
በኃይለሥላሴም በደርግም ኦሮሞ እንደማኝኛውም ዜጋ የራሱ ድርሻ ነበረው፡፡ ይህ የኦሮሞ ትውልድ ግን ድርሻ አልነበረኝም ይላል፡፡ ዛሬ ግን አስተውሉ አሮሞ ምንም ውስጥ የለም፡፡ ሲስተማቲካል ሙልጭ ብሎ ከኢትዮጵያ ተሳትፎ ውስጥ ወጥቷል፡፡ ኦሮሞ በንግድ ውስጥ የለም፣ በስልጣን የለም፣ በትልልቅ ተቋማት የለም፣ ድሮ በሚታወቅበት በመከላከያ ሰራዊት መሪነት ውስጥ እንኳን ባዶ እንዲሆን ነው የተደረገው፡፡ ብልጦቹን የኦሮሞ ልጆች ሲስተማቲካሊ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ተደረገ፡፡ አሮሞን ዛሬ ብታዩት ምንም የለውም፡፡ ባለሀብት ጥሩ! ባለስልጣን ጥሩ! ኦሮሞ ምንም ውስጥ የለም፡፡ ኦሮሞ ኦሮሚያ የምትባል የቅዠት አገር ውስጥ ነው የሚኖረው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ አሮሞ የለም፡፡ ይሄው ዛሬ 26 ዓመት አለፈው አሁንም አልነቃ ብሏል፡፡ ቋንቋ፣ ከተማ፣ የቦታ ሥያሜ ምናምን እያሉ ይደልሉታል፡፡ መሠረታዊ ማንነቱንና በአገሪቱ ያለውን ኢኮኖሚያዊም በሉት ማህበራዊና ፖለቲካዊ ድርሻ ግን እንዳይኖረው ተደርጎ ተጠርንፏል፡፡ ናዝሬት አዳማ፣ ደብረዘይት ቢሾፍቱ፣ ዝዋይ ባቱ፣ ተባሉ መልካም፡፡ ግን ለኦሮሞ ምን ጠቀመው; ኦሮሞ በእንደነዚህ አይነት መደለያዎች እንደሚዘወር ስለተረዱት ታሪክም እውነትም መጠበቅ አያስፈልግም ብቻ ኦሮምኛ በማድረግ ኦሮሞን አፉን መዝጋት እንደሚቻል ሰዎቹ ተማምተናዋል፡፡ አዳማ በትክክልም ታሪካዊ ሥያሜዋን እንዳገኘች አልጠራጠርም መልካም ይህ ለኦሮሞ ሳይሆን ሌላውም ይጋራዋል፡፡ ዝዋይን ባቱ ብሎ መሠየም ግን ኦሮሞን ለመደለል ከተከደበትም አካሄድ በላይ ታሪካዊ ስህተትና የሌሎችን ታሪክ የሚጋፋ ነበር፡፡ ይህ ቦታ ከጥንት ጅምሮ ከዜይ ሕዝብ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ከኦሮሞም ሕዝብ በፊት የዜይ ሕዝብ በዚህ ቦታ ይኖር ነበር፡፡ ሀይቁ በእነዚሁ በዜይ ሕዝቦች ስም ዝዋይ ተባለ ከተማው ደግሞ ከሀይቁ ሥያሜውን አገኘ፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው በወያኔና ኦሮሞን ከኢትዮጵያዊነት ቦታ ድራሹን ያጠፉት በቅዠት አገር በሚያኖሩት ነው፡፡ ኦሮሞን የከበበው ሕዝብ ሁሉ ኦሮሚያ የምትባለው አገር እውን ብትሆን ኦሮሞ ዋና ጠላታቸው እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ ለአለፉት 26 ዓመት የኦሮሞ ሕዝብ ያልተጋጨው አዋሳኝ የለም፡፡ ምክነያቱም በኦሮሞነት ሌላውን እንዲጠላ በመደረጉ ነው፡፡ እናም ዛሬ ኦሮሞ ሲባል የትኛውም ሕዝብ በበጎ አያይውም፡፡ እንደውም አማራ ከተባለው ጋር በተወሰነም ቢሆን መግባባቱ አለ፡፡
አሁን አዲስ አበባን ለኦሮሞ ጥቅም ማስከበር በሚል የተደረገው ይሄው ለዘመናት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሲቆመር የነበረው አሰራር ነው፡፡ አሮሞ በሌሎች ሕዝቦች እንዲጠላ ማድረግ የበለጠ ባዶ እንዲሆን የበለጠ እንዲምታታ ማድረግ፡፡ ኦሮሞ ከአልታገለ ወያኔ ብዙ እድሜ እንዳላት ታውቃለች፡፡ የወያኔ መጥፊያዋ ኦሮሞ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር የተባበረ ዕለት ነው፡፡ በወሳኝነት ቦታ እንዲሳተፍ አይፈለግም፡፡ ምክነያቱም በራስ መተማመን እንዳያመጣ፡፡ እንዲሁ የተወናበደ በራሱ የማይተማመን ኦሮሞ ነህ በሚል እየተደለለ እንዲኖር ነው በዋናነት እየተሰራበት ያለው፡፡ አስቂኙ የኦሮምን ጥቅም ያስጠብቃል የተባለው የአዲስ አባባ ከተማ አዋጅ ፍፁም ሕገ ወጥ ከመሆኑም በላይ ዳግም አሮሞን ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ሕብረት እንዳይኖረው የሚያደርግ፣ ግን ምንም አይነት ትቅም እንዳይኖረው የተቆለፈበት ነው፡፡ በግልፅ ግን የኦሮሞ ገበሬዎች በስፋት እንደሚፈናቀሉ ደንግጓል፡፡ አላማውም መሬቱን ከኦሮሞ ማጽዳት ነው፡፡ ልብ በሉ ዛሬ ሰዎቹ ገንዘብ ስላላቸው መሬቱን ሊገዙት ይችላሉ፡፡ ለኦሮሞ ገበሬውም በቂ ገንዘብ ሊሰጡት ይችላሉ፡፡ በዚህ ሂደት አዲስ አበባና ዙሪያዋ ከኦሮሞ የጸዳች አካባቢ ይሆናል፡፡ ቀመሩ ይህ ነው፡፡
ለኦሮሞ ወጣቶች ሥራ እንሰጣለን የሚለው ሌላው አሳዛኝ ንቀት ነው፡፡ የኦሮሞ ወጣት የሀብት ባለቤት ሳይሆን የሚሆነው ተቀጣሪ ባሪያ ነው፡፡ ሀብቱ ውስጥ መቼም እድል እንዳይኖረው ሰርተውበታል፡፡ የእነሱን ፋብሪካዎችና ድርጅቶች ለማንቀሳቀስ ኦሮሞ ያስፈልጋል፡፡ ድሮስ የጉልበት ሠራተኛ የሚሆነው ማን ነው; ይህ አሳዛኙ ነገር አንዱ ነው፡፡ በአጠቃላይ ይህ አዋጅ አሮሞን በቀጣይም ከተሳትፎ በማራቅ በራስ መተማመኑን ሁሉ በማጥፋት የተገዥነት እውነታውን አሜን ብሎ እንዲቀበል የተደረገ ነው፡፡ አዲስ አበባን የሚሟገተው ኦሮሞ መላው ኦሮሚያ የተባለውን አገሩን ራሱ እንዳጣ አያውቅም፡፡ በዚህ አዋጅ ብዙዎች ጮቤ ረግጠዋል፡፡ ይህ ይጠበቅ ነበር፡፡ ይህንንም ታስቦ ነበር አዋጁ፡፡ አዋጁ የኦሮሞን ሕዝብ ዝም ለማሰኘት ታስቦ የወጣ እንጂ ወያኔ የደረሰችውን ሕገመንግስቷ አንቀጽ49/5 የሚለው ጋር ምንም አይገናኝም፡፡ አዋጁ አዲስ አበባ በኦሮሚያ እምብርት ላይ በመሆኗ እያለ በተደጋጋሚ ይናገራል፡፡ ይህ ማሳከር ነበር፡፡ አንቀጽ ተብዬው የሚለው አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል ስለሚገኝ ነው የሚለው፡፡ መሀል ማለት አካለ ነው ማለት አደለም፡፡ ራሱን የቻለ አስተዳደርም አለው፡፡ አዲስ አበባ የራሱ መስተዳደር እንዲኖረው የሆነበት ብዙ ምክነያቶች ይዘረዝራል፡፡ አዲስ አበባ ከሥያሜዋ ጀምሮ ሕገ ምንግስት ተብዬው ያጸደቀው ነው፡፡ አሁን ፊንፊኔ ምናምን ኦሮሞን ለማስደሰት ነው፡፡ የኢስ አባባ መንገዶችና ሰፈሮች እንደአስፈላጊነቱ በኦሮምኛ ይሰየማሉ ይላል፡፡ ይህም ያው አሮሞን ለመደለል ነው፡፡ በእንደእነዚህ ያ ነገሮች እንደሚረካ እናውቃለን ብለው ስለሚያስቡ፡፡ ሲጀምር የአዲስ አበባ መንደሮች የኦሮምኛን ሥያሜያቸውን አጥፍተውም አያውቁም፡፡ አሁንም ቢሆን ፒያሳና መርካቶን እንቀይር ካልተባለ የኦሮምኛ ሥያሜዎች እንዳሉ ናቸው፡፡ ከጊንፊሌ፣ ቀበና፣ የካ፣ ቦሌ፣ ጉለሌ፣ ምናም፡፡ እንግዲህ 7ኛ አብነት ምናምን የሚባሉትን ኦሮሞ እንደሚያስበው አማራ አልሰየማቸውም፡፡ ለቡ፣ አቃቂ፣ ቃሊቲ፣ ለመሆኑ ግን አማርኛው የት ነው፡፡ ምን አልባት መገናኛ፡፡ ኮተቤም አማርኛ አደለም፡፡ መንገዶቹም አሁን ተሰይመው ያሉት በአብዛኛው በሌሎች ሕዝቦች ነው፡፡ መቼም ኦሮሞ ነፍጠኛ የሚላቸው አንዱንም መንገድ በሥማቸው አልሰየሙም፡፡ እንዲህ ነው በኦሮሞ ላይ እየተሰራ ያለው ድራማ፡፡ ኦሮሞ በዚህ ከቀጠለ በቁጥርም አናሳ እንደሚሆን ይሰማኛል፡፡ በአለፉት 26 ዓመት ከምንም ነገር ውስጥ እንዳይታይ ተደርጎ በፖለቲካ ውዥንብር ውስጥ ከሌሎች ጋር እንዲቃርን ሲደረግ ነው የኖረው፡፡ አሁንም ብዙው አልነቃም፡፡
ሰሞኑን አቶ ለማንና ቡድናቸውን የሚያወድስ ጽሁፍ ጽፌ ነበር፡፡ እርግጥ ትንሽ ማየት እንዳለብን ተናግሬም ነበር፡፡ እስከዛሬ እየመጡበት በአለው ነበር ለገመግም የሞከርኩት፡፡ በዚች በአዲስ አበባዋ አዋጅ ዋና ጮቤ ረጋጭ እንደሆኑ ሳይ ግን እስካሁንም ለካ ሕዝብን በእነሱ ቀለበት ውስጥ ለመክተት ነው የሚል ጥርጣሬ አደረብኝ፡፡ ከጥርጣሬም በላይ እነለማ የኦሮሞን ሕዝብ ለቀጣይ አመታት ለሽያጭ እንዳቀረቡት ተሰማኝ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ይህ አዋጅ ዛሬ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን አዋጁን ራሳቸው እንደሚፈልጉት አዘጋጅተው የተወሰነ በተለያዬ ሚዲያዎች ሕዝብ ምን ይላል የሚለውን ለማወቅ ሲለቁና አይ እኛ አናውቀውም ሲሉ ከርመው ያው አሁን ያወጁት በዛ መሠረት ነበር፡፡ እነ ለማ አሳምረው ያውቁ ነበር፡፡ በሕግም በሞራልም፣ በምንም ዋስትና የሌለውን አዋጅ በኦሮሞ ሕዝብ ሥም አውጀው እነሱ ዋጋ ተቀበሉበት፡፡ በዚህ አዝናለሁ፡፡ አቶ ለማን መስሎኝ መጀመሪያ ሥራዎ የታሰሩ የሕዝብ ልጆች እንዲለቀቁ ማድረግ ነው የሚል ምክርም ሞክሬ ነበር፡፡ ለነገሩ ብዙ ሌሎች የኦሮሞ ልጆችም አቶ ለማን በዚህ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡ መክረዋል፡፡ አሁን ግን ሳይ ገና የተናገሩት እንኳን ከሰው ጆሮ ገብቶ ሳይደመጥ የኦሮሞን ሕዝብ የገበያ ማቅረባቸው አሳዝኖኛል፡፡ እንደእኔ ይህን አዋጅ የአቶ ለማ ቡድን መቀበል አልነበረበትም ብቻ ሳይሆን በዚህ ወቅት ምንም አይነት ነገር በዚህ ጉዳይ ላይ ተባባሪ መሆን አልነበረበትም፡፡ ይህ 23ዓመት ሥራ ላይ ያልዋለ አዋጅ ዛሬ ሕዝቡ ፍጹም ከዚህ የተለየ ጥያቄ እየጠየቀ በአለበት ወቅት ነው ለማ የ23 ዓመት ሻጋታ ሕዝብ ትዝ የማይለውን ጉዳይ ያነሱት፡፡ እሱም የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ ለለስኩልህና አርፈህ ተቀመጥ ለማለት፡፡
በአጠቃላይ የኦሮሞ ሕዝብ ወደነበረበት ማንነቱ ከአልተመለሰ እንዲሁ ይቀጥላል፡፡ አሁን አማራውንም እንደኦሮሞው ከታሪክና ማንነት ለማምከን ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ኦሮሞን በተሳካ ሁኔታ እንዳመከኑት የተረዱት አሁን አማራውን ብሄረተኛ በሚል እያጦዙት ነው፡፡ ልብ በሉ በወያኔ የዘወር የነበረው የኦነግን እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ሲኦል ማድረግ ነበር፡፡ 26 ዓመት ሕዝቡን ከኢትዮጵያዊነቱ አመከነው፡፡ ጀግኖች አባቶቹን አስጣለው ዛሬ ወኔ የሌለውና አላቃሻ አናሳ ከሚባሉትም በታች አቅም የሌለው ሆነ፡፡ ለዘመናት እየተገደለም እየታሰረም ቢሆን አማራ የተባለው ወያኔን ሲፈታተናት ነበር፡፡ ይህም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው እምነቱ ጽኑ በመኆኑ ነው፡፡ አሁን ወያኔ ኦሮሞን እንዴት እንዳመከነቸው የሰራላትን ሥልት በአማራው ላይ በከፍተኛ ትኩረት እየሰራችበት ነው፡፡ ዛሬ አማራ የሚባለው እንደ አሸን የበዙ ድርጅቶች አሉት ሁሉም ይነታረካሉ፡፡ ብዙ ትውልድ ቤተ አማራ የተባለ የወያኔ ተላላኪ ተከታይ ሆኖ ገደል እየገባ ነው፡፡ አማራ በአማራነቱ አደለም ታሪክ ያለው፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ እንጂ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከሌለ ጉልበት፣ ወኔ፣ ኣላማ የለም፡፡ አማራ በጊዜ ከአልነቃ በኦሮሞ የሆነው መምከን እንደሚመጣበት አትጠራጠሩ፡፡ ዛሬ ኦሮሞ የሰፈረበት ምድር የሌሎች ሆኖ ቢሆን ወያኔ አዲስ አበባ ላይ አደለም ደደቢት ቦታ ባልኖራት፡፡ አማራን ነፍጠኛ ሲሉት ያጣጣሉት መስሏቸው ነበር፡፡ ግን አዎ ነፍጠኛ ነኝ እኮራለሁ በዚህ ሲል ጭራሽ ወኔና ጉልበት እንደሆነው ገብቷቸዋል፡፡ አሁን የሚያዋጣው አማራን ተበዳይ ነህ በሚል የበታችነት ስሜት እንዲኖረው ማድረግና እንደኦሮሞ ከታሪክም፣ ከወኔም ማምከን ነው፡፡ ኦሮሞም ተጨቁነሀል እየተባለ ነው የክብር ታሪኩንና ጀግኖች አባቶቹን ጥሎ ዛሬ ከምንም የሌለ መካን የሆነው፡፡ አንዴ ከታሪክና ከማንነቱ ከወጣላቸው የሚያደርጉትን እነሱ ያውቃሉ፡፡ ቤተ አማራ አማራውን ከታሪክና ከማንነት ለማምከን ኦነግ የተባለው የኦሮሞ ኮፒ በአማራ እንደሆነ ሰው ልብ ሊል ይገባዋል፡፡ ኦሮሞን ይሄው ዛሬ መላውን ኦሮሚያን ነጠቀውት አዲስ አባባንም ሰጠንህ ሲሉት እየተደሰተ ነው፡፡ ጊዜ በአገኙ ቁጥር ከቁጥሩም ያሳንሱታል፡፡ እነሱ በአዲስ አበባ ብቻ አደለም በሌላውም ዋና ዋና የኦሮሞ ግዛቶች ይስፋፋሉ፡፡
አመሰግናለሁ
ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ!
አሜን!
ሰርጸ ደስታ