ዩቶፒያ ኢትዮጵያ (መስፍን ማሞ ተሰማ)

“ብዙ ህልም ባለበት ዘንድ እንዲሁም ብዙ ቃል ባለበት ሥፍራ በዚያ ብዙ ከንቱ ነገር አለ።” መፅሐፈ መክብብ ምዕ፤ 5 ቁ፤ 7

**************************************

ቀባሪው የነገ ሞቱን በሟች ሞት እያየው፤ ዛሬን ሞቶ ባያድርም ሟችን ቀብሮት አሟሟቱንም አይቶታልና – ለዚህ ነበር እኒያ “አያልቅባቸው” አብናቶቻችን “አሟሟቴን አሳምረው” ማለታቸው። በሞታቸው ቋሚው እረፍት እንዳይነሳቸው፤ ሠላም እንዲሰጣቸው። ‘ኖረና ተሞተ’ን እንዳይተርትባቸው . . . አላስ! . . . ኦሮማይ!

እነሆ በዩቶፒያ ኢትዮጵያ ግና ‘ኖረና ተሞተ’ ተረት ሳይሆን ዕለት ተዕለት ዓመት ተዓመት ‘ለልማታዊው መንግሥት’ የሚከፈል ግብር ሆኗል። የምናብ ዓለሟን – ዩቶፒያ ኢትዮጵያ – የገነባው የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ገዢ በበኩሉ ‘ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ ሆኗል ፤ አሥራ አንድ በመቶ ሮኬታዊ ዕድገት ተመዝግቧል፤ ያለ ወደብ ማደግ መመንደግ ሲቻል ወደባችን ይመለስ እያላችሁ የቁራ ጩኸት አታብዙ፤ ሀብቱን በመቶ ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጥር ገበሬ ተፈጥሯል ፤ የንግድ መነሻ ካፒታል የፈለገ ሠፌዱን ይዞ ወርቅ ካለበት ሄዶ ማፈስ ይችላል፤ ኢኮኖሚያችን አስተማማኝ በመሆኑ እርዳታ ለጋሾች ሳይቀሩ ከኢትዮጵያ ላይ የርጥባን እጃቸውን ሰብስበዋል፤ በሀገረ ኢትዮጵያ በፖለቲካ አመለካከቱ የተነሳ ወህኒ የወረደ እስረኛ የለንም፤ በምድረ ኢትዮጵያ በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንድነት ፤ ፍቅርና እኩልነት ላይ የተገነባ ፌዴራሊዝም መስርተናል፤ እና ወዘተርፈዎችንም ሁሉ ይላል።

ቅዠትና ዕውነት በዩቶፒያ ኢትዮጵያ ተደባልቀዋል። ዕውነቱ ቅዠት ሲባል ቅዠቱ ዕውነት ሆኗል። ሚሊዮን ወሚሊዮናት ሲራቡ ጥቂቶች ቁንጣን ያቁነጠንጣቸዋል። አእላፍ ታዛ ሲያጡ ጥቂቶች በፈጠሩዋት ዩቶፒያ ኢትዮጵያ በተንጣለለ ቪላ በተንቆጠቆጠ ‘ማንሽን’ ውስጥ ይኖራሉ። ባይሆንማ ኖሮ በዩቶፒያዋ ኢትዮጵያ እኒያ ሁሉ ግፉዐን በቆሼ ሱናሚ ታፍነው አያልቁም ነበር። ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የህወሃት/ኢህአዴጓ ዩቶፒያ ኢትዮጵያ ተምሳሌ ናት፤ መስተዋት። በዕውኗ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የህይወት መናኸሪያ ተምሳሌ። የቆሼ ተምሳሌነቱ በድፍን ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆንም ቅሉ በተለይ እና በአስከፊ መልኩ ግን በትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር አፈሙዝ በምርኮ የወደቀው ህዝብ ህይወት ገፅታ ይንፀባረቅበታልና ወይንም ተንፀባርቆበታልና። (ፎቶው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የቆሼ ነዋሪዎች መኖሪያ ሰፈር ነው፤ ወይም ነበር)

እነሆ ደግሞ ቀጣዩ በዩቶፒያ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩት ዘመነኞች መኖሪያ እንጂ በሆሊ ዉድ ፊልሞች ወይም ለትንግርት የሚታዮት የናጠጡ ቢሊየነሮች መኖሪያ አይደለም፤ የሚገኘውም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍል ከተማ መሆኑን ልብ ይሏል። በአንድ ክፍለ ከተማ የሁለት ዓለም ነዋሪዎች ገፅታ !! * (ፎቶ 1)

እነሆ በዕውኗ አትዮጵያ ውስጥ የግፍና የሥቃዩ፤ የድህነቱና የዘር መድልዖው፤ የእስሩና የቶርቹ ፤ የምዝበራውና የፍንገላው ፤ የእናቶች ዋይታና የወጣቶች ሰቆቃ ጠርዙና ገደቡ ለፅሁፍም ሆነ ለስሚ ወይም ለንግግር ወደማይቻልበት ደረጃ ተሸጋግሯል። በተለይ በማዕከላዊ እስር ቤት ከአራቱም ማዕዘናት በታፈኑ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው የበደል የሥቃይና የግፍ ጣራ ሰው የመሆንን ተፈጥሯዊ መለኪያዎች ሁሉ የጣሰ በመሆኑ አንደበትን ከፍቶ ለመግለፅ እንኳን አልተቻለም። ለዩቶፒያ ኢትዮጵያ ገዢዎች ግና ይህ ሁሉ የህልውናቸው ዘፈን ፤ የግዛት ዘመናቸው ግብር ፤ የጀግንነታቸው ኒሻን መሆኑ እንጂ ሌላ ትርጉም አይሰጣቸውም።

የዩቶፒያ ኢትዮጵያ አጋፋሪው የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (ህወሃት) ስብሰብ ሰው ከመሆን የሰብዕና ተፈጥሮ መለኪያዎች ጠቅልሎ የወጣ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ያፈራቸው ሰዋዊ አውሬዎች ስብስብ ነው። የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (ህወሃት) ባለሟሎች በዋናነት የተገኙትም – ከአማራው አብራክ የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፤ ከኦሮሞው አብራክ  የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ)፤ ከደቡብ ብሄረሰቦች አብራክ የደቡብ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ደህዴግ) – ሲሆኑ እነሆ አጋፋሪያቸው ሲያስነጥስ እነርሱን እያሳላቸው፤ አጋፋሪያቸው ሆዱን ሲቆርጠው እነርሱን እያስቀመጣቸው፤ አጋፋሪያቸው ሲያዛጋ ከያብራካቸው የወጡትን ወጣቶች ግብር እያቀረቡ … ይኸው የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (ህወሃት) ምሶሶ ሆነውና እንኮኮ ተሸክመውት ሩብ ምዕተ ዓመት አኑረውታል። በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረው እልቂት ፤ ግፍ ፤ ሰቆቃ ፤ ቶርች ፤ የዘር ማፅዳት ፤ የሀገር ንብረት ዘረፋ እና ወዘተርፈዎች ሁሉ እኒህ የህወሃት ሎሌዎች ከህወሃት እኩል ተጠያቂዎች ናቸው። የቆሼው ዕልቂትም የህወሃትና የባለሟሉቹ ውጤት ነው።

በዚያ ቀነ ጎደሎ – ቅዳሜ መጋቢት 2 ፤ 2009 ዓ/ም ሌሊት – (መቼም ቢሆን ባለፈው ሩብ ምዕተ ዓመት ለኢትዪጵያውያን ሞልቶ አያውቅም) በዚያ የቆሼ ናዳ ታፍነው በሲቃ ያለቁትን ህፃናት፤ እናቶች፤ አረጋውያንና ወጣቶች ጣዕር እንደው ለሚሊ ሰከንድ እንኳ ሰቆቃውን በእዝነ ህሊና ለማየት የሚቻል ከሆነ እነሆ አንባቢ ሆይ ይህንን ታደርግ ዘንዳ እጠይቅኻለሁ……..አፍህን ግጠም አፍንጫህንም በሁለት ጣቶችህ ግጥም አድርገህ ያዝ እና ቆይ ……. ለምን ያህል ሰከንድ ቆየህ? ምን ተሰማህ? ልብህ ከደረትህ ልትፈነቀል ስትንደፋደፍ  ደምህ ወዳናትህ ሲምዘገዘገ አልተሰማህም? ጭንቅ ጥብብ አላለህም? እንግዲህ በዚያ ድቅድቅ ጨለማ እንደጨለማ የጠቆረ ቆሼ አፍኗቸው መሪር በሆነ ሲቃና ጣዕር ታፍነው ያለቁትን ወገኖቻችንን ሞት እንደምን “ሞት” የሚለው ቃል  ሊገልፅላቸው ይችላል?! አዎ ቀደምቶቻችንን መስማት ካቆምንና ታሪካቸውን ክደን ማዋረድ ከጀመርን አምስት አሥርታትን አስቆጠርንና አንጂ እነሱስ “አሟሟቴን አሳምረው” ብለው ነበር። ደግሞም እስከዛሬ ምሥጢሩ ያልሰረፀብንን ዘመን አይሽሬ ፍልስፍና እንዲህ በማለት አስተምረውን ነበር – እናት አባት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል / እህት ወንድም ቢሞት በሀገር ይለቀሳል / ሀገር የሞተ’ለት ወዴት ይደረሳል?! – ለመሆኑ ያለ ምክንያት ይሆን እንዴ የተረቱት? “ኖረና ተሞት” መባሉስ ምሥጢሩ እስከምን ገብቶናል? ለመሆኑ እኛ ኢትዮጵያውያን (በተለይም በዚህ ዘመን) ኖረን እምንሞተው መቼ ነው?!

ዕውነት ነው የዕውኗ ኢትዮጵያውያን “ከሞቱት በላይ ከቆሙት በታች” (አበው እንዳሉት) ሆነን መኖር የጀመርነው በተለይና በዋናነት ዩቶፒያ ኢትዮጵያ ከተመሰረተችበት ዘመን አንስቶ ነው ፤ 1983 ዓ/ም። እነሆ ባሳለፍናቸው ሁለት ዓሥርታት ተኩል ቆሼ በህወሃት/ኢህአዴግ ዘመነ አገዛዝ የምንገኝበትን አኗኗራችንን እና አሟሟታችንን ማሳያ ሐውልታችን ሆኗልና ከቶም ሌላ ምሳሌ አናነሳም።  ቆሼ ለታሪክ ነጋሪ ካበቃቻቸው አንዱ አሸናፊ እንዳለ የተባለ ወጣት ነው። እርሱ ያንን የቆሼን የሰቆቃ ህይወት ኖሮታል ፤ የቆሼን ቁጣ ግን አምልጧል። ቆሼ ተወልዶ ቆሼ መኖር ምን እንደሆን ለጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን እንዲህ ብሎታል።

ክፉ ነው ደሃ መሆን (ለቆሼ ሠፈር ልጆች) የችግሩ ጥግ ቆሻሻ ላይ የላስቲክ ቤት ያሰራሃል፡፡ መሠረት ስለሌለህየሚያውቅህ የሚያስብልህ መንግስት አይኖርህም፡፡ ጥሩ መልበስ ንፁህ መብላት ያንተ የልብ መሻቶች አይሆኑም፡፡አንገትህን ደፍተህ ነገን ትናፍቃለህ፡፡ ተፈጥሮ ፊቷን አዙራብህ ስትፍጨረጨር ሠዎች በፈጠሯቸው ተልካሻ ምክንያቶችሕይወትህ ያልፉል፡፡ ቤትህ ተንዶ ማቅ ላይ ብትሆን እንኳን ጩኸትህን የሚሰማ አምቡላንስ እንጂ የሚያድን ወገንየለህም፡፡ ምክንያቱም አንተ ደሃ ነህ! ‹‹ምስኪን›› (ትርፍራፊ) እየበላህ ያደክ የተማርክ ደሃ ! ይሄ ነው የኔና የሠፈሬልጆች ኑሮ፡፡ ይሄም ኑሮ ሆኖ ይሄ ሁሉ ሃዘን ታዲያ ስለምን? … ዳሩ አንድ ቀን እንደ ሠው የምንታይበትና የምንኖርበትቀን ይመጣል፡፡ የሟቾቹ ቁጥር ከፍና ዝቅ ማለት አይጠቅመንም፡፡ … ለሞቱት ነፍስ ይማርልን ! … በጣር ላይ ላሉትምእግዚአብሔር ይሁናቸው፡፡ ወይ ቆሼ ምግባችንም፤ ሞታችንም አንተው ትሆን ! …›› *(2)

 

ይሀ አንጀት የሚበላው ገለፃ የቆሼ ህይወት ገፅታ ነው። ይህ ደግሞ የሚሊዮናት ኢትዮጵያውያንም ህይወት ነፀብራቅ ነው። የዩቶፒያ ኢትዮጵያ ገዢዎችና ዝርያዎቻቸው ግን ይህንን ህይወት አያቀውቁትም። ለእነርሱና ለዝርያዎቻቸው የማይገባውን እንዲህ ያለ አኗኗርና አሟሟት መኖሩን ሰምተው ለሞቱት የሀዘን ቀን ቢያውጁም ሀዘኑ ተሰምቷቸው ኑሮውም ገብቷቸው ግን አይደለም። እነርሱ የሚኖሩት በዩቶፒያ ኢትዮጵያ ነውና!!

ቆሼ በዩቶፒያ ኢትዮጵያ ለሩብ ምዕተ ዓመት የሰፈነው የኢፍትሃዊው ዘረኛ አገዛዝ ውጤት ነው። በቆሼው ዕልቂት እንደ ሀገር እና እንደ ህዝብ ቅስማችን ተሰብሯል። ኢትዮጵያ ከዚህ የከፋ ቅስም ሰባሪ ሀዘን ሊገጥማት አይችልም። በዩቶፒያ ኢትዮጵያ የሰፈነው አግላይና ጨቋኝ፤ ግፈኛና ዘራፊ፤ እኩይና ጨካኝ ፤ ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ ኢትዮጵያውያን … የጥፋቶችና የክፉ ተግባራት ሁሉ ቁንጮ የሆነ ሥርዐት ነው – የህወሃት/ኢህአዴግ ሥርዐት።

ይህ ሥርዐት ከወልቃይት እስከ ቦረና ከጋምቤላ እስከ ሐረር ሲገድል ሲያስገድል ሲያስር ሲያሳድድ ሲያፈናቅል ሲዘርፍ ሲያዘርፍ በንፁሀን ደም እየዋኘ በእናቶች እንባ እየታጠበ ሩብ ምዕተ ዐመት ጨርግዶ እነሆ ደግሞ ለሁለተኛው ሩብ ምዕተ ዓመት ሀሌታ ደርሷል። እነሆ ደግሞ የቆሼ ደም ይጣራል ፤ የሆራ ቢሾፍቱ ደም ይጣራል ፤ የወልቃይት ፀገዴ ደም ይጣራል ፤ የአኝዋኹ ደም ይጣራል ፤ የኮንሶው ደም ይጣራል … እንግዲህስ አይበቃንም እንዴ?! ወይስ ሰቆቃችን ገና ይቀጥላል ?!

*****************************

ተፃፈ ሚያዚያ 2009 ዓ/ም

ኤፕሪል 2017

ሲድኒ አውስትራሊያ

mmtessema@gmail.com

ማጣቀሻ

*(ፎቶ1) – ከጎልጉል ድረገፅ ጋዜጣ ፎቶ ከነማብራሪያው የተወሰደ ፤ http://www.goolgule.com/regardless-of-tplfs-cover-up-the-drought-is-escalating-and-schools-are-closing/

*(2) ከጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ፌስ ቡክ የተገኘ፤

https://www.facebook.com/getu26/posts/1544759092230993

* ቁጥር ያልተሰጣቸው ፎቶዎች በቆሼ ሱናሚ ካለቁት ጥቂቶቹና የህዝቡ ሀዘን ከታየባቸው – ከሶሻል ሚዲያዎች የተገኙ ናቸው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s