የለውጥ አዋጅ!!!…. እንቢልታው ይነፋ! ነጋሪት ይጎሰም! | ሰሎሞን ተሰማ ጂ.

 

ሰሎሞን ተሰማ ጂ.
Email:- solomontessemag@gmail.com http://www.semnaworeq.blogspot.com

እደግመዋለሁ፡፡ እደጋግመዋለሁ!!! “የለውጥ አዋጅ፣ ይታወጅ!!!” እንቢልታው እየተነፋ፣ ነጋሪቱም እየተጎሰመ፣ በለውጥ ረጅም ጎዳና ላይ ለመዝመት እንነሳ!!! ረጅሙን ጉዞ፣ እልህ አስጨራሹን ጉዞ፣ አሁኑኑ እንጀምረው፡፡ አዎን!!! ነጋሪቱ ይጎሰም!!! እንቢልታውም ይነፋ!!! ለለውጥ የተዘጋጃችሁ ሁሉ፣ ማቄን ጨርቄን ሳትሉ፣ አቅማችሁ የፈቀደውን፣ ቤታችሁ ያፈራውን፣ ስንቅና ትጥቃችሁን ይዛችሁ ውጡ!!! ለውጡ፣ ያለያንደንዳችን በጎ አስተዋፅኦ ፍጹም አይሳካምና-ኑ ውጡ፡፡ ኑ!!! ታገፈጡ፡፡ ለውጥን ራሱንም ተጋፈጡት! እንቢልታው ሲነፋ፣ ነጋሪቱም ሲጎሰም፣ በሰመመን እንቅልፍና ዱካክ ውስጥ ሆናችሁ፣ የቀን ቅዠት ከሚንጣችሁ፣ “ኑ!!! ውጡ!!!” ይላችኋል ለውጡ!!!
የለውጥ አዋጅ ሲታወጅ፣ ነጋሪቱ ሲጎሰም፣ እንቢልታውም ሲነፋ፣ በሰመመን ድብርት ውስጥ፣ ካለ ሆኖ የሚያንቀላፋ፣ ወየውለት፡፡ ዝቅ ብሎ ባቱን! ከፍም ብሎ አንገቱን! ይቆርጠዋል-የታሪክ ሰይፍ፣ ይወገዳል ከመጪውም ሰልፍ! አዎን! ትልቅ ታሪክ ያለን፣ ለሺህ ዘመናት የኖርን፣ ለጽድቅና ለክብር፣ ቀን ከሌት የተጋን፣ ትልቅ ሕዝብ ነን፤ ማንም ያልደፈረን፡፡ አሁንም ቢሆን፣ አንገታችንን ያልደፋን፣ በክብር ተመልተን፣ ልዕልናችንን ይዘን፣ ወደፊት የምንጓዝ፣ ዘላለማዊዎች ነን፡፡ ዓለም ስትለወጥ፣ ከዘር አባዜ ወጥታ፣ የእያንዳንዱን ሰው መብት፣ ስትሰጥ እኩል በኩል ገምታ፤ ባረጀና ባፈጀ ወግ ውስጥ ታስረን፣ በዘር አባዜ ስንገላመጥ፤ ባለማቀፍ ሴራ ጥርስ ውስጥ፣ ገብተን እንደማንሰለቀጥ – ምንም ዋስትና የለንም፡፡ ስለዚህም፣ የለውጡ አዋጅ እንዲታወጅ፣….. ነጋሪቱ ይጎሰም!!! እንቢልታውም ይነፋ!!!

የአዋጁን ጥሪ ለመስማት፣ ካለ የማዳመጥ ችግር ያለበት፤ የለውጡን ዘማች ሰልፈኞችም ለማየት፣ ካለ የማየት ችግር ያለበት፣ ቱርጁማን ይቀጠርለታል፤ ግን፣ መከተል አለበት፡፡ ለውጡ ማንንም አይመርጥም፤ ማንንምም አይጥልም፡፡ የታሪክ ሚዛን ነው፤ ሁሉንም ይሰፍራል፡፡ የታሪክ ጎዳና ነው፤ ሁሉንም ያስኬዳል፡፡ የታሪክም ሰልፍ ነው፤ ሁሉንም ይጣራል፡፡ “ኑ! ተቀላቀሉኝ፣ እንዳትቀሩብኝ” ይላል፡፡ የምንጓዘው ወደ ግለሰብ ነፃነት ነው፤ የምንዘምተው ወደ እኩልነት ነው፡፡ እያንዳንዳችን “በሕግ ፊት” እኩል ወደ ምንዳኝበት፤ እያንዳንዳችን በሀገር ጉዳይ ላይ እኩል ወደ ምንተችበት፤ እያንዳንዳችን በብሔራዊ ጥቅማችን ላይ እኩል ወደ እምንሰማበት፤ ወደዚያ መፃኤ ግብ፣ ባንድነት የምንተምበት ሰዓት አሁን ነው፤ አሁን ነው!!! የለውጥ አዋጅም የሚታወጅበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ አልሰማሁም ብሎ የሚቀር ካለ፣ አላየሁም ብሎም የሚያመነታ ካለ፣ ከፍርድ አያመልጥም፤ ምንም እንኳን እንጦሮጦስ ቢሰጥም-ከፍርድ አያመልጥም፡፡ በስደተኝነት ቢያላክክ፣ በምንተዳዬም ቢብሰከሰክ፣ ከፍርድ አያመልጥም፡፡ ፍርዱም የታሪክ ነው፤ ትዕዛዙም አዋጅ ነው፡፡ አዎን! ነጋሪቱ ይጎሰም!!! እንቢልታውም ይነፋ!!! ድው…! ድም….!!! ግው-ግም!!! ግው-ግም!!!

የአዛውንቶችና የአንጋፋዎች ተግሳጽና ምክር የሚደመጥበት፤ የጎልማሶችና የባልቴቶች ሚና የሚወደስበት፤ የወጣቶችና የታዳጊዎች አቅም ጎልቶ የሚወጣበት ወቅት፣ አሁን ነው፡፡ አሁን ነው፣ አዲሱንና ግዙፉን ኢትዮጵያዊነት የምናድሰው፡፡ ያሻንን የምናመርትበት፤ የሚያዋጣንንም የምንነግድበት፤ የሚያስፈልገንን የምንገበይበት፤ ልባችን የወደደውን የምንቀስምበት፤ የፈቀድነውንም የምንጽፍበት፤ “ማለት ያለብንንም ሁሉ የምንናገርበት” ወቅት እንዲመጣ ከፈለግን፣ የለውጥ አዋጁ መታወጅ አለበት፡፡ የአዋጁም ማብሰሪያ፣ እንቢልታው ይነፋ! የሰልፉም ማጀቢያ፣ ነጋሪቱ ይጎሰም! ኢትዮጵያዊነት ጸንቶ እንዲኖር፣ ከዓለም እስከ-ዓለም፣ ለዘላለም-ዓለም፣ እንቢልታው ይነፋ!!! ነጋሪቱም ይጎሰም!!! ድው…!!! ድም….!!! ግው-ግም!!! ግው-ግም!!!

ለውጡ — አርበኞችን ይሻል፤ በእውቀትና ክህሎት የታጠቁትን፡፡ ለውጡ — ከያኒያንን ይሻል፤ ከስር ከስር ተከታትለው የሚያነውሩትን፡፡ ለውጡ — ገንቢዎችን ይሻል፤ ግሩም መሠረት የሚጥሉለትን፡፡ ለውጡ — አንጥረኞች ይሻል፤ አሽሞንሙነው የሚያስጌጡትን፡፡ ለውጡ — ዘማሪዎች ይሻል፤ ግነን-ፍነን የሚሉትን፡፡ ለውጡ — ፈካሪዎች ይሻል፤ የዕለት ውሎውን የሚዘግቡለትን፡፡ ለውጡ — ተኳሾችን ይሻል፤ እንዳይናቸው ብሌን የሚጠብቁትን፡፡ ለውጡ — ቀሳውስትን ይሻል፤ ሑዳዴን የሚይዙለትን፡፡ ለውጡ — ሼኪዎችን ይሻል፤ ሮመዳን የሚፆሙለትን፡፡ ለውጡ — ዘማሪዎችና ዘያሪዎችን ይሻል፤ በየእምነታቸው የሚታደሙለትን፡፡ ለውጡ — ቆንጃጅትንና ጉብሎችንም ይሻል፤ ጉዞውን የሚያስቀጥሉለትን፡፡ አዋጁ ትዕዛዝ ነው፤ ማንም የማይቀርበት፡፡ ስለዚህም፣ ነጋሪቱ ይጎሰም! እንቢልታውም ይነፋ! ላዲሱ ዘመን፣ ላዲሱ ተስፋ!!!

በስደትና በእንክርት አዙሪት፣ በባዕድ አገር የምንሳቀቅበት፤ ውጡና ግቡ የማንባልበት፣ በቀቢፀ-ተስፋ ውስጥ ሆነን፣ ጉፋያ አካላችንን የሚወዘወዝበት፤ በቆዳችን ቀለምና በክሳታችን የምንለካበት፤ ሰብዓዊ ክብራችን ታውቆ፣ በምልዓት የምንገንበት፤ ያ ዘመን እንዲጀመር፣ ጎሑም ፈክቶ እንዲቀድ፤ አዋጁን አዳምጠን፣ አለብን ምላሽ መስጠት፡፡ ሥራዎችን ተከፋፍለን፤ መሪዎችን አስቀድመን፤ አማካሪዎቻችን መርጠን፤ ከሳሽና ፈራጆችን፣ አቃቤዎችንም ይዘን፤ ስንቅ አቅራቢዎቻችንን፣ አበዛዎቻችንን አውቀን፤ ቀያሾቻችንን እና ተላሚዎቻችን አደራጅተን፤ ለቃፊሮቻችንን እና ለሕገ-ደንባችን፣ ከልባችን ታዘን፤ አንጋሽና ቀዳሾችን፣ ወይዛዝርቱንም ይዘን፤ ወደማይቀረው መፃኤ-ዕድል በጋራ መሄድ አለብን፡፡ ይህ ነው፣ ምኞታችን! ይህም ነው፣ ራዕያችን! የቁም ቅዠታችንንና የቁም ሰመመናችንን፣ እንደጦስ ዕቃ ጥለን፤ ባዲስ መንፈስ፣ ባዲስ ወኔ፣ በብጽአት ተመልተን፤ ወደምሉዑ ዘመን፣ በድል መጓዝ ነው አለብን፡፡ ስለዚህም፣ እንቢልታው ይነፋ! ነጋሪቱም ይጎሰም! ድው…!!! ድም….!!! ግው-ግም!!! ግው-ግም!!!

ነጋሪቱ ሲጎሰም፤ እንቢልታውም ሲነፋ፤ ያኔ ደማችን በትክክል ይሞቃል፤ ወኔያችንም ይግላል፡፡ ለውጥ በባሕሪው፣ ደመ-ቀዝቃዛነትን ይጠላል፡፡ እንደለውጥና እንደነውጥ ያሉት ክስተቶች፣ ደመ-ቀዝቃዛነትን አጥብቀው ይንቃሉ፡፡ ረጋ ብሎ የሚያስብ እንጂ፣ ረግቶ የሚቀርን፣ ለውጣችን አይፈልግም፡፡ ስለዚህም፣ ደሙ-የሚንተከተክ፣ ወኔው የጋለ፣ ቅስሙም ያየለ፣ የብረት ቆሎ ነኝ፣ እንቢኝ! እያለ፤ የሚንተገተግ የንግግር ክህሎት ያለው፣ ጋዜጠኛና ያደባባይ ተናጋሪ፣ በእጅጉ ይፈለጋል፡፡ እጅግ ትጉህና እጅግ ብርቱ የሆኑም ሳይንቲስቶች፣ ከልክ በላይ ያስፈልጉናል፡፡ ያሸነፉትን ሕዝብ፣ በጠላትነት የማየዩ፤ ያጋዟቸውን ሕዝቦች፣ እንበቀል የማይሉ፤ በታሪክ ሕሊና ውስጥ፣ መርምረው “የሚምሩ”፤ በስነ-ምግባር የዕዝ ካምፓቸው ውስጥ፣ ደግነትን የሚያበስሩ፤ ጥላቻን ተራምደው፣ በቀልን የሚሽሩ፤ የለውጥ ሰልፈኞች፣ በሺሆች የሚቆጠሩ፤ ውለው አድረውም፣ ሚሊዮኖች የሚያፈሩ፤ ቢሊዮኖች የሚመሩ፤ ኢትዮጵያውያን ይፈለጋሉ፡፡ ዛሬውኑ-ጉዞአቸውን ያለማመንታት የሚጀምሩ፡፡ ማቄን ጨርቄን የማይሉ፤ ስንቄን ወርቄን ለለውጡ አዋጣለሁ የሚሉ፤ አሁኑኑ ይፈለጋሉ፡፡ ስለዚህም፣ ለለውጡ አዋጅ ማብሰሪያ፣ እንቢልታው ይነፋ!!! ነጋሪቱም ይጎሰም!!! ድው…!!! ድም….!!! ግው-ግም!!! ግው-ግም!!!

ኑ! ወደ አዲሱ ዘመን፣ በምልዓትና በኩራት፣ ዛሬውኑ እንትመም፡፡ ድዉ! ድም! ኑ! የዘረኝነትን እና የጎጠኝነትን ጥንባሳ፤ የሕግ-ጥሰትንና የመድሎን ነቀርሳ፤ በዕርቀ-ሰላምና በምሕረት ወላንሳ፤ ዳግም እንዳያገረሽ፣ መቼም እንዳይነሳ፤ አድርገን እንደምስሰው፣ ከምድረ-ገጽ ሐበሻ፡፡ ኑ! ባንድነት ሆነን፣ የትውልዶችን ያድሎ ሰንሰለት፣ እግረ-ሙቃችንን በጣጥሰን፤ ባልቴትና መበለቷን፣ ባለትዳር ሆነች ፈትቷን፤ ላጤም ሆነች ሳዱላ፣ ባለቡቅራሟንም ይዘን፤ ለወንዶቹ የምንሰጠውን፣ ለሴቶቹም አካፍለን፤ የጋራ ዕድላችንን፣ በጋራ እንድንወስን፤ አሁኑኑ እንቀሳቀስ፣ አሁኑኑ እንትመም….፡፡ ነጋሪቱ ይጎሰም! ይበል ድዉ! ድም! ወላጆቻቸውን በስደት፣ በበሽታና በጣዕረ-ሞት፤ የተነጠቁ ወጣቶች፣ ወላጅ አልባም ሕፃናት፤ አሳዳጊ የሌላቸውም—የእጓለ-ማውታናት፤ ሞጋሳ ሆኑ ጉዲ-ፈቻ፣ ቃልቻም ሆኑ ቦረን-ቲቻ፤ በባሕልና በቋንቋቸው፣ እኩል ወደሚማሩበት፤ ኹሉ-በኵሉኼት፣ የሆነችን የእኩል ቤት፤ በውዴታ እንድናቆም፣ በፍቃደ ሃያል ስሜት፤ መንቀሳቀስ ነው ያለብን፡፡ ስለዚህም፣ እንቢልታው ይነፋ!!! ነጋሪቱም ይጎሰም!!! ድው…!!! ድም….!!! ግው-ግም!!! ግው-ግም!!!

ይኼንን ጀብዱአችንን፣ ከስር ከስር ተከታትለው፤ ለዓለም የሚያበስሩን፤ ይኼንን ድላችንን፣ በመቅረጽ-የሚቀዱልን፣ ጋዜጠኞች፣ አርታኤዎች፣ ዘጋቢዎችና ፀሐፍት፣ ደራሲያንና ተዋንያን፣ ፀሐፌ-ተውኔቶች፣ የፊልም አዘጋጆችና የፊልም ሞያተኞች፣ አሁኑኑ ይፈለጋሉ፡፡ ሰልፈኞችን ባፍላ-ወኔ፣ በግጥምና በዜማ፣ የሚያወድሱና የሚያሞግሱ፣ የለውጥንም መንፈስ፣ ተግተው የሚቀሰቅሱ፣ ሙዚቀኞችና ዳንኪረኞች፤ ገጣሚና አዝማሪዎች፤ አሁኑኑ ይፈለጋሉ፡፡ ለለውጡ ዘፀአት፣ ጉዞ ስንጀምር፤ ሙሴና አሮንን፣ አሲዘናቸው በትር፤ ክርስቶስና ኤልያስም፣ ሲመለከቱ ወደምድር፤ ነብዩ ሞሐመድም፣ ሲፈቅዱልን ከይር፤ ያኔ እናውቀዋለን፣ መለፈፉን አዲስ ተዓምር፡፡ “አላህ”ም አልነው እግዚአብሔር፣ ነውና የዘላለም ስውር ምስጢር፤ ሰልፋችንን ተቀላቅሎ፣ ይሻገራል ወደ አልማር፤ በረከትና ረድኤትን ወደምንነሸነሽበት ሀገር፡፡ ሳንራብና ሳንጠማ፣ ሳናዝንና ሳንከፋ፤ ሳንሞትና ሳንገል፣ ሳንነሳና ሳንደፋ፤ ወደ አብርሆቱ ስፍራ፣ ወዳሰረጽነው ተስፋ፤ ልንደርስ አንችልምና፣ ከቶ አንቁረጥ ተስፋ፡፡ ስለዚህም፣ ይታወጅ የለውጥ አዋጅ!!! እንቢልታው ይነፋ!!! ይጋም — ነጋሪትም ይጎሰም፡፡ ይበል ድው…!!! ድም….!!! ብም-ብም!!! ብም-ብም!!! ድው…!!! ድም….!!! ግው-ግም!!! ግው-ግም!!!

አሁን ላለንበት ዘመን፣ አሁን ለደረስንበትም፤ ባባጣና ጎርባጣ፣ በገደልና በሰርጥም፤ በባሕርና ሸለቆ፣ በሸንተረርና ስምጥም፤ አልፈንና ተርፈን ነው፣ በጃንጥላ አልወረድንም፤ በፓራሹት አልዘለልንም፡፡ ገዢዎቻችንም በሙሉ፣ እንደመና አልወረዱም፡፡ “ስዩመ-እግዜር ነን” ያሉት ሆኑ፤ “ስዩመ-ሕዝብ ዲሞክራቶቹም”፤ ላሉት ክብር ለመብቃት፣ በፓራሹት አልዘለሉም፡፡ የጫኑትን ሃሳብ ይዘው፤ ሸንተረርና ኮረብታውን፣ እንደገመሬ ቧጠው፣ እንደፍልፈል ጉድጓድ ምሰው፣ እንደጃርትም ጭስን ታጥነው’ንጂ፤ ዩፎዎች (U.F.Os) አይደሉም፣ የፈለሱ ከማርሱ ዓለም፡፡ እንቢልታው ሲነፋ! ነጋሪቱ ሲጎሰም! ልቡ ትር-ትር ሳትል፤ ለሰልፉ ወኔው የሚግም፤ ወደ ሙሉው የአልማር ምድር፣ በክብር የሚገባ፣ በሐሴት ለመኖር፤ አሁኑኑ ይነሳ፣ ዛሬውኑ ጉዞ ይጀምር፡፡ ኃያል ሕዝቦች ሆነን፣ በአፍሪካም ሆነ በመላው ዓለም፣ ዳግም ከፍ ብለንና ገነን፣ እንድንወጣ ካስፈለገን፤ ያያት ያባቶቻችንን ሐጢያት፣ መዘክዘኩን ትተን፤ ላልተፈጸመ ታሪክ፣ ሐውልት ማቆሙን ንቀን፤ ላልተሰራውም ግፍ፣ ጣዖት ከማምለክ ታቅበን፤ ራሳችንን እንደጴጥሮስ፣ ለምስዋትነት አጭተን፤ የለውጡ አዋጅ ሲለፈፍ፣ እንቢልታው ሲነፋ፣ ነጋሪቱ ሲጎሰም፤ በጋራ እንንቀሳቀስ፤ ከቶ አንቁረጥ ተስፋ!!! ድው…!!! ድም….!!! ግው-ግም!!! ግው-ግም!!!

አዎን! እንቢልታው ይነፋ! ነጋሪቱም ይጎሰም! ትናንትና ነጋሪትና እንቢልታዎችን ሠርተናል፡፡ ዛሬ ደሞ፣ የሠራናቸውን እንቢልታዎች እንነፋቸዋለን፤ ያበጀናቸውንም ነጋሪቶችም እየጎሰምን አልማር ወደተሰኘው ምድር እንነጉዳለን፡፡ ነገም፣ ኃያል ሕዝብ ሆነን፣ በዓለም መድረክ ላይ በምልዓት እንታያለን፡፡ ኃያል ሕዝቦች ሆነን፣ እምቅ የሆነውን የራሳችንን ሀብት፣ ለቀጣይ ትውልዶቻችን በመቆጠብ፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል፣” ከሚል-የወደል አህያ ብሒል፤ ወጥተን እንደሰው ሰብአዊ፣ እንደ መላዕክትም አማናዊ፤ ሆነን የለውጡን አዋጅ መታዘዝ አለብን፡፡ እናም፣ እንቢልታው ይነፋ!!! ነጋሪቱም ይጎሰም!!! ይበል ድዉ! ይበል ድም! ዛሬውኑ እንነሳ! አሁኑኑ አንትመም! በዘመን ጎርፍ ውስጥ፣ ከምንሆን እርም! ይነፋ እንቢልታው! ይጎሰም ነጋሪቱ! ይበል ድዉ! ድም! ምድርና ሰማዩ በወኔ እስኪግም! ድውውውው! ግግግግግም! ምድርና ሰማዩ ዘላለም ያስገምግም! ድው…!!! ድም….!!! ግው-ግምምም!!! ግው-ግምምም!!!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s