በቆሸ አደጋ የወያኔ መንስኤነት እና የችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሔ! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 2, 2009ዓ.ም. ምሽት 2 ሰዓት አካባቢ በተለምዶ ቆሸ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ በደረሰ የመሬት መደርመስ አደጋ 16 የሚሆኑ በሥርዓት የተገነቡና ካርታ (ንድፈ ምድር) ያላቸው መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ቦታ ተረክበው መኖሪያ ቤት የመገንባት አቅም የሌላቸው ወገኖች ለማረፊያ የቀለሱት በርካታ የላስቲክ (የተለጥ) ቤቶች ተደርምሰው በመዋጣቸው እውስጣቸው የነበሩ በርካታ ወገኖች ማለቃቸው ይታወሳል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ 113 ወገኖች እንዳለፉ አገዛዙ አስታውቋል፡፡
ይህ ቁጥር ግን “ከተዳፈኑት ውስት በሕይዎት ያለ ወገን ይኖር እንደሆን፣ ካልሆነም አስከሬን አውጥቶ ለመቅበር!” በሚል አደጋው የደረሰባቸው ቤተሰቦች ቆፋሪ ማሳልጦችን (ኤክስካቫተር ማሽኖችን) በግል ተከራይተው እንዲሁም መንግሥት ላከው በተባለው ተመሳሳይ ማሽን (ማሳልጥ) እየተደረገ ባለው ጥረት የተገኘ አኃዝ ነው፡፡

የዘመናችን ጥጋበኞች የሚያትረፈርፉትን ምግብ በጨዋና ኃላፊነት በሚሰማው ሰው ደንብ ንጽሕናው እንደተጠበቀ ለየኔቢጤ ወይም ለድሀ መስጠት ስለማይወዱና ስለማይፈልጉ ይሄንን እህል አጥቶ ስንት ጦም አዳሪ ድሀ ሕዝብ ባለባት ሀገር የሚተርፋቸውን ምግብ ከቆሻሻ ጋር ስለሚጥሉ ይሄንን ከዕኩይና ግፈኛ የዘመናችን ጥጋበኞች ከቆሻሻ ጋር የሚጣልን ምግብ እየተመገቡ በዚያ ቆሻሻ ስፍራ ላይ በእነኛ የላስቲክ (የተለጥ) ቤቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩትንና ተደርምሶ በተዳፈኑበት አካባቢ ግን እነኝህ ወገኖች አቋጣሪ፣ ተቆርቋሪና አሳቢ አግኝተው “በሕይዎት ያለ ካለ፣ ካልሆነም አስከሬናቸውን አውጥቶ በክብር ለማሳረፍ!” በሚል እስከ ትናንት ድረስ ጥረት እየተደረገ አይደለም፡፡ በመሆኑም በዚህ አደጋ ያለፉ ወገኖቻችን አሁን እየተጠቀሰ ካለው ቁጥርም ከእጥፍ በላይ ሊሆን እንደሚችን መገመት ይቻላል፡፡

ለመሆኑ እነኝህ ወገኖቻችን በቦታው ለመኖር ፈጽሞ በማይመቸውና ለጤና አደገኛ በሆነ ቆሻሻ ሥፍራ ላይ ሔደው ለመስፈር ምን አስገደዳቸው? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ዜጎች በሀገራቸው ጤንነታቸውና ደኅንነታቸው ተጠብቆ ሠርቶ የመኖር፣ መጠለያ የማግኘትና የመሳሰሉት መሠረታዊ ፍላጎታቸው ተሟልቶላቸው የመኖር የማይጣስ የማይገሰስ ሙሉ መብት አላቸው፡፡ የየትኛውም ሀገር ሕገመንግሥት ይሄንን ያረጋግጣል፡፡ ይህ መብት በየትኛውም ሁኔታ ሊጣስ ሊገሰስ ሊገፈፍ የማይችል ሰብአዊ መብት ጭምርም ነው፡፡ መንግሥት ነኝ የሚል አካል ይሄንን የማሟላት ግዴት አለበት፡፡ ልብ በሉ መልካም ፈቃድ ሳይሆን ግዴታ ነው ያለበት፡፡ በምንም መልኩ ይሄንን መሠረታዊ የዜጎች መብት ሊገፍ፣ ሊነፍግ አይችልም፡፡ ያለውን መሬት ለዜጎች አብቃቅቶ የማከፋፈሉን ፍትሐዊ ሥራ መሥራትና ዜጎችን የሀገራቸው ተጠቃሚ ማድረግ ነው ግዴታውና ኃላፊነቱ፡፡ ምክንያቱም በሕዝብ ጥቅሞችና ጉዳዮች ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ የመወሰን ሥልጣንና ኃላፊነት ያለው ሕዝብ እንጅ መንግሥት ስላልሆነ፡፡ መንግሥት የሕዝብን ውክልና ይዞ የሕዝብን ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ማስፈጸም ብቻ ስለሆነ ተግባሩ፡፡ ለሀገር ኢኮኖሚ (ምጣኔ ሀብት) እድገት ከመሬት ሽያጭ ከሚገኝ መጠነኛ ገቢ ይልቅ ዜጎች የመሬት ባለቤት ሆነው መሬቱ ላይ የሚፈጥሩት ሀብት ነው ሀገርን ሊለውጥ ሊያበለጽግ የሚችለው፡፡ ያደጉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየን ይሄንን ነው፡፡ ቁልፉ አስተሳሰብ ይሄ ከሆነ ሊሠራ የሚገባው ሥራ ዜጎችን በሰፊው የመሬት ባለቤት ማድረጉ ነው እንጅ የመሬት ባለቤትነትን መብት ማሳጣት አይደለም፡፡ ይህ ከተደረገ ግን ውሳኔው ሥልጣን የያዘን አካል ጥቅም የሚያስከብር ቡድናዊ ውሳኔ እንጅ የሀገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሕዝባዊ ውሳኔ አይሆንም፡፡

ምን ያህሎቻችን ከላይ የጠቀስኩትን መሠረታዊ መብት እንደምናውቅና ይህን መብታችንንም ማስከበር፣ ማስጠበቅ እንዳለብን እንደምንገነዘብ አላውቅም፡፡ እንደማየው ሕዝቡ ይሄንን መሠረታዊ የዜጎችን መብት የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ መንግሥት ነኝ ከሚለው አካል ችሮታን ሲጠብቅ እንጅ የመንግሥት ግዴታው እንደሆነ አውቆ መብቱ እንዲጠበቅለት ሲጠይቅ ብሎም ሲያስገድድ አላይምና፡፡ መንግሥት ለባለሀብቶች በሽያጭ የቤት መሥሪያ መሬትና መሠረተ ልማት ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ከ90 ከመቶ በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁጥር ለምንይዘው ቤት የመሥራት አቅም ለሌለን ድሀ እና የድሀ ድሀ ዜጎች ጭምር መጠለያ የማቅረብ ግዴታም አለበት፡፡ ይሄንን እናውቃለን ወይ?

ወያኔ መንግሥት ነኝ እንደማለቱ ይሄንን ግዴታውን የመወጣት ግዴታ ነበረበት፡፡ ወያኔ እንኳንና የዜጎችን መብትና የእሱንም ግዴታ በማክበር ቤት የመገንባት አቅም ላላቸው ዜጎች መሬት በመስጠት፣ ቤት የመገንባት አቅም ለሌላቸው ዜጎች ደግሞ የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ከአነስተኛ እስከ ከፍ ያለ የኪራይ ዋጋ የሚጠይቁ የኪራይ ቤቶችን ገንብቶ በማቅረብ ዜጎች ቤት እንዲኖራቸው በማድረግ የዜጎችን መብትና ጥቅም ሊጠብቅ ሊያከብር ግዴታውንና ኃላፊነቱንም ሊወጣ ይቅርና ይህ በመንግሥት ስም ራሱን ያስቀመጠው የወንበዴ ቡድን ከከተማ እስከገጠር አስቀድሞ የመሬት ይዞታ የነበራቸውን ወገኖች ሳይቀር መሬታቸውን እየነጠቀ ለባዕዳንና ለባለሀብቶች በመቸብቸብ ዜጎች በዜግነታቸው ከሀገራቸው ሊያገኙት የሚገባቸውን ጥቅምና መብት አሳጥቷል፣ ነጥቋል፣ ገፏል፡፡ በዚህ ዝርፊያውም እራሱን በከፍተኛ ደረጃ በማድለብ ላይ ይገኛል፣ መሬትን የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ዋነኛ መጠቀሚያ መሣሪያው አድርጎ በመጠቀምም የግፍ አገዛዙን ለማራዘም ጥረት እያደረገበት ይገኛል፡፡

እነኝህ ወገኖቻችን ለኑሮ የማይስማማ፣ ለጤና አደገኛ በሆነው ቆሻሻ ስፍራ ላይ ሔደው ለመሥፈር የተገደዱት ማንም ሊገስሰው፣ ሊሽረው የማይችል በዜግነታቸው በሀገራቸው መጠለያ አግኝተው ጤናቸውና ደኅንነታቸው ተጠብቆ የመኖር መብት እንዳላቸው ተረድተው በራሳቸው ወጪ አንድ ጥግ ላይ ጎጆ ቢጤ ቀልሰው ለመኖር ሲሞክሩ “የጨረቃ ቤት ነው፣ ሕገወጥ ሰፋሪዎች ናቹህ!” እያለ በሌለ አቅማቸው የቀለሷቸውን ጎጆዎች እያፈራረሰ መድረሻ ቢያሳጣቸው ነው “ይህ ስፍራ ቆሻሻ ነውና አይፈለግም ይሆናል!” ብለው እዚያ ቆሻሻ ላይ ደሳሳ ጆጎ እየቀለሱ፣ የላስቲክ (የተለጥ) ቤት እየወጠሩ ለመስፈር የተገደዱት፡፡

የደርግ መንግሥት ይሄንን የዜጎችን መሠረታዊ መብትና የመንግሥትነትን ግዴታ በመገንዘብ ይመስላል የመሬት ላራሹንና ትርፍ የከተማ ቤትን የመውረስ አዋጆችን በማወጅ መሬት ላልነበረው ዜጋ የመሬት ባለቤት አድርጓል፣ ቤት የመሥራት አቅም ላላቸው የከተማ ነዋሪዎች ለካርታ (ንድፈ ምድር) እና ለተመሳሳይ ጉዳዮች አነስተኛ ወጪ በማስከፈል በነጻ ቤት የመገንቢያ መሬት ለዜጎች ሲያቀርብ ነበር፣ ቤት የመገንባት አቅም ለሌላቸው ወገኖች ደግሞ እንደየአቅሙ ከሃምሳ ሳንቲም ጀምሮ በጣም አነስተኛ ኪራይ የሚከፈልባቸውን የኪራይ ቤቶችን ገንብቶ እንዲሁም በአዋጅ የተወረሱ ቤቶችን በማቅረብ የዜጎችን መብትና የመንግሥትነቱን ግዴታ ለማክበር፣ ለመጠበቅና ለመወጣት ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ ወያኔ መንግሥት ነኝ ካለ ይሄንን የደርግን ፈለግ መከተል ሲኖርበት ያልተከተለው “የሚከተለው ርዕዮተዓለም ከደርግ የተለየ ስለሆነ ነው!” እንዳንል የሚከተለው ርዕዮተዓለም ከደርግ የሚለይ አይደለም አንድ ነው፡፡ ወያኔ የሚከተለው የኢኮኖሚ (የምጣኔ ሀብት) ሥርዓት ነጻ (ሊበራል) ቢሆን ኖሮ ከገጠር እስከ ከተማ መሬትን ከዜጎች እየነጠቀ ለባለሃብቶች መስጠቱ ባልገረመን ነበር፡፡

ሙቱ የወያኔው መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ይሄንና ተጓዳኝ ነገሮችን በተመለከተ በአንድ ወቅት ላይ ተጠይቀው ሲመልሱ ያለአንዳች ሐፍረትና የተጠያቂነት ስሜት ነበረ በብዙኃን መገናኛ “ከተማ ለቆ መውጣት ነው!” ብለው በመናገር አገዛዛቸው የአፓርታይድ (የመድሎ) ወይም ለባለሀብቶች ብቻ የቆመ አገዛዝ መሆኑን ያረጋገጡት፡፡

ሰሞኑን ይሄ አሁን የደረሰብንን አደጋ በተመለከተ በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛዎች አንድ የታዘብኩትና በጣም ያናደደኝም እንቅስቃሴ ነበር “በአደጋው ላለፉ ወገኖች ክብር ሲባል ብሔራዊ የሐዘን ቀን ይታወጅልን!” ብሎ አገዛዙን የሚጠይቅ እንቅስቃሴ፡፡ በጥያቄያቸው መሠረትም ብሔራዊ የሐዘን ቀኑ ሲታወጅ ፈንጠዝያ አይሉት ምን ተመልክቻለሁ፡፡ በእውነት በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ በቃ ይህችን ታክል ነው የምናስበው? ይህ አደጋና መንስኤው እኮ በሌሎች ሀገራት ቢሆን ኖሮ ሀገር የሚንጥ መንግሥት የሚገለባብጥ ዐመፅ ያስነሣ ነበረ እኮ ጃል! ይሄን አጋጣሚ ተጠቅመን ሌላው ቢቀር ዜጎችን ለዚህ አደጋ የዳረገው ኢፍትሐዊ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓቱ እንዲቀየር መንቀሳቀስ አልነበረብንም ወይ? ቆይ እንጅ የሐዘን ቀኑ ስለታወጀ ወያኔ ማረፊያ መድረሻ አሳጥቷቸው ቆሻሻ ላይ ሔደው ለመስፈር የተገደዱትንና ለዚህ አደጋ የተዳረጉትን ወገኖች አከበረ ወይም ክብር ሰጣቸው ማለት ነው? ይሄንን ያህል ወገን በራሱ በግፍ አስተዳደሩ ምክንያት ለሕልፈት ተዳርጎ እያለ ጉዳዩን ከመጤፍ ሳይቆጥር ብሔራዊ የሐዘን ቀን ሳያውጅ የማለፉን አሳዛኝና አስገራሚ ሁኔታ ለቀጣይ ትውልድ ይታወቅ ዘንድ ለታሪክ ትቶ ማለፍ ሲገባ ያለ ሐሳቡ ያለፍላጎቱ አሳስቦና ጎትጉቶ የሐዘን ቀን ማሳወጁ ግፉ ለደረሰባቸው ወገኖችና ላለው ቀሪ ዜጋ የሚጠቅመው ምንድን ነው? ይህ አደጋ በዚህ ስፍራ ላይ ሲከሰት ይሄኛው ለስድስተኛ ጊዜ የተከሰተ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ወያኔ ግን ኃላፊነት ተሰምቶት “ዜጎችን ከአደጋ የመጠበቅ ግዴታ አለብኝ!” ብሎ አንዳች ያደረገው ነገር ባለመኖሩ ይሄው የከፋው አደጋ ሊከሰትና በርካታ ወገኖቻችንን ልናጣ ቻልን፡፡ እና ታዲያ ይሄ ሁሉ እየሆነ እየታየ ልንንቀሳቀስ ይገባን የነበረው የሐዘን ቀን መጠየቅ ነው ወይ?

ወያኔ የወገኖችን የዜጎችን መሠረታዊ የዜግነትና ሰብአዊ መብታቸውን ገፎ መድረሻ ማሳጣቱን እስከቀጠለ ጊዜ ድረስ ነገም ተቸግረው እዚህ የቆሻሻ ቦታ የሚሠፍሩና ለተመሳሳይ አደጋ የሚዳረጉ ወገኖች መኖራቸው ይቀራል ወይ? ካለስ የአደጋው መንስኤ ሁላችንም ላይ ያነጣጠረ እንደመሆኑና እንደዜጋም አፋጣኝ መፍትሔ መፈለግ የለብንም ወይ? ወገን ሆይ! ሀገርህን እኮ ተነጥቀህ በገዛ ሀገርህ ባይተዋር፣ ስደተኛ፣ ተጉላላይ፣ ተንጓላይ፣ ተቅበዝባዥ ሆነህ እኮነው ያለኸው! የአንድ ሀገር ሕዝብ ሀገሩን ነጥቆ ቀምቶ በገዛ ሀገሩ የመኖር ዋስትናውን፣ የዜግነት መብቱንና ጥቅሙን አሳጥቶ ዕለት ዕለት እያሳደደ፣ እያፈናቀለ ሀገሩን ለባዕዳንና ለባለሃብቶች እየቸበቸበለት ያለውን አንባገነን አገዛዝ በዝምታ መመልከት አለበት ወይ?

ዜጎች በዜግነታቸው መሠረታዊ መብታቸውና ጥቅማቸው ተከብሮላቸው በገዛ ሀገራቸው ተረጋግተው መኖር ካልቻሉ ዜጎች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ጥቅም፣ ሀገሬ ብሎ ለማለት የሚያስችላቸው መብት ሌላ ምን አለና? ነገ ጠዋት በዚህች ሀገር ላይ ጥቃት ቢቃጣ “ሀገሬ!” ብሎ ተነሥቶ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ሉዓላዊነቷን የሚያስከብረው ማን ነው? መሬታችን ተነጥቆ የተሰጣቸው ባዕዳን ባለሀብቶች ናቸው እንዴ? ወይስ ጥቂት የናጠጡ ባለሀብት ዜጎቻችን? ይሄ ወያኔ መድረሻ ያሳጣው ድሀ ሕዝብ እና መሬቱ እየተነጠቀ ለባዕዳን እየተሰጠበት ያለው ገበሬ አይደለም ወይ? እንዲህ የደም ዋጋ ከፍሎ ያቆያትን እና ነገ አንድ ነገር ቢፈጠርም “ሆ!” ብሎ ተነሥቶ መራር መሥዋዕትነትን የሚከፍልላትን ዜጋ በምን ሒሳብ፣ በየትኛው መሥፈርት ነው ከገዛ ሀገሩ ሊያገኘው የሚገባው ጥቅምና መብት ተነፍጎት ባይተዋር፣ ተሳዳጅና የበይ ተመልካች ሊደረግ የሚገባው? እኮ በየትኛው ፍትሐዊ አሠራር? በወያኔ ዓይነቱ ኢፍትሐዊ የአፓርታይድ (የመድሎ) አገዛዝ ካልሆነ በስተቀር!

እናም የዋሁ ወገኔ ሆይ! የችግሩ መፍትሔ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ማሳወጁ ሳይሆን ስንት ዋጋ ከፍለህ ያቆየሀትንና ወደፊትም የምትከፍልላትን ሀገርህን ነጥቆ የባዕዳንና የባለሃብቶች ብቻ ያደረገብህን፣ በገዛ ሀገርህ ተሳዳጅ፣ ተፈናቃይ፣ የበይ ተመልካች ያደረገህን አንባገነን የወንበዴ አገዛዝ ማስወገድ ነውና በየጊዜው በአገዛዙ የግፍ አስተዳደር መንስኤነት አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር ማላዘኑን ትተህ የችግሮችህ ሁሉ ምንጭ የሆነውን ወያኔን ለመገርሰስ ቆርጠህ ተነሥ! ሳትውል ሳታድር ክንድህን በግፈኛው በጠንቀኛው አገዛዝ በወያኔ ላይ አንሣ! ይህን ማድረግ ካልቻልክ ግን ነገም ያንተ እጣ ከእነኚህ አደጋው ከደረሰባቸው ወገኖች የተለየ እንደማይሆን እወቀው!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s