ህዝባችን የሚሻው መሰረታዊ ለውጥን እንጂ ቀጣይ ወታደራዊ አገዛዝንና ባዶ ተስፋን  አይደለም – ሽንጎ

ሕወሀት/ ኢህአዴግ እንደተሽመደመደና መግዛት አንዳቃተው በተዘዋዋሪ አመነ።፤ይህ ሁኔታ ሰፊ የህዝብ መነሳሳትን ይቀስቅሳል ብሎ የፈራው ሕወሀት/ኢህአዴግ ከስድስት ወራት በፊት የጀመረውን ወታደራዊ አገዛዝ በመላ ኢትዮጵያ ይቀጥላል ሲል በጠቅላይ  ሚኒስቴር ሐይለማርም ደሳለኝ በኩል  በዛሬው እለት ለ”ፓርላማ” በቀረበው  ሪፖርት አረጋግጧል። አስቂኝ የሆነው ይህ ንግግር፣ 82% የኢትዮጵያ ህዝብ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲቀጥል ይፈልጋል ይላል። በአማራና ኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (65% ኢትዮጵያውያን) ስርአቱን ሙሉ በሙሉ እየተቃወሙት እንደሆነ እየታወቀ 82%  ድጋፍ ከየት እንደሚመጣ የህወሀት/አህአዴግ በለስልጣኖች ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ እነርሱ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሉት የህወሀት/ ኢህአዴግን አባላት ብቻ ከሆነ ሌላ ነገር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ንግግራቸው በተለይ ኢኮኖሚውንና እድገትን በተመለከተ  እጅግ የተምታታና መጨበጫም የሌለው ነው፣ ባንድ  በኩል የኢትዮጵያን  ህዝብ ተጨባጭነት የሌለው “እናድጋለን” የሚል ባዶ  ተስፋ ሊመግቡ የሞከሩ ሲሆን  በሌላ በኩል ግን በተጨባጭ የእርሻ ምርት እንደቀነሰ፣ የውጭ ንግድ ገቢ ለሶስት ተከታታይ አመታት እንዳሽቆለቆለ፣ የዋጋ ግሽበት እንዳሻቀበ ከውጭ የሚገኝ እርዳታ እንደወደቀ፣የግብርና ምርት ኤክስፖርት እንደደቀቀ ፤ ድርቅ በየቦታው እንደተስፋፋ፣የሀገሪቱ እዳ እየጨመረ እንደሆነ ስርአቱ ከ26 አመት ስልጣን በሓላ ሀገሪቱን በምግብ ራሷን ማስቻል እንዳልቻለ አምነዋል። ባጠቃላይ ሚዛን ሲታይ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ስርአቱን እድገት ሳይሆን ውድቀት አሽመድምዶ እንደያዘው አምነዋል።

የፖለቲካ ድርድርን በሚመለከት የተናገሩትም እንዲሁ እጅግ አሳዛኝ ፤ ሀገራዊ ሀላፊነት የጎደለው  ነው፡ “ማንም አስገድዶን አይደለም ለድርድር የቀረብነው” “ተጽእኖ ሲደረግብን በፍጹም ፍንክች አንልም” በማለት በግልጽ ቋንቋ ይህ መንግስት እጅግ ችክ ያለ ደረቅ አንደሆነ፣ እና ከሁኔታወች ጋር መጓዝ እንደማይችል፣ ለእውነተኛ ለውጥ የተዘጋጀ እንዳልሆነ ሰጥቶ መቀበልን ሳይሆን በራሱ መስመር ብቻ መጓዝን እንደሚገፋ አረጋግጠዋል። የተጀመረው ድርድር እሩቅ እደማይሄድም የጥርጣሬ ጥላ አጥልተውበታል። ይህ ታዲያ ሀላፊነት የጎደለው ለፍጥጫና ለቀጣይ ግጭት የሚጋብዝ እንጂ ለሰላም በር ከፋች አይደለም፡፡

ያው እንደተለመደው አሁንም ፖለቲካዊ ተቃውሞን በወታደራዊ ሀይል ለመጨፍለቅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደሚያራዝሙ ከመግለጽ ውጭ፤ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በዚህ ንግግራቸው በሀገራችን የተከሰቱትን ዋና ዋና የፖለቲካ ግጭቶች  ለመቅረፍ ምን እንደሚያደርጉ ያቀረቡት ምንም ተጨባጭ የፖለቲካ መፍትሄ የለም።

በራሳቸው ጭንቅ የተወጠሩት ጥቅላይ ሚኒስቴሩና  ንግግራቸው ሁሉ ያተኮረው በድርኢጅታቸው የውስጥ ፡ተሀድሶ” ላይ ነው። ይህ አይነቱ ንግግር ለፓርቲያቸው የውስጥ ስበሰባ እንጂ ለህዝብ የሚቀርብ አይደለም፣፡ ምክንያቱም  ከ 26 አመት ስልጣን በሓላ የኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ህወሀት/ኢህአዴግ መታደስ ቅንጣት ያክል ስሜት የለውም። የሚፈልገው ግፈኛውንና ከፋፋዩን የኢህአዴግ /ህወሀትን ስርአት በማስወገድ የስርአት ለውጥን እውን ማድረግ  ነውና።

ባጠቃላይ ሙሉውን ንግግር አንገታቸውን ደፍተው የፈጸሙት  ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከቃላት ይልቅ በድምጻቸውና  በሰውነታቸው ሁኔታ  (ቦዲ ላንጉጅ) ምን ያክል የተጨነቁና ተስፋም የቆረጡ  አንደሆነ ግልጽ አድርገዋል።

እጅግ ገላጭ የሆነው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ተሰባሳቢዎቹ “የፓርላማ ተወካዮች”  ግማሾቹ ሲያንቀላፉ የታዩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ “ምን ማለቱ ነው” የሚል በሚመስል ሁኔታ እርስ በርስ ሲንሾካሾኩ ተስተውሏል።

ከዚህ ውጭ ግን የሚገርመው በሙሉ ንግግሩ መሀል የተለመደው ረጂም ተከታታይ ጭብጨባ እንኳ አለመደመጡ ጠቅላላ ታዳሚዎቹ ምን ያክል በጭንቅ ላይ እንደሆኑ አሳብቆባቸዋል።

አዎ ስርአቱ የሚገኝበት ሁኔታ በውነትም የሚያሰጨንቅ ነው። የእርሻ ምርት  ከወደቀ፣ ኑሮ ውድነት ከጨመረ፣ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ካልተቻለ፣ የውጭ እርዳታ ከቀነሰ፣ ድርቅ ከተስፋፋ ፣ ኮንትሮባንድ ንግድ ሀገሪቱን ካጥለቀለቀ፤ ምርታቸውን የሚገዛ እየቀነሰ ከሄደ   የፖለቲካ ግጭቱ ከቀጠለ ህዝቡ ስቃዩ ይጨምራል ማለት  ነው፤ ህዝብ ይራባል  ማለት ነው ። ህዝብ የመብት ማጣቱ ይጨምራል ማለት ነው። ታዲያ ባለፈው አመት በኢትዮጵያ እንዲሁም  ከጥቂት አመታት በፊት  በግብጽ ሊቢያና የመን እንዳየነው፤ የተከፋ ህዝብ፣ የተራበ ህዝብ መሪዎቹን ይበላል። ይህ ማንም የማይገታው የተፈጥሮ ህግ ነው።

እኛ የምንለው  መፍትሄው መቆዘምና መጨነቅ ወይም እውነታውን መካድ፣ በጨለማ ውስጥ መደናበርና  ባዶ ተስፋ ለመመገብ መሞከር ሳይሆን ሀገራችንንና ህዝባችንን ገደል እየጨመረ ያለውን የህወሀት/ኢህአዴግ ፖሊሲ አሽቀንጥሮ መጣል ነው። በሙሉ ቅንነት ለሁሉም የሚጠቅመውን ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሄራዊ መግባባት እና ብሄራዊ እርቅን ተግባራዊ አሁኑኑ ማድረግ ነው።

ለዚህም

  • በተለያየ ሰበብ አስባብ  ለእስር የተዳረጉትን የፖለቲካ እስረኞች ሁሉ በተለይም ደግሞ አንደ አንዱአለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ፤ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናና ኮሎኔል ደመቀን የመሳሰሉ የፖለቲካ መሪዎች፣ እንደ እስክንድር ነጋና ተመስገን ደሳለኝ፣ የመሳሰሉት ጋዜጠኞች  ወዘተ አሁኑኑ እንዲፈቱ  ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል። ባጠቃላይ የህሊናና የፖለቲካ እሥረኞች ሁሉ አላንዳች ቅድመ ሁኔታ  ከእሥር ነጻ ሊሆኑ ይገባል።
  • መሰረታዊ የሆኑ የዴሞክራሲ መታፈንን፣ የሰብአዊ መብት መገፈፍን፣ የህግ የበላይነት መጥፋትን የመሰሉት ጉዳዮች በግልጽ ውይይት ተደርጎባቸው እነዚህን እውነታዎች ለ26 አመታት ያስቀጠለው ሁኔታ የሚወገድበትን መንገድ በጋራ መሻት የግድ ይላል፡። በግፍ የተጎዱ ሁሉ ሊካሱ የሚችሉበትን ሁኔታም ማመቻቸት ተገቢ ነው።
  • መሰረታዊ መብትን የሚገድቡና የሚጥሱ ህግጋቶችን ለምሳሌ የሲሺክ ማህበራትን፣ የፖለቲካና  የመብት ታጋይ ድርጅቶችን እንዲሁም መስል  እንቅስቃሴዎችን የሚያኮላሸውን ህግ፣ የጸረ ሽብርተኝነት ህግ፤ የሚዲያ ሕግ ወዘተ መሰረዝ አስፈላጊ ነው። ህገ መንግስቱም የሀገራችንን ህዝብ ፍላጎት በሚያንጸባርቅ መልኩ የሚሻሻልበትን ሁኔታ መመርመርና መተግበር ይኖርበታል።
  • በቅርቡ በአማራ በኦሮሞና ሌሎችም ክልሎች የተነሱትን የብዙ ወገኖቻችን ህይወት የተገበረባቸው መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች በጥሞናና በሀገራዊ ሀላፊነት መመርመር መወያየትና መፍትሄ መፈለግን የግድ ይላል፡ በነዚህ አካባቢዎች የሚካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻም ባሰቸኳይ መስቆም የግድ ነው፡
  • በህዝባችን ላይ የተጫነውን የጭንቅ ቀንበር ማስወገድ አስፈላጊ ነው። ለዚህም በመላ ሀገሪቱ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና ኮማንድ ፖስት ባሰቸኳይ ማንሳት ያስፈልጋል። ማንም ኢትዮጵያዊ  አሁንም ከየሰፈሩ እየተጎተተ የማይታሰር በወታደርና ደህንነት ሰራተኞች የማይደበደብ፣ እንደፈለጉ የማያስሩት እንደሚሆን ከቃላት ባለፈ በተጨባጭ ማሳየት አስፈላጊም አጣዳፊም ሆኖ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን አለበት።
  • በሀገሪቱ መሰረታዊ የፍትህ ሥርአት፣ የምርጫ ቦርድ፣ የምርጫ ሂደት፣ የሰራዊት እዝ፤ የደህንነት ቢሮ፤ ወዘተ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነትና የፓርቲ ተቀጽላነት ወጥተው መላ ህዝብን ሊያገለግሉ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ማካሄድና መሰረታዊ የእርምት እርምጃም መወሰድ ይኖርበታል።
  • የጋራ ችግሮቻችንን ከስር መሰረቱ ለመፍታትና ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ፣ አግላይነትን አስወግዶ በሀገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉ የሚሳተፉበት ሂደትን ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል። ብሄራዊ መግባባትና እርቅ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ስብስብ ወይም ድርጅት የፈለገውን ወስኖ በሌላው ላይ የሚጭነው ወይም “ከፈለጋችሁ ተቀበሉ ካልፈለጋችሁ ተውት “ የሚባል ሳይሆን፣ ሁሉም ወገን የሂደቱም ሆነ የውጤቱ ባለቤት ሊሆኑ የሚችሉበት መሆን ይኖርበታል። ያሁኑ አካሄድም ገና ከጅምሩ ሁሉንም ባለድርሻዎች ያሳተፈ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።

ሽንጎ ደግሞ ደጋግሞ እንደገለጸው ፍላጎታችን በሀገራችን ውስጥ ህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ እንዲሁም አንድነት፣ እኩልነት፣ የህግ የበላይነትና ዴሞክራሲያዊ መብትን ተግባራዊ ማድረግ ሲሆን፣ ይህን በማድረግም የአመጽ፣ የጦርነት፣ የአሳሪና ታሳሪ አዙሪት፣ ቂም በቀልና ቁርሾ  እንዲያከትም ማድረግ ነው።

በ26 አመት ተሞክሮ እንደማይሰራ የተረጋጋጠን አካሄድ ለማስቀጠል መሞከር ትርፉ ይበልጥ ግጭትንና ሁከትን መጋበዝ ብቻ ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s