መኪና አሳዳጅ ውሾች – በዳንኤል ክብረት

አንድ የአፍሪካ የሽምቅ ውጊያ መሪ ለብዙ ዓመታት በሽምቅ ውጊያ ታግሎ ነባሩን መንግሥት ካስወገደ በኋላ ለ12 ዓመታት ሀገሪቱን መራ። ሕዝቡ በሽምቅ ተዋጊነቱ ጊዜ የወደደውን ያህል በመንግሥትነቱ ጊዜ ሊወደው አልቻለም። ሲመጣ በጭብጨባና በሆታ ተቀበለው፣ ሲውል ሲያድር እያዘነበት ሄደ፣ ሲቆይ ተቀየመው፣ ሲሰነብት ተቃወመው፣ ሲከርምም ዐመፀበትና ከሥልጣኑ አባረረው። “ከሽምቅ ውጊያ በኋላ” After “Gorilla fighting” የተሰኘውን መጽሐፉን ሲጽፍ ከሀገሩ ተባርሮ በሰው ሀገር ያገኘው ናይጄርያዊው ደራሲ ቶማስ ኙዌንጌ ስሙን እንደማይጠቅስ ቃል ገብቶለት አነጋግሮት ነበር። የሽምቅ ውጊያ መሪው ‘ሆ’ ብሎ በእልልታ የተቀበለው ሕዝብ ‹ሂድ› ብሎ በቁጣ ለምን እንዳባረረው ሲገልጥለት እንዲህ ነበር ያለው።

“የነበረውን መንግሥት ጥለን ሥልጣን ለማግኘት ታግለናል። ሕዝብን ከጭቆና ነጻ ለማውጣት፣ ፍትሕና እኩልነትንም ለማስከበር ታግለናል። አሁን ሳስበው የተዘጋጀነው እስከ ቤተ መንግሥቱ ላለው ጉዞ ነበር። ቤተ መንግሥት ስንገባ ምን ማድረግ እንዳለብን በቅጡ አላሰብንበትም። የነበረውን ስለ ማስወገድ እንጂ የተሻለ እንዴት እንደምናመጣ በደንብ አልሠራንም። ቤተ መንግሥቱን ከውጭ ስታየውና ውስጡ ሆነህ ስትኖርበት ይለያያል። ሥልጠኑን ለማግኘት ስትታገልና ስታገኘው ልዩነት አለው። መሬት ላይ ሆነህ ተራራውን ስታየውና ተራራው ላይ ሆነህ ተራራውን ስታየው እንደሚለያየው ዓይነት። ነባሮቹን ችግሮች አስወግደናል፤ ግን በአዳዲስ ችግሮች ነው የቀየርናቸው፤ ነባሮቹን ጦርነቶች አስቁመናል፤ ግን በአዳዲስ ጦርነቶች ነው የተካናቸው፣ ነባሮቹን ቅሬታዎች ፈትተናል፤ ግን በአዳዲስ ቅሬታዎች ነው ቦታቸውን ያስያዝነው› ነበር ያለው።

ማግባት የሚመኙ፤ ግን ካገቡ በኋላ ምን እንደሚያደርጉ ያልተዘጋጁ፤ ገንዘብ የሚፈልጉ፤ ገንዘቡን ቢያገኙ ምን እንደሚሠሩበት በቅጡ ያላቀዱ፤ ውጭ ሀገር ለመሄድ የሚኳትኑ፤ ሄደው ምን እንደሚሆኑ ያላሰቡ፤ ተምሮ መጨረስ እንጂ ጨርሰው ምን እንደሚያደርጉ የተሰላ ዕቅድ የሌላቸው፤ ባለ ሀብት መሆን እንጂ ሀብቱን እንዴት እንደሚይዙት ዕውቀቱም ዝግጅቱም የሌላቸው፤ ሥልጣን ላይ መውጣትን እንጂ ሲወጡ ለሚሆነው ነገር የሠለጠ ሐሳብ ያልቋጠሩ፤ ፌስ ቡክ መክፈት እንጂ ከፍተው ምን እንደሚያደርጉ ባለማቀዳቸው ሺ ጊዜ ፕሮፋይል ፎቶ የሚቀያይሩ፤ የሚዲያ ዕድል ለማግኘት እንጂ ሲያገኙ እንዴት ዘልቀውና ልቀው መቆየት እንደሚችሉ ያላሰላሰሉ – “መኪና አሳዳጅ ውሾች” ተብለው ይጠራሉ።

ማግባት አንድ ነገር ነው። በትዳር መዝለቅ ደግሞ ሌላ። ሀብት ማግኘት አንድ ነገር ነው፤ ትውልድ የሚሻገር ተቋም መመሥረት ደግሞ ሌላ። ታዋቂነትን ማግኘት አንድ ነገር ነው። እንደተወደዱና እንደተከበሩ መኖር ደግሞ ሌላ። ወደ ኪነ ጥበቡ አምባ መዝለቅ አንድ ነገር ነው። እንደተካኑና እንደተደነቁ መኖር ደግሞ ሌላ። የተሳለ፣ የበሰለ፤ የደቀቀ፣ የተሰለቀ ዕቅድ የሚያስፈልገው ከተራራው ጫፍ፣ ከሀብቱ ማማ ማዶ፣ ከሥልጣኑ እርከን ባሻገር፣ ከታዋቂነቱ ክብር ወዲያ፣ ከትዳሩ ጎጆ አልፎ፣ ከትምህርቱ ምረቃ በኋላ ያለውን መንገድ አስልቶ፤ ትርፍና ኪሣራውንም ገምቶ ለመነሣት እንዲቻል ነው።
በአንድ ወቅት “መቶ ሺ ብር ብታገኝ ምን ታደርገዋለህ?” ተብሎ የተጠየቀ ሰው “መጀመሪያ ስጠኝና ከዚያ በኋላ እነግሃለሁ” አለ ተብሎ ተቀልዷል። ካሳቀም ሊያስቅ የሚገባው የሰውየው የዕቅድ አስተሳሰብ ነው። ከበደ ሚካኤል በጻፉት ተረትና ምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ የምናገኘው ዘፋኙ ጫማ ሰፊ የገጠመውኮ ይሄ ነው። ከጫማ ቤቱ በላይ እየኖረ የጫማ ሰፊውን ያህል ደስታን ያላገኘው ባለጠጋ የዚህን ጫማ ሰፊ ዘፈን እየሰማ ይዝናና ነበር። በነጻ መዝናናቱ ቀማኛነት ስለመሰለው ጫማ ሰፊውን ጠራና አንድ ከረጢት ወርቅ ሰጠው።

ጫማ ሰፊው አመስግኖ ወጣና ቤቱ ገባ። የመጀመሪያው ጥያቄ ‹የት ላስቀምጠው› የሚል ነበር። ጫማ ሰፊው አሮጌ ጫማ ለማስቀመጥ እንጂ ወርቅ ለማስቀመጥ የሚችል ነገር የለውም። ሲሠራ የዕለት ጉርሱን የዓመት ልብሱን ለማግኘት እንጂ ሀብታም ለመሆንና ወርቅ ለመሰብሰብ አላሰበም። እዚያም እድርሳለሁ የሚል ምኞትም አልነበረውም። ለእርሱ ወርቁ ድንገቴ የሆነበትም ለዚህ ነው። ድንገቴ ሀብት የሚያገኙ ሰዎች የሚደርስባቸው የአእምሮ ድቀት ይህን የመሰለ ነው። አንዳንዶቹም ወጣ ወጣና እንደ ሸምበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ የሆኑት ለዚያ ነው። “እንዴት እንደመጣ የማታውቀውን እንዴት እንደሚሄሄ አታውቀውም” ይባላል።

ጫማ ሰፊ ዕንቅልፍ አጥቶ ነው ያደረው። ኮሽ ባለ ቁጥር “ሌባ ወርቅ ማግኘቴን ሰምቶ ሊወስድብኝ መጣ› እያለ። ለዕለት ጉርሱ ብቻ የሚሠራው ጫማ ሰፊ ወርቅ የትና እንዴት እንደሚቀመጥ አያውቅም። እርሱ ወርቅ ለማግኘት አልተዘጋጀም። ሚሠራው ለማግኘት ነው። ሲያገኝ ምን እንደሚያደርግ ግን ያሰበው ነገር የለም። “ስጠኝና ምን እንደምሠራ እነግርሃለሁ” እንዳለው ሰውዬ።
ወላጆቻቸውን ወይም ታላላቆቻቸውን አስቸግረው ሱቅ የሚከፍቱ፣ ታክሲ የሚይዙ፣ ሆቴል የሚጀምሩ፣ ወጣቶች “ብቻ አንድ ነገር ይከፈትልኝ፣ ውዬ የምገባበት ላግኝ፣ ይኼው እገሌ ተከፍቶለትና ተገዝቶለት ዛሬ ማን ይደረስበታል” በሚል ስሜት ይጀምሩታል እንጂ ያሰብኩትን ባገኘው ከዚያ እንዴት እቀጥለዋለሁ? ብለው ብዙም አይጨነቁም። የመጀመሪያው ቀን የሞላው ሱቅ እንዲሁ የሚኖር ይመስላቸዋል። መኪና በራሱ ባትሪና ሞተር መንቀሳቀስ ካልቻለ ስለገፉት ብቻ አይሄድም። የመገፋቱ ዓላማ መጀመሪያ ባትሪና ሞተሩ እንዲሠሩ፤ ሠርተውም ራሳቸውን ችለው እንዲሽከረከሩ ነው። እንግፋው- እንንዳው አይሆንም።
የወላጆቻቸውን ሀብት ስለማግኘት ብቻ ሲያስቡ የኖሩ ልጆች ናቸው ወላጆቻቸው ዐርፈው ሀብታቸውን ሲወርሱ ማስተዳደሩ አቅቷቸው አንዴ በሐራጅ፣ አንዴ በዕዳ ያስሸጡት። ወላጆቻቸው የለፉበትን እንጂ ያለፉበትን አልወረሱም። “ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምር፣ ሲይዙት ያደናግር” የሚለው ደርሶባቸዋል። እንደ ውሻው መኪናውን ለማግኘት ደከሙ እንጂ መኪናውን ቢያገኙም እንደሚያደርጉት አስበውት አያውቁም።

አንድ የሚጮኽ ውሻ የነበረው ገበሬ ነበር አሉ። ውሻው መንገድ ዳር ይሆንና መኪና ባለፈ ቁጥር መኪናውን ለመያዝ እየጮኸ ይከተለዋል። የውሻውን የዘወትር ተግባር ያየ ጎረቤቱ ገበሬውን ጠየቀው። “ይኼ ውሻህ ምን ሞኝ ቢሆን ነው የሚበርር መኪና ለመያዝ እንዲህ መከራውን የሚያየው? ለመሆኑ አንድ መኪና እንኳን መያዝ የሚችል ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀው። የውሻው ባለቤትም ሳቅ አለና “እኔ የሚገርመኝ እርሱ አይደለም። በዚሁ ከቀጠለ አንድ ቀን አንዱን መኪና ነክሶ ሊይዘው ይችል ይሆናል። እኔን የሚገርመኝ ሌላ ነው› አለው። ጎረቤቱም ከዚህ የባሰ ምን ይገርምሃል?” ሲል ጠየቀው። የውሻው ባለቤትም “እኔን የሚገርመኝ እንደምንም ብሎ መኪናውን አንድ ቀን ቢያገኘው ምን ሊያደርገው እንደሚችል አለማሰቡ ነው” አለው ይባላል።

የመኪና አሳዳጅ ውሾች ዋናው ጠባይ ይኼ ነው። ቢያገኙት ምን እንደሚያደርጉት በቅጥ ያላሰቡበትን ዓላማ ይከተላሉ። ከዚያስ? ለሚለው መልስ የላቸውም። የሚያደርጉት ሌላው ስላደረገው፣ ብዙ ስለተወራለት፣ ሰው ሲያደርገው ስላዩት፣ ወይም ማስታወቂያዎቹ ስለጮኹለት ይሆናል። መኪና ስለመያዝ እንጂ ወዴት አቅጣጫ እንደሚነዱት አይዘጋጁም። ኮሌጅ ለመግባት እንጂ በኮሌጅ ለመዝለቅ፣ ዘልቀውም ኮሌጅ ለመበጠስ አይዘጋጁም። ውጭ ሀገር ለመሄድ እንጂ እዚያ ለሚገጥማቸው ውጣ ውረድ በውጭም በውስጥም አላቀዱበትም። ፓርቲ ለመመሥረት እንጂ፣ በፓርቲ ውስጥ ለመዝለቅ የወጠኑት ስልት የለም፤ ማኅበር ለማቋቋም እንጂ የማኅበርን ማዕበልና ንውጥውጥ (ዳይናሚክስ) ችለውና አሸንፈው ለመዝለቅ የተለሙት ትልም የለም። ዕቅድ ከምኞት የሚለየው በሦስት ነገር ነው። ወደምታስበው ዓላማ የሚወስድህን ትክክለኛ መንገድ አጥርተህ ካወቅከው፤ በመንገዱ ለሚገጥምህ ደስታና ኀዘን እኩል ከተዘጋጀህና ዓላማህ ላይ ስትደርስ በዓላማህ ለመዝለቅ የሚያስችል በቂ ስልት ካለህ።

እንሂድ ተብሎ ከቤት አይወጣም። የትና እንዴት እንደሚኬድ፤ ሲደረስም ምን አንደሚደረግ ሳይታወቅ። ሊቃውንት “በሕይወት ውስጥ 10 በመቶው ከማግኘት፣ 90 በመቶው ግን ከአያያዝ ይሟላል› ይላሉ። ገንዘብ በሎተሪም ይገኛል፣ ወድቆም ይገኛል፣ በውርስም ይገኛል፣ በስጦታም ይገኛል፣ ተዘርፎም ይገኛል። አያያዝ ግን በስጦታም፣ በውርስም፣ በስርቆትም፣ በሎተሪም አይገኝም።
ካገኘኽው በኋላ ምን እንደምታደርገው፣ እንዴት እንደምትይዘውና የት እንደምትወስደው የማታውቀውን ነገር ‹ለማጣት አግኝተኸዋል ማለት ነው። ልክ እንደ መኪና አሳዳጁ ውሻ።

ጊዜውን የሚጠብቀው የስኳር ፖለቲካ – በ‘ስኳር’ – በፋኑኤል ክንፉ (ሰንደቅ)

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ በዘረጋችው መጠነ ሰፊ የስኳር ልማት ዙሪያ መንግስታቸው ትምህርት ማግኘቱን ከመግለጽ ውጪ፣ አንድም ተጠያቂ አካል ማቅረብ አልቻሉም። ለሁሉም ጊዜ አለው እንደሚባለው፣ አንድ ቀን በዚህ ስኳር ልማት ዙሪያ ኃላፊነት የሚወስዱ በሕግ የሚጠየቁ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ኖራቸው አይቀሬ እንደሆነ የአደባባይ እውነት ነው።

በዚህ ጽሁፍ ካለፈው ሳምንት የከሰም ጉብኝታችን የቀረውን ክፍል ይዘን ቀርበናል። በተለይ የከስም ስኳር ፋብሪካ እና የእርሻው ዘርፍ ምን እንደሚመስል የሚያካፍሉን፣ ሁለት በስኳር ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ኃላፊዎችን አነጋግረናል።

ከእነዚህም መካከል የከሰም የፋብሪካ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ዋበላ አንዱ ናቸው። አቶ ታደሰ ከሃያ ስድስት ዓመት በላይ በስኳር ኢንዱስትሪው ውስጥ አገልግለዋል። በወንጂ እና በአርጆ ዴዴሳ ስኳር ፋብሪካዎች ሰርተዋል። ሌላው በከሰም የእርሻ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ምሩጽ ወልዳይ ናቸው። አቶ ምሩጽ በስኳር ኢንዱስትሪ ውስጥ ለሰላሳ አራት አመት አገልግለዋል። ቀደም ብለው በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ አሁን ደግሞ በከሰም ስኳር ፋብሪካ እያገለገሉ ይገኛሉ።

እነዚህ ከፍተኛ የስኳር ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች መንግስት በዘረጋው የስኳር ልማት ስትራቴጂ ላይ ከልምዳቸው በመነሳት ያካፈሉን ቁምነገር አለ፤ ሰሚ ካለ ይስማ። በተጨማሪም በወቅታዊ የከሰም ስኳር ፋብሪካ የሥራ ክንውን ዙሪያ አነጋግረናቸዋል። መልካም ንባብ።

“የስኳር ልማቱ ላይ ስትራቴጂክ የሆነ

የአስተሳሰብ ክፍተት አለበት”

አቶ ታደሰ ዋበላ

የፋብሪካ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ

ሰንደቅ፡- ፋብሪካው እስካሁን በፕሮጀክት ደረጃ ነው ያለው ወይንስ ፋብሪካውን ሙሉ ለሙሉ ተርክባችሁታል?

አቶ ታደሰ ዋበላ፡- አዎ በፕሮጀክት ደረጃ ነው። በቅርቡ በአፕሪል 28 እስከ 30 ባሉት ቀናት “performance guaranty” test አድርገናል። ይህ ማለት ፋብሪካው 6ሺ ቶን አገዳ ቢቀርብለት በሰባ ሁለት ሰዓት ውስጥ ያለማቋረጥ ይፈጫል? የሚለውን ለመፈተሽ ነው። አገዳ አከማችተን ባደረግነው ፍተሻ ፋብሪካው በሰባ ሁለት ሰዓት ውስጥ 6ሺ አንድ መቶ አገዳ ፈጭቷል። ፋብሪካው በጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው።

የፋብሪካው የአዋጭነት ጥናት እንደሚያሳየው፣ በአገዳው ውስጥ መገኘት ያለባቸው የንጥረ ነገሮች መጠን በመቶኛ ሲያስቀምጥ፤ ፋይበር 13 ነጥብ 5፣ ሱክሮስ ከ13 በላይ እና ባዕድ ነገሮች 3 በመቶ የሆነ የሚል ነው። ከአሚባራ የሚመጣው አገዳ ግን በመቶኛ ሲገለፅ፤ ፋይበር 19፣ ሱክሮስ ከ10 በታች፣ ባዕድ ነገሮች ከ3 እስከ 7 በመቶኛ ናቸው። ባዕድ ነገሮች በበዙ ቁጥር ስኳር እንዳይወጣ ከማድረጋቸውም በላይ ስኳሩን ይዘው ወደ ሞላስስ ይዘልቃሉ። ከባዕድ ነገሮች የፀዳ አገዳ ሲሆን ብቻ ነው ጥሩ ስኳር ማግኘት የሚቻለው። ስለዚህም በእርሻው ላይ መስራት ይጠበቅብናል።

ሰንደቅ፡- የፋብሪካው ብቃት (Efficiency) እንዴት ነው?

አቶ ታደሰ ዋበላ፡-አጠቃላይ የፋብሪካው የሰዓት ኤፊሸንሲ 80 በመቶ ይሆናል ተብሎ ተቀምጧል። ይህ ማለት በቀን 4ሺ 800 ቶን አገዳ ፋብሪካው መፍጨት ይጠበቅበታል። ዳሩ ግን ከአሚባራ በቀን 4ሺ 800 አገዳ ማምጣት ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም። አሁን ባለው ደረጃ በአብዛኛው የሚመጣው 3ሺ 700 ቶን አገዳ ነው። ለዚህ ምክንያቶቹ የመንገዱ ርቀትና መንገዱ ያልተስተካከለ መሆን፣ የአሚባራ ማሳ ለጥጥ የተዘጋጀ በመሆኑ አገዳውን ከማሳ ማንሳት አመቺ አይደለም። አገዳው በዶዘር እየተገፋ ለመጫን ስለሚሰናዳ ዶዘሩ በርካታ ባዕድ የሆኑ ነገሮች አብሮ ከአገዳው ጋር ገፍቶ ያመጣል። ይህም በመሆኑ ብዙ ባዕድ ነገሮች ፋብሪካው እያጣራ ያራግፋቸዋል። በፋብሪካ የገባው የሱክሮስ መጠን እና የሚወጣው የስኳር መጠን በጣም የሚገርም ነው።  ፋብሪካው ዘመናዊ (Distributed control system) በመሆኑ 7 ነጥብ 8 ሱክሮስ እየገባ 7 አካባቢ ስኳር እየወጣ ነው።

ባለፈው አመት የፋብሪካው እቅድ ሲያዝ ለፋብሪካው የሚቀርበው የሱክሮስ መጠኑ የተገመተው 10 ነጥብ 38 በመቶ ሲሆን እየቀረበ ያለው የአገዳው የሱኩሮስ መጠን ይዘት 7 እና ከዚያ በታች በመቶኛ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት፤ ከአሚባራ የሚመጣው አገዳ ዕድሜው ከ32 ወር በላይ በመሆኑ እርጅና ተጭኖታል። አገዳ ለምርት መድረስ ያለበት ግን ከ14 እስከ 16 ወር ጊዜ ውስጥ ነው። ይህ ማለት ከአሚባራ የሚመጣው አገዳ ስኳሩን ጨርሶ ወይም ለራሱ ስኳሩን ተጠቅሞት ነው። እንደዚህ እድሜው ከፍ ያለ አገዳ ለቀድሞዎቹ ለወንጂ እና ሸዋ ፋብሪካዎች ቀርቦ ቢሆን፣ አንድም ስኳር ማግኘት አይቻልም። በዕቅድ ደረጃ ከአረጀ አገዳ የተጠበቀውም የስኳር መጠን ስህተት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ስለዚህም ይህ መደገም የለበትም። መሬት ላይ ባለው ነገር ማቀድ እንደሚገባን አሳይቶን ያለፈ የምርት ዘመን ነው ማለት ይቻላል።

ሰንደቅ፡- የፋብሪካው አቅም እና የአገዳውን አቅርቦት እንዴት ይገልፁታል?

አቶ ታደሰ ዋበላ፡- በመጀመሪያው ምዕራፍ ማለትም አሁን ባለበት ደረጃ በቀን 6ሺ ቶን አገዳ ፈጭቶ ስድስት ሺ ኩንታል ያመርታል ተብሎ የተመሰረተ ፋብሪካ ነው። ሆኖም በተደረገው ማስፋፊያ እና በተገጠሙለት የፋብሪካው ክፍሎች ወደ አስር ሺ ኩንታል የማምረት አቅም ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህም ሲባል የፋብሪካው cane handling, preparation, milling, evaporation and clarification ክፍሎቹ በቀን አስር ሺ ኩንታል ስኳር ፋብሪካው እንዲያመርት ተደርገው የተገመጠሙ ናቸው። ትንሽ መጨመር ከሚያስፈልጋቸው የፋብሪካው ክፍሎች መካከል pumps, pipe, vacuum pan, center fugal ናቸው።

ፋብሪካው በዚህ ደረጃ የተዘጋጀ ቢሆንም አስር ሺ ቶን አገዳ በቀን ለመፍጨት በሚያስችል ደረጃ የተዘጋጀ የአገዳ ምርት የለም። የፋብሪካው የአዋጭነት ጥናት እንደሚያሳየው ፋብሪካው አስር ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም እንዲኖረው የተደረገው ሃያ ሺ ሔክታር መሬት በከሰም ዙሪያ እናለማለን ከሚል ታሳቢ ነበር። አሁን ላይ በፋብሪካው ዙሪያ የለማው አገዳ 3ሺ ሔክታር ነው። እንዲሁም፤ በአሚባራ 6ሺ ሔክታር የለማ መሬት አለ። በድምር 9 ሺ ሔክታር አገዳ ነው ያለው።

በቀን 6ሺ ቶን ለሚፈጭ ፋብሪካ በ9ሺ ሔክታር ላይ የለማ አገዳ በቂ ምርት አይደለም። ምክንያቱም በስሌቱ መሰረት ከሁለት ሔክታር የአገዳ ማሳ የሚገኘው አንድ ቶን አገዳ በመሆኑ ነው። 6ሺ ቶን አገዳ ለሚፈጭ ፋብሪካ በትንሹ 12 ሺ ሔክታር የአገዳ ማሳ ያስፈልገዋል። ይህም የሚሆነው ሞቃታማ ቦታ ለሚተከሉ ፋብሪካዎች ብቻ ሲሆን፤ ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ባለባቸው ቦታዎች የሚተከሉት ፋብሪካዎች 6ሺ ቶን አገዳ ለመፍጨት 15ሺ ሔክታር የለማ አገዳ ያስፈልጋቸዋል።

ሰንደቅ፡- በቀጣይ ዓመት የአገዳው አቅርቦት እንዴት ነው የሚሆነው? የአገዳ ዝርያዎች ቢለያዩም ከ13 እስከ 18 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ በአማካኝ እንደሚደርሱ ማጣቀሻዎች ያሳያሉ።

አቶ ታደሰ ዋበላ፡- በዚህ አካባቢ ከ14 እስከ 16 ወራት ባለው ጊዜያት አገዳ እንደሚደርስ ሰምቻለሁ። የኬን ሳይክሉን መመልከት አስፈላጊ ነው። ለምሳል ዛሬ የተቆረጠ አገዳ ዳግም የሚቆረጠው ከ12 ወር በኋላ ነው፤ በዚሁ መሰረት የቆረጣውን ሁኔታ መከለስ ይገባል። ዋናው አማራጭ ግን በከሰም ዙሪያ አገዳ መትከል ነው። ፕሮጀክቱም አዋጪ የሚሆነው በከሰም ዙሪያ አገዳ ከተተከለ ብቻ ነው።

ሰንደቅ፡- የአንድ ኪሎ ግራም ስኳር የማምረቻ ወጪያችሁ ስንት ነው?

አቶ ታደሰ ዋበላ፡- አዲስ ፋብሪካ ነው። ትክክለኛው ወጪ መሰራት አለበት። performance guaranty test እስከምናካሂድ ድረስ ፋብሪካው በቻይናዎች ይዞታ ውስጥ ነበር። አሁን ኦፕሬሽኑ ወደ እኛ ይዞታ የገባ በመሆኑ ወጪን መስራት እንችላለን። የቀሩ ሥራዎችን ደግሞ በኮንትራት ውል ቻይናዎቹ እንዲጨርሱ እየተደረገ ነው። ያልተሞከሩ የፋብሪካው ክፍሎች መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም። ከእነሱ መካከል የቆሻሻ ማጣሪያ ፕላንት፣ የውሃ ማጣሪያው ሲስተም፣ ኃይል ከሚያመነጩ ተርባይኖች መካከል አንዱ አልተሞከረም። እነዚህን ቻይኖቹ በኮንትራት ውል እየሰሩ ይገኛሉ።

ሌላው ሃያ ስድስት ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት እንችላለን። ከዚህ ውስጥ 6ሺ ቶን አገዳ ለመፍጨት አስራ አንድ ሜጋ ዋት ብቻ ነው የምንጠቀመው። ትርፍ ከ10 ሜጋ ዋት በላይ አለን። ይህንን ትርፍ ኃይል ከብሔራዊ ኃይል ማሰራጫ መስመር ጋር ለማያያዝ ሰብስቴሽን መትከል ይቀራል።

ሰንደቅ፡- ስኳር ማምረት እድሜ ጠገብ ሳይንስ ቢሆንም፣ ስኳር ኮርፖሬሽን አስር ፋብሪካ በአንድ ጊዜ ለመስራት አቅዶ አንዱን እንኳን በቅጡ ማጠናቀቅ አልቻለም። እርስዎ ከሃያ አመት በላይ በስኳር ኢንዱስትሪ ውስጥ ካካበቱት ልምድ አንፃር፣ ለስኳር ልማቱ ውድቀት መሰረታዊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ምን ታዝበዋል? ምንስ ይመክራሉ?

አቶ ታደሰ ዋበላ፡- እንዳልከው ለረጅም ዓመታት በስኳር ፋብሪካ ሰርቻለሁ። የተፈጠሩት ችግሮችን ለመለየት ከደቾች (ኔዘርላንድ) ጀምሮ እንዴት የስኳር ልማት እያደገ እንደመጣ መመልከቱ ተገቢ ይሆናል። በ1953 በወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሲመሰረት በአነስተኛ መጠን ነው የተጀመረው። የአገዳ እርሻ በአክሲዮን ደረጃ በዚያ ዘመን ይሸጡ ነበር። ምክንያቱም ሰው እንደራሱ ቆጥሮ እንዲያለማው በማሰብ ነው። በሒደትም የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ውጤታማ ሆነ። ትርፋማም እየሆነ ሄደ። በተገኘው ትርፍ ግን ወዲያው ፋብሪካ አልተተከለም። ውጤታማነቱ በደንብ ሲረጋገጥ ከስምንት አመታት በኋላ በሸዋ ሌላ ተጨማሪ የስኳር ፋብሪካ ተከፈተ። ስያሜውም ወንጂ ሸዋ ፋብሪካ የሚል መጠሪያም ተሰጣቸው።

ሁለቱ ፋብሪካዎች በቀን በድምር 3ሺ ቶን አገዳ እየፈጩ በዓመት 700ሺ ኩንታል ስኳር ያመርቱ ነበር። ድርጅቱም አትራፊ ሆነ፣ ሠራተኞችም ተጠቃሚ ነበሩ። ሕብረተሰቡንም ተጠቃሚ አደረጉ። ከወንጂ ሸዋ ፋብሪካ ባገኙት ትርፍ ደግሞ መተሐራ ስኳር ፋብሪካን መሰረቱ። መተሐራም የተከፈተው ከስምንት አመት በኋላ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ በሠራተኞች ዘንድ ልምድ ክህሎት እየዳበረ መጥቷል። ወጪያቸውም ኢኮኖሚካል ነበር። ደረጃ በደረጃ በስኳር ልማት ከፍተኛ ልምድና እውቀት በሀገራችን ተገኝቷል። ከሃያ ሰባት አመታት በኋላም ቢሆን በፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ለመትከል ተችሏል።

አሁን በያዝነው አካሄድ ግን የስኳር ፕሮጀክቶች በዝተው፣ አምራች መሆን የቻሉት በጣም ትንሽ ናቸው። አስር የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በአንድ ጊዜ ውጤታማ ለማድረግ የሰው ኃይል የሚጠይቅ ነው። በፕሮጀክቱ ላይ ለተሰማራው የሰው ኃይል በራሱ የደሞዝ ክፍያ በአንድ ጊዜ መፈጸም ከባድ ወጪ ነው። በስኳር ልማቱ ላይ ስትራቴጂክ የሆነው አስተሳሰብ ክፍተት ያለበት ነው። ምክንያቱም አስር ስኳር ፋብሪካ ለመትከል በአንድ ጊዜ ከማቀድ፣ ሁለት ስኳር ፋብሪካዎችን ለመትከል ቅድሚያ ቢሰጥ ኖሮ ዛሬ ላይ የተደረሰበት ሁኔታ ላይ አንገኝም ነበር። ሁለት ፋብሪካዎችን ከተከልን በኋላ ከእነሱ የሚገኙ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች በመነሳት እንዲሁም ወደ ምርት ገብተው አትራፊ መሆናቸውን አረጋግጠን፤ ወደ ተጨማሪ ሁለት ፋብሪካዎች ተከላ ተሰማርተን ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ያጋጠሙን ችግሮች ባልተከሰቱ ነበር። በተጠና ሁኔታ ወደሥራ ገብተን ቢሆን፤ የማምረቻ ወጪያችን ይቀንሳል። እንደሀገር ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆን በቻልን ነበር። አሁንም የረፈደ ነገር የለም። በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ለመስጠት መስራት ይጠበቅብናል።¾

“ከግድቡ በተያያዘ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚያሳውቁ መሳሪዎች በሲስተም ደረጃ ተጠናቀው ወደ መስመር አልገቡም”

አቶ ምሩጽ ወልዳይ

የእርሻ ዘርፍ ሥራአስኪያጅ

 

ሰንደቅ፡- የከሰም ስኳር ፋብሪካ ዘር አገዳ ተከላ የተጀመረው መቼ ነው? የአገዳ አቅርቦቱ ክፍተት እንዴት ሊከሰት ቻለ?

አቶ ምሩጽ ወልዳይ፡- ከሰም አካባቢ ያለውን መሬት በማልማት፣ ለመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ተጨማሪ የአገዳ አቅርቦት ለማዘጋጀት ነበር የመጀመሪያው ዕቅድ። የከሰም ግድብ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እየተገነባም ነበር። የዘር አገዳም ተከላም በወቅቱ በከሰም ጀምረን እያለ መንግስት የአቧራ መልካ እርሻ ልማትን ተረክበን አገዳ እንድናለማ ፈቃድ ሰጠ። ብዙም ሳይቆይ አዲስ መመሪያ ከመንግስት ተላለፈ። ይኸውም፣ በሁሉም የሀገሪቷ ክፍል የስኳር ልማት እንዲዘረጋ በመወሰኑ፣ ከሰም ራሱን ችሎ የስኳር ፋብሪካ እንዲሆን መወሰኑ ተገለፀልን። በተያዘው ዕቅድ መሠረት 6ሺ ቶን በቀን ለመፍጨት 12ሺ ሔክታር ውሃ ገብ መሬት ለማልማት ነበር።

ወደስራ ለመግባት ሁሉ ነገር ከተጠናቀቀ በኋላ፣ በከሰም ግድብ ፍልውሃ በመገኘቱ ፕሮጀክቱ ለረጅም ጊዜ ተጓተተ። በወቅቱ ፍል ውሃውን ለመከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ አልነበረም። አንድ የቻይና ኩባንያ ተቀጥሮ ሥራው ረጅም ጊዜ ወስዷል። ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላም የፋብሪካው የአዋጪነት ጥናት እንደገና ተከለሰ። የተሰጠው ምክንያት የፋብሪካውን አቅም ከፍ ካልተደረገ በስተቀር አሁን በተቀመጠው የፋብሪካው አቅም አዋጪ ሊሆን አይችልም ተባለ። በቀን የሚመረተው የስኳር መጠንም ወደ 10ሺ ከፍ እንዲል እና የአገዳ ማሳው ልማትም ወደ 20ሺ ሔክታር እንዲያድግ ተወሰነ።

ሥራው በተጀመረ መሐከል ላይ ሜቴክ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደረገ። የፋብሪካ ተከላውን በተመለከተ መሰረት ቆፍረው ነበር። ለረጅም ጊዜ በሜቴክ እጅ ከቆየ በኋላ መጀመሪያ ውል አስረነው ከነበረው የቻይናው ኮምፕላንት ኩባንያ ጋር፣ አዲስ ውል አስረን ወደ ሥራ ተገባ። ሜቴክም ከሥራው ወጣ። ኮፕላንት ኩባንያ በአጭር ጊዜ አፋጥነው ፋብሪካውን ጨርሰዋል። ስለዚህ ለአጠቃላይ ፕሮጀክቱ መዘግየት በዋናነት ከግድቡ ጋር በተያያዘ ነው። ከውሃ ኮንስትራክሽ እና ከዲዛይንና ቁጥጥር የመንግስት መስሪያቤቶች ጋር ነበር አብረን ሥንሰራ የነበረው።

ሰንደቅ፡- ለምንድን ነው ይህን ያህል ጊዜ ፕሮጀክቱ ሳይጠናቀቅ የቀረው? አፈፃጸሙ በጣም አናሳ በመሆኑ የለማው መሬት 3ሺ ሔክታር ብቻ የሚጠጋ ነው።

አቶ ምሩጽ ወልዳይ፡- ፋብሪካው ቢዘገይም ደርሷል። የፋብሪካው አቅም እና የአገዳ አቅርቦት በጣም ሰፊ ክፍተት ነው ያለው። ያለውን ክፍተት ለመሸፈን የተደረጉ ጥረቶች አሉ። ከአሚባራ እርሻ አገዳ ባለሃብቶች አልምተው እንዲያቀርቡ ተደርጓል። አሁንም ግን ክፍተት አለ። ዋናው ችግር ግን ከመሬት አቅርቦት እና ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ጋር ተያይዞ የመጣ ችግር ነው። አሁንም መፍትሄ ያላገኘ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ በዚህ ዓመት 1ሺ 500 ሔክታር መሬት ለማልማት አቅደን የነበረ ቢሆንም፣ የመሬት አቅርቦት ግን የለም። የውሃና መስኖ ኢነርጂ መስሪያቤትም ጥሎ ወጥቷል።

ሰንደቅ፡- ውሃ ገብ መሬት የማቅረብ ኃላፊነቱ አሁን ለማን ተሰጥቶ ነው ያለው

አቶ ምሩጽ ወልዳይ፡- አሁን ያለው ሁኔታ ስኳር ኮርፖሬሽን ተረክቦ በራሱ ኃላፊነት እንዲሰራ ነው ያለው አቅጣጫ።

ሰንደቅ፡- በግድቡ በመዘግየቱ ፕሮጀክቱ እንደዘገየ ገልጸውልኛል። አሁንም ግን ግድቡ ከፍተኛ መጠን ውሃ እያፈሰሰ ነው። ቀጣይ የሚገጥማችሁ ችግር አይኖርም?

አቶ ምሩጽ ወልዳይ፡- ግድቡን በተመለከተ ዲዛይኑ ኳሊቲው እንዲሁም ቀሪ ሥራዎቹ ያልተጠናቀቁ አሉ። ኤልክትሮ ሜካኒካል ሲስተሙም ወደሥራ አልገባም። ውሃ መጨመር መቀነስ ብትፈልግ መቆጣጠር አትችልም። አካባቢው የእሳተ ጎሞራ ሲነሳበት የነበረ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ የቀበርናቸው ፊዚዮሜትሪክ መቆጣጠሪያዎች አሉ። እነዚህ ወደ መሬት ውስጥ ሰላሳ ሜትር ተቆፍሮ የተቀበሩና ከግድቡ ጋር የተያያዙ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚለኩ የሚያሳውቁ መሳሪዎች በሲስተም ደረጃ ተጠናቀው ወደ መስመር አልገቡም።

ሶስት ትናንሽ ግድቦችም አሉ። ማስተንፈሻው ተጠናቋል ማለት ይቻላል። ውሃው ሊሄድባቸው የሚችሉ ቦታዎችም ተለይተው ተሰርተው አልተጠናቀቁም። ግድቡ ‘Earth Dam’ በመሆኑ በጠጠር የተሞላ ነው። ውሃውን በመገደቢያነት የተጠቀሙበት የተራራው አጠቃላይ ጂዖሎጂካል ነገሩን ስትመለከተው፣ አንድ ወጥ ድንጋይ አይደለም። በተራራዎቹ መሃል መሃል ላይ ቀይ አፈር የያዘ ክፍት ቦታዎች አሉ። እነዚህ ቦታዎች ፍሳሽ ለማሾለክ የተጋለጡ ናቸው። ከስር በኩል ላለው ክፍት ቦታ በግራውቲንግ ቴክሎጂ ተሰርቷል። የቀረው ግን ተሰርቶ አልተጠናቀቀም። አጠቃላይ በሆነ መልኩ አሁንም ፍሳሽ አለ። በተለይ ውሃው ሲሞላ ከፍተኛ መጠን ይኖረዋል። ፍሳሹ ወደፊት አደጋ ከመሆኑ በፊት በጣም ክትትል ይፈልጋል። ፍሳሽ በርግጥ ሊያጋጥም ይችላል። ከጎን እና ጎን የሚወጣ ፍሳሽ ግን አደገኛ ነው።

ሰንደቅ፡- በእርሻው ውስጥ በርካታ ሰዎች ይኖራሉ። እንስሳዎችም አሉ። በአገዳ ጋሪ ማመላለሻ መንገዶችም ላይ በርካታ ፍየሎችና በጎች ሲተላለፉ ነው የሚታየው። ድርጅቱ ነፃ የእርሻ ዞን መመስረት እንዴት አልቻለም?

አቶ ምሩጽ ወልዳይ፡- ሰዎችን ከአካባቢው አናስለቅቅም። የሚደረገው በተበታተነ ቦታዎች ያሉትን የአካባቢው ነዋሪዎችን በአንድ መንደር ውስጥ እንዲሰፍሩ ቦታዎችን በማስተካከል ማንቀሳቀስ ነው። መንደር ሰርተን ቤቶች ገንብተን፣ ት/ቤት ገንብተን ለማሕበራዊ አገልግሎት የሚሆኑ ቤቶችም ሰርተን በሳቡሬ አካባቢ ያሰፈርናቸው አሉ። ቀደም ብሎ የገነባናቸው ቤቶች የአካባቢው ሕብረተሰብ በሚኖረው መልክና መጠን የነበረ ቢሆንም ሕዝቡ አልተቀበለውም። በእንጨት የተሰሩ በቀላሉ ንፋስ የሚወስዳቸው በጣም ጠባብ ቤቶች ናቸው የሚል ቅሬታ በመቅረቡ ቅሬታቸውን ተቀብለን ዘመናዊ ቤቶች ገነባን። ለቤቶቹ ግንባታ የወጣው ወጪ ከፕሮጀክት አጠቃላይ ወጪዎች አንፃር በጣም ከፍተኛ ሆኖ ተገኘ ስለተባለ መንግስት ውሳኔ ይስጥበት ተብሎ፣ የመንግስት ውሳኔ አገኘ።

የተሰጠው ውሳኔ ማሕበራዊ ተቋሞችን በመገንባት ሕብረተሰቡ እንዲሰባሰብ ማድረግ ነው። እንዲሁም አንድ ሔክታር ለአንድ አባወራ አልምቶ መስጠት። በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉብኝት በመጡ ወቅት የደቡብ ክልል ልምድ ነው ተብሎ አንድ ሔክታር አልምቶ እንደዚሁ ከመስጠት፤ አንድ አራተኛውን አትክልቶች እንዲያለሙበት እና ሶስት አራተኛውን በማሕበር ተደራጅተው አገዳ አልምተው ለፋብሪካው እንዲያቀርቡ ተወሰነ። ከስምምነትም ተደረሰ። አሁን በዚህ የስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ ነው ያለነው። አዲስ የመሬት አቅርቦት ሲገኝ ጎን ለጎን የአካባቢውን ሕብረተሰብ ጥቅም እየጠበቅን እየሰራን ነው። ይህም ማለት የመንግስት ይዞታ ይኖራል፤ የህዝቡም ይዞታ ይኖራል። ሌሎችንም ጉዳዮች ተመካክረን ነው የምናደርገው። ለምሳሌ የከሰም ቀበሌ የቱጋ ይሁን የሚለውን ከሕብረተሰቡ ጋር ተወያይተን ነው የምንወስነው። ስለዚህ ከአካባቢው ሕብረተሰብ ጋር ያለን የሥራ አቅጣጫ ከላይ እንዳስቀመጥኩት ነው። ከአካባቢው የሚለቁበት ሁኔታ አይፈጠርም።

ሰንደቅ፡- ለእርሻ የምትጠቀሟቸው መሣሪያዎች የመለዋወጫ አቅርቦት ምን ይመስላል?

አቶ ምሩጽ ወልዳይ፡- የማሽነሪ መለዋወጫዎች ውሉ ላይ የፋብሪካው ኮንትራክተር የቻይና ኮምፕላንት ነው የሚያቀርበው። ከግዢው ጋር በተገናኘ መጀመሪያ ማቅረብ የነበረበትን መለዋወጫ ኩባንያው አቅርቧል። የቀረበበት ጊዜ በራሱ ክፍተት አለው፤ የዘገየ ነበር። ግዢ ከተከናወነ በኋላ ያቀረበውም ማሽነሪዎች ላይ ክፍተት ነበረው። ኩባንያው ያቀረብኩት በውሉ መሰረት ነው የሚል መከራከሪያ ቢያነሳም፣ አንዳንዶቹ ማሽነሪዎች ከእኛ ሥራ ጋር የማይሄዱ ናቸው። ከኮርፖሬሽን ጋር በተደረገ ውይይት ቬክሎቹን እንዲለወጡ ተደርገዋል። ኩባንያው በዘመናዊ መሣሪያዎች ከስሮ እንዲተካ ተደርጓል።

ሌሎቹ ግን ለምሳሌ ገልባጮቹ ያቀረብኩት በተሰጠኝ ስፔሲፊኬሽን መሰረት ነው አለ። ወደ ሃያ ስድስት የሚሆኑት ገልባጮች እየሰሩ አይደለም። እስካሁንም መግባባት አልተቻለም። ከጥራት አንፃር የሚታዩ ችግሮች አሉ። ትራክተሮቹ የተወሰኑት ይሰራሉ፤ ሞዲፊኬሽንም የሚፈልጉ አሉ። ዋናው ችግር ግን መለዋወጫ ማግኘት አልቻልንም። ሀገር ውስጥ አቅራቢ የሌላቸው ማሽነሪዎች አሉ። ከአመረቷቸው ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እየሰራን እንገኛለን።

 

ሰንደቅ፡- ከሰላሳ አመት በላይ በስኳር ኢንዱስትሪ ውስጥ እንደሰሩ ነግረውናል። ከሰም ፋብሪካን ከመሰረቱ እስከ አሁን ደረጃ የደረሰበትን ያውቃሉ። ከዚህ አንፃር መንግስት በያዘው የስኳር ልማት ስትራቴጂ ላይ ምን አስተያየት አልዎት? ከሰምን ጨምሮ እንዳይደገሙ የሚሏቸው የአሰራር ግድፈቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ምሩጽ ወልዳይ፡- ይህንን ፕሮጀክት የመተሐራ ማስፋፊያ ተብሎ የተረከብነው በ1999 ዓ.ም. ነው። ከዚያ ቀጥሎ በ2004 ዓ.ም. ስኳር ኮርፖሬሽን ተብሎ በአዲስ መልክ ሲቋቋም በከሰም ፋብሪካ ሥር ፕሮጀክቱ ተጠቃለለ። የከሰም ግድብ ግን ቀደም ብሎ በ1996 ዓ.ም. ነው የተጀመረው።

ባይደገም የምንለው፤ ፕሮጀክት በባሕሪው ገደብ አለው። መነሻ አለው፤ መድረሻ አለው፤ የጊዜ ገደብ አለው። ለፕሮጀክት የሚመደብ በጀት መታወቅ አለበት። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ፕሮጀክት ለማስፈፀም ስትገባ አደገኛ ነው። ለምሳሌ አሁን ያለው ፕሮጀክት ገደብ አልነበረውም። ፕሮጀክቱ ወረቀታችን ላይ የጊዜ ገደብ ነበረው፤ በተግባር ግን የተቀመጠ የጊዜ ገደብ አልነበረውም፤ በጣም የተለጠጠ ፕሮጀክት ሆኗል። ለዚህ ፕሮጀክት የተመደበው የገንዘብ መጠን ምን ያህል ነው? የወጣው የገንዘብ መጠን ምን ያህል ነው? ብሩስ ከወዴት ነው የሚገኘው? አሁን ለፕሮጀክቱ ገንዘብ ያስፈልጋል ገና ሃያ ሺ ሔክታር መሬት አቅርቦት ላይ መድረስ ይጠበቅብናል። የፕሮጀክት ምዕራፍ ላይ ሆኖ፣ ብድር መመለስ በጣም ከባድ ነው። እንደዚህ አይነት አሰራር በስኳር ፋብሪካ ልማቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፤ በሌሎች የፕሮጀክት ሥራዎች ላይ መደገም የለበትም።

በእቅድ አለመመራት የሚያመጣው ክፍተት በፍጥነት መስተካከል አለበት። የኮንትራት አድሚኒስትሬሽን አቅም በጣም ከፍ ባለ ደረጃ ማደግ አለበት። አለበለዚያ የሚመጣው ገንዘብ በብድር የሚገኝ በመሆኑ፣ በእቅድ ስለማይሰራ የብድር ገንዘቡ ያልቃል፤ ሥራዎች ግን አያልቁም። ስለዚህ የብድር አዙሪት ውስጥ መዞር መቆም አለበት። ልማት እንደዚህ አይሰራም። ልማት ምላሹ ተሰልቶ ነው የሚሰራው፤ ለሌሎችም እንዲተርፍ ይደረጋል። በወረቀት ላይ የሰፈረ እቅድ እንደሌለ ተደርጎ በሕብረተሰቡ ሲነገር እንሰማለን። እውነቱ ግን በወረቀት ላይ ታሳቢ የሚደረጉ ለፕሮጀክቱ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሁሉም ሰፍረው ነው ያሉት፤ ችግሩ በእቅዱ መሰረት ማስፈጸም ነው። ለምሳሌ የከሰም ግድብ በእቅዱ መሠረት ባለማለቁ ስንት ከፍተኛ ሚኒስትሮችን ያፈራረቀ ግድብ ነው። በሚደረጉ ለውጦች የሚፈጠሩ ክፍተቶች መኖራቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው። አሁንም የሔድንባቸውን መንገዶች ለማስተካከል ብዙ ሥራዎች ያስፈልጋሉ።¾

ብሔርተኝነት ያደርሳል ከጦርነት፣ ያመጣል ጨቋኝ ስርዓት (ክፍል 1 እና 2)

ከዚህ ቀደም “የአማራ-ብሔርተኝነት ከየት ወደየት?” የሚል ፅኁፍ ፅፌ ከጨረስኩ በኋላ በስህተት ከኮምፒውተሬ ውስጥ ስላጠፋሁት ሳይታተም ቀረ። ፅኁፉ በዋናነት “ቤተ-አማራ” የሚባለው ቡድን በሚያቀነቅነው የአማራ-ብሔርተኝነት ላይ ያጠነጠነ ነበር። በእርግጥ እንደ ኢህአዴግ ያለ ጨቋኝ ስርዓት ዜጎች የሚያነሱትን የእኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄን በኃይል ማፈን ባህሪው ነው። የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ሲታፈን ደግሞ የማህብረሰቡ የፖለቲካ ልሂቃን የብሔርተኝነት ስሜት ማቀንቀን ይጀምራሉ።

“የአማራ ብሔርተኝነት” መነሻ ምክንያት የአማራ ሕዝብ የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል መታፈኑ ነው። በመሰረቱ “ብሔርተኝነት” የሕዝብ ንቅናቄ ለመቀስቀስ (mobilization) እና ለማዳፈን (demobilization) ዋና መሳሪያ ነው። የመከፋፈል መርሆችን (Principles of division) በማስቀመጥ የሚታወቀው ፈረንሳዊው ተመራማሪ “Bourdieu” የአንድ ሀገር ሕዝብን የመከፋፈል መሰረታዊ ዓላማና ግብን እንዲህ ይገልፀዋል፡-

“Principles of division function within and for the purposes of the struggle between social groups…What is at stake in the struggle is power over the classificatory schemes and systems which are the basis of the representations of the groups and therefore of their mobilization and demobilization: the evocative power of an utterance which puts things in a different light” Distinction. A social critique of the judgement of taste, 1984.

ከዚህ አንፃር፣ ለምሳሌ የቀድሞ የሕውሃት መስራችና አመራር አረጋዊ በርሄ የትግራይ ሕዝብ የመብትና ነፃነት ጥያቄ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ አና በደርግ መንግስት በኃይል ሲዳፈን የትግራይ ልሂቃን የብሔርተኝነት ስሜትን ማቀንቀን እንደጀመሩ ይገልፃል። በመጨረሻም፣ በብሔርተኝነት ስሜት በመቀስቀስ (mobilization) እና በራስ-የመወሰን መብትን (rights of self-determination) ተስፋ በመስጠት የሕወሃት የትጥቅ ትግል ተጀመረ። በሕወሃት መሪነት የተመሰረተው ኢህአዴግ የደርግ ስርዓት ከስልጣን ካስወገደ በኋላ በብሔር-ልዩነት ላይ የተመሰረተ የአፓርታይድ ስርዓት ዘረጋ።

የብሔር-አፓርታይድ ስርዓት ዓላማና ግብ ደግሞ በሀገሪቱ አብላጫ ድምፅ (majority) ያላቸውን የኦሮሞና አማራ ሕዝብ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዳፈን (demobilization) ነው። ለዚህ ደግሞ ባለፉት አስር አመታት የኢህአዴግ መንግስት የግምገማ ሪፖርቶች ውስጥ “ትምህክተኝነት” እና “ጠባብነት” የመንግስታዊ ስርዓቱ አደጋዎች በሚል ያልተገለፁበት ግዜ የለም። ብሔርተኝነትን እያቀነቀነ ወደ ስልጣን የመጣው ሕወሃት መራሹ የፖለቲካ ቡድን የአማራና ኦሮሞ ሕዝብን የመብትና ነፃነት ጥያቄ “ትምክህተኛ” እና “ጠባብ-ብሔርተኛ” እያለ ያሸማቅቃል። “ትምክህተኛ” እና “ጠባብ-ብሔርተኛ” የሚሉት “Bourdieu” – “the evocative power of an utterance which puts things in a different light” የሚለው ዓይነት ፋይዳ ያላቸው ቃላት ናቸው።

በአጠቃላይ፣ ብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ንቅናቄ የሚወስደው ወደ እርስ-በእርስ ጦርነት ሲሆን መጨረሻው ደግሞ ጨቋኝ ስርዓት መፍጠር ነው። በምንም ዓይነት ተዓምር ቢሆን የብሔርተኝነት ንቅናቄ ወደ ዴሞክራሲ አያደርስም። በመሆኑም፣ ብሔርተኝነት ለሚታገሉለት ሕዝብ መብትና ነፃነት ሆነ ለጎረቤት ሀገር ሰላምና ደህንነት አይበጅም። ለምሳሌ፣ ብሔርተኝነትና በራስ-የመወሰን መብትን ዓላማ አድርገው የተነሱት ሕወሃትና ሻዕቢያን እንመልከት።

በራስ-የመወሰን መብት በክልል ደረጃ ራስን-በራስ ከማስተዳደር እስከ መገንጠል ሊደርስ ይችላል። ሕወሃት ብሔርተኝነት እያቀነቀነ በጀመረው የትጥቅ ትግል አሸንፎ የትግራይ ሕዝብን ራስን-በራሱ እንዲያተዳድር አደረገ። ነገር ግን፣ መብትና ነፃነትን ከማረጋገጥ አንፃር ግን የኢህአዴግ የብሔር ፖለቲካ ለትግራይ ሕዝብ ሆነ ለተቀረው የኢትዮጲያ ህዝብ ከአምባገነንነት ሌላ ያመጣው ትርፍ የለም። በተመሳሳይ፣ የኤርትራ ብሔርተኝነት እያቀነቀነ የትጥቅ የጀመሩት የኤርትራ አማፂያን ከኢትዮጲያ በመገንጠል የራሳቸው ሉዓላዊ ሀገር መሰረቱ። ነገር ግን፣ አሁንም ድረስ የታሪክ ቁስል ከማከክ በዘለለ የኤርትራዊያንን መብትና ነፃነት አልተከበረም። የትጥቅ ትግል ከጀመሩበት የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ መንግስት ቀርቶ ከወታደራዊ ደርግ የባሰ ጨቋኝና ጦረኛ የሆነውን የሻዕቢያ መንግስት ከመፍጠር ባለፈ በኤርትራዊያን መብትና ነፃነት ሆነ በጎረቤት ሀገሮች ሰላምና ደህንነት ላይ ያመጡት ለውጥ የለም።

በአጠቃላየ፣ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መቼም ቢሆን የብዙሃንን መብት፣ ነፃነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አያስችልም። የብሔርተኝነት መጨረሻ ጦርነትና ጨቋኝ ስርዓት ነው። ምክንያቱም፣ የብሔርተኝነት ፅንሰ-ሃሳብ በራሱ ከነፃነት ይልቅ በጠላትነት እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። ብሔርተኝነት የሰው-ልጅን ሰብዓዊነት ገፍፎ ከተራ እንስሳት በታች ያደርገዋል። በእርግጥ አገላለፁ ኃይለ-ቃል የተቀላቀለበት ወይም ግነት የበዛበት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን፣ እውነታው ይሄ ነው። ብሔርተኝነት ሰውን ከተራ እንስሳት ለምሳሌ፣ ከቀበሮ፥ ጅብ፥ ውሻ፥… በታች ያደርገዋል። በኢ-ሰብዓዊነት እሳቤ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ንቅናቄ መጨረሻው የሰዎችን ሰብዓዊ መብትና ፖለቲካዊ ነፃነት የሚገፍፍ ጨቋኝና ጦረኛ መንግስታዊ ስርዓት መመስረት ይሆናል። በቀጣዩ ክፍል “ለምንና እንዴት?” የሚለውን በዝርዝር እንመለከታለን።

ብሔርተኝነት የሰው-ልጅን ወደ አውሬነት ይቀይራል (ክፍል-2)

ታላቁ ደራሲ ስብሃት ገ/እግዜያብሄር አሁን ርዕሱን በረሳሁት ድርሰት ውስጥ በውሻና ሰው መካከል የተደረገ ቃለ-ምልልስ አለ። ሰውዬው ከሚጠጣው አረቄ ትንሽ የቀመሰው ውሻ ሲሰክር በሰውኛ ዘይቤ መሳደብ ይጀምራል፤ “እኛ ውሾች እንደ ሰው “እኛ” እና “እናንተ” ብሎ አናውቅም” ይላል። ባለቤቱ “እንዴት ባክህ?” ሲለው “በቃ…ሁላችንም “እኛ” ነን” ይለዋል። ደራሲው ጋሽ ስብሃት በዚህ ቃለ-ምልልስ ያስተላለፈው መልዕክት በደንብ የገባኝ ከአራት አመታት በኋላ ነው፡፡

የጋሽ ስብሃት ሃሳብ የገባኝ “Edmond Leach” የተባለውን ምሁር ትንታኔ ካነበብኩ በኋላ ነው። እንደ እሱ አገላለፅ፣ ከሰው ልጅ በስተቀር በሁሉም እንስሳት ዘንድ አንድ ዝርያ እስከሆኑ ድረስ ሁሉም “እኛ” ናቸው። ለምሳሌ፣ ውሻ ጥቁር ሆነ ነጭ፣ የፈረንጅ ሆነ የሀበሻ፣ የጀርመን ሆነ የአሜሪካ፣…ወዘዘተተ ሁሉም ደመ-ነፍሳዊ በሆነ የምልክት ቋንቋ ይግባባሉ። ስለዚህ፣ ውሾች ሲጣሉ ሆነ ሲፋቀሩ የሚግባቡበት፥ ስሜታቸውን የሚገልፁበት የጋራ መግባቢያ አላቸው።

የሰው ልጅን ጨምሮ ሁሉም እንስሳት አንድ ዓይነት ተፈጥሯዊ ባህሪ አላቸው። እሱም “ፀብና ጥቃት” (aggression) ውጫዊ እና ውስጣዊ አይደለም። ማለትም፣ የውሻ ፀብና ጥቃት ለምሳሌ በጅብ፥ ቀበሮ፥…ላይ እንጂ የራሱ ዝርያ በሆነ ሌላ ውሻ ላይ ያነጣጠረ አይደለም። በእርግጥ በውሾች መካከል የእርስ-በእርስ ፀብና ጥቃት ሊነሳ ይችላል። ነገር ግን፣ በጣም በተለየ አጋጣሚ ካልሆነ በስተቀር አንድ ውሻ በሌላ ውሻ ላይ እስከ ሞት የሚያደርስ ጥቃት አይፈፅምም። ብዙ ግዜ ታዝባችሁ እንደሆነ፣ አንድ ጉልበተኛ ውሻ ለፀብ ወይም ለመናከስ እየሮጠ ሲሄድ ሌላኛው ውሻ ጭራውን እያወዛወዘ ከተለማመጠው ወይም መሬት ላይ ከተኛ አይነክሰውም። እዚህ ጋር ሊሰመርባቸው የሚገቡ ሁለት ነጥቦች አሉ። አንደኛ፡- ጉልበተኛው ውሻ የሚፈልገው የሌላውን ውሻ ተገዢነት ወይም ተሸናፊነት ነው፣ ሁለተኛ፡- ውሾች በፀብና ግጭት ውስጥ የሆነው እንኳን እርስ-በእርስ በምልክት ይነጋገራሉ፥ ይግባባሉ።

ከሁሉም እንስሳቶች በተለየ የራሱን ዝርያ የሚገድል ፍጡር የሰው-ልጅ ብቻ ነው። “Edmond Leach” ይሄን ኢ-ተፈጥሯዊ የሆነ የሰው ልጅ ባህሪ በዋናነት ከሰው ልጅ የቋንቋ አጠቃቀምና አስተሳሰብ ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ይገልፃል። በእርግጥ የሰው ልጅ ሁሉም ነገር ከራሱ አንፃር የማየት ባህሪ አለው። ቋንቋችንም ከዚሁ አንፃር የተቃኘ ነው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ሰው ለራሱ ቅርብ የሆኑትን ሰዎች፤ እናት፥ አባት፥ ልጆች፥ እህት፥ ወንድም፥ ልጆች፥…ወዘተ ያሉትን “እኛ” ሲል ከዚህ ቀረቤታ ውጪ ያሉትን ደግሞ “እነሱ” ይላል።

“የእኛ” እና “እነሱ” የሚለው እሳቤ አንፃራዊ ነው። “እኛ” የስዩም ቤተሰቦች ከሆንን የጋሽ ስብሃት ቤተሰቦች “እነሱ” ናቸው፣ “እኛ” አሰላዎች ከሆንን “እነሱ” አደዋዎች፥ አሳይታዎች፥…ናቸው። “እኛ” ኦሮሞች ከሆንን እነሱ አማራዎች፥ ትግሬዎች፥ ወላይታዎች፣ “እኛ” ኢትዮጲያዊያን ከሆንን “እነሱ” ግብፃዊያን፥ ኤርትራዊያን፥ ጀርመናዊያን፣ “እኛ” በምድር ላይ የምንኖር ሰዎች ከሆንን “እነሱ” በሌላኛው ዓለም የሚኖሩ “መናፍስት”…ወዘተ ናቸው።

በጣም ቅርብ የሆኑትን “እኛ” ባህሪና እንቅስቃሴያቸውን በቀላሉ ማወቅ፥ መገመትና መግባባት ይቻላል። በጣም ሩቅ የሆኑትን “እነሱ” ደግሞ ባህሪና እንቅስቃሴያቸውን በቀላሉ ማወቅ፥ መገመትና መግባባት አይቻልም። ለእኛ በጣም ቅርብ የሆኑትን ስራና ተግባር በቀላሉ ማወቅና መገመት፣ እንዲሁም በንግግር መግባባት ስለሚቻል የፍርሃትና ስጋት ምንጭ ሊሆኑ አይችሉም። ለእኛ በጣም ሩቅ የሆኑት ደግሞ በእለት-ከእለት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ስለሌላቸው ምንም ስጋትና ፍርሃት ሊፈጥሩ አይችሉም።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ “እኛ” እና “እነሱ” የሚለው እሳቤ አንፃራዊ ነው። በዚህ መሰረት፣ ሩቅ ባሉት “እነሱዎች” እና ቅርብ ባሉት “እኛዎች” መካከል ሌላ ሦስተኛ “እነሱዎች” አሉ። እነዚህ ሦስተኞቹ “እነሱዎች” ከቦታና ግዜ አንፃር ለእኛ ቅርብ ቢሆኑም ሥራና ተግባራቸውን ግን በቀላሉ ማወቅና መገመት፣ እንዲሁም ተነጋግሮ መግባባት አይቻልም። “በእኛዎች” እና በሦስተኛ “እነሱዎች” መካከል ላለው ልዩነት መነሻ ምክንያቱ ተነጋግሮ መግባባት አለመቻል ነው። “እኛ” እና “እነሱ” በሚለው እሳቤ መሰረት፣ ሰዎች የተለየ ቋንቋ ሲናገሩ፣ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ሲሳናቸው፣ በዚህም አንዱ የሌላውን እንቅስቃሴና ባህሪ ማወቅና መገመት ሲሳነው፣ “እኛ” ሰዎች፥ ሌሎቹን ደግሞ ከሌላ የእንስሳት ዝርያ የመጡ ለምሳሌ “ውሾች” አድርገው ይስላሉ።

የሰው ልጅ በቅርቡ ካለ ሰው ጋር መነጋገርና መግባባት ከተሳነው፣ በዚህም የሰውዬውን እንቅስቃሴና ባህሪ ማወቅ ሆነ መገመት ከተሳነው፣ አንዱ በሌላው ላይ ስጋትና ፍርሃት ይጭራል። በቅርብ የሚኖሩ ሰዎች የማይነጋገሩ፥ የማይግባቡ፥ የማይተዋወቁና የማይተማመኑ እርስ-በእርስ እንደ ሌላ ፍጡር መተያየት ይጀምራሉ። አንዱ ራሱን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር እያየ ሌላውን ግን እንደ አውሬ ማየት ይጀምራል። እንደ “Edmond Leach” አገላለፅ፣ ይህን ግዜ የሰው ልጅ ከሰብዓዊነት ወደ አውሬነት ይቀየራል፡-

“…our propensity to murder is a back-handed consequence of our dependence on verbal communication: we use words in such a way that we come to think that men who behave in different ways are members of different species. In the non-human world whole species function as a unity. …If anything in my immediate vicinity is out of my control, that thing becomes a source of fear. This is true of persons as well as objects. If Mr X is someone with whom I cannot communicate, then he is out of my control, and I begin to treat him as a wild animal rather than a fellow human being. He becomes a brute. His presence then generates anxiety, but his Jack of humanity releases me from all moral restraint: the triggered responses which might deter me from violence against my own kind no longer apply.” A Runaway World: Lec. 3: Ourselves and Others, 1967   

ከሰው ልጅ በስተቀር ሌሎች እንስሳት ምንም ያህል ቢራራቁ ወይም ቢቀራረቡ፣ አንድ ዓይነት ዝርያ እስከሆኑ ድረስ በምልክት ቋንቋ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ይችላሉ። ስለዚህ፣ በመካከላቸው ምንም ያህል ልዩነት ቢፈጠር አንዱ ሌላውን እንደ ሌላ ዝርያ ፍጡር አይመለከተውም። እዚህ ጋር ጋሽ ስብሃት በሰውኛ ዘይቤ “በውሾች ዘንድ “እኛ” እና “እነሱ” የሚባል ነገር የለም” ያለው ማስታወስ ተገቢ ነው። በእርግጥ ውሾች አንድ ዓይነት መግባቢያ ቋንቋ አላቸው። ስለዚህ፣ ከጎንደር ሆነ አሳይታ፣ ከአክሱም ሆነ ወላይታ፣ …ከየትኛውም አከባቢ የመጡ ውሾች እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ይችላሉ። ነገር ግን፣ ከተጠቀሱት አከባቢዎች የመጡ ሰዎች በአንድ ቦታ ቢገናኙ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት አይችሉም።

እንደ “Edmond Leach” አገላለፅ፣ ሁለት የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች በጋራ ጉዳይ ላይ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ከተሳናቸው አንዱ ራሱን እንደ ሰው ሌላውን ደግሞ እንደ ሌላ ፍጡር (አውሬ) ማየት ይጀምራል። ይሄ ነገር ግን በውሾች መካከል አይከሰትም። በመሆኑም፣ ሰዎች በብሔርና በዘር ቡድን መስርተው ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ እርስ-በእርስ ሲጨፋጨፉ ውሾች ግን ሁሉም “እኛ” ስለሆኑ እርስ-በእርስ አይገዳደሉም። በአጠቃላይ፣ በ”እኛ” እና “እነሱ” እሳቤ ከሚመራው የሰው ልጅ በስተቀር የአንድ ዝርያ እንስሳት እንዲህ በጭካኔ እርስ-በእርስ አይገዳደሉም።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ እርስ-በእርስ መገዳደል እንደ ማንኛውም እንስሳ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ አይደለም። የሰው ልጅ ግን በዘር/ብሔር/ሀገር ተቧድኖ እርስ-በእርስ ይገዳደላል። ለዚህ ዋናው ምክንያት አንዱ ወገን ራሱን እንደ ሰው፣ ሌላውን ደግሞ እንደ ሌላ ፍጡር (አውሬ) መመልከቱ ነው። የሰው ልጅ ራሱን “እኛ” እና “እነሱ” ብሎ ለመመደብ የሚጠቀምበት ዋና መለያ መስፈርት “ቋንቋ” ነው። በተመሣሣይ፣ አንድን ብሔር ከሌላው ለመለየት አንዱና ዋንኛው መስፈርት ቋንቋ ነው። በሀገራችን በስፋት የሚስተዋለው የብሔርተኝነት ስሜት በዋናነት ቋንቋን መሰረት ያደረገ ነው።

ስለዚህ፣ “ብሔርተኝነት” ሁለት ጎን-ለጎን የሚኖሩ የተለያየ ብሔር ተወላጆችን እንደ ሌላ ፍጡር (አውሬ) እንዲተያዩና እንዲጨካከኑ፣ በዚህም እርስ-በእርስ እንዲገዳደሉ በሚያደርግ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ መሰረት፣ ብሔርተኝነት የሰው ልጅን የአውሬነት ባህሪ እንዲላበስ በማድረግ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው። እንዲህ ያለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መቼም፥ የትም ቢሆን ሕዝብን ወደ ጦርነትና እልቂት የሚወስድ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ብሔርተኝነት በራሱ የጠባብ አስተሳሰብ/አመለካከት ውጤት ነው። በአማርኛ መዝገበ ቃላት “ጠባብ አስተሳሰብ/አመለካከት” የሚለውን፤ “ጥልቀት የሌለው፣ በስፋት የማይገነዘብ፥ አርቆ ማየት የጎደለው” የሚል ፍቺ አለው። በተመሳሳይ፣ “ጠባብ ብሔርተኛ” የሚለው ደግሞ “ለጎሳው ብቻ የሚያስብና የሚያደላ፣ በሌላው ላይ ጥላቻ የሚያሳይ” ማለት ነው። ስለዚህ፣ ከብሔርተኝነት በስተጀርባ ለራስ ብሔር ተወላጆች የተሻለ ክብርና ዋጋ መስጠት፣ ለሌሎች ብሔር ተወላጆች ደግሞ ከእኛ ያነሰ ክብርና ዋጋ መስጠት እንዳለ መገንዘብ ይቻላል።

ከዚህ አንፃር፣ ብሔርተኝነት የአንድን ብሔር መብትና ነፃነት ከማረጋገጥ ባለፈ ራስን ከሌሎች የተሻለ አድርጎ በማሰብ ወይም ለሌሎች ብሔር ተወላጆች ዝቅተኛ ግምትና ክብር በመስጠት ላይ የተመሰረተ ነው። ስለ ራሱ ጎሳ ብቻ የሚያስብና በሌላው ላይ ጥላቻ ያለው የፖለቲካ ቡድን ከራስ-ክብር (Self-respect) ይልቅ በራስ-ወዳድነት (Egoism) የሚመራ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ለራስ ክብር (Self-respect) የሚደረግ የነፃነትና እኩልነት ትግል የመጨረሻ ግቡ የሁሉም ዜጎች መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው። ስለዚህ፣ የትግሉ እንቅስቃሴም የሰብዓዊነት (humanity) እና የጋራ እሰቶችን (common values) በማስረፅ የሚካሄድ ነው።

በራስ-ወዳድነት (Egoism) የተመሰረተ የብሔርተኝነት ትግል የመጨረሻ ግቡ የሁሉም ዜጎች መብትና ነፃነት ሳይሆን የአንድን ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው። ስለዚህ፣ የትግሉ እንቅስቃሴም በዋናነት የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ወይም ብሔር ተወላጆችን ልክ እንደ አውሬ በመመልከትና በኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና ጭካኔ የተሞላ ነው። ታዋቂው ፈላስፋ “Jean Jacques Rousseau” እንዲህ ያሉ በበታችነትና በራስ-ወዳድነት ስሜት የናወዘ የፖለቲካ አመለካከት የሚያራምዱ ሰዎች ያለ ምንም ምክንያት ወይም ጉዳት ወደ ፍፁም አውሬነት ሊቀየሩ እንደሚችሉ እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“…men who neither valued nor compared themselves could do one another much violence, when it suited them, without feeling any sense of injury. In a word, each man, regarding his fellows almost as he regarded animals of different species, might seize the prey of a weaker or yield up his own to a stronger, and yet consider these acts of violence as mere natural occurrences, without the slightest emotion of insolence or despite, or any other feeling than the joy or grief of success or failure.” WHAT IS THE ORIGIN OF INEQUALITY AMONG MEN, AND IS IT AUTHORISED BY NATURAL LAW?, 1754, Trans. by G. D. H. Cole.

በአጠቃላይ፣ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ፍፁም ስህተት ከመሆኑ በተጨማሪ የአውሬነት መገለጫ ነው። በማንኛውም ግዜ ቦታ ቢሆን በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሀገርን ወደ የእርስ-በእርስ ጦርነት የሚያስገባና ጨቋኝ ስርዓት በመዘርጋት የሚቋጭ የድኩማኖች መንገድ ነው። በአጠቃላይ፣ ብሔርተኝነት የሰው ልጅ አውሬነት መገለጫ ነው። ከዚህ በተቃራኒ፣ ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት የሚደርግ ሕዝባዊ ንቅናቄና ትግል እንዴት መጀመርና ምን መሰረት ማድረግ እንዳለበት በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን።

የወልቃይት ጠገዴን የአማራ ማንነት ጥያቄ ለማፈን የተሄደበት መንገድ . (ክፍል ሁለት) – አያሌው መንበር

የህወሃትን መዋቅር ከላይ እስከታች ያናጋውን የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት የአማራ ብሄርተኝነት የማንነት ጥያቄ ስርዓቱ ለጊዜውም ቢሆን እድሜየን ለማራዘም ያግዘኛል ያለውን ሁሉ ተጠቅሟል።የጥያቄውን አመራር ኮሚቴዎች ጎንደር ድረስ በመምጣት ከማፈን ጀምሮ እስከ ጀምላ ማሰር እና ማሰደድ ደርሷል።የታፈኑትና የታፈሱትን አብዛኛዎቹን ያለ ስማቸው ስም በመስጠት “በሽብርተኝነት መዘገብ” እስከመክሰስ ሲደርስ ያመለጡት ደግሞ አይናችን እያየ ለህወሃት ስቃይ አንዳረግም በማትለ በለመዱት ጫካ ገብተዋል።ጫካ የገቡትን ለማፈንም ያለ የሌለ ሀይሉን እየተጠቀመ ይገኛል።

ከዚህ ተግባሩ ጎን ለጎን ዋናውቹ ታሰረዋልና ህዝቡን ማባበል እችላለው ብሎም አስቦ ነበር።ከዚህ ስልት አንዱ #የእነ_አዲሱ ለገሰ #የጠገዴ ነዋሪዎችን ያናገሩበትና ያለውጤት የተበተነው ይገኝበታል።ምን ልትሰሩ መጣችሁ? ከሚለው ጥያቄ እኛን የት ታውቁናላችሁ? እስከሚል ንቀት ያለው አነግገርም ነግረዋቸዋል።በዚህ ያዘነው አቴ አዲሱ የአዞ እምባ እንዳነባም ቀደም ብለን ጠቅሰን ነበር።የሆነው ሆኖ የጉዞው አካል የበፊቱን አብዛኛው አመራር/ደጋፊ በእስር እና በጫካ የሚገኘውን የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ኮሚቴ በሽማግሌ ስም ውድቅ ለማደርግና የፈለጉትን አላማ ለማሳካት ነበር።በዚህም ሽማግሌ ምረጡ ሲባሉ አብዛኛዎቹ ሀቀኛ የሚባሉትን ይወክላሉ።ከዚያም እነ አዲሱ ይመለሳሉ።

ሁለተኛው ጉዳይ የእነ #ስብሃት ነጋና #አባይ ፀሀየ እንዲሁም በረከትና አዲሱ የተሳተፉበት #የባህር ዳሩ የአቫንቲ ሪዞርት (የአላሙዲን ሆቴል) ስብሰባ ነበር።በወቅቱየዚህ ስብሰባ መረጃን ለማግኘት ፈታኝና ጥብቅ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ዘግይቶም ቢሆን በሁለቱም ወገን (ከአማራና ከትግራይ) 40 ሽማግሌዎች ተገኝተዋል ተብሏል።የአማራዎቹ ሽማግሌዎች ጥያቄ ሲጠይቁም ዝም፤አስተያየት ስጡ ሲባሉም ዝም በማለታቸው ውይይቱ ፈተናና ያለውጤት የተጠናቀቀ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።ላለመናገራቸው ምክንያቱ እስካሁን ተናግረን ምን አተረፍን?፣እኛንም እንደሌሎች ለማሰር ነው፣ ቀድመን የወከልናቸውን አስረው እንዴት እንደገና ሌላ ሽማግሌ ይወክላሉ? ከሚል የመጣ ነበር።
የስብሰባው አላማም በክፍል አንድ የጠቀስኩትን ጥያቄውን ወደ መንግስት ከማቀረባቸው በፊት ህዝቡን በማወያየት የሰሩትን ስራ ውድቅ በማድረግ የህወትሃን ፍላጎት ለማሟላት በሚያስችል ሌላ ደካማ ሽማግሌ/ኮሚቴ ለማዋቀር ነበር።

እንደ መረጃው ምንጭ ከሆነ የባህር ዳሩ ስብሰባ በአማራ በኩል ወደቦታው የተገኙት ሽማግሌዎች በሙሉ ልብ አናደርግም በማለታቸው ስብሰባው ከታቀደው ጊዜ ቀድሞ ተጠናቀቀ።እነ አባይ ፀሀየና ስብሃትም በስብሰባ ስርዓት ሳይቋጩ ወይም በብስጭት ስብሰባውን አቋረጡት።
እንግዲህ ህወሃት ሁለት እድል ሞክራ ከሸፈባት ማለት ነው።አንደኛው ኮሚቴዎችን ማሳረ ሲሆን ሁለተኛው የቀድሞውን ዋናውን ኮሚቴ በሌላ አሻንጉሊት የመተካት ነበር ሁለቱም ከሸፉ።

በባህር ዳሩ የተበሳጩት እነ አባይ ፀሀየ የወሰዱት መፍትሄ ሌሎች ሰዎችን በደህንነት ተቋሙ አማካኝነት አስፈራርቶ ወይም በገንዘብ አታሎ “እኛ እኮ ጥያቄ የለንም ድሮም ህዝቡ ምን አደረገ ጥቂት <<ፀረ ሰላሞች እና ሆዳም አመራሮች ናቸው>> እንጅ እንዲሉ መላ ይዘይዳሉ።በዚህ መሰረት የተወሰኑ ሰዎች ተፅዕኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ የተባሉ ይታፈኑና #አዲስ_አበባ ይወሰዳሉ።ከዚያም በተናጠል “ልናስርህ ነው፤ከምናስርህ ከህዝቡ ውስጥ ሂደህ ድሮም እኛ ምንም አላደረግንም ጥቂት ሰዎች እና የብአዴን አመራሮች (ጥቂቶቹ ለህዝብ የማይጨነቁ) የፈጠሩት ነው፤አሁን ተፀፅተናል” የሚል ቅስቀሳ ከሰራህ ገንዘብ እንሰጥሃለን ከእስራትም ትድናለህ በማለት የተወሰኑ ሰዎች በዚህ መንገድ ይሰማራሉ።

ከዚያም በኋላ ህዝባዊ ስብሰባ እንዲጠራ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ሚናውን እንዲጫወቱ ይደረጋል።ስብሰባው ሲጠራ ዓላማው ሳይነገር “ከስብሰባው የቀረ መሳሪያው ይገፈፋል” በሚል ትዕዛዝ ብቻ ይጠራለ።ከዚያም ምርጫ ስለሌላቸው አብዛኛው #የታች_አርማጭሆ ሰው ሳንጃ ላይ ይገኛል።ስብሰባው ላይ እነዚያ የተዘጋጁ አካላት እና እነርሱ ያዘጋጇቸው ሰዎች አስተያየት ይሰጡና አዲስ አበባ ላይ የታቀደው ተልዕኮ ይፈፀማል።በዚህ ስብሰባም ሁለት ነገር አለው።አንደኛው ባህር ዳር ላይ የከሸፈውን ኮሚቴውን በሌላ ሽማግሌ የመተካት ሀሳብ መንገድ ለመጥረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “ትምክህተኛ ፀረ ሰላም” በሚል ከህዝቡ ወግነዋል የተባሉ የብአዴን አመራሮችን ለወጥመድ ማዘጋጀት ነው።

ከዚህ ስብሰባ ላይ እነዚህ አዲስ አበባ ላይ ተዘጋጁ ከተባሉት በተጨማሪ ሊያሳምኑ ይችላሉ የተባሉ ሰዎችም በጉዳዩ ላይ የጠለቀ እውቀት ሳይኖራቸው “የአማራ እና የትግራይ ህዝብ እኮ አብሮ የኖረ ህዝብ ነው” በማለት ቅን ሀሳብ ሰንዝረዋል።በዚህ ሂደት ውስጥ ታዋቂው ተመራማሪና ፀሀፊ ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ ተሳትፏል።ዶ/ር አለማየው በሙያውም በህዝቡም እጅግ የተከበረ ነው።ይሁንና እርሱ ስለፍቅር የመስበክን ጥቅም እንጅ ከስብከቱ በስተጀርባ ስላለው ሴራ ያውቃል ብየ አልገምትም።ዶ/ር አለማየሁን ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ አግኝቸዋለው።በስልክም እንዲሁ አውርቸው አውቃለው።በጣም ቅንና ሲያናግሩት የማይከብድ ሰው ለክልሉ ህዝብ ሲበዛ ተቆርቋሪ ነው።የሆነው ሁኖ በአሁኑ እንዴት እንደተሳተፈ ግን ለእኔም ግልፅ አይደለም።

ከዚህ አስር ሚሊዮን ብር ወጣበት ከሚባለው ከታች አርማጭሆው ስብሰባ ማግስት ሁለት ስብሰባዎችም ታቅደው ነበር።አንዱ ጠገዴ ውስጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ #ትግራይ ውስጥ ነው።#የጠገዴው መረጃው ቀድሞ በመውጣቱ ሊከሽፍ ሲችል የትግራዩ ግን አሁንም ለማካሄድ ታስቧል።ይህንን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪ ማስጠንቀቂያ መልዕክት ይደርስ ዘንድ ጠይቋል።ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ በትናንትናው እለት #ማይደሌ (#ከዳንሻ ቅርብ እርቀት ) የመንግስት ወታደሮች ወደጎንደር በመምጣት ላይ የነበሩ አማራ የመንግስት ሰራተኞች ላይ ድብደባ ፈፅመዋል።

ከፍተሻ ጣቢያው ላይ አስቁመው በስዓቱ መኪናው ውስጥ ሲጫወት የነበረውን የቴዲ <<አጼ ቴወድሮስ>> ሙዚቃ ለምን ታዳምጣላችሁ? በሚል እና መንገደኞች ትግረኛ አንችልም በአማርኛ አውራን በሚሉ ጊዜ ለምን አባታችሁ ነው ትግረኛ የማትናገሩ እየቻላችሁ? በሚል ዘግናኝ እና ጭካኔ የተሞላበት ድብደባ ተፈጽሞባቸው ወደ ሆስፒታል ተልከዋል።
ይህንን ተክትሎ የጀምርኩትን የወልቃይትን ጥያቄ የማፈን ስልት ያሰናክልብኛል ያለው የትግራዩ ነፃ አውጭ ድርጊቱን የፈፀሙትን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ሰምተናል።

የህወሃት መንግስት የአማራን ህዝብ የልብ ትርታ የሆነውን የወልቃይት ጉዳይ ማፈኑ የሚጠበቅ ቢሆንም የአማራን ህዝብ ስነልቦና ግን ከቶውንም መስበር አይችልም።እንዲያውም ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች እነ ራያ ጠንከር ብለው ለመብታቸውና ማንነታቸው ሲሉ ስርዓቱን ማስጨነቅ ጀምረዋል።በየአካባቢው ያለው አማራም ወልቃይት ሆይ ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ በማለት የጀምረውን ትግል የእነ አቤ ቃል አለብን በማለት ትግሉን ስልቱን እየቀያየረ እየተጓዘ ነው።ወልቃይት የትግል መነሻችን ብቻ ሳትሆን የማታገያም ስትራቴጅያችን ጭምር መሆኗ ታስቦ ሀምሌ አምስትም በየአመቱ ይዘከር ዘንድ አብዛኛው ሀይል ተስማምቶ በልዩ ልዩ ዝግጅት ለማክበር ዝግጅቱ ተጠናቋል።

ወልቃይት ሆይ ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ!!!!

የፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር የመረጧቸው አጀንዳዎች ይፋ ሆኑ

ምንም ለውጥ አያመጣም የተባለለትና ህወሃት ኢህአዴግ ከወራት በፊት አንዴ ውይይት በሌላ ጊዜ ደግሞ ድርድር በማለት በራሱ ልክ ጠፍጥፎ የፈጠራቸው ፓርቲዎችን ጨምሮ ከሰላማዊ ተቃዋሚዎች ጋር ድርድር እንቀመጥ ብሎ ጥሪ ሲያስተላልፍ ወራቶች ቢይልፉም አንኳር አንኳር የሆኑ ነጥቦችን ተዘለው ለድርድር የተስማሙበት ሰነድ ይፋ ሆኗል፡፡

በድርድሩ አገዛዙ ከገባበት አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣት ሲል ቢያንስ በግፍ የታሰሩትን “የህሊና እስረኞች”ን ይፈታል የሚል ግምት ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በሚያሳዝን ሁኔታ ለአጀንዳነት እንኳን ሳይበቃ መቅረቱ ስርዓቱ ምን ያህል በደመነፍስ ውስጥ እንዳለ የበለጠ ያሳያል ተብሏል።

ፓርቲዎቹ የቀረቱን የድርድር አጀንዳዎች ለመምረጥ ዛሬ ስብሰባ የነበራቸው ሲሆን አጠቃላይ የድርድር አጀንዳዎች ይፋ ሆነዋል።

ፓርቲዎቹ ዛሬ ባካሄዱት 13ኛ ዙር ውይይት በይደር ባቆዩዋቸው ረቂቅ የድርድር አጀንዳዎች ላይ ሀሳብ ከተለዋወጡ በኋላ ለድርድር የሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ ተስማምተዋል።

በዚህም መሰረት የምርጫ ህጎች እና ተያያዝ ጉዳዮች በድርድር አጀንዳነት ከጸደቁት መካከል አንዱ ነው።

በዚህ አጀንዳ ስርም፦

• የፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብ

• የ1999 ዓ.ም የምርጫ ህግ

• የ2002 ዓ.ም የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ይበኙበታል።

አዋጆች እና ተያያዝ ህጎች የሚለው አብይ የድርድር አጀንዳም በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድርድር ሊካሄድበት ፀድቋል።

በዚህ አብይ አጀንዳ ስርም፦

• የፀረ ሽብር ህግ

• የመገናኛ ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነት ህግ

• የበጎ አድራጎት እና ማህበራት ማደራጃ አዋጅ

• የታክስ አዋጅ

• የመሬት ሊዝ አዋጅ እና የልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ ሁኔታ በንኡስ የድርድር አጀንዳነት ፀድቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፦

• የዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ ተቋማት አደረጃጃት

• ዜጎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውሮ የመስራት መብት

• የክልል መንግስታት ህጎች

• ወቅታዊ እና ኢኮኖሚ ወለድ የህዝብ ጥያቄዎች

• በሄራዊ መግባባት

• የፍትህ ተቋማት አደረጃጀት እና አፈጻጸም አዋጆችም በፖለቲካ ፓርቲዎች ለድርድር የፀደቁ አጀንዳዎች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባቀረቡት ሀሳብ መነሻነት ኢህአዴግ በፀረ ሽብር ህግ እና በመገናኛ ብዙሃንና መረጃ ነጻነት አዋጅ እንዲሁም በፓርቲዎች

ምዝገባ አፈጻጸም ላይ ከህግ ውጭ በቁጥጥር ስር የዋሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር እና አባላት ካሉ በአዋጆቹ ላይ በሚደረግ ድርድር ሊቀርብ ይችላል ብለዋል።

ውድቅ የተደረጉ የድርድር ረቂቅ አጀንዳዎች

1.የህገ መንግስት ማሻሻያ

ኢህአዴግ በህገ መንግስቱ ማሻሻያ እንዲረግባቸው በተጠየቁ ሶስት አንቀጾች ማተልም አንቀጽ 39፣ አንቀጽ 46 እና አንቀጽ 72 አልደራደርም ሲል አቋሙን አሳውቋል።

2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ ለድርድር የቀረበው ረቂቅ አጀንዳም ኢህአዴግ ሀገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆና ስለአዋጁ መደራደር በማለቱ ውድቅ ተደርጓል።

3 የመሬት ስሪት ፖሊሲ

የመሬት ስሪት ፖሊሲን በተመለከተ ለድርድር የቀረበው ረቂቅ አጀንዳ “የመሬት ስሪት የኢህአዴግ ልዩ ፖሊሲ በመሆኑ መሬት የህዝብ እና የመንግስት ነው የሚለው አቋም ለድርድር አይቀርብም በማለቱ” ውድቅ ተደርጓል።

4. የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የድንበር ወሰን

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የድንበር ወሰን በፓርቲዎች ድርድር ሳይሆን በሀገራት መንግስታት መካከል የሚከናወን በመሆኑ ለድርድር የቀረበው ረቂቅ አጀንዳ ውድቅ ተደርጓል።

5. የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች

“የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞች አሉ” ተብሎ በፓርቲዎች የቀረበው ረቂቅ የድርድር አጀንዳ ላይ “የህግ እንጂ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኛ የለም” የሚል ሀሳብ ከኢህአዴግ በመቅረቡ አጀንዳው ለድርድር አልበቃም።

ከዚህ በተጨማሪም ኢህአዴግ “አልደራደርበትም ያለው ረቂቅ አጀንዳ፤ ህጋዊ እና ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ በውጭ ሀገር ሆነው እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፖለቲካ ሀይሎ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሳተፉ” የሚለውን ነው።

ይህንን አጀንዳ ያቀረቡት አምስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አጀንዳው ለድርድር አለመቅረብ ላይ ተስማምተዋል።

በመጨረሻም ፓርቲዎቹ ለድርድር የመረጧቸው አጀንዳዎች ቅደም ተከተል፣ የድርድር ጊዜ ሰሌዳ እና የድርድር መጀመሪያ እና መጨረሻ ጊዜ በአደራዳሪ ኮሚቴው ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ በመስማማት የዛሬው ውይይታቸውን አጠናቀዋል።

የፕሮፌሰር አስራት ወልደዬስ የቀብር ስነስርዓት በሥላሴ ቤተክርስቲያን ተፈፀመ ።

የፕሮፌሰር አስራት ወልደዬስ አጭር የህይዎት ታሪክ

አስራት ወልደዬስ ከአባታቸው ከአቶ ወልደዬስ አልታዬና ከእናታቸው ከወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌ ሰኔ 12 ቀን 1920 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ፡፡ የአስራት አባት አቶ ወልደዬስ አልታዬ በጸሓፊ ትዕዛዝ ኃይሌ ወልደ-ስላሴ አስተዳደር ውስጥ በጸሃፊነትና በአስተዳደር ተግባር የተሰማሩ ነበሩ፡፡ እናታቸውም በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር አሥራት የሶስት ዓመት ህጻን እያሉ ወላጆቻቸው በፍች ምክንያት ስለተለያዩ ከእናታቸው ጋር ወደ ድሬዳዋ አቀኑ፡፡ አስራት ድሬዳዋ በነበሩበት ወቅት ጣሊያን ኢትዮጵያን ትወራለች፡፡ በዚህ ወቅት በእነ ሞገስ አስግዶምና አብርሃም ደቦጭ ግራዚያኒ ላይ የተደረገ የግድያ ሙከራን ለመበቀል ከግራዚያኒ በተላለፈ በቀል በሶስት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ33 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዶማ፤ በአካፋና በገጀራ ተጨፍጭፈው ተገደሉ፡፡ የአስራት አባት አቶ ወልደዬስ አልታዬም እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ተጨፍጭፈው በአርበኝነት ሞቱ፡፡ እናቱ ወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌም የባለቤታቸው ሞት ተጨምሮበት ብዙም ሳይቆዩ ታመው በሞት ተለዩ፡፡
ወላጆቹን በሞት የተነጠቀው ታዳጊ ከአያቱ ከወይዘሮ ባንቺወሰን ይፍሩ-ለሱሲሉ ጋር መኖር ጀመረ፡፡ አጎቱ አቶ ዘውዴ ወረደወርቅ እዚያው ድሬዳዋ ይኖሩ ነበርና ታዳጊውን የቄስ ትምህርት እንዲማር አስገቡት፡፡ የቄስ ትምህርት ቤት በነበረበት ወቅት በቀለም አቀባበሉ ጎበዝ ነበር ይላሉ አስተማሪው አለቃ ለማ፡፡ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ‹‹አስራት በልጅነት በጣም ጎበዝ በመሆኑ ዓመት ሳይሞላው ወንጌሉን ከቁጥሩ አንበልብሎ፤ ከፍካሬ እስከ ነቢያት ደግሞ ድቁና ተቀበለ›› ይላሉ፡፡ ከቄስ ትምህርቱ ጎን ለጎን ድሬዳዋ ይገኝ ከነበረው ፈረንሳይ ሚሲዮን ገብቶ ቀለም መቁጠር ጀመሮም ነበር፡፡ የእናቱ አባት ቀኛዝማች ጽጌ ወረደወርቅ ታዋቂ አርበኛ ነበሩ፡፡ በመሆኑም ጣሊያን አርበኞችን ወደ ጣሊያን ሐገር ወስዶ በሚያስርበት ወቅት ቀኛዝማች ጽጌም አንዱ ታሳሪ ነበሩ፡፡ ቀኛዝማች ጽጌ ከሶስት ዓመት ተኩል እስር በኋላ ሐገራችን ነጻ ወጥታ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ አስራትን አዲስ አበባ አስመጥተው በ1934 ዓ.ም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አስገቡት፡፡ ትምህርት ቤት በገባ በአመቱ በ1935 ዓ.ም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከአጠቃላይ ተማሪዎች አንደኛ በመውጣት የካሜራ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ በወቅቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ወጣቶች መካከል ላቅ ያለ ውጤት ያስመዘገቡትን ወደ ውጭ ሐገር ልኮ ማስተማር ተጀምሮ ነበርና አስራትም በዚሁ የትምህርት ዕድል ምክንያት ግብጽ ወደሚገኘው የእንግሊዞች ቪክቶሪያ ኮሌጅ ተላከ፡፡ በቪክቶሪያ ኮሌጅ ለአምስት ዓመታት ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በስኮላሽፕ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሐገር እስኮትላንድ ኤደንብራ ዩንቨርስቲ አቀና፡፡ በወቅቱ ህግ እንዲያጠና ከትምህርት ሚንስቴር ቢነገረውም አሻፈረኝ ብሎ ህክምና ኮሌጁን ተቀላቀለ፡፡


ትምህርቱን እንደጨረሰም ፈጥኖ ወደ ሐገሩ ተመለሰ፡፡ በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚንስተር የነበሩት አውቁ አርበኛ ደጃዝማች ጸሐይ እንቁስላሴ አስጠርተው የጤና ሚንስትርነቱን ቦታ እንዲይዝ ይጠይቁታል፡፡ ዶክተር አስራት ግን አይሆንም ሲል ተቃወመ፡፡ በዚሁም የተነሳ የልዕልት ጸሃይ ሆስፒታልን ተቀላቀለ፡፡ ለአምስት ዓመታት በልዕልት ጸሐይ ሆስፒታል ካገለገለ በኋላ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሐገር አቀና፡፡ አደንብራ ዩንቨርሲቲ ገብቶ ቀዶ ህክምናን አጠና፡፡ በቀዶ ህክምና ዘርፍ አስራት የመጀመሪያው ኢትየጵያዊ ሐኪም ነው፡፡ ከዚህ በኋላ አስራት በእድሜም በማዕረግም እያደገ ስለሆነ አንቱ አያልን አንናገራለን፡፡ እነ ዶክተር አስራት እስኪተኩት ድረስ የሀገራችን የህክምና ዘርፍ በነጮች የተያዘ ነበር፡፡ ዶክተር አስራት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የህክምና ማሰልጠኛ እንዲከፈት በመወትወታቸው ምክንያት የጥቁር አንበሳን ሆሰፒታል እውን አደረጉ፡፡ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲቋቋም የቴክኒክ ኮሚቴውን የመሩት ዶክተር አስራት ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1965 ዓ.ም የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እውን ሲሆን ፕሮፌሰር አስራት ተባባሪ ፕሮፌሰር በመሆን የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ዲን ሆኑ፡፡ በደርግ ወቅትም በካድሬዎች ይደረግባቸው የነበረውን ከፍተኛ ጫና ተቋቁመው ሐገራቸውን ሳይለቁ ህዝባቸውን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በወቅቱ በተደጋጋሚ ዘመቻ የተላኩ ሲሆን የሄዱበትን ዘመቻ በክብር ለመወጣት በቅተዋል፡፡ በዚህም መሰረት በ1968 ዓ.ም በቀዳጅ ሐኪምነት በቃኘው ሆስፒታል አስመራ፤ በ1969 ዓ.ም እንደገና በቃኘው ሆስፒታል አስመራ፤ በ1970 ዓ.ም በራዛ ዘመቻ በቀዳጅ ሐኪምነት እና ቡድን መሪነት በመቀሌ ሆስፒታል፤ እንዲሁም በሰኔ 1971 ዓ.ም በቀዳጅ ሐኪምነት ምጽዋ ዘምተው ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በህክምናው ዘርፍ ‹‹አስራት የተባለ ጸበል ፈልቋል›› እስከመባል የደረሰ አንቱታን ያተረፉ ብቁ ሐኪም ነበሩ፡፡ ኢህአዴግ ከሌሎች 42 ምሁራን ጋር ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በ1985 ዓ.ም እስከሚያባርራቸው ድረስ በትጋት ያገለገሉ የሐገር ባለውለታ ነበሩ፡፡ በሙያቸው የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን ጥቂቶቹን ለመዘርዘር ያክል የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ የፈረሰኛ ደረጃ፤ የዳግማዊ ምኒልክ ኒሻን የፈረሰኛ ደረጃ፤ የአብዮታዊ ዘመቻ አርማ ፤ አለም አቀፍ የወርቅ ሜርኩሪ (በግል አስተዋጽኦ)፤ የቀይ ባህር ኒሻን አንደኛ ደረጃ ይገኙበታል፡፡
የደርግ ስርዓት ተሸንፎ ኢህአዴግና ሻዕቢያ ስልጣኑን በተቆጣጠሩበት ወቅት ሰኔ 24 ቀን 1983 ዓ.ም በተደረገው የሽግግር መንግስት ቻርተር ውይይት ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ወክለው የተገኙት ፕሮፌሰር አስራት ‹‹ሐገር ላስገነጥል ተወክዬ አልመጣሁም›› በማለት ተቃውሞ ያሰሙ ብቸኛው ሰው ነበሩ፡፡ ‹‹ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ምንም ጉዳይ ሊወስን፤ ሊያግድ ወይም ሊሰርዝ አይችልም›› በማለት ጉባኤው እያደረገው ያለው ውሳኔ ኢ-ዲሞክራሲያዊ መሆኑን አስረግጠው ሞገቱ፡፡ በዚህ ንግግራቸውም የተነሳ ከጉባኤው ሲወጡ ብዙ ማስፈራሪያና ዛቻ ያካሂዱባቸው ነበር፡፡
በወቅቱ በኮንፈረንሱም ሆነ በሽግግር መንግስቱ ምንም ውክልና ያልነበረው የአማራ ህዝብ በየአካባቢው ግፍና መከራን ማስተናገድ ጀመረ፡፡ ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው ምሁራን በመነጋገር የመላው አማራ ህዝብ ድርጅትን ታህሳስ 2 ቀን 1984 ዓ.ም መሰረቱ፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበርም ፕሮፌሰር አስራት ሆነው ተመረጡ፡፡ ፕሮፌሰር አስራት የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት በሐገር ውስጥና ከሐገር ውጭ ድርጅታቸውን ማስተዋወቅና የተቃጣውን የዘር ፍጅት ለመመከት ጥረት አደረጉ፡፡ ከሐገር ውጭ ጉዞ በማድረግ በስዊድን፤ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ፤በሎሳንጀለስና ኒዮርክ በመዟዟር የድጋፍ ቻፕተሮችን አቋቋሙ፡፡ በሐገር ውስጥ በነበረው የህዝብ ጥያቄ መሰረት በደብረ ብርሃን ዘርያዕቆብ አደባባይ ታህሳስ 11 ቀን 1985 ዓ.ም በተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ታሪካዊ ንግግር አደረጉ፡፡ የድርጅታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነት ማግኘት እረፍት የነሳው የሽግግር መንግስት ፕሮፌሰሩን ‹‹ጦርነት ቀስቃሽ ንግግር›› አድርገዋል ሲል ከሰሳቸው፡፡ የዚህን ንግግር ጦርነት ቀስቃሽ መባል የሰማ የአካባቢው ህዝብም ‹‹እስካሁን አማርኛ እናውቃለን ስንል ኖረናል፡፡ አሁን ግን በሽግግር መንግስቱ በአዲስ መልክ መማር ሊገባን ነው›› ሲል ምጸቱን ገልጾ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ተጠርተው በ50 ሺህ ብር ዋስና ከአገር እንዳይወጡ እገዳ ተጥሎባቸው ተለቀቁ፡፡ በዚያው ዓመት ከጎጃም ከመጡ አርሶ አደሮች ጋር አሲረዋል በሚል ‹‹ለጥያቄ ይፈለጋሉ›› ተብለው ሐምሌ 5 ቀን 1985 ዓ.ም ተጠርተው ለ24 ሰዓታት ከታሰሩ በኋላ በ20 ሺህ ብር ዋስትና ተለቀቁ፡፡ ከዚያ በኋላ ሐምሌ 12 በነበረው ተለዋጭ ቀጠሮ ዋስተናቸው ተነስቶ ለ43 ቀናት ከታሰሩ በኋላ ነሐሴ 24 ቀን 1985 ዓ.ም ሊፈቱ ችለዋል፡፡ በወቅቱ በተደጋጋሚ እየተጠሩ ዋስትና ከመጠየቃቸው የተነሳ ‹‹የዋሶች ባንክ ማደራጀት ሳይኖርብኝ አይቀርም›› ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸው ነበር፡፡
ከተደጋጋሚና አሰልች የፍርድ ቤት ምልልስ በኋላ ሰኔ 20 ቀን 1986 ዓ.ም የዋለው ችሎት ከጎጃም ገበሬዎች ጋር አስረዋል በሚለው ክስ የሁለት ዓመት እስር ተፈረደባቸው፡፡ ሐገራቸውን በታማኝነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያገለገሉ ሽማግሌ በጡረታ እድሜያቸው ከርቸሌ ወረዱ፡፡ በወቅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ፕሮፌሰሩን ‹‹የህሊና እስረኛ›› ሲላቸው የፍርድ ሒደቱንም ‹‹መረጃ አልባ›› ሲል አጣጥሎታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በእንጥልጥል የቆየው ደብረ ብርሃ ንግግር ክስ ተቀስቅሶ በሳምንት እስከ ሶስትና ሁለት ጊዜ ፍርድ ቤት እየተመላለሱ የሰላቻቸው ፕሮፌሰር አስራት ‹‹የምታውቁትን ውሳኔ የዛሬ 6 ወይም 9 ወር ከምትሰጡኝ ዛሬውኑ አሳውቁኝና እስር ቤት ቁጭ ብዬ መጽሐፍ ላንብብ›› ሲሉ ለችሎቱ በምሬት ተናግረው ነበር፡፡ ታህሳስ 18 ቀን 1987 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፕሮፌሰሩን የ3 አመት አስር በየነባቸው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ፕሮፌሰር አስራት ከ150 ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት ተመላልሰዋል፡፡ ከርቸሌ ታስረው በነበረበት ወቅት ከፖለቲካ እስረኞች ተለይተው ከፍታብሔር እስረኞች ጋር እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን መጽሃፍትና ጠያቂም በፈለጉት መጠን አያገኙም ነበር፡፡
የእስር አያያዛቸው የከፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በ1972 ዓ.ም የጀመራቸው የልብ ሕመም ተባብሶ እንዲሁም የስኳር መጠናቸው በመጨመሩ ከፍተኛ የጤና ችግር ላይ ወደቁ፡፡ ለብዙ በሽተኞች መድኀኒት የነበሩት አስራት ህክምና ተከልክለው የበሽታ መጫዎቻ ሆኑ፡፡ ከስኳራቸው ከፍ ማለት ጋር ተያያዞ አይናቸው ማዬት አልቻለም፡፡ ሰውነታቸውም እንደፈለጉ ሊታዘዛቸው አልቻለም፡፡ የልብ ድካማቸው ጨምሯል፡፡ ሕክምና እንዲያገኙ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ሳይቀር ደብዳቤ ጻፉ፡፡ መፍትሄ ግን አላገኙም፡፡ የኋላ ኋላ ሲዳከሙ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቢወሰዱም ህመማቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ መፍትሄ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ በመጨረሻም እ.ኤአ ታህሳስ 27 ቀን 1998 ዓ.ም ወደ ውጭ ሐገር ሄደው እንዲታከሙ ተፈቀደ፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ በመድከማቸው አውሮፕላን ውስጥ በሐኪሞች እየታገዙ ወደ ለንደን ሆስፒታል በረሩ፡፡ ከ3 ቀናት ቆይታ በኋላ ወደ አሜሪካ ሆስተን አመሩ፡፡ በአሜሪካ ቅዱስ ሉቃስ ኤጲስቆጳል ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት እንደተሻላቸውና ከልቡ ሲያስባቸው ለነበረው ህዝብ መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ ትንሽ እንደተሻላቸው ዘመዶቻቸው ወደሚገኙበት ፊላደልፊያ ከወር በፊት ተዛውረው በነበረበት ወቅት ባልታወቀ ምክንያት ህመማቸው ተባብሶ ተዳከሙ፡፡ ሞትን ድል ሲያደርጉት የኖሩት ሐኪም ግንቦት 6 ቀን 1991 ዓ.ም ፊላደልፊያ በሚገኘው ፔኒሲለቫኒያ ዩንቨርሲቲ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው በዕለተ አርብ በተወለዱ በ71 ዓመታቸው አረፉ፡፡ በወቅቱ የፕሮፌሰሩን ሞት ትልልቅ የአለም መገናኛ አውታሮች ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ነበር፡፡
የፕሮፌሰሩ አስከሬን ታላላቅ እግንዶች፤ ቤተሰቦቻቸውና አድናቂቆቻቸው በተገኙበት ግንቦት 15 ቀን አሸኛኘት ተደርጎለት ከዋሽንግተን ዲሲ ጉዞ ጀመረ፡፡ ግንቦት 15 የተነሳው የፕሮፌሰሩ አስከሬን ሮም አርፎ ግንቦት 17 ቀን 1991 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 ሲሆን ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደረሰ፡፡ በስፍራው ሲጠባበቅ የነበረው ህዝብ አስከሬኑን በከፍተኛ አጀብ ለገሐር ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አደረሰው፡፡ ግንቦት 17 ቀን ሌሊቱን ጸሎተ ፍትኃት ሲደረግ አድሮ በማግስቱ አስከሬናቸው በመሰረቱትና በኋላም በሞቱለት ድርጅታቸው (መአህድ) ጽ/ቤት ጥቂት ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ስላሴ ካቴድራል አመራ፡፡ በስላሴ ካቴድራል ፍትሃትና ጸሎት ከተደረገላቸው በኋላ ስላሴ እንዳይቀበሩ መንግስት በመከልከሉ ምክንያት በባለወልድ ቤተክርስቲያን እንዲያርፉ ተደረገ፡፡ ይኸው ላለፉት 18 ዓመታት በባለወልድ የቆየው አጽማቸው ዛሬ ወደሚገባው ቦታ ስላሴ ካቴድራል ሊዛወር ችሏል፡፡ ፕሮፌሰር አስራት ወልደዬስ የሁለት ወንዶች ልጆች አባትም ነበሩ፡፡
.
ይኸ ጽሁፍ ዛሬ ቀብራቸው ቦታ ላይ የተነበበ ሲሆን የፕሮፌሠሩን ሙሉ የህይዎት ውጣ ውረድ ማወቅ ለምትፈልጉ አንጸባራቂው ኮከብ በሚል ርዕሥ የጻፍኩትን ሥለ ፕሮፌሠር የህይዎት ታሪክ የሚያትት መጽሃፍ ማንበብ እንደምትችሉ እጋብዛለሁ።
©ጋሻው መርሻ

ጣራው ለሚያፈስ ቤት -የወለል እድሳት፣ ይገረም አለሙ


መላ አከላቷን ዝንጀሮ እሾህ ወግቷት
መቆም መራድ መቀመጥ ተስኖአት
የትኛውን እንንቀልልሽ ብለው ቢጠይቋት፣
ብታስቀድሙልኝ የመቀመጫየን
እኔ እነቅለዋለሁ ቁጭ ብዬ ሌላውን ፣ በማለት መለሰች ቅድሚያ የሚሰጠውን ነገር ስላወቀች ፡፡

ጣሪያው በሚያፈስ ቤት ውስት እየኖሩ ክረምት በመጣ ቁጥር እየተሰቃዩ በጋ  ሲሆን የወቅት መለዋወጥ የተፈጥሮ ባህርይ መሆኑ ተዘንግቶ ነገር አለሙን በመርሳት ወለሉን ቢያድሱት ግድግዳውን ቀለም ቢያብሱት አይቀሬ ነውና ክረምት ሲመጣ የሚሆነውን አስቡት፤ከንቱ ልፋት አጉል ብክነት፡፡

የቤቱ ወለል እድሳት ቢሻ፣ ግድግዳው ቀለም ቢያምረው፣ ጣራው ደህና እስከሆነ ድረስ መኖር አይከለክልምና ቅድሚያ መቀመጫየን እንዳለችው ዝንጀሮ መቀመጫን አስተካክሎ ሌላ ሌላውን በሂደት ቀን ሲፈቅድ አቅም ሲጎለብት ማደስ ይቻላል፡፡ ጣሪያው የሚያፈስ ቤት ውስጥ እየኖሩ ክረምቱ አልፏል ብሎ ወለል ማደስ ቅድግዳ ቀለም መቀባት ግን አንድም ሞኝነት ሁለትም አጭበርባሪነት ነው፡፡እንዲያም ሲል ከዛሬ ያለፈ አለማሰብ ይሆናል፡፡በአን ጎራ ካለነው እኛ ከምንባለው እነማን ከየትኛው ጎራ እንደሆኑ  እናንተው አስቡት፡፡

ሀገራችን ቤታችን ናት፤ ጣራዋ በብልሽትም በእርጅናም ተበለሻሽቶ በበጋ ለጸሀይ ሀሩር፣ በክረምት ለዝናም ዶፍ ብንዳረግም  ለምደን ተላማምደነው  እንኖራለን፡፡ገዢዎቻንም የእኛ ቻይነት፣ የፈረንጆቹም ጩኸት እንዴትነት ገብቷቸው ወለሉን እያደሱ፣ ግድገዳውን ቀለም እየቀባቡ  ለአላፊ አግዳሚውም ሆነ ለደርሶ ሀጅ ጎብኝው ችግሩ አንዳይታወቅ አንደውም ያማረ የሰመረ መስሎ አንዲታይ በማድረግና መኖሩን ችለውበታል፡፡ ያማረው ቤታችን ሞንዳላው ኑሮአችን እያሉ በሚያሰሙት ፕሮፓጋንዳም እኛን እያደነቆሩም አቀጣጫ እያሳቱም ከፈረንጆቹ ጋር እየተሞዳሞዱ ረብጣው ሳይነጥፍባቸው፣ ዲፕሎማሲያዊው ድጋፍ ሳይቋረጥባቸው፣ሲገድሉና ሲያስሩ የሚሰማው ተቃውሞም ከቃል ወደ ተግባር ሳይሸጋገርባቸው ሀያ ስድስት ዓመት እንደዋዛ ገዙን፡፡ ሁሉንም ነገር አይተው ገምተው ጠብ- መንጅቸውንም ተማምነው ገና አርባ አመት አንገዛችኋለን እያሉ ነው፡፡ ይበሉ! የታገሉት ለምንና ለማን ሆነና፡፡ ጥያቄው እኛ የምንባለው ከተቃውሞው ጎራ ያለነው ብዙ እኛዎች ያለፈውን የሰሩትን እያየን የወደፊት ምኞት ዝግጅታቸውን እየሰማን ምን አልን ምንስ አደረግን ነው ? ብዙዎቻችን ካለንበት ነቅነቅ ያላልነው  ከመማረር ወደ ማምረር ተሸጋግረን  ራሳችንን ከሰቀልንበት ከፍታ አውርደን ከመጯጫህ ወጥተን  አገዛዝ በቃን በማለት  የምንችለውን ጠጠርም ቢሆን ለማስቀመጥ ዝግጁ ነን ወይ? ነው ጥያቄው ይህ ካልሆነ ወያኔ ከምኞት ፍላጎቱም በላ ይገዛናል፡፡ አንደ አያያዛችን ከሆነ ብዙዎቻችን በአፋችን እንጮሀለን እንጂ በወያኔ የተፈጸመው ነገር ሁሉ ውስጣችን ዘልቆ አልተሰማንም ለዚህም ነው ከመማር ወደ ማምረር መሸጋገር ያልቻልነው፡፡ ይህ ባይሆንማ ኖሮ ወቅት እየጠበቀ ወያኔ በሚሰጠን መጫወቻ ከአንልፋችን እየባነንን በምናሰማው ውግዘት ጩኸት  ጣሪያው ለሚያፈስ ቤት የወለል እድሳት የምንጠይቅ ባልሆነ ነበር፡፡ በእኔ እምነት ጣራው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው፡ እንደ አብርሀም ሊንከን አባባል የህዝብ፣ በህዝብ፣  ለህዝብ፣  የሆነ መንግሥት ፡፡ ስለሆነም ይህ በሌለበት/በተነፈግንበት/ ሀገራችን  ሌሎች የህግም በሉት የሰብአዊ መብት፣ የቋንቋም በሉት የሀይማኖት ጥያቄዎችን ማንሳት  ታሰርን ተሰደድን ተገደልን እያሉ መጮህ ከሂደቱ ለማትረፍ እንጂ ከግቡ ለመድረስ የማንታገል ያስመስላል፡፡

ዴሞክራሲ ቅንጦት ተደርጎ በሚታይበት አገዛዝ ውስጥ እየኖሩ ስለ ቋንቋ፣ስለ ሀይማኖት፣ስለ ብሄር ብሄረሰብ፤ስለ ህግ በላይነት፣ስለ ሰብአዊ መብት መከበር ስለ ነጻ ምርጫ ወዘተ ማሰብ፣  መጠየቅ፣ መጮህ ጣራው በሚያፈስ ቤት እየኖሩ ወለል ለመቀየር ግድግዳ ለማደስ የመንደፋደፍ ያህል ነው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ሲሆን ምላሽ የሚያገኙ ናቸው፡ ብቻ ሳይሆን ያለ እነዚህ ተግባራዊነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊኖር ስለማይችል ወያኔ በሥልጣን ለመቆየት ጠመንጃውን እንደሚተማመን ሁሉ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ለሥልጣን የሚበቃ ግለሰብም ይሁን ፓርቲ እነዚህን ነገሮች ማክበርና ማስከበር የህልውናው ጉዳይ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ከፈረሱ ጋሪው የሆነውን መያዣ መጨበጫ ያጣውን ነገራችንን በማስወገድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ በሚያስችለው መንገድ አንደየአቅማችን እንራመድ፡፡ለዚህ ደግሞ ቀዳሚው ነገር ራስን መለወጥ ነው ፡፡ እዚህ ላይ አንድ ዘመን ተሸጋሪ አባባል ብጠቅስ ማለት የፈለኩትን ይበልጥ የሚያሳይልኝ መሰለኝና እነሆ!

የአሜሪካፕሬዝዳንት የነበሩት አብርሀም ሊንከን ለኮንግረስ ያስተላለፉት ሁለተኛው መልዕክታቸው ተብሎ በሚጠቀሰው ንግግራቸው «አንድ ትውልድ ያልፍና ሌላ ትወልድ ይተካል፣ ዓለም/መሬት ግን ለዘለአለም ትኖራለች፡፡ ጸጥ ረጭ ያለው ያለፈው ግዜ ፍልሰፍናዎች (ዶግማስ) አውሎ ነፋሳዊ ለሆነው ለዛሬው ችግር ለመፍትሄነት አይመጥኑም፡፡ ጊዜያችን ችግር ያዘለ ስለሆነ በአዲስ ሁኔታ ማሰብና በአዲስ ሁኔታም መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ራሳችንን ከሰቀልንበት ከፍታ ማውረድ ይገባል፡፡ ያን ግዜ አገራችንን ለማዳን እንችላለን፡፡ ታሪክን ልናመልጥ አንችልም፣ልንሸሸው አይሆንልንም፣ ክፉም ሰራን ደግ እንዘከራለን፣ (እንታወሳለን) ግለሰባዊ መታወቅ ወይም አለመታወቅ አንዳችንንም ሆነ ሁላችንን አያተርፈንም፣የምናልፍበት እሳታዊ ፈተና (ፍርድ) በክብር ወይንም በውርደት ማለፋችንን ይመሰክራል»

ብዙዎች እኛ ፤ እነርሱ ወያኔዎች ምንም በሉዋቸው ምን ባነገቡት ዓላማ ሊደርሱበት በሚያስቡት ግብ አንድ ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ አይደለም ሰው ነፋስ አያስገቡም፡፡እንዲህም በመሆናቸው ነው ታግለው ያሸነፉት፣ ሀያ ስድስት ዓመታትም በዙፋኑ ለመዝለቅ የበቁት፡፡ በተቃውሞው ሰፈር ያለነው እኛ ግን ብዙ እኛዎች ነን፡፡ ሰንደቅ ኣላማ ለብሶ ከሚፎክረው፣ ኢትዮጵያ እያለ ከሚዘምረው፣ የብሄር ኩታ ለብሶ ከሚያቀነቅነው ፖለቲከና አይደለሁም እያለ ከሚሸውደው  ወዘተ ብዙ እኛዎች መካከል  የቤታችን ጣራ ተቀይሮ ሁላችንም የጸሀዩ ሀሩር ሳጠብሰን፤ የክረምቱ ዝናም ሳያበሰብሰን መኖር የምችልበት ቤት እንዲኖረን ምን ያህሉ ነን ከምር የምንሻው ተብሎ ቢጠየቅ  ከብዙዎቹ ተግባር በማየት የምናገኘው ምላሽ አሉታዊ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ለወያኔ ግዞት ያመቻቸን መሰረት አልባው ልዩነታችን መሰረት የለሽ በመሆኑ ለገላጋይ ዳኛ ለመካሪ ሽማግሌም የሚመች አይደለም፡፡ ብዙዎች በቤታችን ጣራ መቀየር በየግላቸው ያምናሉ፣ነገር ግን ይህን እምነት የጋራ ለማድረግ ይቸገራሉ፣ለምክንያትነት የማይበቃው ሰበባቸው የሚያሳብቅባቸው ደግሞ ጣራው እኔ በምለውና በምፈልገው መንገድ ካልሆነ በስተቀር ባይለወጥ ይቅር የሚሉ ከራስ በላይ የማያስቡ መሆናቸው ነው፡፡ በግልጽ ቋንቋ ለመናገር እኔ አባዋራ የማልሆንበት ቤት አንኳን ጣራው ግድግዳውም ይደርመስ የሚሉ ነው የሚመስሉት፡፡

አንዳንዶቹ ደግሞ ለስሙ ከተቃውሞው ጎራ ከትመዋል እንጂ አድራጎት ንግግራቸው የተቃውሞ አይደለም፡፡ ጣራው እያፈሰሰም ለጸሀይ እየዳረገም ቢሆን ወለሉ ከታደሰ ግድጋዳው ቀለም ከተቀባ ርካታ የሚሰጣቸው አይነት ናቸው፡፡ ያ ባይሆን  ከሀያ ስድስት አመታት አገዛዝ በኋላ ዛሬ ስለ ህግ በላይነት፣ ስለ ሰብአዊ መብት መከበር፣ ስለ ሀብት እኩል ተጠቃሚነት፣ ስለ ፍትህ ወዘተ ለወያኔ  ማላዘኑ በቆመ ነበር፡፡ እነዚህ ከእባብ እንቁላል እርግብ የሚጠብቁ ሊባሉ የሚበቁ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ሁሉ ቢቀርና ቢረሳን  የህዝቡ ጥያቄ ትክክል ነው፣ የሰጡትን ዝም ብሎ የማይቀበል ጠያቂ ትውልድ ፈጥረናል ወዘተ ብለው ተመጻድቀውና ተሳልቀው ለተቃውሞ መውጣቱም ሆነ ያነሳው ጥያቄ ትክክል ነው ያሉትን ህዝብ በገፍና በግፍ አስረው እያስተማርነው ነው ተሀድሶ እየሰጠነው ነው ከሚሉ ሰዎች ምን ሊገኝ ጥያቄ እንደሚቀርብ ጩኸት እንደሚሰማ አይገባኝም፡፡

እያዩያ አለማስተዋሉ፣እየሰሙ አለማዳመጡ፣ እያነበቡ አለመገንዘቡ በእኛ ሰፈር በመብዛቱ እንጂ ወያኔዎች ከጅምሩ በመቃብራችን ላይ ሲሉ በግልጽ ነግረውናል፡፡ጽፈው አስነብበውናል፣ በተለያየ መንገድ በዘፈንም በፊልም አሳይተውናል፡፡እኛ ሰፈር ግን በምኒልክ ዘመን የደነቆረ ምንይልክ ይሙት እንዳለ ይኖራል እንደሚባለው ሆነን በወያኔ ድል ማግስት የተጀመረው ጩኸት፣ልመና ተማጽኖ፣ ስድብ ዘለፋ የመግለጫ ተቃውሞ  ወይ መሻሻል ሳይሳይ ወይ አርጅቶ ገለል ሳይል እስካሁን አለ፡፡

ሎሬት ጸጋየ  ገብረ መድህን የአባቶቻችን ነገር ሳስታውሰው ትዝ የሚለኝ ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ እንዳለው  እስከ ዛሬ የመጣንበት የፖለቲካ ጨዋታ አላዋጣም፣ የያዝነውም ተለይይቶ ጉዞ  ከምንለው ቦታ የሚያደርስ አልሆነም ስለዚህ ራሳችንን ፈትሸን፣ አመጣጣችንን ገምግምን ድክት ጥንካሬአችንን ለይተን፣ለዘመኑ የሚስማማውን አስተሳሰብ እንያዝ፣ ለትግሉ የሚመጥነው መንገድ እንከተል በማለት የሚታትሩ ብቅ ሲሉ ከወያኔ ሰፈር ባልተናነሰ ጩኸቱ የሚበዛውም ሆነ  ትንሽ ትንሽ መሰናክል ማስቀመጥ የሚጀመረው እኛ ከምንባለው ብዙዎቹ እኛዎች በኩል ነው፡፡

ቤቱ ጣራው ዝናብ ቢያፈስም፣ ጸሀይ ቢያስመታም ወለሉ ካማረ፣ ግድግዳው ቀለም ከተቀባባ ለእኔ ይመቸኛል፤ የጣራው ነገር አያስጨንቀኝም ማለት መብት ነው ምርጫ ነው፡፡ ለዴሞክራሲ ነው የምታገለው የሚል ሁሉ ይህን ምርጫ መቀበል የሰዎቹን መብት ማክበር ይገባዋል፡፡እነርሱ ደግሞ ጣራው መቀየር አለበት ብቻ ሳይሆን ካልተቀየረ በቤቱ ውስጥ መኖር አንችልም በሚለው ወገን እየተከለሉም እየተመሳሰሉም እያደናገሩም መኖሩን አቁመው አቋማቸው ጥቅም የሚያገኙበት ሳይሆን ከልብ የሚያምኑበት ከሆነ   መብታቸውን በይፋ መጠቀም እምነታቸውን በግልጽ ማራመድ ይኖርባቸዋል፡፡መሸፋፈን ለመኝታ ግዜ ብቻ ይሁን፡፡ ማለባበስ ይቁም!

በጣም አስቸጋሪው መፍትሄ አጥቶ የግዞት ዘመናችንን እያራዘመው ያለው በጣራው መቀየር ላይ ልዩነት ሳይኖር መቀየር ያለበት እኔ በምለው መንገድ ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ ነው፡፡የነገሩ ክፋት የሚብሰው ደግሞ የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች በሚሉት መንገድ ለመቀየር ስንዝር የተግባር እንቅስቃሴ የማያደርጉ መሆናቸው ነው፡፡ተግባሩ ቀርቶ እንዴት በምን ሁኔታ በማን ጣራው መለወጥ እንደሚችል ግልጽ አቋም የላቸውም፡፡ አቋማቸውን ገልጸው መንገዳቸውን አሳይተው ሊደርሱበት የሚያልሙትን ግብ ነግረው ደፋ ቀና በሚሉት ላይ ለመዝመት ግን እንቅልፍ የላቸውም ፡፡እንዲህ መሆን የለበትም፣ አንደዚህ ለምን ይደረጋል፣ በዚህ መንገድ ለምን ይኬዳል ከማለት በስተቀር እንዲህ ይሁን በዚህ መንገድ መሄድ ያዋጣል ወዘተ በተግባር ቀርቶ በቃል ደረጃ እንኳን አይናገሩም፡፡

ግልጽ አቋም በጣራው መለወጥ ላይ፣ የቤታችን ጣራ ከተለያየ አቅጣጫ ብዙ ስም የወጣለት ገዢዎቻችንም ሊያደናብሩንና አቅጣጫ ሊያስቱን በከጀሉ ቁጥር አዳዲስ ስም እያወጡ  በአንድ ያልረጉበት ሲሆን የምንሻው ግን ግልጽ ነው፡፡ዴሞክራሲያዊ ጣራ፡፡ ወራጅና ማገሩ ቆርቆሮና ምስማሩ በህዝብ ለህዝብ የህዝብ ሆኖ የሚሰራ ጣራ፡፡ይህን የሚጠላ ወይንም የማይፈልግ በአንደበቱ ባይናገረውም በተግባሩ እንለየዋልን፡፡የመጀመሪያው ወያኔና በዙሪያው ተኮልኩለው ተጠቃሚ የሆኑት ናቸው፡፡ለጥቆ የምናገኛቸው ሀያ ስድስት አመት ሙሉ ተቀዋሚ መባል ያልሰለቻቸው ምን አልባትም የሚያኖራቸው ወያኔ ተሰናብቶ ዴሞክራሲያዊ ሥርኣት ቢሰፍን ወለሉ ይታደስ ግድግዳው ቀለም ይቀባ አይነት የይስሙላ ተቃውሞ እያሰሙ መኖር አይችሉምና የጣራውን ለውጥ አይፈልጉትም፡፡ ሲስልስ ወያኔን ከማውገዝና ከማጥላላት ባለፈ የተጀመረም ሆነ የተሰነቀ ነገር የማይታይባቸው ነገር ግን ይህንኑ መኖሪያቸው ያደረጉ እናት ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ብሉኮ ብትከናነብ ህዝባችን ተገደለ ታሰረ በዘራችን ብቻ ተጠቃን  እያሉ ነሸጥ ሲያደርጋቸውም በመገንጠል እያስፈራሩ፣ ሰከን ያሉ እለት ደግሞ ስለ አንድነት እየዘመሩ ያሉ፣ የሚኖሩ ወገኖች ያኔ ይህን ማድረግ አይችሉምና በአፋቸው የሚናገሩት/የሚነግዱበት  ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በተግባር እውን ሲሆን ለማየት ይሻሉ ብሎ ማሰብ ይቸግራል፡፡

በድርድርም በሉት በግርግር፤በሰላማዊ ሰለፍም በሉት በጩኸት፣በጽሁፍም ይሁን በንግግር የሚቀርቡ ጣራውን በመለወጥ ላይ የማያተኩሩ ነሮች ሁሉ ጣራው ለሚያፈስ ቤት የወለል እድሳት የመፈልግ ያህል ነውና ሲብስም እቅጣጫ የሚያስት ትግል የሚያዘናጋ ለገዢዎች እፎይታ የሚሰጥ ወዘተ ነውና ይታሰብብት፡፡ በሁሉም መንገድ በየትኛውም መስመር ትግል ጣራውን ለመቀየር፡፤

የአማራ ብሄርተኝነት ትናንትም ነበር ዛሬም አለ ወደፊትም ይኖራል [ቬሮኒካ መላኩ]

…………
በእድገት ደረጃ ቁልቁል የሚያድገው ካሮት ነው። የአማራ ብሄርተኝነት ቁልቁል እንደ ካሮት ሳያድግ ወደ ላይና ወደ ፊት መገስገስ ከጀመረ ብዙ ጊዜ ሆነው ። ይሄን በማደግ በመመንደግ ያለ ብሄርተኝነት በአረጄ እና በአፈጀ አስተሳሰብ ወደ ኋላ የሚጎትት ካለ በቀቢፀ ተስፋ ልንጠራወዝ ብሎ አስቦ ካልሆነ ፍሬ ሊያመጣ አይችልም ። በጥራዝ ነጠቅ ትንታኔ የአማራ ብሄርተኝነት በፌስቡክ ላጲስ እንሰርዛለን ብለው የሚያስቡ ካሉ እርማቸውን እንድያወጡ ይመከራሉ ።

የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ፣ ፈላስፋወች እና የታሪክ ተመራማሪዎች የ”ብሔር”ን አፈጣጠር በተመለከተ ሶስት ዋና ዋና አስተሳሰቦች ያስቀምጣሉ ።
ሶስቱም የብሄር አስተሳሰቦች ስለብሄር አመጣጥና አፈጣጠር የየራሳቸውን መልስ ይሰጣሉ ፡፡
1 ~ Primordial (ተፈጥሯዊ ) ~
ተፈጥሯዊ የሚባለው የብሄር አስተሳሰብ አፅንኦት ሰጥቶ እንደሚያስረዳው ብሄር የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ወቅት ጀምሮ የኖረና ሰዎች እርስ በእርሳቸው ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ጥቅማቸውን ያስጠብቁበት የነበረ ተፈጥሯዊ ሲወረድ ሲዋረድ የመጣ የጋራ መገለጫ ነው የሚል ነው፡
2~ constructed (በማህበራዊ ሂደቶች የተፈጠረ ።)
ሁለተኛው አስተሳሰብ ‹‹ብሄር›› የተፈጠረው በተለያዩ ምክንያቶች በጊዜ ሂደት በተለይም በማህበራዊ ግንኙነት የተፈጠረ እና ትርጉሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀየረ የመጣ ነው የሚል ነው።
3~ Instrumental Theory ( ልሂቃን ለስልጣን መሳሪያነት የፈጠሩት ) የሚሉ ናቸው ።

ሶስቱም የብሄር አመጣጥ ቲዮሪዮች የተለያየ ትንታኔ ቢሰጡም ብሄር የሚባለው ነገር ከሰው ልጅ ቋንቋ ፣ አገር ፣ ዘር ፣ ደም ፣ ባህል እና ስነልቡናዊ ማንነት ጋር እንደሚዛመዱ ይስማማሉ።
አሁን በዚህ የፌስቡክ ፅሁፍ እያንዳንዱን የብሄር አመጣጥ ለማስረዳት መሞከር አንባቢን ማሰልቸት እንደሆነ ስለሚገባኝ ከአማራ ብሄርተኝነት ጋር በማያያዝ ጥቂት ነገር ለማለት ፈልጌ ነው።

” ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት እንጅ የአማራ ብሄርተኝነት የለም ”

ይሄ አስተሳሰብ አዲስና ከፍተኛ የሆነ የአስተሳሰብ መፋለስ የያዘና የአማራ ብሄርተኝነትን ጨፍልቆ እና ዳምጦ ለኢትዮጵያ የሚያስረክብ ነው ። ይሄን አስተሳሰብ ስንመለከተው “አማራ የሚባል ብሄር የለም ” ከሚለው ጋር ተቀራራቢ የሆነ ድምፀት ያለው አስተሳሰብ ነው ።
የራስን የብሄር ማንነት መምረጥ ፣ ማሳደግ እና መጎልበት መብት ነው ሆኖ እያለና ሚሊዮኖች በክብር ከፍ አድርገን የያዝነውን ማንነት ዝቅ አድርጎ ማየት ወይም ከነጭራሹ ‘የለም’ ብሎ መከራከር መሰሪነት ነው ።

የተለያዩ ምሁራኖች በብሄር ጉዳይ ላይ ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ፅፈውበትና ይሄው ምርምራቸው የተረጋገጠ እውነት በሆነበት ዘመን የግእዙን የብሄር ፍች ወስዶ “ብሄር ማለት አገር ማለት ብቻ ነው ” ብሎ መደምደምና ከዚህም ተነስቶ “የአማራ ብሄርተኝነት የሚባል የለም ” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ ድፍረት ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ነው።
በመሰረቱ ማነንት ተደራራቢ፣ተለጣጭ መሆኑ እየታወቀና ሃገራዊ ብሄርተኝነት ( Civic nationalism) እና ዘውጋዊ ብሄርተኝነት (Ethnic nationalism) አንዱ ሌላውን ሳይተካውና ሳይጨፈልቀው አብረው መሄድ እንደሚችሉ እየታወቀ የአማራን ብሄርተኝነት ዳምጦና ጨፈላልቆ ሌላ ስም መስጠትና መካድ ሳይንሳዊ ያልሆነና ከቡና ላይ ወሬ የማይዘል እንቶ ፈንቶ ነው ።

በመጨረሻ አማራ በገዛ አገሩና በገዛ ምድሩ ላይ እየኖረ በየእለቱ የውርደት አተላ እየተጋተ መኖሩ በቃኝ በማለት እና ይሄን የመሰለ የማንነት ውርዴት ” አማራ ብሄርተኝነትን ” አርማዬ አድርጌ ተደራጅቼ እዋጋለሁ ብሎ ተነሳስቶ እያለና ውጤትም እያመጣ ባለበት ሁኔታ “አማራ ብሄርተኝነት የሚባል የለም ” የሚል ዘመኑን ያልዋጄ ወለፈንዴና ዋግ የመታው አስተሳሰብ ፋይዳ የለውም።

ይድረስ ለትግል አባቴ አንዳርጋቸው ጽጌ (የአርበኛ ታጋዩ ትውስታ)

የአርበኛ  ታጋዩ ትውስታ

ተ—ጠ—ቀ—ቅ!!

ለፍትህ፣ለእኩልነት፣ለዴሞክራሲያዊ መብት መከበር፣ለሰባዊ መብት ልዕልና መጠበቅ፣ለኢትዮጵያ አንድነት ሲሉ—ውድ ህይወታቸውን አሳልፈው ለሰጡ ሰማዕታት ጓዶቻችን የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት እናድርግላቸው!! —-ይበቃል!!

ታች!!

ለተሰው ጓዶቻችን ያደረስነውን የህሊና ጸሎት ከደመና በታች አያስቀርብን እያልኩ፣ወደ ዋናው ቁም ነገሬ ልግባ። በቅድሚያ ግን ከዝች ወረቀት ላይ የሰፈረችው መልዕክት ወይም ትዝብት አሊያም ትውስታ ልበላት የኔና የኔ ብቻ ናት!! ግድፈት ካሳየሁም ከወዲሁ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ። በዚህ ከተግባባን ወደ ዋናው ፍሬ ነገር ይዣቹህ ልንጎድ፦Andargachew Tsige is Ethiopian

ብዕሬን ከጣቶቼ አዋድጄ፣ ከነጩ ወረቀት ጋር አቀናጅቼ እንዴት ሃሳቤን ምሉዕ አድርጌ መግለጽ እዳለብኝ ግራ ገብቶኛል። ሆህያት አነሱብኝ፣ ቃላቶች ኮሰሱብኝ፣ ያንተን ስብዕና፣ተከለ ቁመና ለመግለጽ የሚመጥኑ ሃረጋት፣ ዐረፍተ-ነግሮች፣ አንቀጾች ባወጣ ባወርድ ሁሉም ዝቅ አሉብኝ። ግን እንደ ምንም ብየ እነኝህን ሆህያት ባይመጥኑህም አጠራቀምኩኝ። ቃላትን ከቃላት አጋጭቼ ፣ሃረጋት ሰርቼ፣ ዐረፍተ ነገር መስርቼ፣ እነኝህን አንቀጾች ፈጠርኩ።

በእርግጥ አንተ ውዳሴ እና ዝማሬ እደማትሻ ጠንቅቄ አውቃለሁ። በርሃ ላይም ደጋግመህ ነግረህናል። ልናመሰግንህ፣ ልናግዝህ ስንል እንኳን “በሉ ዝበሉ ምንሰርቼ!፣ አልደከመኝም! እራሴው ነው የማደርገው” ትለን ነበር። ሁልጊዜም ከማውራት ይልቅ ስራን ነው የምታስቀድመው። <<ንድፈ ሃሳብንና ተግባርን አቀናጅቶ የሚጓዝ ሰው ደስ ይለኛል>> ትለን ነበር። <<ጋሼ>> ብለን እንኳን እንድንጠራህ አትፈቅድልንም።

ዛሬ ግን ጋሼ እንድልህ ፍቀድልኝ። በእርግጠኝነት ጋሼ ብዬ በመጥራቴ ቅር እንደማትሰኝብኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እናም ጋሼ አንተና ጥቂት ጓዶችህ የዘራቹትን የነጻነት ንጹህና ምርጥ ዘር ዛሬ አምሮበታል!! እጅግ አብቧል!! ፍሬውንም በቅርብ ጊዜ ታየዋለህ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።ስታስተምረን፣ ስትመክረን፣ ስታወያየን <<ታጋይ ከአቅሙ በላይ በሚገጥሙት ሁኔታዎች ምክንያት ይማረካል፣ ይቆስላል፣ ይሰዋል—ግን ትግሉ ይቀጥላል!!>> ትለን ነበር። እናም ልክነህ ጋሼ። አባባሉስ <<ታጋይና ሚስማር ሲመቱት ይጠብቃል>> አይደል የሚባለው።አንተን ቢያስሩህም፣ ቢገርፉህም፣ የተለያዩ ሰቆቃዎችን ቢፈጽሙብህም—ትግሉን አላሰሩትም!!

ያነጽከን!! የቀረጽከን!! ያንተ አርበኛ ታጋይ ልጆችህ አደራህን ዝንፍ ሳናደርግ ትግሉን አስቅጥለነዋል። እናም እልፍ ሁነናል!! በእያንዳዱ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ መግባት ችለናል። ጠላታችን ተንቀጥቅጧል!! ፈርቷል!! ርዷል!!! በዚህም እንኳን ደስ አለህ

በእርግጥ አንዳንድ የኔ ብጤ ግብዞች እንዴት በእስር ቤት እየተሰቃየ እንኳን ደሳለህ ይለዋል የሚሉ አይጠፍም። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከመከራ፣ ከፍዳ ነጻ ለማውጣት ብዙ ግፍና ሰቆቃዎች ተፈጽመውበታል። የሚፍጸሙበት ሰቆቃዎች አይሰሙትም ነበር። እንዲያውም በእሱ ላይ ሰቆቃ የሚፈጽሙበትን <<አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው>> እያለ ጸሎት አድርሶላቸዋል።

አንተም ጋሼ ስለኢትዮጵያዊያ መከራና ፍዳ ስትል ከወጣትነትህ ጀምረህ አሁንም ድረስ እድሜ ሳይገድብህ፣ እርጅና ሳይጫጫንህ መስዋእትነት ከፍለሃል! እየከፈልክም ትገኛለህ።ነገርግን እየከፈልከው ያለው መስዋዕትነት መና አለመቅረቱን እና  በሰውነትህ ላይ ካለው ቁስል ይልቅ የወጠንከው ትግል እየጎመራ መሄዱ የበለጠ እረፍት እንደሚሰጥህ ስላወኩ ነው እንኳን ደስአለህ ያልኩህ።

ሲጀመር እውነት እንናገር ከተባለ በኢትዮጵያዊያን ላይ እየደረሰ ያለው የኑሮ መናወጥ፣ የነጻነት እጦት፣ የፍትህ መጥፋት፣ የመብቶች መረገጥ፣ ስደት፣እስራት፣ ግርፋት፣የግፍ ሞት— እንደሌሎች እያዩ እንደማያዩት፣ እየሰሙ <<ጀሮ ዳባ ልበስ>> እንደሚሉት አልሆንም ብለህ እንጂ፤ የደመቀ ትዳርህን! የሞቀ ኑሮህን—ዕንቡጥ የአብራክህን ክፋይ ልጆችህን ጣል እርግፍ አድርገህ ትተህ፣ ለመቻል የሚከብደውን ችለህ በርሃ የወረድከው። አብዛኛው ሰው እንደ ምድራዊ ገነት የሚመለከተውን የምዕራቡ ዓለም ኑሮ ረግጠህ፣ ከምቾትና ከድሎት ይልቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ያስቀደምከው። ዛሬ ላይ ሁነህ ነገን አይተሃል። እናም ጋሼ ላደረክልን ነገር ሁሉ እናመሰግንሃለን። ያንተ ቁስል ለራስህ ባይሰማህም ለእኛ ለታጋዮቹ ግን አጥንታችን ድረስ ዘልቆ በመግባት ይሰቅስቀናል።

በጊዜው ይገርመኝ የነበረው የመንፈስ ጽናትህ!! የማይናወጠው ጥንካሬህ!! እኛ ወጣቶቹ እንኳን ደከመን ስንል አንተ ግን አንድም  ቀን <<ኧህ!>> ብለህ ያለማወቅህ ነው። ያን ተራራ!! ያን ቁልቁለት!! ያን አቃቅማ!! ያን እሾህና እንቅፋት ችለህ፣ በዚያ ዳገት ሃያ ሃያ  ሊትር ውሃ የሞሉ ሁለት ጀሪካኖችን፣ በግራና ቀኝ እጆችህ አንጠልጥለህ ስትወጣ ትንፋሽህን ከፍ አድርገህ ስትተነፍስ አይቼህም፣ ሰምቼህም አላውቅም። በእርግጠኝነት አልደክምህ ብሎም አይደለም። እኛም ሰዉ መሆንህን እና ሰባዊ ባህሪያትን መላበስህን እንረዳልን። ግን ለዓላማህ ስትል ሁሉንም ነገር ዋጥ አደረከው። የሚሰማህን ሁሉ እንደማይሰማህ ቆጠርከው። የደፈረሰ ውሃ አብርኸን ጠጥጠተሃል። ተረኛ አስመጋቢ ሆነህ እንጀራ ጋግረህና ወጥ ሰርተህ አብልተህናል። የሆነውን ሁነሃል። አፈር ላይ ተኝተህ ድንጋይ ተንተርሰሃል። ክብር!! ለአንተ ለትግል አባታችን ይሁን እላለሁ። ጋሼ እኛ ልጆችህ አንድም ቀን እንኳን ዘንግተንህ አናውቅም። ሁሌም በውስጣችን ታትመህ አለህ። አስተምሮትህ በህይወት እስካለን ድረስ ይኖራል። እኛ ብናልፍም  ከትውልድ ወድ ትውልድ ይተላለፋል።

ዛሬ እስርቤት ውለሃል። ያ ትወጣው ትወርደው የነበረውን ዳገት ዛሬም ለመውጣት ለመውረድ እግርህ ይፈልገው ይሆናል፣ እንደ አይንህ ብሌን ትሳሳላቸው የነበርካቸውን ታጋይ ልጆችህን፣ አይንህ ይራብ ይሆናል ግን በእርግጠኝነት ጋሼ ስጋህ የሚፈልገውን ሽቶ በይሆናል ቢቀርም፣ መንፈስህ ግን ከእኛ ጋር ነው!! የእኛ መንፈስም ካንተጋ ነው!! ስጋህን ነውጂ ማን መንፈስህንና ልብህን ቆልፎ አስቀርቶት?

ቆለፍነበት አሉ ስጋ ብቻ አግተው

የልቡን መብረሩን ማን? በነገራቸው።

እናም ጋሼ አምባገነኖች እንደ ቅዠታቸው የነጻነት ቀንዲሎችን በማሰር፣ በመግደል የተጀመረው ትግል የሚዳፈን ቢሆን ኖሮማ ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ቀንበር ነጻ ባልወጣች ነበር። ኔልሰን ማንደላ በሮቢን ደሴት ጠባብ ክፍል ውስጥ ለ27 ዓመታት ታሰረ! ተሰቃየ!። ይባስ ተብሎም አሜሪካ ድርጅቱንና መሪዎቹን በሽብርተኝነት ባህር  መዝገብ ውስጥ አሰፈረች። ግን የሆነው ሌላ ነው። ትግሉ አይነቱን እየቀየረ በመላው ደቡብ አፍሪካ እንደ ሰደድ ዕሳት ተቀጣጠለ። የማንዴላ መታሰር ሺ ማንዴላዎችን አፈራ። አፓርታይድም ተገረሰሰ። ።

ሼ ምንም እንኳን ወያኔ ብዙ ሚሊዮን ዶላሮችን አፍሶ  የመን ድረስ በመዝመት አንተን ቢያግትም፣ ያንተ መታገት ሺ አንዳርጋቸው ጽጌዎች እንዲ ፈጠሩ ምክኒያት ሁኗል። ለሃገሩ ዘብ የሚቆም፣ መብቱን ለማስመልስ ህይወቱን አስልፎ ለመስጠት የቆረጠ <<እኔም አዳርጋቸው ጽጌ ነኝ>> ያለ ትውልድ አፍርተሃል።

ይሁን እንጂ ጋሼ አንተ የደማህላትን፣ እንደ ክርስቶስ ስቃይና መከራ የተቀበልክላትን ኢትዮጵያን ለመናድ፣ ንደውም የራሳቸውን ስውር ዓላማ ለማሰካት ጥቂት ሃይሎች ከግራም ከቀኝም መኖራቸውን ሳልደብቅ እነግርሃለሁ። ግን በመሪዎቻችን ሆደ-ሰፊነትና ብስለት፣ በእኛ በአባላቶች ጠቢብነት ከሁሉም ሃይሎች ጋር በጋራ ለመስራት ብቻ ሳይሆን የጋራ አገራችን በጋራ ገንብተን ለመጓዝ በልበሙሉነት እየተንቀሳቀስን ነው። በዚህም የስውር ጥቅም አሳዳጆችን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቃቸው እና እርቃናቸውን እንዲቀሩ እያደረግን ነው።ባስተማርከን አስተምህሮት፣ በሰጠኸን አዳራ፣ ባስገባህን ቃልኪዳን፣ ባወረስከን ጽናት ኢትዮጵያ ከጨቋኞች መድፍ ወጥታ!! ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተመስርቶ፣ ሁሉም ልጆቿ በዕኩልነት የሚኖሩባት አገር እስከምትሆን ድረስ፣ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፤ እመነን ጋሼ አናቅማማም!! ወደኋላ አንልም!!

የአርበኛ  ታጋዩ ትውስታ

 

ሜቴክ በመባል የሚጠራው ድርጅት የሀገሪቱን ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ እየዘረፈ መሆኑ በይፋ ተነገረ

#የፍኖተ ዴሞክራሲ ዜናና ኃተታ – ቀጣይ ፍካሬ ዜና -ሰኔ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. (Finote Democracy News/Analysis -20 June 2017)

#ርዕሰ ዜና #ወያኔ ከተቃዋሚዎች ጋር ድርድር እያደረገ አለመሆኑ ተገለጸ

#ሜቴክ በመባል የሚጠራው ድርጅት የሀገሪቱን ሀብት በከፍተኛ ሁኔታ እየዘረፈ መሆኑ በይፋ ተነገረ

#የተምች ወረራ በስፋት እየተሰራጨ መሆኑ ተነገረ

#እምቧጮ የተሰኘው የውሀ ላይ አረምን ማጥፋት እንዳተቻለ ታወቀ

#በርካታ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ እርክብክብ እንደሚፈጸም ይፋ

#በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የውሀ መቋረጥ በመከሰቱ ኗሪዎች መቸገራቸው ታወቀ

#የነዳጅ እጥረት እንደቀጠለ መሆኑ እየተስተዋለ ነው

#አሜሪካ ዜጎቿ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ያወጣችው ማዘዣ መራዘሙ ታወቀ ##ዝርዝር ዜና##

ከመነሻውም ወያኔ ምክክር እንጂ ድርድር ለማድረግ ፍቃደኛ ባለመሆኑ መድረክ የተሰኘው የተቃዋሚ ድርጅቶች ስብስብና ሰማያዊ ፓርቲ በዚህ በወያኔ የማፋዘዣ ድራማ ላለመሳተፍ ወስነው ማቋረጣቸው የሚታውቅ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዐት ከወያኔ ጋር እየተመካከሩ የሚገኙት እራሱ ወያኔ የጠፈጠፋቸው የወያኔ እጅ ስራ የሆኑት ብቻ እንደሆኑ ሁኔታውን በቅርብ ከሚከታተሉ ወገኖች መገንዘብ ተችሏል፡፡ በዚህ ወያኔ የውጪ ታዛቢዎች የተገኙበት ስብሰባ እንደሆነ በሚገልጸው ንግግሩም ሆነ ምክክሩ ወያኔ ከወያኔ ጋር መሆኑን በአጽንኦት በመጥቀስ የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ ይህ ዐይነቱ ከወያኔ ጋር የሚደረግ መሞዳሞድና በየስብሰባው ፍጻሜ መለኪያ ማጋጨት በወያኔነት እንደሚያስፈርጅም በርካቶች ያስረዳሉ፡፡ ወያኔ የጭቆና እድሜ ገመዱን ለመቀጠል እንዲህ ዐይነቱን የትግል ማፋዘዣ ሴራ ቢነድፍም ሕዝባዊ አመጹን ከሰላማዊነት ወደ መሳሪያ አመጽ ማሸጋገሩን ብዙዎች ያስረዳሉ።
የወያኔና የቻይና የሽርክና ኩባንያ እንደሆነ የሚታወቀው ሜቴክ የተባለው ኩባንያ ከአሁን ቀደም በስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ስም ከ77 ቢሊዮን ብር በላይ መዝረፉ የሚታወቅ ነው፡፡ እነዚህ የስኳር ፋብሪካዎችም ወደ ሥራ መግባታቸው ቢነገርም አንድም ፋብሪካ ያመረተው ምርት ገበያ ላይ እየታየ አለመሆኑ እያነጋገረ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በቅርቡ በቀረበው የዋናው ኦዲተር አመታዊ የሂሳብ ዘገባ እንደሚያስረዳው የያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታን ለማከናወን ተረክቦ የግንባታውን አርባ ሁለት ከመቶ ብቻ በመፈጸም ከክፍያው ስልሳ ከመቶውን መውሰዱ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ዝርፊያ ሳይበቃው ቀሪውን ግንባታ ለማከናወን የሦስት ነጥብ አራት ቢሊዮብ ብር ተጨማሪ ክፍያ መጠየቁ ሜቴክ ዘራፊ ለመሆኑ ማመሰካሪያ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
በጥር ወር መጨረሻ በተለያ በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች መከሰቱ የታወቀው የተምችና የአባጨጓሬ ወረርሽኝ በአሁኑ ሰዐት ከጠቅላለው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሰማንያ ከመቶ በላይ የሚሆኑትን እንዳዳረሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ የተምች ወረራ ርሀቡ እየጸና በሄደባቸው በሰሜንና ደቡብ ኦሞ፣ በወላታ፣ በሆሳእና፣ በቡታጅራ፣ ወዘተ. መከሰቱ ችግሩን ተደራራቢ እያደረገው መሆኑን በርካቶች ስጋታቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ በትግራይ፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻጉል፣ በጎጃም፣ በጎንደር፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በወሎ ወዘተ. በርካታ የበቆሎ ማሳዎችን እያወደመ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡ ይህ የተምች ወረራ በዚሁ ሁኔታ እየተስፋፋ ከቀጠለ የርሀብተኛውን ቁጥር ከእጥፍ በላይ ሊያንረው እንደሚችል ብዙዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ከሁለት ወራት በፊት በጣና ሀይቅ መከሰቱ የተገለጸው እምቧጮ የተሰኘው አረም እስካሁን ማጥፋት ባለመቻሉ የውሀ ውስጥ እንስሳትን ቁጥር እያመነመነ በመሄድ ሊያጠፋ ይችላል የሚለው ስጋት እያደገ መሆኑ በስፋት እየተነገረ እንደሆነ ተገንዝበናል፡፡ ይህ አረም በዐባያታና በሻላ ሀይቆችም መከሰቱ ስጋቱን እያናረው መሆኑን ተረድተናል፡፡ የአረሙ ምንጭ ሊሆን የሚችለው በወያኔ የንግድ ድርጅቶች ካለምንም የጥራት ፍተሻ ከውጪ የሚገቡት ባዳበሪያና ከተለያዩ የእርሻ ምርምር ጣቢያዎች ምርጥ ዘር እየተባሉ ገበሬው በግዳጅ ማሳው ላይ እንዲጠቀማቸው የሚደረጉት ሊሆኑ እንደሚችሉ የእርሻ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አርቲፊሻል ዘረ-መል /ጄኔቲካሊ ሞዲፋይድ/ ዘሮችን ውስጥ ውስጡን ለማስተዋወቅ የሚደረገው ድብቅ ሴራ ውጡት ሊሆን እንደሚችልም የሚያስረዱ የእርሻ ጠበብቶች ቁጥር በርካታ ነው፡፡
የመንገድ፣ የጋራ መኖሪያ ህንፃ ግንባታዎች፣ የጤና፣ የትምህርትና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ግንባታዎች የግንባታ ጥራታቸው በእጅጉ የወረደና ለአደጋ የሚዳርግ መሆኑ እየታወቀ ከግንባታ ድርጅቶች ጋር በሙስና እርክብክብ እንደሚፈጽም ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተሰበሰበው የሕዝብ ምሬት ያስረዳል፡፡ የአውራ ጎዳናዎች ግንባታ እርክብክብ ግንባታው ሳይጠናቀቅ ስለሚካሄድ ተገነባ የተባለው መንገድ ስድስት ወራት ሳያገለግል ከአገልግሎት ውጪ እንደሚሆን መረዳት ተችሏል፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ወለላቸው አፈር እየተሞላ፣ ግድግዳዎቹ ውስጥ ወረቀትና ፕላስቲካ እየተጠቀጠቀ እንደሚያስረክቧቸው በመግለጽ ምሬታቸውን በርካቶች ሲያሰሙ ተደምጠዋል፡፡ በእንዲህ ያለው ዝርፊያ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ከፍተኛ ወያኔዎች ካዝና እንደሚገባ የሚታወቅ መሆኑን ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡
ዘንድሮ ክረምቱ ቀደም ብሎ የገባ ቢሆንም በበርካታ የአዲስ አበባ መንደሮች ውሀ የሚታደለው በፈረቃ ነው፡፡ በፈረቃ ውሀ የሚያገኙ አካባቢዎች ምንም ከማያገኙት ጋር ሲነፃፀሩ የተሻሉ መሆናቸው ይነገራል፡፡ በአዲስ አበባ በበርካታ አካባቢዎች ውሀ ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ በቦቴ እየታደለ ሲሆን ከቦቴ ውሀ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ እራቅ ካለ ቦታ ውሀ በግዢ መጠቀም የግድ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ በሳምንት ለውሀ ከሁለት መቶ እስከ ሦስት ብር ወጪ የግድ ይላል፡፡ በአዲስ አበባ በመስመር የሚታደለው ውሀ አንዳንዴ ድፍርስና የሚከረፋ ሽታ እንዳለው ኗሪዎች በምሬት ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ሰሞኑን በኮተቤ ዜሮ ሁለት በሚባለው አካባቢ ውሀ ጭርሱን በመጥፋቱ በቦቴ እየታደለ መሆኑን ከአካባቢው ኗሪዎች መገንዘብ ተችሏል፡፡
ከዛሬ ሶስት ወራት በፊት የተከሰተው የነዳጅ እጥረት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን በአዲስ አበባ በተለያዩ የነዳጅ ማደያዎች የሚታየው የተሽከርካሪዎች እረጃጅም ሰልፎች ማስረጃዎች መሆናቸው ካለማከራከሩም በላይ ጥቂት የማይባሉ የነዳጅ ማደያዎች ምንም ዐይነት ነዳጅ እንደሌላቸውም መገንዘብ ተችሏል፡፡ የናፍጣ እጥረት ከሁሉም በባሰ ሁኔታ በመሆኑ የናፍጣ ተሸከርካሪ ያላቸው ከአዲስ አበባ ውጪ እየተጓዙ ናፍጣ ለመሸመት መገደዳቸውን ያስረዳሉ፡፡ ወያኔ የስርጭት እንጂ የክምችት እጥረት እንደሌለ በተለያዩ ጊዜያት ቢገልጽም አንዳንዶች የዚህ እጥረት ሰበቡ የውጪ ምንዛሪ መሟጠጥ ሊሆን እንደሚችል ሲያስረዱ ሌሎች ደግሞ የዐባይ ገድብ መዘዝ የፍጻሜው መጀመሪያ፣ የአረባች ማእቀብ ሊሆንም ይችላል ሲሉ ይደመጣል፡፡
ከዚህ ቀደም አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተቀጣጠለ በመሄድ ላይ ያለውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ አሜሪካኖች ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ እንዳያደርጉ ያወጣችውን ማስጠንቀቂያ በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ማራዘሟን ገልጻለች፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎት በየጊዜው በሚቋረጥባት ሀገር የዜጎቿን ሁኔታ በቅርበት መከታተል እንደሚሳናት በመግለጽ ዜጎቿ ወደ ኢትዮጵያ በፍጹም ጉዞ እንዳያደርጉ ማስጠንቀቋ ታውቋል፡፡ በተለይ ደግሞ ወያኔ በስቸኳይ አዋጅ ስም ይፋዊ የአፈና አገዛዝ እየሆነ መቀጠሉ አሳሳቢ መሆኑን በመጥቀስ በማንኛውም የአሚሪካ ዜጋ ላይ ወያኔ የአሜሪካን ኤምባሲን ሳያሳውቅ ምንም ዐይነት እርምጃ እንዳይወስድ አስጠንቅቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎችም ሕዝባዊ አመጹ ወደ ትጥቅ አመጽ በተሸጋረባቸው ጎንደርና ባህር ዳር እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ በጽኑ ማሳሰቡ ታውቋል፡፡

– See more at: http://www.satenaw.com/amharic/archives/34764#sthash.EZyQDHRp.dpuf