ሕወሓትና ኢትዮጵያዊነት – የሕወሓት የክህደት ታሪክ

ሰማሀኝ ጋሹ (ዶ/ር)

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሕወሃት ሰፈር እየተሰማ ያለዉ ሰለ ኢትዮጵያዊነት የመቆርቆር ስሜት ከማስገረም አልፎ ለሀገር አንድነትና ሉአላዊነት በመታገል የሚታወቀውን የህብረተሰብ ክፍል ‘በባንዳነትና አገር ክህደት’ እየወነጀለ ይገኛል። በተለይ የ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለአለም የጤና ድርጅት ዳይሬከተር ጀነራልነት ዉድድር ጋር በተገናኘ በህወሓት አባላትና ጀሌዎች በማህበራዊ ሚድያ እየተናኘ ያለዉ ግለሰቡን ለእጩነት መቅረብ የሚቃወሙትን የህብረተሰብ ክፍሎች ‘ባንዳዎች’ በሚል ከፈተኛ የስም ማጥፈት ዘመቻ ነዉ። ሁኔታዉን አስገራሚ የሚያደርገዉ ሕወሃትን እቃወማለሁ የሚለዉ የአረና ፓርቲ አመራሮች ሳይቀሩ ቴድሮስ አድሃኖምን የማይደግፍ ባንዳ እንደሆነ የሚገልፅ መግለጫ አዉጥተዋል። ከዚህ ቀደም ሲልም የአባይን ግድብ አስመልክቶ በተነሳዉ ዉዝግብ በተመሳሳይ ከአባይ ግድብ በፊት ሰብአዊ መብት ይከበር የሚሉትን ኢትዮጵያዉያን ‘ከሀዲዎች’ና ‘የሻእብያ ተላላኪዎች’ በሚል ለማሸማቀቅ ከፈተኛ ሙከራ ቢያደርጉም በዉጭ ሃገራት የሞከሩት የቦንድ ሽያጭ  እንደተጨናገፈ ቀርቷል። በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ በታሪክ በሀገር ከሃዲነት የሚታወቀዉ የሕወሃት ቡድን እንዴት ድንገት የኢትዮጵያዊነት ዋስና ጠበቃ ሆኖ ብቅ ሊል በቃ የሚለውን እንቆቅልሽ መመርመር አስፈላጊ ይሆናል።TPLF flag and Ethiopian flag

የሕወሃት የክህደት ታሪክ

ሕወሃት ከተመሰረተበት እለት ጀምሮ ኢትዮጵያና ኢትዮጲያዊነት ለሚባል እሴት ከፈተኛ ጥላቻ እንዳለዉ ታሪክ ከትቦት አልፎአል። ይህንን የክህደት ታሪክ ልዩ የሚያደርገዉ የትግራይ ህዝብና የቀድሞ ነገስታቱ ለኢትዮጵያዊነት ካሳዩት ቀናዊነት በተፃራሪነት የቆመ መሆኑ ነዉ። በ1968 ዓም ሕወሃት ባወጣዉ ማኒፌስቶ ትግራይን የኢትዮጵያ አካል አድርጎም አይመለከታትም።

ትግራይ አክሱም እስከወደቀችበት ጊዜ ድረስ የአክሱም መንግሥት እየተባለች ትጠራ ነበር። ኣክሱም ከወደቀች በኋላም እራሷን በማስተዳደር ለብዙ ጊዜ ብትኖርም ቅሉ ኣልፎ ኣልፎ ባካባቢዋ ለነበሩት ነገሥታት ግብር መክፈሏ አልቀረም።

የሕወሃት ለኢትዮጵያዊነት ያለዉ ጥላቻ የመነጨዉ ኢትዮጵያዊነትን ከአማራ ህዝብ ታሪክና ባህል ጋር የተቆራኘ አድርጎ ስለሚመለከተዉ ነዉ። የትግራይ ችግርና እርዛት ተጠያቂዉ አማራዉ እንደሆነ በማኒፌስቶዉ ያትታል።

በኣፄ ዪሐንስ ዘመነ መንግስት ኃይሏ በርትቶ በአካባቢዋ የነበሩትን ነገሥታት በቁጥጥሯ ሥር አውላ ነበር፤ ይሁን እንጅ አፄ ዩሐንስ ከሞቱ በኋላ በዳግማዊ ምኒልክ ኣማካኝነት ትግራይ በሸዋው ማእከላዊ ግዛት ሥር ወደቀች። ከዚህ ጊዜ ሀኋላ ነው የአማራው የመሳፍንት ቡድንና ተከታዮቹ የትግራይን ነፃነት ገፈው የሕዝቧን አንድነት ያናጉት። ግልጽና ስውር በሆኑ ዘዴዎችም (ሸዋዊ ዘይቤዎች) የትግራይ ሕዝብ በድንቁርና፣ በበሽታ፣ በረሃብ አዘቅት ውስጥ እንዲሰምጥ ያደረጉት። በተለይም ትግሬነቱን በፍጥነት እንዲክድና ያለውድ በግድ “አማራ ለማድረግ” ያልሞከሩት ዘዴ ባይኖርም መሬቱ ተቆራርሶ ስለተወሰደበትና የተደራረበ ጭቆና ስለደረሰበት አገሩን ጥሎ ተሰደደ። ባጠቃላይ ባሁኑ ጊዜ ትግራይ ነፃነቷ የተገፈፈች፣ መሬቷ ተቆራርሶ የተወሰዳባትና የተወሳሰብ ችግር የደቆሰው ሕዝብ የሚኖርባት ጭቁን ብሔር ናት።

በዚህም መሰረት በሕወሃት እምነት የትግራይ ህዝብ ብሔራዊ ትግል ፀረ-የአማራ ብሔራዊ ጭቆናና ከኢምፐርያሊዝም ነፃ የሆነ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ማቋቋም መሆኑን በወቅቱ ይፋ አደረጓል። አማራዉን ለማጥፋት በዋናነት ኢትዮጵያዊነትን መምታት እንዳለበት በማመን ሕወሃት የሞት ሽረት ትግል ማድረግ ጀመረ። ለዚህ የታሪክ ክህደት ጅማሮ ኢትዮጵያ የሚባለዉ ሃገር በዳግማዊ አፄ ምኒልክ እንደተፈጠረችና የመቶ አመት ታሪክ ብቻ እንዳላት ቢያንስ እስከ 2000 ዓም ድረስ የማያቋርጥ ዘመቻ አካሄደ። በጊዜዉ የነበሩት እነ መኢሶንና ኢሕአፓ የመሳሰሉት ፓርቲዎች ሕወሃት ከሚያራምደዉና በጊዜዉ ፋሽን ከነበረዉ ከማርክሳዊ የመደብ ትግልና የብሄር ብሄረሰቦች የራስን እድል በራስ መወሰን መብት ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም እነዚህን ፓርቲዎች ሕወሃት አምርሮ ይጠላቸዉ ነበር። ይህ ጥላቻዉ በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት የተፈጠረ እንዳልሆነ ግልፅ ነበር። ነገር ግን እነዚህን ፓርቲዎች ሕወሃት የሚመለከተዉ የአማራ ፓርቲዎችና ኢትዮጲዊነትን ለማስቀጠል የሚሰሩ ፓርቲዎች አድርጎ ነበር። በዝነኛዉ የ 1968 ማኒፌስቶዉ ሕወሃት መኢሶንና ኢሕአፓን  የመሳሰሉትን ድርጅቶችን ‘ ተራማጅ” ነን ባዮች የሸዋ ምሁራን ትምክህተኞችና አድርባዮች ሆነው ስለሚገኙ በአንድ የፖለቲካ ማህበር ሥራ ተራማጅ ዓላማ ይዞ አብዮት ለማካሄድ እንደማይቻል’ ያስረዳል።

ይሄ በህወሃት ቡድን የተጠነሰሰዉ ፀረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከሚባሉት የጎረቤትና የአረብ ሀገሮች በመታገዝ 17 አመቱ የትጥቅ ትግል ወቅት ቀጠለ። በመጨረሻም መንበረ ስልጣኑን በ1983 ዓም ሲቆጣጠር ኢትዮጵያን የማፈራረሱን ፕሮጀክት አጠናክሮ ቀጠለ። በፕሮግራሙ ጠላት አድርጎ ያስቀመጠዉን የአማራዉን ማህበረሰብ ለመበቀል ወሳኝ ምእራፍ አድርጎ የተመለከተዉን ኢትዮጵያዊ እሴቶችንና ተቋማትን ማፈራረሱን ተያያዘዉ። ለዚህ አላማ የመጀመርያዉ እርምጃ በሰኔ ወር 1983 ዓም በተደረገዉ የሽግግር መንግስት ምስረታ ምንም አይነት ህብረ ብሄራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይካፈሉ መከልከል ነበር። በጉባኤው እንዲካፈሉ የተፈቀደላቸዉ የጎሳ ፓርቲዎች ብቻ ነበሩ። ኢትዮጵያዊነትና አማራነት ያንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸዉ ብሎ የሚያምነዉ ሕወሃት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ አማራዎችን ከስራ በማባረር አማራዉ በየቦታዉ ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ እንዲኖር አደረገ። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል የሚኖረዉ አማራም እንዲጨፈጨፍ ሁኔታዉን አመቻቸ።

ሌላዉ ኢትዮጵያዊነትን የማዳከም አጀንዳዉ የጎሳን ፖለቲካ በሀገሪቱ ዉስጥ መዘርጋትና ኤርትራን በማስገንጠል ሀገሪቱን ወደብ አልባ ማድረግ ነበር። አንዳንድ ወገኖች በጎሳ ላይ የተመሰረተዉ የፌዴራል ስርአት መብታችንን ያስከብርልናል ብለዉ ቢያምኑም የፖለቲካ ስርአቱ መዘርጋት ዋና አላማ አማራዉን ለማዳከም ኢትዮጵያን ማዳከም የሚለዉን አላማ ለመፈፀም የታቀደ ነዉ። በተለይ በአማራዉና በኦሮሞው መካከል የማይታረቅ ቅራኔ እንዳለ አስመስሎ በማቅረብ ሁለቱን ማህበረሰቦች በማጋጨት ስልጣኑን ማራዘም ነዉ። የአዲስ አበባ ህዝብ በማያቋርጥ ከበባ (siege) ዉስጥ እንዲኖር የተፈለገዉ ከዚሁ የሕወሃትን መሰሪ አላማ ለማስፈፀም ነዉ። በሽግግሩ ወቅት የነበረዉን የክልል 14 የአዲስ አበባ መስተዳድር አፍርሶ በህገ መንግስቱ የአዲስ አበባ ሁኔታ ግልፅ ባልሆነ መልኩ እንዲቀመጥ ተደርጓል። በአንድ መልኩ የኦሮምያ ክልል የባለቤትነት መብት እንዳለዉ ያልተቀመጠ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ አዲስ አበባ ራሱን የማስተዳደር መብት እንደሌሎች ክልሎች እንዳይኖረዉ ተደርጓል። በኢትዮጵያዊነት ላይ ይማያወላዉል አቋም ያለዉ የአዲስ አበባ ህዝብ እኔ ከሌለሁ ኦሮሞ ይዉጥሃል በሚል የሕወሃት ማስፈራርያ በስጋት እንዲኖር ተፈርዶበታል።

በኢትዮጵያ ዘምናዊ ታሪክ ዉስጥ በሃገር ክህደት ስራዉ ተወዳዳሪ ያልነበረዉ መለስ ዜናዊ ለዚህ የፀረ ኢትዮጵያዊነት ራእይ አስፈፃሚነት ሚና ሕወሃት ያዘጋጀዉ ሰዉ ነበር። ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል በፊርማዉ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደብዳቤ የፃፈዉ መለስ ዜናዊ በፀረ ኢትዮጵያዊ ንግግሮቹ ይታወቃል። ‘ባንዲራ ጨርቅ ነዉ፥ የአክሱም ሃዉልት ለወላይታዉ ምኑ ነዉ’ ፤ እንኳን ከናንተ ተፈጠርኩ’ በሚሉት ንግግሮቹ የሚታወሰዉ ዘረኛዉና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ከዩንቨርስቲ ጊዜዉ ጀምሮ በኢትዮያዊነት ላይ ከፈተኛ ጥላቻ እንደነበረዉ በቅርብ የሚያውቁት ምስክርነታቸዉን ሰጥተዋል። በአጠቃላይ ይሄ ሕወሃት ለዘመናት ያራመደዉ ፀረ ኢትዮጵያዊነት በይዘት ያልተቀየረ ቢሆንም በቅርፁ ግን ለዉጥ አሳይቷል። ይህንን ያካሄድ ለዉጥ በሚቀጥለዉ ክፍል እናያለን።

ኢትዮጵያዊነትን እንደ መሳርያ መጠቀም

ጠላቴ ነዉ የሚለዉን የአማራ ማህበረሰብ ኢትዮጵያዊነትን በመምታት ካዳከመዉና አማራዉ ይዞት ነበር የሚለዉን ስልጣን የአንድ አካባቢ ሰዎች  ከተቆጣጠሩት በኋላ የኢትዮጵያ እንደ ሃገር መቀጠል ለሕወሃት ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ተረዳ። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነትን አስፈላጊ ለሆነ የፖለቲካ አላማ ብቻ (instrumental approach) በመጠቀም እንዳይጠፋም እንድያድግም የሚያደርግ ፖሊሲ መከተል ጀመረ። ይህም ማለት አንድ ለሆነ የፖለቲካ ግብ ኢትዮጵያዊነትን ከተጠቀመ በኋላ ኢትዮጵዊነት አንሰራርቶ ስልጣኑን እንዳያሰጋዉ ‘ትምክህተኛና የቀድሞዉ ስርአት ናፋቂዎች’ በሚል እንደገና መድፈቅ ነዉ። የዚህ ፖሊሲ አዋጭነት የተሞከረዉ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ነበር። በ1991 በተካሄደዉ የድንበር ጦርነት ወቅት የኤርትራን ሃይል መቋቋም ያቃተዉ ሕወሃት የኢትዮጵያን ህዝብ ለጦርነቱ ለማሰለፍ የሚጠላዉን ኢትዮጵያዊነትን እንዲሰብክ ተገደደ። መገናኛ ብዙሃን የተከለከሉትንና የጦርነት ናፋቂዎች ዜማዎች ናቸዉ የተባሉትን ሀገራዊ ዜማዎች በስፋት እንዲያሰሙ የተደረገ ሲሆን ህዝቡም ሃገሩን ለማሰመለስ ተንቀሳቀሰ። ጦርነቱን ኢትዮጵያ በአሸናፊነት ብትወጣም ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኤርትራ የሚያደላዉ መለስ ዜናዊ ጦሩ ሙሉ በሙሉ ሻእብያን ሳይመታ እንዲቆም አዘዘ። ጦርነቱን በድል እንድንወጣ ከፈተኛ ሚና የተጫወቱት የቀድሞዉ መንግስት ወታደሮች እንደገና በስፋት ከሰራዊቱ ተቀነሱ። ስለ ኢትዮጵያዊነት በሚድያዉ የሚሰበከዉ ቀስ በቀስ እንዲቀር ተደርጎ እንደ ቀድሞው ‘ነፍጠኞችና ትምክህተኞች’ በሚል ኢትዮጵያውያንን ማሳደድ ተጀመረ።

ሕወሃት እንደገና የ1997ን ምርጫ ተከትሎ የኢትዯጵያዊነትን ካባ መልበስ ጀመረ። በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የታጀበዉ የቅንጅት ማእበል የምርጫ ዘመቻ የዘረኞችን አጥር በብርቱ የነቀነቀዉ ሲሆን ኢትዮጲያዊነት ሊያጥፋዉ የማይችል እሳት መሆኑን ሕወሃት ተረዳ። ምርጫዉን በሃይል ከጨፈለቀ በኋላ እንደገና ኢትዮጵያዊነትን እንደ መሳርያ መጠቀም አማራጭ የሌለዉ መሆኑን ተገነዘበ። መለስ ዜናዊ የ2000 ዓም የሚልንየም በአል ሲከበር ባደረገዉ ንግግር የመቶ አመት ነዉ  በማለት ሲያጣጥለዉ የነበረዉን የኢትዮጵያን ታሪክ ምንም ሀፍረት ሳይሰማዉ ሀገሪቱ የብዙ ሺህ አመት ታሪክ እንዳላት መሰከረ። ከዚህ በመቀጠልም ሕወሃት የባንዲራ ቀን ማክበር ፥ ልማታዊ መንግስት በሚል የኢትዮጵያን ትንሳኤ አብሳሪ ሆኖ ብቅ አለ። የአባይ ግድብ ፕሮጀክትም ዋናዉ አላማ ህዝቡን ለማታለልና ኢትዮጵያዊ ለመምሰል የሚያደርገዉ ጥረት አካል ነዉ።

በእዉነት ሕወሃት ስህተቱን አርሞ ኢትዮጵያዊነትን ተቀብሎ ቢቀጥል እሰየዉ የሚያሰኝ ነገር ነው። ነገር ግን አሁንም ኢትዮጵያዊነትን የሚፈልገዉ ስልጣኑን ለማራዘምና ህዝቡን ለማታለል መሆኑ ግልፅ ነዉ። ለዚህም ብዙ አብነቶች ማቅረብ ይቻላል። አሁንም በኢትዮጵያዊነት ካባ ስር የአንድ አካባቢ ሰዎች ኢኮኖሚዉን፥ ፖለቲካዉን፥ ወታደሩንና ደህንነቱን ተቆጣጥረዉ መቀጠላቸዉ ዋናዉ ማስረጃ ነዉ። ሌላዉ ማስረጃ አሁንም እዉነትኛ በኢትዮጵያዊነት ላይ እምነት ያላቸዉን የፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎች ማሰርና መግደልን መቀጠላቸዉ ነዉ። እነ ቴዲ አፍሮ፥ እስክንድር ነጋ፥ ህብታሙ አያሌዉ፥ ተመስጌን ደሳለኝ፥ አንዱአለም አራጌና ሌሎች ታጋዮች በእስር እንዲማቅቁ የሚደረገዉ ብቸኛዉ ወንጀላቸዉ ኢትዮጵያን መዉደድ ሆኖ በመገኘቱ ነዉ። አሁንም ማንኛዉንም ለስልጣናቸዉ የሚሰጋቸዉን የኢትዮጵያዊነት እንቅስቃሴ በ‘ ትምክህተኝነት’ በማሳበብ መምታቱን ቀጥለዉበታል። ኢትዮጵያውያን በሊቢያ በታረዱ ጊዜ ድርጊቱን አዉግዞ የወጣዉን ህዝብ የቀጠቀጡትና በቅርቡ በአማራ ክልል የተነሳዉን አመፅ ለመጨፍለቅ ያደረጉት ጭፍጨፋ እዉነተኛ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንይነሳሳ ስለሚፈልጉ ብቻ ነዉ።

ትዉልዱ የህገሩን ታሪክና ባህል እንዳያዉቅ በማድረግ በቁስና በሱስ ሰቀቀን ብቻ እንዲሞላ ያደረጉት ለኢትዮጵያዊነት ካላቸዉ ጥላቻ የመነጨ ነዉ። ህገሪቱ በጎሳ ተከፋፍላ ከነገ ዛሬ ተበተነች እያልን እንድንሰጋ የተደረገዉ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተደረገዉ የረጅም ጊዜ ስራ ዉጤት ነዉ። እንዲህ ኢትዮጵያዊነትን ታጥቀዉ ለማጥፋት ላለፉት 40 አመታት የተሰማሩት የሕወሃት ጀሌዎች ናቸዉ ለኢትዮጲዊነቱ በህይወቱ የሚወራረደዉን ህዝብ ‘ከሃዲና ባንዳ’ እያሉ የሚሰድቡት። የቱንም ያህል እንደ እስስት ቢቀያየሩ የሕወሃት መሪዎችና አባለት ታሪክ በሃገር ክህደትና ማፈራረስ  የሚስታዉሳቸዉ ናቸዉ። ስለዚህም የምንወዳትን ሀገራችንን ከሕወሃት መንጋጋ አላቅቆ ከተደቀነባት ጥፋት በማትረፍ ወደ ሙሉ ክብሯ መመለስ የትዉልዱ ሃላፊነት ነዉ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s