄ ገዳይ

የተማረከ የተበነደ ፤ የሚያነሣው ሲሆን አባይ

ኢትዮጵያዊነትን ያስረጀ ፤ ክህደትን ያሠለጠነ

የተሠወረ ይመስል ፤ ድብቅ ምሥጢር የሆነ

የሐበሻነትን መለያ ፤ በአደባባይ ያኮሰመነ

የእንቢተኝነቱን ጽናት ፤ ከውስጥ ሰልቦ ያመነመነ

ብቁ ትጉ ዜጎቿን ፤ ጆሮ አስይዞ ያስመነነ

የቃል ኪዳን ልጅነትን ፤ እያስካደ ያስኮነነ

ታሪክ ቅርስ እሴታችንን ፤ ከል አልብሶ የከደነ

ሐሰት ሐሰቱን ያነገሠ ፤ እውነት እውነቱን ያዳፈነ

የራስን ወርቅ አስጥሎ ፤ መዳብ ጠጠር ያስለመነ

ሕዝብን የናቀ ያሳዘነ ፤የተዳፈረ ሉዓላዊነት

ወገናዊ ያልሆነ ፤ ባዕዳዊ ሸፍጥ ምጸት

በሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ፤ የተደበቀ እብለት

እውነቱ እየታወቀ ፤ በገሐድ በፋኖ ሕይዎት

የሀገራቸውን ጥቅሞች ፤ ለድርድር በማያቀርቡት

ለሉዓላዊነት ሲሉ ፤ ሞትን ገለው በሚሞቱት

ኢትዮጵያዊውን እሴት ፤ በጽናት በሚጠብቁት

በቀደመው በጥንት ዘመን ፤ ከሀገር አልፎ በአህጉራት

ኢትዮጵያዊነት በምልዓት ፤ ናኝቶ በነበረበት

በዚያ ዘመን ቢነሣ ፤ ሆኖ የሚታይ እብደት፡፡

በል እንግዲህ ወገኔ ፤ አውቀህም ይሁን ሳታውቅ

ጠይቀሀልና ጥያቄ ፤ በእጅጉ የሚያስደንቅ

ኢትዮጵያዊነት ማለት ፤ ሲተነተን ሲዘረዘር

ከአደኛኘት እስከ አሞጋገት ፤ ከአስተዛዘን እስከ አመራረር

ከአስተካከም እስከ አገነባብ ፤ ከአሣሣል እስከ አነጣጠር (አንጠረኛ)

ከአጠናን እስከ አፈለሳሰፍ ፤ ከአነባበብ እስከ አመሠጣጠር

ከአወጋግ እስከ አመራረክ ፤ ከአቀራረብ እስከ አመራመር

ከአጻጻፍ እስከ አቆጣጠር ፤ ከአስተሳሰብ እስከ አኗኗር

ከአከዋወን እስከ አቀጣጠር ፤ ከአዘገጃጀት እስከ አከባበር

ከአመጋገብ እስከ አለባበስ ፤ ከአስተዳደግ እስከ አነጋገር

ከአፈነጣጠዝ እስከ አለቃቀስ ፤ ከአዚያዚያም እስከ አደነካከር

ከአመራረቅ እስከ አረጋገም ፤ ከአመላለክ እስከ አሥተዳደር

ለዓለም የተገለጠ ፤ በመልከጼዴቅ በዮቶር

የራሱ መሠረት ያለው ፤ የሥልጣኔ ፈለግ

የራሱ ትውፊት ያለው ፤ እውነት የሆነ የሚታደግ

የራሱ ቀለም ያለው ፤ የብቻው መለያ ብልጹግ

የራሱ እምነት ያለው ፤ የተለየ ባሕልና ወግ

የራሱ ሥርዓት ያለው ፤ አከዋወን አደራረግ

የራሱ ይትበሀል ያለው ፤ የተወደዱ ደጋግ

ምዕራባዊ ያልሆነ ፤ ምሥራቃዊም ወዲያ ጥግ

ዓረባዊ ያልሆነ ፤ አውሮፓዊም አጭሉግ

ከማንም ያልተወረሰ ፤ ያልመጣ ተሻግሮ አፍላግ

ያወረሰ እንጅ የሰጠ ፤ ሁሉን ያረገ ዕዱግ

የራሱ ብቻ የሆነ ፤ ሉዓላዊ ማዕረግ

ይሄ ማለት ነው ወዳጀ ፤ የኢትዮጵያዊነት ድር ማግ

ይሄንንም የሚኖረው ነው ፤ ኢትዮጵያዊው ብትፈልግ፡፡

ወደ ኋላህ ተመልሰህ ፤ ማንነትህን ብትፈትሽ

ቱባውን ታገኘዋለህ ፤ ሳይበራረዝ ሳይበላሽ

ሲጠበቅላት የኖረውን ፤ በንግሥታት ነገሥታቷ

ከራሷው የበቀለውን ፤ የሆነውን የገዛ ሀብቷ

ኢትዮጵያዊ መሆን ካሻህ ፤ ጽዱ ንጥር ሐበሻ

አምጣውና ያንን ኑረው ፤ መደበላለቅ ሳትሻ

ያንን ተቀባ ተላበሰው ፤ አውልቀህ የሌላን ቆሻሻ

ዱካህ ብቻ ነው መድኅንህ ፤ ከጥፋት ማምለጫ መሸሻ

በልክህ የተሠራልህ ፤ አይጠብ አይሰፋህ ድርሻ

ይሄንን ሳታደርግ ግን ፤ ሳትመለስና ሳትረዳ

ኢትዮጵያዊ ነኝ እንዳትል ፤ እሷ አታውቅህም ነህ ባዳ

ምሁር ዐዋቂ ነኝ እንዳትል ፤ ጎሎሀል ዕውቀት የላቀ

ራስን የማወቅ ያህል ፤ አክብረህ መመስከር ላላወቀ

ጤነኛም ነኝ እንዳትል ፤ ይዞሀል የአእምሮ በሽታ

አንተነትህን አስጠፍቶህ ፤ ሌላ እንድትሆን የሚያምታታ

ይሄን በሚያህል ድንቁርና ፤ ወርቅ አንተነትህን ባስናቀ

ተውጠህ ሰምጠሀል ውጣ ፤ ዕውቀት አለልህ የመጠቀ

ይሄን በሚያህል በሽታ ፤ ሉዓላዊ ክብርህን ባስጣለ

ተለክፈህ አብደሀል ንቃ ፤ ጤና አለልህ ያማለለ

ድንቁርናው በርትቶብህ ፤ የለኝም ካልከኝ በር መውጫ

በሽታውም ጸንቶብህ ፤ አጣሁ ካልከኝ ፈውስ መስጫ

ከቶውንም ቃናው የለህ ፤ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ

ምንም እንደሆንክ አላውቅም ፤ ለምን ምንድን ነው ያንተ ምርጫ ?

ነጭ ነው ቢጫ ወይስ ዓረብ ፤ መልክህ ምንድን ነው ዓይነቱ ?

የማንነትህ ምንጭ አሻራ ፤ ወዴት ይመስልሀል መሠረቱ ?

አይደለም እንዳትሳሳት ፤ ያለህን አሳይ ሐቅ አውራ

እራስህን አታጃጅል ፤ ጆሮህን አትስጥ ለፈጠራ

የነጭ ቢጫ ዓረብ አይደለም ፤ ነው እንጅ የጥቁር አውራ

የተገፋው ሕዝብ መመኪያ ፤ መኩሪያ መከታ ባለአደራ

እራስህን ጠይቅ መርምረው ፤ ታሪክን አስመስክር ለእምነቱ

ልማዳዊ አይሁን መንገድህ ፤ ውስጥህ ምን ይልሀል ስሜቱ?

ራስህን ለእውነት አስገዛ ፤ ምክንያታዊ ይሁን ስሌቱ!

ወገናዊ ይሁን አድልኦህ ፤ ኢትዮጵያዊ ይሁን ቅኝቱ!

እራስህን ቅጥረኛ አርገህ ፤ የጠላት ሎሌ አትሁን ከንቱ!

ጠፍተህ ለማጥፋት አትትጋ ፤ ይሰማህ የክህደት ውርደቱ!

የማንም ምስክር አያሻህ ፤ ሕሊናህ ውስጥ አለ እውነቱ!

ከራስህ ተለይተህ ላትለይ ፤ ሆነህ ላትሆን ሌላ

ምንም አማራጭ የለህም ፤ ድመቅ በራስህ ገላ!

ተመለስ ከክህደትህ ፤ ሆነህ እንዳትቀር ሰንካላ!

አቅመቢስ ድኩም ሰባራ ፤ ለምንም የማይሆን ሰላላ!

ንቃ ከመተተኞች ፍዘትህ ፤ አዚሙን ሽረህ በኤላ

ተመለስ ወደአንተነህ ፤ እሱ ነው የሚያዋጣህ ከለላ፡፡

ሥራ በእናት አባትህ ትጋት ፤ በሰጠን ኃያሉን ዱላ!

ቀድሞ አንግሦህ በነበረው ፤ እስከ እስያ ሁላ!

ትጋ ተሯሯጥ ጽና ፤ ቅበር ስንፍናን ጥላ!

አሳድ ድህነትህን አባር ፤ አርቅ ከሀገርህም ክላ!

ባርክ በአንተው ጸሎት ፤ መርቅ ሕይዎት ለአንተ ታዳላ!

ፈትን በራስህ ጉልበት ፤ ዘይድ በራስህ መላ!

ኩራ በአንተው ማንነት ፤ ዝመት ወኔህን ሙላ!

ፎክር በአንተው ጋሻ ጦር ፤ ደንፋ በአንተው ሽለላ!

አቅራራ በአንተው ቀረርቶ ፤ ብረቅ እንደ እሳት ጎመራም ፍላ!

አውጅ ነጋሪት ጎስም ፤ ጨክን በሠይፍህ ቅላ!

ምጠቅ በራስህ ዕውቀት ፤ ጽና በራስህ መሐላ!

አውጋ በራስህ ቋንቋ ፤ ተቀኝ ቅኔህ ይራቀቅ ይስላ!

ፍረድ በራስህ ፍትሕ ፤ በዳይ እንዳይኖር ሚያጉላላ!

አንብብ በራስህ ፊደል ፤ ቀምር በቁጥርህ አስላ!

ብራና መጻሕፍትህን ፤ ሲሳይ ያወረዱትን ለሌላ!

እያንዳንዳቸውንም በዝብዝ ፤ ጥርግርግ አርግና ብላ!

አዚም በራስህ ዜማ ፤ አስንቅ ሌላን አስጠላ!

አዝምር በራስህ ሁዳድ ፤ መጽውት መዓድህን ሙላ!

አክብር የራስህን በዓላት ፤ መንፈስህ ይታደስ በተድላ!

ሙሉ ነውና ማንነትህ ፤ በራስህ እሴቶች ጉላ!

ከማንም ምንም አያሻህ ፤ ዕወቅ አትሁን ተላላ!

እንኳን ለራስህ ቀርቶ ፤ ብዙ ተርፈሀል ለሌላ፡፡

ኢትዮጵያዊና ኢትዮጵያዊነት ፤ በእነዚህ እሴቶች ካልተለካ

በምን ይመዘን ይመስልሀል ፤ ሀገርስ በምኗ የምትመካ ?

ከአማራ ኦሮሞ ትግሬ ፤ ከጉራጌ ወላይታ ሱማሌ

ከሁሉም ብሔረሰቦች ፤ እነዚህን እሴቶች ካለ አሌ

ኢትዮጵያዊነት ውስጡ የለም ፤ ሸጦ በልቶታል በአሞሌ!

ይማር ይመከር ይገራ ፤ እራሱን እስኪያውቅ ተላሌ፡፡

ብቻ የራሳችን ይሁን እንጅ ፤ የተገነባ በሐበሻ ዘየ

የአማራ እሴት ነው የተባለው ፤ የሱማሌውም ሆኖ ካልታየ

የወላይታው ሀብት የተባለው ፤ የትግሬውም መሆኑ ከታበለ

እሱ ደሞ እዚህ ምን አገባው ፤ የኔ ጉዳይ ነው ከተባለ

ይሄ ሰው ምኑም አልገባው ፤ ገና ገና ብዙ ችግር አለ፡፡

በል እስኪ ንገረኝ እኮ በል ፤ ኧረ እንዴት ሆኖ ነው ወገኔ

ሁላችንም እንዲህ እያልን ፤ ያሰብን ጊዜ ያኔ

አንድነት ያለው ጠንካራ ሕዝብ ፤ ያልተቃረጠ ሥልጣኔ

ሰላማዊት ምቹ ሀገር ፤ ሉዓላዊ ማንነት ውርስ

ዘመን ተሸጋሪ ታሪክ ፤ ሳይበረዝ ሳይከለስ

እንደምን ሆኖ ይኖርሀል ፤ መቸና ከወዴት ሊመጣ?

ምንስ ያሰመጠህ መሰለህ ፤ እዚህ ካለህበት ሁሉ ጣጣ?

መውደቅ የጀመርክበትን ዘመን ፤ መለስ ብለህ ብታየው

ሌላም ምክንያት አልነበር ፤ እንደዚህ ባሰብክ ጊዜ ነው፡፡

የኔ ነው ሌላው ምን አገባው? ፤ የምትለው ቅርስ የተጫነ

ተው ሲታወቅብህ ታፍራለህ ፤ ያ ቅርስ የአንተ እንዳልሆነ!

ነገሮች ተገለባብጠው ፤ የታሪክ አጋጣሚ ሆነና

የአንተ እንደሆነ እንድታወራ ፤ አረገህ ጊዜ ሳተና

ባለቤቱ ዝም ያለውን ፤ የሁሉም ነው ብሎ አስቦ

አንተም እያወክ እውነቱን ፤ ልትነጥቅ ከዳዳህ ከደቦ

እውነቱ ይነገርሀል ፤ ዋ ትዋረዳለህ በኋላ!

ዐርፈህ ተቀመጥ በአደብ ፤ በእናት ኢትዮጵያ እንዳትጠላ፡፡

ወገኔ እኔስ ልመርቅህ ፤ ነው ብለህ እንዳትንቀው የኩታራ

ልብ ይስጥህና ያድርግህ ፤ በማንነትህ የምትኮራ!

በፍቅር በመከባበር ፤ ተሳስበህ ጠባቂ አደራ!

የማይፈታ አንድነት ያለህ ፤ በእኩያን ጠላቶች ሴራ!

የማንነት እሴቶችህን ፤ በሉላዊነት ሽርሸራ

ለድርድር ያማታቀርብ ፤ ቆራጥ ሀሞተ ኮስታራ!

በራስህ ዱካ እሮጠህ ፤ ሌሎቹን ባረገው ሲራራ

ለስኬቶችህ የምትበቃ ፤ በመላው ዓለም የምትበራ!

የምትደምቅ የምትፈካ ፤ የምትነግሥ የምትፈራ!

አሜን! በለኛ ወገኔ ፤ ልሳንህ አሜንን ይጣራ!

ከአሜን ይቀራልና ፤ አሜን አሜን አሜን ምራ!

አሜን አሜን አሜን ምራ ፤ አሜን አሜን አሜን ምራ!

ጥቅምት 2004 ዓ.ም.
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s