በአማራዊነት መንፈስ ላይ ጀምበር አትጠልቅም | ቬሮኒካ መላኩ

 

በአለም ላይ የሚነገር አንድ ረጅም እድሜ ያስቆጠረ የፖለቲካ ምሳሊያዊ አባባል (Maxim) አለ ። ” ዘላቂ ሰላምን የምትሻ ከሆነ ለጦርነት ተዘጋጅ ” ይላል። ጥንካሬህን አይተው ጠላቶችህ ይፈሩሃል። ድል አድራጊነትህን ገምግመው የሚፋለሙህ ይጠፋሉ እንደ ማለት ነው።
ቻይናዊው የጦር ጄነራል፣ ስትራቴጂስት እና ፈላስፋ ሰን ዙ. በበኩሉ
” ጠላትን ለይቶ ማወቅና በጠላት ላይ ቁርጥ አቋም መውሰድ የድል ግማሽ ያህል ነው፡፡ ” አይነት አባባል አለው ፡፡ የአማራ ህዝብ ደረጃቸው ይለያይ እንጅ የተለያዩ ጠላቶች ነበሩት አሁንም አሉት ። ከዋናው ጠላቱ ወያኔ ጀምሮ ጥቃቅን ጠላቶች ነበሩት አሁንም አሉት ።

በአሜሪካ አገር የመጀመሪያው የጥቁሮች ጋዜጣ በ 1827 ዓ.ም ሲቋቋም እንደ ታላቅ መሪ መፈክር አድርጎ የተነሳው << ለእኛ ማሰቡን ፣ለራሳችን መናገሩን ለእኛ ተውልን… … የራሳችንን ታሪክ ከማንም የበለጠ ለመናገር የምንችለው እኛው ነን> > የሚል ነበር ።
በአጭሩ ለማለት የፈለጉት ለራሳችን ጉዳይ ሞግዚት አያስፈልገንም የሚል ነበር ። እኔም ዛሬ በዚች አጠር ያለች ጦማሬ አማራ ስለራሱ ለመናገር ሞግዚት አያስፈልገውም ምክንያቱም ትከሻችን ጭንቅላታችንን ለመሸከም አይከብደውም የሚለውን አፅንኦት በመስጠት አማራዊነት ግቡን ይመታ ዘንድ አንዳንድ ጠቃሚ የምላቸውን ነጥቦች ለመዳሰስ እሞክራለሁኝ።

ባለፉት 25 አመታት አንዳንዶች የሉም ብለውናል። የደረሰብን አሰቃቂና ኢሰብአዊ ድርጊት የፈለገውን ያህል አስከፊ ቢሆንም አሁን ባለንበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን ።
አሁን አሁን አማራ ሳይሆኑ የአማራን ማሊያ ለብሰው ጨዋታውን የሚያደፈርሱት ብዙ ናቸው ። አንደ ብአዴን ያሉት አማርኛ ተናጋሪ ህውሃቶች አማራ ሳይሆነ አማራን ወክለው “አማራ ለሺህ አመታት የጨቆናቸውን ብሔር ብሔረሰቦች ስህተቱን ያርማል” ይሉናል። እኛ የምንኮራበትን የሺህ አመታቶች የኋላ ታሪክ እነሱ ይቅርታ የሚያስጠይቅ ስህተት አድርገው ይደሰኩራሉ ። እነዚህ የዘመናችን ፕሮፓጋንድስቶች የሚሰድቧቸው አባቶቻችን የመላ ጥቁር ህዝብና የሦስተኛ አለም መመኪያ የሆነውን የአድዋን ጦርነት በጀግንነት በመዋጋት የኮሎኒያሊዝምን ተስፋፊነት በመግታት በባርነት ሥር ይማቅቁ ለነበሩት የትግል አርአያ በመሆን የድል ችቦን አቀጣጥለው ነፃነትን አስገኝተዋል። ይሄን አኩሪ ታሪክ እነሱ ቢያጣጥሉት እና ቢንቁት አይደንቀንም ። የነፃነትን ዋጋ የሚያውቀው ነፃ ህዝብ ነው። አማራ ደሞ እንደ ስያሜው ትርጓሜ ነፃ ህዝብ ነውና ነፃነትን ያከብራል።


የአፍሪካን ነፃነት እና በራስ መተማመን ጠርበው ቀርፀው እዚህ ካደረሱ ህዝቦች በዋናነት የሚጠቀሱት አማሮች ናቸው።
ከአማራ ህዝብ አብራክ ወጡ የተባሉት የኢትዮጵያ ነገስታት ኢትዮጵያን ሲገዙ ባንድራቸውን ከህንድ ውቅያኖስ እስከ የመን ተክለው ነበር። የግሪክ አማልክት ሳይቀሩ ሰርተው ሰርተው ሲደክማቸው ለእረፍት የሚመጡት ወደ እኛው የጊዮን ምንጭ አባይ ነበር ። የአማልክቶች አባት የሆነው ታላቁ ዚየስ በሰለቸውና በደከመው ቁጥር ” እስቲ ወደነዚያ መልከ መልካምና ደጋግ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ልሂድ ” ነበር የሚለው ።

በረጅሙ የስልጣኔ ጉዞው የራሱን ፍልስፍና ያበቀለው የአማራ ህዝብ ለአፍሪካ ህዝቦች የኩራት ምንጭ ነበር።
መላው አፍሪካ አህጉር ታሪኩን በአፈ ታሪክ ሲቀርፅ ኢትዮጵያውያን ታሪካቸውን በሚፃፍ ቋንቋ ይዘግቡ ነበር ። በአማራዎቹ አማርኛ ቋንቋ ።
አማራ ለ 85 ብሄር ብሄረሰብ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹና እህቶቹ በአፍሪካ ብቸኛ የሆነውን አማርኛና ግእዝ ያበረከተ ህዝብ ነው ።ለዚህም ምስክሩ አማርኛ መላው ሀገሩ መነገሩ ነው።
ተወደደም ተጠላም ዛሬ ራሱ አማርኛ በአፍሪካ ውስጥ የራሱ ፊደል ያለው ብቸኛው ቁዋንቁዋ ነው። ነገ የሚያንቀሳቅሰው ከተገኘ የአፍሪካ ህብረት የስራ ቁዋንቁዋ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም።

የሶስት ሺ ወይም ከዚያ በላይ እድሜ ያለው ታሪክ ባለቤቶች ብንሆንም ረዥም ትግል እና ብዙ መስዋእት ብንከፍልም ለውለታችን የተከፈለው ጠላትነትን ነው።
በአለም ታዋቂነትና ክብር ለኢትዮጵያ የሰጡትን የቀድሞ ስልጣኔ መስራች ህዝቦች ብንሆንም ያገኘነው ምላሽ ” ትምክተኛ “የሚል ነው።
ሙሴ በሲና ተራራ ፣ ክርስቶስ በታቦር ተራራ እና ቡድሃ በሂማሊያ ተራራ የሰበኩትን ፍቅርን እና አንድነት በኢትዮጵያ ብንሰብክም ያተረፍነው ጥላቻን ነው።ምናልባት የአማራ ጥፋት ነው ከተባለ ይህችን ድንቅ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ከስንቱ ቅኝ ገዥና ፋሽስት ጋር እየተጋደለ እዚህ ማድረሱ ነው።

የህውሃት ፋሽስቶች በኢትዮጵያ ለደረሰው ኢኮኖሚያዊና ማሀበራዊ ችግሮች ሁሉ አማራን ተጠያቂ በማድረግ ፀረ አማረነት አይነተኛ የትግል መሳሪያቸው አድርገው ተጠቅመውበታል።
ጠላትን ፈጥኖ አለማወቅ ከባድ ጉዳት የሚያስከትል ስህተት ነው። አማራ ጠላቱን ቀልጥፎ አለማወቁ ዋጋ አስከፍሎታል። አማራ እኮ ግብፅን በግዮን አባይ ውሀ ብቻ ማንበርከክ ይችላል! እንዴ አማራ እኮ ጣልያንን ያንበረከከ ህዝብ ነው።

እናም አማራ ሀያል እንዲሆን አራት ነገሮች የግድ ያስፈልጉታል።
1~ ጠንካራ አእምሮ
ምሳሌ እንደ እራኤላውያን ~ ጠቅላላ የእስራኤል ቆዳ ስፋት ሰሜን ሸዋን አታክልም ። በህዝብ ቁጥር ካሰላናቸው ደሞ የአዲስ አበባ ከተማን ነዋሪ አያክሉም ነገር ግን የአለምን ፖለቲካና ኤኮኖሚ የሚዘውሩት እነዚህ ህዝቦች ናቸው። ለዚህ ምስጢሩ አንድ እና አንድ ነው ይሄውም በትምህርት የዳበረ አእምሮ ባለቤት ህዝቦች መሆናቸው ነው።
2~ ጠንካራ ኢኮኖሚ (እንደ አሜሪካውያን)
3~ ጠንካራ መከላከያና ብሄርተኛ ሰራዊት(እንደ ሩሳውያን)
4 ~ ጠንካራ ነፃ የአማራ ሚዲያ(እንደ አሜሪካው CNN)።
እነኝህ ከላይ የተጠቀሱት ከሞላ ጎደል ያንድ ሀገር የጥንካሬ መስፈርት ናቸው ። የአማራ ህዝብ እነዚህን ተሞክሮዎች በመውሰድ የቀደመ ገናናነቱን የማይመልስበት ምክንያት አይኖርም።

እርግጥ ዛሬ አማራ ህዝብ የወደፊቱዋ ኢትዮጵያ እርሾ ይሆኑ ዘንድ ዘመን የሚሻገር ህልም አስጨብጦ በመንፈስ የወለዳቸው ልጆች ዛሬ ህልሙን እውን ለማድረግ ቆርጠዋል። በውነት ቃሉን ጠብቀው፤ እርሱን ብለው በማያሻማ ቋንቋ አፎቱን ከሰገባው አዉጥተዋል። እኛም ያባቶቻችን ልጆች ነን ብለዋል።
ዛሬ አማራዊነት ከስጋና ከደም በላይ ነዉ። አማራዊነት መንፈስ ነው። ሚሊዮኖች ሊሞቱለት ከፊት የቆሙለት አይዲዮሎጅ ነው።። አማራዊነት በጥቁሩ ሰማይ ላይ እንደ አጥቢያ ኮከብ የሚያንጸባርቁ ኮኮቦች ። በአማራዊነት መንፈስ ላይ ፀሃይ አትጠልቅም እኛም ቅዤት የሌለበት ጤነኛ የአማራን ነፃነት እናልማለን።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s