የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ድፍረትና ንቀት | ይገረም አለሙ

22 ፓርቲዎች የፕሮፌሰሩን ፓርቲ ጨምሮ ከወያኔ ጋር በወያኔ ጋባዥነት ድርድር ጀምረዋል የሚለውን ዜና እየሰማን ባለንበት መድረክ ከኢህአዴግ ጋር የብቻ ድርድር ይፈልጋል ምክንያቱም ዋንኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ስለሆነ የሚል ነገር በፕ/ር በየነ አንደበት ሲነገር ሰማን፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ እንመራለን የሚሉት ርስ በርስ ስለሚተዋወቁ እናንተ 22ትም ሆናችሁ 102 አትረቡም ጠንካራው እኔ የምመራው መድረክ ነው ማለታቸው ተቀባይነት ባይኖረውም አያስገርምም፡፡ ህዝቡ መድረክን ርስተ ጉልት ስላደረጉት እርሳቸውም ሆነ ስለ መድረክ ምንም እንደማያውቅ ቆጥረው ይህን ማለታቸው ግን የድፍረታቸውን ልክ የንቀታቸውን መጠን ነው የሚያሳየው፡፡ በወያኔ መሪዎችም በተቀዋሚ ተብየዎችም አክብሮት የተነፈገው ህዝብ ፡፡

የፕ/ር በየነን ንግግር እንደሰማሁ እኔ ከማውቀው በላይ ፈጥኖ በአእምሮየ የታወሰኝ አቶ አሰፋ ጫቦ በአንድ ጽሁፋቸው የገለጹዋቸው ነው፡፡ አንዲህ ይላሉ አቶ አሰፋ ፕ/ር በየነን ሲገልጹዋቸው፡፡ “በየነ ጴጥሮስ እላይ በጨረፈታ ለማሳየት ለሞከርኩት ስራው መላውን አለም ደጋግሞ ዞሯልኮ! በዚህ 25 አመት ሙሉ የድርጅቶች መሪነቱ ምን ፈየደ? ምንስ ተናገረ? ምንስ ጻፈ ?የሚል ቢኖር ጉዱ ይፈላ ነበር። የሚል ሰው አለመኖሩ የበጀው መስለኝ። እንዳይኖሩ አድርጎ ይሆን?አሁን ግርማን ላከበት? አንዳንዴ ያኔ ከባንክ ገንዘብ ይዞ ጠፍቶ በኋላ የወያኔ አባል ሁኖ የገንዘብም ምክትል ሚንስቴር እንደሆነው ሰውዬ በየነ ጴጥሮስም የወያኔ አባል ይሆን? እላለሁ ይኸው ለ25 አመት ያ ሁሉ ሰው ወህኒ ሲወርድ በየነ አለምን ይዞራል”ነበር ያሉት፡፡ አዎ! ለምን አንዴት ወዘተ ብሎ የሚጠይቅ ጠፋና እኝህ ሰው ከማንም የበለጥሁ ከሁሉም የታመንሁ ዋንኛው ተቀዋሚ እኔ ነኝ ለማለት በቁ፡፡ ወይ ድፍረት ወይ ንቀት፡፡

ርሳቸውን ለዚህ ካበቃቸው ነገር አንዱ መድረክን ከፍት አድርገው ሳያዩ ዋንኛው ተቀዋሚ እያሉ የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ስራ ነው፡፡ ቢታይ ግን መድረክ ቢከፍቱ ተልባ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ያው ተልባውም በየነና በየነ ብቻ ነው ለማለት የሚያስችል ማስረጃ ማቅረብ ስለምችል በድፍረት እናገራለሁ፡፡

በየነ በሁለት ካርድ፤ ፕ/ር በየነ በ1993 ዓም ሀ ብለው ፖለቲካው ከጀመሩ ግዜ አንስቶ በሁለትና በሶስት ካርድ ነው ሲጫወቱ የኖሩት አሁንም የሚጫወቱት፡፡ በአንድ ግዜ የብሄርም ሀገራዊም ፓርቲ ሊቀመንበብር ሲሆኑ አይተን ርሳቸውን ብቻ ሳይሆን በዚህ ሁኔታ ምስክር ወረቀት የሰጣቸውን ም/ቦርድንም ታዝበናል፡፡የኋላውን ልተወውና አሁን እያደረጉ ያለውን እንይ፤ ለድርድር የተዘጋጁት 22 ፓርቲዎች ናቸው ሲባል እነማን ናቸው ብዬ ፍለጋ ገባሁ፣ ከአገኘሁት ዝርዝር ውስጥ አንድ ቀድሞ ሰምቼው የማላውቅ ፓርቲ ስም አገኘሁና ስጠይቅ ሳጠያይቅ የፕ/ር በየነ መሆኑን ሰማሁ፡፡(የሚመሩት ያላልኩበትን ምክንያት ተረድታችሁልኝ ይሆን!) በአንድ ወገን ፓርቲያቸው ከሌሎች ጋር በመሆን ለድርደር በሉት ለውይይት ተቀምጠዋል፣በሌላ በኩል ደግሞ በመድረክ ሰም ተናጠል ድርድር ይጠይቃሉ፡፡ ምን አልባት ይህ አንዱ የዋና ተቀዋሚነታቸው መግለጫና ማረጋገጫ ይሆን!

መድረክ ቢከፍቱ ተልባ፣በስምንት ፓርቲዎችና በሁለት ተዋቂ ግለሰቦች የተመሰረተ ተብሎ ዋንኛው ተቀዋሚ ፓርቲ እየተባለ ሲሞካሽ ውስጡን የምናውቀው ሰዎች መድረክ በጠንካራ መሰረት ላይ ያልቆመ ምንም የማይፈይድ የት ሊደርስም የማይችል አንደሆነ ተናግረናል ጽፈናል፣በዚህም ስድብ ፍረጃ ውንጀላ አስተናግደናል፡፡ዋንኛው ተቀዋሚ እያሉ የሚያሞግስቱም ሆኑ ዜና የሚሰሩት ወገኖች ግን ጠለቅ ብለው ለማወቅ ቀርቶ ትንሽ ገለጥ አድርገው ለማየት ፍላጎቱም የላቸውምና መድረክም እንደ ወያኔ በቁጥር ጨዋታ ቢከፍቱ ተልባነቱን ደብቆ ይኖራል፣

መቼም መድረክ ጠንካራ ነው ከተባለ ራሱ ፓርቲ አይደለምና በአባሎቹ ማንነትና ምንነት ነው የሚሆነው፡፡ይህ እንዳይታወቅ አንድም አባል ፓርቲዎቹ በሙሉ አይገለጹም ሁለትም በየግዜው የስም ለውጥ ይደረጋል፡፡ መድረክ ሲመሰረት ስማቸው የሰፈረውን ፓርቲዎች ይዛችሁ እነዛው በየግዜው ያደረጉትን ውህደት የስም ለውጥ ብትመለከቱ መድረክ ማነው የሚለው ይጠፋባችኋል፡፡ ይህ መለዋወጥ እንዳለ ሆኖ ከመስራቾቹ ወጣ የተባለ አልሰማንምና እዛ ላይ ተመልሰን ፓርዎቹን እንይና የመድረክን ጥንካሬ ወይ ድክመት እንመስክር፡፡

ከመነሻው በስምንት ፓርቲዎችና ሁለት ተዋቂ ግለሰቦች የሚለው አገላለጽ ተገቢም ትክክልም አልነበረም፣ የቱንም ያህል ቢገዝፍ ግለሰብ ግለሰብ ነው፡፡ወይ ሰዎቹ ዝና ካልፈለጉ ወይ ሌሎቹ በእነርሱ ስም የሆነ ነገር እናተርፋለን ብለው ካላሰቡ በስተቀር የሰዎቹ መጠራት አስፈላጊ አልነበረም፣ ሆኖም አልቀጠለምና አነጋጋሪነቱ አብቅቷል፡፡

ሁለተኛው ስህተት ህብረትና ግንባር አይደለም የተናጠል ፓርቲያቸውን መርተው አንድ ርምጃ ማስኬድ ያልቻሉ ሰው( ራሳቸውን ለምክትል ሚኒስትርነትና ለፓርላማ ወንበር ማብቃታቸው ርምጃ ነው ካልተባለ) ሰው ሊቀመንበር ማድረጉ ነው፡ይህን መሰረት አድርጎ እስካሁን የዘለቀው ነገር ደግሞ መድረክ መድረክ ከፕ/ር በየነ ይዞታ መላቀቅ አለመቻሉ ነው፡፡ እነርሱም አንደ ወያኔ ተጨፎኑ እናሞኛችሁ እያሉን ሊቀመንበርነት በዙር ነው ይሉናል እንጂ ፕ/ር በየነ የመድረክ ፑቲን ሆነው ነው የምናያቸው፡፡

የመድረክ አባል ፓርቲዎች፣

አንድነት-“ ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር አንዲሉ ሁሉም እንገፍ እንገፍ ሲል እናያለን እንጂ የፖለቲካ ትግል የጀመረው ደቡብ ህብረት ነው”ፕ/ የሚሉት ፕ/ር በየነ ባይቀበሉትም ከመድረክ አባላት የተሻለ አቅም የነበረው አንድነት ነበር፡፡ ግና ከመነሻውም የመድረክ አባል እንዲሆን የተፈለገው ገኖ መውጣት የጀመረውን ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ለማሽመድመድ ነበርና ይሄው ተሳክቶ ዛሬ አንድነት በመድረክ ውስጥ ስሙ እንጂ በአካል የለም፡፡ ይህን ያህል አባላት አሉት ለሚለው የቁጥሩ ጨዋታ ቢጠቅም እንጂ ከዚህ የሚዘል ፋይዳ የለውም፡፡

አረና ፣ ስለዚህ ፓርቲ በቂ መረጃ የለኝም፣ ቢሆንም ግን መድረክን ከበየነ ርስተ ጉልትነት ለማላቀቅ ባይችልም ከቁጥር መግለጫነት የዘለለ ፓርቲ እንደሆነ አስባለሁ፡፡
ኦፌኮ- የመድረክን መሰራቾች ቁጥር ሰምንት አድርሰውት የነበሩት በአንድ ብሄር ሰም የሚጠሩት የአቶ ቡልቻና የዶ/ር መረራ ፓርቲዎች ተዋህደው የፈጠሩት ነው ኦፌኮ፡፡ ፓርቲው በኦሮምያ አካባቢ ሰፊ መሰረትም ተቀባይነትም እንዳለው ቢታወቅም መድረክ ውስጥ ያለው በአቅሙ መጠን አይደለም፡፡ ሌላ ሌላው ቢቀር በኦሮምያ ከአንድ አመት በላይ ዜጎች ሲገደሉ ሲታሰሩ ኦፌኮ ያላባራ ጩኸት ሲያሰማ ከመድርክ በኩል የሰማነው ዋንኛ ተቀዋሚ ሊያሰኘው ቀርቶ የኦፌኮን አባልነት የሚመጥን አይደለም፡፡ በርካታ የኦፌኮ አመራሮች ሲታሰሩም የመድረክ ደምጽ ለስላሳ ነው፡፡ የም/ል ሊቀመንበሩን የዶ/ር መረራ እስር ደግሞ መድረክ አይደለም ዋንኛ ተቀዋሚ ተቀዋሚም አንዳልሆነ ያሳየ ነው፡፡ መሪው ታስሮ ዝም የሚል ነእደምን ፓር ሊባል ይበቃል፡፡ በአንጻሩ ደቡብ ውስጥ በተለይ ደግሞ ሀድያ አካባቢ አንድ ነገር ሆነ ከተባለ የመድረክ ጩኸት ነው ቀድሞም ገኖም የሚሰማው፡፡
የበየነ ፓርቲዎች፣ከሀብዴድ እስከ ኢማዴ-ዴህአፓ ድረስ ፕ/ር በየነ የተጠሩባቸው ወይንም ዪጠሩባቸው ፓርቲዎች ህብረቶች ግንባሮች ወዘተ ግራ ስለሚያጋቡኝ ነው ጠቅለል አድርጌ የበየነ ፓርቲዎች ማለቴ፡፡መድረክ ውስጥ እንኳን ደቡብ ህብረት፤ኢዴኃህ፣ሶሻል ዴሞክራሲ፣ማህበረ ዴሞክራሲ ደቡብ ህብረት፣የሚባሉ በርሳቸው የሚመሩ ፓርቲዎች ነበሩ ወይንም አሉ፡፡ መድረክ ሲመሰረት ኢዴኃህና ደቡብ ህብረት ነበሩ ከትንሽ ግዜ በኋላ ደግሞ ደቡብ ህብረትና ሶሻል ዴሞክራሲ ሆኑ፤አሁን ያሉት ሰንትና እነማን አንደሆኑ ባላውቅም (የምርጫ ቦርድ ድረ ገጽም አዲስ መረጃ አይሰጥም)አዲስ ፓርቲ መስረተው ይሁን ወይ አዋህደው ወይንም የአንዱን ሰም ለውጠው ባይታወቅም የኢትዮጵያ ማህበራዊ ዴሞክራቲክ -ደቡብ ህብረት አንድነት ፓርቲ በምህጻሩ ኢማዴ-ዴህአፓ የሚባል ፓርቲ አላቸው፡፡ በዚህ ፓርቲ አማካኝነትም ነው ከ 22ቱ አንዱ ሆነው ለድርድር የቀረቡት፡፡
ኢዴአን፣ይሄ ስሙም መሪዎቹም የማይታወቅ መድረክ የህን ያህል ፓርቲዎች ስብስብ እያሉ የሚዘግቡ ጋዜጠኞችም ሆኖ የሚያወድሱ አባል ደጋፊዎች ለማወቅ ጥረት ያላደረጉበት ከስም ማጀቢያነትና ከቁጥር ማብዣነት ያለፈ ታይቶ የማያውቅ አሁንም በድረክ የአባላት ዝርዝር ውስጥ ይኑር አይኑር የማይታወቅ ነው፡፡
ሶዲኃቅ- ስሙ እንደሚነግረን ቅንጅት ነው፤ግን እንኳን የተቀናጁት ፓርቲዎቸ ራሱ ቅንጅት ተብየው ከነመሪዎቹ አይታወቅም፡፡ ለቁጥር ማደሚቂያነት ግን ውሏል፡፡ አሁን በስም አንኳን መኖር አለመኖሩ አይታወቅም ፡፡

ይሄ ነው እንግዲህ ዋንኛው ተቀዋሚ ፓርቲ ተብሎ የሚነገርለት፣ ፕ/ር በየነንም ለድፍረትና ንቀት ንግግር ያበቃ፤አጀኢብ ነው፡፡ በምርጫ 2007 ከ200 የበለጠ እጩ ማቅረብ ያልቻለ መሆኑንም አክሉበት፡፡

በመጨረሻ ፕ/ር በየነ መድር በኢምፔሪያል ሆቴል ባዘጋጀው ሲፖዚየም ላይ ባቀረቡት የጥናት ወረቀት የአንድና ሁለት ሰው ፓርቲዎች ፓርቲ እየተባሉ የህብረት አባል እንዲሆኑ መደረጉ ላለፉት ህብረቶች መዳከም ዋና ምክንያት ነው ብለው ነበር፡፡ ከላይ ያየናቸው የመድረክ አባሎች ሰንቶቹ ከዚህ ነጻ ናቸው፣የፕ/ር በየነን ፓርቲዎች ጨምሮ?

የኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮት: በስህተት ላይ ስህተት በመድገም ስህተትን ማረም!

ሳተናው

ከስዩም ተሾመ

በጦላይ የተሃድሶ ማዕከል በአንድ የማደሪያ ክፍል ውስጥ በአማካይ 100 ሰልጣኞች (እስረኞች) አብረው ያድራሉ። እኔ በነበርኩበት ክፍል ውስጥም 98 ሰልጣኞች (እስረኞች) ነበርን። የተሃድሶ ሥልጠናው ከቀኑ 11፡00 ላይ ይጠናቀቃል። ከምሽቱ 12፡30 በኋላ የመኝታ ቤቶቹ በሮች ከውጪ ይዘጋሉ። ከዚያ በኋላ እስከ ንጋቱ 12፡30 ድረስ በጣም አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር የመኝታ ክፍሉ በር አይከፈትም። ማታ ማታ አብዛኛው ሰው ከአንዱ ፍራሽ ወደ ሌላው ፍራሽ እየተዟዟረ “ወሬ” ይሰልቃል። ከአንድ ሰው በስተቀር አብዛኞቻችን ሥራ-ፈቶች ነበርን። ይህ ብቸኛ ሰው ከአርሲ ሮቤ የመጣው “ገመቹ” ነው። (ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ትክክለኛ ስሙ ተቀይሯል)

ገመቹ የአምስት ልጆች አባትና በጣም ታታሪ ሰው ነው። ዘወትር በሥራ እንደተጠመደ ነው። ከስልጠና መልስ የተለያየ ቀለም ያላቸውን የሲባጎ ገመዶችን በመጎንጎን የኢትዮጲያና የኦሮሚያ ባንድራ ምስል ያላቸው የጥርስ መፋቂያዎችን እየሰራ አንዱን በ10 ብር ይሸጣል። ለእኔም አንድ መፋቂያ ሰርቶ በአስር ብር ሸጦልኛል። አንድ ቀን “ገሜ… እስካሁን ስንት መፋቂያ ሰርተሃል?” ብዬ ስጠይቀው “አንድ መቶ በላይ ነው” ብሎኛል። የተሃድሶ ሥልጠና ሊጠናቀቅ አከባቢ የገመቹ ገበያ በጣም ደርቶ ነበር። በማዕከሉ የሚገኙ የፌደራል ፖሊሶች ሳይቀሩ የገመቹን የእጅ-ሥራ ለመግዛት ሲሻሙ ነበር። በዚያ ምንም መስራት በማይቻልበት፣ ሁሉም ሰው ሥራ-ፈት (ሥራ-አጥ) በሆነበት ቦታ ገመቹ ከጥርስ መፋቂያ ብቻ ከአንድ ሺህ ብር በላይ ገቢ አግኝቷል።

 

የተሃድሶ ሥልጠናው ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ከማዕከሉ ስንወጣ በየትኛው የሥራ መስክ ተደራጅተን መስራት እንደምንፈልግ መጠይቅ ሞልተን ነበር። ከዚያ በፊት ግን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የቢሮ ኃላፊዎች በቦታው ተገኝተው በክልሉ እና በፌዴራሉ መንግስት ትብብር ተግባራዊ ሊደረግ ስለታቀደው የሥራ እድል ፈጠራና ድጋፍ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተውናል። ገመቹም ወደ አርሲ ሮቤ ሲመለስ በየትኛው የሥራ መስክ ተደራጅቶ መስራት እንደሚፈልግ በመጠይቁ ላይ ሞልቷል። ያን ዕለት ማታ “ገሜ… አሁንማ መንግስት በማህበር አደራጅቶ የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግልህ ነው። በየትኛው የሥራ-መስክ ለመሰማራት አቀድክ?” ስል ጠየቅኩት። የገመቹ ምላሽ ግን በጣም አስገራሚ ነበር። “ማ… እኔ?! እኔ አምስት ልጆች አሉኝ። ከማንም ሰነፍ ጋር ተደራጅቼ አገልጋይ ከምሆን ከልጆቼ ጋር ተደራጅቼ ብሰራ ይሻለኛል። የመንግስት ድጋፍ ከምር ከሆነ ለእኔና ልጆቼ ብድር ቢሰጠን መልካም ነበር” አለኝ።

የጦላይ የተሃድሶ ማዕከል ዋና አስተባባሪ የነበሩት ኮሚሽነር በስልጠናው መጠናቀቂያ ላይ ካቀረቡት ሪፖርት ላይ ብቻ በመነሳት በማዕከሉ ከነበሩት 5670 አከባቢ ሰልጣኞች (እስረኞች) ውስጥ 1474 (26%) በአመፅና ረብሻ ተግባር ተሳትፈዋል በሚል ማስረጃ የቀረበባቸውና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው። የተቀሩት 74% ደግሞ በአመፅና ረብሻ ተግባር ስለመሳተፋቸው ይሄ ነው የሚባል ማስረጃ ያልቀረበባቸው፤ እንዲሁ በአጉል ጥርጣሬ፣ በተሳሳተ መረጃ፥ ጥቆማ ወይም በተሳሳተ ሰዓትና ቦታ በመገኘታቸው ምክንያት ተይዘው የታሰሩ ናቸው። ገመቹ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው። በአጠቃላይ፣ ከተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች ተይዘው እንደ ጦላይ ባሉ የስልጠና ማዕከሎች የወንጀል ምርመራና የተሃድሶ ስልጠና ሲሰጣቸው ከነበሩት ውስጥ አብዛኞቹ ያለ በቂ ማስረጃ የታሰሩ ነበሩ።

በእርግጥ እንደ አንድ የክልሉ ተወላጅ ሆነ እንደ ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ ባለፉት አመታት የኦሮሞ ሕዝብ ሲያነሳቸው የነበሩትን የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትህ ጥያቄዎችን በሞራልና ሃሳብ ደግፈው፣ እንዲሁም በተግባር ጭምር ተንቀሳቅሰው ሊሆን ይችላል። የክልሉና የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ይህን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ በኃይል ለማፈን ያደረጉት ጥረት ሁኔታውን ወደ አላስፈላጊ ግጭትና ሁከት አንዲያመራ አድርጎታል። በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ለታየው የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ዋናው ምክንያት ሕዝቡ ለሚያነሳቸው የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በተለያየ ደረጃ ያሉ የመንግስት አካላት ተገቢ የሆነ ምላሽ አለመስጠታቸው መሆኑ ጥርጥር የለውም። ከዚህ አንፃር፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው “የኢኮኖሚ አብዮት” ያሉበትን መሰረታዊ ክፍተቶች እንመልከት።

በመጀመሪያ ደረጃ፣ የሕዝቡ መሰረታዊ ጥያቄ “የክልሉ ህዝብና መስተዳደር ሕገ-መንግስታዊ መብትና ነፃነት ይከበር!” የሚል ነው። ይህን በመብትና ነፃነት ላይ ማዕከል ያደረገ የዴሞክራሲ ጥየቄ “በኢኮኖሚያዊ አብዮት” ምለሽ ለመስጠት መሞከር ፍፁም ስህተት ነው። “ኦሮሚያን ለአመፅ፣ አዲስ አበባን ለቆሻሻ የዳረገች አንቀፅ” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ፅሁፍ ላይ በዝርዝር እንደተገለፀው፣ ከኢኮኖሚ አብዮት በፊት የሕግ-የበላይነት መቅደም እንዳለበት በዝርዝር ተገልጿል። ለምሳሌ፣ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) ተግባራዊ ማድረግ በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል። ይህን የክልሉን ሕዝብና መስተዳደር ልዩ ጥቅም እንዲረጋገጥ የተቀመጠን ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ በተጨባጭ የፖሊሲ ጥናት ያልተደገፈ የኢኮኖሚ ዕቅድን ተግባራዊ ለማድረግ መጣደፍ ተገቢ አይደለም።

ሁለተኛ፡- በኢኮኖሚ አብዮቱ የመሪነት ሚና የሚጫወተው ክልላዊ መስተዳደሩ መሆኑ ራሱን የቻለ ሌላ ችግር ነው። በእቅዱ መሰረት ኦዳ የተቀናጀ ትራንስፖርት፣ ኬኛ የመጠጥ ማቀነባበሪያ፣ አምቦ ፕመር ማምረቻ፣ የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ እና የኦሮሚ የግንባታ ኩባኒያዎች እንደሚቋቋሙ ተገልጿል። ይህን የክልሉን ወጣቶችና አርሶ-አደሮች ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለለት ዕቅድ ተግባራዊ የሚያደርገው ግን የክልሉ መስተዳደር ነው። በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉ ሕዝብ ሲያነሳቸው ከነበሩት ጥያቄዎች ውስጥ፤ የክልሉ መንግስት በሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች የአብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አለማረጋገጡ፣ የክልሉ መስተዳደር በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ውስጥ የተዘፈቀ መሆኑ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አለመሆኑ፣ …እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። እነዚህና ሌሎች ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ግንባር ቀደም ተጠያቂ የሆነው መስተዳደሩ ነው፡፡ ይሄው አስተዳደራዊ ስርዓት ዕቅዱን በአግባቡ ተግባራዊ ያደርጋል ብሎ ማሰብ በራሱ የዋህነት ነው።

 

ሦስተኛ፡- በእርግጥ አብዛኞቹ የክልሉ ወጣቶች በአመፅና ተቃውሞ አንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉት በመብትና ነፃነት እጦት እንጂ በሥራ-አጥነት ምክንያት አይደለም። ይሁን እንጂ፣ ሥራ-አጥነት በራሱ ሕዝቡ ከሚያነሳቸው የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች አንዱ ነው። ነገር ግን፣ እሱም ቢሆን አሁን በተቀመጠው አቅጣጫ ዘላቂ መፍትሄ አያገኝም። “የሥራ-ዕድል በብር አይገዛም” በሚለው ፅሁፍ በዝርዝር እንደገለፅኩት፣ የክልሉ መንግስት ለወጣቶች ተጨማሪ የሥራ-ዕድል ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት በተሳሳተ እሳቤ እና የአገልግሎት አስጣጥ ሥርዓት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ተጨባጭ የሆነ ለውጥና መሻሻል ማምጣት አይቻልም። በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት ክፍተቶች አንዱ ከላይ በፅሁፌ መግቢያ ላይ ገመቹ “ከማንም ሰነፍ ጋር ተደራጅቼ አገልጋይ ከምሆን…” በማለት የገለፀው የአሰራር ሥርዓት ነው። በክልል ሆነ በሀገር ደረጃ “ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት የሥራ-ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ…” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተው አሰራር ከሥራ-ሰሪዎች ይልቅ ሥራ-አጦችን የሚያበረታታ ነው።
በመሰረቱ ልዩ ድጋፍና ማበረታቻ መሰጠት ያለበት ለሥራ-ፈጣሪዎች እና/ወይም ለሥራ-ሰሪዎች እንጂ ለሥራ-አጦች አይደለም። ሥራ-ፈጣሪዎች ወይም ሥራ-ሰሪዎች የሚባሉት የራሳቸውን የቢዝነስ ተቋም ለመመስረት እና/ወይም ለመምራት የሚያስችል ልዩ ክህሎት፥ ልምድና ብቃት (entrepreneurial qualities) ያላቸው ናቸው። እነዚህ መንግስት የሚደረግላቸውን ድጋፍና ማበረታቻ በመጠቀም በዋጋና ጥራት ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አገልግሎት ማቅረብ ይችላሉ። በዚህም ድጋፍና ማበረታቻው የተቋማቱን ምርትና ምርታማነት፣ እንዲሁም ተወዳዳሪነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሳድገዋል። ይህ በኢኮኖሚው ውስጥ ተጨማሪ እሴትና የሥራ-ዕድል ይፈጥራል። ሙያዊ ክህሎትና ብቃት ላላቸው ወጣቶች አማራጭ የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል። ሁሉም ወጣቶች ባላቸው ዕውቀትና ክህሎት ልክ ተወዳድረው የመስራትና የተሻለ ገቢ የማግኘት እድል ይኖራቸዋል።

ነገር ግን፣ የሥራ-ዕድል ለመፍጠር በሚል ሥራ-አጥ ወጣቶችን በማህበር ሰብስቦ ድጋፍና ማበረታቻ መስጠት ኪራይ ሰብሳቢነትን ከማስፋፋት የዘለለ ፋይዳ የለውም። ሥራ-አጥ ወጣቶች የራሳቸውን የቢዝነስ ተቋም ለመመስረት እና/ወይም ለመምራት የሚስችል ልዩ ክህሎት፥ ብቃትና ልምድ የላቸውም። ምንም ያህል ድጋፍና ማበረታቻ ቢደረግላቸው በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አገልግሎት ለማቅረብ የሚስችል ግለሰባዊና ተቋማዊ አቅም መገንባት ይሳናቸዋል። በመሆኑም፣ ከመንግስት የሚደረግላቸውን ድጋፍና ማበረታቻው ተጠቅመው ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ተጨማሪ እሴት ለመፍጠር፣ እንዲሁም ለወጣቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅማቸው በጣም በጣም ዝቅተኛ ነው። በዚህ ረገድ በጋራ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ላይ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ለተደራጁ ተቋማት የ“Sub-contracting” ውል በመስጠት ከሥራ ጥራትና አገልግሎት አቅርቦት ጋር ተያይዞ፣ እንዲሁም ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት አንፃር የነበረው ክፍተት እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

በአጠቃላይ፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው “ኢኮኖሚ አብዮት” የክልሉን ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ የማይመልስ፣ ክልላዊ መስተዳደሩ ያለበትን የመልካም አስተዳደር ችግርና አቅም ማነስ የማይቀርፍ እና በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ግቡን አይመታም። ይህ የኢኮኖሚያ አብዮት በስህተት ላይ ስህተት በመደጋገም፣ አንዱን ስህተት በሌላ ስህተት ለማረም መሞከር ነው። ስህተት የሰራ አካል በተመሣሣይ ግንዛቤና እሳቤ ውስጥ ሆኖ የቀድሞ ስህተቱን በሌላ ስህተት ለማረም ጥረት የሚደረግበት ዕቅድ ግቡን ሊመታ አይችልም

አድዎስ “ያ ትውልድ” – ቬሮኒካ መላኩ

 በባእድና በተውሶ ርእዮት ሰክሮ
በ “ቸ ” እና በ “ሸ ” ፊደል ልዩነት አፈሙዝ ተማዞ በሳንጃ ተሞሻልቆ ደም የተፋሰሰው ትውልድ ግማሽ ክፍለ ዘመን እያለፈው ነው ። ህውሃት እና ብአዴን የዛ ትውልድ መሪ ተዋናዮች የነበሩና አሁንም በስልጣን ላይ ቁጭ ብለው አሁን ለደረስንበት አገራዊ ኪሳራ የዳረጉን ናቸው ። አሁንም የአገራችንን የፖለቲካ መዘውር የሚዘውረው ይሄው ትውልድ ነው ።
ይሄን ትውልድ አስገድደን እንኳን መቀየር ባንችል በተፈጥሮ ሂደት በ5 አመታት ውስጥ ጃጅቶ ከእነርእዮቱ መሞቱ አይቀርም። ባይሞት እንኳን የተንኮል መረብ የሚጠነስስበት አእምሮው አክስፓየርድ አድርጎ የአንጎሉ ሶፍትዌር ” No disc ” የሚልበት ደረጃ ስለሚደርስ አሳሳቢ አይሆንም ። እርግጥ ታሪክ የትውልዶች ትዝብት ነውና አሳፋሪ ታሪካቸውን መዝግቦ ያልፋል ።

በህውሃት እና በብአዴን መካከል ያለውን የተተኪ የፖለቲካ ሃይል ከገመገምነው ሰፊ የሆነ ልዩነት አለ ። እዚህ ላይ አንባቢ ልብ እንድልልኝ የምፈልገው ጉዳይ አለ ። እኔን የብአደን ተስፈኛ ለማድረግ ባትሞክሩ ጥሩ ነው ። እኔ የፖለቲካ አሰላለፉን እና መፃኢውን ሁኔታ ለመተንተን የሚሞክር አድርጎ ማሰቡ የተሻለ ነው።

የህውሃትንና የብአዴንን መፃኢ ሁኔታ ከተተኪ ወጣቶች አንፃር ከገመገምነው ህውሃት የተተኪ ድርቀት ያለው ድርጅት ነው። የህውሃት ተተኪ ወጣት ቅጥ ባጣ ዘረፋ እና ገንዘብ ባመጣው ሱስ የተነደፈ ፣ በወሲብና በሃሽሽ ሱስ የተለከፈ የላሸቀ እና በቅንጦት የሚሰቃይ ከመሆኑ አንፃር እንኳን የህውሃትን የበላይነት ሊያስጠብቅ ይቅርና ህውሃትን ድርጅታዊ ህይወት ማስቀጠል ከቻለ የሚደነቅ ነው።
በተቃራኒው የብአዴን ተተኪ ነው የሚባለው ወጣት በአማራ ብሄርተኝነት የተቃጠለ ፣ በአለፉት 25 አመታት በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው በደል የሚያመው ፣ ውስጥ ውስጡን ህውሃትን የሚጠየፍ አድፍጦ ቀን የሚጠብቅ ሃይል ነው።

ህውሃት እና ብአዴን አሁንም የሚዘወሩት አካላቸው በጃጄ ፣አእምሯቸው በላሸቀ ነገር ግን በተንኮልና በሴራ በተካኑት የዛ ትውልድ አባላት ናቸው። አሁን በተጨባጭ ህወሓት እድሜዋን እየቀጠለች ያለችው በነባር የብአዴን አባሎች ነው፡፡ ከአምስት አመታት በኋላ ህውሃት በበረከት ስምኦንና በአድሱ ለገሰ አይነት የጃጁና በአካላዊ ልምሻ በሚሰቃዩ ሰዎች ልትቀጥል አትችልም ። አዲሱ እና አድፍጦ የሚጠባበቀው የአማራ ትውልድ ደሞ እሳት ልሶ እሳት ጎርሶ በአማራነት ስነ ልቡና ተጠምቆ እያደገ ያለ ትውልድ ነው።

ስለ ሃይል አሰላለፉ ይሄን ካልኩ በአማራው በኩል አሳሳቢ ጉዳዮች አሉ ።በወያኔ ርእዮት አለም ተጠምቀው ” አማራ ጠላታችን ነው ” የሚል ሃይማኖት ካላቸው ህዝቦች ጋር አብረን መኖር እንችላለን የሚሉ አማራዎችን ሳይ ይገርመኛል፡፡ በነፈሱ ጎማዎች በ 80 km per hour ለመንዳት እንደመሞከር ያለ ቅዤት እና ራስን ወደ ገደል ለመወርወር እንደ መዘጋጀት ያለ አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታ ነው።
እኛ የኛ አባቶች እና አያቶች ለኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ነፃነት በመሞት ነፃ መሬት አስረክበውናል ብለን ስንናገር እና ለባንዴራችንና ለወገናችን ክብር እንዋደቃለን ስንል እነሱ ትምክተኛ ይሉናል። በነፍጥ አገርና ዳር ድንበርን ስንጠብቅና ጠላትን እያንበረከክን ኢትዮጵያን ስናኮራ ነፍጠኛ ይሉናል።
በብሄር አትከፋፍሉ አትጥበቡ እያልናቸው አልሰማ ብለው ስለብሄራቸው እያወሩ እኛም ስለአማራ ማውራት ስንጀምር መረበሽ ይጀምራሉ።

ለአማራ ከአሁን በኋላ የተለመደው /ኮንቬንሽናል/ አንድነት ከእንግዲህ እንደማይሰራ ተረድተን፤ ከጥገናዊ ለውጥ ወደ ስር ነቀል አገራዊ ለውጥ ቀይረን፤ እኛ ወገንና ዜጋ ስንላቸው፥ እነሱ አማራ ጠላታችን ነው መጥፋት አለበት ብለው የተነሱብንን የነፈሱ የሰሜን ጎማዎች አውልቀን ጥለን፤ የተሻለች አዲስ ኢትዮጵያን በመመስረት ካልቻልን ባለፉት 60 ዓመታት በዚች አገር ላይ ከተፈፀመው ብሔራዊ ብልግና አዙሪት መቼም አንወጣም፡፡

በጥገናዊ የአንድነት አስተሳሰብ ከዚህ ቪሽየስ ሰርክል በፍፁም መውጣት አይቻልም፡፡ ወያኔን እርሱት፤ ወያኔን አሸንፈን ሌላ የተሻለ ኢትዮጵያዊ መንግስት ብንመሰርት እንኳን ከተከዜ ማዶ ያለ የአማራ ጥላቻ እስከ አጥንቱ የዘለቀው ተጋፊ አናሳ ቡድን ጊዜ ጠብቆ ዳግም የሚፈነዳ ሃላፊነት የማይሰማው ታይም-ቦምብ ነው፡፡
እስራኤል ፍልስጤምን ወገኖቼ ናችሁ ብላ ብትዘናጋ ኖሮ በምድረ ከንዓን ላይ እንደ አሁኑ አይነት ቦታ አይኖራትም ነበር፡፡
ከእንግዲህ ካዛክ ለሩሲያ ወገኑ አይደለም፡፡ አንድ ብሄር እምብርቱ እስኪወጠር እየበላ የሚጨፍርባት ሌላው በድህነት የሚሰቃየው አንሶት በጥይት የሚቆላባት የፖለቲካ አሰላለፍ ያለባት አገር የሚፈልግ ካለ የዋህ ነው ።
አማራ እንደሩሲያ ከተፍገመገመበት ዳግም ይነሳል፤ መብቱ ሙሉ በሙሉ የሚከበርበት አዲስ ውብ አገር ኢትዮጵያንም መመስረት እንችላለን።

 

ተያያዥ መረጃ – ተንቀሳቃሽ ምስሉን ከታች ይመልከቱ::

በቆሸ አደጋ የወያኔ መንስኤነት እና የችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሔ!

 

ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 2, 2009ዓ.ም. ምሽት 2 ሰዓት አካባቢ በተለምዶ ቆሸ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ በደረሰ የመሬት መደርመስ አደጋ 16 የሚሆኑ በሥርዓት የተገነቡና ካርታ (ንድፈ ምድር) ያላቸው መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ቦታ ተረክበው መኖሪያ ቤት የመገንባት አቅም የሌላቸው ወገኖች ለማረፊያ የቀለሱት በርካታ የላስቲክ (የተለጥ) ቤቶች ተደርምሰው በመዋጣቸው እውስጣቸው የነበሩ በርካታ ወገኖች ማለቃቸው ይታወሳል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ 113 ወገኖች እንዳለፉ አገዛዙ አስታውቋል፡፡

ይህ ቁጥር ግን “ከተዳፈኑት ውስት በሕይዎት ያለ ወገን ይኖር እንደሆን፣ ካልሆነም አስከሬን አውጥቶ ለመቅበር!” በሚል አደጋው የደረሰባቸው ቤተሰቦች ቆፋሪ ማሳልጦችን (ኤክስካቫተር ማሽኖችን) በግል ተከራይተው እንዲሁም መንግሥት ላከው በተባለው ተመሳሳይ ማሽን (ማሳልጥ) እየተደረገ ባለው ጥረት የተገኘ አኃዝ ነው፡፡

የዘመናችን ጥጋበኞች የሚያትረፈርፉትን ምግብ በጨዋና ኃላፊነት በሚሰማው ሰው ደንብ ንጽሕናው እንደተጠበቀ ለየኔቢጤ ወይም ለድሀ መስጠት ስለማይወዱና ስለማይፈልጉ ይሄንን እህል አጥቶ ስንት ጦም አዳሪ ድሀ ሕዝብ ባለባት ሀገር የሚተርፋቸውን ምግብ ከቆሻሻ ጋር ስለሚጥሉ ይሄንን ከዕኩይና ግፈኛ የዘመናችን ጥጋበኞች ከቆሻሻ ጋር የሚጣልን ምግብ እየተመገቡ በዚያ ቆሻሻ ስፍራ ላይ በእነኛ የላስቲክ (የተለጥ) ቤቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩትንና ተደርምሶ በተዳፈኑበት አካባቢ ግን እነኝህ ወገኖች አቋጣሪ፣ ተቆርቋሪና አሳቢ አግኝተው “በሕይዎት ያለ ካለ፣ ካልሆነም አስከሬናቸውን አውጥቶ በክብር ለማሳረፍ!” በሚል እስከ ትናንት ድረስ ጥረት እየተደረገ አይደለም፡፡ በመሆኑም በዚህ አደጋ ያለፉ ወገኖቻችን አሁን እየተጠቀሰ ካለው ቁጥርም ከእጥፍ በላይ ሊሆን እንደሚችን መገመት ይቻላል፡፡

ለመሆኑ እነኝህ ወገኖቻችን በቦታው ለመኖር ፈጽሞ በማይመቸውና ለጤና አደገኛ በሆነ ቆሻሻ ሥፍራ ላይ ሔደው ለመስፈር ምን አስገደዳቸው? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ዜጎች በሀገራቸው ጤንነታቸውና ደኅንነታቸው ተጠብቆ ሠርቶ የመኖር፣ መጠለያ የማግኘትና የመሳሰሉት መሠረታዊ ፍላጎታቸው ተሟልቶላቸው የመኖር የማይጣስ የማይገሰስ ሙሉ መብት አላቸው፡፡ የየትኛውም ሀገር ሕገመንግሥት ይሄንን ያረጋግጣል፡፡ ይህ መብት በየትኛውም ሁኔታ ሊጣስ ሊገሰስ ሊገፈፍ የማይችል ሰብአዊ መብት ጭምርም ነው፡፡ መንግሥት ነኝ የሚል አካል ይሄንን የማሟላት ግዴት አለበት፡፡

ልብ በሉ መልካም ፈቃድ ሳይሆን ግዴታ ነው ያለበት፡፡ በምንም መልኩ ይሄንን መሠረታዊ የዜጎች መብት ሊገፍ፣ ሊነፍግ አይችልም፡፡ ያለውን መሬት ለዜጎች አብቃቅቶ የማከፋፈሉን ፍትሐዊ ሥራ መሥራትና ዜጎችን የሀገራቸው ተጠቃሚ ማድረግ ነው ግዴታውና ኃላፊነቱ፡፡ ምክንያቱም በሕዝብ ጥቅሞችና ጉዳዮች ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ የመወሰን ሥልጣንና ኃላፊነት ያለው ሕዝብ እንጅ መንግሥት ስላልሆነ፡፡ መንግሥት የሕዝብን ውክልና ይዞ የሕዝብን ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ማስፈጸም ብቻ ስለሆነ ተግባሩ፡፡ ለሀገር ኢኮኖሚ (ምጣኔ ሀብት) እድገት ከመሬት ሽያጭ ከሚገኝ መጠነኛ ገቢ ይልቅ ዜጎች የመሬት ባለቤት ሆነው መሬቱ ላይ የሚፈጥሩት ሀብት ነው ሀገርን ሊለውጥ ሊያበለጽግ የሚችለው፡፡

ያደጉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየን ይሄንን ነው፡፡ ቁልፉ አስተሳሰብ ይሄ ከሆነ ሊሠራ የሚገባው ሥራ ዜጎችን በሰፊው የመሬት ባለቤት ማድረጉ ነው እንጅ የመሬት ባለቤትነትን መብት ማሳጣት አይደለም፡፡ ይህ ከተደረገ ግን ውሳኔው ሥልጣን የያዘን አካል ጥቅም የሚያስከብር ቡድናዊ ውሳኔ እንጅ የሀገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሕዝባዊ ውሳኔ አይሆንም፡፡

ምን ያህሎቻችን ከላይ የጠቀስኩትን መሠረታዊ መብት እንደምናውቅና ይህን መብታችንንም ማስከበር፣ ማስጠበቅ እንዳለብን እንደምንገነዘብ አላውቅም፡፡ እንደማየው ሕዝቡ ይሄንን መሠረታዊ የዜጎችን መብት የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ መንግሥት ነኝ ከሚለው አካል ችሮታን ሲጠብቅ እንጅ የመንግሥት ግዴታው እንደሆነ አውቆ መብቱ እንዲጠበቅለት ሲጠይቅ ብሎም ሲያስገድድ አላይምና፡፡ መንግሥት ለባለሀብቶች በሽያጭ የቤት መሥሪያ መሬትና መሠረተ ልማት ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ከ90 ከመቶ በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁጥር ለምንይዘው ቤት የመሥራት አቅም ለሌለን ድሀ እና የድሀ ድሀ ዜጎች ጭምር መጠለያ የማቅረብ ግዴታም አለበት፡፡ ይሄንን እናውቃለን ወይ?

ወያኔ መንግሥት ነኝ እንደማለቱ ይሄንን ግዴታውን የመወጣት ግዴታ ነበረበት፡፡ ወያኔ እንኳንና የዜጎችን መብትና የእሱንም ግዴታ በማክበር ቤት የመገንባት አቅም ላላቸው ዜጎች መሬት በመስጠት፣ ቤት የመገንባት አቅም ለሌላቸው ዜጎች ደግሞ የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ከአነስተኛ እስከ ከፍ ያለ የኪራይ ዋጋ የሚጠይቁ የኪራይ ቤቶችን ገንብቶ በማቅረብ ዜጎች ቤት እንዲኖራቸው በማድረግ የዜጎችን መብትና ጥቅም ሊጠብቅ ሊያከብር ግዴታውንና ኃላፊነቱንም ሊወጣ ይቅርና ይህ በመንግሥት ስም ራሱን ያስቀመጠው የወንበዴ ቡድን ከከተማ እስከገጠር አስቀድሞ የመሬት ይዞታ የነበራቸውን ወገኖች ሳይቀር መሬታቸውን እየነጠቀ ለባዕዳንና ለባለሀብቶች በመቸብቸብ ዜጎች በዜግነታቸው ከሀገራቸው ሊያገኙት የሚገባቸውን ጥቅምና መብት አሳጥቷል፣ ነጥቋል፣ ገፏል፡፡ በዚህ ዝርፊያውም
እራሱን በከፍተኛ ደረጃ በማድለብ ላይ ይገኛል፣ መሬትን የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ዋነኛ መጠቀሚያ መሣሪያው አድርጎ በመጠቀምም የግፍ አገዛዙን ለማራዘም ጥረት እያደረገበት ይገኛል፡፡

እነኝህ ወገኖቻችን ለኑሮ የማይስማማ፣ ለጤና አደገኛ በሆነው ቆሻሻ ስፍራ ላይ ሔደው ለመሥፈር የተገደዱት ማንም ሊገስሰው፣ ሊሽረው የማይችል በዜግነታቸው በሀገራቸው መጠለያ አግኝተው ጤናቸውና ደኅንነታቸው ተጠብቆ የመኖር መብት እንዳላቸው ተረድተው በራሳቸው ወጪ አንድ ጥግ ላይ ጎጆ ቢጤ ቀልሰው ለመኖር ሲሞክሩ “የጨረቃ ቤት ነው፣ ሕገወጥ ሰፋሪዎች ናቹህ!” እያለ በሌለ አቅማቸው የቀለሷቸውን ጎጆዎች እያፈራረሰ መድረሻ ቢያሳጣቸው ነው “ይህ ስፍራ ቆሻሻ ነውና አይፈለግም ይሆናል!” ብለው እዚያ ቆሻሻ ላይ ደሳሳ ጆጎ እየቀለሱ፣ የላስቲክ (የተለጥ) ቤት እየወጠሩ ለመስፈር የተገደዱት፡፡

የደርግ መንግሥት ይሄንን የዜጎችን መሠረታዊ መብትና የመንግሥትነትን ግዴታ በመገንዘብ ይመስላል የመሬት ላራሹንና ትርፍ የከተማ ቤትን የመውረስ አዋጆችን በማወጅ መሬት ላልነበረው ዜጋ የመሬት ባለቤት አድርጓል፣ ቤት የመሥራት አቅም ላላቸው የከተማ ነዋሪዎች ለካርታ (ንድፈ ምድር) እና ለተመሳሳይ ጉዳዮች አነስተኛ ወጪ በማስከፈል በነጻ ቤት የመገንቢያ መሬት ለዜጎች ሲያቀርብ ነበር፣ ቤት የመገንባት አቅም ለሌላቸው ወገኖች ደግሞ እንደየአቅሙ ከሃምሳ ሳንቲም ጀምሮ በጣም አነስተኛ ኪራይ የሚከፈልባቸውን የኪራይ ቤቶችን ገንብቶ እንዲሁም በአዋጅ የተወረሱ ቤቶችን በማቅረብ የዜጎችን መብትና የመንግሥትነቱን ግዴታ ለማክበር፣ ለመጠበቅና ለመወጣት ጥረት ያደርግ ነበር፡፡
ወያኔ መንግሥት ነኝ ካለ ይሄንን የደርግን ፈለግ መከተል ሲኖርበት ያልተከተለው “የሚከተለው ርዕዮተዓለም ከደርግ የተለየ ስለሆነ ነው!” እንዳንል የሚከተለው ርዕዮተዓለም ከደርግ የሚለይ አይደለም አንድ ነው፡፡ ወያኔ የሚከተለው የኢኮኖሚ (የምጣኔ ሀብት) ሥርዓት ነጻ (ሊበራል) ቢሆን ኖሮ ከገጠር እስከ ከተማ መሬትን ከዜጎች እየነጠቀ ለባለሃብቶች መስጠቱ ባልገረመን ነበር፡፡

ሙቱ የወያኔው መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ይሄንና ተጓዳኝ ነገሮችን በተመለከተ በአንድ ወቅት ላይ ተጠይቀው ሲመልሱ ያለአንዳች ሐፍረትና የተጠያቂነት ስሜት ነበረ በብዙኃን መገናኛ “ከተማ ለቆ መውጣት ነው!” ብለው በመናገር አገዛዛቸው የአፓርታይድ (የመድሎ) ወይም ለባለሀብቶች ብቻ የቆመ አገዛዝ መሆኑን ያረጋገጡት፡፡

ሰሞኑን ይሄ አሁን የደረሰብንን አደጋ በተመለከተ በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛዎች አንድ የታዘብኩትና በጣም ያናደደኝም እንቅስቃሴ ነበር “በአደጋው ላለፉ ወገኖች ክብር ሲባል ብሔራዊ የሐዘን ቀን ይታወጅልን!” ብሎ አገዛዙን የሚጠይቅ እንቅስቃሴ፡፡ በጥያቄያቸው መሠረትም ብሔራዊ የሐዘን ቀኑ ሲታወጅ ፈንጠዝያ አይሉት ምን ተመልክቻለሁ፡፡ በእውነት በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ በቃ ይህችን ታክል ነው የምናስበው? ይህ አደጋና መንስኤው እኮ በሌሎች ሀገራት ቢሆን ኖሮ ሀገር የሚንጥ መንግሥት የሚገለባብጥ ዐመፅ ያስነሣ ነበረ እኮ ጃል! ይሄን አጋጣሚ ተጠቅመን ሌላው ቢቀር ዜጎችን ለዚህ አደጋ የዳረገው ኢፍትሐዊ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓቱ እንዲቀየር መንቀሳቀስ አልነበረብንም ወይ? ቆይ እንጅ የሐዘን ቀኑ ስለታወጀ ወያኔ ማረፊያ መድረሻ አሳጥቷቸው ቆሻሻ ላይ ሔደው ለመስፈር የተገደዱትንና ለዚህ አደጋ የተዳረጉትን ወገኖች አከበረ ወይም ክብር ሰጣቸው ማለት ነው? ይሄንን ያህል ወገን በራሱ በግፍ አስተዳደሩ ምክንያት ለሕልፈት ተዳርጎ እያለ ጉዳዩን ከመጤፍ ሳይቆጥር ብሔራዊ የሐዘን ቀን ሳያውጅ የማለፉን አሳዛኝና አስገራሚ ሁኔታ ለቀጣይ ትውልድ ይታወቅ ዘንድ ለታሪክ ትቶ ማለፍ ሲገባ ያለ ሐሳቡ ያለፍላጎቱ አሳስቦና ጎትጉቶ የሐዘን ቀን ማሳወጁ ግፉ ለደረሰባቸው ወገኖችና ላለው ቀሪ ዜጋ የሚጠቅመው ምንድን ነው? ይህ አደጋ በዚህ ስፍራ ላይ ሲከሰት ይሄኛው ለስድስተኛ ጊዜ የተከሰተ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ወያኔ ግን ኃላፊነት ተሰምቶት “ዜጎችን ከአደጋ የመጠበቅ ግዴታ አለብኝ!” ብሎ አንዳች ያደረገው ነገር ባለመኖሩ ይሄው የከፋው አደጋ ሊከሰትና በርካታ ወገኖቻችንን ልናጣ ቻልን፡፡ እና ታዲያ ይሄ ሁሉ እየሆነ እየታየ ልንንቀሳቀስ ይገባን የነበረው የሐዘን ቀን መጠየቅ ነው ወይ?

ወያኔ የወገኖችን የዜጎችን መሠረታዊ የዜግነትና ሰብአዊ መብታቸውን ገፎ መድረሻ ማሳጣቱን እስከቀጠለ ጊዜ ድረስ ነገም ተቸግረው እዚህ የቆሻሻ ቦታ የሚሠፍሩና ለተመሳሳይ አደጋ የሚዳረጉ ወገኖች መኖራቸው ይቀራል ወይ? ካለስ የአደጋው መንስኤ ሁላችንም ላይ ያነጣጠረ እንደመሆኑና እንደዜጋም አፋጣኝ መፍትሔ መፈለግ የለብንም ወይ? ወገን ሆይ! ሀገርህን እኮ ተነጥቀህ በገዛ ሀገርህ ባይተዋር፣ ስደተኛ፣ ተጉላላይ፣ ተንጓላይ፣ ተቅበዝባዥ ሆነህ እኮነው ያለኸው! የአንድ ሀገር ሕዝብ ሀገሩን ነጥቆ ቀምቶ በገዛ ሀገሩ የመኖር ዋስትናውን፣ የዜግነት መብቱንና ጥቅሙን አሳጥቶ ዕለት ዕለት እያሳደደ፣ እያፈናቀለ ሀገሩን ለባዕዳንና ለባለሃብቶች እየቸበቸበለት ያለውን አንባገነን አገዛዝ በዝምታ መመልከት አለበት ወይ?

ዜጎች በዜግነታቸው መሠረታዊ መብታቸውና ጥቅማቸው ተከብሮላቸው በገዛ ሀገራቸው ተረጋግተው መኖር ካልቻሉ ዜጎች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ጥቅም፣ ሀገሬ ብሎ ለማለት የሚያስችላቸው መብት ሌላ ምን አለና? ነገ ጠዋት በዚህች ሀገር ላይ ጥቃት ቢቃጣ “ሀገሬ!” ብሎ ተነሥቶ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ሉዓላዊነቷን የሚያስከብረው ማን ነው? መሬታችን ተነጥቆ የተሰጣቸው ባዕዳን ባለሀብቶች ናቸው እንዴ? ወይስ ጥቂት የናጠጡ ባለሀብት ዜጎቻችን? ይሄ ወያኔ መድረሻ ያሳጣው ድሀ ሕዝብ እና መሬቱ እየተነጠቀ ለባዕዳን እየተሰጠበት ያለው ገበሬ አይደለም ወይ? እንዲህ የደም ዋጋ ከፍሎ ያቆያትን እና ነገ አንድ ነገር ቢፈጠርም “ሆ!” ብሎ ተነሥቶ መራር መሥዋዕትነትን የሚከፍልላትን ዜጋ በምን ሒሳብ፣ በየትኛው መሥፈርት ነው ከገዛ ሀገሩ ሊያገኘው የሚገባው ጥቅምና መብት ተነፍጎት
ባይተዋር፣ ተሳዳጅና የበይ ተመልካች ሊደረግ የሚገባው? እኮ በየትኛው ፍትሐዊ አሠራር? በወያኔ ዓይነቱ ኢፍትሐዊ የአፓርታይድ (የመድሎ) አገዛዝ ካልሆነ በስተቀር!

እናም የዋሁ ወገኔ ሆይ! የችግሩ መፍትሔ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ማሳወጁ ሳይሆን ስንት ዋጋ ከፍለህ ያቆየሀትንና ወደፊትም የምትከፍልላትን ሀገርህን ነጥቆ የባዕዳንና የባለሃብቶች ብቻ ያደረገብህን፣ በገዛ ሀገርህ ተሳዳጅ፣ ተፈናቃይ፣ የበይ ተመልካች ያደረገህን አንባገነን የወንበዴ አገዛዝ ማስወገድ ነውና በየጊዜው በአገዛዙ የግፍ አስተዳደር መንስኤነት አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር ማላዘኑን ትተህ የችግሮችህ ሁሉ ምንጭ የሆነውን ወያኔን ለመገርሰስ ቆርጠህ ተነሥ! ሳትውል ሳታድር ክንድህን በግፈኛው በጠንቀኛው አገዛዝ በወያኔ ላይ አንሣ! ይህን ማድረግ ካልቻልክ ግን ነገም ያንተ እጣ ከእነኚህ አደጋው ከደረሰባቸው ወገኖች የተለየ እንደማይሆን እወቀው!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

ህዝባችን የሚሻው መሰረታዊ ለውጥን እንጂ ቀጣይ ወታደራዊ አገዛዝንና ባዶ ተስፋን  አይደለም – ሽንጎ

ሕወሀት/ ኢህአዴግ እንደተሽመደመደና መግዛት አንዳቃተው በተዘዋዋሪ አመነ።፤ይህ ሁኔታ ሰፊ የህዝብ መነሳሳትን ይቀስቅሳል ብሎ የፈራው ሕወሀት/ኢህአዴግ ከስድስት ወራት በፊት የጀመረውን ወታደራዊ አገዛዝ በመላ ኢትዮጵያ ይቀጥላል ሲል በጠቅላይ  ሚኒስቴር ሐይለማርም ደሳለኝ በኩል  በዛሬው እለት ለ”ፓርላማ” በቀረበው  ሪፖርት አረጋግጧል። አስቂኝ የሆነው ይህ ንግግር፣ 82% የኢትዮጵያ ህዝብ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲቀጥል ይፈልጋል ይላል። በአማራና ኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (65% ኢትዮጵያውያን) ስርአቱን ሙሉ በሙሉ እየተቃወሙት እንደሆነ እየታወቀ 82%  ድጋፍ ከየት እንደሚመጣ የህወሀት/አህአዴግ በለስልጣኖች ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ እነርሱ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሉት የህወሀት/ ኢህአዴግን አባላት ብቻ ከሆነ ሌላ ነገር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ንግግራቸው በተለይ ኢኮኖሚውንና እድገትን በተመለከተ  እጅግ የተምታታና መጨበጫም የሌለው ነው፣ ባንድ  በኩል የኢትዮጵያን  ህዝብ ተጨባጭነት የሌለው “እናድጋለን” የሚል ባዶ  ተስፋ ሊመግቡ የሞከሩ ሲሆን  በሌላ በኩል ግን በተጨባጭ የእርሻ ምርት እንደቀነሰ፣ የውጭ ንግድ ገቢ ለሶስት ተከታታይ አመታት እንዳሽቆለቆለ፣ የዋጋ ግሽበት እንዳሻቀበ ከውጭ የሚገኝ እርዳታ እንደወደቀ፣የግብርና ምርት ኤክስፖርት እንደደቀቀ ፤ ድርቅ በየቦታው እንደተስፋፋ፣የሀገሪቱ እዳ እየጨመረ እንደሆነ ስርአቱ ከ26 አመት ስልጣን በሓላ ሀገሪቱን በምግብ ራሷን ማስቻል እንዳልቻለ አምነዋል። ባጠቃላይ ሚዛን ሲታይ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ስርአቱን እድገት ሳይሆን ውድቀት አሽመድምዶ እንደያዘው አምነዋል።

የፖለቲካ ድርድርን በሚመለከት የተናገሩትም እንዲሁ እጅግ አሳዛኝ ፤ ሀገራዊ ሀላፊነት የጎደለው  ነው፡ “ማንም አስገድዶን አይደለም ለድርድር የቀረብነው” “ተጽእኖ ሲደረግብን በፍጹም ፍንክች አንልም” በማለት በግልጽ ቋንቋ ይህ መንግስት እጅግ ችክ ያለ ደረቅ አንደሆነ፣ እና ከሁኔታወች ጋር መጓዝ እንደማይችል፣ ለእውነተኛ ለውጥ የተዘጋጀ እንዳልሆነ ሰጥቶ መቀበልን ሳይሆን በራሱ መስመር ብቻ መጓዝን እንደሚገፋ አረጋግጠዋል። የተጀመረው ድርድር እሩቅ እደማይሄድም የጥርጣሬ ጥላ አጥልተውበታል። ይህ ታዲያ ሀላፊነት የጎደለው ለፍጥጫና ለቀጣይ ግጭት የሚጋብዝ እንጂ ለሰላም በር ከፋች አይደለም፡፡

ያው እንደተለመደው አሁንም ፖለቲካዊ ተቃውሞን በወታደራዊ ሀይል ለመጨፍለቅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደሚያራዝሙ ከመግለጽ ውጭ፤ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በዚህ ንግግራቸው በሀገራችን የተከሰቱትን ዋና ዋና የፖለቲካ ግጭቶች  ለመቅረፍ ምን እንደሚያደርጉ ያቀረቡት ምንም ተጨባጭ የፖለቲካ መፍትሄ የለም።

በራሳቸው ጭንቅ የተወጠሩት ጥቅላይ ሚኒስቴሩና  ንግግራቸው ሁሉ ያተኮረው በድርኢጅታቸው የውስጥ ፡ተሀድሶ” ላይ ነው። ይህ አይነቱ ንግግር ለፓርቲያቸው የውስጥ ስበሰባ እንጂ ለህዝብ የሚቀርብ አይደለም፣፡ ምክንያቱም  ከ 26 አመት ስልጣን በሓላ የኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ህወሀት/ኢህአዴግ መታደስ ቅንጣት ያክል ስሜት የለውም። የሚፈልገው ግፈኛውንና ከፋፋዩን የኢህአዴግ /ህወሀትን ስርአት በማስወገድ የስርአት ለውጥን እውን ማድረግ  ነውና።

ባጠቃላይ ሙሉውን ንግግር አንገታቸውን ደፍተው የፈጸሙት  ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከቃላት ይልቅ በድምጻቸውና  በሰውነታቸው ሁኔታ  (ቦዲ ላንጉጅ) ምን ያክል የተጨነቁና ተስፋም የቆረጡ  አንደሆነ ግልጽ አድርገዋል።

እጅግ ገላጭ የሆነው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ተሰባሳቢዎቹ “የፓርላማ ተወካዮች”  ግማሾቹ ሲያንቀላፉ የታዩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ “ምን ማለቱ ነው” የሚል በሚመስል ሁኔታ እርስ በርስ ሲንሾካሾኩ ተስተውሏል።

ከዚህ ውጭ ግን የሚገርመው በሙሉ ንግግሩ መሀል የተለመደው ረጂም ተከታታይ ጭብጨባ እንኳ አለመደመጡ ጠቅላላ ታዳሚዎቹ ምን ያክል በጭንቅ ላይ እንደሆኑ አሳብቆባቸዋል።

አዎ ስርአቱ የሚገኝበት ሁኔታ በውነትም የሚያሰጨንቅ ነው። የእርሻ ምርት  ከወደቀ፣ ኑሮ ውድነት ከጨመረ፣ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ካልተቻለ፣ የውጭ እርዳታ ከቀነሰ፣ ድርቅ ከተስፋፋ ፣ ኮንትሮባንድ ንግድ ሀገሪቱን ካጥለቀለቀ፤ ምርታቸውን የሚገዛ እየቀነሰ ከሄደ   የፖለቲካ ግጭቱ ከቀጠለ ህዝቡ ስቃዩ ይጨምራል ማለት  ነው፤ ህዝብ ይራባል  ማለት ነው ። ህዝብ የመብት ማጣቱ ይጨምራል ማለት ነው። ታዲያ ባለፈው አመት በኢትዮጵያ እንዲሁም  ከጥቂት አመታት በፊት  በግብጽ ሊቢያና የመን እንዳየነው፤ የተከፋ ህዝብ፣ የተራበ ህዝብ መሪዎቹን ይበላል። ይህ ማንም የማይገታው የተፈጥሮ ህግ ነው።

እኛ የምንለው  መፍትሄው መቆዘምና መጨነቅ ወይም እውነታውን መካድ፣ በጨለማ ውስጥ መደናበርና  ባዶ ተስፋ ለመመገብ መሞከር ሳይሆን ሀገራችንንና ህዝባችንን ገደል እየጨመረ ያለውን የህወሀት/ኢህአዴግ ፖሊሲ አሽቀንጥሮ መጣል ነው። በሙሉ ቅንነት ለሁሉም የሚጠቅመውን ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሄራዊ መግባባት እና ብሄራዊ እርቅን ተግባራዊ አሁኑኑ ማድረግ ነው።

ለዚህም

  • በተለያየ ሰበብ አስባብ  ለእስር የተዳረጉትን የፖለቲካ እስረኞች ሁሉ በተለይም ደግሞ አንደ አንዱአለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ፤ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናና ኮሎኔል ደመቀን የመሳሰሉ የፖለቲካ መሪዎች፣ እንደ እስክንድር ነጋና ተመስገን ደሳለኝ፣ የመሳሰሉት ጋዜጠኞች  ወዘተ አሁኑኑ እንዲፈቱ  ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ይሆናል። ባጠቃላይ የህሊናና የፖለቲካ እሥረኞች ሁሉ አላንዳች ቅድመ ሁኔታ  ከእሥር ነጻ ሊሆኑ ይገባል።
  • መሰረታዊ የሆኑ የዴሞክራሲ መታፈንን፣ የሰብአዊ መብት መገፈፍን፣ የህግ የበላይነት መጥፋትን የመሰሉት ጉዳዮች በግልጽ ውይይት ተደርጎባቸው እነዚህን እውነታዎች ለ26 አመታት ያስቀጠለው ሁኔታ የሚወገድበትን መንገድ በጋራ መሻት የግድ ይላል፡። በግፍ የተጎዱ ሁሉ ሊካሱ የሚችሉበትን ሁኔታም ማመቻቸት ተገቢ ነው።
  • መሰረታዊ መብትን የሚገድቡና የሚጥሱ ህግጋቶችን ለምሳሌ የሲሺክ ማህበራትን፣ የፖለቲካና  የመብት ታጋይ ድርጅቶችን እንዲሁም መስል  እንቅስቃሴዎችን የሚያኮላሸውን ህግ፣ የጸረ ሽብርተኝነት ህግ፤ የሚዲያ ሕግ ወዘተ መሰረዝ አስፈላጊ ነው። ህገ መንግስቱም የሀገራችንን ህዝብ ፍላጎት በሚያንጸባርቅ መልኩ የሚሻሻልበትን ሁኔታ መመርመርና መተግበር ይኖርበታል።
  • በቅርቡ በአማራ በኦሮሞና ሌሎችም ክልሎች የተነሱትን የብዙ ወገኖቻችን ህይወት የተገበረባቸው መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎች በጥሞናና በሀገራዊ ሀላፊነት መመርመር መወያየትና መፍትሄ መፈለግን የግድ ይላል፡ በነዚህ አካባቢዎች የሚካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻም ባሰቸኳይ መስቆም የግድ ነው፡
  • በህዝባችን ላይ የተጫነውን የጭንቅ ቀንበር ማስወገድ አስፈላጊ ነው። ለዚህም በመላ ሀገሪቱ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና ኮማንድ ፖስት ባሰቸኳይ ማንሳት ያስፈልጋል። ማንም ኢትዮጵያዊ  አሁንም ከየሰፈሩ እየተጎተተ የማይታሰር በወታደርና ደህንነት ሰራተኞች የማይደበደብ፣ እንደፈለጉ የማያስሩት እንደሚሆን ከቃላት ባለፈ በተጨባጭ ማሳየት አስፈላጊም አጣዳፊም ሆኖ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን አለበት።
  • በሀገሪቱ መሰረታዊ የፍትህ ሥርአት፣ የምርጫ ቦርድ፣ የምርጫ ሂደት፣ የሰራዊት እዝ፤ የደህንነት ቢሮ፤ ወዘተ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነትና የፓርቲ ተቀጽላነት ወጥተው መላ ህዝብን ሊያገለግሉ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት ማካሄድና መሰረታዊ የእርምት እርምጃም መወሰድ ይኖርበታል።
  • የጋራ ችግሮቻችንን ከስር መሰረቱ ለመፍታትና ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ፣ አግላይነትን አስወግዶ በሀገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉ የሚሳተፉበት ሂደትን ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል። ብሄራዊ መግባባትና እርቅ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ስብስብ ወይም ድርጅት የፈለገውን ወስኖ በሌላው ላይ የሚጭነው ወይም “ከፈለጋችሁ ተቀበሉ ካልፈለጋችሁ ተውት “ የሚባል ሳይሆን፣ ሁሉም ወገን የሂደቱም ሆነ የውጤቱ ባለቤት ሊሆኑ የሚችሉበት መሆን ይኖርበታል። ያሁኑ አካሄድም ገና ከጅምሩ ሁሉንም ባለድርሻዎች ያሳተፈ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።

ሽንጎ ደግሞ ደጋግሞ እንደገለጸው ፍላጎታችን በሀገራችን ውስጥ ህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ እንዲሁም አንድነት፣ እኩልነት፣ የህግ የበላይነትና ዴሞክራሲያዊ መብትን ተግባራዊ ማድረግ ሲሆን፣ ይህን በማድረግም የአመጽ፣ የጦርነት፣ የአሳሪና ታሳሪ አዙሪት፣ ቂም በቀልና ቁርሾ  እንዲያከትም ማድረግ ነው።

በ26 አመት ተሞክሮ እንደማይሰራ የተረጋጋጠን አካሄድ ለማስቀጠል መሞከር ትርፉ ይበልጥ ግጭትንና ሁከትን መጋበዝ ብቻ ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

ዶ/ር መራራ ጉዲና እና እስክንድር ችሎት ላይ ተናገሩ – ነገረ ኢትዮጵያ

”ህዝባዊ እንቢተኝነት በየትኛውም ሀገር እንደ ሽብር ተቆጥሮ አየውቅም” ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

”መንግስት ባልታጠቁ ዜጎች ላይ ያልተመጣጠነ የሀይል እርምጃ ሲውስድ ዜጎች ሳይታጠቁ እራሳቸውን ለመከላከል የወሰዱት እርምጃ ሽብር አይደለም” ዶ/ር መረራ ጉዲና
(በሰማያዊ ብሄራዊ ሸንጎ የህዝብ ግንኙነት ንዑስ ኮሚቴ)

ችሎቱ ለዛሬ የተቀጠረው አቶ ዬናታን ተስፋዬ በቀረበበት የሽብር ክስ ቀሪ መከላከያ ምስክሮችን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና ዶ/ር መረራ ጉዲናን ለመስማት ሲሆን ሁለቱም የመከላከያ ምስክሮች ቅርበው የስላማዊ ትግል መርህዎችና አቶ ዬናታን ተስፋዬ በተከሰሰበት በኦሮምያ የተነሳውን ህዝባዊ ትቃውሞ በተመለከተ ቃላቸውን ሰጠዋል። በመጀመርያ ምስክርነታቸውን የሰጡት ዶ/ር መረራ ጉዲና ህዳር 2008 ዓ/ም በኦሮምያ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ በተመለከተ ለችሎቱ ሲያስረዱ ህዝቡ ወደ አደባባይ የወጣው በፍትህና በመልካም አስተዳደር እጦት ነው። ህዝቡ ለረጅም አመታት በግፍ ላይ የነበረና የአካባቢው አስተዳዳሪዎች በአግባቡ ስላላስተዳደሯቸው የተነሳ ተቃውሞ ነው። ህዝቡ ባዶ እጁን ለተቃውሞ መውጣቱንና የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ያልተመጣጠነ እርምጃ መውሰዳቸው ሁኔታውን ያባባሰው ይህ የሀይል እርምጃ መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም እኔ ሶስት መንግስታት አይቻለሁ፤ የሚነሱባቸው ጥያቄዎች ሰላማዊና በህገመንግስቱ የተፈቀዱ ናቸው። ኢትዬጵያ ውስጥ ግን የህዝብን ጥያቄ ከሽብርተኝነት ጋር ማያያዝ አለ። ነገር ግን የተጠቀ አመፅ አልነበረም። የታጠቀ ሀይል እንኳ መንግስትን ለመጣል ቢሞክር፤ ሰላማዊ ዜጎች እስካልነካ ድረስ ሽብርተኝነት አይደለም በማለት ለችሎቱ አስረድተዋል።

ከዚህ እንቅስቃሴ ጀርባ ማን አለ? ተብለው በአቶ ዬናታን ጠበቃ የተጠየቁ ሲሆን አለን የሚሉ ድርጅቶች እንዳሉና እውነታው ግን ገንፍሎ የወጣ የህዝብ ብሶት መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል።
አምስተኛ የመከላከያ ምስክር ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በሰላማዊ ትግል መርሆች ላይ ማብራርያ የሰጠ ሲሆን ሰላማዊ ትግል ከዲሞክራሲያዊ ስርዓት ጋር የሚደረግ ትግልና ከአምባገነን ስርዓት ጋር የሚደረግ ትግል እንዳለ ለችሎቱ አስረድተዋል። በዲሞክራሲያዊ ስርዓት በምርጫ የሚደረግ ሲሆን፤ እንደ ኢትዬጵያ አይነት በአምባገነን ስርዓት ባለበት የሚደረግ ትግል ደግሞ ህዝባዊ እምቢተኝነትን (civil disobedienc) ያጠቃልላል።

የትጥቅ ትግል የራሱ የሆነ አለም አቀፍ ህግ ያለው መሆኑንና ሽብር ደግሞ ምንም አይነት የጦርነት ህግ የሌለው በተመቸው መንገድ ማንኛውንም ተቋማትና ህዝብን ኢላማ ያደረገ ነው። ህዝባዊ እምቢተኝነት(civil disobedience) የዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር የሚደረግ ትግል እንደሆነና ያልተፈቀዱ ህዝባዊ ስብሰባዎችና ሰላማዊ ሰልፎች ማድረግን እንዳሚያካትት የሲቪል መብቶች ተሟጋች አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ህንድን ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ለማውጣት የታገሉት ማህተመ ጋንዲ በይፋ ህዝባቸውን ሲያስተምሩ እንደነበር በምሳሌነት ጠቅሰዋል። የአቶ ዬናታን ድርጊትም ሀሳብን በነፃነት መግለፅ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ በህዝባዊ እምቢተኝነት የትግል ስልት እንደሚካተት ለችሎቱ አስረድተዋል። ህዝባዊ እንቢተኝነት በየትኛውም ሀገር እንደ ሽብር ተቆጥሮ አያውቅም ብለዋል።

ችሎቱም የመከላከያ ምስክሮችን ከአዳመጠ በሁዋላ ተጨማሪ የመከላከያ የሰነድ ማስረጃዎችን ለመቀበል ለመጋቢት 27/2009 ዓ/ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

የቆሼው እልቂት ድንገተኛ አደጋ ወይስ የመንግሥት ሴራ? – ዘመድኩን በቀለ | ሊያነቡት የሚገባ አዳዲስ መረጃዎች

 

 

 

በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የከተማዋ የአዲስ አበባችንን ቆሻሻ በዚያ ስፍራ መጣል ከተጀመረ 50 ዓመታት እንዳለፉት መረጃዎች ያመለክታሉ ። እንደ ሰለጠኑት ዓለማት ቆሻሻን መድፋትና በአንድ ቦታ መከመር እንጂ ቆሻሻን ሰብስቦ ለልማት ለማዋል በየግዜው ሀገሪቱን የመግዛት ዕድሉን ባገኙት ገዢዎችን በኩል ፈቃደኝነቱም ሆነ ተነሳሽነቱ እንደሌለ ይታወቃል ።

የሆነው ሆኖ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ነው የተባለ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ስፍራ ዛሬ ከህዝቡ መብዛትና ከከተማዋ መስፋፋት ጋር ተዳምሮ የቆሻሻ መጣያ ስፍራው የከተማዋ እንብርት የሆነ ሥፍራ ላይ ራሱን እንዲያገኝ ጊዜ ግድ ብሎታል ።

ኢህአዴግ ከ97 ቱ ምርጫ በኋላ በከተማዋ ነዋሪዎች የደረሰበትን ክፉኛ የሆነ ሽንፈት ለመቀልበስና የሕዝቡንም ልብ ወደ ቀልቡ ለመመለስ ሲል ከ15 ዓመት እንቅልፍ በኋላ በሀገራችን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የከተማ ልማት ፖሊሲን በመቅረጽ የእውር ድንብሩን ሥራ መጀመሩን መጀመሩን እናውቃለን ። ኮንዲሚንየም ፣ ባቡር የመሳሰሉትን ልማቶች ህዝቡ አገዛዙን እጁን በመጠምዘዝ በግድ ያመጣው መሆኑም ይታወቃል.? ወዘተ

የሆነው ሆኖ በቆሼ ከከተማዋ ነዋሪ ብዛት የተነሳ በሥፍራው የሚጣለው ቆሻሻ ወደ ተራራነት ከመቀየሩም ሌላ ከቆሻሻው የሚወጣው መጥፎ ጠረን ፤ እንኳን በዚያ አካባቢ ሊያስኖር ይቅርና በአካባቢው በሚገኘው የቀለበት መንገድ ላይ በፍጥነት እያሽከረከሩም ሊያልፉ ቢሞክሩ ሽታው ጥርቅም ብሎ በተዘጋ ኘስኮት ገብቶ ለበሽታ የሚዳርግ መጥፎ ጠረን መማጎት እንደሁ የማይቀርበት ስፍራም ነው ። ቆሼ ።

መንግሥት የቆሻሻ መጣያ ሥፍራውን ከአዲስ አበባ ክልል በማውጣት ወደ ኦሮምያ ክልል ወስዶ ቦታውን በማጽዳት ልማት ላይ ማዋል እንደሚፈልግና በዚህም በኩል ሰፊ የሆነ እንቅስቃሴ መጀመሩንም በሚድያዎቹ አማካኝነት ከነገረንም ቆይቷል ። በዚህም መሠረት በሥፍራው ላይ የባዮ ቴክኖሎጂ ፋብሪካ በማቋቋም እንዲያውም ከቆሻሻው በሚወጣ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ጭምር ቅድመ ዝግጅቱን ጨርሶ ወደ ትግበራ ለመግባት ይፋ አድርጎልን ነበር ።በዚህ በኩል የተከበሩ Eshetu Homa Keno መረጃዎችን በመጎልጎል ቢተባበሩን ምንኛ ያማረ እንደሚሆን አትጠይቁኝ

በዚህም ምክንያት በቆሼ አካባቢ ለተወሰኑ ጊዜያት ቆሻሻ መድፋትም እንዲቆምም ተደርጎ ነበር ። በቆሼ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪ ዜጎችም የቆሼ አስቀያሚ ሽታ ባይጠፋላቸውም በመጠኑም ለጥቂት ጊዜም ቢሆን እፎይታን አግኝተው እንደነበር ነዋሪዎቹ ይናገራሉ ። ነገር ግን በኦሮሚያ የሚጣለው የአዲስ አበባ ቆሻሻ ቆሻሻ በክልሉ ተቃውሞ ከተነሳባቸው አንዱ ምክንያት የነበረው ይህ ጉዳይ በመሆኑም ፤ መንግሥት ሳይወድ በግዱ በድጋሚ ፊቱን ወደ ቆሼ ለማዞር ተገደደ ።

አሁን ቆሼ የከተማዋ የአዲስ አበባ እንብርትና ለመሬት ነጋዴው መንግሥታችን ደግሞ ሽንኩርት የሆነ ሥፍራም ነው ። እናም መንግሥት ሆዬ ቆሼ የተባለውን ሥፍራ ቸርችሮ ለመሸጥ ምራቁን አዝረብርቦ እንደጎመዠበት የተገለፀ ሀቅም ሆነ ፣ ይህን በካሬ ሜትር ሲቸበቸብ እንደ ሜሪኩሪ ሽያጭ ብር የሚዛቅበትን ስፍራም አጽድቶ ለመረከብም ቋመጠ፣ ተቁነጠነጠም ። ነገር ግን በፈለገው ሰዓት መሬቱን እንዳይረከብ ጋሬጣ ከፊቱ ተጋረጠበት ። ይኽ ጋሬጣም ድኅነት አሯሩጦ መኖሪያቸውን ከቆሻሻ ሥር ቆሻሻ እያሸተቱ እንዲኖሩ የፈረደባቸውና በህጋዊ መንገድ ካርታ ከመንግሥት ተሰጥቷቸው ጎጆ ቀልሰው በአካባቢው የሚኖሩት ምስኪን ዜጎችን ነበሩ ። እነዚህን ዜጎች እንዴት ከዚህ ስፍራ እንደሚያስነሳቸው መምከር የያዘውም ወዲያው ነው ።

ኢህአዲግ ሆዬ ቋምጦም አልቀረ በኮልፌ ቀራንዮ አስተዳደር በኩል ከ400 በላይ አባወራዎችን በመሰብሰብ ” ቦታው ለልማት ስለተፈለገ በአስቸኳይ ልቀቁ ” የሚል መመሪያና ትእዛዝ መሰል ነገር ለነዋሪዎቹ ይነገራቸዋል ። ነዋሪዎቹም በበኩላቸው ልማቱን እንደማይቃወሙ እንዲያውም ከዚህ አሰቃቂና አስከፊ ስፍራ ለቆ መሄድ የሚጠቅመው ራሳቸውን በመሆኑ የልማቱ አጋር መሆናቸውን ለክፍለከተማው አስተዳደር ይነግራሉ ። ነገር ግን ከቦታው ለመነሳት ተገቢ ካሳና ምትክ የሆነ መሬት ከተሰጣቸው ከቦታው ለመነሳት ነገ ዛሬ ሳይሉ በፍጥነት እንደሚነሱ ጭምር ፈቃደኝነታቸውን በመግለጽ አቋማቸውን ለመንግሥቱ ይገልጻሉ ።

የከተማው አስተዳደርም መልሶ ለዜጎቹ አስደንጋጭ የሆነ እና ተሰምቶ የማይታወቅ ምላሽ ይሰጣቸዋል ። ” ምትክ ቦታም ሆነ የምሰጣችሁ ገንዘብ የለኝም ” በማለት ለነዋሪዎቹ በመግለጽ ያም ሆነ ይህ ግን ከቦታው በአስቸኳይ እንዲነሱ መወትወቱንና ማስፈራራቱን ቀጠለ ። ነዋሪዎቹም አሁንም ቢሆን ከኖሩት በታች ከሞቱት በላይ ስለሆንን የፈለጋችሁትን አምጡ በማለት በእንቢተኝነታቸውና በአቋማቸው ይፀናሉ ።

እስከዚህ ድረስ ያለውን እና ቀጥሎ ያለውንም ነገር የሚነግረኝ በቆሼ አደጋ ይቅርብ ዘመዱን ያጣና ከአደጋ የተረፈ ወዳጄ መሆኑን ልብ ይሏል ።

ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ እንዲህ ሆነ ። መረጃውን የሰጠኝ ወዳጄ ትረካውን ይቀጥላል ።

እኔም በትረካው መሃል ጥያቄዬን አቀርባለሁ ። ጥያቄዬም በግልጽ ለህወሓት የሚቀርብ ነው ። ኢህአዲግ የካሴቱ ከቨር ስለሆነ ለመመለስ ይቸገርብኛል ብዬም ነው ። እንቀጥል ።

፩ኛ ፦ የቆሼ የተራራ ክምር ከመደርመሱ በፊት ሐሙስ ቀን ማለት ነው ያለወትሮው አንድ ኦራል ሙሉ መኪና የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ወታደሮች የቆሻሻ ተራራውን ዙሪያ ከበብው ቆሙ ። መቆሙን ይቁሙ ጥያቄው ለምን ቆመው ውለው አደሩ.?

፪ኛ፦ በቀጣዩ አርብ ቀን መከላከያና ፌደራል ፖሊሶቹ ሥፍራውን ለቅቀው በምትኩ የቆሼ ዙሪያ በከተማዋ ፖሊስ እንዲከበብ ተደረገ ። ለምን ተደረገ.?

፫ኛ ፦ ይሄ ሁሉ ሲሆን ማንኛውም ሰው ቆሼን አቋርጦ እንዳይሄድ ለምን በፖሊሶቹ ተከለከለ.? ለምን ተከለከለ? ። አሁን ጥርጣሬው ከፍ ይልና ወለል ያለ ምስል ይፈጠርልናል ።

፬ኛ፦ በምስኪኖቹ የቆሼ ነዋሪ ቤቶች ላይ የቆሻሻ ክምሩ ከመናዱ በፊት የተሰማው ከባድ የፍንዳታ ድምጽ ተከሰተ ። ይህ የከባድ ፍንዳታ ድምጽ ከየት የመጣ ነው ? ይሄንን ዜና ቤተሰባቸውን በሙሉ በአደጋ ያጡ አንዲት እናት ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ መናገራቸው ልብ ይሏል ።

፭ኛ ፦ መቼም የመከላከያና ሠራዊቱና የፌደራል ፖሊሶቹ ቆሼን ከበው ሲከርም ነዳጅ እየቆፈሩ ነበር እንደማንባል እርግጠኛ ነኝ ።

፮ኛ፦ ለወትሮው አደጋ በደረሰበት ሥፍራ በቶሎ የማይገኙት የከተማዋ የፖሊስ ሠራዊት አባላት የዚያን ዕለት በዚያ ፍጥነት እልፍ አእላፋት ሆነው በዚያ ቁጥር እንዴት በስፍራው ሊፈስሱ ቻሉ.?

፯ኛ፦ አደጋው እንደደረሰ የአካባቢው ነዋሪዎች የነፍስ አድን ሥራ ለምሥራት ሲንቀሳቀሱ በፖሊሶቹ ለምን ተከለከሉ.?

፰ኛ፦ ከሁለት ሰው ቤት ውስጥ እንኳን 16 ሰዎች መሞታቸውን እያየን እና እየሰማን ከዚያ ሁሉ ሰው መኖሪያ ቤት ውስጥ የሟቾችን ቁጥር በ60 እና 70 ወስኖ መናገሩስ የጤና ነውን? ። ለነገሩ መንግሥት በቁጥር በኩል 60 ነው ካለ ትክክለኛውን ቁጥር ለማወቅ 60ን በ20 እና በ30 ማባዛት ብቻ ነው ።

እንግዲህ እኔ በአካባቢው አደጋው ከደረሰበት ሥፍራ የተረፈ ዜጋ ስለ አደጋው ሲያጫውተኝ ወደ አእምሮዬ የመጣ ጥያቄ ነው ያቀረብኩት.? እንዲያው መንግሥቱ ምላሽ ይሠጠኛል ብዬ ሳይሆን እንዲሁ ለጫወታ ያህል መጠየቄ ነው ።

✔ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋል እንዲሉ በነገራችን ላይ እግረ መንገዴን ሌላ ጥያቄ መጠየቅ ስላማረኝ ጠይቅ ጠይቅም ስላለኝ ሌላ ጥያቄ ልጠይቅ ።

፩ኛ፦ እኔ የምለው ወገኖች ሲጎዱ 10 ሚልየን ብር መዥረጥ በማድረግና በመርዳት የሚታወቀው የሶማሌ ክልል መንግሥት አሁን ምነው ድምፁ ጠፋ.?

፪ኛ፦ ለአዝማሪ እና ለአንዳንድ ጋለሞታ የፊልም አክተሮችና ሞዴላ ሞዴሎች ቪላ ቤትና ሚልዮን ብር በማደል የሚታወቁት ሼካችን ይህን አደጋ አልሰሙ ይሆን? ደሃ እንደሚያፀዱ እንጂ እንደሚረዱ ባውቅም ጥያቄ መጠየቅ መብቴ ስለሆነ ነው እንዲህ መጠየቄ ።

፫ኛ፦ የምንወደው ሕዝባችን እያሉ ዘውትር በስሙ እየማሉ ሀብታም የሆኑት አርቲስቶቻችን መሬት ለሚሰጣቸው ክልል ካልሆነ በቀር አጋርነታቸውን ለቆሼ ሰዎች ለማሳየት ለምን አልፈቀዱ ይሆን.?

፬ኛ፦ እነዚያ ርኹሩኽና አዛኝ ለህዝባቸውም የሚንሰፈሰፍ አንጀት ያላቸው ቅዱሳን የሃይማኖት አባቶቻችንስ ተጎጂዎችን ከቦታው ድረስ ሄደው ለማጽናናት ያልደፈሩት ቦታው ርቆባቸው ይሆን.? ወይስ የቆሼ ሽታ ስኳርና አስማቸውን እንዳይቀሰቅስባቸው ሰግተው.?

አረ እኔስ እንደው ምን አይነት እና ምን የሚሉት ቀባጣሪ ነኝ በእናታችሁ ። አሁን እኔ ምን አገባኝ እና ነው እስኪ አሁን ከመሬት ተነስቼ የማይመለስ ጥያቄ ይዤ የምቀባጥረው.? አረ ምን አይነቱ ቀባጣሪ ነኝ በማርያም ። አረ አፉ በሉኝ ወዳጆቼ! ሆሆይ!

ቆሼ ድህነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ የሚታይበት ሥፍራ ነው ። ቆሼ እነ አላሙዲን ጠግበው የደፉትን የምግብ ትራፊ ክቡር የሆነ የሰው ልጅ በህይወት ለመኖር ሲል ከውሻ ጋር እየተጋፋ የሚጠነባ ቆሻሻና ግማት የሰው ልጅን ከማያስቀርብ የቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ትራፊ እየለቀሙ የሚኖሩበት ስፍራ ነው ። ቆሼ እውነተኛውን የኢትዮጵያን 11% ከመቶውን የእድገት ደረጃ የምናይበት ሥፍራ ነው ።

የሚያሳዝነው በቆሼ ዜጎች እንደ ቆሻሻው እነሱም ቆሻሻ ለብሰው ፣ ቆሻሻውን ምግብ አድርገው ፣ ቆሻሻው ላይ መኖሪያቸውን ሠርተው ፣ በመጨረሻም በቆሻሻው ሥር በቁማቸው እንዲቀበሩ እና በቆሻሻ ክምር እንዲወገዱ ተደረጉ ። ነፍስ ይማር ምስኪን ወገኖቼ.!

ይሄ የዘር ማጥፋት ድርጊት ነው ። ለጥፋቱ ተጠያቂው የሚሆነው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው ። በኢህአዴግ ታሪክ አደጋ በደረሰበት ሥፍራ በመገኘት ዜጎችን ማጽናናት ፈፅመው የማያውቁት የከተማው ከንቲባ በአደጋው ሥፍራ መገኘት በራሱ ሌላ ጥያቄ የሚፈጥር ነው ። ከንቲባ ድሪባ አደጋው በደረሰበት ሥፍራ ተገኝተው የአዛኝ ቅቤ አንጓችነትን ሥራና የማስመሰል ድራማ ሠርተው እንዲሄዱ ተደርጓል ። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም የኃዘን ስሜት ተሰምቶኛል አይነት ጫወታ እንዲጫወቱ ተገድደዋል ። ምክርቤቱም ወድዶ ሳይሆን በግዴታው የ3 ቀን ብሔራዊ የሐዘን ቀን ማወጁን አይተናል ።

አሁንማ በየሳምንቱ ሳይሆን በተለያየ ምክንያት ለሚሞተው እና ለሚገደለው ህዝብ በየዕለቱ የሐዘን ቀን ሊታወጅ ባንዲራም ዝቅ ሊል ነው ማለት ነው ።

አሁን ቦታው ጸድቷል ። የካሳ ክፍያ የሚጠይቁ ዜጎች ቁጥርም ከነዘር ማንዘራቸው እንዲወገዱ ተደርጓል ። አሁን ልማታዊው መንግሥታችን በድሆቹ ሬሳ እና በድሆቹ ደም ላይ የፈለገውን አይነት ልማት መገንባት ይችላል ። ካሬ ሜትሩ በሚልየን ብርም መቸብቸቡ ቀጣዩ የእነ ሪፖርተር ጋዜጣ ዜናም እንደሚሆን ይጠበቃል ።

ነገር ግን የድሆች ደም በእግዚአብሔር ዘንድ ዋይ ዋይ ይላል ። የአቤል ደም እሪሪሪ ብሎ ይጮኻል ።እናም ጓደኞቼ መንግሥትም ከኦሮምያ ክልል በተነሳበት ተቃውሞ ምክንያት አዲስ አበባን ወደ ጎን ማስፋቱን ትቼ ውስጧን በማጽዳት ልማቴን አካሄዳለሁ ብሎ በተናገረው እቅድ ምክንያት የማጽዳት ሥራውን በዚህ መልኩ ጀምሮታል ። ነገ ደግሞ ተረኛው የትኛው ሰፈር ይሆን.? እሳት የሚለቀቅበት ፣ ድማሚትም የሚቀበርበት? የሚለውን ጥያቄ እየጠየቅን ለጊዜው እንሰነባበት.?

በቀጣይ በኢትዮጵያ የአንድ ብሔር ወይም ጎሳ ሕጻናትን መንግሥታችን እንዴት ለበሽታ እየዳረገ እንደሆነ የሚያሳይ መረጃ እጄ ገብቷልና እሱን እስካቀርብላችሁና ለመወያየት እስክንችል ድረስ ግን በቸር ቆዩኝ ጓደኞቼ ።

ይኽንንም ራሴው ዘመድኩን በቀለ ጻፍኩት ። +4915217428134 ደግሞ የቫይበር ፣ የኢሞና የኋትስአፕ መልእክቶችን የምቀበልበት የእጅ ስልኬ ነው ።

ሻሎም. ! ሰላም. !

ዘመድኩን በቀለ ነኝ ።
መጋቢት 7/ 2009 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ

የኦሮሞ-ሶማሊ አብሮነት መድረክ “ወንድም እና እህት የሆነው የኦሮሞና የሶማሊ ህዝብ በጋራ ሆነን የህወሓትን የ26 አመታት ጭቆና እንመክታለን!” ሲል መግለጫ አወጣ

 


መጋቢት 7፣ 2009 ዓ.ም

ከህዳር ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ማለትም ላለፉት አምስት ወራት በሶማሊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚደንት የሚታዘዘው ገዳዩ የልዩ ፖሊስ ኃይል አዋሳኝ የኦሮሚያ አካባቢዎችን በመውረር ብዛት ያላቸው ንፁሀንን በመግደልና በማፈናቀል ላይ እንዳለ ይታወቃል። ጥቃቱ እየተፈፀመ ያለው በአምስት የኦሮሚያ ዞኖችና በ14 አዋሳኝ ወረዳዎች ላይ ነው። በተለያዩ ዘገባዎችና የአይን እማኞች መሰረት እስካሁን ቢያንስ 200 ንፁሀን ተገድለዋል ብዙ ቁጥር ያላቸው ቆስለዋል። ገዢው የህወሓት ቡድን ጥቃቱን በሁለቱ ወንድማማችና እህትማማች የሶማሊና የኦሮሞ ህዝቦች መካከል የተነሳ የድንበር ውዝግብ አድርጎ ለማቅረብ ቢሞክርም፣ እውነታው ግን ከኦሮሚያ የተነሳበትን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማዳከም የጠነሰሰው ሴራ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም። በሁለቱ ክልሎች መሀከል ያለው ድንበር እ.ኤ.አ. በ2005/6 ህዝበ-ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑ ይታወቃል።

ሁለቱ ተጎራባች የሶማሊና የኦሮሞ ህዝቦች ለብዙ ክፍለ ዘመናት በሰላም አብረው የኖሩና የሚፈጠሩ አለመስማማቶችን በመወያየት የሚፈቱበት ባህል ያላቸው ናቸው። የህወሓት መሰሪ ሴራም በሁለቱ ህዝቦች ላይ እየፈፀመ ካለው ወንጀል ተጠያቂነት የሚያድነው አይደለም።

ልዩ ፖሊስ በመባል የሚታወቀው ቅጥረኛ ቡድን ንፁሀንን ማጥቃት የጀመረው በኦሮሚያ ክልል አይደለም፣ ይልቁንም ላለፉት አስር አመታት በህወሓት ቀጥተኛ ትእዛዝ የሶማሊ ክልል ህዝብን ሲያሸብር የኖረ ቡድን ነው። በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን፤ ግድያን፣ አስገድዶ መድፈርን፣ መንደሮችን ማቃጠልና የመሳሰሉትን ሲፈፅም ቆይቷል።

እናም የኦሮሞ-ሶማሊ አብሮነት መድረክ እነዚህን ህወሓት መራሽ በህዝቦቻችን ላይ የሚፈፀሙ የጭካኔ ተግባራትን እያወገዝን፣ ወንድምና እህት የሆነው የኦሮሞና የሶማሊ ህዝብ በጋራ እንዲቆም ጥሪ እናቀርባለን። እየተፈፀመ ያለው ጥቃት ህወሓት በእጅ አዙር በኦሮሞ ህዝብ ላይ የከፈተው ጦርነት እንጂ በፍፁም በኦሮሞና በሶማሊ ህዝብ መካከል የተፈጠረ ግጭት አይደለም።

በጋራ ሆነን የህወሓትን የ26 አመታት ጭቆና እንመክታለን!
ድል ለኦሮሞና ለሶማሊ ህዝቦች!

ከጥልቅ አክብሮት ጋር!

የኦሮሞ-ሶማሊ አብሮነት መድረክ ተወካዮች:-

ገረሱ ቱፋ
መሀመድ ሀሰን
ነጃት ሃምዛ
ናጌሳ ኦዶ ዱቤ
ጀማል ዲሪዬ ካሊፍ
ጀዋር መሀመድ
አብዱላሂ ሁሴን
ደሀብ መ. አብደላ
ጥበቡ ስሜ
ሀዲ ሉቅማን
ግርማ ጉተማ
ሰለሞን ኡንጋሼ
ፀጋዬ አራርሳ
ጋዲሳ አብራሂም
ኤደኦ ዳወኖ
ለቱ ቡሻን
አማን ማልዴዎ
እንድሪስ ነገዎ

ውክልናቸውን በግላቸው ያፀደቁ የብሄር ፖለቲከኞች – ዳንኤል ሃይሌ

ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ በብሄር ተደራጂተናል የሚሉት ድርጅቶች ገና ከስልጣን ደጃፍ ሳይደርሱ ድፍረታቸው እና ንቀታቸው ማንነታቸውን ፍንትው አርጎ እያሳየነው።

ዛሬ ማውራት የምፈልገው እኔ ስለወጣሁበት አማራ ነው የሌሎቹን በይደር እንያዘው። የአማራን ህዝብ መደራጀት ከቶ ማንም የሚቃወም ይኖራል ብዬ አላስብም ምክንያቱም ስለዲሞክራሲ የምናልም ከሆነ ሰዎች በምንም ይሁን በምንም የመደራጀት መብታቸውን ልናከብር ይገባል እንዲሁም እነሱም የሌላውን የማክበር ግዴታ አለባቸው ብለን እናምናለን። ፍትህ እና ዲሞክራሲ በጠፍባት ሀገር ዜጎች በማንኛውም መልኩ የመደራጀትና ሀሳባቸውን በነፃነት ገልፀው መኖር በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን እኮ በምን ስሌት ነው እኔ የዚህ ቢሄር ተወካይ ነኝ ወይም በግልፅ ቋንቋ “እኔ የአማራ ብሄር ተወካይ ነኝ እደራደርለታለሁ” የምንለው?

አዎ እውነት ነው የአማራ ህዝብ የሞት አዋጅ የታወጀበት ባልሰራው በደል ባለፋት 25 ዕመታት የዘር ማጥፍት ሲፈፅምበት ቆይቷል። ለዛም ነው ተደራጅቶ እራሱን መታደግ አለበት የምንለው ሆኖም ባሳለፍነው አንድ አመት ውስጥ የተፈለፈሉት ታላቁን የአማራ ህዝብ እንወክላለን የሚሉን ድርጅቶች ህዝባችን ብለው የተነሱለትን ህዝብ ስነልቦና እንኳን ማንበብ የማይችሉ ከራሳቸውም የተጣሉ ሆነው አግኝተናቸዋል። አብዛኛዎቹ የተፈበረኩት በወያኔ የውጭ የፓለቲካ እስትራቴጂክ መዋቅር ውስጥ መሆኑን በግዜ ተጉዘን መረዳት ችለናል ፤ እደውም አንዳንዴም “አግ7 ወደስልጣን ከሚመጣ ከብአዴን ጋር ተስማምተን እንሰራለን” ትዕግስታቸው ሲያልቅ ብለው የሚናገሩም አሉ። ምን እሚሉት ፈሊጥ ነው ከገዳይ ጋር እሰራለሁ ማለት?

የህዝብ ውክልና ምንድነው?

ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የፓለትካ አጣብቂኝ ውስጥ ሆነን ስለህዝብ ውክልና ማውራት ማለት አላዋቂነት ነው ተብሎ ሊታለፍ አይገባም በማንአለብኝነት የተሞላ የስልጣን ጥማት የነገሰበት አስተሳሰብ ነው።

አምባገነኑን የወያኔ አፓርታይድ ስርአት ሳንጥል እና በነፃነት አገራችን የፖለቲካ ሜዳ ላይ ፖሊሲያችንን አቅርበን ቆሜልሀለው የምንልውን ህዝብ ይሁኝታ ሳናገኝ አይ እኔ የተወለድኩት ጎጃም፣ጎንደር፣ወሎ…ወዘተ ስለሆነ እኔነኝ ተወካይህ በማንነትህ ላይ እደራደራለሁ ማለት የጠገበውን ወያኔን አዉርዶ የራበውን ምትኩን ማንገስ ነው የሚሆነው። ለዛም ነው ምንም እንኳን የአስተሳሰብ ልዩነት ቢኖረንም አምባገነኑን የወያኔን ስርአት በጋራ ጥለን በነፃነት ለተጨቆነው ህዝብ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሀሳባችንን አቅርበን ውክልናን የምንረከበው። በተቃራኒው ግን አሜሪካ አገር ቁጭ ብሎ አገር ቤት ወያኔ ሲወድቅ ስልጣን እንደሚያገኝ እርግጠኛ መሆን የሚፈልጉ ቆሜለታለው የሚሉት ወገን ሞት ምንም የማይመስላቸው ሆነው አግኝተናቸዋል።

አግ7 እንኳን እግር በሌላቸው የወያኔ ድርጅቾች በወያኔም አይፈርስ! አግ7 ውስጥ ምንያህል አማሮች እንዳለን እናንተም ታውቃላችሁ አሁን እናንተም ደረታችሁን ነፍታችሁ እየታገልን ነው የምትሉት ትግል ወልዶ ያሳደገው አሁን ላለንበት ያንገዛም እቢተኝነ ማዕበል ያበቃው አግ7 ነው! እኛም አማራ ነን የህዝባችን ሞት የሚገለን።

አልመሸም ገና ብዙ መንገድ ይቀረናል አብረን ብንጟዝ ቶሎ ያሰብንበት እንድርሳለን የወገኑ ስቃይ የሚያመው ሁሉ ልዩነቱን አቻችሎ ለአንድ ጠላት ወያኔ በጋራ ይነሳ!

 

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ዳንኤል ሃይሌ

 

በቆሸ አደጋ የወያኔ መንስኤነት እና የችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሔ! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 2, 2009ዓ.ም. ምሽት 2 ሰዓት አካባቢ በተለምዶ ቆሸ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ላይ በደረሰ የመሬት መደርመስ አደጋ 16 የሚሆኑ በሥርዓት የተገነቡና ካርታ (ንድፈ ምድር) ያላቸው መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ቦታ ተረክበው መኖሪያ ቤት የመገንባት አቅም የሌላቸው ወገኖች ለማረፊያ የቀለሱት በርካታ የላስቲክ (የተለጥ) ቤቶች ተደርምሰው በመዋጣቸው እውስጣቸው የነበሩ በርካታ ወገኖች ማለቃቸው ይታወሳል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ 113 ወገኖች እንዳለፉ አገዛዙ አስታውቋል፡፡
ይህ ቁጥር ግን “ከተዳፈኑት ውስት በሕይዎት ያለ ወገን ይኖር እንደሆን፣ ካልሆነም አስከሬን አውጥቶ ለመቅበር!” በሚል አደጋው የደረሰባቸው ቤተሰቦች ቆፋሪ ማሳልጦችን (ኤክስካቫተር ማሽኖችን) በግል ተከራይተው እንዲሁም መንግሥት ላከው በተባለው ተመሳሳይ ማሽን (ማሳልጥ) እየተደረገ ባለው ጥረት የተገኘ አኃዝ ነው፡፡

የዘመናችን ጥጋበኞች የሚያትረፈርፉትን ምግብ በጨዋና ኃላፊነት በሚሰማው ሰው ደንብ ንጽሕናው እንደተጠበቀ ለየኔቢጤ ወይም ለድሀ መስጠት ስለማይወዱና ስለማይፈልጉ ይሄንን እህል አጥቶ ስንት ጦም አዳሪ ድሀ ሕዝብ ባለባት ሀገር የሚተርፋቸውን ምግብ ከቆሻሻ ጋር ስለሚጥሉ ይሄንን ከዕኩይና ግፈኛ የዘመናችን ጥጋበኞች ከቆሻሻ ጋር የሚጣልን ምግብ እየተመገቡ በዚያ ቆሻሻ ስፍራ ላይ በእነኛ የላስቲክ (የተለጥ) ቤቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩትንና ተደርምሶ በተዳፈኑበት አካባቢ ግን እነኝህ ወገኖች አቋጣሪ፣ ተቆርቋሪና አሳቢ አግኝተው “በሕይዎት ያለ ካለ፣ ካልሆነም አስከሬናቸውን አውጥቶ በክብር ለማሳረፍ!” በሚል እስከ ትናንት ድረስ ጥረት እየተደረገ አይደለም፡፡ በመሆኑም በዚህ አደጋ ያለፉ ወገኖቻችን አሁን እየተጠቀሰ ካለው ቁጥርም ከእጥፍ በላይ ሊሆን እንደሚችን መገመት ይቻላል፡፡

ለመሆኑ እነኝህ ወገኖቻችን በቦታው ለመኖር ፈጽሞ በማይመቸውና ለጤና አደገኛ በሆነ ቆሻሻ ሥፍራ ላይ ሔደው ለመስፈር ምን አስገደዳቸው? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ዜጎች በሀገራቸው ጤንነታቸውና ደኅንነታቸው ተጠብቆ ሠርቶ የመኖር፣ መጠለያ የማግኘትና የመሳሰሉት መሠረታዊ ፍላጎታቸው ተሟልቶላቸው የመኖር የማይጣስ የማይገሰስ ሙሉ መብት አላቸው፡፡ የየትኛውም ሀገር ሕገመንግሥት ይሄንን ያረጋግጣል፡፡ ይህ መብት በየትኛውም ሁኔታ ሊጣስ ሊገሰስ ሊገፈፍ የማይችል ሰብአዊ መብት ጭምርም ነው፡፡ መንግሥት ነኝ የሚል አካል ይሄንን የማሟላት ግዴት አለበት፡፡ ልብ በሉ መልካም ፈቃድ ሳይሆን ግዴታ ነው ያለበት፡፡ በምንም መልኩ ይሄንን መሠረታዊ የዜጎች መብት ሊገፍ፣ ሊነፍግ አይችልም፡፡ ያለውን መሬት ለዜጎች አብቃቅቶ የማከፋፈሉን ፍትሐዊ ሥራ መሥራትና ዜጎችን የሀገራቸው ተጠቃሚ ማድረግ ነው ግዴታውና ኃላፊነቱ፡፡ ምክንያቱም በሕዝብ ጥቅሞችና ጉዳዮች ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ የመወሰን ሥልጣንና ኃላፊነት ያለው ሕዝብ እንጅ መንግሥት ስላልሆነ፡፡ መንግሥት የሕዝብን ውክልና ይዞ የሕዝብን ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ማስፈጸም ብቻ ስለሆነ ተግባሩ፡፡ ለሀገር ኢኮኖሚ (ምጣኔ ሀብት) እድገት ከመሬት ሽያጭ ከሚገኝ መጠነኛ ገቢ ይልቅ ዜጎች የመሬት ባለቤት ሆነው መሬቱ ላይ የሚፈጥሩት ሀብት ነው ሀገርን ሊለውጥ ሊያበለጽግ የሚችለው፡፡ ያደጉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየን ይሄንን ነው፡፡ ቁልፉ አስተሳሰብ ይሄ ከሆነ ሊሠራ የሚገባው ሥራ ዜጎችን በሰፊው የመሬት ባለቤት ማድረጉ ነው እንጅ የመሬት ባለቤትነትን መብት ማሳጣት አይደለም፡፡ ይህ ከተደረገ ግን ውሳኔው ሥልጣን የያዘን አካል ጥቅም የሚያስከብር ቡድናዊ ውሳኔ እንጅ የሀገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሕዝባዊ ውሳኔ አይሆንም፡፡

ምን ያህሎቻችን ከላይ የጠቀስኩትን መሠረታዊ መብት እንደምናውቅና ይህን መብታችንንም ማስከበር፣ ማስጠበቅ እንዳለብን እንደምንገነዘብ አላውቅም፡፡ እንደማየው ሕዝቡ ይሄንን መሠረታዊ የዜጎችን መብት የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ መንግሥት ነኝ ከሚለው አካል ችሮታን ሲጠብቅ እንጅ የመንግሥት ግዴታው እንደሆነ አውቆ መብቱ እንዲጠበቅለት ሲጠይቅ ብሎም ሲያስገድድ አላይምና፡፡ መንግሥት ለባለሀብቶች በሽያጭ የቤት መሥሪያ መሬትና መሠረተ ልማት ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ከ90 ከመቶ በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁጥር ለምንይዘው ቤት የመሥራት አቅም ለሌለን ድሀ እና የድሀ ድሀ ዜጎች ጭምር መጠለያ የማቅረብ ግዴታም አለበት፡፡ ይሄንን እናውቃለን ወይ?

ወያኔ መንግሥት ነኝ እንደማለቱ ይሄንን ግዴታውን የመወጣት ግዴታ ነበረበት፡፡ ወያኔ እንኳንና የዜጎችን መብትና የእሱንም ግዴታ በማክበር ቤት የመገንባት አቅም ላላቸው ዜጎች መሬት በመስጠት፣ ቤት የመገንባት አቅም ለሌላቸው ዜጎች ደግሞ የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ከአነስተኛ እስከ ከፍ ያለ የኪራይ ዋጋ የሚጠይቁ የኪራይ ቤቶችን ገንብቶ በማቅረብ ዜጎች ቤት እንዲኖራቸው በማድረግ የዜጎችን መብትና ጥቅም ሊጠብቅ ሊያከብር ግዴታውንና ኃላፊነቱንም ሊወጣ ይቅርና ይህ በመንግሥት ስም ራሱን ያስቀመጠው የወንበዴ ቡድን ከከተማ እስከገጠር አስቀድሞ የመሬት ይዞታ የነበራቸውን ወገኖች ሳይቀር መሬታቸውን እየነጠቀ ለባዕዳንና ለባለሀብቶች በመቸብቸብ ዜጎች በዜግነታቸው ከሀገራቸው ሊያገኙት የሚገባቸውን ጥቅምና መብት አሳጥቷል፣ ነጥቋል፣ ገፏል፡፡ በዚህ ዝርፊያውም እራሱን በከፍተኛ ደረጃ በማድለብ ላይ ይገኛል፣ መሬትን የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ዋነኛ መጠቀሚያ መሣሪያው አድርጎ በመጠቀምም የግፍ አገዛዙን ለማራዘም ጥረት እያደረገበት ይገኛል፡፡

እነኝህ ወገኖቻችን ለኑሮ የማይስማማ፣ ለጤና አደገኛ በሆነው ቆሻሻ ስፍራ ላይ ሔደው ለመሥፈር የተገደዱት ማንም ሊገስሰው፣ ሊሽረው የማይችል በዜግነታቸው በሀገራቸው መጠለያ አግኝተው ጤናቸውና ደኅንነታቸው ተጠብቆ የመኖር መብት እንዳላቸው ተረድተው በራሳቸው ወጪ አንድ ጥግ ላይ ጎጆ ቢጤ ቀልሰው ለመኖር ሲሞክሩ “የጨረቃ ቤት ነው፣ ሕገወጥ ሰፋሪዎች ናቹህ!” እያለ በሌለ አቅማቸው የቀለሷቸውን ጎጆዎች እያፈራረሰ መድረሻ ቢያሳጣቸው ነው “ይህ ስፍራ ቆሻሻ ነውና አይፈለግም ይሆናል!” ብለው እዚያ ቆሻሻ ላይ ደሳሳ ጆጎ እየቀለሱ፣ የላስቲክ (የተለጥ) ቤት እየወጠሩ ለመስፈር የተገደዱት፡፡

የደርግ መንግሥት ይሄንን የዜጎችን መሠረታዊ መብትና የመንግሥትነትን ግዴታ በመገንዘብ ይመስላል የመሬት ላራሹንና ትርፍ የከተማ ቤትን የመውረስ አዋጆችን በማወጅ መሬት ላልነበረው ዜጋ የመሬት ባለቤት አድርጓል፣ ቤት የመሥራት አቅም ላላቸው የከተማ ነዋሪዎች ለካርታ (ንድፈ ምድር) እና ለተመሳሳይ ጉዳዮች አነስተኛ ወጪ በማስከፈል በነጻ ቤት የመገንቢያ መሬት ለዜጎች ሲያቀርብ ነበር፣ ቤት የመገንባት አቅም ለሌላቸው ወገኖች ደግሞ እንደየአቅሙ ከሃምሳ ሳንቲም ጀምሮ በጣም አነስተኛ ኪራይ የሚከፈልባቸውን የኪራይ ቤቶችን ገንብቶ እንዲሁም በአዋጅ የተወረሱ ቤቶችን በማቅረብ የዜጎችን መብትና የመንግሥትነቱን ግዴታ ለማክበር፣ ለመጠበቅና ለመወጣት ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ ወያኔ መንግሥት ነኝ ካለ ይሄንን የደርግን ፈለግ መከተል ሲኖርበት ያልተከተለው “የሚከተለው ርዕዮተዓለም ከደርግ የተለየ ስለሆነ ነው!” እንዳንል የሚከተለው ርዕዮተዓለም ከደርግ የሚለይ አይደለም አንድ ነው፡፡ ወያኔ የሚከተለው የኢኮኖሚ (የምጣኔ ሀብት) ሥርዓት ነጻ (ሊበራል) ቢሆን ኖሮ ከገጠር እስከ ከተማ መሬትን ከዜጎች እየነጠቀ ለባለሃብቶች መስጠቱ ባልገረመን ነበር፡፡

ሙቱ የወያኔው መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ይሄንና ተጓዳኝ ነገሮችን በተመለከተ በአንድ ወቅት ላይ ተጠይቀው ሲመልሱ ያለአንዳች ሐፍረትና የተጠያቂነት ስሜት ነበረ በብዙኃን መገናኛ “ከተማ ለቆ መውጣት ነው!” ብለው በመናገር አገዛዛቸው የአፓርታይድ (የመድሎ) ወይም ለባለሀብቶች ብቻ የቆመ አገዛዝ መሆኑን ያረጋገጡት፡፡

ሰሞኑን ይሄ አሁን የደረሰብንን አደጋ በተመለከተ በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛዎች አንድ የታዘብኩትና በጣም ያናደደኝም እንቅስቃሴ ነበር “በአደጋው ላለፉ ወገኖች ክብር ሲባል ብሔራዊ የሐዘን ቀን ይታወጅልን!” ብሎ አገዛዙን የሚጠይቅ እንቅስቃሴ፡፡ በጥያቄያቸው መሠረትም ብሔራዊ የሐዘን ቀኑ ሲታወጅ ፈንጠዝያ አይሉት ምን ተመልክቻለሁ፡፡ በእውነት በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ በቃ ይህችን ታክል ነው የምናስበው? ይህ አደጋና መንስኤው እኮ በሌሎች ሀገራት ቢሆን ኖሮ ሀገር የሚንጥ መንግሥት የሚገለባብጥ ዐመፅ ያስነሣ ነበረ እኮ ጃል! ይሄን አጋጣሚ ተጠቅመን ሌላው ቢቀር ዜጎችን ለዚህ አደጋ የዳረገው ኢፍትሐዊ የመሬት አሥተዳደር ሥርዓቱ እንዲቀየር መንቀሳቀስ አልነበረብንም ወይ? ቆይ እንጅ የሐዘን ቀኑ ስለታወጀ ወያኔ ማረፊያ መድረሻ አሳጥቷቸው ቆሻሻ ላይ ሔደው ለመስፈር የተገደዱትንና ለዚህ አደጋ የተዳረጉትን ወገኖች አከበረ ወይም ክብር ሰጣቸው ማለት ነው? ይሄንን ያህል ወገን በራሱ በግፍ አስተዳደሩ ምክንያት ለሕልፈት ተዳርጎ እያለ ጉዳዩን ከመጤፍ ሳይቆጥር ብሔራዊ የሐዘን ቀን ሳያውጅ የማለፉን አሳዛኝና አስገራሚ ሁኔታ ለቀጣይ ትውልድ ይታወቅ ዘንድ ለታሪክ ትቶ ማለፍ ሲገባ ያለ ሐሳቡ ያለፍላጎቱ አሳስቦና ጎትጉቶ የሐዘን ቀን ማሳወጁ ግፉ ለደረሰባቸው ወገኖችና ላለው ቀሪ ዜጋ የሚጠቅመው ምንድን ነው? ይህ አደጋ በዚህ ስፍራ ላይ ሲከሰት ይሄኛው ለስድስተኛ ጊዜ የተከሰተ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ወያኔ ግን ኃላፊነት ተሰምቶት “ዜጎችን ከአደጋ የመጠበቅ ግዴታ አለብኝ!” ብሎ አንዳች ያደረገው ነገር ባለመኖሩ ይሄው የከፋው አደጋ ሊከሰትና በርካታ ወገኖቻችንን ልናጣ ቻልን፡፡ እና ታዲያ ይሄ ሁሉ እየሆነ እየታየ ልንንቀሳቀስ ይገባን የነበረው የሐዘን ቀን መጠየቅ ነው ወይ?

ወያኔ የወገኖችን የዜጎችን መሠረታዊ የዜግነትና ሰብአዊ መብታቸውን ገፎ መድረሻ ማሳጣቱን እስከቀጠለ ጊዜ ድረስ ነገም ተቸግረው እዚህ የቆሻሻ ቦታ የሚሠፍሩና ለተመሳሳይ አደጋ የሚዳረጉ ወገኖች መኖራቸው ይቀራል ወይ? ካለስ የአደጋው መንስኤ ሁላችንም ላይ ያነጣጠረ እንደመሆኑና እንደዜጋም አፋጣኝ መፍትሔ መፈለግ የለብንም ወይ? ወገን ሆይ! ሀገርህን እኮ ተነጥቀህ በገዛ ሀገርህ ባይተዋር፣ ስደተኛ፣ ተጉላላይ፣ ተንጓላይ፣ ተቅበዝባዥ ሆነህ እኮነው ያለኸው! የአንድ ሀገር ሕዝብ ሀገሩን ነጥቆ ቀምቶ በገዛ ሀገሩ የመኖር ዋስትናውን፣ የዜግነት መብቱንና ጥቅሙን አሳጥቶ ዕለት ዕለት እያሳደደ፣ እያፈናቀለ ሀገሩን ለባዕዳንና ለባለሃብቶች እየቸበቸበለት ያለውን አንባገነን አገዛዝ በዝምታ መመልከት አለበት ወይ?

ዜጎች በዜግነታቸው መሠረታዊ መብታቸውና ጥቅማቸው ተከብሮላቸው በገዛ ሀገራቸው ተረጋግተው መኖር ካልቻሉ ዜጎች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ጥቅም፣ ሀገሬ ብሎ ለማለት የሚያስችላቸው መብት ሌላ ምን አለና? ነገ ጠዋት በዚህች ሀገር ላይ ጥቃት ቢቃጣ “ሀገሬ!” ብሎ ተነሥቶ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ ሉዓላዊነቷን የሚያስከብረው ማን ነው? መሬታችን ተነጥቆ የተሰጣቸው ባዕዳን ባለሀብቶች ናቸው እንዴ? ወይስ ጥቂት የናጠጡ ባለሀብት ዜጎቻችን? ይሄ ወያኔ መድረሻ ያሳጣው ድሀ ሕዝብ እና መሬቱ እየተነጠቀ ለባዕዳን እየተሰጠበት ያለው ገበሬ አይደለም ወይ? እንዲህ የደም ዋጋ ከፍሎ ያቆያትን እና ነገ አንድ ነገር ቢፈጠርም “ሆ!” ብሎ ተነሥቶ መራር መሥዋዕትነትን የሚከፍልላትን ዜጋ በምን ሒሳብ፣ በየትኛው መሥፈርት ነው ከገዛ ሀገሩ ሊያገኘው የሚገባው ጥቅምና መብት ተነፍጎት ባይተዋር፣ ተሳዳጅና የበይ ተመልካች ሊደረግ የሚገባው? እኮ በየትኛው ፍትሐዊ አሠራር? በወያኔ ዓይነቱ ኢፍትሐዊ የአፓርታይድ (የመድሎ) አገዛዝ ካልሆነ በስተቀር!

እናም የዋሁ ወገኔ ሆይ! የችግሩ መፍትሔ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ማሳወጁ ሳይሆን ስንት ዋጋ ከፍለህ ያቆየሀትንና ወደፊትም የምትከፍልላትን ሀገርህን ነጥቆ የባዕዳንና የባለሃብቶች ብቻ ያደረገብህን፣ በገዛ ሀገርህ ተሳዳጅ፣ ተፈናቃይ፣ የበይ ተመልካች ያደረገህን አንባገነን የወንበዴ አገዛዝ ማስወገድ ነውና በየጊዜው በአገዛዙ የግፍ አስተዳደር መንስኤነት አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር ማላዘኑን ትተህ የችግሮችህ ሁሉ ምንጭ የሆነውን ወያኔን ለመገርሰስ ቆርጠህ ተነሥ! ሳትውል ሳታድር ክንድህን በግፈኛው በጠንቀኛው አገዛዝ በወያኔ ላይ አንሣ! ይህን ማድረግ ካልቻልክ ግን ነገም ያንተ እጣ ከእነኚህ አደጋው ከደረሰባቸው ወገኖች የተለየ እንደማይሆን እወቀው!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com