የአማራ ህልውናና መብት የሚከበረው በራሱ ትግል እንጅ በሕገመንግሥቱ አይደለም። (ከይገርማል)

ሕገመንግሥት የአንድ ሀገር ገዥ/የበላይ ሕግ ነው። ሌሎች ህጎች የሚወጡትና ተፈጻሚ የሚሆኑት ሕገመንግስቱ ላይ የሰፈሩትን ጽንሰሀሳቦች መሰረት አድርገው ነው። ከህገመንግሥቱ ጋር ተቃርኖ ያላቸው ሌሎች ህጎች ተቀባይነት የላቸውም። ይሁንና እኛ ሀገር እንዲህ አይነት ነገር አይሰራም። እንደሚታወቀው በህወሀት አምባገነንነት ስር በምትማቅቅ ሀገር ውስጥ ነው የምንኖረው። ለሚፈለገው ተግባር ጠቀሜታ ይሰጣል ተብሎ እስከታመነ ድረስ በህገመንግሥቱ ላይ የሰፈሩ መብቶችን የሚጥስ የወያኔ ሀሳብ በአንድ ቀን አዳር ተረቆ ህግ ሆኖ ሊወጣ ይችላል። ወያኔ እንደድርጅት ይቅርና አንድ የወያኔ ሹም ሕገመንግሥቱን የሚጥስ ተግባር ቢፈጽም ምንም ማለት አይደለም። እንዲህ ያሉ ሁኔታወች ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙ በመሆኑ በማናችንም ላይ መደናገር አይፈጥርብንም። ሕገመንግሥቱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሀገሪቱ ዕኩል መብት ያላቸው መሆኑን ይናገር እንጅ ዕውነታው ግን እንደዚያ አይደለም። ለሕገመንግስቱ ከበሬታ መስጠትና ተገዥ መሆን የሚጠበቀው ከወያኔና በላተኞቹ ውጪ ባለው ማህበረሰብ ዘንድ ነው። በተለይ በአማራው ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ በሕገመንግሥቱ አግባብ ለመዳኘት የሚቻል አይደለም፤ ለአማራው ስለማይሰራ። ለ26 ዓመታት ያህል የደረሰውን የሰውና የንብረት ጥፋት በተመለከተ ለሚነሳው የሕዝብ ጩኸት ጆሮ ሰጥቶ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ አማሮች ተለይተው ለምን የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ ቻሉ፣ ምን ያህል ሰው ተገደለ፣ ምን ያህል ሕዝብ ተፈናቀለ፣ ሰዎች የተገደሉት በምን እና እንዴት ነበር፣ የጠፋው ንብረት አይነትና መጠን ምን ይመስላል? በሚል ዝርዝር ሁኔታውን ለማወቅ የተደረገ ጥናት የለም፤ በአጥፊወች ላይ ርምጃ ለመውሰድም አልታሰበም። የብሔር ብሄረሰቦችና ሕዝቦችን መብት ያስከብራል ተብሎ የወጣው ሕገመንግሥት ለአማራው አይሰራም።

 

ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የምታገኘው ልዩ ጥቅም አለ ሲባል ብዙም አልገባኝም ነበር። አሁን እንደተረዳሁት ክልሉ ብቻ ሳይሆን የክልሉ ኗሪም የአዲስ አበባ ልዩ ተጠቃሚ እንደሆነ ነው። ይህም ማለት በአንድ ሀገር እየኖርን በዋና ከተማችን አዲስ አበባ የዜጎች የጥቅም መበላለጥ ተፈጠረ ማለት ነው። የጥቅም መበላለጥ ማለት ዕኩል መብት አለመኖር ማለት ነው። በመሰረቱ የአንድ ሀገር ዜጎች የተለያየ መብትና ጥቅም ሊኖራቸው አይገባም። ክልሎች በራሳቸው ሰዎች የመተዳደር አስፈላጊነት በህግ በተሰጣቸው ኃላፊነቶች በስራቸው የዋሉትን ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሐብቶች ለማስተዳደር፣ ለማሳደግና ሕዝባዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ፣ በክልሉ የሚኖረው ሕዝብ የዴሞክራሲያዊ መብቱ እንዲጠበቅ፣ በክልሉ ሀብትና አገልግሎት ፍትሀዊ ተጠቃሚ እንዲሆን (እኩል እድል እንዲያገኝ)፣ በቋንቋው እንዲማር/እንዲዳኝ፣ ባህልና ወጉን እንዲያጎለብት፣ እና ሰላሙ እንዲረጋገጥ ለማስቻል እንጅ በሀገሪቱ ዜጎች መሀል ልዩነት ለመፍጠር መሆን አልነበረበትም።

 

ይቅርታ ይደረግልኝና የአንዳንድ ሰዎች ሁኔታ ምኑም አይገባኝም። ስለፍላጎትና አቅርቦት (demand and supply) አንስተው ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ልዩ ተጠቃሚ የመሆን መብት ሊኖረው እንደሚገባ ሊያስረዱ የሚሄዱበት መንገድ በጣም ግራ የሚያጋባ ነው። በመሰረቱ አዲስ አበባ የሚመረት የእርሻ ምርት የለም ቢባልም አዲስ አበባ የሚመረት የፋብሪካ ውጤት ግን አለ። ኦሮሚያ የግብርና ምርት አቅራቢ ስለሆነች ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ሊጠበቅላት ይገባል ከተባለ አዲስ አበባ አምርታ ወደኦሮሚያ ለምትልከው የፋብሪካ ውጤትም ልዩ ጥቅም  የመጠየቅ መብት አላት ማለት ነው። ለነገሩ ያህል ነው እንጅ ለአዲስ አበባ የግብርና ምርት የሚቀርበው ከኦሮሚያ ብቻ አለመሆኑን ማንም ያውቃል። ሊሆን የሚገባው በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖሩ የኦሮሚያ ክልል ኗሪወች ቢፈናቀሉ ተመጣጣኝ ካሣ የማግኘት መብት እንጂ ማንም ዜጋ በሀገሩ ላይ የበለጠ ተጠቃሚና ዝቅተኛ ተጠቃሚ የሚያደርግ የተለያየ መብት አይደለም። በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ዕኩል መብት ያላቸው ናቸው። ዜጎቹ በፈለጉበት ቦታ ተዘዋውረው የመኖር፣ የመስራትና ሐብት የማፍራት መብት አላቸው። በርግጥ ክልሎች ሕገመንግሥቱን ተከትለው በሚያወጧቸው አካባቢያዊ ህጎች የመገዛትና እንደማንኛውም የክልሉ ዜጋ በማህበራዊ ጉዳዮች የመሳተፍ ግዴታ ሊኖርባቸው ይችላል።

 

“ለኦሮሚያና ለኦሮሞ ሕዝብ ተሰጠ የተባለው ልዩ ጥቅም እዚህ ግባ የማይባል ተራ ነገር ነው፤ ወያኔ በኦሮሚያ የተነሳበትን የሕዝብ አመጽ ለማብረድ ሲል እንደደነበረ የወሰደው ርምጃ ነው” ብለው የሚያስቡም አሉ። እኔ ግን እንደዚያ አላስብም። የማምነው ነገር ቢኖር አማራውን አቅም አልባ ለማድረግ እየወሰዱ ያሉት ቀደም ብሎ የተጠና ዕቅድ እንደሆነ ነው። መጀመሪያ ወልቃይትንና ራያን ከአማራው ለመንጠቅ ሲያስቡ የኦሮሞ ድጋፍ እንዲኖራቸው አዲስ አበባን ጨምሮ እጅግ ሰፊ አካባቢ ለኦሮሚያ ሰጡ፤ በከሚሴና በባቲ የሚኖሩት ኦሮሞወች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በሚል በልዩ ዞን እንዲደራጁ እንዲደረግ ለጉዳይ አስፈጻሚው ብአዴን ትዕዛዝ አስተላለፉ። አማሮች በዛ ብለው በሚገኙባቸው ሌሎች ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ቀርቶ በቋንቋቸው እንዲማሩ፣እንዲዳኙ፣ ይባስ ብሎ እንደወልቃይትና ራያ ባሉት አካባቢወች በቋንቋቸው እንዲናገሩ እንኳ ዕድሉ አልተሰጠም፤ እንዲያውም መሬታችሁን እንጅ እናንተን ስለማንፈልጋችሁ ወደክልላችሁ ሂዱ ተብለው ከሞት የተረፉት እየተፈናቀሉ ግፍ ተፈጸመባቸው እንጂ። ሰው ያልገባው ከምንም በላይ የጎሠኞች የተጠናከረ ትብብር መኖሩን ነው። የሚለያዩት በመለስተኛ ፍላጎቶች ሲሆን ዋና ጠላት ነው ብለው ሁሉም የሚስማሙበት ደግሞ አማራውን ነው። በአንዳንድ ልዩነቶች ሲናቆሩ ይቆዩና አማራው በእግሩ ለመቆም ቻቹ ችግራ/ወፌ ቆመች ለማለት ሲጀምር ልዩነታቸውን ትተው ሁሉም በአንድ ላይ ይነሱበታል፤ ወፌ ቆመች ሳይሆን ወፌ ላላ ነው የሚገባህ ብለው ስቃዩን ያበሉታል። ጎሠኞች እንደውሻ እርስ በርስ ቢነካከሱም ጠላት ነው ብለው የፈረጁት አማራ ላይ ግን ተባብረው ሊያጠፉት ይነሳሉ።

 

ወያኔወች አንድ ነገር ለማድረግ መጀመሪያ መምከር ከዚያ መወሰን፣ ውሳኔውን በሀይልም ቢሆን ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀስ፣ በመጨረሻም የሚቃወሙትን በተለያየ መንገድ ማስታገስ ከተቻለ ሕዝባዊ ጩኸቱ የአንድ ሰሞን ይሆንና ቀስ በቀስ እየተለመደ ይሄዳል የሚሉት ስልት አላቸው። ይህ ስልት ጠላት ነው ብለው የፈረጁትን አማራ አናሳና ከፉክክር የራቀ በማድረግ በሂደት ጭራሹን እንዲጠፋ ያቀዱትን እቅድ ለማሳካት የሚከተሉት የአሰራር ዘዴ ነው።

 

የወቅቱ አማራን የማዳከሚያ ስልታቸው ከአዲስ አበባ ጋር ያለውን ታሪካዊ ቁርኝት ጨርሶ መበጠስ ሆኗል። በዚህም መሰረት በአባቶቻችን ከተማ አማራው እንደሌላ ሀገር ዜጋ እንዲቆጠር ሲደረግ ባለቤት ነው ለተባለው ኦሮሞ ልዩ ጥቅም ሰጠን ብለው አውጀዋል። ብአዴን እንደለመደው ውሳኔውን አብሮ አጽድቋል። የኦነግ ጀሌወች በደስታ ጮቤ እየረገጡ “ገና ብዙ ይቀራል” እያሉ ነው። ዕውነታቸውን ነው፤ ገና ብዙ ይቀራል። የኦሮሞ ድርጅቶች የወያኔ የክፉ ቀን ደራሽ ሆነው የሚቃጣበትን ሁሉ ለመመከት የተቀመጡ ኃይሎች መሆናቸውን ማንም የተገነዘበ አይመስልም። በአንዳንድ ልዩነቶች ተጣላን ብለው በተኳረፉ ጊዜ የኦነግ አመራሮች ወደየሚፈልጉት ሀገር የተጓዙት በቦሌ በኩል ነበር። ውጭ ከወጡ በኋላም በወያኔ ላይ የተባበረ ኃይል እንዳይነሳ የብተና ስራ በመስራት ላይ ናቸው። አንዳንድ የኦነግ አመራሮች እንደነ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚፈለጉ ስላልሆኑ  አሁንም ቢሆን ሰበብ እየፈጠሩ ወደ ኢትዮጵያ ወጣ ገባ ማለታቸውን አላቆሙም።

 

የአማራው ችግር ብዙ ነው። አሁን ደግሞ በዋና ከተማው ባህርዳር ህልውና ላይ ያንዣበበ አደጋ ተከስቷል። አደጋው ለከተማዋ ህይወት የሆነው ጣና በእምቧጮ አረም መወረር እና ሆን ተብሎ ወደሀይቁ በሚለቀቅ ፈሳሽ መበከል ምክንያት የመጣ ነው። ወደሀይቁ የሚፈሰው ቆሻሻና ጎጂ ኬሚካል ሀይቁን ቤታቸው አድርገው በሚኖሩ እንስሳት ላይ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል የሚያጠያይቅ አይደለም። የክልሉ መንግሥት በከተማው ቁጭ ብሎ ይህን ብክለት ለምን ዝም ብሎ እንደሚመለከት የሚታወቅ ነገር የለም። ጣናን የወረረው ባዕድ አረም እንዴት መጣ? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ያለ አይመስለኝም። ቢኖርም አረሙ በሌሎች አካባቢወችም የተከሰተ አመጣጡ በውል ያልታወቀ ነው የሚል ሊሆን ይችላል። ወያኔ በተንኮል ሰይጣንን የሚያስንቅ፣ የሚያስቀና መሆኑን ላልተረዳ የሚናገሩትን ሊያምን ይችላል። አረሙ እንዴት ጣና ላይ ብቻ ተከሰተ የሚል ጥያቄ እንዳያስነሳ በሌሎች ሀይቆች አካባቢም በስሱ በተን አድርገው ጣና ላይ አፍስሰውብን ቢሆንስ! አዎ እንደዚያ ነው! እኛ ጣናን የወረረውን አረም ስናርም እነሱ ደግሞ ሌላ የቤት ስራ ሊሰጡን ይዶልታሉ።

 

ከማን ጋር ነው የሚዶልቱት ቢባል መልሱ ከኦነግና መሰል የጎሣ ድርጅቶች ጋር የሚል ይሆናል። የጎሳ ድርጅቶች የተመሰረቱበት መሰረታዊ ፍላጎት ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ለማስቻል ነው የሚል ቀና የመሰለ ሀሳብ የያዘ ይምሰል እንጂ በውስጡ ተሸፍኖ የተቀመጠ የአማራውን መጥፋት ለማቀላጠፍ ሁሉንም ባለድርሻ የማድረግ እና የአንድነት ኃይሉን ቦታ የማሳጣት እጅግ አደገኛ ሀሳብ አለው። የጎሣ ድርጅቶች አንድ ናቸው ስንል ዝም ብለን ከመሬት ተነስተን አይደለም። በአማራው ላይ የሚደርሰው ማሳደድ እና ግድያ የተለየ እንዳይመስል አልፎ አልፎ የሌሎች ጎሣወች የርስ በርስ ግጭት ቦግ ብሎ እልም እንዲል ይደረጋል። እንዲህ ያለው ነገር በአማራ ላይ ለሚደርሰው መከራ ሽፋን ተብሎ የሚፈጸም የክፋት ስራ ነው። በዚህ ወቅት የሚጠፋው የሌሎች ጎሣ አባላት ህይወት የጠላትን ጦር ለመምታት እንዲያስችል መተላለፊያውን ከፈንጂ በማጽዳት ተግባር ተሰማርተው መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ ወታደሮች የሚቆጠር ነው።

 

አማራው ህልውናውን ለመከላከል ይደራጅ ስንል የዘር ማጥፋትን እንከላከል ማለታችን ነው። በዚህ ያልተደሰቱ ወገኖች አማራ ዘረኛ ሆነ በሚል ከብዙ አቅጣጫ ጦርነት ከፍተዋል። አማራ በዘሩ ከተደራጀ ከወያኔ ምኑን ተለየ ብለው ይከራከራሉ። “የተደራጀነው ራሳችንን ከጥቃት ለመከላከል እንጂ ዘረኛ ለመሆን አይደለም። ለ26 ዓመታት ያህል እንደ አውሬ ስንታደን ማንም የተቆረቆረልን አልነበረም።” ብለው መከላከያ ለሚያቀርቡት አማሮች የሚሰጠው መልስ የአማራው ችግር የሚፈታው የመላው ኢትዮጵያ ችግር ሲፈታ ብቻ ነው የሚል ነው። እኒህ ሰዎች ያልገባቸው ነገር በኢትዮጵያዊነት እንደራጅ ቢሉም የሚቆሙት ብቻቸውን መሆኑን ነው። በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር ብዙሀኑ የሌላ ጎሣ አባላት ያሉት እናት በየሚሏቸው በየጎሣ ድርጅቶቻቸው ውስጥ ነው። በአንድነት ስም ከተሰባሰቡትም መሀል ምን ያህል ተልዕኮ ተሰጥቶት እንደመጣ መገመት ይከብዳል። ጎሰኝነትን አውግዘው ለኢትዮጵያ እንሟገታለን ብለው ከልብ የተሰለፉ የሌላ ጎሣ አባላት ምን ያህል ናቸው? “እዚያ ቤት የሚደረገውን ሂዳችሁ እዩ!” የተባሉትስ?

 

ከዚህ በፊት በነበሩት የአንድነት ድርጅቶች ላይ ምን ደረሰ? ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ መልሱ የአንድነት ድርጅቶች የነፍጠኛውን ስርአት ለመመለስ የሚያልሙ ናቸው ተብለው እንደተወገዙ ነው። እነ መኢአድ፣ አንድነት፣ ቅንጅት እንዲዳከሙ የተደረጉት የነፍጠኛ ስርአት አራማጆች ናቸው በሚል አይደለም? በኢትዮጵያዊነት በተደራጁት ሰላማዊ ድርጅቶች ውስጥ ተመልካችን እንዳይከፋው በሚል አማራው ከአመራር ቦታ እንዳይደርስ ተወስኖ ከታች ሆኖ ቢደግፍም “አማራ የታየበት ሁሉ የተወገዘ ነው” በሚል ስሜት የነፍጠኛ ድርጅት ነው እየተባለ ሲከሰስና በተንኮል እንዲፈርስ ሲደረግ ነው የምናውቀው።

 

በ1997 ዓ ቅንጅት ሲያሸንፍ የነፍጠኛው ስርአት አንገቱን ቀና እያደረገ ነው ተብሎ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ታግለን የስርአት ለውጥ ለማምጣት ነው የተደራጀነው ሲሉ የነበሩት በጎሣ የተደራጁ ተቃዋሚ ኃይሎች ጭምር ክተት እንዳወጁበት መርሳት አይኖርብንም። ሻዕቢያም በበኩሉ በቅንጅት ማሸነፍ ደስታ እርቆት ብዙ ሲቀሰቅስ እንደነበረ የምናስታውሰው ዕውነት ነው። በደርግ ጊዜ ኢሕአፓን ከላይ ሆነው ይመሩት ከነበሩት ውስጥ ዋናውን ቦታ በመያዝም ሆነ በብዛት ከአማራው ይልቅ ትግሬወች ይበልጡ ነበር። ነገር ግን አማሮች ስለታዩበት ነበር በፓርቲው ውስጥ የነበሩትን ትግሬወች የአማራ አሽከር እያሉ ሲያዋርዷቸው የነበሩት፤ ከትግራይ ክልል ውጡ ተብሎ ድርጅቱ ውጊያ የተከፈተበት! እናሳ! ምን ሁኑ ነው የሚባለው? ለአማራው ማን ይታገል? ሳይደራጅ ብትንትን ብሎ ይጥፋ!

እንዲህማ አይሆንም!! እጅና እግሩን አጣጥፎ መከራን መቀበል ሳይሆን ተደራጅቶ እየታገለ መስዋዕት መሆንን ለተተኪወቹ ማውረስ መተኪያ የሌለው የህይወት መድኅን ነው። አማራው የራሱን ልጆች ድምጽ ብቻ ያድምጥ! ጨርሶ ላለመጥፋት መውተርተር የራሱ እንጅ የሌላ የማንም ድርሻ አይደለም። “ለእኛው ያለነው እኛው ስለሆንን ህልውናችንን ለመከላከል እንደራጅ” ብለው የተነሱትን አማሮች ትግላቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ እንቅፋት መፍጠር ሳይሆን መደገፍ የማንም በፍትህ እና በዕኩልነት የሚያምን ዜጋ ሁሉ ኃላፊነት ነው።

 

አንዳንዴ ራሳችን የምናውቀውን ዕውነትም ቢሆን በሌላ ሰው አንደበት ሲነገር ስንሰማው ክብደቱ የበለጠ ሊገለጽልን ስለሚችል በድጋሚ የምክር ሀሳቤን እንድሰነዝር ይፈቀድልኝ። “ብአዴን ውስጥ ያላችሁ አማሮች ልብ ግዙ! ትግሉ እናንተን ጨምሮ መላ አማራውን ነጻ ለማድረግ የሚደረግ ትግል ነው። የአማራ ታጋዮች የናንተን መብት ጭምር ለማስከበር ነው እየታገሉ ያሉት። የነርሱን ትግል መደገፍ የራሳችሁንና የቤተሰባችሁን ህልውና ማረጋገጥ ነው። አማራን ለማጥፋት የሚደረገው ደባ እናንተን የሚምር አይሆንም። በአንድ ወቅት አንድ የሽግግር መንግስቱን ቻርተር በማጽደቅ ሂደት የተሳተፈ ሰው ጋር ስናወራ፦

 

“የድርጅት አባል የሆንሁበትን ቀን መርገም የጀመርሁት በሽግግር መንግስቱ ቻርተር ተሳታፊ በነበርሁበት ጊዜ ነበር። ማንም እየተነሳ ‘አማራ ልብ የለውም። ዱሮም በስልጣን ላይ እንዲቆይ ያስቻለው ጀግንነቱ ሳይሆን ቀድሞ የነቃ ስለነበረ ብቻ ነው። ይህንን ዕውነታ እዚህ ያላችሁት አማሮችም አትስቱትም። አሁን ግን ሁላችንም ነቅተናል’ ሲሉን አለቆቻችንንም በመፍራት በየተቀመጥንበት ወንበር ተሸማቀን ጭብጥ አክለን ነበር የምንቀመጠው። ሁኔታው ሲታይ የአንድን ሀገር ጊዚያዊ መተዳደሪያ ህግ ለማጽደቅ ሳይሆን አንድን ሕዝብ ለመወንጀልና ለማዋረድ ሆን ተብሎ የተሰናዳ ስብሰባ ነበር የሚመስለው። እየነገርሁህ ያለሁት የአንድን ሀገር ጊዜያዊ ሕግ ለማውጣት በተሰበሰበ ከፍተኛ ጉባዔ መባል ያልነበረበትን በእኛ ላይ ያነጣጠረ የብልግና ንግግሮችን ቀንሼ ነው” ብሎኛል ከልቡ እያዘነ።

 

የአማራ ልጆች ተጋድሎ ይህንን ሁሉ ሸክማችሁን ለማቅለልም ስለሆነ በዕኩል ዐይን ታይተን መብታችን እንዲከበር ለሚደረገው ትግል የበኩላችሁን ድርሻ መወጣት ይኖርባችኋል። ይህ ትግል የእናንተ የክብር አካል ነው። የአማራው ትግል ከተኮላሸ በስድብ ብቻ ሳይሆን በአለንጋም እየገረፉ እንደሚያሰሯችሁ ልትገነዘቡት ይገባል። ስለዚህ በመጀመሪያ ድርጅታችሁን ከሰርጎ ገቦች ለማጽዳት ውስጥ ለውስጥ ተነጋገሩ። የእኛ ባልሆኑ ሰዎች አንመራም የሚል ጽኑ አቋም ይኑራችሁ። በረከት ስምዖንም ሆነ ተፈራ ዋልዋ ወይም አዲሱ ለገሰ የታገሉት ለህብረ ብሄራዊ ድርጅቱ ኢሕዴን እንጅ ለአማራው አልነበረም፤ ደግሞም አማራ አይደሉም። ስለዚህ የነርሱን አመራርም ሆነ ምክር አንፈልግም ብላችሁ ከድርጅት አባልነት ሰርዟቸው። ከዚያም በየቀበሌው የማደራጀት፣ በአካባቢ ሚሊሽያ ስም ወታደራዊ ስልጠና የመስጠት፣ የማስታጠቅና የተከፈተባችሁን የዘር ጥቃት ለሕዝባችሁ በማስገንዘብ ራሳችሁን ለመከላከልና በጉልበት የተነጠቃችሁትን ታሪካዊ ይዞታችሁን ለማስመለስ በጽናት መቆም ይገባል። ዛሬ በእጃችሁ ያለውን ዕድል ካልተጠቀማችሁበት ወደፊት እንደምትጸጸቱበት አትጠራጠሩ። አማራነት እኮ መከበሪያም ማስከበሪያም ነው፤ የጥቁር ዘር ኩራት፣ የነጻነት ምልክት፣ የጀግንነት ምሳሌ ነው። ዛሬ በናንተ ጊዜ ከመሬት ወድቆ ማንም ሲረጋግጠው ዝም ብላችሁ ስትመለከቱ፣ ያም አልበቃ ብሏችሁ ከጠላት ወግናችሁ የጥፋቱ ተባባሪ ስትሆኑ በልጅ ልጆቻችሁ እንዴት ትታወሱ ይሆን! አሁንስ ህሊናችሁን አይቆረቁራችሁም! ብትሞቱስ ነፍሳችሁ እረፍት ታገኛለች! “እንዲያው ከምኑ ነው የተፈጠሩት!” መባሉ ብቻውን አያሸማቅቅም!”

 

አዲስ አበባ ፊንፊኔ የሚለው ስም በተለዋጭ ተይዞላታል። መንገዶቿም፣ አደባባይዋም እንደአስፈላጊነቱ ዲማ ነገዎ ጎዳና፣ ሌንጮ ለታ አደባባይ እየተባለ ይሰየምላታል። በአማራ ስም የሚጠሩ ኦሮሞወች ምን እንዳሰቡ አይታወቅም። ወደፊት ዶሮ ግብር ድረስ ያለውን የአማራ መሬት ወደትግራይ ለማካለል ሲታሰብ የኦሮሚያን ድጋፍ ለማግኘት ሲባል የከሚሴ ኦሮሞወች ወደኦሮሚያ መካለል አለብን የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ ይደረግና ቆቦ በጉልበት፣ ከሚሴ የሕዝብ መብት መከበር አለበት በሚል ሽፋን አማራን ይሰናበታሉ። እንዲህ እንዲህ እየተኮረኮመ አማራ ወደነበር ይሸጋገራል።

 

የአማራ ህልውናና መብት የሚከበረው በራሱ ትግል እንጅ በሕገመንግሥቱ አይደለም።  መፍትሄው ቆፍጠን ማለት ነው፤ ንፋስ ሳያስገቡ እጅ ለእጅ ተያይዞ መፋለም ነው። ያን ጊዜ አማራ እንደአውሬ መታደኑ ይቀርና ሁሉም ሰው መሆኑን አምኖ ይቀበላል። አሁን የሚንቀው ሁሉ ያከብረው ይጀምራል። የሚናገረው በቁምነገር ይደመጣል። ከሚሸሸው የሚቀርበው ይበዛል። የያዘው ይበረክታል የሄደውም ይመለሳል።

 

ትንሳኤ ለአማራ!

ትንሳኤ ለኢትዮጵያ!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s