ሕገ መንግሥቱ ዐማራ ሕዝብን አይመለከትም፤ (ሙሉቀን ተስፋው)

(መጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም፤ https://www.facebook.com/brannaradio/)፤ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው ጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም የከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የሰጠው ውሳኔ ነው፡፡

በ2005 ዓ.ም ከመተከል ከተፈናቀሉ የዐማራ ተወላጆች መካከል ሁለት ሰዎች በ2006 ዓም በዶክተር ያቆብ ኃይለ ማርያም አማካይነት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መሥርተው በልደታ ምድብ ችሎት ሲከራከሩ ቆይተው ነበር፡፡ ለዶክተር ያቆብ ኃይለ ማርያም ውክልና ሰጥተው ሲከራከሩ የቆዩት ገበሬዎች ቄስ መሥፍን አስፋው እና አቶ አቻምየለው ደሴ ይባላሉ፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት ዶክተር ያቆብን በዚህ ጉዳይ አነጋግሬያቸው ነበር፡፡ ‹‹በየቦታው የተፈናቀሉትንና የሚፈናቀሉትን የዐማራ ተወላጆች ጉዳይ በተጠናከረ መልኩ ለመሄድ አሁን የያዝነው ክስ ወሳኝነት አለው፤ ፍርድ ቤቱ መንግሥት ጣልቃ ሳይገባበት ትክክለኛ ውሳኔ ከሰጠ የሌሎች ተበዳይ ዐማሮች ጉዳይ ካሳ መጠየቅ የሚችሉ ከመሆኑም በላይ ቅጣት ካለው ካሁን በኋላ ማፈናቀሉም ሊቆም ይችላል›› ነበር ያሉት፡፡ ሆኖም ውሳኔው ከተሰጠ በኋላ ዶ/ር ያቆብ በጉዳዩ ላይ አሁን ያላቸውን ለማግኘት ሞክረን አልተቻለም፡፡

በጠበቃቸው በኩል የቀረበው የገበሬዎች ክስ 839,600.00 የወደመና የተዘረፈ ንብረት ግምት ሲሆን በተጨማሪም በተሠራባቸው ሕገ ወጥና አረመኔያዊ ተግባር የክልሉ ባለሥልጣናት ተገቢውን ቅጣት አግኝተው የሞራል ካሣም ጭምር እንዲከፈላቸው ነበር፡፡ ከሳሾች በተፈናቀሉበት ቀዬ ከ15 እስከ 20 ዓመት ቤተሰብ መስርተው፣ ልጆችን ወልደውና ሀብት አፍርተው ከመኖራቸውም በተጨማሪ ማናቸውንም የአንድ ዜጋ ግዴታዎች ሳያጓድሉ ቆይተዋል፤ ግብር ይከፍላሉ፤ ምርጫ ይመርጣሉ፣ የልማት ይከፍላሉ ወይም በአጭር አነጋገር ማናቸውንም የሚጠበቅባቸውን ጉዳይ ይፈጽማሉ፡፡ በዚህ ሒደት በ2005 ዓም በማስታወቂያ አካባቢውን ለቃችሁ ውጡ መባሉ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 32 ማንኛውም ዜጋ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብቱን የሚጥስ በመሆኑ ሕገ ወጥ ነው በማለት ነበር የተከራከሩት፡፡

ተከሳሾቹ የፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴር፣ የቤኒሻንጉል ክልል መንግሥትና የመተከል ዞን ቡለን ወረዳ አስተዳደር ሲሆኑ ያቀረቡት መከራከሪያ ቀድሞ ይኖሩበት አካባቢ መሻኛ አላመጡም እንዲሁም በክልሉ ለመኖር ፈቃድ አልጠየቁም የሚል ነው፤ ወይም የክልሉ መንግሥት እንዲመጡ ጋብዟቸው ስላልሆነ በክልሉ ለመኖር አይችሉም የሚል አንድምታ ያለው መልስ ለፍርድ ቤቱ አቀረቡ፡፡
ምንም እንኳ ከሳሾች ከ15 እስከ 20 ድረስ ሲቆዩ በሕጋዊነት መሆኑ ዕሙን ቢሆንም እስካሁን ባለው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ማንም ዜጋ በፈለገው አካባቢ በፈለገው ሰዐት መሔድና መኖር እንደሚችል እንጅ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ለመሔድ የፈለገ ሰው የመግቢያ ቪዛ መጠየቅ እንዳለበት ወይም መጀመሪያ ከነበረበት አካባቢ የመውጫ ቪዛ መጠየቅ አለበት የሚል ምንም ዓይነት ሕግ የለም፡፡

ከዓመታት እንግልት በኋላ የከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠው ውሳኔ ግራ የሚያጋባ ከመሆኑም በላይ ሕገ መንግሥቱ የዐማራ ሕዝብን እንደማይመለከት በትክልል ያስገነዘበ ሆኗል፡፡ በፍርድ ቤቱ በውሳኔው ዜጎች በመረጡት ቦታ የመዘዋወር መብት ስላላቸው መፈናቀላቸው አግባብ አይደለም ካለ በኋላ የወደመባቸው ንብረት ካሣ ግን አይከፈላቸውም ብሏል፡፡ ይኸው ችሎት ተጎጅዎች ንብረታቸውን አውድመው ለአፈናቀሏቸው ሰዎች ፍርድ ቤት ለተመላለሱበት ወጪያቸውን መሸፈን አለባቸው ሲል አስደናቂ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ሕገ መንግሥትና የዐማራ ሕዝብ እንዲህ ናቸው፡፡ የሕግ ባለሙያ ሰዎች በዚህ ላይ ተነስታቸው ትንታኔ ብትሰጡበት መልካም ነው፡፡

(ሙሉቀን ተስፋው)

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s