“ጓደኞቼን – ፍቱልኝ!” (ሀብታሙ ምናለ)

ሀብታሙ ምናለ

ኅዳር 8 ቀን 2009ዓ.ም ከረፋድ ጀምሮ ጓደኛዬና የሥራ ባልደራቢያዬ ከሆነው ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ ጋር ተገናኝተን ደግመን ደጋግመን ስለነባራዊ የሀገራችን ሁኔታ በተለይም ሰለ ጓደኞቻችን፡- ጋዜጠኛ ኢዩኤል ፍሥሓ ዳምጤ፣ ጋዜጠኛና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ዳግማዊ ተሰማ፣ ብሌን መስፍን፣…….. ሌሎቹም ስለመያዛቸውና፣ መታሰራቸው ተገቢ አለመሆኑን አወሳን፤ ከገዢው መንግሥት በኩል፡- እነዚህ ወጣቶች የሚታሰሩት፣ የሚደበደቡት፣ በተደጋጋሚ ለሀገራቸው መሆኑን የሚረዳ፣ የሚያውቅ፣ የሚያገናዝብ አንድ ባለሥልጣን እንዴት ይታጣል? ከታሰሩት ወጣቶች መካከል የተወሰኑት የኢህአዴግን የግዴታ ‹‹የተሃድሶ ሥልጠና›› ቋቅ እያላቸውም ቢሆን ግተዋቸው ወጥተዋል፡፡ ነገር ግን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰበብ ኢህአዴግ አብዝቶ ካቄመባቸው መካከል ኢዩኤል ፍሥሓ ዳምጤን ከጥቅምት 23 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ያለምንም ክስ በጠባቧ ክፍል ውስጥ ሆኖ “የኢህአዴግን የመጨቆኛ መንገድ አሁንም እያሳለጠ ይገኛል” ኢህአዴግ ያልተረዳው ኢዩኤልን ያለጥፋቱ ማሰሩ የኢዩኤል አስተሳሰብ መጀመሪያውንም ፍፁም ትክክል መሆኑን ያረጋገጠለትና፣ በድጋሚ ለተሻለ ብልሃት ተኮር ትግል እንዲዘጋጅ የሚያደርገው መሆኑን ነው፡፡ ብለን እያወጋን ውለን ቀኑን አብረን አሳልፈን፤ አመሻሽ ላይ ወደነበረን ቀጠሮ ለመጓዝ ከነበርንበት 4 ኪሎ ወደ ቀጠሯችን ቦታ ተንቀሳቀስን፡፡ አካባቢው ግርግር ቢሆንም የኢትዮጵያዊ ግዴታ በሆነው ተጋፍቶና፣ ተሰልፎ ታክሲ መያዝ እኛም ግዴታችንን ተወጥተን፤ ታክሲ ውስጥ ብንገባም አናንያ መቀመጫ ቦታ ይዞ እኔ ጋር ሲደርስ ታክሲው በመሙላቱ እኔ ስላልገባሁ ሁለታችንም “በቃ እዛው ቀጠሯችን ቦታ ላይ እንገናኝ!” ተባብለን ተለያየን፡፡ እኔም ቀጥሎ በመጣው ታክሲ ተሳፍሬ ቦታው ላይ ብደርስም አናንያ የለም፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልኩ ላይ ብደውልም ጥሪ አይቀበልም፡፡ ቀጠሮን የነበረን ሰው ጋር ብደውልም “አልመጣም!” አለኝ፡፡ “ምን ተፈጠረ?” በማለት ኤልያስ ጋር ብደውልም ስልኩ ዝግ ነው፡፡ አብሮት ከማይለየው ዳንኤል ሺበሺ ጋር ደጋግሜ ብሞክርም መልስ የለም፡፡ ነገሩ ግራ አጋብቶኝ ጠዋት በተደጋጋሚ ስልካቸውን ብሞክርም የአንዳቸውም ስልክ መልስ አይሰጥም፡፡ በጠዋት ወዳጅ ዘመድ ሶስቱንም ይገኙበታል ወደ ተባለው ቦታ በመሄድ ሁሉ ፍለጋ ተጀመረ፡፡ ምንም ፍንጭ አልተገኘም፡፡ ከሰዓት በኃላ ገርጂ አካባቢ ባለው ፖሊስ ጣቢያ እንደታሠሩ ሰምተን ብንሄድም፤ ስንቅ ማቀበል እንጂ ማግኘት እንደማይቻል ተነገረን፡፡ ያሉበትን ማወቅ በመቻሉ ለቤተሰብ ትንሽም ቢኾን እፎይታ ኾነ፡፡Jiret Magazine cover

ከነበሩበት ጣቢያ ወደ ቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከጥቂት ቀናት በኃላ አዛወሯቸው፤ መጠየቅም ተፈቀደ፡፡ አናንያ ከታክሲ እንደወረደ ወዲያው ተረባርበው እንደያዙት እኔም ስመጣ እንደሚቀላቅሉኝ ተስፋ አድርገው እንደነበርና ስዘገይባቸው እሱን ይዘውት እንደሄዱ አወጋኝ፡፡ “ለካ የሸገር ታክሲዎች ከደኅንነትም በማዘግየት ያተርፋሉ!” በማለት ተቀላለድን፡፡ ኤልያስና ዳንኤል፡- ካዛንችስ አካባቢ ካፌ ውስጥ በተቀመጡበት መሳሪያ በማውጣት ጭምር እንደያዟቸው ገልጠውልኛል፡፡ “ጓደኞቼ ምን አጠፉ?” ዳንኤል ሺበሺ ሰላማዊ ትግልን ከልቡ በማመን የአንድነት ፓርቲ አባልና አመራር ሆኖ አገልግሏል፡፡ “ምርጫ ቦርድ” ፓርቲውን በኢህአዴግ ትዕዛዝ ሲያፈርሰው እሱ እስር ቤት ነበር፤ ከወጣም በኃላ የየትኛውም ፓርቲ አባል አልሆነም፡፡ በቀድሞ በፖለቲካ አመለካከት ከንፈር ነክሶ ለማጥቃት መነሳት እራሱን “መንግሥት ነኝ!” ብሎ ከሚጠራ አካል አይጠበቅም፡፡ ዳንኤል፡- ምን ፈለገ?፤ ለኢትዮጵያስ ምን አይነት አመለካከት አለው?፤ ለኢህአዴግስ የሚጠቅም ምን ሀሳብ አለው? ብላችሁ ተረዱ፡፡ ያን ጊዜ ዳንኤልን በማሠራችሁ፤ ምን እንዳጣችሁ ትረዱታላችሁ፡፡ ለሰላማዊ ትግል ክብር ካላችሁ “ዳንኤል ሺበሺ ሰላማዊ ታጋይ ነው!” ፍቱት!

ጋዜጠኞች ምን አደረጉ? መንግሥት ፈቅዶ በሚሰጠው ሚዲያ የጋዜጠኝነት ሙያቸውን ተጠቅመው በመጻፋቸው ምንድን ነው ጥፋታቸው? መንግሥት የግል ሚዲያን እግር በእግር ተከትሎ በማጥፋቱ ለብዙ ጊዜያት ከሚዲያ ርቀዋል፡፡ አናንያ በእራሳቸው ልሳን በኾነው በፋና ብሮድካስት ጣቢያ በሞጋች ላይ አቅርበውት፡- ነጻነት እንደሌለ፣ አፈና እንደበዛ “ኢህአዴግ ከጥልቅ መታደስ፤ ወደ ጥልቅ መበስበስ” እየሄደ መሆኑን አስረግጦ ነግሯቸዋል፡፡ ሁሉም ጋዜጠኞች በቻሉት አቅም የመንግሥት አካሄድ ለሀገሪቷም አደጋ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ መጻፋቸው መንግሥትን አስቆጥቶ እንዲታሰሩ ካደረገ ማነው? ነገ ወደ ግል ሚዲያ የሚመጣው፤ በአሁኑ ወቅትም ህዝቦች፡- የሚታሰሩት፣ የሚከሰሱት ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመ በኃላ አዋጁን የተላለፈን ነው? ወይስ ከአዋጁ በፊትም ሆነ አሁንም “ይሄን ሥርዓት ይፈትናሉ!” ያላቸውን ወጣቶችን ማሰር የፈለገው? አሁንም ኢህአዴግ በኮማንድ ፖስቱ “የማዳኛ ባላ” ተደግፎ አይቆምም፤ ህዝቡን በማሰር ሰላም አይመጣም!፤ ህዝብና መንግሥት እየተፋተጉ መኖሩ ኃላ ጉዳት የከፋ ነው፡፡

አናንያ ሶሪ፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ ኤልያስ ገብሩ በቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ያለምንም ፍትህ ሶስት ወራቶችን አስረዋቸው የነበረ ሲኾን ከእዚህ ጣቢያ ከየካቲት 10 ቀን 2009ዓ.ም ጀምሮ አቶ ዳንኤልን ሺበሺን በጣም አሰቃቂ ለጤና ጉዳት በሚዳርግ ሁኔታ ቄራ መስጊድ አጠገብ ባለ ፖሊስ ጣቢያ፤ ኤልያስ ገብሩን ቂርቆስ ፖፖላሬ ፖሊስ ጣቢያ፤ አናንያ ሶሪ ደግሞ ካዛንችስ 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አሁንም ቀጣይ የግፍ ቀናትን ለመጨመር ታስረው ይገኛሉ፡፡

በእዚህ አጋጣሚ ሳልፅፈው ባልፍ አዕምሮዬ ላይ ሲጮህብኝ የሚኖር ታሪክ አጋጥሞኛል፡- ጓደኞቼ ታስረውበት የነበሩበት ጣቢያ ውስጥ 4 ወር የሆናቸው ምንም አይነት ፖለቲካዊ አመለካከት የሌላቸው እስረኞች አሉ፡፡ አንድ ቀን አንድ ፖሊስ አንዲት ሴት እና ሶስት ህፃናትን ይዞ መጣ፡፡ አንዱን እስረኛ ፖሊሱ አስጠራውና እንባው ሊወርድ ሲታገለው ከንፈሩን ነክሶ፡- “ባለቤትህ ጎዳና ልጆቿን ይዛ መንገድ ላይ ምፅዋት ስትጠይቅ አይቻት ነው፤ እዚህ መጥታ አንተን ስትጠይቅ በመልክ በደንብ አውቃታለሁ፤ ለእዛም ነው ያመጣኋት” ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ ሳግ እየተናነቀው ስሜቱን መቆጣጠር አቅቶት በፍጥነት ሄደ፡፡ እኔም ያስጠራኋቸው እስኪመጡ ድረስ ይሄን አሳዛኝ ታሪክ አይቼ ያስጠራኃቸውን ማናገር አቃተኝ ልክ እንደመጡ “ያ ሰውዬ በምን ምክንያት ታሰረ?” አልኳቸው:: ዞረው አይተውት:- “ኮማንድ ፖስቱ ነው የያዘው” አሉኝ:: እሱን ለይቼ በመጠየቄ “ታውቀዋለህ? እንዴ” አሉኝ በጭንቅላቴ አላውቀውም ብዬ መለስኩ፡፡ አስሬ “ምን ሆነሃል?” ቢሉኝም ስሜቴ ጥሩ አለሆን አለኝ እነሱን ማውራትም ስላቃተኝ “በቃ ነገ እመጣለሁ” ብዬ ወጣሁ፡፡ ስወጣ አንዱ ፖሊስ ልብ ብሎ እያየኝ ኖሯል “ስማ ይሄ ብቻ እንዳመስልህ አንዷም በሏን ልጆቼን ለምኜ ማብላት ጀምሬያለሁ፤ ስትለው እንደ እብድ ነው የጮኸው፤ ወንድ ልጅ ሲያለቅስ እንዴት ያማል መሰለህ” አለኝ፡፡ ፖሊሱ ቀለል አድርጎ እየነገረኝ ነው እኔ ግን አይኔ በእንባ ተከደነ፤ ሰውነቴን የንዴት ላብ እያጠመቀኝ ነው፡፡ በአዕምሮዬ ስንት ቤት ፈርሷል፤ ስንቱ ችግር ላይ ወድቋል ብዬ ሳሰላስል (“ወንድ ልጅ አደባባይ ላይ አያለቅስም!” የሚለው መርኋ እዚህ ጋር ስህተት መሆኑን ገባኝ) “ልመናን አስወግዳለሁ!” የሚለው መንግሥት አደባባይ ላይ ልመና ሲወጡ ማነው የሚታደጋቸው? የሚያድጉት ልጆች፡- “በኢህአዴግ ዘመነ- መንግሥት አባታችን በግፍ ታስሮ ጎዳና ወጥተን ነበር” ብለው ጥቁሩን አሻራ ማስታወሳቸውም አይቀርም፡፡ እራሱን “ኮማንድ ፖስት” ብሎ የሚጠራው አካል ማንን እንዳሰረ፣ በመታሠራቸው ሀገርና ህዝብ ላይ ያመጣው ችግር ተገንዝቦ በአስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ቤተሰብ ፈርሷል፤ ልጆች ጎዳና ወጥተዋል፡፡ ይሄ ግፍ ጊዜ ቆጥሮ ይመጣል!፡፡

ኢህአዴግ ይሄን አካሄድ አጢኖ ሁሉንም ሊፈታ ይገባል፡፡ ህዝቡ በሽራፊ ነዋይ የሚታለልበት ጊዜ ላይ እንዳልሆነ ሊያውቅ ይገባል፡፡ እኔ የጓደኞቼ ሳቅና ጨዋታ ሊቀርብኝ ይችላል፡፡ ሀገሪቷ ግን ብዙ ልጆቿ የጎዳና ሲሳይ ሆነዋል፤ ሲለምኑ ታይቷል፤ ለ“ሥልጠና” በሚል ሰበብ ታጉረውባት ይሰቃያሉ፡፡ ኢህአዴግ ቂምና ጥላቻ ከማምጣት ውጪ ምንም ሊያተርፍ አይችልም፡፡ በእስር እየማቀቁ ያሉ ወገኖች ነገ ሀገራቸውን፡- ከእዚህ መንግሥት እንዴት? መቀበል እንዳለባቸው ተረድተው ከእስር ይወጣሉ፡፡ እነሱ በአካለ ሥጋ ቢታሰሩም ህዝቡ ግን አዕምሮው ታስሮ እንደሚኖር ቀድመው ተረድተውታልና፡፡ የባሰ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ኢህአዴግ እራሱን ሊያስተካክል ይገባዋል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ!

– See more at: http://ecadforum.com/Amharic/archives/17495/#sthash.97oFkqC3.dpuf

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s