ክቡር ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ከዚህ ዓለም የተለዩበትን 18ኛ ዓመት አሥመልክቶ የወጣ መግለጫ

አያሌው ፈንቴ
ግንቦት6ቀን2009ዓ.ም.

ሰማዕቱ ክቡር ፕሮፌሰር አሥራት ወልደዬስ የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት(የመዐሕድ)ፕሬዝዳንት የዛሬ 18ዓመት ግንቦት 6ቀን 1991ዓም(እ አ አ ሜይ 14ቀን 1999ዓም) በፔንሲልቫንያ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ፊላደልፊያ አሜሪካ አገር በህክምና ላይ እንዳሉ ከዚህ ዓለም እንደተለዩ ይታወቃል።በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣በተለይ ደግሞ የአማራው ሕዝብ ይህን ዕለት አስቦት የሚውለው በታላቅ ሀዘንና ቁጭት ነው።

ክቡር ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ከዚህ ዓለም የተለዩበትን 18ኛ ዓመት

ክቡርነታቸው ለኢትዮጵያ ሀገራዊና ሕዝባዊ አንድነት እንዲሁም እኩልነትና ዲሞክራሲያዊ ሕይወት ግኝት የከፈሉት አቻ የለሽ መሥዋዕትነት፣በታሪክ ዓምድ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ከመያዙም ባሻገር፣ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የሚኖር ነው።

ፕሮፌሰር! ከትግሬ ዘረኞች ሥልጣን መያዝ ጋር ተያይዞ የመጣው የጎሳ ፖለቲካ ገና ከመነሻው ችግር ሊያሥከትል እንደሚችል በግልፅ ከመናገር አንሥቶ የመከራ እሳቱም ሲቀጣጠል ያንን ለማጥፋት በቀዳሚነት የተሰለፉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነበሩ።ለምሳሌ በ1983ዓም የትግሬ ዘረኞችና ዕድምተኞች ያካሄዱትን የኢትዮጵያን ሀገራዊና ሕዝባዊ አንድነት የመናድ ተግባር፣የኮንፈረንሱን ምንነትና ተልዕኮ በጀግንነት በመዋጋት ድምፃቸውን አጉልተው ያሠሙ ጀግና ነበሩ።

በ1984ዓም ዐማራው በአርባጉጉ፣በበደኖ፣በአረካ፣በአሰቦት ገዳም፣በአሩሲ ነገሌና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ህይወቱ እያለ ዓይኑ ሲጎለጎል፣ሕይወቱ እያለ ቆዳው ሲገፈፍ፣ሕይወቱ እያለ ሥጋውን ቆርጠው “ብላው እያሉ” ሲያሰቃዩት፣ሕይወቱ እያለ ቤት ዘግተው ሲያቃጥሉት፣ሕይወቱ እያለ ወደገደል ሲወረውሩት፣ሕፃናት ከእነቤተሰቦቻቸው ሲታረዱ፣የዕርጉዞች ሆድ ሲቀደድና ሽሉ ሲጣል፣ የዐማራው ልጃገረዶች ሲደፈሩ፣ሲዋረዱና ተማርከው በባርነት ሲያገለግሉ፣አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉና ሌሎችም ተዘርዝረው የማያልቁ የዘር ማጥፋት ሰቆቃዎች ሲፈፀሙበት፣ፕሮፌሰር አሥራት አይተው እንዳላዩ፣ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነው ማለፍ አልቻሉም።

በዚህን ጊዜ ዐማራው አለሁ ባይ ተቆርቋሪ የሌለው መሆኑን ተገንዝበው፣አጋር ሊሆኗቸው ከሚችሉ ወገኖች ጋር ዐማራውን ከጨርሶ ጥፋት ለማዳን በሚቻልበት ጉዳይ መክረው መዐሕድን በመመሥርት፣ቀን ጨልሞበት አለሁ ባይ ወገን አጥቶ በደም ተጨማልቆ የሚቃትተውን ዐማራ “የሚያሥጥልህ ሕግና ሥርዓት የለም፣ሞት ወይም ሕይወት ብለህ ራሥህን አዘጋጅተህ ባላጋራህን ተቋቁመህ ባለህ ኃይል ተከላከል” በማለት በሥነ ልቦና ገነቡት።

ፕሮፌሰርም በአንድ ወቅት እንዳሉት  በአራት እግሩ በመሄድ ላይ የነበረው ዐማራ አንገቱን ቀና አድርጎ በሁለት እግሩ መሄድ ጀመረ።ይህም የመጀመሪያው የፕሮፌሰር አሥራት ቆራጥ አመራር የሕይወት ፍሬ  ውጤት ነበር።በዚህን ጊዜ የትግሬ ዘረኞች  የፕሮፊሰር እንቅስቃሴ ሥላስደነገጣቸው እግር በእግር ክትትሉን ተያያዙት።

ፕሮፌሰር! ዙሪያ ገባውን በጠላት ተከብበው  ሲዋከቡ፣ ችግርና ፈተና ሳይበግራቸው፣ከፊት ለፊታቸው የተጋረጠውን ግዙፍ ኃይልና አደጋ ከምንም ሳይቆጥሩ፣በዚህ በቀውጢ ሰዓት ከማንም ቀድመው ፣የአገር ግንጠላ ወደፊት የሚያስከትለውን ችግር አሻግረው አይተው ሀቁን በመናገር እና በአማራው ላይ የሞት፣የመታሰርና የመሰደድ አደጋ  ማጥላቱን አሥመልክቶ፣ለአገርና ለሕዝብ ዘላቂ ሰላም፣ለፍትሕና እኩልነት ያለማወላወል በቁርጠኝነት በመቆም ሳይቃጠል በቅጠል በማለት እምቢ ለሀገሬ፣እምቢ ለወገኔ፣እምቢ ለዳር ደንበሬ፣ብለው በታላቅ ቆራጥነት መታገላቸው አርአያነቱ ምንጊዜም የማይረሳ ነው።  

በኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት፣በህዝቡ የጋራ ዕድልና ተስፋ ላይ ዘወትር በማሴር ላይ ያለው ፀረ-አማራው የትግሬው ቡድን፣ ፕሮፌሰር አሥራትን  ከጎጃም ከመጡ ገበሬዎች ጋር በመዐሕድ ጽህፈት ቤት በመሰብሰብ የአድማ ወንጀል ፈፅመሀል” በሚል የሀሰት ክስ መሥርቶ 2ዓመት ፈረደባቸው፣ “ደብረ ብርሃን ላይ ሕዝብ የሚቀሰቅስ ንግግር አድርገሃል በሚል አንድ ሌላ ክስ መሥርቶ 3ዓመት ፈረደባቸውየጎጃም፣የጎንደርንና የሰሜን ሸዋን ሕዝብ ለአመፅ አዘጋጅተሃል”በሚልም ወንጅሎ፣ ባንዲት 80እሥረኞች በሚገኙባት ዛኒጋባ 81ኛው እሥረኛ ሆነው  ከገቡ በኋላ ለበርካታ በሽታዎች ተዳረጉ።ይሄ ቢታወቅም በጊዜው አሥፈላጊውን ህክምና በመነፈጋቸው በሽታው ሥር እየሰደደ ሄዶ አሥጊ ደረጃ ላይ ሲደርስ ሆስፒታል ገብተው ተስፋ በሌለው ሕክምና ቆይተው፣ነገ ዛሬ ህይወታቸው ያልፋል ሲባል ወደውጭ አገር ተልከው አሁንም ተስፋ በማይሰጥ ሕክምና ቆይተው አረፉ።

ዘረኞቹ ትግሬዎች!  ፕሮፌሰር አሥራትን በፈጠራ ወንጀል አሥረው  አምስት ዓመት አንገላተውና አሠቃይተው በቁመና ከገደሏቸው በኋላ በማምጠጫ ዕድሜያቸው ወቅት ለይስሙላ ህክምና ወደውጭ አገር ማስወጣታቸው በዘረኞቹ ላይ የሚመጣውን ተቃውሞ ለማርገብ የሚረዳቸውና የፖለቲካ ትርፍ የሚያሥገኝላቸው መሥሏቸው ይሆናል ግን አይደለም። ይህ ድርጊት የሚያሳዬው ዘረኞቹ፣በአማራው ሕዝብ ላይ ያላቸውን መረን የለቀቀ ጥላቻና ፋሽስታዊ ተልዕኮ በመሆኑ፣ቁጣችን አይሎ፣ጥርስ እንድንነክስ ተገደናል።

በማይቀረው የሠው ልጅ መጨረሻ በሆነው ሞት በአካል ከእኛ የተለዩን ፕሮፌሰር አሥራት፣ጉልበታቸውን፣ዕውቀታቸውን፣ገንዘባቸውንና ዕምነታቸውን፣ብሎም  ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡት፣ ለአገርና ለሕዝብ አንድነት ሲሉ ነበር።ዘረኛውን ወያኔን ግን በልበሙሉነትና በጀግንነት ሲታገሉ አልፈዋል።

አሪስቶትል! ሥለጀግንነት ሲናገርለታላቅነት ተግባር ራሱን ያዋለ ሠው፣የሠብዓዊ ክብር ዓርማ ነው ብሎ ነበር።

ጀግኖች ግብና ዓላማ ቀርፀው የሚራመዱ በመሆናቸው ድፍረት፣ልበሙሉነትና አይበገሬነት መለያቸው ሥለሆነ ታላቅነት ከውስጣዊ ጀግንነት ሥሜታቸው ሥለሚመነጭ ምንጊዜም ከትግሉ ግንባር በቅድሚያ የሚቆሙ የትግል ፋና ወጊዎችና ገድል ፈፃሚዎች ናቸው።መከራና ፈተና አይበግራቸውም።ድሎት አያታልላቸውም።ለህዝብ ኖረው፣ሥለሕዝብ ታግለው፥ለሕዝብ ሲሉ ሕይወታቸውን ሠጥተው ያልፋሉ።

በየዘመናቱ ያለፉ መሪዎችንና የሀይማኖት አባቶችን፣ለምሳሌ የእነአቡነ ጴጥሮስንና የእነአፄ ቴዎድሮስን ተጋድሎ ሥናጤን፣የጠላትን ቅሥም ሰብረው የኢትዮጵያዊንትን የጀግንነት ገድል አሥመዝግበው ማለፋቸውን እናስታውሳለን። አፄ ቴዎድሮስ!ለጠላት እጄን አልሰጥም ብለው በጀግንነት እንደተሰው ለማንኛችንም ገሀድ ነው።ፕሮፌሰር አሥራት! የእነዚህ ትውልዶች አደራ ተረካቢ በመሆን ለህይወታቸው ሳይሳሱ ጠላትን ፊት ለፊት ተጋፍጠው አልፈዋል።

ኢትዮጵያ በሽዎች ለሚቆጠሩ ዘመናት የነፃነት ባለቤት ሆና የኖረችበት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋናውና አንዱ ኢትዮጵያ የጀግኖች መሀን አለመሆኗና ጀግኖች ልጆቿ በተለያየ ቦታና ጊዜ በከፈሉት መሥዋዕትነት እንደነበር ታሪክ ይመሠክራል።የክቡር ፕሮፌሰር አሥራት የመስዋዕትነት ትግል ለዚህ በቂ መረጃ ነው።

ሥለሆነም ለአማራው ህልውና፣ለሀገር ሉዐላዊነትና ለህዝብ አንድነት ቀናኢ የሆነው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ታሪክና ትውልድ የማይረሳው ተግባር ፈፅመው ያለፉት ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ፣ከዚህ ዓለም የተለዩበትን 18ኛ ዓመት አሥመልክቶ በታላቅ ሀዘንና ቁጭት አሥቦት እንዲውል እያስታወስን፣ይህን ዕለት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋና ድል ጋር አያይዞ የሚከበርበት ወቅት አሁን ባለው የጊዜና የሁኔታ ውስብስብነት ቢዘገይም አይቀሬ መሆኑን ሳናሰምርበት አናልፍም።

አሥራት የዘመናችን ታላቅ ሠው፣የፅናትና የልበሙሉነት፣የሀቀኝነትና የብልህነት፣የአርቆ አስተዋይነትናሚዛናዊነት ተምሳሌት በመሆን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ልብ በህያውነት የሚታወሱ ናቸው።

ዛሬ ፕሮፌሰር አሥራት ቢያልፉም፣ዓርማውን አንግበው፣በአይበገሬነት ሞትን እየሞቱ  የሚታገሉ እንደ እንጉዳይ የፈሉና እሳት የላሱ ሚሊዮን አሥራቶች መፈጠራቸው ሊያኮራን ይገባል። የሚሊዮን አሥራቶች መፈጠር ቢያስደስተንም፣ትግሉ እሥካሁን የተናጠል  ነው።

በዚህ አጋጣሚ ላሥታውስ የምፈልገው  እነክቡር ፕሮፌሰር አሥራት መዐሕድን  ያቋቋሙት እዚያው እሳቱ ካለበት አገር ውስጥና ሕዝቡ መሀል በመሆኑ፣ወሳኝ ሚና እንደነበረው ይታወቃል።መሆንም የነበረበት ይኸው ነው። እኛም በውጭ ሀገራት የምንኖር አማራዎች፣በየምንኖርባቸው ሀገራት የመዐሕድ የድጋፍ ኮሚቴዎች  አቋቁመን፣አገር ቤት የተቋቋመውን  የእነፕሮፌሰር አሥራትን መዐሕድ፣በገንዘብና በሎቢ ድጋፍ  እንረዳ ነበር።የምንታዘዘውም ሌሎች ጉዳዮች ሲኖሩ ትብብራችንን እናሳይ ነበር።

ዛሬም ውጭ አገር ከምንኖረው የሚጠበቀው ይኸው ነውና እንወቅበት እላለሁ። መዐሕድ ጥሩ መሪም ሥላጋጠመው  በአጭር ጊዜ ውሥጥ የሕዝብ ድጋፍ አገኘ፣በወቅቱ ያራመደው የሰላም ትግል ብቻ በመሆኑ ተጠቂ ሆነ። መዐሕድ  እንደነበረው የሕዝብ ድጋፍ መሣሪያ አለመታጠቁ ነው እንጂ ቢታጠቅ ኖሮ ድሉ የራሱ ይሆን እንደነበር አልጠራጠርም።

ታዲያ ዛሬ እየገደልኩ እሞታለሁ በሚል የአማራ ተጋድሎዎች ግብ ግብ ላይ እሥከሆኑ ድረስ፣የአገርቤቱ ትግል አንድወጥ እንዲሆን  ሁላችንም እንተባበር፣እንረባረብ። ይህ አገር ቤት እንደእነፕሮፌሰር መዐሕድ ከሕዝቡ መሀል  የሚኖር ድርጅት ወሳኝ ሚና መጫወት ይችላል።እኛ  ውጭ አገር የምንገኘው ደግሞ  የሲቪክም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች  አገር ቤት ለሚንቀሳቀሰው አንድ ኃይል የደጋፊነት  እንጅ፣ የወሳኝነት ሚና ሥለማይኖረንየገንዘብና የሎቢ ተግባራት ላይ መረባረብ ይገባናል እላለሁ።

ይህ መሠረታዊ የሆነ የትግል ሀ ሁ እንደሆነ ለማንኛችንም የተሰወረ ሥላልሆነ፣ የተናጠሉ ትግል  በአንድነቱ ትግል እንዲተካ  መልዕክቴን አሥተላልፋለሁ። ይህ ዓይነቱ  አካሄድ ብቻ ነው  ለአማራው ወገናችን ጥርጊያ መንገድ በመክፈት ፋይዳ ኖሮት ለድል የሚያበቃው።

ዛሬ ላለንበት ሁኔታ በትምህርት ሠጭነት  ያገለግል ዘንድ አንድ ነገር መጥቀስ እገደዳለሁ።ይኸውም በአንድ ወቅት “ መዐሕድን በመደገፍ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የተቋቋምነው ድርጅቶች ወደአንድነት መጥተን አንድ የአውሮፓ ቦርድ እንመሥርት” በማለት አንደኛው የድጋፍ ድርጅት የጥሪ ደብዳቤ ይልክልናል። ደብዳቤውም በጊዜው የተቋቋሙትን ድርጅቶች ይጠቅስና አንዱን ድርጅት ይዘለዋል።ይህ ደብዳቤ ለእነፕሮፌሰር አሥራት መዐሕድም ተልኳል።ይህንን ዝግጅት ለሚያዘጋጀው የድጋፍ ድርጅት ደውዬ ከመካከላችን አንዱ ድርጅት እንደተረሳ ሥጠቅስ፣ የተሰጠኝ መልስ “እሱ ኢሠፓ ነው” የሚል ነበር።ትክክል አለመሆኑን ሥላመንኩበት ሃሳቤን አቀረብኩ ግን አልሆነም።ከዚያም በቀጥታ ለፕሮፌሰር አሥራት ደውዬ “እንዲህ የሚል የጥሪ ደብዳቤ ደርሶናል”ሥላቸው።አዎን “ለእኛም ደርሶናል፣ድርጅት ተፈጥሮ ልርዳችሁ ሲለን፣ደሥ ይለናል፣የሚፈጠረው ግን ችግር ለመፍጠር ከሆነ ባይፈጠር ይሻላል”ነበር ያሉት።

በመጨረሻ! የአሥራትን ውለታ እንዴት እንከፍላለን ሥንል፣ የትግል ዓርማቸውንና የመንፈስ ጥንካሯቸውን ተላብሰን በመታገል ነው።በኢትዮጵያ ምድር የዓሥራት ዓላማ ተግባራዊ እሥከሚሆን  ድረስ ትውልድ ሁሉ ትግሉን መቀጠሉ ውለታ ከፋይነቱን የሚያረጋግጥ ይሆናል።

የሰማዕቱ የአሥራት ሥራ ህያው ሆኖ ለዘለዓለም ይኖራል!

ለአማራው ህልውናና ለነፃነት የሚደረገው ትግል እሥከድል ይቀጥላል!

ሞት  ለፀረ-አማራዎች

አያሌው ፈንቴ

 

 

 

የፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ የህይወት ታሪክ!

                                       የአሥራት ዕድገትና ትምህርት

ፕሮፌሰር አሥራት ሰኔ 12 ቀን 1920 ዓም ከአባታቸው ከአቶ ወልደየስ አልታዬና ከእናታቸው ከወ/ሮ በሰልፍ ይዋሉ ፅጌ  በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ:: ሦስት ዓመት ሲሆናቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ድሬዳዋ ሄደው የቤተክርስቲያን ትምህርት በመከታተል በሰባት ዓመት ዕድሜያቸው ዳዊት ደግመው አጠናቀዋል::አስተማሪያቸው የነበሩት አለቃ ለማ ወልደ መስቀል እንደመሰከሩት ፕሮፌሰር አሥራት በጣም ጎበዝ ተማሪ ስለነበሩ ዓመት ሳይሞላቸው ወንጌልን ከነቁጥር ከፍካሬ እስከነቢያት በመድገማቸው  ዲቁናም ተቀብለዋል::  በዕድሜያቸው ሳይሆን በትምህርት ባሳዩት ብልጫ የተማሪዎች አለቃም ነበሩ::

ፈረንሣይ ት/ቤት ገብተው ዘመናዊውን ትምህርት ለመከታተል በመሰናዳት ላይ ሳሉ ኢጣልያ አገራችንን ሥለወረረች ትምህርታቸው ሊሰናከል በቅቷል:: የካቲት 12ቀን 1929 ዓም ኢጣልያ አዲስ አበባ ውስጥ በአካፋና በዶማ በግፍ ከጨፈጨፋቸው ብዙ ሽህ የነፃነት ሰማዕታት ኢትዮጵያውያን መካከል የፕሮፌሰር አሥራት አባት አንዱ ናቸው:: እናታቸውም በህመም ሞቱ:: አያታቸው ቀኛዝማች ፅጌ ወረደወርቅ በግዞት ወደኢጣልያ አገር ተወስደው ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ወደአገራቸው ተመልሰው ፕሮፌሰር አሥራትን ከድሬዳዋ ወደአዲስ አበባ አመጧቸው:: ፕሮፌሰርም ለአምስት ዓመት ያህል ከቤተሰብና ከአካባቢ ከሚገኘው ትምህርት በስተቀር መደበኛ ትምህርት ለመከታተል አልቻሉም ነበር:: ኢጣልያ ከተባረረም በኋላ እስኪረጋጋ ድረስ በሚል ለዘጠኝ ወራት ያህል አልተማሩም::

 

ከዚህ በኋላ በ1934 ዓም በተፈሪ መኮነን ት/ቤት በመግባት ዘመናዊውን ትምህርት መከታተል ጀመሩ::ፕሮፌሰር አዲስ አበባ ከመጡ ጀምሮ ከአያታቸው ተለይተው አይውሉም ነበር።  አያትና የልጅ ልጅ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ተያይዘው ነበር  የሚዘዋወሩት። አሥራት ከልጅነታቸው ጀምሮ ብልህና ያስተማሯቸውን ወዲያውኑ የመቀበል የላቀ ተሰጥኦ ነበራቸው:: ጠላት እንደወጣ ራዲዮ በየአደባባዩ ተተክሎ ስለነበር አያታቸው አሥራትን ራዲዮ የተናገረውን አዳምጠው እንዲመጡ ሲልኳቸው በጥሞና አዳምጠው የሰሙትን ሁሉ ለአያታቸው ልቅም አድርገው ይነግሯቸው ነበር::

 

አያታቸው አሥራትን በፍትህ አዋቂነታቸው ያደንቋቸው ስለነበር በቤተሰብ መካከል አለመግባባትና ጥል ሲፈጠር ሁኔታውን ሰምተውና  አመዛዝነው ዳኝነት እንዲሰጡ ያዟቸው ነበር:: አያታቸውም አሥራትን በክርስትና ስማቸው ”መልአከ ብርሃን” ነበር የሚሏቸው:: ”ሀገራችን ጥበብ የሚያውቁ ልጆች ቢኖሯት እኮ ትልቅ ሀገር ነበረች….የማይናቅ ሕዝብና ባህል አላት”እያሉ የሀገር ፍቅርና የወገን አንድነትን መሠረትና ጥቅም ያስተምሯችው ነበር::ፕሮፌሰር አሥራት ስለሕግና ፍትህ ግንዛቤ ማግኘትና ጽኑ የሀገር ፍቅር ስሜት በልባቸው መንደድ የጀመረው በዚያ ጊዜ ነው::

 

በተፈሪ መኮነን ት/ቤት የዛን ጊዜው የትምህርት ደረጃ እንደዛሬው አልነበረም:: ት/ቤቱ እስከ 30 የሚደርሱ ክፍሎች ሲኖሩት ጎበዝ የሚባል ተማሪ የሚገባው አነስተኛ ክፍል ውስጥ ነበር:: 30ኛው ክፍል ማለት ዝቅተኛው  ሲሆን  1ኛ ክፍል ከፍተኛው የጎበዞች ክፍል ነበር:: በመጀመሪያ አሥራት ቀደም ብለው ንባቡንና ሌላውንም ተምረውት ስለነበር ሲፈተኑ ጥሩ ውጤት ስላገኙ 13ኛ ክፍል  ገቡ::በዚሁ ዓመት ከተማሪዎች ሁሉ ልቀው በመገኘታቸው ወደ 1ኛ ክፍል ተዛወሩ:: በ1935 ዓም ከጠቅላላው የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች አንደኛ በመውጣታችው የካሜራ ሽልማት አገኙ::

 

በዚሁ ዓመት የከፍተኛ ትምህርት ዕድል አግኝተው ወደግብፅ አለክሳንድሪያ ሄዱ::በቪክቶሪያ ኮሌጅም ገቡ::የሀገር ናፍቆትና የበዓላት አለመጣጣም ቢያስችግራቸውም ትምህርቱን በሚያስደንቅ ሁኔታ አጣደፉት:: መጀመሪያ ላይ ያስገቧቸው በዝቅተኛ ደረጃ በሚገኝ ክፍል ቢሆንም በመጀመሪያ ”ተርም” ባገኙት አስደናቂ ውጤት ወደ2ኛ ደረጃ ተሸጋገሩ::ጎበዝ ተማሪ በኮሌጅ የመኝታ ክፍሎች ሀላፊ ይሆን ነበርና አሥራትም ኃላፊ ሆኑ::አብረዋቸው የተማሩትን የዮርዳኖስ ንጉስ የነበሩትን ሁሴንንና ሌሎችንም ያስጠኑ ነበር::

 

አሥራት ትምህርት የመቀበል ችሎታቸው የላቀ መሆኑ የሚያስደንቅ ነበር::ቀደም ብሎ ያልተጤነውና በኋላ ላይ ጎልቶ የታየው ግን ለሃይማኖታቸው ያላቸው ጽናትና  አትንኩኝ ባይነታቸው ነው::አሥራት በሰው ሀገር ያውም በአረብ ሀገር ግብፅ ”በፆም አልበላም” በማለት የትምህርት ቤት ሀላፊዎቻቸውን ያስቸግሩ ነበር::በአንድ ወቅት ብላቴን ጌታ ሎሬንሶ ትዕዛዝ ግብፅ ሄደው ሳለ ”አሥራት በፆም አልበላም ብሎ አስቸገረ” ተብሎ ተነገራቸው::

 

ሎሬንሶ አሥራትን አቅርበው ”እኛ እንኳን እንበላ የለም አንዴ አንተም መብላት አለብህ”በማለት ምክርና ግሳፄ ቢሰጧቸው ”እርስዎ ገደል ቢገቡ እኔ ገደል እገባለሁ ወይ?” በማለት ቁርጥ ያለ መልስ ሰጥተዋቸዋል::

አሥራት በግብፅ የአምስት ዓመት ቆይታቸው ከፍተኛ የትምህርት ውጤት አግኝተዋል::እንግሊዝ ሀገር ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያስችለውን የሁለት ዓመት ትምህርት ያጠናቀቁት በአንድ ዓመት ብቻ ነበር::በዚሁ ውጤታቸው ወደእንግሊዝ ሀገር ሄደው ስኮትላንድ በሚገኘው ኤደንብራ(ኤደንበርግ)ዩኒቨርሲቲ ገቡ።

 

በወቅቱ ከነበሩት የትምህርት ሚኒስትራችን ሳይቀር በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት እንዲከታተሉ ቢታዘዙም አልተቀበሉትም::ልባቸው የፈቀደውና ፍላጎት ያደረባቸው የህክምና ሙያ ማወቅን ነበርና የህክምና ትምህርት ለመከታተል ወሰኑ::ህክምናን የመረጡበት ምክንያት

 

(1ኛ )የታመሙ እናታቸው ሆስፒታል ገብተው መሞታቸው፣(2ኛ)አንድ ጊዜ ከግብፅ ለዕረፍት ወደሀገራቸው መጥተው ሳሉ ታመው ሆስፒታል ገብተው ሲታከሙ ብዙ ስዎች እየሞቱ እሬሳቸው ሲወጣ ማየታቸው፣ (3ኛ) ”የፈረንጅ ጥበብ ማወቅ”የሚለው የአያታቸው ምክር በውስጣቸው ማደሩ የመሳሰሉ ነበሩ::

 

                                      

                                               አሥራትና ህክምና

 

አሥራት በኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የህክምና ተማሪና ከጠላት ወረራ በኋላ ወደውጭ ሀገር ከተላኩት ኢትዮጵያውያን መካከል 42ኛው ነበሩ::ከስድስት ዓመት በኋላም ትምህርታቸውን አጠናቀው ተመረቁ::ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአንድ ዓመት ያህል በሁስፒታሉ ልምምድ ሲያደርጉ ቆይተው በ1947ዓም መደበኛ ሥራቸውን በልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል ጀመሩ:: ከፋሽስት ወረራ በኋላ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሐኪም ናቸው::

 

በፋሽስት ወረራ ወቅት ጠላትን ካስጨነቁት ስመ ጥሩ አርበኞች መካከል አንዱ ደጃዝማች ፀሐዩ እንቁ ሥላሴ ነበሩ::ደጃዝማች ፀሐዩ ጠላት ተባሮ ነፃነት ከተመለሰ በኋላ የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነቱ ሥራ ከነበራቸው ችሎታ ጋር እንደማይጣጣምና ለእርሳቸው እንደማይመጥን ስለተገነዘቡ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ሥራውን እስከሚረከቧቸው ድረስ ኃላፊነቱን ለፈረንጆች አሳልፎ ላለመስጠት ቀን ይጠብቁ ነበር::ጊዜው ደረሰና የተማሩ ኢትዮጵያውያን ብቅ ማለት ጀመሩ::

 

”እኛ በአርበኝነት ይህችን አገር ከኢትዮጵያ ጠላቶች ሥንጠብቃት ከረምን።አሁን የተማራችሁት ኢትዮጵያውያን ተገቢውን አመራርና ኃላፊነት ለመውሰድ ስለመጣችሁ በጣም ተደስተናል::እኔም ከፈረንጆቹ እጅ እንዳይወድቅ ስጠብቅ የነበረውን ይህንን የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነቱን መቀመጫ ተረከብ::ለአስረካቢነት ያበቃኝን አምላክ አመሰግነዋለሁ::በጣም ደስ ብሎኛል::ይህንንም ለግርማዊ ጃንሆይ አስረዳለሁ” በማለት ደጃዝማች ፀሐዩ ለፕሮፌሰር አሥራት ነገሯችው::

ደጃዝማች ፀሐዩ ይህንን ቢሉም ሥልጣኑን እንዲረከቡ የተጠየቁት ሐኪም ፈቃደኛ አልሆኑም::ይበልጥ ለአገርና ለወገን መሥራት የሚያስችላቸው በቀጥታ በህክምናው ሞያ ተሰማርተው መገኘቱ እንደሆነ አስረዱ::ደጃዝማች ግን አረኩም::ብቻ የወንበሩ ርክክብ ሳይሆን ቀረ::ሐኪሙም በቀጥታ በሙያው ውስጥ ገቡበት::ዕውቅ ሐኪም ለመሆንም በቁ::

 

የአምስት ዓመት የሕክምና አገልግሎት ከሰጡ በኋላ እንደገና ወደ ብሪታንያ ሄደው ኤደንብራና ኢንግላንድ ውስጥ በሚገኙት ሮያል ኮሌጅ ኦፍ ሰርጀንስ በቀዶ ሕክምና ልዩ ትምህርት ተከታትለው አጠናቀቁ::ይህን ለመከታተል ቀደም ብለው መሄድ ነበረባቸው::ይህን አስመልክተው በአንድ ወቅት ከጋዜጠኞች ለቀረበላችው ጥያቄ  ሲመልሱ ”አያቴ ያማችው ነበርና እኔ በሌለሁበት የሞቱ እንደሆን እፀፀታለሁ ብዬ ዘገየሁ:: ደህና እየሆኑ ሳያችው ግን ሄድሁ:፡  ብቻ እድለኛ አልነበርኩም ሞቱ! ሳልቀብራቸው ቀረሁ”በማለት በቁጭትና በፀፀት መልሰዋል::

 

አሥራት ከፍተኛ የቤተሰብ ፍቅር አላቸው::ይህ ፍቅር ጠንካራ የወገን መውደድን ትቶላቸው አልፏል:: በልዕልት ፀሐይና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች በሰርጀንና በዋና ሰርጀንነት/የቀዶ ጥገና ሐኪምነት/ ከሰላሳ ዓመታት በላይ ሕመምተኞችን በቅንነትና ባለመታከት አገልግለዋል::

በአገራችን የህክምና አገልግሎቶችና ልዩ ልዩ ጥናቶች ውስጥ በሃላፊነት ደረጃ ከመካፈላቸውም በላይ በቀድሞው “የኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ” የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ የሕክምና ፋካልቲ ዲንም ነበሩ::

የሕክምና ዳይሬክተር በነበሩበት ጊዜ የልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል ተስፋፍቶና ተጠናክሮ እንዲገኝ በብርቱ ጥረዋል:: በኢትዮጵያ እራሳቸው ያልተሳተፉበት ዋና ዋና የህክምና ፖሊሲ  አወጣጥና አገልግሎት አልነበረም ብሎ መናገር ይቻላል::

 

ፕሮፌሰር አስራት ባሳለፉት ሠላሳ ዓመታት   የህክምና ዘመን  ውስጥ የአያሌ ሕሙማንን ሕይወት ስለማትረፋቸውና ለሙያቸው ከፍተኛ ፅናት ያላቸው ስለመሆኑ በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ:: በቀን እስከ አስራ ስምንት ሰዓት ድረስ የሰሩባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው:: በተለይም ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት መኖሪያቸው በቅጥር ግቢ ውስጥ ስለነበር የጠናበት በሽተኛ ከመጣ እርሳቸው መጠራታቸው የግድ ነበር:: የተረኝነት ጉዳይ የለም::

 

                                        ስለሞያቸው ምሥክርነት

 

-በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎቸ የራሳቸው ምስክርነት አላቸው። በወቅቱ ለረጅም ዓመታት ፀሐፊያቸው የነበሩ እንዲህ ይላሉ። ”ከእርሳቸው ጋር በፀሐፊነት ለረጅም ጊዜ ሠርቻለሁ።ሌት ተቀን ይሠራሉ።የሕክምናውንም የአስተዳደሩንም ሥራ ይሠራሉ። የምሳና የቁርስ ጊዜ ማክበር  የሚባል ነገር የለም።የእርሳቸውን ሁኔታ እያየሁ የምሳ ሰዓቴን ለመሠዋት ተገድጃለሁ። በታካሚዎቻቸውም ሆነ በሥራ ባልደረቦቻቸውም ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ አላቸው።ከሁሉ የሚደንቀኝ ደክሞኛል ማለትን ያለማውቃቸው ነው።”

 

-በልዕልት ፀሐይና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎቸ ሰላሳ ዓመታት ያገለገሉት ሲስተር አልማዝ ለማ  ፕሮፌሰር አሥራትን የሚያውቋቸው ከነርስነት ሙያ ተማሪነታቸው ጊዜ ጀምሮ ነው። ”ፕሮፌሰር አሥራት ለሕመምተኞቻቸው ታላቅ አክብሮት አላቸው። ሰው አይመርጡም ።በሥራው ዓለም ከወጣትነት ጀምሮ እስከተለየኋቸው ጊዜ የማይሰለቹና የማይደክሙ ባለሙያ ሆነው ነው ያገኘኋቸው።ከባድ የልብ ኦፕራሲዮን ካደረጉም ወዲህ አልተለወጡም።ሌት ተቀን የሚሠሩባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው። በጣም እናከብራቸዋለን።ለሙያቸው ከፍተኛ ፍቅር ስላላቸው እኛንም አርዓያነታቸውን ለመከተል አስቸለውናል።

 

በሽተኞችም በእርሳቸው ላይ ያላቸው እምነት በጣም የላቀ ነው።ከሃያ አምስት ዓመት በፊት ከአርባ ምንጭ የመጡ አንድ ታካሚ አዛውንት <አሥራት የሚባል ጠበል ፈልቋል ስላሉኝ ነው ወደዚህ የመጣሁት> ያሏቸውን አስታውሳለሁ።በርሳቸው ላይ ያላቸውን አመኔታና ከበሬታ ለመግለፅ ያሉት እንደሆነም እረዳለሁ፧ የቀዶ ሕክምናውን ጥበብ ከመካናቸውና መሥራት ከመጀመራቸው በፊት ሁለገብ ሐኪም ነበሩ።ያዋልዱም ነበር።”ይላሉ ሲስተሯ።

 

-ዶክተር ሥዩም ዮሴፍ ፕሮፌሰር አሥራትን ከሃያ ስድስት ዓመታት ጀምሮ ያውቋቸዋል።የፕሮፌሰር አሥራት የሕክምና ተማሪም ነበሩ። ”ፕሮፌሰር አሥራት አስተማሪዬ ነበር።እንከን የማይወጣለት አስተማሪ ነው።ተማሪው ማግኘት ያለበትን እውቀት አግኝቷል ብሎ ካላመነ ከክፍሉ ንቅነቅ አይልም።ለሙያው ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት አለው።ሕይወቱን በሙሉ ለዚህ ተግባር ያዋለ ነው።ሕመምተኛም ሲሰቃይ ይሰቃይል፡ ሲታመም ይታመማል። ሰብዓዊነትን የተላበሰ ነው።

የተጣራ ሥራ ነው የሚሠራው።ሱፐር ሰርጀን ነው።አስፈላጊውን የቅድሚያ ምርመራ ሳያካሂድ ቀዶ ሕክምና አያደርግም።ከቀደደ በኋላም ደህና ነው ብሎ በሽተኛውን አይተውም። በተለይ ሰባ ሁለት ሰዓት እስኪሞላ በቀን አራት ጊዜ ያህል ተመላልሶ ይጠይቃል።ከዚያ በኋላም የበዓላት ቀን ሳይመርጥ ይጠይቃል።

በሽተኛን በጎሳው በሃይማኖቱ ወዘተ አይመርጥም።ለሰው ሕይወት ከፍተኛ ዋጋ ይሰጣል ። በበሽተኞቹም ሆነ በሥራ ባልደረቦቹ ዘንድ አክብሮትና አድናቆትን የተቸረና የተወደደም ነው።ላመነበት ነገር ከቶውንም ወደኋላ አይልም፧በብዙዎች ባለሙያዎች ዘንድ እንደ አባትና አስተማሪ የተከበረና የታፈረም ነው። እርሱ አይናገረው እንጂ ችግረኞችን በገንዘብ ጭምር ይረዳል።” ብለዋል ዶክተር ሥዩም።

 

-አንድ የ18 ዓመት ዕድሜ ያለው የግሪክ ወጣት ለሽርሽር ናዝሬት ሄዶ በድንገት በጥይት ይመታል።አዲስ አበባ መጥቶ አሥራት የቀዶ ጥገና ያደርጉለታል።ቀዶ ሕክምናውን ያደረጉት እርሳቸው በመሆናቸው በከተማው ያሉት የግሪክ ኮሙኒቲ አባላት ተደናግጠዋል።

በሦሥተኛው ቀን ዶክተር አሥራት ለኮንፈረንስ ውጭ አገር መሄድ ስለነበረባቸው የልጁን ሁኔታ ለቀሩት ሐኪሞች አደራ ብለው ሄዱ።ይህንን አጋጣሚ ያገኙ የግሪክ ኮሙኒቲ አባላት ከግሪክ አገር ግሪካዊ ፕሮፌስር እንዲመጣ የጃንሆይን ፈቃድ ይጠይቃሉ።ተፈቀደላቸውና ግሪካዊው የሕክምና ፕሮፌሰር መጥተው የልጁን ሁኔታ መርምረው ከተገነዘቡ በኋላ ለሐኪም ቤቱና ለጃንሆይ ”ከመገረምና ከመደነቅ በቀር የምጨምረው ነገር የለም።እዚህ አገር እንዲህ ያለ ነገር ከተሠራ እኔ ለምን ተጠራሁ? ” ብለው ወደአገራቸው ተመለሱ።

 

-በፕሮፌሰር አሥራት ድንቅ ችሎታ የተደነቁት ግሪኮች ብቻ አልነበሩም እንግሊዞችም ተደንቀዋል አድናቆታቸውንም በፅሁፍ ገልፀዋል።እንግሊዛዊቷ ወይዘሮ ማግደሊን ዋይን ወደኢትዮጵያ መጥተው በአደጋ ምክንያት ከሞት አፋፍ ላይ ይደርሳሉ። ፕሮፌሰር አሥራት ቀዶ ሕክምና አድርገው ሁለት ቀን አውለው ካሳደሯቸው በኋላ ሴትዮዋ ለንደን ደርሰው ሕክምና ላይ እንዳሉ ሞቱ ።

ይሁንና ፈረንጆቹ የሴትዮዋ ነፍስ እስከዚያ ቀንም ድረስ መሰንበቱ በአሥራት ችሎታ መሆኑን ተገንዝበው ፕሮፌሰርን አደነቋቸው።ይኸውም ይታወቅ ዘንድ የብሪታኒያ አምባሳደር ከፃፉት ሌላ የብሪታኒያ ቆንሲል የፃፈው ትርጉም እነሆ ”ተወዳጁ አሥራት  በቅድሚያ የኒክ ታይለር እህት በደረሰባቸው አሰቃቂ አደጋ ወቅት ላሳዩት ደግነትና ወደር ለማይገኝለት ችሎታዎ ጥልቅ ምስጋናዬን በብሪታኒያ ቆንስል ስም አቀርባለሁ።መጨረሻው ጥሩ እንደማይሆን ብገምትም ከአደጋው በኋላ በትንሹ ሕይወታቸውን ሁለት ጊዜ እንዳቆዩላቸው ተረድቻለሁ።

የፈፀሙት የላቀ ተግባር ሁሉ ከፍተኛ አድናቆት አሳድሮብኛል።በሙያዎ ለፈፀሙት ምግባር አስፈላጊ ሲሆን የሚያስፈልግዎን እንዲገልጹልኝ በክብሮት አስታውቃለሁ።በአሁኑ ጊዜ ገንዘብ ምንም አይደለም። ከዚህስ ይልቅ ለእኛ ትልቁና አስፈላጊያችን ደግነትዎ ችሎታዎና የችግራችን ተካፋይነትዎ ነው። እንደገና አመሰግነዎታለሁ።”

 

-“ዕውቁ የቀዶ ሕክምና ሀኪም ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ካሉበት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንድገባ ተወሰነና ረቡዕ ቀን ተኛሁ። ባለቤቴ በሦሥት ቀኔ መጣች፡፤…..ኢትዮጵያዊ ያገቡ እንግሊዛዊ ሌት ተቀን ይንከባከቡኝ ነበር።…ሦስት የብሪታንያውያን ኮሚዩኒቲ አባሎችም ደም ሰጡ።ይህ ሁሉ እንክብካቤ ግን ትርፍ አንጀቴን መንጥቀው ከገላገሉኝ ካለ ተደናቂው ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ምንም አልነበረም።” ጆናታን ቴሌ(ዘጋርዲያን ጋዜጣ)

 

-“35ዓመት ሙሉ ባደረጉልኝ ጥረት ይኸው የቀረው አንድ እግሬ በእሳቸው ኃይል ቆይቶልኛል።አሁን ልጆቼን የማሳድገውና የምኖረው በዓሥራት ነው።በዕውነት ልዩ ሠው ናቸው።ሰው አክባሪና ደግ ፍጡር ናቸው።ዕድሜ ለአሥራት። የሚገርመኝ የሁሉንም ሥራ ይሠራሉ።ግን አይደክሙም።” አቶ ሀብታሙ በቀለ

 

-”..10ዓመት ሙሉ ስታመም ዘጠን ጊዜ ኦፕራሲዮን አድርገውኛል። እንደሳቸው ሕሙማኑን እጅግ የሚወድ ለሰው ነፍስ አጥብቆ የሚጨነቅ አላየሁም።..”  አቶ አጥናፉ ተሰማ

 

እኚህ በችሎታቸው የሚተማመኑ የሕክምና ባለሙያ በሳል ትሁትና ቆፍጣናም ናቸው።አንደበታቸው ቁጥብ ግን አሳማኝ ነው።የሚያወጧቸው ሃሳቦች ደርዝ አላቸው። ከነጥቡ ውጭ አይዘልም። የማስታዎስ ችሎታቸውም የዋዛ አይደለም።ወደኋላ ተመልሰው ቀንና ዓመተ ምህረት ጠቅሰው ድረጊቱን መዘርዘር ይቻላቸዋል። ነገር ፈጥኖ ይገባቸዋል። በአሁኑ ጊዜ የተላበሱት አረጋዊ ስብዕናቸው አክብሮት እንዲቸራቸው አድርጓቸዋል።በንግግራቸው ውስጥ የእግዚአብሔርን ኃያልነት ባግባቡ ሳያነሱ አያልፉም።ስለሥራቸውም አድናቆት ሲሰጣቸው ”ብቻየን አላደረግሁትም ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር እንጂ ” ማለትን ይደጋግማሉ።

 

በ1972ዓ.ም.ደርግ ፕሮፌሰር አሥራትን በዘመቻ ሥም ወደምፅዋ ልኳቸዋል።ውስጥ አዋቂዎች ዛሬ እንደሚናገሩት በወቅቱ የተላኩት ”አድሀሪ” በሚል ሰበብ እንዲገደሉ ሁኔታዎች ለማመቻቸት ነው ይላሉ።ፕሮፌሰር ሞትን አዝለው በዘመቻው ላይ በትጋትና በጥንካሬ ተካፍለዋል።የዘመቱት ለማከም እንጅ ለመዋጋት አይደለም።አዎ በውቅቱ ያከሙት የኢትዮጵያን ወታደር ብቻ አልነበረም።የሻዕቢያን ወዶገብና ምርኮኞች ጭምር ነበር።

 

በወቅቱ  ዘርና ጎሳ ሃይማኖትና እምነት ሳይለዩ የፖለቲካ ወገናዊነት ሳያሳዩ የኢትዮጵያን ልጆች ሁሉ እኩል አክመዋል።ፕሮፌሰር አሥራት ሕይወት ለማትረፍና ከሥቃይ ለማዳን የማያደርጉት የለም።ለበሽተኞቻቸው ያላቸው ፍቅርና የሚያደርጉት እንክብካቤ እጅግ ከፍተኛ ነው።

 

አብረዋቸው ከሚሰሩት የሥራ ባልደረቦቻቸው ይልቅ ለበሽተኞቻቸው ያደላሉ።በሥራ ዋዛ ፈዛዛ የለም።ትንሽ ጥፋት ከተሰራ ይቆጣሉ።በሕይወት ቧልት አይውቁም። ማንም ይሁን ማን ትክክል ያልሠራ ከመሰላቸው መናገራቸው አይቀርም።ፈረንጅ ይሁን አበሻ ዶክተር ይሁን ነርስ በሥራ ይሉኝታ የላቸውም።

ስህተት አይተው ስለማያልፉ የምትፈራቸው አንዲት ነርስ ጧት የለበሰችውን ከሰዓት በኋላ ለውጣ  ትመጣለች።ታዲያ ጓደኞቿ ”ጧት ሌላ ለብሰሽ አሁን ይኸን ምን አስለወጠሽ?”ይሏታል።”አሁን ከዶክተር አሥራት ጋር ነው የምሠራው”ትላለች። ”ታዲያ ቢሆንስ ”ይሏታል። ”የጧቱ ጠበብ ያለ ነበር አሁን ይህን ሠፊ ልብስ የለበስኩት ዶክተር ሲቆጡኝ ስለሚያልበኝ እንዳይጣበቅብኝ ብዬ ነው” በማለት ተናግራለች።

በሽተኞቻቸው ዘንድ ሁል ጊዜ ሳቂታና ፊታቸው እንደበራ ነው። ”በሽተኛ አይጉደልበት ፣በሽተኛ አይከፋ ፣የተቻለው ሁሉ ይሟላለት ” ነው የሚሉት።በሽተኞች የአሥራትን ሕክምና ብቻ ሳይሆን የእጅ ዳበሳቸውንም ጭምር ይወዱታል።የሥራ ባልደረቦቻቸው ”የበሽተኛ ጠበቃ ”ይሏቸዋል።

 

                                           ሥራት በፖለቲካ ውስጥ

በ1983ዓ.ም.የደርግ መንግሥት ወድቆ ኢሕአዴግ ሲተካ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ፋካልቲ ዲን ነበሩ።የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በመረጧቸው መሠረት በሰኔ 1983ቱ ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተዋል። በኮንፈረንሱ ላይ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል የሚፈቅደውንና”መገንጠል” የኢትዮጵያ የወደፊት መተዳደሪያ እንዲሆን የሚያረጋግጡትን አንቀጾች የተቃወሙ ብቸኛ የጉባዔ ተሳታፊ ነበሩ።በተለይ ስለኢትዮጵያና ስለኤርትራ ታሪክ የተሰጠውን ትንተና የማይቀበሉት መሆኑን ገልፀዋል።

”ይህ ጉባዔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምንም ጉዳይ ሊወስን ሊያግድ ወይም ሊሰርዝ አይችልም። ሆኖም የኢትዮጵያን የአሁኑን ተጨባጭ ሁኔታ በመመርኮዝ የወንድማማቾች ደም መፋሰስ የቆመ በመሆኑ አሁን የሰፈነውን የሰላምና የዲሞክራሲያዊ ሂደት መሠረት በማድረግ፡ የኢሕአዴግና የሕዝባዊ ግምባር ሀርነት ኤርትራን ልዩ ግንኙነት በመጠቀም ወንድማማችና እህትማማች በሆኑት ሕዝቦች መካከል የዘለቄታ ቅራኔ እንዲወገድና በኢትዮጵያዊነትና በይቅር ለእግዚአብሔር መሠረት በአስቸኳይ የሚስማሙበትን  መንገድ መፈለግ ለመሸጋገሪያ መንግሥት ተቀዳሚ ተግባር እንዲሆን ጉባዔው እንዲያሳስብ ይህን ሀሳብ በአክብሮት አቀርባለሁ ” ነበር ያሉት።

ከዚህ ኮንፈረንስ በኋላም የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን በመወከል በተቋቋመው የሽግግር መንግስት በተወካዮች ምክር ቤት አባልነት እንዲሰሩ ተደጋጋሚ ጥሪ ተደርጎላቸው አልተቀበሉትም።የኤርትራን መገንጠል በግልጽ መቃወማቸውና ተቋቋመ በተባለው የተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ላለመሳተፍ የወሰዱት ቁርጠኛ አቋም በወያኔና ሻዕቢያ ጥርስ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ!  የአገር መፍረስ የአንድነት መናጋት የታሪካችን መደለዝ አንገበገባቸው።በተለይ ዐማራው ዐማራ ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ በያለበት በግፍ መገደሉ መዘረፍ መታሰሩ መሰደዱ ሊሸከሙት የማይችሉት ስቃይ ሆነባቸው።ይህን አገር የማፍረስ ኢትዮጵያውያንን በዘር በጎሳና በጎጥ እየለዩ እርስ በርስ የማጫረስ አፍራሽ ፖሊሲ በሰላማዊ ሁኔታ ለመታገል የመደራጀትን አስፈላጊነት አመኑበት።

ሥለዚህም ቆርጠው ከተነሱ ወንድሞቻቸው ጋር በመመካከር መዐሕድን አቋቋሙ።በፕሬዚዳንትነትም መሩት። መዐሕድና ፕሮፌሰር አሥራት ታሪካዊ አንድነታችን ይከበር፡ ዐማራውን አትግደሉት አትረዱት አታንገላቱት ሰበዓዊ መብቱን አትንፈጉት በማለት ተከራከሩ። ለመንግስት አካላት፣ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ፣ለዓለም ሥላም ወዳድና ሰባዓዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅቶች ሁሉ አቤት አሉ። ”ዴሞክራሲያዊ ነኝ ”ባዩን ወያኔን  እርቃኑን አስቀሩት።

ኢሕአዴግ የመዐሕድንና የፕሮፌሰር አሥራትን እርምጃ አልወደደም። ገና ከጅምሩ ”ነፍጠኞች፣ ትምክህተኞች፣ያለፈው ሥርዓት ናፋቂዎች ” ወዘተ …እያለ ማውገዝ ጀመረ።መዐሕድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍ ያለ ሕዝባዊ ተቀባይነትን አገኘ። የኢሕአዴግ ጥላቻና ጥቃትም አደገ። በተለይ ከ1985ዓ.ም.ጥር ወር ጀምሮ ግልጽ ጥቃት ሠነዘረ።አባላትና መሪዎችን መግደል  ማቁሰል ማፈን ማሰርና ማስፈራራቱን በመንግሥት የመገናኛ ብዙሀን  በሠፊው በሚሰራጭ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አስደግፎ አጧጧፈ። አሥራትም የዚህ ጥቃት ኢላማ ሆኑ። ከጥር 1985ዓ.ም. ጀምሮ በፀጥታ ኃይሎች ሥውር ክትትል ይደረግባችው ጀመር። በሁለትና በሦሥት መኪናዎች ዙሪያቸውን እየተከበቡ ግራ እንዲጋቡ እንዲጨነቁና እንዲፈሩ ለማድረግ ተሞከረ።ሰበብ ተፈልጎ ክስ ተመሠረተ ።ከሕግና ከሥርዐት  ራሳቸውን ያራቁ ለመምሰልም በመንግስት መገናኛ ብዙሀን ሳይቀር ”ካሉበት ለሕግ እንዲቀርቡ ”የሚል ጥሪም ተላለፈ።

ታህሣሥ 11ቀን 1985ዓ.ም. በደብረ ብርሃን ከተማ በተደረገው ሕጋዊ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር ”የጦርነት ቅስቀሳ ”ተባለና ፕሮፌሰር አሥራት በፖሊስ ታሰሩ።በ50ሽህ ብር ዋስትና ተለቀቁ።

ከጎጃም ከመጡ ገበሬዎች ጋር በመዐሕድ ጽህፈት ቤት በመሰብሰብ የአድማ ወንጀል ፈፀሙ የሚል ሌላ ክስ ተመሥርቶ ጉዳዩን የቀጨኔ አውራጃ ፍርድ ቤት በቀዳሚ ምርመራ ማየት ጀመረ ።

ከሐምሌ 12 ቀን 1985 ዓ.ም. ጀምሮ የዋስትና መብት ተነፍጓቸው በእስር እንዲቆዩ ተወሰነ።ጉዳዩ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ቀርቦ ከ 43 ቀናት እሥር በኋላ በ 30ሽህ ብር ዋስትና ተለቀቁ። ይህ ክስ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርቦ መደበኛ ክርክር ሲደረግበት ከቆየ በኋላ ከሰኔ 20ቀን 1986 ዓ.ም. ጀምሮ በሁለት ዓመት እሥራት እንዲቀጡ ተወስኖ ወደ ወህኒ ወረዱ። በደብረብርሃኑ ንግግር ክስ ከውህኒ ቤት ወደ ፍርድ ቤት ሲመላለሱ ከቆዩ በኋላ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ታህሣሥ 18 ቀን 1987ዓ.ም. የሦሥት ዓመት እሥራት ተፈረደባቸው።

መስከረም 10 ቀን 1987ዓ.ም. በዋለው የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ በመገኘት የሁለት ወራት ናፍቆቱን ለመወጣትና የእንኳን (የ67ኛ የልደት በዓላቸው)  አደረሰዎ የመልካም ምኞት መግለጫ ስሜቱን ለማስተላለፍ በፍትህ አደባባይ በተገኘው ደጋፊያቸውና ወዳጅ ዘመዳቸው ላይ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎቸ የፈፀሙት ድብደባ እንግልትና እሥራት የፕሮፌሰርን ህሊና ስላቆሰለው ”ጠበቃ አያስፈልገኝም።ምንም ክርክር ሳያስፈልግ ቅጣቱ ይሰጠኝ። ” በማለት ለፍርድ ቤቱ በማመልከታቸው ችሎት ተዳፍሯል በሚል 6ወራት እሥራት ተፈረደባቸው።ይሁንና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቀርቦ ወደ አሥር ቀናት ዝቅ ብሏል።

ሰኔ የፕሮፌሰር አሥራት የልደት ወር ነው። ለወህኒ የበቁትም በዚሁ በሰኔ ወር ነው። 67ኛ የልደት በዓላቸው ሰኔ 11ቀን ሲሆን፧ የእስር ቀናቸው ደግሞ ሰኔ 20 ቀን ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ”በጎጃም በጎንደር በሰሜን ሸዋ የተደራጁ የወንበዴ ቡድኖች አሰማርታችኋል።”በሚል ከሌሎች ተከሳሾች ጋር አራተኛ ክስ ተመስርቶባቸዋል። ፕሮፌሰር እስካሁን ድረስ ከ100 ጊዜ በላይ በፍርድ ቤት ቀጠሮ ተመላልሰዋል።ስድብ ማስፈራራት ማሳደድና ማሰር የፕሮፌሰር አሥራትን ቁርጠኝነትና ሕዝባዊ ወገናዊነት የበለጠ አጠናከሩት እንጂ አላዳከሙትም።

ፕሮፌሰር አሥራት ሰውን በሰውነቱ ይወዱታል።የችግሩና የመከራው ተካፋይ ናቸው።እንደቁጡነታቸውና አትንኩኝ ባይነታቸው አይደሉም።የሰው ችግርና ብሶት በቀላሉ ነው የሚገባቸው። ሰውን ለሥልጣኑ ወይም ለገንዘቡ ሲሉ የተለየ አክብሮትና እንክብካቤ አያደርጉም።ሀብታምና ሥልጣን አላቸው ከሚባሉት ይልቅ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ያከብራሉ።

አሥራት ተንኮልና ልታይ ልታይ ባይነት የለባቸውም።ውሸትና ውሸታምን አጥብቀው ይጠላሉ።አንድ ሰው ሲዋሽ ከያዙት እንደሰው አይቆጥሩትም።ማንኛውንም ነገር በእርግጠንነት ማወቅ ይፈልጋሉ።”መስሎኝ ነው ” የሚል መልስ የሚሰጣቸውን አይወዱም።በተፈለገው መንገድ ቢነገራቸው የሚያሳምናቸው ሆኖ ካላገኙት አይቀበሉትም።

ሥለምግብ ብዙ አይጨነቁም። ለዛውም ቢሆን የአገራቸውን ምግቦች ይመርጣሉ። የኢትዮጵያን የባህል ሥርዓት ጠንቅቀው እንደማወቃቸው ዋና የሥርዓቱ ተከራካሪና ተከታይም ናቸው።የሚወደድ የአነጋገር ስልት አላቸው።ማንም ከእርሳቸው ጋር ቢነጋገር ዓይኑን ለመስበር እስኪያቅተው ድረስ ይመስጣል።

በንግግራቸው ውስጥ እንግሊዝኛ ደባልቀው መናገር አይወዱም።የሙያ ቃል እንኳን ሲገጥማቸው ግልፅና አጭር የአማርኛ ቃል ይፈልጉለታል። ከሙያቸው ውጭ በንባብ ያዳበሩት ሰፊ ግንዛቤ አላቸው።

ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ!  (1ኛ) የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ የፈረሰኛ ደረጃ፣  (2ኛ) የዳግማዊ ምኒልክ ኒሻን የፈረሰኛ ደረጃ፣  (3ኛ) የአብዮታዊ ዘመቻ ዓርማ፣  (4ኛ) ዓለም አቀፍ የወርቅ ሜርኩሪ / በግል አስተዋጽኦ/    (5ኛ)  የቀይ ባህር ኒሻን አንደኛ ደረጃ  ተሸልመዋል።

እድሜያቸውን ለሕዝብ አገልግሎት የሰጡት ምሁር አሁንም አገርና ሕዝብን ለመታደግ፡ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል።ላደረጉት አስተዋጽኦ ግን የተሸለሙት እሥር ነው።እሥራቱ ከሚወዱት ሕዝብ የለያቸው በአካል ብቻ ነው። እሳቸውም ”በወህኒ ቤት አጥር ተከልዬ አካላዊ የመንቀሳቀስ ነፃንቴ ቢታገድም ምንጊዜም ቢሆን ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ነፃነት ያለኝ ሃሳብና ጭንቀት ሊታሰር አይችልም”ብለዋል።

በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች ለሰላምና ዲሞክራሲ ለሰብዓዊ መብት መከበር የቆሙ ወገኖች ሁሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።በዓለም ዙሪያ ለምሳሌ በአሜሪካ በአውሮፓ ወዘተ… በተደጋጋሚ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል።ምስላቸውን ያዘሉ ካኔትራዎች ፖስት ካርዶች መለዮዎች ማስታወሻ ደብተሮችና አጀንዳዎች በዓለም ዙሪያ ተሰራጭተዋል።አሥራት ይፈቱልን የሚሉ መዝሙሮች ተዘምረዋል። አሥራት ግን አልተፈቱም። በክስ ላይ ክስ ነው የተከተላቸው።

በፍርድ ቤቱ የቀጠሮ ቀን አሥራትን ያሉ ሁሉ በፖሊስ ተደብድበዋል፧ታስረዋል፧በዝናብ በፀሐይና ብርድ ተሰቃይተዋል። ”አሥራት የቁርጥ ቀን ልጅ የቁርጥ ቀን መሪ ” ”ማንዴላ ” ”ጋንዲ” እያለ መፈክር አሰምቷል። በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የአንድነት ደጋፊዎች ሁሉ ከጎናቸው ቆመዋል።

የውጭ አገር ሰዎችም ባሉበት ሆነው ፕሮፌሰር አሥራት እንዲፈቱ ጥረዋል።የ1987 ዓ.ም. የገና በዓልን አስመልክቶ ከአሥራ ሁለት ሽህ በላይ የእንኳን አደረሰዎትና የይበርቱ ፖስት ካርዶች በወህኒ ቤት አድራሻ ልከውላቸዋል።

በአሜሪካ አገር በየዓመቱ በሚዘጋጀው የኢትዮጵያውያን የባህልና የስፖርት በዓል በተቀዳሚ የክብር እንግድነት በተከታታይ ለሁለት ዓመት ተጋብዘዋል።

 

እንደሚታወቀው ክቡር ፕሮፌሰር አሥራት  በፈጠራ ክሶች  ተከሰው ከእሥር ቤት ወደፍርድ ቤት፣ከፍርድ ቤት ወደእሥር ቤት እየተመላለሱ ባሉበት ወቅት በደረሰባቸው እንግልትና የትግሬ ዘረኞች አረመኔያዊ  ተግባር  ህመምተኛ ሆኑ። በበሽታው ሲሰቃዩ ከቆዩ በኋላ፣ለይስሙላ ህክምና ይሰጣቸዋል እየተባለ በሀኪም ቤት ምልልስ ብቻ ከፍተኛ መጉላላትና የሞራል ጥቃት እንዲደርስባቸው ከመደረጉም ባሻገር ህመሙም ቀስ በቀስ እየጎዳቸው እንዲሄድ ሆን ተብሎ ተሠራበት።

ዘረኛው የትግሬዎች አገዛዝ! ክቡር ፕሮፌሰር አሥራትን እንደማይድኑ (ቀድሞ እንደገደላቸው)ካረጋገጠ በኋላ የሚመጣውን የሕዝብንና የዓለምን የተቃውሞ ገፅታ ለማርገብና ሠብዓዊ መሥሎ ለመታዬት፣በወቅቱ እንዳይታከሙ ተደርጎ በሞት አፋፍ ላይ ከደረሱ በኋላ ወደውጭ አገር ለከፍተኛ ህክምና ተላኩ ተብሎ ተነገረ።ይህም ለፖለቲካ ጠቀሜታ ሲባል የተደረገ እንጅ እንዲድኑ አልነበረም።

ክቡር ፕሮፌሰር አሥራትም በማይቀረው የሠው ልጅ መጨረሻ በሆነው ሞት ግንቦት 6ቀን 1991ዓም(እአአ ሜይ 14ቀን 1999ዓም) በፔንሲልቫንያ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ፊላደልፊያ አሜሪካ አገር በህክምና ላይ እንዳሉ ከዚህ ዓለም ተለዩን።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣በተለይ ደግሞ የዐማራው ሕዝብ ይህን ዕለት በየዓመቱ አሥቦት የሚውለው በታላቅ ሀዘንና ቁጭት ነው።

                               ክቡር ፕሮፌሰር አሥራት ከተናገሯቸው አንዳንዶቹን ለላሙና !

ፕሮፌሰር! መዐሕድ የተመሠረተበትን 2ኛ ዓመትና የወጣቶችን ምክር ቤት ምሥረታ ምክንያት በማድረግ  ከአደረጉት ንግግር እና በሌሎች ጊዜያት ከተናገሯቸው የተወሰዱ አንዳንድ ትውሥታዎች፣

-”በእንደዚህ ያለ አሥጨናቂ የሆነ የመከራ ጊዜና ወቅት፣ራሱን ደፍቶ፣ያልከፋው መስሎ፣ሆደ ሠፊ በመሆን የተጣለበትን መከራ ሁሉ ሳይቸኩል ችሎ፣ፈጣሪውን ለምህረት እየተማፀነ፣ራሱንም ሳያጋልጥ ለመፍትሔ በሥልት የእሚሠናዳ ታላቅ ሕዝብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ነው።” “ኤሕአዴግ በገባበት ጊዜ የፖሊስ ሠራዊት በመበተኑ ያለ ፖሊስ፣ፍርድ ቤት በመበተኑ ያለ ፍርድ ቤቶች፣ለአንድ ዓመት ተኩል በእሚያሥገርም ፀጥታ እራሱን ጠብቆ በመኖሩ፣መንግሥት ነኝ ባይ የ እማያሥፈልገው ጨዋ ሕዝብ መሆኑን አሥመስክሯል።”

-”ዛሬ ታላቁ የዐማራው ጠላት ዐማራው ነው።አንዳንድ የደላውና  ዐወቅሁ ባዩ፣የዐማራ ድርጅት በመቋቋሙ አልሥማማምእያለ ሲዋልል፣ሌላው ደግሞ በጠቋሚነት፣በአሳባቂነት፣በአድርባይነት፣በገዳይነት የገዛ ወንድሙን ለዕለት ሆዱ ፍላጎት ሲልከፍተኛ በደል እያደረሰ ነው።እሥካሁን ድረስ የተሠራው ተሠርቷል።ከእንግዲህ ወዲህ ግን እንደነኚህ ያሉትን፣ጠላትነታቸውንእንዲያውቁ ማድረግና ይሉኝታም ስፍራ የሌለው መሆኑን በጥብቅ ልናሳስብ እንወዳለን።በሌላ በኩል ሌላው የዐማራ ክፍልተኮላሽቶና ተኝቶ በማንቀላፋት ላይ ይገኛል።ይህ ክፍል ቢቃጠልም እንኳ ሊሠማው ስላልቻለና አልነቃም ብሎ ስለቀረ፣ያለውዕድል እንደሚባለውዐማራው ሲተኛ የሚበላው ጅብ ነው።””

-”አንዳንዶቻችንም በተመቻቹ መቀመጫና አልጋ ላይ እየተንፈላሰስን፣እንደተለመደው የጭራ ፀጉር መሰንጠቅና በዳመና ላይ ፎቅ በመሥራት ጊዜያችንን ሥናሳልፍ፣ ”አህያ ወይም ሀድጊ”በመባል መሳለቂያነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣የዋህነትም ጭምር ብቻ ሳይሆን በሃገርና በወገን ላይ ከፍተኛ በደል ማድረስ መሆኑን ተደጋግሞ የተመሠከረለት ነው።”

-”የተማርንና ለመማራችን የምሥክር ወረቀት የያዝን ሥለሆነ ባለሙሉ መብት ነን የማለት ዘመኑ አልፎ  ከአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ጋር አክትሟል።ዛሬ ሥራችን  አቋማችንና ሃሳባችን በሁላችንም ላይ የእሚጠራ ምሥክር መሆኑን እንገንዘብ።ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ንቃተ ሕሊና የላቀ በመሆኑ፣ምንም በአፈሙዝ ልጓም ምክንያት ግፊቱ ባይሰማንም ወደፊት የእሚጠይቁንና የእሚፋረዱን ብዙ መሆናቸውን ከአሁኑ መገንዘብና ለወገን ተገቢውን አስተዋፅዖ ማድረግ ብልህነት ነው።”

-”የታሪክ አጋጣሚ ሆነና በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያኖች በጎሣ፣በዘር፣በሃይማኖትና በቋንቋ በመለያየት ተከባብሮና አንድ ሆኖ የኖረው ሕዝብ ያለፍላጎቱ አንድነቱ እንዲናጋ ከመደረጉም በላይ የኔ ብሎ የሚኖርበት አገርም ወደማጣት እየተገደደ ነው።ሆኖም ዛሬ በዚህች ሃገር በቀሎች መሣሪያነት ብንጎዳም፣የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፣ኢትዮጵያ እንደሆነች ሊያጠፏት የእሚቅነዘነዙት ይጠፏታል እንጂ እናት ሃገር ኢትዮጵያን ጠብቀው፣እንደ እንጉዳይ በእሚፈሉ ጀግኖች ልጆቹዋ በአንድነቷ ታፍራና ተከብራ እንደምትኖር የእማያጠራጥር መሆኑን ሙሉ ዕምነቴን አረጋግጣለሁ።”

-”..ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ችግር፣ ሃሳብና ሃዘን ላይ ይገኛል።እንደ እርግማን ይሁን ወይም በፍርድ ቤት እንደተፈረደበት ይመስል እነኚህን ችግሮች የሚያባብስ እንጂ የሚያሻሽልለት አንዳችም አጋር አላገኘም።…”

-“…የፖለቲካ ባለሥልጣኖች ከክፋት ወደደግነት እንዲመለሱ…ኃላፊነት ተሰምቷቸው ለሕግና ለሕዝብ ፍላጎት እንዲገዙ…በሰላማዊ መንገድ ለማሳመን በአጋጠመኝ ዕድል  ሁሉ ድምፄን ከማሰማት አልቆጠብም።…”

– “…ለሀገሩና ለወገኑ ክብርና ደህንነት ደረቱን ለጥይት በመሥጠት የቆረጠው አርበኛም ያለቀኑ አልወደቀም፣አልሞተም።እንዲያውም ከተፈጥሮ ሞቱ በኋላም ቢሆን በታሪክ ውስጥ እየኖረና ኢትዮጵያንም በታሪክ እያኖረ ነው።…”

-”መዐሕድ ለዚህች  ሀገር ሕዝብ በአጠቃላይና ለብሶተኛው ዐማራ ሕዝብ ፍትህ ከመጠየቅ ባሻገር ያቀረበው ሌላ ጥያቄ የለም።…”

-”የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ተከብሮ፣ሕዝቡ በእኩልነትና በወንድማማችነት አብሮ የሚኖርበት ሥርዓት እንዲሰፍን ማድረግ  የአሁንም ሆነ የወደፊት መሠረታዊ ዓላማው ነው።”

-”..እርግጥ ነው መዐሕድ ነፃ መሬት ወይም የታጠቀ ሠራዊት የለውም።ሆኖም የመዐሕድ ነፃ መሬት የእያንዳንዱ ዐማራና የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ ልብ መሆኑን እንድትገነዘቡልን እንወዳለን።…”

-”…ሌላው የመዐሕድ ችግር ሁሉም እንደሚያውቀው ማንኛውንም የኢትዮጵያ ችግር በዐማራው ላይ እንደሚላክኩት ሁሉ ኢሕአዴግ እንዳይጋለጥበት  የሚፈልግባቸውን  ችግሮች ሁሉ በመዐሕድ ላይ ማላከክ የተለመደ ነው።..”

-“…ዛሬ የኤርትራ ጉዳይ ፈንድቷል።እኔ መጀመሪያ ጠላት ተደርጌ የተወሰድኩት የኤርትራን የመገንጠል ጉዳይ በሰኔ የሽግግር ኮንፈረንስ ላይ ትክክል አይደለም ብዬ  ሥለተቃወምኩ ነው።ይኸው ዛሬ ከመንግሥት ጀምሮ እሥከታች ድረስ ሁሉም የሚያጨበጭብበት ጉዳይ ሆኗል።ይፋቱ ካላችሁ ደግሞ ፍቺውን በደንብ በህግ አድርጉ፣አንጠልጥሎ መተው ሌላ ጣጣ ያመጣል ብዬ ነበር።ይኸውና ዛሬ መጣ።”

-“የአካባቢው ሃገሮች፣የወዳጅና የጠላት መንግሥታት፣የዓለም አጠቃላይ ሁኔታ ግምት ውስጥ ገብቶ፣በመጨረሻ ኢትዮጵያ በሚያመቻት ጊዜ ሉዓላዊነቷን ማስከበር አለባት””    ጥቅምት 1991ዓ.ም.

                                  ሥለፕሮፌሰር አሥራት ሌሎች ሠዎችስ ምን ይላሉ?

-”..ከሃያ ዓመት በላይ አውቃቸዋለሁ።ለፕሮፌሰር አሥራት ከፍ ያለ ግምት አለኝ።ሥራ የማይሰለቹ ማንኛውንም የሕክምና ጥያቄ የማይንቁ ባለሙያ ናቸው… ፕሮፌሰር ያካበቱትን የሙያ ጥበብ አሠራሩንና አስተሳሰቡን ለምደው የራሳቸውን (ወጥነት ያለው ቱባ) ሥራ ማውጣት የሚችሉ ናቸው።…የኢትዮጵያን ባህል ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው።”    ፕሮፌሰር ነቢያት ተፈሪ

-”…የአሥራት የልጅነት መምህሩ ነኝ፣የኔታ ነው የሚለኝ፣ያከብረኛል፣አለቃም አድርጌው ነበር። ረጋ ያለ፣ከሰው ተግባቢ፣ሰው አክባሪ ፣ሲጠየቅ የሚናገረው በቀላሉ ይገባሃል፣ኩራት አያውቅም፣ጠባዩ ያው ነው። አሁን እኔ 93 ዓመቴ ነው፣ በ85 ዓመቴ  ይኸን ሆዴን ተቀድጃለሁ።የቀደደኝም አሥራት ነው እናንተ ፕሮፌሰር ብላችሁታል፣አዳነኝ።አሥራት በራዲዮ <አስተማሪዬን አክሜ ያዳንሁት በጣም ያስደስተኛል> ብሎ ሲናገር በአገሩ ተሰማ።ታዲያ እንዴት ኮራሁ መሰለህ።አሥራት ሰዓት ሸልሞኛል፣ገንዘብም በየጊዜው ሠጥቶኛል።እኔማ ድሮም ድሮም ልጅ ሆኖ ትልቅ ሠው እንደሚወጣው ተረድቻለሁ።..”  የፕሮፌሰር አሥራት የልጅነት መምህር አለቃ ለማ ከስድሳ ዓመት በፊት የነበረውን አስታውሰው ከተናገሩት(በ1981ዓ.ም.)

-”እኔ በመሠረቱ ለአማራው መቆርቆር የጀመርኩት ሻዕቢያ፣ወያኔና ኦነግ አዲስ አበባ ከመግባታቸው ቀደም ብሎ ኦነግ ወለጋ ውስጥ ከ300 በላይ አማራዎችን ብቻ መርጦ “ለሰብሰባ ትፈለጋላችሁ”ብሎ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ከሰበሰበ በኋላ በላውንቸር ከጨረሰበት ጊዜ  አንሥቶ ነው።አዲስ አበባም ከገቡ በኋላ የአማራው ሰቆቃ  እየከፋ ሲሄድ፣የእነክቡር ፕሮፌሰር አሥራት  መዐሕድ ብቅ ብሎ ለአማራው ጥብቅና ሲቆም የተሰማኝ ደሥታ ወደር አልነበረውም።በዚያን ጊዜ በአካባቢዬ ሥለአማራው አፉን ሞልቶ የሚናገር ሥላላጋጠመኝ፣ማንና እነማን ለአማራው እንደሚቆረቆሩ ለማወቅ እጅግ በጣም ከባድ ነበር።ነገር ግን  የአማራው ሰቆቃ ውሥጥ ውስጡን የሚሰማቸው ወገኖች ይኖራሉ የሚል የግል ግምት ነበረኝ።

ያም ሆነ ይህ  በአካባቢያችን በግልፅ ሥለአማራው  ለመናገርና ለማውራት  በማይታሰብበት ወቅት፣”አማራን አሥጨርሶ የሚመጣ አንድነት በአፍንጫዬ ይውጣ” በማለት፣በድፍረትና በቁጭት ገፈታትሬ በመውጣት፣የአካባቢዬ ህብረተሰብ ፈለገም አልፈለገም፣ወደደም ጠላም፣የአማራው ተቆርቋሪና ደጋፊ እንደሆንኩኝ እንዲያውቅ ተገዷል።በዚህን ጊዜ የተወሰነው አማራ  “የኢትዮጵያ አንድነት ነው እንጅ  እንዴት አማራ ትላለህ” በሚል በተግሣፅና በማናናቅ ሲተቸኝ፣አንዳንዶቹ ደግሞ “እኛ ተደባልቀናል፣አሁን ከየትኛው እንሁን?”ሲሉ፣ሌላው ክፍል ደግሞ “አማራ ብሎ መነሳት ዕብደት ነው” እያለ ቢተችም፣ከሁሉም የከፋውና መሰናክል ፈጣሪዎቹ  “ከአማራ ተፈጥረናል” የሚሉት  ነበሩ። ዛሬም ቢሆን ችግር ፈጣሪዎቹ እነሱው ናቸው።በሌላ በኩል ግን ባይናገሩም ውስጥ ውስጡን ደስ የሚላቸው አማሮች  እንደሚኖሩ ገምቻለሁ።

ይህ በዚህ እንዳለ  መዐሕድ በተቋቋመበት ዓመት 1984ዓም ፕሮፌሰር አሥራት ሥዊድን  አገር ሥቶክሆልም ከተማ ለሥራጉዳይ መጡ። አንዲት እህታችን (ለነገሩ የእሷም ዘሯ አማራ ነው፣ግን የአማራው ጉዳይ እንደማይመለከታት ነው የገባኝ) “አንተ አማራ!አማራ!  ትላለህ፣ፕሮፌሰር አሥራት እዚህ አገር መጥተውልሃል”ትለኛለች። አድራሻቸውን እንዳገኘሁ ሄጄ አገኘኋቸው። አነጋገራቸው፣ተግባቢነታቸው ብሎም ራሳቸውን የማያከብዱ ሰው ሆነው ሳገኛቸው በጣም እረካሁ።

እሥከዚህ ጊዜ ድረስ በአካባቢዬ አይንህ ላፈር እየተባልኩም ቢሆን በፊት ለፊት ብቻዬን አማራ ከማለት በሥተቀር፣ሌሎች የሚደግፉ ሥለመኖራቸው  ምንም ፍንጭ ሥላላየሁ፣የድጋፍ ድርጅትም ለማቋቋም አልደፈርኩም ነበር። ታዲያ ፕሮፌሰርን በግሌ አግኝቼ ቁምነገሮችን ከተለዋወጥን በኋላ  “ብችል ሰዎች ካገኘሁ እሠዬው ነው፣ ካልሆነ ግን ትግሉ ጊዜ ሥለማይሠጥ አንዳንድ ለጊዜው የቅርብ ሠዎችን ፈልጌ የድጋፍ ኮሚቴ አቋቁማለሁ”  አልኳቸው።”እሱን እናንተው ወሰኑ” አሉኝ።ከመሠናበቴ በፊት ተዘጋጅቼና አሥቤበት ሥለሄድኩኝ “ሁለት ሽህ(2000)ዶላር ብዙም ባትሆን፣ለመዐሕድ የሥራ ማካሄጃ ትረዳ ዘንድ” በሚል ሥሠጥ፣”አደርሳለሁ” ሲሉኝ፣ደስ ብሎኝ ወደ ቤቴ  ተመለስኩ።እሳቸውም ወደ ኢትዮጵያ  እንደተመለሱ ሳይውል ሳያድር ደብዳቤ  ፅፈው “ያችን የቸርከኝን በተገቢው ቦታ አውለናታል” ብለው ሲልኩልኝ የበለጠ አንጀቴን በሉት፣ምክንያቱም ትንሽ ነው፣ ትልቅ ነው፣ ብለው ሳይንቁ  ቁምነገር ሥላሳዩኝ ነው ።

ከዚያም  በኋላ የአንድነት ጋዜጣ እየመጣ ሲበተን ሠዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፣የድጋፍ ድርጅትም ለማቋቋም በቃን።አብሮ የመሥራት ሁኔታችንም ዳብሮና አምሮ ሲጓዝ ኖሮ እሳቸው ሲታሰሩ ድርጅቱም አብሮ መታሠር ጀመረ።

ፕሮፌሰርን አሜሪካ አገር ፔንሲልቫንያ ሆስፒታል ለመጠየቅ ሄጄ  እንዳየኋቸው እንባዬ ቀደመኝ።ከክፍሉ ወጣሁ።ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ተመልሼ ገባሁ።  “ጤና ይሥጥልኝ ፕሮፌሰር”አልኳቸው።ጤና በነበሩበት ወቅት ብዙ የሥልክ ልውውጥ እናደርግ ሥለነበር፣የህመሙ ብርታት በድምፄ እንዳይለዩኝ ይታገላቸው ይሆን  ብዬ ሥለተጠራጠርኩ፣ “ማን እንደሆንኩ አወቁኝ” ብዬ ሥጠይቃቸው፣”መች አጣሁህ”  አሉኝ።   ትንሽ ቆዬት ብለው “ገደሉኝ አይደለም” ሲሉ ተደመጡ።ይህንን መሥማት የበለጠ ያደማል።

ምኞቴና ፍላጎቴ እንዲድኑ፣ተጨባጩ ሁኔታ ደግሞ እንደማይድኑ እየተሟገቱኝ ዕርሜን አውጥቼ  ተመለስኩ። መጀመሪያ ስዊድን  ሀገር በመጡበት ወቅት ሳገኛቸው የተጎናፀፍኩትን ደስታ፣አሜሪካ ሀገር ሂጄ በሀዘን ለውጨው መጣሁ።”     አያሌው ፈንቴ

-”ስለፕሮፌሰር አሥራት ብዙም የማውቅ ባልሆንም በሙያቸው፣በኢትዮጵያዊነታቸውና በወገን አፍቃሪነታቸው አኩሪ ሥም እንዳላቸው አውቃለሁ። መቼም የሰው ልጅ ከሞት የሚቀር ባይሆንም የእርሳቸው ዜና ዕረፍት ከምንም በላይ የሚያሳዝነኝ በአንድ ምክንያት ብቻ ነው።ይህንን ያቀጣጠሉትን የትግል ፍሬና የወገናቸውን መልካም ሕይወት ደርሶ ሳያዩት በማለፋቸው ነው።”     የአንድ ቢሮ ፀሀፊ

-”ፕሮፌሰር አሥራት እኮ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው የተፈጠሩ አይደሉም።ለሕዝብ ተፈጥረው ሕዝብን አገልግለው ለሕዝብ የተሰው ታላቅ አርበኛ ናቸው።”የመርካቶ ነጋዴ

-”..ብዙዎች ሥለህክምና ሙያቸው ይመሰክራሉ።በእርግጥ ይህ ሁሉ ምሥክርነት ቢያንሳቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይደለም።እኔ ደግሞ በመዐሕድ አውቃቸዋለሁ።ደፋር፣ሃሳባቸውን በተገቢው መንገድ በግልፅ ቋንቋ ማስረዳት የሚችሉ፣ሰው አክባሪ፣ድካምን የማያውቁ፣ለቆሙለት ዓላማ የመጨረሻውን መስዋዕትነት የከፈሉ ጠንካራ መሪ ናቸው።..”  የመዐሕድ አባል

7.”ማጣት እንጂ ማቆየት ባልታደለች ሃገር ውስጥ ተፈጥረው ሳይጠገቡ ያለፉ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ ነበሩ።”         ያሩሲ ወርቅ

                       

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s