አማራ ወዳጆችን ማብዛት ፤ ባላንጣዎችንም መቀነስ የሚችለው በራሱ ጠንክሮ ሲወጣ ብቻ ነው! (መርከቡ ዘለቀ)

 በወቅቱ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአማራ ህዝብ ላይ እጣታቸውን የሚቀስሩ ቡድኖች ብዙ  መሆናቸውን እየተመለከትን ነው፡፡ በእርግጥ  ህወሓትና ግብረ አበሮቹ የሀገር  ሀብት እስከ ዳር ደንበሯ እየዘረፉ ባለበት ዘመን ለሀገር ጠበቃ ሆኖ የተገኘ ሁሉ ጠላት  ሊበዛበት የግድ ነው፤ የሚጠበቅም ነው፡፡ ከአማራ ህዝብ ታሪካዊ ጠላቶች (ህወሓት፤ ሻብዕያና ኦነግ) በተጨማሪ የዛሬዎቹ ግንቦት 7 እና  ሀገራዊ ንቅናቂ ተብየው ቡድንም የአማራን ህዝብ የሚወክሉ ድርጅቶችን በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ በማውገዝ ላይ ይገኛሉ፡፡

አሁን ግን እጅግ እየገረመንና እየመረረን የመጣው ግንቦት 7 የተባለው ሳያፈራ የጨነገፈው የምውታን ስብስብ የሚፈጥረው የማያባራ ንትርክ ነው፡፡ለዚህም ዋናው ምክንያት የግንቦት7 ከአሳዳሪዎቹ የተሰጠውን የቤት ስራ ለመስራት ሲል  ነው በአማራ ስም የተደራጁ ቡድኖችን በባላንጣነት የፈረጀው፡፡

ስለእውነት ግን  ግንቦት 7 ለምን በአማራ ስም የተደራጁ ቡድኖችን ያወግዛል? ለምን ጸረ-ኢትዮጵያና በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የጠራ አቋም ከሌላቸው ቡድኖች ጋር አብሮ ለመስራት እየታተረ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የማይደፈርስ  አቋም ካላቸው የአማራ  ድርጅች ጋር መስማማት/አብሮ መስራት  ተሳነው?

እኔ ግንቦት 7ን  ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ከሚያስተላልፋቸው ፕሮፓጋንዳዎች  አንፃር ስመለከተው ራሱን በራሱ እያጠፋ/እየገደለ (ስዊሳይድ እየፈጸመ) ያለ ድርጅት መሆኑን ነው፡፡ ይህ እሳቤ እውነት የሚሆነው ግን ግንበት 7ን እንደ ሀገራዊ ድርጅት አድርገን  ከወሰድነው ነው፡፡ አሁን አሁን ግን ግንቦት 7 አገራዊ ድርጅት መሆኑ ቀርቶ ዘረኛና ጸረ-ኢትዮጵያ ድርጅት መሆኑን እያስመሰከረ ነው፡፡ዘረኛነቱን ባወጣው የድርጅቱ ውስጠ ድንብ(ከአማረኛ በተጨማሪ ሌላ ቋንቋ ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን የገለጸበት) በሚገባ ተገለጾ ይገኛል፤ ጸረ-ኢትዮጵያነቱም የሻዕቢያ ተላላኪ በመሆኑና  ከሌሎች ጸረ-ኢትዮጵያ ቡድኖች ጋር በጋራ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚያደርገው አንቅስቃሴ ይገለጣል፡፡

ግንቦት 7 የህወሓትን መንግስት ማስወገድ(በህልሙ) የሚፈልገው ስልጣን ከህወሓት ወደ ግንቦት 7 ሰዎች በማሸጋገር ሌላ ዘረኛና የጥፋት ሰርአት ለመመሥረት እንጅ ሥር ነቀል  ለውጥ በኢትዮጵያ በማምጣት ሁሉም ዜጎች እኩል የሚስተናገዱባት ሀገር ለመፍጠር አይደለም፡፡ለዚህም ነው የህወሓትን በቋንቋ ላይ የተዋቀር ፌደራሊዝም እንዲቀጥል የሚፈልገው፤ ለዚህ ነው በዘር ላይ የተዋቀሩ ቡድኖችን ሲቀላቀሉ የህወሓትን ዘራኛ እና አግላይ  አስተዳደር የሚቃወሙ ቡድኖችን የሚኮንነው፡፡

ግንቦት 7 በቋንቋ ላይ የተመሠረተውን የወያኔ ክልላዊ አስተዳደር እንዳለ እቀበላለሁ ከሚልባቸው ምክንያቶች አንዱ  የግብረ አበሮቹን ፍላጎት ለማሟላት ሲሆን የእነርሱም ምኞት በህወሓት ዘርኛ መንግስት ከአማራ ህዝብ የነጠቁትን ሰፊ መሬት እንደያዙ በሂደት ለመሸሽ ነው፡፡ ነገር ግን በእውነት የግንቦት 7 ጥረቅሞች የፖለቲካ ሰዎች ናቸው ወይ? አስተማማኝ አጋሩን  አውግዞ  ከመሰናክሉ ጋር የሚዶልቱ፤ በአሜሪካ ውብ ሆቴሎች እየተንፈላሰሱ አረበኞች ነን እያሉ በአረበኛ ስም የሚቀልዱ፤ ስለ ኢትዮጵያ እንታገላለን እያሉ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ዘንድ የሚሸጎጥ/የሚወተፉ፤ ጦር ሜዳ ሳይውሉ ነውጡን የፈጠርነው  እኛ  ነን እያሉ ያለ ሀፍረት በአደባባይ የሚዋሹ፤ ውጤት በሚስገኝ  ስራ ላይ ከማተኮር ይልቅ በየጊዜው የንትርክ መድረክ ያሚዘጋጁ፤ ስለ ኢትዮጵያ እንታገላለን እያሉ በጀግና ኢትዮጵያውያን ደም እና አጥንት ተለወሶ   የተጻፈውን የኢትዮጵያ ታሪክ  ኢሳት በተባለው ሚዲያቸው የሚያርክሱ ከሆነ  ግንቦት 7 ጤና የጎደላቸው ሰዎች  ስብስብ እንጅ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ግንቦት 7  የጤነኛ ሰዎች ስብስብ ቢሆን ኑሮ ጸረ-ኢትዮጵያ አቋሙን ለማራመድ እንኳ  አካሄዱን  ከአጋሮቹ ከወያኔ እና ከሻዕብያ ይማር ነበር፡፡ በአርግጥ ከኦነግ ሊማር  አይችልም ምክንያቱም ኦነግም ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ አንድ ጥይት እንኳ ሳይተኩስ በለንደን ሆቴሎች እየተዝናና ኢትዮጵያን አናፈርሳለን   የሚል መናኛ  ድርጅት በመሆኑ፡፡ ኦነግ መፈክሩ ብቻ ሳይሆ የሚገርመው ህልሙን ለማሳካት የሚጠቀምበት  ስልት/ ስተራቴጅም ከንቱ ነው፡፡

ስለ እውነት ግን  አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ከዚህ ጸረ-አማራ እና ጸረ-ኢትዮጵያ ከሆነው  ግንቦት 7 ድርጅት  ጋር አሁንም አባል ሁነው የሚደክሙ የአማራ ተወላጆች ካሉ እነርሱም  በእውነት አብደዋል ማለት ነው፡፡ እርግጥ ነው ከአንድ አመት በፊት ብዙዎቻችን ተሸውደን ነበር፡፡ ስለ ኢሳትና ግንቦት 7 በየቀኑ  ወሬ/ዜና  ሳንሰማ ከዋልን አንድ  ትልቅ ነገር እንዳመለጠን  ይሰማን ነበር፤ ስለ ግንቦት 7 ሲወራ የተስፋ ጭላንጭል ይታይን ነበር፡፡ የግንቦት 7ን  ድብቅ አጀንዳ በብዕራቸው ለተፋለሙና ላጋለጡ ውድ ኢትዮጵያን  ምስጋና ይግባቸውና  አሁን በግንቦት 7 ላይ የነበረው ተሰፋና መልካም ስሜት በሀገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ  ላይመለስ ሙቶ ተቀብሯል፡፡ የሚቀጥለው ሥራ ግንቦት 7 እንደ ህወሓት ስረ ሰዶ/ገንግኖ ሳያስቸግር  በሁሉም መስክ መፋለምና ማጥፋት  ነው፡፡

የአማራን  ህዝብ ከጥፋት ለመታደግ ከእውነት እየሰሩ ላሉ ቡድኖች የማስተላልፈው መልክት የአማራ ህዝብ  ብዙ ወዳጆች እንዲኖሩትና የባላንጣዎቹም ቁጥር  እንዲቀንስ  ከተፈለገ  ብቸኛው አማራጭ  መንገድ አማራ  በራሱጠንክሮ  መውጣት አለበት የሚል ነው ፡ ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ማንም እየተነሳ የአማራን ህዝብ ሲያዋርድ፡ ሲዘርፍ፤ ሲያሳድድ፡ በግፍ ሲገድል ፤ ደም እና አጥነቱን የገበረበትን ታሪካዊ መሬቱን ሲነጥቀው የኖረበት ብቸኛው ምክንያት  አማራ ጠንክሮ ባለመውጣቱ/ባለመደራጀቱ  እንደሆነ ሁላችንም የሚያስማማ  አብይ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ለዚህም ነው ተልካሻው ግንቦት 7 እንኳ ሳይቅር ያለ ምንም ሀፍረትና ፍርሀት ከ30 ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን  የአማራ ህዝብ  እራስህን ከጥፋት ለመከላከል መደራጅት የለብህም  እያለ እያፌዘ  የሚገኘው፡፡ ይህ ትዕቢት ህወሓትና ሻዕቢያ ከሚያሳዩት ትዕቢትም በላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ የአማራና የኢትዮጵያ ጠላቶች የትዕቢታቸው ምንጨ ለረጅም ጊዜ ማንም ሳይነቃ በወታደራዊ ኃይል መዘጋጀታቸው ብቻ ነው፡፡ ግንቦት 7 ግን በአውላላ ሜዳ ላይ የሚጮህ ከንቱ ሲሆን   ሌላውን ሊያጠቃ ይቅርና እራሱን ለመከላከል እንኳ የማይችል ቡድን ነው፡፡

ለመሆኑ ግን ግንቦት 7 በየትኛው አቅሙና ህጋዊ ሰውነቱ ነው የሌሎችን የመደራጀት መብት  ቻሪና ከልካይ የሆነው? ግንቦት 7 ውስጣዊ ማንነቱ ሻዕቢያና ወያኔ መሆኑ እየታወቀ ከግንቦት 7 ጋር አብሮ ለመስራት የሚመኝ የአማራ ድርጅትስ እንዴት ሊኖር ይችላል?  የግንቦት 7ም ሆነ የሀገራዊ ንቅናቄው ኢለማ አማራና ኢትዮጵያ ናቸው ፡፡ ለዚህ ነው ግንቦት 7 በሚያካሂደው  ስብሰባ ላይ ሁሉ በአማራና በኢትዮጵያ ታሪክ  ላይ የሚዘምተው፡፡

ግንቦተ 7 አማራንና ኢትዮጵያን ለማጥቃት ከሚጠቀሙባቸው ስልቶች አንዱ ሰርጸ ደሰታ እንደገለፀው “የወያኔ  የክትሰዎችን” በመጠቀም ነው ፡፡ ለዚህም ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያምን በሲያትል ስብሰባ ተገኝተው ያደርጉትን  የወረደ ንግግር  እንደምሳሌ መውስድ እንችላለን፡፡ ግን ስለ እውነት እንነጋገረ ከተባለ ፕሮፌሰሩ አሁን ኢትዮጵያ በታሪኳ  አይታው የማታውቀው ቀውስ ውስጥ በገባችበት ወቅት  ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፤ ስለመተሳሰብና በጋራ  ስለመስራት ነው መስበክ/መናገር ያለባቸው  ወይስ ሊያግባቡ በማይችሉ  ጉዳዮች ላይ? አጼ ቴዎድሮስ ያለ ጊዜያቸው የተፈጠሩ ታላቅ መሪ መሆናቸው እየታወቀ አፄ ቴዎድሮስ ከህዝቡ ጋር አልተግባቡም  ነበር ማለት ከፕሮፌሰሩ የሚጠበቅ የወቅቱ ንግግር ነው ወይ? ኢትዮጵያ  ከሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ከተውጣጡ ጀግና እና አረበኛ  ልጆቿ ተከብራ የኖረች ሀገር መሆኗ እየታወቀ ጀግናው በላይ ዘለቀ ጎጃሜ ቢሆንም ማንነቱ ኦሮሞ ነው ማለት በእውነት እንኳስ የፕሮፌሰር ንግግር ሊሆን ቀርቶ ፌደል ያልቆጠረ ሰው  እንኳ ሊናገረው ይገባል ወይ?

ሰረጸ ደስታ  ሰለ ኦረሞ ደጋግሞ እንደገለጸው  አሮሞ እኮ የራሱ ጀግና አላጣም ነበር፤  ችግሩ  ጀግኖቹን ሁሉ የነፍጠኛ ወዳጆች ናቸው ብሎ በመካዱ ባዶ እጅኑ  መቅረቱ ነው ፡፡ እንበልና ጀግናው በላይ ዘለቀ ኦሮሞ ነው ብለን ብንቀበላቸው ፕሮፌሰሩ ምን ይፈጠር ነው የሚሉን? አማራ ጀግና  የለውም ለማለት ከሆነ ፈጽሞ  አያስኬድም፡፡ በእውንት አንድ ስሙን ለጊዜው የማላሰታወሰው ወንድሜ ስለ ፕሮፌሰሩ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በለጠፈው ጽፍ ለጽሁፉ የሰጠው ርዕስ “መገለባበጥ እንደ—— መክሸፍ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን” የሚል ነበረ፤ እውነት ነው በጣም ከሽፈዋል ፕሮፌሰሩ፡፡

በነገራችን ላይ ስለ ኮሌኔል መንግስቱ ኃይለማሪያምና የወታደራዊ መንግስት የውድቅት መንስኤዎች በሚያትት መጽሃፍ ላይ እንዳነበብኩት መንግስቱ ኃይለማሪያም እጅግ ካዘነባቸው ምሁራን መካከል ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያምና ደ/ር ኃይሉ አርአያ ይገኙባቸውል፡፡ መንግሰቱ ኃይለማሪያም እንደሚለው ወያኔ 1983ዓ.ም ሰሜን ሸዋ በደረሰበት ወቅት ምሁራኑ ለኢትዮጵያ አዋጭ መንገዶችን ከማቅረብ ይልቅ ለወያኔ አስተዋፆ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ማተኮራቸውን በማንሳት በወቅቱ  እንዳዘኑባቸው አንብቢያለው፡፡

ስለዚህ ግንቦት 7 የወያኔን የክፉ ቀን ልጆች ከየቦታው እየመዘዘ ለመጠቀም የሚያደርገው ትርፍ የማያስገኝ አካሄድ ውድቀቱን ከማፋጥን ውጭ  ሌላ ትርፍ አያስገኝለትም ፤ ስልቱ ተነቅቶበታል፤ የክት ሰዎችም እነማን እንደሆኑ  እየታወቀ ነው፡፡

ሌላው ላለፈው 40 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያን ለማፈረስ የሻዕብያና ወያኔ አሽከር ሆኖ ሌት ከቀን ሲሰራ የኖረውና አሁንም ከዚህ ነውረኛ ሰራው ያልታቀበው አቶ ሌንጮ ለታ በሲያትሉ ስበሰባ “ የኢተዮጵያ ጉዳይ ያሳስበኛል” ሲል የምጸት ንግግር እንዳደረገ አነበብን፡፡ ይገርማል!  ስለ አቶ ሌንጮ ለታ  ምንነት አቶ ሰርጸ ደስታ በሚያስደት ሁኔታ የገለጸው ስለሆነ መድገም አያስፈልገም፡፡ ዶ/ር ብረሀኑ ነጋም የአሻንጉሊቶችን ስብስብ (ሀገራዊ ንቅናቄ ተብየውን) ኢትዮጵያን የሚመጥን ድርጅት ነው በሚል ያደረገውን ንግግር እንዲሁ በድረ ገጽ አነበብን ፡፡ በእውነቱ ኢትዮጵያን የሚወክለውና የሚመጥነው ኢትዮጵያን ለማፈረስ ሲጥር የኖረውና አሁንም ኢትዮጵያ ብሎ መጥራት የሚጸፈው፤ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓለማ ሲያይ የሚበረግገው  የሌንጮ ለታ  ድርጅትና የሻዕቢያ ተላላኪ የሆነው  የግንት 7 ድርጅት በአንድ ላይ የመሠረቱት የጥፋት ቡድን እንዴት ነው ኢትዮጵን የሚመጥነው?   ምን አልባትም በውስጥ ወይራ  ንግግር  ደ/ሩ ማለት የፈለገው  ኢትዮጵያን ለማፍረስ አቅም ያለው ጸረ-ኢትዮጵያ ድርጅት መሥረተናል ለማለት ሊሆን ይችላል፡፡ ይኸኛውም  ሀሳብ ቢሆን ሊሳካላቸው  የሚችል አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ እጅግ የምትገርም ሀገር ናተ፡፡ በክፉ ቀን ከጎኗ ተሰልፈው መሰዋት የሚከፍሉ እንዳሉ ሁሉ ችግር በገጠማት ቁጥር ከቅጥረኞች ጋር በማበር ያለማንም  ተከላካይ የቡድን ጥቅማቸውን ለማሳካት የሚሮጡ  ብዙ ናቸው፡፡በተለይ በአሁኑ ወቅት ከዘረኛው ህወሓት ትግሬ በተጨማሪ  ኦነግና ግብረ አበሮቹ አሁን እየሰሩት ያለው የቆሸሸና ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት ይህንኑ ነው፡፡ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር የሁሉም ጠላት በሆነው በወያኔ ላይ ክንዳቸውን ማንሳት ሲገባቸው እንገነጠላልን፤ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት እንዲሁም  በባንዲራዋ ላይ መደራደር ይገባናል ይሉናል፡፡ ሀገረ ውስጥ ያለው የህወሓት ቡችላ  ኦህዴድም በአዲስ አበባ ላይ እየሰራ የሚገኘው ሴራ ከኦነግ  ጋር በመተባበር ነው፡፡ ለመሆኑ ግን ከሃዲውና ዘራፊው ወያኔ ያለማንም ተከላካይ የሚተላልፈው የክህደት ውሳኔ ተቀብሎ የሚኖር ህዝብ ሊኖረ እንደማይችል እንዴት ኦህዴዶች/ኦነጎች መረዳት ተሳናቸው? ኦህዴዶች እና ኦነጎች የሸዋ  ኦሮሞ ጀግኖችን እያዋረዱ ለምን በአዲስ አበባ ላይ መስገብገብ አበዙ? የሸዋ ጀግኖችን  ከጠሉ ጀግኖቹ ከሌላው ወገናቸው ጋር ተባብረው የመሠረቷትን ከተማ ለምን ይፈልጓታል?  ግለሰቡን ከጠሉ ንብረቱን መመኝት አያስኬድም፡፡ የኦህዴዶችና ኦነጎች ዘዴ ግልጽ ነው፡፡ የገቢያ ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው የወቅቱን የፖለቲካ  ቀውስና የአማራን አለመጠናከር ተጠቅመው አዲስ አበባን  በግርግር ለመንጠቅ  ነው፡፡ የወያኔ ስልትም እንዲሁ  ግልጽ ነው፡፡ የአማራን የትግል አቅጣጫ ማስቀየርና ጠላቱንም ማብዛት ነው፡፡

 

ወደ ማጠቃለያ መልክቴ ስመለስ በአማራ ስም ተደራጅታችሁ አማራን  ከጨርሶ መጥፋት ለመከላከል   እየተንቀሳቀሳችሁ የምትገኙ ቡድኖች ሁሉ መረዳት የሚገባችሁ አብይ ጉዳይ  አማራ  ከፍተኛ  ፈተና ውስጥ የገባ መሆኑን ተርድታችሁ ይህን ከፍተኛ ፈተና በአሸናፊነት ለማለፍ በአንድነትና በጽናት በመቆም  ቆራጥ እና  ሀገር ወዳድ ወገናችሁን ማደራጀትና ወደ ትግል መምራት ይኖርባችኋል፡፡ እያንዳንዱ አማራም በሀወሓት ትግሬና በግበረ አበሮቹ  የተገፈፈውን ነፃነቱን ለማስመለስ የትኛውንም አይነት መሰዋትነት ለመክፈል ዝግጁ  መሆን ይኖርበታል፡፡ ልጆቻችን  በኢትዮጵያ እንደዜጋ  ተከብረውና መብታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ከፈለግን እኛ  መሰዋት ልንከፍል የግድ ነው፡፡  ማለፋችን ላይቀር ስደትንና ውርደትን ልጆቻችን አውርሰን ማለፍ የለብንም፡፡

 

ድል  ለኢትዮጵያ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s