የአውሬው ፈጫሳዎች – ያየያየ ዪልማ

 

በዚህ አለም የሚታወቀውን ታላቁን ክፉ – “ሰይጣንን” እንደ ብልት ሆነው : አካሉን የሚያሟሉ ሁለት የጭራቅ ውሉዳት፡ ሰው በላዎች ፣ በጋራ ማህተም ያሰሩበትን ስምምነት እንዳነበብኩ ይህ ሆነ፡፡ ተገረምኩ! እንደተገረምኩም እስካሁን አለሁ!!!

በስምምነቱ ላይ አንዱ ፈራሚ ሆኖ የቀረበውና ውክልናውም የኔውን ህዝብ (ኢትዮጵያዊያንን) ያስቀደመው ጉድ፡ ገሃዱ ያገሬ ታሪክ አይቶት የማያውቀው በህዝቡ ላይ ፡ እጅግ ክፉ መሆኑ ከመቼውም በላይ ጠልቆ ገባኝ፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ስም ከፊት አስቀድሞ ስምምነት የተፈራረመው፤ በሰው ደም ፈጫሳ ቃልኪዳኑን ከሰይጣን ጋር እያደሰ መንበሩን የሚፀናው፤ ከጃንሆይ በተመነተፈ ስያሜ እራሱን የሚያስጠራው “ጠሃዩ መንግስታችን” ነው፡፡

ይህ ተራ አውሬ አይደለም፤ ይለያል፡፡ ቀለቡ የንፁኃን ስጋ ፣ የሚጋተው ደግሞ የምንዱባንን ደም ሲሆን፣ ህዝበ ኢትዮጵያ፤ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች የገጠር ቀዬዎች፣ ደሃ ከተሜ ሆነ ገበሬው ለስፍራው ሁሉ ሻጋታ በመሆኑ ፡ ከነጭርንቁሱ ይነሳና ከተማ ከገጠር ይልማ ተብሎ የምንዱባኑ ወገኔ ቤት ንብረት ሲፈርስ ጥሪቱ ሲቃጠል፤ ጭቁኑ ህዝብ ሁሉ መና ሆኖበት በስቃይ ለሰማያት ዋይታውን ሲያሰማ፤ የደሃው ህዝብ ጩኸት ለአውሬው የመንፈስ ማንቂያ ሙዚቃው፣ የዚህ ሁሉ የደሃ ጥሪት ቃጠሎ እና የጥቀርሻው ሽታ፣ ለአውሬው ቆሌ የሚያውድ ልዩ የሽቱ መአዛው ፣ ዶጋ ከሚሆነው የወገኔ ጥሪት ደግሞ – የገንዘብ መኸሩ ሆኖለት አውሬው ሃሴትን ይሰበስባል፡፡ በነዚህ ተደጋጋሚ ግፎች የደለበ ስለሆነ ነው አውሬው የታሪካችን ልዩው – የሚል ድምዳሜ ላይ ለሰየም ያበቃኝ፡፡

የዚህ ድምዳሜ ዋነኛ መነሻ የሆነኝ እና የዚህ ሀተታ አስኳል የሆነው ታዲያ፡ በኢሃዲግ እና በአሸባሪው የሶማሊያ አንጃ አል-ሸባብ መካከል ጂሊብ በሚባል የሶማሊያ አንድ ከተማ በ2011 የተፈረመው ስምምነት ነው፡፡ ውሉን እንዳነበብኩ ያልኩት አንድ ነገር ነው፡፡ በዚህ አይነት ስንት ሸፍጥ ይሆን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተደረገው ብዬ እየዘገነነኝ ብዙ አሰብኩ፡፡ ደግሞም ተስፋዬ ታላቅ ነው፡ እንደዚህ ሁሉንም በሚስጥር ይዘው እንደማይዘልቁት እሙን ስለሆነ፤ የተደረገውን ሁሉ ፈጣሪ በጊዜው ይግለጠው ብዬ፤ ፈጥኜ ብእሬን አነሳሁና ለነብስያዬ ያባሽውን እንትፍ በይ በማለት እነሆ ምስክርነቴን እሰጣለሁ፡፡

እንደዛሬ ኢትዮጵያዊያን በዘርና በጎጥ ልክፍት ታጥነው ተከፋፍለው ልዩነትን ማሳል ሳይጀምሩ እና አንድ ሳሉ፤ “ኢትዮጵያ ተወረረች!” የሚለው፡ “ያ” ሰማያት በአንድ ላይ የሚያስተጋቡት የማይደራደሩበት የመርዶ ድምፅ፤ ልክ የማይክል ጃክሰንን “ትሪለር ሙዚቃ” የመግቢያ ምት ሲሰማ አንዳች ልዩ ስሜት እንደሚወርረው የፖፕ ሙዚቃ አፍቃሪ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሆ ብሎ ተነስቶ የፈጫሳ ዶሮ ከሆነበት የወያኔ-ኤርትራ ጦርነት ጀምሮ በዚህ መንግስት ምሪት የተደረጉ ዋነኛ ክስተቶች በሙሉ ፣ ከፊት ለፊት ገፅታ አመክንዮአቸው በስተጀርባ አስገራሚ የፈጫሳ ሸፍጥ ያጨማለቃቸው ናቸው፡፡

“ያ” ጦርነት፤ የወያኔ-ኤርትራው ማለቴ ነው፤ መነሻ ምክንያቱ ባድመና ዛላንበሳ ሳይሆን- የወያኔና የሻእቢያ በትግል ወቅት የነበረ ሚስጥራዊ ስምምነት በመፍረሱ ነበር፡፡ የኤርትራን ነባራዊ ሁኔታ ቀድሞ ያሰላው ሻእቢያ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ጨው የተበተኑትን ዜጎቹንና የደሃውን የኢትዮጵያ ገበሬ ምርት እንዲሁም አጠቃላይ የኢትዮጵያን ምድራዊ ሃብት ስሌት ውሰጥ ከትቶ ሲያበቃ፡  በኢትዮጵያ ዱቄት ቡኮ አብኩቶ መልሶ ለኢትዮጵያውያን መብል ሸጦ ፤ በትግል ስምነታቸው አማካኝነት ኤርትራን “የአፍሪካ ሲንጋፖር” ሊያደርግ ሲወጥን ቀን እስኪያልፍላቸው እምቢ ያላሉት የወያኔ ፊታውራሪ አውሬዎች፡ ያቺ ታላቅ ኤርትራ- ለምን “ታላቋ ትግራይ” አትሆንም ብለው ከአምስት ቢሊየን በላይ የሚቆጠር የቀድሞው የኢትዮጵያ መገበያያ ብር ሻእቢያ እጅ ላይ እንዳለ ዋጋ ሲሳጡበት ነበር፤ ህዝብ በወያኔ-ኤርትራው ጦርነት አውሬው የመጀመሪያ ፈጫሳውን ያደረሰው፡፡ እንጂ ባድመን ለማስመለስ አልነበረም፤ ባድመማ መች ተመለሰ፡ ከነበረው ተቆርሶ ተሰጠ እንጂ፡፡

ከዚህ የጀመረው የአውሬው የፈጫሳ ልማድ እና ክፋት ያለማባራት አድጎ እና ዳብሮ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ መልክ፤ ያ በሰውም በአምላክም ፊት እንደነብር ዝንጉርጉርነት እስኪለይ ደማቅ የነበረው የኢትዮጵያ ልዩ ማህተብ በአውሬው እየተበጠሰ፡ ሌላ ስውር የክፋት ስፌት በላይዋ ላይ እየተሰፋ፣ ዘመን ተሸጋሪ ውበቶቿ የእርጅና ካባና ስያሜ እየተደረበባቸው ያቺ ጥላሁን ሲገልጽ ሆዳችን የሚባባላት እና የምናውቃት ውቧ ባለፀጋ ቀዬ ግርማዎቿ ሁሉ እንደአበቃለት የእባብ ቆዳ እየተንሰረሰረ በሚጓዝ የማይሰማ የጊዜ ሂደት አውሬው ወዟን አውልቆ እንደጣለው አየሁና አዘንኩ፡፡ ግን ደግሞ እኔ ከማውቀውና ከተጣለው የኢትዮጵያ ግርማ ስር ቆሜ፡ አንዳንድ ሊረሱ የማይችሉ የበላይ ሸንጎ ጉልበትን የሚያሳዩ ነገሮች ትውስ አሉኝና፤ ይቅር በለኝ አልኩ፡፡ አዎ ይህ ሸንጎ ካሻው፡ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሁሉ በወጉ ለሚናገር ሰንደቅ፣ እንዲሁ ለሚያጣቅስ ደግሞ ባንዲራ የሚል ስያሜ ያለውን መለያችንን ፤ በሶስት ደቂቃ ውስጥ ደርዘን ጊዜ ያክል ጊዜ እየደጋገመ ፤ በንቀት ጨርቅ ፣ ጨርቅ ፣ ጨርቅ ፣ ጨርቅ…. እያሉ በማናለብኝነት መጣራት ለሚቀናቸው አገር አልባዎች፤ እንደ ዘመነ ፈርኦን ሰማያት ፈርደው፤ ከተያዙበት ቅፅበት አንስቶ በቢጫ ቁስል መላ አካልን መትቶ፡ እንደ ማንኪያ ቀንጥሶ ሲያፈራርስ በአይኔ ስላየሁ ትውስታው ፈገግ አሰኘኝ እና ተፅናናሁ፡፡

… አምላክ ይግለጥላችሁ! የአዲስ አበባ መንደሮች ስላረጁ ብቻ አልፈረሱም፤ ያፈረሳቸው አንድ ነገር ነው! ነዋሪዎቹ ሁሉ በጋራ የሚያውቁት የሚያስታውሱት (Collective Memory) ይህ ተውስታቸው ደግሞ ለአውሬው ጠንቅ ስለሆነ እንጂ፡፡ ከአድዋ ዘመቻና ድል እስከ ቅርቡ የ1997 ምርጫ ድረስ የሆኑትን ከአህጉር እስከ ሃገር ምድሪቷን የናጡ ማእበሎችን፡ ከነግለታቸው የሚያስታውስ የቁራ እኩያዎች፡ ከማይሞት ትዝታቸው ጋር አንድ ላይ ችምችም ብለው ይኖሩ ስለነበር ነው መንደሮቹ ሁሉ የፈረሱት፤ ተጋንኗል ብሎ የሚል ካለ፡ ለምን ይመስላችኋል ከነ አራት ኪሎ አይነት ፈራሽ መንደሮች የሚፈናቀሉ ምንዱባን እንደ ደንጊያ ካብ አስር ቦታ ተበትነው ሲያበቁ፡ የእውነት ማጣቀሻቸው ኢቲቪ ብቻ በተደረገባቸው አዲሶቹ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዙሪያ የሚያሰፍራቸው ለምን ይሆን… ብቸኛዎቹ እንዳነሳሳቸው የሰፈሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከፍልውሃ ሚካኤል (ልዩ ስሙ-አልታድ) የሰፈሩት ብቻ ናቸው አንድ ላይ የሰፈሩት፤ እነሱንም በሁለት ፖሊስ ጣቢያ ተከብበዋል፤ ይህ ስህተትም አስፋሪው ግለሰብ ስለሆነ እንጂ አውሬው ቢሆን አይስተውም፡ አልደገመውም፡፡

…አባይን ገድቦ የሚያቆም ስፍራ በአማራ ክልል ስላልነበረ አይደለም አባይ ከአማራው ደጃፍ ርቆ እየፈሰሰ ሱዳን ከመግባቱ በፊት ህዳሴ ተብሎ የተገደበው፤ መጀመሪያም ቢሆን አባይን ያክል ጉድ ወንዝ ከጣና ፣ ከጎኑ ደግሞ አማራ የሚባል ብሄር ተፈጥሮ ፈቅዳ በማኖሯ ዘላለም የሚያርረው የአውሬው ቆሽት፡ በአማራ ህዝብ ጥላቻ ጥምቀት በፈጠሙ የአውሬው ፍለፋዮች ሸፍጥ፡ አባይን የወለደውን የአማራን ምድረ-ማህፀን ሾተላይ አድርገው፡ ህዝቡን ባገሩ ካባይ ቆርጠው ማለያየታቸው አባይን አሶሳ ላይ መገደባቸው፡፡ ለዘመናት ግብፅ የኢትዮጵያዊያንን ቁጭትና እንባ ከአሸዋ እየለወሰች በልታ ስትሳለቅ እንደኖረች እንዲሁ፡ አውሬውም ከአማራው ህዝብ ማጣት እና ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ላቦት በተቀማ ገንዘብ ፡ ሲሚንቶ ገዝቶ የቂም ግንብ ገንብቶ፡ በገባው ውል መሰረት ወደ ከርሱ ዶላር ሲያጋብስ አማራውን ይህ በወሰኔ የሚለው ካባይ የሚጣቀስ አንዲት ጥሪት ለመቶ አመት እንዳይኖረው መሆኑ ነው እንጂ፡፡

… “አንቀፅ 39” ያስፈለገው ሌሎች ብሄሮች ማንነታቸው ሊጠፋ ደርሶ ካፋፍ ስለነበረ ነው ወይስ… በጥላቻ “መንበረ-ፀባኦቱ” ደደቢት – በአማራ ጥላቻ ሰልጥነውና ሰይጥነው ለኪዳናቸው ፀጉር ባንጨባረረሩት አውሬዎች የጥላቻ ኪዳን ምክንያት ነው … እዚያ በበረሃ ክፋት ያነገቡት የአውሬው ደቀመዛሙርት ውርስ ገቢር መሰረት፡ ከሁሉ ከሁሉ : አማራ የሚባል ሰደድ እሳትን በውስጡም ህብረብሄራዊ መስተጋብርን ያቀፈችውን ኢትዮጵያን አፍኖ ለማጥፋት የተመረጠ አመዳቸው ስለሆነ ነው እንጂ፡፡ በአውሬው አስተምህሮት መሰረት፡ ኦሮሞነት ከአማራነት በመሰረታዊ የብሄር ይዘት እንደማይለይ ቢያውቅም፤ ለአማራ ያለው አቻ የማይገኝለት በቁንፅል ቲዎሪ ላይ የሚመሰረት ጥላቻ ምክንያት፤ አማራ የሚለውን ስም እንደ ብሄሮች መካነ መቃብር አድርጎ ስለሚቆጥር፡ ለዚህ ብሄረ በላ ሰደድ እሳት ደግሞ ማቆሚያው ይህ አንቀፅ እንዲሆን ስለተፈለገ ነበር፡፡ ይህ እሳት ሸዋን በልቶ አወይቦ መልክ አሳጣው፡ ስለዚህ ትንሷን ትግሬን ሰልቅጦ ሳያጋሳ ማርከሻ የሚሆን አንቀፅ እናርቅቅ፡ ለራሳችንም አያቶቻችን ከሺህ አመት በፊት ያለፉትን ኋላቀር ጎጠኝነትንና፡ በተለይ ጠማማውን ልባችንን እናሰንብት ተብሎ የተበጀ ኢትዮጵያዊነትንን በገሃድ የመካጃ ቅልስ፡ ኢትዮጵያዊነት የሚለውን ጠይም ጥላ ከመሰረቱ የናጋንበት ውል እንጂ፡ የብሄር ብሄረሰቦች ቫለንታይንስ ዴይ እንዳይመስላችሁ!!!፡: “እነሱ” የሚጨፍሩት፡ አውሬው ነሻጣ የሚያመጣ ዜማ በአበል አስጠንቷቸው ነው፡፡

ታላቁ የስነፅሁፍ ሊቅና የስነፅሁፍ ኖቤል ተሸላሚ ታጎር : ባንድ አጋጣሚ ሲናገር፤ “ሁልቆ መሳፍርት የሆነው የሰው ባህሪ አለምን ከነሞላዋ ለየግሉ በውስጡ ተላብሷል፤ የትኛውም የዝህች አለም ጥልቀት ከሰውልጅ ውስብስብ ተሰጥኦ አይልቅም፤ ስለሆነም የአለም እውነታ በሰው ሃቅ ውስጥ ይጠቃለላል!” ብሎ ሰውን ገልፆ ነበር፡፡ …”ቀለም” አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ እና ቀይ ከለሮችን ጠቅልሎ እንደሚወክልና እንደሚገልፅ እንዲሁ፡ – ኢትዮጵያዊም! በባንዲራው ስር የሚታወቅ ነበር: የአውሬው ሸፍጥ ሺህ አመት ወደኋላ አሽቀንጥሮ ጣለን እንጂ፡፡

የማያልቀውን የአውሬውን የሸፍጥ ዝርዝር በዚሁ ገታ ላድርግና ወደመነሻዬ ልግባ፡፡ ለማመን ቢከብድም ይህንን ስምምነት በአይኔ በብረቱ አይቼዋለሁ፡፡ በላቲን ቃላት በሶማሊኛ ቋንቋ የተፀፈው ይህ ስምምነት ጥቅል የሆነ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ድርሻዎች ለሁለቱ ተፈራራሚዎች ተዘርዝሮ የሰፈረበት እንዲሁም ስምምነቱን የሸመገሉትም ሆኑ አውሬው ኢሃዲግን ወክለው የፈረሙትንም ጭምር በሰው ደም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሚስጥራዊ ሰነድ ነው፡፡ ተፈራራሚዎቹ የየራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት አላማ ይዘው የመጡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን መንግስት በስምምነቱ ላይ ወክለው ፊርማቸውን ያኖሩት አቶ አብዲ መሃሙድ ኡመርም ስምምነቱን በማስፈፀም የተገባላቸውን ቃልኪዳን ( እነጉርሱም ፉኛን ቢራን፤ ፉግግን የሚታከኩትን ባለደጋ ለም መሬት የያዙትን የኦሮምያ ስፍራዎችን በሂደት ሊያገኙ በመሆኑ ሽልማታቸውን እያሰቡ) መንግስትን ወክለው የተገኙ ሲሆኑ፡ አልሸባብን የወከሉት ደግሞ ሼክ ሙክታር አብዙቤር የሚል ቲተር ያላቸው የአልሸባብ ሰው ናቸው በባለ ስድስቱ ገፅ የፈጫሳ ምህላ ግርጌ ላይ ፊርማቸውን ያሰፈሩት፡፡

 

የውሉ ይዘት በአጭሩ በተገለፁ ዝርዝር ሃሳቦች የሁለቱንም ወገኖች ጥቅም እንዲያስጠብቅ የተዘጋጀ ቢሆንም ፤ በጋራ የውል ስምምነቱ ላይ አውሬው ለአሸባሪ አንጃ እውቅና ሰጥቶ የተስማማባቸውን የሽብር ሽርክናዎች እንጂ ስለያንዳንዱ መስመር ማተት አያስፈልግም፡፡

በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ከተቀመጡ ግዴታዎች ባጭሩ፡-

 • ….የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ ሶማሊያ ለሚንቀሳቀሰው አልሸባብ ከኪስማዮ ወደብ የሚያገኘውን ጥቅም ጨምሮ ሌሎች እስላማዊ ህግን በህዝቡ ላይ ተግባራዊ እያደረገ የሚሰበስበውን ገቢውን ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለአንጃው ሊያከብርለትና በምንም መልኩ ጣልቃ እንዳይገባበት፤
 • በጁባላንድ ላይ የተለየ ፍላጎት እያሳየ ያለውን እና ራስ ኮምባኒን ጨምሮ ጁባላንድን እንደ ራስ ገዝ በሶስት የምትከፈል ፌደራላዊ ክልል እንድትሆን ሁሉንም አይነት ድጋፍ ከሚያደርገው የኬንያ መንግስት ጋር የኢትዮጵያ መንግስት እንዳያብር፤
 • በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግስት ከአሚሶም የሚያገኘውን ማናቸውን መረጃዎች ከአልሸባብ ጋር በፍጥነት እንዲለዋወጥ፤
 • የአፍሪካ ህብረትንና ኢጋድን ሁለቱ ተፈራራሚዎች ለሰፈሯቸው ፖለቲካዊ አላማዎች እንዳስፈላጊነቱ በስውር ጥቅም ላይ ማዋል፡ በዚህም ዋነኛዋን የአልሸባብ እንቅፋትን ኬንያን ዋነኛ ኢላማ ማድረግ፤
 • የኢትዮጵያ መንግስት ለአልሸባብ ሎጂስቲካዊና ወታደራዊ ድጋፎችን በቁስ ( ይህ ከመሳሪያ እስከ ተሸከርካሪ የደርሳል) ሊደግፍ ፡ ድጋፉም እንደ አስፈላጊነቱ ደግሞ በሽያጭ ሊያቀርብ ለዚህም ባይዶዋና አፍመደው የተባሉ ስፍራዎችን ለየብስና በጥርጊያ አየር ማረፊያነት የቁስ ማቅረቢያ ስፍራዎች ሆነው እንዲያገለግሉ መስማማታቸውን ወታደራዊ መረጃዎን ለመለዋወጥ የታሰሩ የመገኛኛ የሬድዮ ሞገዶችን ሚስጥራዊ ልውውጥ ያጠቃልላል፡፡
 • የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋሩ የሶማሊያ መንግስት የሚጋረውን በዚህ ረገድ ፡ ለአልሸባብ ህልውና ጠቃሚ ሊሆን የሚችል ማንኛውም አስፈላጊ መረጃዎችን፡ ወታደራዊ ደህንነቶቹንም ጭምር በመጠቀም ለአንጃው በፍጥነት እንዲያቀብል የተስማማበት የጋራ ውሉ ካሰፈራቸው አንኳር ሃሳቦች መካከል የሚገኙ ናቸው፡፡

በአልሸባብ በኩል ከተቀመጡ ግዴታዎች ባጭሩ፡-

 • የዚህ ስምምነት ዋነኛ ግዴታ ከኢትዮጵያ ድንበር ውጪ ተበትነው በሰሜን ሶማሊ አቅራቢያ እንዲሁም በዚሁ በጁባ ላንድ የሚገኙ የኦኤንኤሌፍ ቡድንን እና መሰል ሌሎች የኢትዮጵያ መንግስት ጠላቶችን በተመለከተ የተጠናከረ መረጃ የመሰብሰብና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቋሚነት መለዋወጥ፤
 • አልሸባብ ከኤርትራ መንግስት ጋር እንዳለው የሚከስሱ ፕሮፖጋንዳዎችን በአላማ ያለማስተባበል
 • ይህንን ስምምነት ጨምሮ ማናቸውም የሁለትዮሽ ስምምነቶች የአጋር መንግስት መጠሪያቸው የሻእቢያ መንግስት መሆኑ ብቻ እንዲታወቅ ግዴታውን ያለስህተት መጠበቅ
 • የኢትዮጵያ መንግስት ከኦጋዴን እስከ ቡረኦና ላስአኖት(የሶማሊ ላንድ ግዛቶች) ድረስ የሚያደርጋቸውን የየብስ የባህር ንግድ እንዲሁም የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶች በምንም መልኩ እንዳስተጓጓሉ
 • ይህ ስምምነት ከተፈረመ ጀምሮ የትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት ከአንጃው የሚነሳ ምንም አይነት የፀጥታ ችግር እንዳይገጥም ታማኝ መሆን
 • ለኢትዮጵያ መንግስት የሚፈፀሙ ማናቸውም ክፍያዎች የአከፋፈል ሁኔታ በኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎት ላይ የሚመሰረት እና በሌላ አባሪ ዝርዝር የስምምነት ማእቀፍ የሚከወን መሆኑን መቀበል ለአልሸባብ የቀረቡ የውል ግዴታዎች ናቸው፡፡

ይህንን ስምነት ለፍሬ እንዲበቃ በማድረግ ለአልሸባብ ህልውና በሙሉ ዋልታነት ፊርማ አኑሮ ያረጋገጠው የኢትዮጵያ መንግስት በንፁሃን ደም የደለበ እውነተኛ አውሬ መሆኑን ጨርሼ ያረጋገጥኩት ይሄኔ ነው፡፡ እነዛን ሁሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሶማሊያዊያንን ደም በየቀኑ ከሚያፈስ አሸባሪ ቡድን ጋር ኢሃዲግ ማህተም ማሰሩ መቼም ቢሆን የምገረምበት ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ስምምነት የኢትዮጵያ መንግስት ጢምቢራን የሚያዞር የዶላር ናዳ ወደ ጎሮሮው አመት አመት እንዲፈስለት ያደረገ፡ የሽብር ቡድን ስለሆነ መረዳት አይከብድም፡፡ በተለይ ደግሞ ከ2004 አንስቶ እስካሁን ድረስ ጎረቤታችን ኬንያ በዚሁ ቡድን ከልክ በላይ መታመሷ ባንፃሩ ለአልሸባቦች የእኛ አገር ርቋቸው አንዴም ሳይደርሱብን መኖራቸው ሲታይ ምስሉ ግልፅ ሆኖ ይታያል፡፡

አውሬው እስትንፋሱ ክፋት፣ ስጋው ሸፍጥና ተንኮል፣ ድምፁም እንደእባብ ስውርና መርዛም የሚፊለፍላቸውም እፉኝቶች ናቸው፡፡ ሌላ ሊወልድ አይችልም፤ የኢትዮጵያ ልጆች ግን ዘራቸው ከአርያም ቆዳቸውም የማይቀየር ነው፡፡ አሮጌ ጨርቅ ተብሎ የተጣለውን ሊቀየጥ የማይችለውን ቀለመ-አርያም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራቸውን ከአፈሯ ውስጥ ወጥተው ለብሰው ይነሳሉ!!! ምክንያቱ ደግሞ የሃያሉ የአምላክ ቃልኪዳን እንቁ ከሆነችው ከኢትዮጵያ ጋር እንጂ በደም ግብር ከጨቀየ አውሬ ጋር አያብርም፣ እግዚብሄር ፃድቅ ነውና፡፡ ብቻ ልጆቿ አምላካቸውን ድምፅ ሰምተው ይነሱ እንጂ የንፁሃንን ደም እየፈጨሰ ያለው አውሬ ስሪቱ ሸክላ ስለሆነ ከብርቱ የኢትዮጵያ ልጆች ጡጫ አይተርፍም፤ እኔም እንግዲህ ለእውነት ድርሳን ከሚተጉት ጎራ እድል ቀላቅላኝ ብእሬን አንስቼ እነሆ እውነት እንካችሁ ጉድ ብላችሁ ይችን ፀሎት ወደ አርያም አድርሱ እባካችሁ፡፡ …አምላክ ሆይ በቃችሁ በለን! ጠላታችንን ከመርገጫን ስር አስገባ፣ ያቺም ቀን ቅርብ ትሁን፣ አሜን፡፡ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር፡፡

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s