ኤርትራን በሚመለከት የሕወሐት “አዲስ ፖሊሲ” ምን ሊሆን ይችላል?

 

(ዮፍታሔ)

‘በኤርትራ አዋሳኝ የትግራይ ወረዳዎች ሰዎች እየታፈኑ ይወሰዳሉ፣ ሰላም ባለመኖሩ እነዚህ ወረዳዎች በልማትም ወደኋላ ቀርተዋል’ በማለት በኤርትራ ላይ “ጠንከር ያለ ርምጃ” እንዲወሰድ ethiopiafirst. com የተባለው የወያኔ ደጋፊ የሚዲያ ተቋም ሰፊ የቪዲዮ ዘገባ የሠራበትና ከርሱ በፊትም በ Facebook ታዋቂ የሆኑ የወያኔ ደጋፊዎች ይህንኑ “ጠንከር ያለ ርምጃ” በተደጋጋሚ ሲያቀነቅኑት የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው። ያንን ተከትሎም የአገዛዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኤርትራን በሚመለከት እስካሁን የተደረገው “ተመጣጣኝ ርምጃ” ስላልሠራ ሕወሐት “አዲስ ፖሊሲ” እንደሚከተል አስታውቋል።


ከዚህ መግለጫ በኋላ የሕወሐት አገዛዝ ተከታታይ የዲፕሎማሲ ዘመቻ ላይ መሆኑን የሚጠቁሙ በርካታ እንቅስቃሴዎች እየታዘብን እንገኛለን። የቱርክ መሪ ጉብኝት፣ የሳውዲና የተባበሩት አረብ ኤምሬት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጉብኝት፣ የሱዳኑ አልበሽር ጉብኝት፣ የኳታር መሪ ጉብኝት፣ ከደቡብ ሱዳኑ መሪ ሳልቫ ኪር ጋር የተደረገ የወታደራዊ ትብብር ቃልኪዳን፣ የሕወሐት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአልጀሪያ ያደረገው ጉብኝት፣ ወዘተ በጣም በአጭር ጊዜ በተከታታይ የተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ናቸው።
እነዚህ ጉብኝቶችና የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች በአጭር ጊዜና በተከታታይ የተደረጉ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ በመሪዎች ደረጃና በዝግ የተደረጉ ግንኙነቶች ከመሆናቸው በተጨማሪ በመግለጫቸው ላይ ሁሉም በ”ጸጥታ”ና የአካባቢውን ፖለቲካ በሚመለከት በትብብር ለመሥራት መስማማታቸውን የሚገልጹ ናቸው።
በዚሁ ተመሳሳይ ጊዜ የሳውዲ መንግሥት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሦስት ወር ውስጥ ወደአገራቸው እንዲመለሱ የወሰነ ሲሆን ውሳኔው ከሀገር ጸጥታ ጋር የተገናኘ እንደሆነም አልሸሸገም። ሕወሐትም መጀመሪያ በኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ በነገሪ ሌንጮ፣ በትናንትናው ዕለት ደግሞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ በመለስ ዓለም በኩል ኢትዮጵያውያን ከሳውዲ ወደኢትዮጵያ እንዲመለሱ ባልተለመደ መልኩ ከማስጠንቂቂያ ጋር እየወተወተ ይገኛል። ለ 4000 ኢትዮጵያውያን የመመለሻ ዶክመንት (Travel Document) መስጠቱን፣ ሌሎች የሚቀሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንዳሉና ወያኔ ለዚሁ ሲል የእዝ ጣቢያ (Command Post) እንዳቋቋመም ገልጿል። ከሳውዲ አረቢያ ተጓዥ ኢትዮጵያውያን ሕጋዊ በሆነና ባልሆነ መንገድ ትርፍን የሚያግበሰብሰው ወያኔ እነዚህን ወገኖቻችንን እንደገና ወደኢትዮጵያ እንዲመለሱ መወትወቱ ከምን የመነጨ እንደሆነ ማወቅ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
ሌላም አለ። ወያኔ ሕዝባዊው ትግል በተፋፋመበት ጊዜ ለይስሙላም ቢሆን በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ”ተቃዋሚ ፓርቲዎች” ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ በመሆን ድርድር ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ትንሽ ሳይቆይ ግን በመጀመሪያ ድርድሩን ውይይት ነው በማለትና በማቃለል በኋላም ያለምንም ውጤት ድርድሩ እንዲበተን በማድረግ ቋጭቶታል። ከተወሰኑት ጋር ከዚያ ወዲህ የቀጠለ ውይይት ሊኖር ይችላል ቢባልም ከይስሙላ እንደማያልፍ ለመገመት አያስቸግርም። ይህን ያነሣሁት የሕወሐትን የወቅቱን መንፈስ (Mindset) ለማሳየት እንጂ ድርድሩ ቢሳካ እንኳን የሚፈለገውን ለውጥ ያስገኛል በማለት አይደለም።
እንግዲህ እነዚህንና ሌሎችንም ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎችን ስንመለከት ነው የሕወሐት “አዲስ ዕቅድ” ምን ሊሆን እንደሚችል ለመጠየቅ የምንገደደው። የሕወሐት አዲስ ዕቅድ በቀጥታ የሚመለከተው ኤርትራን ሊሆን ቢችልም በተጓዳኝ ከኢትዮጵያውያንና ይልቁንም ከአማራው ተጋድሎ ጋራ ቀጥተኛ ግንኙነት ሊኖረው ስለሚችል ስለዕቅዱና ሊያስከትለው ስለሚችለው ውጤት አስቀድሞ ማወቅ ለመዘጋጀት ይጠቅማል።
ለመሆኑ የሕወሐት “አዲስ ዕቅድ” ምን ሊሆን ይችላል? ለሚለው ጥያቄ በአጭሩ ሦስት መላ ምቶችን ማቅረብ ይቻላል። “አዲሱ ዕቅድ” ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ብቻ ነው የሚል፣ ከኤርትራ ጋር ዕርቅ ማድረግ ነው የሚልና በኤርትራ ላይ “ጠንካራ ርምጃ” መውሰድ ነው የሚል ናቸው።
የመጀመሪያው በሕወሐት አንጃዎችና በትግራይ ብሔረተኝነት አቀንቃኞች ዘንድ በኤርትራ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወሰድ ከፍተኛ ግፊት በሕወሐት አመራር ላይ ሲደረግ ስለቆዬ አመራሩ ለዚህ ጥያቄ የይስሙላ መልስ በመስጠት ይህን ግፊት ለማርገብ ብቻ ያደረገው የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ነው የሚለው ነው። ከሕወሐት የቅጥፈትና የቀላማጅነት ታሪክ ይህ ሊሆን አይችልም ባይባልም በተከታታይ ከሚደረጉት የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችና በሕወሐት ላይ እየጠነከረ ከመጣው የአገር ውስጥና የውጭ ተቃውሞ በመነሣት ወያኔ አሁን የተነሣበትን ተቃውሞ በፕሮፖጋንዳ ብቻ መፍትሔ ሰጥቶ ለማለፍ ያስባል ለማለት አስቸጋሪ ነው። አገዛዙም ያውቃል ሕዝቡም ይህን ጠንቅቆ ያውቃል።
ይህ ከሆነ የቀሩት ሁለቱ አማራጮች ዕርቅና “ጠንከር ያለ ርምጃ” የሚሉት ይሆናሉ።
በኤርትራ ላይ “አዲሱ ዕቅድ” ዕርቅ ነው የሚሉ ወገኖች ከሚያቀርቧቸው ምክንያቶች ጥቂቶቹ ከኢትዮጵያ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከሚያደርጉት አገሮች ሁሉም ባይሆኑ አብዛኞቹ (ሳውዲ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬት፣ ኳታር፣ ሱዳን) ከኤርትራም ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸው መሆኑን በመጥቀስ ሲሆን (የሱዳኑ መሪ ከኢትዮጵያው ጉብኝቱ ቀጥሎ ወደኤርትራ ማቅናቱን ይጠቅሳሉ) ወያኔ በአገር ውስጥ ካለበት ውጥረት የተነሣ በኤርትራ ላይ የኃይል አማራጭ ለመውሰድ አይሞክርም የሚሉ ናቸው። የወያኔ ደጋፊ በመሆኑ የሚታወቀው “ሪፖርተር” ጋዜጣም በትናንትናው እትሙ ስለኳታሩ መሪ ጉብኝት ባወጣው ዘገባ ማጠቃለያ ላይ የሚከተለውን አስፍሯል፦
“በነዳጅ ሀብቷ የምትታወቀው ኳታር ኤርትራ ከሱዳንና ከጂቡቲ ጋር ዕርቅ እንድትፈጥር ጥረት ያደረገች ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመረችው ግንኙነት ሙቀት በዚሁ ከቀጠለ ኢትዮጵያንና ኤርትራን የማስታረቅ ፍላጎት እንዳላት የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።”
ከዚህም በተጨማሪ በሕወሐትና በሻእቢያ መካከል ከጦርነቱ በኋላ የተተካው ግልጽ ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት (No war, no peace) ሁኔታ ለሁለቱም (ለሻእቢያና ለወያኔ) የተመቻቸው ስለሆነ እንዲቀጥል ይፈልጉታል የሚሉ አሉ። ስለዚህ አዲሱ ዕቅድም ሆነ የሚታየው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ከጸብ ይልቅ ወደድርድርና ከተቻለም ወደዕርቅ ለመሄድ የሚደረግ ጥረት ነው ባይ ናቸው።
በሌላ በኩል የሕወሐት “አዲስ ዕቅድ” የሻእቢያን አቅም በእጅጉ ሊያዳክም ከሚችል ጠንከር ካለ ወታደራዊ ርምጃ ጀምሮ ሻእቢያን እስከማስወገድ ሊደርስ እንደሚችል የሚከራከሩ ሰዎች ምክንያታቸውን የሚያቀርቡት በሚከተለው መንገድ ነው።

በመጀመሪያ ነገር በኢትዮጵያ ውስጥና በአካባቢው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ማጤን ያስፈልጋል። እነዚህ አንዳቸውም እውነተኛ ዕርቅ ተግባራዊ ሊሆን የሚችሉበትን መንገድ አያመለክቱም። ሕወሐት በሕዝብ የተነሣውን ተቃውሞ ለመፍታት የሄደበት መንገድ (በአገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ጋር ያደረገው ውይይትን ጨምሮ) እና በቅርቡ በሕወሐት እየተከናወነ ያለው የማራቶን ዲፕሎማሲም እንዲሁ ወደዕርቅ የሚሄድን መንግሥት መንፈስ አያሳዩም በማለት ይንደረደራሉ።
ከጦርነቱ በኋላ የተከተለው (“No war, no peace”) ሁኔታ በመጀመሪያ አካባቢ ለሁለቱም አገሮች የተሻለው አማራጭ ሆኖ ቆይቶ ሊሆን ይችላል። ሆኖም እየቆየ ሲሄድ የተሻለ አማራጭ መሆኑ ቀርቶ ሁለቱንም አገሮች ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላቸው እንደሆነ የሚታወቅ ነው በማለት ይቀጥላሉ። ለምሳሌ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ሻእቢያንና የኤርትራን ሕዝብ በእጅጉ በመጉዳቱ ሻእቢያ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ለመቀየርም ሆነ አንዳችም ረብ ያለው ልማት ለማከናወን ባለመቻሉና ይልቁንም ያለውን የሰውና የተመናመነ የገንዘብ አቅም ከጦርነት ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እያዋለ ስለሚገኝ የኤርትራ ሕዝብ ለከፍተኛ ድኅነት፣ ወጣቱም በገፍ ለስደት ተዳርጓል። ይህ ደግሞ ሻእቢያም ሆነ የኤርትራ ሕዝብ ከነበራቸው ሕልም ጋራ በእጅጉ የሚጋጭ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ኤርትራ ከሌላው ዓለም የተገለለችና በየብዙሐን መገናኛው “የአፍሪካ ሰሜን ኮሪያ” እየተባለች መቀጠሏ በሁሉም መስክ ኤርትራን እየጎዳ ስለሆነ ሻእቢያ አሁን ያለው ሁኔታ እንዲቀጥል ይፈልጋል ማለት የተሳሳተ ግምገማ ነው። በተለይም ማዕቀቡ ሻእቢያን ብዙ ዋጋ እያስከፈለው ስለሆነ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች ከመርዳት ጀምሮ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እየተሳተፈ የሚገኘውም በዚህ ምክንያት ነው በማለት ይሞግታሉ።
ይህ ድርጊት ደግሞ፤ ይላሉ በመቀጠል፤ በወያኔ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ (የኤርትራ እንቅስቃሴ እስካሁን የጎላ ሆኖ ሳይሆን ተቃዋሚዎች የፈጠሩት መንፈስ) እየጠነከረ እንዲመጣ አስተዋጽኦ ማድረጉ የታወቀ ነው። ሕወሐትም “በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ቀውስ” ሻእቢያን በተደጋጋሚ ተጠያቂ አድርጓል።
በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ ጫፍ ወያኔን አንቅሮ በመትፋት ሕዝባዊ ትግሉን በግልጽና በስውር አፋፍሟል። ወያኔም የተፈጠረበትን ስጋት በተደጋጋሚ አምኗል። አምኖም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አገሪቷን እያስተዳደረ ይገኛል። ሆኖም እነዚህን አብይ ስጋቶች ለዘለቄታው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊሻገራቸው እንደማይችል ያውቃል። የሀገር ውስጡን ውጥረት ፈርቶ በኤርትራ ላይ የሚደረግን የኃይል ርምጃ ቢሸሽ የአገር ውስጡ እንቅስቃሴ እየሰፋና እየጎለበተ መሄዱን አያስቀረውም። እስካሁን የታየው የትግል እድገት ይህንን ያረጋግጣል። ጥቂት ደፋር ዜጎች፣ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች አገዛዙን ፊት ለፊት በመጋፈጥ የጀመሩት ትግል በመጀመሪያ ወደሙስሊሙ ማኅበረሰብ፣ ከዚያም ወደኦሮሚያ ክልል፣ ወደኮንሶና በመጨረሻም ወደአማራ ክልል ሊዛመት ችሏል። በአማራ ክልል ደግሞ ትግሉ አንድ ርምጃ አድጎ ወደትጥቅ ትግል ተቀይሯል። ስለዚህ ወያኔ ከተቻለ አናጥሎ ካልሆነም በኤርትራ አሳቦ የአማራውን የትጥቅ ትግል ደርቦ ከመግጠም ሌላ አማራጭ የለኝም ብሎ ሊያስብ እንደሚችል እነዚህ ወገኖች በአንክሮ ያስገነዝባሉ። ኤርትራን በሚመለከት እስካሁን የነበረው የ“ተመጣጣኝ ርምጃ” ፖሊሲ ስላልሠራ “አዲስ ፖሊሲ” እንደሚያስፈልገው በግልጽ ያመነውም ለዚህ ነው በማለትም ይከራከራሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የሻእቢያ በሥልጣን መቆየት (በአሰብ ወደብ ካስጠጋቸው አገሮች ፍላጎትና ከፈጠሩለት የገንዘብ አቅም ጋር) ለወያኔ ሕልውና ትልቅ ሥጋት መሆኑ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንደማይሄድ ይታወቃል። ሌላ ተመሳሳይ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ቢፈጠርና የትጥቅ ትግሉ ከጠነከረ ሻእቢያ እንዳሁኑ ዝም ብሎ መመልከቱን ትቶ ሊሳተፍበት ቢወስን የወያኔ እጣ ምን ሊሆን ይችላል? በማለት ይጠይቁና እንዲህ ዓይነት ሕዝባዊ ቁጣ እንደገና መፈጠሩ የማይቀር ከሆነ ያ ከመሆኑ ቀድሞ በሻእቢያ በኩል ያለውን ስጋት ማስወገድ ያስፈልጋል ብሎ ወያኔ ሊያምን የሚችልበት ሰፊ ዕድል መኖሩን መዘንጋት የለብንም በማለት ይከራከራሉ።
በሌላ በኩል ለሻእቢያ፤ በራሱ የሙስና፣ የብልሹ አስተዳደር፣ የዘቀጠ የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ አፓርታይድን በሚያስንቀው ዘረኝነቱና ስግብግብነቱ የተነሣ አገር ማስተዳደር ከተሳነውና ሕዝባዊ መሠረቱን ካጣ በመውደቂያው ዋዜማ ላይ ከሚገኝ ከወያኔ ጋራ ዕርቅ ማድረግ የማይታሰብ ነው ባይ ናቸው። ልጡ ከተራሰ ጉድጓዱ ከተማሰ የወያኔ ሥርዓት ጋር ዕርቅ ማድረግ ይልቁንም ለሻእቢያ ትልቅ ዋጋ የሚያስከፍለው ይሆናል። ሻእቢያ ከወያኔ ጋር ዕርቅ ሲያደርግ ከተቃዋሚዎችና ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በድጋሚ ከፍተኛ መቃቃር ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ ለወያኔ ሰርግና ምላሽ ይሆንለታል። ምክንያቱም ለወያኔ ስጋቱን የሚያስወግድለት ብቻ ሳይሆን ሻእቢያን ከተቃዋሚዎችና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ ስለሚያደርግለት ነው በማለት ይሞግታሉ። ይህ ታዲያ ለዘለቄታው ኤርትራን በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑን ሻእቢያ አይገነዘብም? በማለት ይጠይቁና ዕርቁ ወያኔ ሻእቢያን አናጥሎ ለመምታት የተመቸ ሊያደርገው እንደሚችልም ይጠቅሳሉ።
በወያኔ በኩል ደግሞ ሌላም አለ በማለት ይቀጥላሉ። ዕርቁ እውነተኛ እንዲሆን ከሁሉም በላይ ሻእቢያ የተጣለበት ማዕቀብ መነሣት አለበት። ባድመ ዋናው ጉዳይ ነው ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። የባድመ ጉዳይ ቀላል ነው ለማለት ባይቻልም ማዕቀቡ ግን ከዚህ በላይ ነው። ማዕቀቡ ካልተነሣ ለሻእቢያ ዕርቅ ማድረግ ምንም ትርጉም አይኖረውም። ይህ ከሆነ ለወያኔ በሻእቢያ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ማስነሣት ሲቆይ ዋጋ ያስከፍለኛል ብሎ እንዲሰጋ አያደርገውምን? ብለው በመጠየቅ ወያኔ በአሁኑ ሰዓት ይህን ሊያስፈጽም የሚፈልግበት ተጨባጭ ሁኔታ የለም በማለት ይከራከራሉ።
በኤርትራ ላይ የታሰበው “አዲስ ዕቅድ” ዕርቅ ከማድረግ ይልቅ ጠንከር ወዳለ ርምጃ ሊያተኩር እንደሚችል በመግለጽ የሚከራከሩት ወገኖች አሁን ከኢትዮጵያ ጋር የማራቶን ዲፕሎማሲ በማድረግ ላይ ያሉትን አገሮች የፖለቲካ አሰላለፍና ዓለም አቀፍ ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሣት የኢትዮጵያ “አዲስ ዕቅድ” ለዕርቅ የተመቸ እንዳይሆን አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል እንዲህ በማለት ይጠቅሳሉ።
በመጀመሪያ የመካከለኛውን ምሥራቅ (በተለይም የሶሪያን ጉዳይ) ማንሳት አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም የሶሪያ ግጭት የአንድ አገር ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ ዓለምን በሁለት ጎራ እያሰለፈ ያለና ጠንቁም ወደአገራችን የመድረስ እድል ያለው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል በማለት ይቀጥላሉ።
በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጋር ለየት ያለ ዲፕሎማሲ እያደረጉ ያሉት አገሮች ቱርክ፣ ሳውዲ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬት፣ ኳታርና ግብፅ በሶሪያ ጉዳይ አሰላለፋቸው በተለያየ ጎራ ቢሆንም በዚሁ ግጭት ጠንካራ አቋም የወሰዱ አገሮች መሆናቸው ይታወቃል። በተጨማሪም የየራሳቸው የወዳጅነትና ያለመግባባት ታሪክ አለ። ለምሳሌ ቱርክና ግብፅ በአብዛኛው በመልካም ወዳጅነት የሚታወቁ ቢሆንም ከሙርሲ መወገድ ጋር በተያያዘ ግብፅ የቱርክን አምባሳደር ከአገር እስከማባረር መድረሷ ይታወቃል። በቅርቡ የረገበ እስከመሰለበት ድረስ ባሳውዲና በቱርክ መካከልም ከአረብ ስፕሪንግ የተጀመረ ያለመግባባት በግብፅ ጉዳይ በተቃራኒ ወገን እስከመቆም የደረሰ ነበር (ሳውዲ ለአልሲሲ የመንግሥት ግልበጣ በግልጽ ድጋፍ አድርጋለች ቱርክ የሙርሲን መውረድ ተቃውማለች)። ቀደም ሲል ሶሚሊያ ኳታርን በኤርትራ በኩል አልሻባብን ትረዳለች በማለት ስትከስ ነበር። ኢትዮጵያም እ. ኤ. አ በ 2008 በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በኩል በኳታር የሚገኘውን የአልጃዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በመጥቀስና የኳታርን መንግሥት “በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሽብርተኞችን ይረዳል … የኢትዮጵያን ጸጥታ ለማናጋት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም” በማለት የዲፕሎማሲ ግንኙነቷን አቋርጣ ነበር። ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ ኳታር በወያኔና በሻእቢያ መካከል ከመድረክ በስተጀርባ እርቅ ለማድረግ ጥረት እያደረገች ነው የሚል ዜና ተሰምቷል። ግብፅ ደግሞ በቅርቡ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ያለውን ውጥረት የምታባብሰው ኳታር ናት በማለት ትከሳለች። ኳታርና ግብፅ በሶሪያ ጉዳይም በተቃራኒ አቅጣጫ ናቸው። ቱርክና ሳውዲም በሶሪያ ግጭት በተቃራኒ ወገን ናቸው። ከዚህ ሌላ ሳውዲና የተባበሩት አረብ ኤምሬት የአሰብን ወደብ ተከራይተዋል። ወያኔ ደግሞ ለቱርክና ለሱዳን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም የሚያገኙበትን መንገድ በየጊዜው ሲያመቻች ቆይቷል። አሁንም እያመቻቸ ነው። በዚህ ምክንያት ወያኔ የነዚህን አገሮች መሪዎች በተከታታይ ለጉብኝት መጋበዙ ትርጉም የሚሰጥ ቢሆንም በነዚህ አገሮች መካከል ያለው ውስብስብ ግንኙነትና የየአገሮቹ ጥቅም ዕርቁን ተግባራዊ ለማድረግ የተመቸ ያደርገዋል ማለት በጣም አስቸጋሪ ነው በማለት ይተነትናሉ። የንግድ ወይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊጨርሰው ለሚችለው የዕርቅ ወይም የኢኮኖሚ ትብብር የአንድ አገር መሪ (አብዛኞቹ አገራት የራሳቸው ስጋት ያለባቸው ናቸው) በሌላው አገር ለጉብኝት መገኘቱስ ምን ያህል የተለመደ ነው? በማለት ይጠይቁና ምናልባት የታሰበው ነገር እውነት ሲሆን “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” እንዳይሆን ጠንካራ ቅድመዝግጅቶችን ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ያሰምሩበታል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s