አንድ ሀገር ከብዙ አመታት በፊት እቆመበት ቦታ ላይ አሁንም እንዴት ሊቆም ይችላል? – ሸንቁጥ አየለ

 

 

ከዛሬ ሶስት እና አራት አመታት በፊት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጥቁር ሰዉ አልበሙን ሲያወጣ በማህበራዊ ሚዲያዉ እና በግል ጋዜጦች ላይ ኢትዮጵያዉያን ከፍተኛ ጭቅጭቅ ዉስጥ መዉደቃችን ይታወሳል:: ዛሬም ቴዲ አፍሮ አዲስ ካሴት ሲያወጣ ኢትዮጵያዉያን እዚያዉ እነበርንበት ጭቅጭቅ ማጥ ዉስጥ መልሰን ተዘፍቀናል::ከዛሬ ሶስት እና አራት አመታት በፊት እነበረዉ ጭቅጭቅ ዉስጥ እኔም ተሳታፊ ነበርኩና በግል ጋዜጦች እና በማህበራዊ ሚዲያዉ ላይ የጻፍኩትን ጽሁፍ አሁን መለስ ብዬ ሳነበዉ በጣም ገረመኝ::አሁን ለተነሳዉ ጭቅጭቅ የጻፍኩት ይመስላል::

አንድ ሀገር ከሶስት እና አራት አመታት በፊት እቆመበት ቦታ ላይ እንዴት አሁንም ሊቆም ይችላል? እዚያዉ ላይ መቸከል? ለነገሩ ተገረም ብሎኝ እንጅ ኢትዮጵያን ወያኔ 26 አመታት ሙሉ ቸክሏት ያለዉ አንድ ቦታ ላይ ነዉ::

አለም በፈጣን ግስጋሴ በቴክኖሎጅ ለዉጥ ዉስጥ በዬ ደቂቃዉ ይፋጠናል::ሌላዉ ቀርቶ በወራት እና በሳምንታት ዉስጥ ሊታመኑ የማይችሉ የቴክኖሎጅ ለዉጦች ይከሰታሉ::የአለም ማህበረሰብ እሩጫዉ እና ግስጋሴዉ ከነዚህ ለዉጦች ጋር እራሱን ለማስተካከል ነዉ:: አለም በፈጣን የቴክኖሎጅ ግስጋሴ እየታገዘ ወደ አስገራሚ ብልጽግና እየገሰገሰ ነዉ::

እኛስ ? እኛማ ጉደኞቹ ትናንት ላይ ተቸክለን ላለመስማማት ከፍተኛ ማጥ ዉስጥ ሰጥመናል::እግዚአብሄር እንደ ወያኔ አይነት ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን የሚዘራ ወንበዴን ሀይልን በላያችን ላይ ጉልበት ሰጥቶብን ሀያ ስድስት አመታት ህዝብ በጭቅጭቅ ይናጣል:: ዛሬም አባቶቹን በሚረግም እና አባቶቹ እንዳይረገሙ በሚከላከል ትዉልድ መሃከል ኢትዮጵያ ተቀስፋ ተይዛለች::ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት በሚቃትት እና ኢትዮጵያዊነት እሴቴ ከቶም አይነካም በሚል ትዉልድ መሃከል ሀገሪቱ ተቀስፋ ተይዛለች::

ወያኔም በዚህ መሃል በደናቁርት ልቡ በሚያጠነጥናት ተንኮሉ እየታመነ እግሩን አንፈራጦ ሰይጣናዊ አገዛዙን የሚያስቀጥልበትን ስልት በጥልቀት ከተከፋይ የዉጭ አማካሪዎቹ ጋር ሆኖ ያንሰላስላል:: ለማንኛዉም በቀለም ቀንድ (2006 ዓ.ም በቅፅ 01) ላይ የወጣዉን ጽሁፌን ለተግርሞአችሁ እንዲሆን እንዲሁም እንዴት አሁንም አንድ ቦታ እንደተቸከልን እንድታንሰላስሉበት ብዬ አካፈልኳችሁ::

መልካም ንባብ::

=======================================

ኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት የስነ ጥበብ ማዕከል ሲሆን ለምን ጦር ሰባቂ ይበዛል?:- ቴዲ አፍሮን እንደ ማሳያ

ሸንቁጥ አየለ

—————————————————————————————————————————–

ስነ ጥበብ እንደ ስሙዋ መልኩዋና አገልግሎቱዋ ብዙ ነዉ:: አምባገነኖች ለራሳቸዉ ፍላጎት ይጠመዝዙዋታል:: እንዲያዉም

የሶሻሊስት ርዕዮተ አለም የሚያራምዱ ጥበበኞች እንደሚነግሩን ከሆነ ሶሻሊስታዊ ስነ ጥበብ አለች:: ይህች ስነ ጥበብ ታዲያ ዋና ግቡዋ ሶሻሊዝምን ማራመድ እና ወደ ህዝቡ አዕምሮ ዉስጥ ሶሻሊዝምን ከመክተትም በዘለለ የህዝቡ ስነ ባህሪ በሶሻሊስታዊ መርህ እንዲታነጽ ማድረግ ነዉ:: ብልህ ምዕራባዉያን መንግስታት የሀገራቸዉን እሴት በመላዉ አለም ለማሰራጨት ብሎም የሀገራቸዉን ሀያልነት ለመስበክ ይገለገሉባታል:: የሆሊዉድን የፊልም ስራዎች ማስተዋል በቂ ነዉ:: የሆሊዉድ ፊልሞች ምዕራባዉያን ሲያሸንፉ

ብሎም የእነሱ ባህላዊ እሴት ፍጹም የበላይ መሆኑን ለመላዉ አለም እንደሰበኩ ይኖራሉ::

አንዳንድ ባለ አዕምሮ የስነጥበበ ባለሞያዎች ደግሞ ስነጥበብን የሰዉ ልጆችን እኩልነት ለማራመድ እንደ ቁልፍ መሳሪያነት

ይጠቀሙባታል:: አንዳንድ የዋሆች እንደሚመስላቸዉ የስነ ጥበበ ሞያተኞች ከወገናዊነት የነጹና አቁዋም አልቦ ይመስሉዋቸዋል:: ስነ ጥበበኞች ግን በዚህኛዉም ሆነ በዚያኛዉ ወገን ወይም በራሳቸዉ ማዕከላዊ ዛቢያ ላይ ቢሽከረከሩም ከወገናዊነት እና አንድን ጭብጥ ከማራመድ ነጻና ገለልተኛ መሆን አይችሉም::

በአሁኑ ዘመን ያሉ ኢትዮጵያዊ የስነ ጥበበ ባለሞያዎችን በሶስት ጎራ ከፍለን ልናያቸዉ እንችላለን:: አንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትና

በርከት ያሉት ያለዉን ስርአት ለማገልገል ብቻ የሚኖሩ ናቸዉ:: ሌላም ስርዓት ቢመጣም መልሰዉ ስርዓቱ እንደሚፈልገዉ

የሚያገለግሉ ናቸዉ:: ምንም አይነት የተለዬ ስርዓት ቢመጣ ትናት ጥቁር ያሉትን ዛሬ ነጭ ብለዉ ለማቅረብ አይቸገሩም:: እነሱ

አቁዋም የምትባል ነገር የላቸዉም:: በአንድ ወቅት ስለ አንድ ዘፋኝ አንድ የሀገራችን ፖለቲከኛ ሲጠየቅ የጨመሩባቸዉን ነገር እንደ

ማንቆርቆሪያ ማንቆርቆር ብቻ ነዉ ስራቸዉ እንዳለዉ::

ሁለተኞቹ ቡድኖች ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ የጎሳ ብሄረተኝነተ እሴትን ማዕከላቸዉ ያደረጉ ናቸዉ:: ፈጹም የራሳቸዉ አቁዋም

አላቸዉ:: ኢትዮጵያ የጋራ እሴት አላት ብለዉ አያስቡም/አያምኑም:: ኢትዮጵያ ሀገር ናት ብለዉም አያምኑም:: በርቀት ህልማቸዉ

ኢትዮጵያ ብትፈርስ ደስተኛ ናቸዉ:: ሶስተኞቹ ቡድኖች ደግሞ ኢትዮጵያዊነት እሴትን የስነ ጥበብ ስራቸዉ ማዕከል ያደረጉ ናቸዉ:: በእነዚህ ቡድኖች ህሳቤ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የጋራ ማንነት ያላት ከሰዉ ዘር መነሻ እስከ አሁን የቀጠለች ሳባዊት ኩሻዊት ካማዊት እሴት የተዋሃደባት ብሎም ክርስትና እስልምና አይሁድነት አብሮ ተለዉሶ የወጣባት ኢትዮጵያ አለች:: እነዚህ የስነጥበብ ሀይሎች ሀይለኛ ናቸዉ:: ለያዙት አላማም የማያወላዳ ፍልስፍና አላቸዉ:: ሀገሪቱ መከራ ዉስጥ በወደቀችበት ጊዜና ህዝቡ

በሚደናገርበት ሰዓት ስለ ኢትዮጵያዊነት በማቀንቀን የህዝቡን ህብረት ሲስብኩ ተስተውለዋል:: እንዲህም ይላሉ:: “ቢለያይም

ቁዋንቁዋ አንድ ነዉ ደማችን ..” ብለዉ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ሳያፍሩና ሳይሸማቀቁ ያቀነቅናሉ::

ስለ ሌሎቹ ሌላ ጊዜ እመለስበት ይሆናል:: ለዛሬ ግን ቴዲ አፍሮ ላይ ማተኮር ፈልጌአለሁ:: ምክንያቴ ደግሞ ቴዲ አፍሮ የሰሞኑ የጭብጨባ ወጀብ ብቻ ሳይሆን የዱላም መዓትም

እያረፈበት ያለ የጥበብ ሰዉ በመሆኑ ነዉ:: ቴዲ አለም ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ ሊሳተፍ ሲልም ሆነ አሁን ከኮካ ኮላ ጋር ተጣላ

ሲባል እየተነሳ ያለዉ አቡዋራ ምክንያቱ አንድና አንድ ነዉ:: ቴዎድሮስ ካሳሁን ኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴትን ማዕከሉ አድርጎ መዝፈኑ

ነዉ:: በቴዎድሮስ ካሳሁን የማይናወጥ እምነት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የጋራ ማንነት ያላት ከሰዉ ዘር መነሻ እስከ አሁን የቀጠለች

ሳባዊት ኩሻዊት ካማዊት እሴት የተዋሃደባት ብሎም ክርስትና እስልምና አይሁድነት አብሮ ተለዉሶ የወጣባት ሀገር ነች:: በዘፎኖቹ

የሚሰብከን ይሄን ነዉ::

ጥያቄዉ ግን ቴዲ አፍሮ እንዲህ ስለ ህዝብ ዉህድነት ሲሰብክ ለምን ጦር ሰባቂዎች በዙበት የሚለዉ ነዉ?

ቴዲ አፍሮ የጠለቀ ጭብጥ በቁዋጠሩ ሙዚቃዎቹ እንደሚነግረን ኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት አለዉ:: ይህ የጋራ ኢትዮጵያዊ እሴት

አይሁዱን: እስላም ክርስቲያኑን ያፋቅራል::ይህ የጋራ ኢትዮጵያዊ እሴት ጥንታዊና ስር የሰደድ የጋራ ምድር ያለዉ የጋራ ታሪካዊ

መሰረት ያለዉ ዉህድ ኢትዮጵያዊ ህዝብን አስተሳስሮ አቁሞአል:: ኢትዮጵያዊነት ለቴዲ አፍሮ የጎሳዎች ድምር ሳይሆን

የኢትዮጵያዉያን ማህበረሰብ ዉህደት ነዉ::ይህ ዉህደት ደግሞ ከድምር የበለጠ የጋራ መስተጋብር ነዉ (the whole is greater

than the sum)::

ይህ ማለት ለቴዲ አፍሮ የሀሳብ ማጠንጠኛዉ ብሎም መድረሻ ራዕይዉ ዉህድ የሆነዉ ኢትዮጵያዊ እሴት ነዉ::

ቴዲ ከሙዚቃ በላይ በገዘፈዉ ጭብጡ የሚያስተላልፈዉ የጋራ ኢትዮጵያዊ እሴት መልዕክቱ አንድ ነዉ:: ይሄዉም ህያዉ የሆነ ቆሞ

የሚሄድ እና የሚራመድ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ የተገነባና በዉህደት የተሰራ ኢትዮጵያዊነት ነዉ:: ለዚህ ማሳያዉ የአድዋ

ድልን የገለጸበት የተራቀቀ ዘይቤ ነዉ:: ቴዲ አፍሮ እንደሚተርክልን ያ ድል የዚህ ወይም የዚያ ብሄረሰብ/ማህበረሰብ ድል ሳይሆን

የሁሉም ዉህድ ማህበረሰብ ድል ነዉ:: ኢትዮጵያዊ ማህበረሰቦቹን በጀግኖቻቸዉ ወክሎ ዉህድ ሂደቱን ግን ከድምር በዘለለ

ያቀርበዋል:: ይህን የገለጸዉ በዉህዱ ኢትዮጵያዊነት ዘይቤ ነዉ::

በዚህ የአድዋ ዉህድ ድልም የኢትዮጵያዊነት የጋራ ማንነት ተጠብቆአል:: ከዚህም ዘሎ ቴዲ እንደሚተርክልን የመላዉ የጥቁር ዘር

ቀና ብሎ በማንነቱ እንዳያፍር ዉህዱ ኢትዮጵያዊ ህዝብ ታሪክ ሰርቶአል:: የአሜሪካዉ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር እንዳሉትም

የአድዋ ድል የለወጠዉ የመላዉን የአዳምን ዘር የታሪክ ፍሰት ነዉ:: በፕሮፌሰሩ ታሪካዊ ትንታኔ መሰረትም የአድዋ ድል የመላዉ

የጥቁር ዘር አዲስ የማንነት ዉልደት ምዕራፍ ነዉ:: ቴዎድሮስ ካሳሁን ከፕሮፌሰሩ ጋር የመከረ ይመስል የፕሮፌሰሩን ሀሳብ አንድ

በአንድ በሙዚቃ ሰንቆ አቅርቦታል:: የሚገርመዉ የቴዎድሮስ ካሳሁን ግጥም የተጻፈዉ ፕሮፌሰሩ መጽሃፋቸዉን ከማሳተማቸዉ

በፊት ነበር:: ፕሮፌሰሩም ቢሆኑ መጽሃፋቸዉን ያሳተሙት የቴዲን ዘፈን ሰምተዉ አይደለም:: የራሳቸዉን ምርምር አድርገዉ እንጅ::

ቴዲ አፍሮ ስለጥንታዊ ሳባ: ስለ ባህረነጋሽ: ስለ ታላላቅ የህዝብ ዉህደት ሂደቶች እንዲሁም ሁለቱ የሀገሪቱ ታላላቅ እምነቶች እንዴት

ተቻችለዉ በጋራ እንደ ኖሩ ለማሳዬት ይባትታል:: ቴዎድሮስ ካሳሁን ልዩ ልዩ የሀገሪቱን ቁዋንቁዋዎች በአንድ አቀናብሮ ለማሳዬት

በተቻለዉ ይሞክራል::

ኢትዮጵያዊነት እሴት ልባቸዉን ቀስፎ የያዛቸዉ ወገኖች ያጨበጭባሉ:: አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች ጥርሳቸዉን

ይነክሳሉ:: ጥርሳቸዉን ነክሰዉም አይቀሩም ጦር በዚህ ሰዉ ላይ ይወረዉራሉ:: አድዋ ባርነትን እንጅ ምን አተረፈልን ሲሉ በነጭ ቅኝ

ባለመገዛታቸዉ እየተቆጩ ይጽፋሉ:: ያባቶቻቸዉን ታሪክ በሙሉ በእግራቸዉ ረግጠዉ ከኢትዮጵያዊ የጋራ ማንነት ይልቅ

በኢትዮጵያዉያን መሃከል ልዩነትና ጥላቻ ከፍ ብሎ ይዉለበለብ ዘንድ አበክረዉ ይሰራሉ::

ቴዎድሮስ ካሳሁን የተሸከመዉ እሤት ኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት አለዉ ብሎ ለሚያምነዉ ኢትዮጵያዊ ወገን የኩራት ምንጭ ሲሆን

ኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት የለዉም: ኢትዮጵያዊነት አቀንቃኞች መደምሰስና መጠረግ አለባቸዉ ብለዉ በአቁዋም ለጸኑ አክራሪ የጎሳ

ብሄረተኞች ግን የብስጭት ምንጫቸዉ ነዉ:: ለዚህ በቂ ምክንያት አላቸዉ:: አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች ዋናዉና የመጨረሻ ግባቸዉ አንድ ብቻ ነዉ:: እሱዉም ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ተረት ተረት ናት ስለሆነም መገነጣጠል አለባት የሚል የማያወላዉል እና የማያወላዳ አቁዋም አላቸዉ:: ሆኖም ይሄን የመጨረሻዉን ግባቸዉን ወደ መድረክ

ከማቅረባቸዉ በፊት ሊሰሩዋቸዉ የሚገቡ የደረጃ በደረጃ የቤት ስራዎች አሉዋቸዉ:: እነዚህን የደረጃ በደረጃ የቤት ስራዎች ልዩ ልዩ

ኢትዮጵያዊ ማህበረሰቦች/ብሄረሰቦች በደንብ እንዳይረዱዋቸዉ ማደናገሪያ ዘዴዎች አብጅተዉላቸዋል:: ህዝቡ የሚያስተዉላቸዉ

በብዥታና በድንግርግርም እንዲሆን ህዝቡን በልዩ ልዩ መልክ ያደናግሩታል:: ከማደናገሪያቸዉ ዋና ዋና ነጥቦችም:-

-ኢትዮጵያ የሚባል ወጥ ህዝብ የለም:: ኢትዮጵያ እያለ የሚጮህዉ ይሄኛዉ ወይም ያኛዉ ማህበረሰብ ብቻ ነዉ:: ሆኖም ኢትዮጵያ

እያሉ መጮህ ትምክህት እና ጊዜዉ ያለፈበት የሞኞችና የሁዋላ ቀሮች ባህል ነዉ:: ኢትዮጵያ የሚባለዉ ሀገር በመቶ አመት ዉስጥ

የተፈጠረ ተረት ተረት አገር ነዉ::ጥንታዊ ታሪክ አለዉ እሚባለዉ የፈጠራ ድርሰት ነዉ:: አሁን የምናያት ኢትዮጵያ በምኒልክ በቅኝ

ግዛት የተፈጠረች ሃገር ነች::

-ይሄኛዉ መሬት የእኛ መሬት ብቻ ነበር:: እነ እከሌ መጥተዉ ወረሩን:: ስለዚህ እነዚህን ከዚህ መሬት ላይ ጨፍጭፈን እናባራቸዉ::

-ይሄኛዉ ህዝብ መጤ ህዝብ ነዉ:: ነዋሪና ባለቤቶች እኛ ነን:: በመሆኑም በሀገሩ ላይ ያለዉ ሀብት ሁሉ ለእኛ ይገባል:: አሁን እዚህ ከተማ ዉስጥ ፎቅ ሰርተዉ እና ሱቅ ከፍተዉ ልዩ ልዩ ንግዶችን አከናዉነዉ ሀብት ያፈሩ ማህበረሰቦች በሙሉ ሃብታቸዉን ያፈሩት

በዘረፋ ነዉ:: ስለሆነም እዚህ ከተማ የሚነግደዉ ማህበረስብ የኛ ወገን ስላልሆነ የሰራዉ ሱቅ : የሰራዉ ፎቅ እና ያፈራዉን ሀብት

ሁሉ ተወላጁ እጣ ተጣጥሎ ሊወርሰዉ ይገባል::

– እኛ እንዲህ ተበድለናል እነዚያ ደግሞ እንዲህ ተበድለዋል:: ስለሆነም ሀገሩን በጋራ እናፍርሰዉ::

– ሀገሩ ሲመራና ሲተዳድር የነበረዉ በአንድ ማህበረሰብ ሆኖ የኢትዮጵያ ታሪክም ምንም የጋራ እሴት የለዉም:: ህዝቡም

አልተዋሃደም:: ለምሳሌ ንጉሰ ነገስት አጼ ኃይለስላሴ እንዲሁም ንግስት ኢሌኒ የብዙ ኢትዮጵያዊ ዉህድ ዉጤት ናቸዉ የሚባለዉ

ሀሰትና ተረት ተረት ነዉ::

– ከዚህኛዉ ማህበረሰብ ጋር አትጋቡ:: ከዚህኛዉ ማህበረሰብ ጋር ከተጋባችሁ ግን የማህበረሰባችሁ ጠላት ናችሁ::

-ስለ ኢትዮጵያ አንድነትና ታሪክ የሚያቀነቅኑ ኢትዮጵያኒስቶችን ማሸማቀቅ አለብን

በነዚህ ሁሉ ማደናገሪያዎች ግን ጥላቻን ስለመርጨታቸዉ እርግጠኛ መሆን ይፈልጋሉ:: ኢትዮጵያዉያን ሆድ እንዲባባሱ

ማድረጋቸዉን ማረጋገጥ ዋናዉ ስራቸዉ ነዉ:: እናም አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች ቅደመ መገንጠል ስራቸዉን በድንብ ሳያርፉና

ሳይታክቱ እየሰሩ ነዉ:: አልደከሙም አልታከቱም:: የትም ቢሆኑ አቁዋማቸዉ አንድ ነዉ:: አይወላዉሉም:: በኢትዮጵያ ምደር

ቢመቻቸዉም ባይመቻቸዉም: የመጨረሻዉ ጣሪያ ላይ ቢደርሱም: ከስር ቢሆኑም: በዉጭ ሀገር ቢኖሩም ይህችን የመገንጠል

ህልማቸዉን አይተዋትም:: በስነልቦናቸዉ እራሱ ከብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ግንጥል ናቸዉ:: እናም ጠንክረዉ ይሰራሉ:: ስራቸዉ የደረጃ

በደረጃ የቤት ስራ እንዳለበት ጠንቅቀዉ የተረዱት ከረዥም ጊዜ የትግል ልምድ ብሁዋላ ነዉ::

ለምሳሌም በቁዋንቁዋ : በታሪክ : በባህል: በእምነት በመልክዓምድር በስነልቦና ከብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ጋር አንድ የነበረዉ የኤርትራ ህዝብ በአክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች የሀሰት ፕሮፖጋንዳና ነገን ባላገናዘብ መልክ እንዴት የተለዬ ህዝብ ተብሎ እንደሄድ በደንብ አጥንተዋል:: ምንም እንኩዋን ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል እንጅ ኢትዮጵያ ቅኝ ያልገዛቻት ሀገር መሆኑዋን ልባቸዉ ቢያዉቅም ኤርትራ በኢትዮጵያ ቅኝ የተገዛች አገር የሚለዉ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በደንብ እንደሰራ አስተዉለዋል:: ሆኖም ይሄን ፕሮፖጋንዳ በደንብ መሬት ለማዉረድ እረዥም አመታት አስፈላጊ እንደነበረና የኤርትራን ህዝብ ኢትዮጵያዊ አይደለም ብሎ ለማሳመን ጊዜ ፈጅቶ አንደነበረ በደንብ አስተዉለዋል:: ለዚህም የስነጥበብ ድርሻ ከፍ ያለ እንደነበር ተሞክሮን ከኤርትራ ወስደዋል::

እናም አሁን ኢትዮጵያ በዝግታ ትፈርስ ዘንድ ትግል የያዙ የጎሳ አክራሪ ሀይሎች ሞኝ አይደሉም::

በጣም ብልህና ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ሀይሎች ናቸዉ:: ደግሞም ልምድ የሚያካፍላቸዉ አለ:: የትግል ልምዳቸዉ በደንብ እንደነገራቸዉ እና እንዳስረዳቸዉ

ኢትዮጵያዊነት እጅግ ዉህድነት ስለሆነ በቀላሉ ብትንትኑን ማዉጣት እንደማይችሉ ተረድተዋል:: አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች

በልባቸዉ የማይክዱት ሀቅ አለ:: ይሄዉም ኢትዮጵያዊነት ዉህድነት መሆኑን:: ኢትዮጵያዊነት

አይሁድነትን ; ክርስትናን እና ሙስሊምነትን ጠምዝዞ ዉህድ ኢትዮጵያዊ እሴትን የማልበስ አቅምና ጉልበት ያለዉ ታላቅ ሚስጥረ

መሆኑን አክራሪዎቹ የጎሳ ብሄረተኞች ተረድተዋል:: እንዴዉም በድንብ አድርገዉ አጥንተዉታል::

ደግሞም አሁን ሌላ የተረዱት ነጭ እዉነት አለ:: ይሄዉም ኢትዮጵያዊነት ስሜት እና ለጋራ ኢትዮጵያዊ እሴት ተቆርቁሮ የመቆም

ጉልበት ከህዝባችን ዉስጥ ሲሙዋሽሽ አስተዉለዋል:: በድንብ ተረድተዋል:: በዚህም ልባቸዉ ተነፍቱዋል:: በከፍተኛ የድል ተራራ

ላይ የወጣ ስሜትን ለብሰዋል:: እናም ከንግዲህ አንዳንድ የቀሩ እንጥፍጣፊ ኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚያዉለበልቡ የሚያርገበግቡ

ግለሰቦች ከመጡ እንዳያንሰራሩ አድርጎ መሰባበር ወሳኝ መሆኑን አስምረዉበታል::

የኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት እሴትን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ የሚደረግ የርብርቦሽ ስራ ብቻ እንደቀራቸዉም መክረዋል::

እናም ቴዲ አፍሮ ብቻዉን በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያዊነት የብሄረተኝነት እሴትን: የዚህችን ጥንታዊትና ባለታሪክ ሀገር የጋራ እሴትን

ከፍ አድርጎ ሲዘምር አስተዋሉ:: ወደ መጨረሻዉ ግብ ተራመድን ሲሉ እንኩዋን ለኢትዮጵያ ለጥቁር ዘር በመላ መኩሪያ ይሆን ዘንድ

ታሪክ የሰሩትን ታላቁን ዳግማዊ አጼ ሚኒልክን በጋራ የሀገር እሴትነት ወክሎ ብቅ አለ:: ስንት ቢሊዮን ብርና ሰዓት አፍሰዉ ቀበርነዉ

ያሉትን ታሪክ እፍ ብሎ ብድግ አድርጎ ወደ ህዝብ ሲያቀርበዉ የኢትዮጵያ ህዝብ አስደንጋጭ በሆነ ደስታ ተቀበለዉ:: ያኔም አክራሪ

የጎሳ ብሄረተኞች ተበሳጩ:: ስለ ጥንታዊት ሳባ ሲያቀነቅን ተረት ተረት ታሪክ ያወድሳል ሲሉ ጣት ቀሰሩበት:: ስለ ሙስሊምና

ክርስቲያን ፍቅርና ህብረት ሲያቀነቅን ምን ህብረት አላቸዉ ሲሉ መግለጫ አወጡበት:: አንዳንዶች ለክርስትና የተቆረቆሩ መስለዉ

ሌሎች ለእስልምና የተቆረቆሩ መስለዉ መግለጫ አወጡበት:: ሆኖም ግባቸዉ አንድ ነበር:; ዉህድ ኢትዮጵያዊነት እንዳይሰበክ እና

የጋራ ኢትዮጵያዊ እሴት እንዳይሰበክ ነበር:: ቴዲ አፍሮን የጠሉት እነሱ የሚያቀነቅኑትን የጎሳ እሴት ከመሸከም ይልቅ የኢትዮጵያዊነት

እሴት ስለተሸከመ ብቻ ነዉ::ቴዲ ኢትዮጵያዊነት ሞቴ ነዉ ብሎአል::ኢትዮጵያዊነት ትምክህቴ ነዉ ብሎአል:: አክራሪ የጎሳ

ብሄረተኞች ደግሞ ሞት ለኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት ብለዋል::

ቴዎድሮስ ካሳሁን አሁንም በኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት ዙሪያ መዞሩን ቀጠለ:: ስለ ፍቅር ይዘምራል ስለ ታላላቅ ኢትዮጵያዊ

አባቶቻችን ይሰብካል ስለ ጥንታዊት ኢትዮጵያ ያቀነቅናል:: አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች ተረት ተረት ስለሚሉት ኢትዮጵያዊ የጋራ እሴት

ሁሉ በማንሳት ኢትዮጵያዊነት የሚያማልለዉን ኢትዮጵያዊ ህዝብ በሀሴት ዳንኪራ ያስረግጣል:: እናም አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች

ተበሳጩ:: አሉም ከእንግዲህ ብዙም ኢትዮጵያዊነት ብሄረተኝነትን የሚያቀነቅኑ ሰዎች ስለሌሉ እየነጠልን ቴዲን ማጥቃት ተገቢ ነዉ

ሲሉ በትር አነሱ:: እናም ቴዎድሮስ ካሳሁን አሁን የጥቃት ኢላማቸዉ ሆኑዋል:: የማህበረሰብ ድረገጾችን እንዲሁም ማንኛዉንም

ሚዲያ በመጠቀም በቴዲ ላይ የስድብ ናዳ ይዘንባል::

ደግሞም ሰሞኑን ከብራዚል የአለም ዋንጫ ተሳታፊነቱ መስተጉዋጎሉ ተአምራዊ ዳንኪራን ፈጥሮላቸዋል:: አንዴ በዘረኝነት ይከሱታል

ሌላ ጊዜ በችሎታ ማነስ:: አስከትለዉ ደግሞ በምኒሊካዊነት:: ሲብስባቸዉም የኢትዮጵያን የሀሰት ተረት ተረት ሰባኪምነት

ይከሱታል:: ለአክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች ኢትዮጵያ ተረት ተረት ነች:: ታሪኩዋ ሁሉ ሀሰት ነዉ:: ንግስት ሳባ ተረት ተረት ነች::

በመጽሃፍ ቅዱስ ያለችዉ ኢትዮጵያ ሀሰት ነች:: ነብዩ መሐመድ በታላቅ ባለዉለታነት የተናገሩላት ኢትዮጵያ ሀሰት ነች:: አባቶቻችን አብርሃና አጽብሃ አንዱ አክሱም ላይ አንዱም ሸዋ ላይ ሆነዉ ዛሬ ባሌ እና ሶማሊያ የሚባለዉን አካባቢ እንዲሁም ከምዕራብና ከደቡብ ያሉ ሰፊ ኢትዮጵያዊ አካባቢዎችን አንድ አድርገዉ ሲያስተዳርሩ የነበሩት ታሪክ ሀሰትና ተረት ተረት ነዉ:: ለአክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች አሁን ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለዉ ህዝብ እራሱ እንኩዋን ሀሰት ነዉ:: ለአክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች በ19ኛዉ ምዕተ ዓለም

አሃመነስ የሚባል ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ 16 ፕላኔቶች ስለመኖራቸዉ የጻፈዉ ፍልስፍና ተረት ተረት ነዉ:: ለአክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች

ኢትዮጵያዉያን የሚያደርጉት ነገር ሁሉ ተረት ተረት ነዉ:: ከዚህም በላይ አጥብቀዉ የሚጠሉት ነገር ታዲያ ኢትዮጵያዊነት የጋራ

ማንነት አለዉ የሚለዉን ጭብጥ አንስቶ የሚያርገብግብን ሀይልን ነዉ::

አንዳንድ የዋህ ኢትዮጵያዉያን እንደሚያስቡት አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች እያጠቁት ያለዉ ቴዎድሮስ ካሳሁንን በግለሰብ ደረጃ

ይመስላቸዋል:: ላንዳንዶች የመሰላቸዉ አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች የጠሉት ቴዲ አፍሮን ነዉ:: ሚስጥሩ ግን እነዚህ ሰዎች የጠሉት

አንድ ነገር ብቻ ነዉ:: ኢትዮጵያዊ የጋራ እሴት የሚባል ነገር ፈጽሞ እንዲኖር አይፈልጉም:: የኢትዮጵያ ታሪክ የዉሸትና የጭካኔ ታሪክ

ነዉ ሲሉ ክደዋል:: ኢትዮጵያዊ ማንነቱን እንዲጠላ እየሰሩ ነዉ:: የኢትዮጵያ ህዝብ ለስንት ሽሕ ዘመናት አብሮ ኖሮም በፍጹም ያልትዋሃደ ህዝብ ብሎም እንደ ዘይትና ዉሃ ፈጽሞ ያልተቀላቀል ህዝብ ነዉ ሲሉ ኢትዮጵያዉያንን በጎሳ ከረጢት ዉስጥ ብቻ ልኬታቸዉን ሰፍተዉላቸዋል:: ቴዎድሮስ ካሳሁን ደግሞ እዚህ እጎሳ ከረጢታቸዉ ዉስጥ አልገባ ብሎዋቸዋል::ሰዉዬዉ ከጎሳ

ከረጢት የገዘፈ ሰብዕና አለዉ:: ዛሬ ዉጭ አገር ድረስ ሄደዉ ፒ ኤችዲና ማስተር አንጠልጥለዉ ሲያበቁ ስለጎሳና ቀበሌያቸዉ ሲዘምሩ ዉለዉ ሲያለቅሱ ቢያድሩ የማይታክቱ ምሁራን እንደ አሸን በፈሉባት ኢትዮጵያ ዉስጥ አንድ ሙዚቀኛ ግን ከጎሳ ከረጢቱ በላይ

የገዘፈ ሰብዕና ለብሶ ብቅ አለባቸዉ:: እናም ተረበሹ::

አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች ሙሴን የስራ አመራር ስርአታ ያስተማረዉን የኢትዮጵያዉያን አባትን የዮቶርን ታሪክ ክደዋል:: የመጽሀፍ

ቅዱሱን ታሪክ ማራከስ ሲያቅታቸዉ የጎጃም ቄሶች በግዕዝ የጻፉት ተረት ተረት ነዉ ሲሉ ዉሸትን ከረባታቸዉ አድርገዋል:: የእንግሊዘኛዉ መጽሃፍ ቅዱስ ሲመጣላቸዉ ደሞ ይህ መጽሃፍ ቅዱስ የሚጠቅሳት ይህችኛዋ ኢትዮጵያ አይደለችም ሲሉ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያላቸዉን እጅግ ጥልቅና ስር የሰደድ ጥላቻ ነግረዉናል:: የኢትዮጵያዉና ነገስታት ታሪክ የሀሰት ታሪክ ሀሰት ነዉ:: ክብረ ነገስት የሚባለዉም የነገስታት ታሪክ መጽሀፍ በትግሬ ደብተራ የተጻፈ ተራ የሀሰት ሰንድ ነዉ ሲሉ ኢትዮጵያዊ የሆነዉ ነገር በእገር ይረገጥ ዘንድ ከአንዳንድ ተንኮለኛ ፈረንጅ ጸሃፊዎች የቃረሙዋትን ቆራጣ መረጃ ለማቅረብ መጽሃፍትን ጽፈዋል:: እንግዲህ

ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ምንም የእዉነት የሆነ እሴት የላትም ማለት ነዉ:: በአክራሪ የጎሳ ፖለቲከኞች አይን::

አክራሪ የጎሳ ብሄረተተኞች ሌላዉ የማሳሳቻ ስልታቸዉ ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ የነገስታት ታሪክ ስለሆነ ዋጋም የለዉ:: እንደ ኢትዮጵያ ታሪክም ልንቆጥረዉ አይገባም ይሉና ይሄን የኢትዮጵያ ታሪክ ብሎ አንስቶ ማቀንቀን ተገቢ አይደለም ሲሉ በብልጠት ኢትዮጵያዊ ታሪክ ይደብዝዝ ዘንድ ይሰራሉ:: የነገስታትና የሀገር መሪዎች ታሪክ እንጅ ወትሮስ ከሃገር ታሪክ ጋር ተሳስሮ የሚነሳዉ

የያንዳንዱ ዜጋ ታሪክ የተጻፈበት ሀገር ወትሮስ የት አለ? እንግሊዝ ነዉ? ሩሲያ ነዉ? ቻይና ነዉ? ነዉ ወይስ የት? ሌላዉ ቀርቶ

በአሁኑ ዘመን በዲሞክራሲያዉያን ሀገራት ( ለማጣቀሻ አሜሪካን ማሰብ በቂ ነዉ) ታሪክ የሚጻፈዉ በፕሬዝዳንቱ ዙሪያ የሚሽከረከሩ

ሀገራዊ ዉሳኔዎችን እያጣቀሰ እንጅ ፕሬዝዳንቱ ማዕከል ያልሆኑበት ታሪክ የት ይጻፋል? ሀገራዊ ዉሳኔዎች ሁሉ የመጨረሻ የመቁዋጫ ዉሳኔ እና የተፈጻሚነት ትዕዛዝ የሚያገኙት በሀገር መሪዉ እስከሆነ ድረስ የሀገራት ታሪክ ማዕከል ሆነዉ የሚወጡት ፕሬዝዳንቱ

ናቸዉ::

ሆኖም አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች ይሄ ጠፍቶአቸዉ አይደልም:: ብቻ አንድ ነገር ይፈልጋሉ:: ያም ነገር በዚህም ሆነ በዚያ

ተብሎ ኢትዮጵያዊ የጋራ እሴት ጠፍቶና ተደምሦ ማዬት የመጨረሻ ግባቸዉ ነዉ:: ይሄን የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት የሚያራግብ

ታሪኩን የሚያጣቅስ ሰዉ ከዚህች ሀገር ለመጨረሻ ጊዜ ተደምሦ ማዬት የሚቁዋምጡበት ወቅት አሁን ሆኖ አግኝተዉታል::

ኢትዮጵያዊ የጋራ እሴትን የሚያቀነቅን ግለሰብ እጅግ ትንሽ አቅም ቢኖረዉም የጥላቻ ቀስታቸዉ ማነጣጠሪያ ይሆናል::

አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች የተለያዩ ማህበረሰቦችን/ብሄረሰቦችን/ በሚወክሉበት ጊዜ እርስ በእርሳቸዉ አይዋደዱም::ሊጠፋፉ

ይደባባሉ:: ሆኖም አንድ ነገር ላይ ይስማማሉ:: ይሄዉም ኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴትን በማጥቃት ላይ አንድነት አላቸዉ:: እናም

በሳሳዉ ኢትዮጵያዊነት ብሄረተኝነት ደን ዉስጥ አንድ ብላቴና ቴዎድሮስ ካሳሁን ወዲህና ወዲያ ሲወራጭ አስተዉለዋል:: ይህ

ኢትዮጵያዊ ብላቴና በታላቅ አክብሮት ንግስተ ሳባን ይጠራታል:: አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች ግን ይህ የኢትዮጵያዊነት ታሪክ ዉሸት ነዉ

ሲሉ ገና ዱሮ ደምድመዋል:: እናም ይሄን ታሪክ የሚያነሳ ሰዉ ተረት ተረት ታሪክ ያጣቅሳል እያሉ ሞራሉን ለመስበር ኢትዮጵያዊ

ትምክህቱን ለማንኮታኮት መስራት ከጀመሩ ቆይተዋል:: ኢትዮጵያዊነት እና የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት በማንም ቢነሳ : በምንም

መልክ ቢነሳ: በየትኛዉም መልክ ቢነሳ ፊታቸዉ ይደምናል : ልባቸዉ ይጠቁራል እራሳቸዉን ለጸብና ለስድብ ያዘጋጃሉ::

የአክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች ጉልበት ገና እየበረታ ይሄዳል:: ጩህትና ስድቡም ገና ምድር ያንቀጠቅጣል:: ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር

ተረት ተረት ሀገር ነች የሚለዉ ቃላቸዉም እስከ ደመና ገና ይወጣል:: የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴትን የሚሰብክን ብሎም የኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት እሴትን የሚያቀነቅንን ሁሉ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ የሚደረግ ርብርብ ጉልበቱን ታክቲኩን እና ስልቱን እየቀያዬረ እና እየበረታ እንደሚመጣ ጥርጥር የለዉም::

በጥቂቱ ግን ዛሬ ዱላዉ በቴዲ አፍሮ ላይ እዬወረድ ነዉ:: ቴዲ አፍሮ በብራዚል አለመሳተፉ ያስደሰታቸዉ ይመስል ጥላቻቸዉን በቴዲ አፍሮ ዙሪያ ያጠሩ መስለዉ (በርካታ ተቀባይ እንዲያገኙ) ቀረቡ እንጅ የዳንኪራቸዉ ምንጭ ኢትዮጵያ በአለም መድረክ ላይ እንደ ሀገር ተወክላ አለመቅረቡዋ የፈጠረባቸዉ የደስታ ስሜት

ነዉ::ኢትዮጵያ የሚለዉ ስም ያማቸዋልና:: ኢትዮጵያ ስትዋረድ ደስ ይላቸዋል:: ኢትዮጵያዊ ሰዉ የላትም ሲባል ዳንኪራ ይረግጣሉ:: ኢትዮጵያ ታሪክ የሌላት ምናምንቴ ሀገር

ናት የሚል ሀሳብ ሲሰሙ ደስታቸዉ ጣሪያ ይነካል:: ኢትዮጵያ የሚል ቃል ሲሰሙ ያማቸዋል ብቻ ሳይሆን የጥላቻ ዛር ያንዘፈዝፋቸዋል:: አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች የረጅም ጊዜ ግባቸዉ ኢትዮጵያዊነትን የሚሸከም ግለሰብ እንዳይወጣ : ኢትዮጵያዊ እሴትም ተንኮታኩቶ እንዲጠፋ ስለሆነ ኢትዮጵያዊነት በአለም መድረክ ላይ እንዲወከል አይፈልጉም:: እናም ኮካ ኮላ ቴዲ አፍሮን

ስላገደዉ ደስ ያላቸዉ ኢትዮጵያ ስለተዋረደች ነዉ:: ኢትዮጵያ ስለደበዘዘች ነዉ:: እነሱ የሚፈልጉት የዚህ ዘመን ትዉልድ በሙሉ

እንደ እነሱ በየ ጎሳዉ ከረጢት ገብቶ ስለጎሳና ቀበሌዉ ብቻ እንዲዘምር ነዉ::
ከጎሳና ከቀበሌ የዘለለ ኢትዮጵያዊ ሰብዕና ያለዉ ሰዉ ከመጣ ግን በጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ይወርዱበታል:: በአሉ ግርማ ደራሲ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ እይታዎቹ ትንቢት ጭምር ያዘሉ ይመስሉ ነበር::
ሀዲስ በሚለዉ መጽሃፉ ዉስጥ በንጉሱ ዘመን እንኩዋን አክራሪ የጎሳ ብሄረተኝነት ብልጭ ብልጭ ስትል ጠቆም አድርጎ በርካታ አንባቢ ሊረዳዉ በማይችል መልክ አቅርቦ ሲያበቃ የአደጋዉን ርቀትም እንደ ቀልድ አሳይቶ አልፎ ነበር:: ያኔ በስነጥበብ ስራ ጥቆማ ነገሮችን ቀደሞ አስተዉሎ የሚያቅድና የተሻለ ሁኔታን መፍጠር የሚችሉ አስተዋይ የሀገር መሪዎች ቢኖሩ ኖሩ መድሃኒቱን ማሳብ ይችሉ ነበር::

እናም ዛሬ አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞች ጉልበት ከመበርታቱ የተነሳ የኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት እሴት አራማጅ ሀይሎች ምንም የጋራ

ነጥብና ታሪካዊ መሰረት እንዳይኖራቸዉ በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ቀንድ ቀንዳቸዉን ከማለት ዘሎ ግለሰባዊ ጥቃት ላይ ደርሶዋል::

እንደተባለዉም ጩህቱና ድንፋታዉ ከደመናት በላይ ደርሶዋል:: ሆኖም በእግዚአብሄር መዝገብ የተጻፈዉ ኢትዮጵያዊነት ነዉና

በምድር ላይ ያለ ምንም ሀይል ኢትዮጵያዊነትን ሊያሸንፈዉ አይችልም:: ቴዲና በርካታ ኢትዮጵያዉያን ሀገራችን ቅድስት ነች ብለው

ያምናሉ:: ይሄም አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞችን ያበሳጫቸዋል:: ኢትዮጵያዊነት ትምክህት ይጎረብጣቸዋል:: ሆኖም መጽሀፉን ገላልጦ

ማንበብ ነዉ:: ቅድስናዋን የሰጣት እግዚአብሄር እንጅ ሰዉ አይደለም:: ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን አይለዉጥም እንዳለ መጽሀፉ::

ነብዩ መሐመድም ይሄን ቅድስናዋን ስለተረዱ ፍትህ ወደ ማይዛባባት ቅዱሳን የእዉነት ሰዎች ወዳሉባት ሀገር ሄዳችሁ ታላቁን እምነት

እስልምናን ጠብቁ ብለዉ ለተከታዮቻቸዉ ያስረዱት ያለምክንያት አይደለም::

ቴዲ አፍሮ ሀገሪቱ የተሰጣትን እና የሆነችዉን አቀነቀነላት እንጅ ቴዲ አፍሮ የፈጠረላት እሴት የለም:: እናም ይህች ኢትዮጵያዊ ትምክህቱ ስለሆነች ቴዲ አፍሮ እንዲህ ብሎ

ዘፈነላት:: እስላም ክርስቲያኑ የሚፋቀርባት … ::: እናም ቴዲ አፍሮ የጥቃት ኢላማ ሆነ:: ለምን ቢባል? ኢትዮጵያዊነት እሴትን

አራምዱዋልና:: ኢትዮጵያዊነት ትምክህትን ሰብኮአልናል:: ኢትዮጵያዊነት ዉህደትን አቀንቅኑዋልና::

ቴዲ አፍሮ የጠለቀ ጭብጥ በቁዋጠሩ ሙዚቃዎቹ እንደሚነግረን ኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት አለዉ:: ይህ የጋራ ኢትዮጵያዊ እሴት

እስላም ክርስቲያኑን ያፋቅራል::ይህ የጋራ ኢትዮጵያዊ እሴት ጥንታዊና ስር የሰደድ የጋራ ምድር ያለዉ የጋራ ታሪካዊ መሰረት ያለዉ

ዉህድ ኢትዮጵያዊ ህዝብን አስተሳስሮ አቁሞአል:: ኢትዮጵያዊነት ለቴዲ አፍሮ የጎሳዎች ድምር ሳይሆን የኢትዮጵያዉያን ማህበረሰብ

ዉህደት ነዉ::

ይህ ዉህደት ደግሞ ከድምር የበለጠ የጋራ መስተጋብር ነዉ (the whole is greater than the sum)::

ኢትዮጵያዊነት አይሁድነትን : ክርስትናን እና ሙስሊምነትን ጠምዝዞ ዉህድ ኢትዮጵያዊ እሴትን የማልበስ አቅምና

ጉልበት እንዳለዉ ሁሉ ዛሬ የሚጮሁትን አክራሪ የጎሳ ብሄረተኞችን ሁሉ ቀስ ብሎ ይዉጣቸዋል:: ኢትዮጵያዊነት ምንድነዉ? ምንስ

የጋራ እሴት አለዉ? ብሎ ለሚጠይቅ ሁሉ ካማዊነት ሴማዊነት ኩሻዊነት በጋራ ተገምደዉ ተዋዉጠዉና ተሰናስነዉ በዉህደት

የፈጠሩት ኢትዮጵያዊ እሴት አለ:: ቴዲ አፍሮ የስነ ጥበቡ ጭብጥ ማጠንጠኛ ማዕከል ያደረገዉ ይሄን ኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት

ነዉ:: እናም ቴዲ ላይ ጦር የሚያሰብቅበት ይሄንኑ ሀቅ በማቀንቀኑ የተነሳ ነዉ:: ጦሩ የተወረወረዉ ወደ ኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት

ላይ እንጅ እንደ ግለሰብ ወደ ቴዲ አፍሮ ላይ አይደለም:: ቴዲን ማኮላሸት ከተቻለ ሌሎች በኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት ዙሪያ

የሚያቀነቅኑ የስነጥበብ ባለሞያዎች እንዳይወጡ ማድረግ ይቻላል የሚል ታሳቢ ነዉ የተያዘዉ::

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s