የኢትዮ ሰማዩን ጌታቸው ረዳ በጨረፍታ

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ግለሰብን ማዕከል ያደረገ በተለይ ሙገሣን ያዘለ መጣጥፍ ጽፌ ስለማወቄ አሁን ትዝ አይለኝም – በለመደብን የዘመን ወረርሽኝ ምክንያት ግለሰቡ ላይ ያለኝን ፖለቲካዊ ተቃውሞ ለማቅረብ ካልሆነ በስተቀር፡፡ አሁን ግን ባልተለመደ ሁኔታ በዚህ ብርቅና ድንቅ ዜጋ ላይ የተሰማኝን በድርበቡ ልናገር ይሄውና ጀመርኩ፡፡ በርሱ ውስጥም እርሱን መሰሎችን ሁሉ እንደማነሳ ይታወቅልኝ፡፡

ሰውን ለመወረፍ የሚተጋ ብዕርና አንደበት መመስገን የሚገባውን ግሩም ዜጋ ለማወደስ ቢሰንፍ አጉል ይሉኝታ ነው፡፡ በሀገሬ ኢትዮጵያ ወቅታዊና ዘመነኛ ሁኔታ ምክንያት እንቅልፍ አጥተው ከሚያ(ድ)ሩ ወገኖች አንዱ መሆኔን ላስታውስ ብደፍር ቅር የሚሰኝ አይኖርም ብዬ እገምታለሁ፡፡ ይህን መናገር ደግሞ አግባብ እንጂ ለራስ ሲቆርሱ ዓይነት ሊሆን አይገባም – የፈራሁ አስመሰለብኝ ልበል? ብዙ መሆን፣ ብዙ ማድረግ፣ ብዙ መሥራት እየቻሉ በሀገራቸው ጉዳይ ሌት ከቀን እየተጨነቁ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያባክኑና በዚያውም ይህችን አጭር ምድራዊ ዕድሜ በከንቱ የሚጨርሱ አሉ – ከነሱ ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ በግርድፍ ግምት በ30 ዓመታት ውስጥ …. ኢትዮጵያ ነፃ እስክተወጣ ከቆየሁ … ወይም ምናልባት ወያኔን ምሥጋን ይንሳውና ልጅ የሚወጣልኝ አይመስለኝም እንጂ የሚወጣልኝ ከሆነ …. ያኔ … እነዚህ ጅምር ዐረፍተ ነገሮች (ያልቃሉ)፡፡ የማይገባ ነገር ሲያጋጥም ትቶ ማለፍ ነው፡፡(የዛሬ ልጅ እንደዱሮው ዘመን ያባትን እግር ማጠብ ይቅርና ነጠላ ጫማ እንዲያመጣልኝ ባዘው በቃና ቲቪና በሞባይል ጌም ምክንያት ልቡ ጠፍቶ ትዛዜን የሚሰማኝ ተኝቼ ሁለትና ሦስት እመም እንቅልፌን ከደቃሁ በኋ ነው – ሊያውስ ወያኔ ሲያስተኛኝ አይደል! ልጅ ዱሮ ቀረ! በዋል ፈሰስ ልጆችን በመቀፍቀፍ የተለበለበ ግንድ እያሳደግን ነው – አእምሮው የኮሰመነ አካላዊ ዕድገት ብቻ!፡፡)

ወደጀመርኩት – ወደገደለው ላዝግም፡፡  ብዙ ጌታቸው ረዳዎች እንደሚኖሩ እገምታለሁ፡፡ እኔ ቢያንስ ሁለቱን አውቃለሁ፡፡ አንደኛው የወያኔ አፋዳሽ የሆነው የራያው ጌታቸው ረዳ ነው – የወያኔው ባለሥልጣን፡፡ የዩንቨርስቲ መምህር እንደነበርና ብዙ ችግር ያለበት ወፍ ዘራሽ ዜጋ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ ሕወሓት ሁለት ታላላቅ ሞኛሞኝ ብሔሮችን የታቀደውን ያህል ባለማጋጨቱ ይህ ጅል ወያኔ በጸጸት መልክ ሲናገር በጀሮየ ሰምቼዋለሁ፡፡ መቀሌ ዩኒቨርስቲ ሲያሰተምር ከንዝህላልነቱ ብዛት የተነሣ ተማሪዎች ለፈተና ተቀምጠው ሳለ የማጠቃለያ ፈተና  ማውጣቱንና ማባዛቱን ረስቶት  ተማሪዎቹ በፈተና አዳራሽ ተቀምጠው እየጠበቁ ፈተናው ተባዝቶ መፈተናቸውን ሁሉ ከውስጥ አዋቂ ሰምቻለሁ፡፡ ሌላም ሌላም ሰምቻለሁ፡፡ ወያኔዎች የሚፈልጉትን ቆሻሻ ስብዕና አንድም ሳያዛንፍ መቶ በመቶ በማሟላቱ ምክንያት ለሥልጣን እንደታጨና እንደተሾመም ሰምቻለሁ፡፡ ለማንኛውም ስለዚህ ሰውዬ አሁን አያገባኝምና ምንም ባልናገር ምርጫየ ነው፡፡

የኢትዮሰማዩ ጌታቸው ረዳ፡፡ ይህ ምርጥ ዜጋ አሁን የሚሠራውን እንጂ የዱሮ ታሪኩን አላውቅም፡፡ ከፎቶው ውጭ በአካልም ሆነ በስልክ አንተዋወቅም፡፡ በሚዲያ ግን በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ የዚህን ሰው ድካምና ልፋት ኢትዮጵያ እናታችን እየመዘገበችለት ቢሆንም የበኩሌን ጥቂት ማለት እፈልጋለሁ – መብቴም ነው፡፡ ጥፋት ቢኖርበት እንደማንባርቅበት ሁሉ በአልሚነቱ አወድሰዋለሁ፡፡

ሰሞኑን አንድ መጣጥፍ ለተቃውሞው ጎራ ልኬ ነበር፡፡ እንደልማድ ሆኖብኝ ከላክሁ በኋላ የመጣጥፉን ርዕስ በኮፒፔስት እቀዳና ጉግል መፈለጊያ ላይ ደፍቼ ፈልግ እላለሁ፡፡ ያኔ በየትኛዎቹ ድረ ገፆች እንደወጣ አውቃለሁ፡፡ በየትኞቹ ደግሞ የቅርጫት ራት እንደሆነ ጊዜ እየሰጠሁ ቀስ በቀስ እረዳለሁ – የምዘናባቸውን ደግሜ በመላክ አስታውሳለሁ፡፡ በየትም ይውጣ በየትም አይውጣ ለኔ ዋናው ቁም ነገር አእምሮየን ሰቅዞ የሚያሰቃየኝ የእምዬ ኢትዮጵያ ጉዳይ ከኔ ወጥቶ ቢያንስ ለአንድ ሰው መድረሱ ነው፡፡ ዕድሌ ከሰመረ በዛ ባሉ ድረገፆች ይለጠፋል፡፡ ነገሬ አልጥም ካለና ከስኳሩ እሬቱ ከበዛ በጥቂቶች ወጥቶ በሌሎቹ ይቀራል፡፡ በውነቱ ምንም አይመስለኝም፡፡ ለምን ድርሻየን ተወጥቻለሁና፡፡ ሁሉንም ማስደሰት እንኳንስ እኔ ፍጡሩ ፈጣሪ ራሱም የሚችል አይመስለኝም፡፡ እናም ቢለጠፍ ባይለጠፍ በተለይ አሁን አሁን ምንም አልልም  – ማለቴ እንደዱሮው አይከነክነኝም፤  ምንአልባት እያደግሁ ይሆን? እንዲያ ከሆነ ደስ ይለኛል፡፡ ማደግን ማን ይጠላል! ይህን ስል ግን የራሳቸው ፍላጎትና የፖለቲካ አቋም የሆነውን ቢሆን የሰዎችን ሃሳብ ግን ተቀብለው ካለ (ምንም አድልዖ ብል ሰው እንዳይታዘበኝ ፈራሁ እንጂ) የሚያስተናግዱ እንደሀበሻ ድረገፅ ያሉ ለሁሉም ተደራሽ ሚዲያዎችን ጠቅሼ ሳላመሰግን ባልፍ አግባብ አይሆንም፡፡(የነዚህ ድረገፆች አስተዋፅዖ መቼስ ከሺህ ባታሊዮን ጦር ይበልጣል፤ ጊዜው ሲደርስ  …)

አቶ ጌታቸው ረዳን ለምን አሁን አነሳሁ? ከሌሎችስ በምን ይለያል? እነዚህን መሰል ጥያቄዎች ማንም ሊጠይቅ ይችላል፡፡

ጌታቸው በርግጥም ጌታቸው ነው፡፡ ስም ይቀድሞ ለነገር ይባላልና፡፡ የጌታቸው ብሔር ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ በወያኔ ቋንቋና የደም ምች ልክፍት ካየነው ደግሞ ጌቾ  ትግሬ ነው፡፡ ጌታቸው ተደብቀው ስለሀገራቸው የሚያብዱና የሚቆዝሙ ጥቂት ትግሬዎችን ወክሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ በወያኔ ዕኩይ ድርጊት ምክንያት – ብዘው ተኝቶ እያንቀላፋ በሚገኝበት ወቅት – እንደጥቂቶቻችን ስለሀገሩ እያበደና እየሰከረ ያለ ግሩም ዜጋ ነው፡፡ ወንድምና እህቶቹ እንደዝንጀሮ ከያሉበት ተጠራርተው ሲያበቁ የኢትዮጵያን ክምር እየዘረጋገፉ የበሉትን በልተው የቀረውን ለነገ እንኳን እንዳይተርፍ ለባዕዳን እየሸጡና እያመነቃቀሩት በሚገኙበት ሁኔታ እርሱ የሞት ዐዋጅ እንደታወጀባቸው ዐማሮች በስደት እየኖረ፣ ድረገፅም ከፍቶ ስለዐማሮች ከዐማሮች ከራሳቸውም በላይ ከፍተኛ መስዋዕትነትን እየከፈለ ያለ ብርቅዬ ዜጋ ነው፡፡ ብዙ ዐማራ ወገኖቹ በወያና በቅጥረኞቹ እየታረዱ በተድላና በደስታ ሲኖር – በሀገር ውጥም በውጭ ሀገርም – እርሱ ግን ክርስቶሳዊ የሚሢሕነት ግዳጁን እየተወጣ ያለ ከንፍሮ የወጣ ንጹሕ ስንዴ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተናግሬ መጨረስ አይቻለኝም፡፡ ደግሞም ማጋነን የሌለበት እውነት ነው፡፡ እባካችሁን የሰውን ጠንካራ ጎን በሕይወት እያለ መመስከርን እንልመድ፡፡ በዚህ ረገድ ፈረንጆች ጎበዞች ናቸው መሰለኝ፡፡  እኛ የሚቀናን መዘራጠጥና መሰዳደብ ይመስለኛል፡፡ ከነብሂሉ “አመስጋኝ አማሳኝ” እንላለን፤ የአመስጋኝን ቅስም ለመስበር፡፡ ኩሸትንና ግነትን፣ በከንቱ መወዳደስንና በእከክልኝ ልከክልህ መንገድ እስካልተራመድን ድረስ በእውነት ላይ ተመርኩዘን ጥሩን ሰው ብናመሰግን ምን አለበት?  ተመስጋኝም ሳይኩራራና ምናባዊ የትዕቢት ቆጥ ላይ ራሱን ሳይሰቅል  ለበለጠ መልካም ሥራ እንዲተጋ ቢሆን አካሄዳችንና መዳረሻችን ያምራል፡፡ አቤት የሚቀረንን ነገር ሳስበው….፡፡ እንደማኅበረሰብና እንደሀገር መኖር ልንጀምር ስንውተረተር ወያኔ መጣና ድራሻችንን አጠፋው፡፡ ከዚህ ሁሉ የሞራል ስብራትና የኑሮ ንቃቃት መቼ ማገገም እንምንጀምር አንድዬ ይወቅ፡፡…

በቀደም ለታ የሰደድኩትን መጣጥፍ በየት እንደወጣ ስፈትሽ ታዲያን በርሱ ድረገፅ መለጠፉን ተረዳሁ፡፡ በጣም ገረመኝ፡፡ ያን መጣጥፍ እንኳንስ የትግሬ ደም ያለበት ሌሎችም ፈርተው ትተውታል፡፡ ከዚያ ቅጽበት ጀምሮ አንዳች ነገር ተሰማኝ፡፡ ሰውነቴንም ወረረኝ፡፡ ገነት ዘውዴን የመሰለች “ዐማራ”፣ ልደቱ አያሌውን የመሰለ “ዐማራ”፣ በብአዴን ውስጥና በሕወሓት ውስጥ ለሆዳቸው ሲሉ ዐማራነታቸውን እንደኮት አውልቀው ጥለው ወይም ዐማራነት ቁምጥና ይመስል ደብቀው ዐማሮችን እያስፈጁ የሚገኙ ዜጎች ቁጥር ቀላል አለመሆኑን የሚገነዘብ ሰው ይህን ሰው ከትግሬዎች ጉያ ፈልቅቆ አውጥቶ እንደዚህ ለዐማራው ዋቢና ጠበቃ እንዲሆን ያደረገ አንድ ኃይል መኖር እንዳለበት ያምናል – ልክ እንደኔ፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሣነው ነገር የለምና ሊሆን ያለው ሁሉ ሊሆን የግድ ሆነ- እናም የኢትዮጵያ አምላክ ይመስገን ዐማሮችን በትግሬ ጎራዴ የሚያስፈጁ ሆዳም ዐማሮች በሞሉባት ኢትዮጵያ ይህን መሳይ ከተራ ስብዕና በላይ ልዩ ስብዕናን የተላበሰ ትግሬ አገኘን፡፡ ይህን ሰው ማመስገንና መውደድ ምንድን ነው ኃጢኣቱ ታዲያ? “የጊዮርስን ግብር የበላ…” እንዳትሉኝ እንዲህ የምለው የአንዳንዶችን ሽርደዳ አስቀድሜ ስለማስብ ነውና ይቅርታ፡፡ (በነገራችን ላይ ጌች – በናታቸው ማሕጸን ውኃ ሆነው ቢቀሩ በሚሻላቸው ከንቱ ዜጎች – የየትኛውም ነገድና ጎሣ አባላት ሊሆኑ ይችላሉ – ዘለፋና ዛቻ እጅ ሳትሰጥ – አምናለሁ ደግሞ እንደማትሰጥ – በጀመርከው የተቀደሰ ተግባር ቀጥል፡፡ ፈለግህንም በመሰል ጥሩ ዜጎች ለማዳበር ሞክር፡፡)

“ታዲያ አሁን ምን ይጠበስልህ?” የሚለኝ ወለፈንዴ አይጠፋም መቼም፡፡ ምንም አይጠበስልኝም፡፡ ጌታቸውም ያደረገው ሰው ሆኖ ከተፈጠሩ ዘንድ ማንም ሊያደርገው የሚገባውንና የሚጠበቅበትን ነው በተግባር ያሣየው – የተሰጠውን መክሊት ተረድቶ በአግባ ተጠቀመበት፤ ለኅሊናው አደረ፡፡ በቃ፡፡ ከማንም ከምንም ሽልማትም ሆነ ከንቱ ውዳሤን የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ በሕይወቱ ቆርጦ ወደ ትግሉ የገባው ልዩ ሙገሳንና ውዳሴን ፈልጎም አይደለም – “በሕይወቱ ቆርጦ” ስል እነአሰፋ ጫቦ፣ እነሻለቃ ጃተኒና መሰል የወያኔና መሰል ሰይጣናት ረጃጂም ክንድ ሰለባዎች ትዝ አሉኝ፡፡ ለማንኛውም ይህንን ተፈጥሯዊ እንደሆነ የምገምትለትን ጠባዩንም ከርሱ ጋር ሳልነጋገር በ”ቴሌፓቲክ” ምናባዊ የጉዞ መስመር አውቀዋለሁ፡፡ የርሱን ዓይነት ዕድል የሚያገኙ ግን እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ በኛ ሀገር ሁኔታ ከአንድ እጅ ጣቶች ቁጥር እንኳን የማይዘሉ ናቸው፡፡ ከዚህ በላይ መታደል የለም፡፡ ሰው “ክሎን” እየተደገ አይዘራ ወይ አይሰራጭ ሆኖ እንጂ ጌችን በላብራቶሪ እያባዙ በመላዋ ሀገራችን ቢዘሩት ይሄኔ ኢትዮጵያ የት በደረሰች፡፡ በመንፈስ ቀናሁብህ ጌታቸው ረዳ!

ጌታቸው እያደረገ ያለው የሚጠበቅበትን ቢሆንም አድናቆትና አክብሮት ሊያሰጠው የቻለውን ነገር ትንሽ ሰፋ አድርጎ መመልከት ተገቢ ነው፡፡ የመንጋን ጭፍን ስሜት አሸንፎ ራስን መሆን እንደብርቅ በሚታይባት ዓለማችን ውስጥ ጌታቸውን የመሰሉ እውነተኛ ሰዎች ቢደነቁና ቢወደሱ ከሚገባቸው በታች ነው፡፡ በዚህ ዘመን ሰው መሆን ወይም ሰው ሆኖ ለመገኘት መሞከር ከባድ ነው፡፡ ለአብነት  ከመንጋህ መውጣት በራሱ አንድም ዕብድ ያሰኝሃል አንድም በሌላው አቅጣጫ ካየነው ለሰው መለኪያነት የሚውል እጅግ ጤናማ ስብዕናን ያሰጥሃል፡፡ ይህ ደግሞ እንደተመልካቹ ነው፡፡ ትግሬዎች ጌችን እንደ ዕብድና ወፈፌ ሊያዩት ይችላሉ፡፡ ጌችን እኔና መሰሎቼ እንደ የሰው መለኪያ ሚዛን ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ እነዚህን መሰል ሰዎች ጠላታቸው ብዙ ነው ታዲያ፡፡ በዚህኛው ጎራ የክህደትን በዚያኛው ጎራ ያለመታመንን ችግር እያተረፉ የሚሰቃዩበት ሁኔታ መኖሩ አይካድም፡፡ ስለዚህም ነው  ይህን ዓይነቱን ፈተና ለማሸነፍ ጠንካራ ስብዕና መላበስ የሚኖርባቸው፡፡ ብዙ ፈላስፎች በወፈፌነት የተፈረጁትና የሚፈረጁት ከመንጋው የስቅሎ ስቅሎ የዕውር ድንብር ዳንኪራ ወጥተው በጤናማ አስተሳሰብ በመመራት ለማኅበረሰቡ የሚበጀውን ነገር ስለሚጠቁሙ ነው፡፡ ስንቶች እኮ ተሰቅለዋል፤ ስንቶች በመርዝ ተገድለዋል፡፡ ስንቶች እኮ ለእስርና ለግዞት ተዳርገዋል፡፡ ስንቶች እኮ ጎዳና ላይ ተጥለው አይሆኑ ሆነዋል፡፡ ይቺ ዓለም?

“ክርስቲያን በመሆኑ ብቻ በእምነቱ የምትገድሉት ከሆነ እኔን ከርሱ ቀድማችሁ ግደሉኝ” ብሎ አንገቱን ለሠይፍ የሚሰጥ ሙስሊም ሲገኝ የሰው መለኪያ ነው፡፡ “እስላም በመሆኑ ምክንያት የምትገድሉት ከሆነ በቅድሚያ የኔን ደረት በጦር ወግታችሁ ግደሉኝ” የሚል ክርስቲያን ሲገኝ ይህ ሰው የሰው መለኪያ ሚዛን ነው – እኔ በፍርሀት ተሸማቅቄ ብዙ ዐማሮች ሲገደሉና ሲታሰሩ በጎመን በጤና እሞቀ ቤቴ ቁጭ ብዬ ስኖር ጌታቸው ረዳ ስለኔ ይጮሃል፤ ስለኔ ይከራከራል – በዘሩ ሳያገባው በነገዱ ሳይመለከተው – ከሞቀ የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥቱ ወጥቶ ለዚያውም፡፡ ሃይማኖትና ዘር ዓለምን እየበጠበጡና ከርሰ መቃብሯን እያቃረቡ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እነዚህን ይበልጡን ሰው ሰራሽ የሆኑ ድንበሮች በመጣስ በሰውነት  የጋራ ገመድ ተመርቶ ለሰው ልጅ አጠቃላይ ነፃነት የቆመ ሰው ጽላት ቢቀረጽለት፣ ግዑዙ ሃውልት ቢቀምት ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም፡፡ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ጌታቸው ረዳ ከነዚህ ዓይነቶቹ ግሩም የዓለም ዜጎች አንዱ መሆኑን የምመሰክርለት መሃላ ቢፈቀድ ኖሮ በኅያው እግዚአብሔር ስም እየማልሁ ነበር፡፡

በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድን ሥርዓት የሚቃወሙና በዚያም ሳቢያ መከራ የሚገፉ ነጮች ነበሩ፡፡ በሌላም በኩል ከነጮቹ ጋር ተባብረው የአፓርታይድን ሥርዓት ዕድሜ የሚያራዝሙ ሆዳም ጥቁሮች ነበሩ፡፡ በፀረ ባርነት ትግል ወቅት (Negritude Movement) ጥቁሮች ለነፃነታቸው ሲታገሉ አንዳንድ ጥቁሮች ደግሞ በተቃራኒው  “ጥቁር የነጮች አገልጋይ እንዲሆን የተፈጠረ ነው” በሚል መፈክርና እምነት ከነጮች ጋር ተደርበው ጥቁሮች ወገኖቻቸውን ይዋጉ ነበር – ለዚያው መከረኛ ሆድ ብለው(ሆዳችን እንኳንስ በጀርባችን አልሆነ የሚባለው እውነት ነው!)፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ ሰው መሆን ከባድ ነው የሚባለው፡፡ ይህን መሰሉን የዘር፣ የቀለምና የሃይማኖት አሽክላ ሰብሮ በመውጣት ለእውነተኛ የሰው ልጅ ነፃነት መቆም ያስቀናል፡፡ ለዚህ ዓይነት ሰው አንድ መጣጥፍ አይደለም ብዙ መጻሕፍት ቢጻፉለትም አሁንም ያንሰዋል፡፡ ይህን ለመናገር አዲስ አበባ ላይ ተገኝቶ ትግሬዎች የሚያደርጉትን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ ከነዚህ ለይቶላቸው ካበዱና መሬትን ለመርገጥ ከተጠየፉ የጠፉ ትግሬዎች ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሰው ማግኘት በበረሃ ላይ በዛፎች የተከበበ ምንጭ (oasis) እንደማግኘት ነው፡፡ የምለው የማይገባው ካለ ወደኢትዮጵያ ይምጣና ትንሽ ይጎብኘን – ካስቻለው፡፡

ስለጌች ሳነሳ ከአንዳንዶች ጋር የሚጋጭባቸውን ሁኔታዎች ዘንግቼ አይደለም፡፡ ጌታቸው የግንባር ሥጋ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ነገርን የማይሸፋፍንና መስሎ ማደርን የማይወድ ሰው ከጥቂቶች ጋር ብቻም ሣይሆን ከብዙዎች ጋር አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም ከሁሉም ጋር መጋጨት አግባብ የሚሆንበት ጊዜ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ወደ ዝርዝሩ መግባት አልፈልግም – መነሻየ ያ ስላልሆነ፡፡ ግን ይህን መሰል ጠባዩን እንደማውቅለትና እንደምረዳለትም በዚህ አጋጣሚ መጠቆም ስለምፈለግ ነው፡፡ በተረፈ በነገር አለመስማማት ወደ ንቁሪያና መዘላለፍ ባይወስደን መልካም ነው፡፡ አለመስማማትን በጨዋነት ገልጦ በሚስማሙባቸው ነጥቦች ብቻ አብሮ መጓዝም ጨዋነትና ብልኅነት ነው – ለሁሉም፡፡ የኛ ሁኔታ ግን ወይ የነርሱ ነህ አለዚያም የኛ ነህ – ከዚህ ውጭ ያለህ አማራጭ ጠባብ  ነው፡፡ አማራጭ የማይሰጥ የልበሥውራን ፖለቲካ አራማጆች ሆነን ተቸግረናል፡፡ ሆደ ሰፊነት በእህል ብቻ ተወስኖ ቀረና ይህቺ ክብ ጠረጴዛ የሚሏት ነገር ለምግብ ቤት አገልግሎት ብቻ ዋለች፡፡ ፈርንጆች በዱላ ቀረሽ ክርክር ከተመነቃቀሩ በኋላ (ኧረ አንዳንዴስ ይደባደባሉ!) ከአዳራሽ ሲወጡ ይረሱትና በፍቅር ወደፊት ይቀጥላሉ፡፡ እኛ ግን አንዴውኑ አንጀምረው እንጂ የሽሚዛችንን እጅጌ መጠቅለል ከጀመርን የመረዝነውን ሰው ጉድጓድ ውስጥ ካላስገባን ዕረፍት የማናገኝ ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ከዚህ በላይ መረገም ደግሞ የለም፡፡ ሰው የመሆኛችን ጊዜ ናፈቀኝ፡፡ የሚገርመው ደግሞ ከሀገር የወጡትም ስንትና ስንት ሥልጣኔና የሰው ልጅን መተሳሰብና አንድነት በየሚኖሩባቸው ሀገራት  እያዩ ዘር ከልጓም ይስባልና አንድም ነገር አይማሩም፡፡ እዚያም ሆነው ማባላትንና ማናከስን ይቀጥላሉ – ቢያንስ በኢንተርኔት ወንጭፍ፡፡

ለማንኛውም ትኩረቴ የኢትዮሰማዩ አዘጋጅ ጌታቸው ረዳ ስለሆነ እንጂ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሳቢያ አድናቆቴንና አክብሮቴን የምገልጽላቸው ብዙ ምርጥ ምርጥ ዜጎች እንዳሉ መናገር እፈልጋለሁ – ስላልተነሳሁበት ለምሣሌ የቴዲ አፍሮን መስዋዕትነት እዚህ ላይ አልጠቀስኩም፤ የጥቁሩን ዕንቁ የኦባንግ ሜቶንም ገድል አላወሳሁም – ማንን አንስቼ ማንን እተዋለሁና፡፡ ስንቱ አረሆ ወያኔን እያወደሰ በየምሽት ክበቡ ቀፈቱን ሲያንዘረጥጥ ይህ ብላቴና -ቴዎድሮ ካሣሁን – ስለሀገሩ ይዋደቃል፡፡ አሁንም “ሰው በመኪናው እንዳይገጭ” እየጸለይኩ ነው በነገራችን ላይ፡፡ ወይ ወያኔ! ወንጀልን በሴከንድ ውስጥ እንዴት ፍጥር እንደሚያደርጓት ይገርመኛል፤ ደግሞም አለማፈራቸው! …

ላጠቃል፡፡ ጌች እግዚአብሔር ይባርክህ፤ አንተን መሰሎችም እግዚአብሔር ይባርካቸው – ለመንታ መንገደኞችም ልብ ይስጣቸው፤ በዘረኝነት የጨለማ አረንቋ ውስጥ ለሚዳክሩትም እግዜር ይድረስላቸው – ያለኝ ብቸኛ ሀብት ምርቃት ነውና እኔንም ጌታ ይስማኝና የልቤ ሞልቶ የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለ40 እና 50 ዓመታት ብቻም ቢሆን ያሳየኝና ይውሰደኝ – ከተመኙ አይቀር እንዲህ ነዋ! ውድ ወንድሜ የኢትዮሰማዩ ጌታቸው ረዳ በመጣጥፌ ምክንያት በሆዴ ያለውን አስወጣሃኝ – እግዜር ይይልህ እንዳልልህ አንጀቴ አይችልም፡፡ ደግሞም አንተን መሰል ቅንና ፀረ ወያኔ የሆኑ ትግሬዎችን እንደማስከፋ በኋላ ላይ በቁጭት ተገንዝቤ በመጣጥፌ ላይ አንድ አንቀጽ ጨምሬ ልኬ ነበር፡፡ አንተ የለጠፍከው ግን የፊተኛውን ነው፡፡ መቼም እስካሁን ዝም ብለህ ትቀመጣለህ ብዬ አልገምትምና ወ(ላ)ልደህ ከሆነ ዘርህ ይባረክ፡፡ በደጉ ዘመን እንደሙሤ ድልድይ ሆነው ይህን ክፉ ዘመን ከሚያሻግሩን ብርቅዬ ዜጎቻችን አንዱ ነህ ብዬ አምናለሁና እግዚአብሄር ጠባይህን አያስለውጥብን፡፡ አንዳንዴ ነሸጥ ሲያደርገን ባለውለታን እንደዚህ ማመስገኑና በደግ ማውሳቱ ክፋት የለውምና ሌሎቻችንም ይልመድብን፡፡ ቻው፡፡ ለገምቢ አስተያየት – ma74085@gmail.com – ማነህ እጅጉ ነህ እጅቡ የተባልክ ሰውዬ ደግሞ በአቡነ አረጋዊ ይሁንብህ የኔ ጽሑፍ ይቅርብህ፤ ስድብ ደግሞ የትንሽነት ምልክት ነው… እንዴ፣ ነውር አይደለም?)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s