የኢህአዴግ መንግስት ጨካኝ ወይስ ጨቋኝ?

“የእንካ ግን አትንካ ፖለቲካ” በሚለው ፅሁፍ የኢህአዴግ መንግስት ጋዜጠኞችን፥ ጦማሪያን፣ ፀኃፊዎችን፣ የመብት ተሟጋቾችንና ተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎችን በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ አማካኝነት ለእስራትና ስደት እንደሚዳርጋቸው ተመልክተናል። በተመሳሳይ፣ በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞና አቤቱታቸውን ለመግለፅ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ብዙዎችን ለሞት፣ የአካል ጉዳትና እስራት ዳርጓል። ነገር ግን፣ የኢህአዴግ መንግስት በፖለቲካው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ዜጎችን ለሞት፥ እስራትና ስደት የሚዳርግበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው? በተለይ ደግሞ ለአመፅና ተቃውሞ በወጡ ዜጎች ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ የሚወስደው ጨካኝ ወይስ ጨቋኝ ስለሆነ ነው? በመሰረቱ፣ አንድን መንግስት ጨካኝ ወይም ጨቋኝ ብሎ ለመፈረጅ በቅድሚያ የመንግስታዊ ስርዓቱን መሰረታዊ ባህሪ ማወቅ ያስፈልጋል።

የዴሞክራሲያዊ መንግስት ተግባራዊ አንቅስቃሴ የሚመራው በእኩልነት መርህ ነው። የአምባገነን መንግስት ሥራና ተግባር የሚመራው ደግሞ በፍርሃት ነው። አምባገነኖች ሀገርና ሕዝብ የሚመሩት በፍርሃትና በማስፈራራት ነው። በመሆኑም አምባገነን መሪዎች ያለ ፍርሃት ሀገርና ሕዝብን ማስተዳደር አይችሉም። “ለምን?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በቅድሚያ ስለ መንግስት አፈጣጠርና ዓላማ የተወሰኑ ነጥቦችን እንመለክት።

በተወሰነ አከባቢ የሚኖሩ ሰዎች (ሕዝቦች) የራሳቸውን መንግስት የሚመሰርቱበት መሰረታዊ ምክንያት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው በሕግና ስርዓት እንዲመራ ለማድረግ፣ በዚህም የሁሉም ዜጎች መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት የጋርዮሽ ስርዓት እንዲኖር ለማስቻል ነው። በዚህ መሰረት፣ የመንግስት ድርሻና ኃላፊነት የሁሉንም ዜጎች መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ለማክበርና ማስከበር የሚያስችል አስተዳደራዊ ስርዓት መዘርጋት ነው። ለዚህ ደግሞ አስፈላጊ የሆኑ አዋጆችን፥ ደንቦችንና መመሪያዎችን ማዘጋጀት፣ የሁሉንም ዜጎች መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራና አሰራር መዘርጋት፣ የአፈፃፀም ሂደቱን መከታተልና ማሻሻል አለበት።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የአንድ መንግስት መሰረታዊ ዓላማ የሁሉም ዜጎች መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ፖለቲካዊ ስርዓት መዘርጋት ነው። ስለዚህ፣ የመንግስት ስራና አሰራር በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ከዚህ አንፃር፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከመንግስት መሰረታዊ ዓላማ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ስለመሆኑ መገንዘብ ይቻላል። ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት በተለየ አምባገነናዊ ስርዓት የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም፣ የአምባገነናዊ መንግስት ከእኩልነት ይልቅ በፍርሃት የሚመራው ነው።

የአምባገነን መንግስት ስራና አሰራር የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን መብትና ነፃነት የሚያረጋግጥና የተሻለ ጥቅምና ተጠቃሚነት እንዲኖረው የሚያስችል ነው። ይሁን እንጂ፣ እያንዳንዱ ሰው በተፈጥሮ ከሌሎች ሰዎች እኩል የመሆን፥ በእኩል አይን የመታየት ፍላጎት አለው። ስለዚህ፣ የተወሰኑ ሰዎችን፥ ቡድኖችን ወይም ማህብረሰብን ከሌሎች የበለጠ ወይም ያነሰ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፖለቲካዊ ስርዓት ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር ይቃረናል። ስለዚህ፣ ዜጎች የአንድን ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ከተመሰረተው ፖለቲካዊ ስርዓት ጋር መሰረታዊ ቅራኔ አላቸው። በመሆኑም፣ በአምባገነናዊ መንግስት የምትመራ ሀገር ዜጎች በተለያየ ግዜና አጋጣሚ ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ ይወጣሉ።

ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ የሚቀሰቀሰው “ከሌሎች “እኩል” መብትና ነፃነታችን ይከበር፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ይኑር” በሚል እሳቤ ነው። በዚህ መሰረት፣ የአመፅና ተቃውሞ ዓላማ የእኩልነት ጥያቄ ነው። በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በአመፅና ተቃውሞ ለሚነሳ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅምና አሰራር ይኖረዋል። የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ አምባገነናዊ ስርዓት ግን የእኩልነት ጥያቄን ለመቀበልም ሆነ ለማስተናገድ የሚያስችል አቅም አይኖረውም።

በመሰረቱ፣ በአመፅና ተቃውሞ አማካኝነት የሚነሳው የእኩልነት ጥያቄ የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ለማስቀረት ዓላማ ያደረገ ነው። ነገር ግን፣ በአምባገነናዊ ስርዓት ውስጥ በዚህ መልኩ የሚነሳ የእኩልነት ጥያቄን ማስቀረትም ሆነ ማስተናገድ አይቻልም። የእኩልነት ጥያቄ ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር የተቆራኘ እንደመሆኑ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞን ማስቀረት አይቻልም። በተመሣሣይ፣ የአምባገነናዊ መንግስት መሰረታዊ ዓላማ የአንድን ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደመሆኑ የእኩልነት ጥያቄን ተቀብሎ ማስተናገድ አይችልም። ስለዚህ፣ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በሰው ልጅ እና የአምባገነናዊ መንግስት ተፈጥሯዊ ወይም መሰረታዊ ባህራያት መካከል የተፈጠረ ግጭት ማለት ነው።

በአመፅና ተቃውሞ አማካኝነት በሚፈጠረው ግጭት ከዜጎች እና ከአምባገነን መንግስት አንዱ ወገን ተፈጥሯዊ ባህሪውን ያጣል። ተፈጥሯዊ ባህሪውን ያጣ ማንኛውም ነገር ሕልውናው ያከትማል። ስለዚህ፣ በአመፅና ተቃውሞ ምክንያት ወይ ዜጎች የሕይወትና አካል ጉዳት ይደርስባቸዋል፣ ወይም አምባገነኑ መንግስት በግድ ተቀይሮ ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ወይም ይወድቃል። በዚህ መሰረት፣ ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች እና በአምባገነን መንግስት መካከል የሚፈጠረው ግጭት ሕልውናን በማረጋገጥ ወይም በማጣት ውጥረት ውስጥ የሚካሄድ ነው።

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ አምባገነን መንግስት ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ በመውሰድ በሰላማዊ ዜጎች ሕይወት፥ አካልና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። ለዚህ ደግሞ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች አሉ። አንደኛ፡- የእኩልነት ጥያቄ ለአምባገነናዊ ስርዓት የሕልውና አደጋ እንደመሆኑ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞን በጣም ይፈራል። ሁለተኛ፡- ያልተመጣጠነ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ከፍተኛ ፍርሃትና ሽብር መፍጠር በሌላ ግዜና ቦታ ተመሳሳይ አመፅና ተቃውሞ እንዳይቀሰቀስ ያደርጋል። በአጠቃላይ፣ የእኩልነት ጥያቄ በሚያነሱ የሕብረሰብ ክፍሎች ላይ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ የሚወስደው በፍርሃትና ለማስፈራራት ነው። ለምሳሌ ባለፈው አመት በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍና በመንግስት የተወሰደው እርምጃ እንደማሳያ ሊጠቀስ ይችላል፦

ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ በመውሰድ በዜጎች ሕይወት፥ አካልና ንብረት ላይ ከፍጠኛ ጉዳት የሚደርሰው የኢህአዴግ መንግስት በራሱ ስለሚፈራና ሕዝብን መስፈራራት ስለሚሻ ነው። ይህ የሆነበት መሰረታዊ ምክንያት ደግሞ መንግስታዊ ስርዓቱ የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው። ስለዚህ፣ የኢህአዴግ መንግስት በዜጎች ላይ የጭካኔ እርምጃ የሚወስደው ጨቋኝ ስርዓት በመሆኑ ነው።

ቁርጥ ግብር – የህውሓት ገጀራ (ካሳ አንበሳው)

ካሳ አንበሳው

Streetside fruit and vegetable store or shop Addis Ababa

የሰሞኑ የማህበራዊ ሚዲያ አጀንዳ አዲስ አበባ ውስጥ በአነስተኛ የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች ላይ የተጣለው ከፍተኛ “ግብር” ነው፤ ይህ ግብር “ቁርጥ ግብር” ወይንም “Presumptive tax” በመባል ይታወቃል፤ “ቁርጥ ግብር” ታማኝ ያልሆኑ ዜጋ የሚቀላበት (የሚወገድበት) ሎሌ የሚተከልበት የህውሓት አንዱ  ስውር ገጀራ ነው:: ይህ ገጀራ ከወያኔ የዕዝ ሰንሰለት ውጭ በንግድ ተሰማርተው የተገኙትን ዜጎች ይቀስፋል፤ የወያኔ ዕዝ <<የህብረት ስራ ማህበራት፣ ጥቃቅን እና አነስተኛ  ኢንተርፕራይዝስ ወ.ዘ.ተ>> በሚባሉ ስያሜዎች የሚታወቁት ናቸው፤ የወያኔ ገጀራው ከሰገባው የሚመዘዘው በአመት አንዴ ነው፤ ብዙ ዜጎችን ሙት እና ቁስለኛ ሳያደርግ ወደ ሰገባው አይመለስም፤ የዚህ ገጀራ ሰለባ ከሆኑት መካከል ጋሽ መሐመድ ሐሰን አንዱ ናቸው::

ጋሽ መሐመድ የአካባቢውን ነዋሪ ልብስ በማጥበብ፣ በማሳጠር እና በመጠገን ስምንት ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ታታሪ ዜጋ ናቸው፤ ከልጅነት እስከ እውቀት የማውቃቸው በዚህ ሙያቸው ነው፤ አንድ ክፉ ቀን የህውሓት እጅ የጋሽ መሐመድን ሱቅ በርቅሳ ግድግዳው ላይ <<ማኔን፣ ቴቄል፣ ፋሬስ> ብላ ጻፈች፤ <<መዘንኩህ (በታማኝነት ሚዛን) ቀለህም ተገኝህ፣ ሱቅህም ለታማኝ ሎሌ ተሰጠች>> ስትል ነው፤  ጋሽ ማሜ ሰምተውት እንጂ አየተውት የማያውቁትን ገንዘብ እንዲከፍሉ ተጠየቁ፤ 5 ሺህ ብር! ጋሽ መሐመድን ብዙም አልደነገጡም፤ ባለመረበሻቸው የተገረሙ ወዳጅ እና ዘመዶች ጠጋ ብለው ሲጠይቋቸው ለሁሉም የሚሰጡት መልስ ተመሳሳይ ነው፤ <<5 መቶ ቢሉኝ ከልጆቼ ጉሮሮ ነጥቄ፣ ተበድሬ ወይም እቁብ ገብቼ  ለመክፍል በደከምኩ፤ አላህ ይስጣቸውና 5 ሺህ ብር ብለው ከዚህ ሁሉ ድካም ገላገሉኝ>> ይላሉ:: ጋሽ ማሜ መሰዋት ሆኑ!

ሌላው የህውሓት ቆንጨራ <<የሙያ ብቃት ማረጋገጫ>> በሚባል ይታወቃል፤ እንጀረ በመጋገር የምትተዳደር አቅመ ደካማ እናት ሳትቀር በህውሓት ሰራዊት <<የሙያ ብቃት ማረጋገጫ>> ስለሌለሽ አክንባሎሽን ስቀይ መባሏ የቅርብ ቀን ትዝታ ነው፤ እንግሊዘኛ ተናገር የተባለ ጊዜ ምላሱ ከትናጋው የሚጣበቅበት ካድሬን (ጸጋዬ በርሄን መጥቀስ ይቻላል) ባለ ሙሉ ስልጣን አንባሳደር አድርጋ የምትሾም ህውሓት አንድን እናት የእንጀራ ጋገራ  የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ካላመጣሽ ምጣድሽን እሰብራለው ማለቷ ግርምታን ያጭራል::

ለቱርክ፣ ለሳውዲ፣ ለህንድ እና ለሎች የውጭ ሃገር <<ባለሃብቶች>> ከሊዝ ነጻ መሬት፣ 70% ብድር እና የአምስት አመት የትርፍ ግብር እፎይታ አዘጋጅታ “ኑ” << ሙሉሄ በኩሉሄ>> የምትለው ወያኔ ምነው ዜጎች ላይ እንዲህ ጨከነች? ጎዳና ላይ አንጥፎ አልያም መስኮት ቀዶ ጉሮሮውን ለመድፈን የሚወተረው ዜጋ ላይ ምነው ልቧ ደነደነ? ብሎ መጠየቅ ተበጊ ነው፤ አጭሩ መልስ <<የኢኮኖሚ ነጻነቱ የተደፈጠጠበት ህዝብ ቢጭኑት አህያ ቢጋልቡት ፈረስ እንደሆነ ስለምትረዳ፤ የኢኮኖሚ ነጻነቱ ዲሞክራሲያዊ መብትን እንደሚያስከትል ጠንቅቃ ስለምታውቅ>> የሚል ይሆናል:: በዚሁ ወደ ፍሬ ጉዳያችን (የኢትዮጵያዊያንን የኢኮኖሚ ነጻነት ያለበትን ደረጃ ወደ መዳሰሱ) እንዝለቅ::

የኢኮኖሚ ነጻነት (Economic Freedom) ዜጎች በፖለቲካ አመለካከት፣ በዘር (በጎሳ ወይም ብሄር)፣ በሃይማኖት ወ.ዘ.ተ አድሎ ሳይደረግባቸው በነጻነት፣ በመረጡትና በፈለጉት የኢኮኖሚ መስክ እንዲሰማሩ (እንዲሳተፉ) የሚያስችል የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ማዕቀፍ ነው::

የዜጎች የኢኮኖሚ ነጻነት በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 41 “የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህላዊ መብቶች” ውስጥ የተካተት ቢሆንም በሃገራችን ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት እጦት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ:: ይህንን ከሚጠቁሙት መረጃዎች መካከል ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን (Heritage Foundation) እና የዎል ስትሪት ጆርናል (The Wall Street Journal) በተባሉ ተቋማት ከ1995 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ በየአመቱ የሚወጣው የኢኮኖሚ ነጻነት ደረጃ (Economic Freedom index) ሪፖርት ዋነኛው ነው:: ይህ አህዛዊ መለኪያ የሚያመለከተው ዜጎች በሃገራቸው ውስጥ በነጻነት (በምርጫቸው)፣ ያዋጣኛል ባሉት የኢኮኖሚ መስክ ሃብታቸውን እና እውቃታቸውን ተጠቅመው (ሌሎች ዜጎችም ይህንኑ የማድረግ መብታቸውን ሳይጋፉ) የማምርት፣ የመሽጥ እና የመለወጥ መብትን ነው::ከስር ከተመለከተው ከግራፉ ማየት እንደሚቻለው በ2013 እና 2014 (እ.ኤ.አ.) ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጭቆና ካለባቸው ሃገራት ውስጥ ተካታለች::

በቅርቡ ይፋ የሆነው የ2017 (እ.ኤ.አ). ይህ የሃገራት የኢኮኖሚ ነጻነት ደረጃ ሪፖርት ኢትዮጵያን ከዓለም 142ኛ፤ ከሰሃራ በታች ካሉ 46 የአፍሪካ ሃገራት ደግሞ 31ኛ አስቀምጧታል:: በዚህ ሪፖርት ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ነጻነት ከሌለባቸው ሃገራት ውስጥ ተካታለት:: ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ሙስና ሲሆን ሌላው ደግሞ መድሎ እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል:: ሪፖርቱ የመንግስት ባለስልጣናት በከፍተኛ ሙስና ውስጥ የተዘፍቁ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ ብድር፣ የመስሪያ ቦታና የስራ ቅጥር የሚያገኙት የገዥው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች መሆናቸውን አስቀምጧል::  “በመንደር ለማሰባሰብ” (Villagization) እና <<ለልማት>> በሚሉ ሰንካላ ምክንያቶች በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ያለፍላጎታቸው ከቀያቸው እንዲነሱ መደረጉ ኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ነጻነት ከሌላባቸው ሃገረት ተርታ ያሳለፍት ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ይሄው ሪፖርት ያትታል:: ሪፖርቱ በመንግስት የተጣለው የግብር አይነትና መጠን የዜጎችን የመስራት፣ የመቆጠብና ኢንቨስት የማድረግ አቅምንና ፍላጎትን በከፍተኛ ደረጃ የሚፍትን መሆኑን በመጥቀስ ይህም ሃገሪቷን የምጣኔ ሃብት ነጻነት ከሌላቸው ሃገራት ግርጌ እንድትሰለፍ ማድረጉን ያብራራል::  ይህ ሪፖርት የግብር ስርዓቱ የዜጎችን የኢኮኖሚ ነጻነት ይጻረራል ሲል የሚጠቅሰው የስራ ቅጥር ግብር ጣሪያ 35% እና የንግድ ስራ ትርፍ ግብር 30% መሆኑን ጠቅሶ ነው:: ይህንን ሪፖርት ያወጡት ተቋማት ሰፋ ያለ ጥናት አድርገው ቢሆን ኑሮ ውጤቱ ከዚህ እጅጉን የከፋ ይሆን እንደነበር አያጠራጥርም:: ለምሳሌ ያክል በቁርጥ ግብር ስርዓት (Presumptive taxation system) በአነስተኝ የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች ቆጥረውት አይደለም አይተውት የማያውቁትን የገንዘብ መጠን በግብር መልክ እንዲከፍሉ እንደሚጠየቁ፤ በዚሁም ምክንያት ንግዳቸውን ለመዝጋት እንደሚገደዱ፤ መንገድ ዳር ጫማ በመጥረግ የሚተዳደሩ ዜጎች ጭምር በወር 12 ብር እንደሚከፍሉ (እንደሚቀሙ)በሌላ በኩል ደግሞ እነ ሃጎስ ከቀረጥ ነጻ ወደ ሃገር ቤት ያስገቧቸውን የኮንስትራክሽን ማሽኖች ለመንግስት ፕሮጀክቶች ሳይቀር በሰዓት እስከ 1,000 ብር በነጭ ወረቀት እያከራዩ በግብር መልክ የሚከፍሉት ሰባራ ሳንቲም እንደሌለ ግንዛቤ ውስጥ አልገባም:: ይህቺ ናት ኢትዮጵያ!

Ethiopia, Freedom Trend

ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን እና የዎል ስትሪት ጆርናል በጣምራ ከሚሰሩት ጥናት በተጨማሪ ለጀርመን የልማት ተቋም በዶ/ር ቲልማን አልቴንበርግ (Tilman Altenburg) ተጠንቶ “Industrial Policy in Ethiopia” በሚል ርዕስ 2010 እ.ኤ.አ. የታተመው ጽሁፍ መደምደሚያ ላይ ከደረሰባቸው ነጥቦች አንዱ የሚከተለው ነው::

“Business and politics are still strongly entwined in Ethiopia…………… party-affiliated endowments have taken many of the business opportunities left for private engagement. It is not always clear to what extent political considerations reflect the business strategies of those firms, and vice versa.” (pp. 29).

“በኢትዮጵያ ንግድ ስራና ፖለቲካ እርስ በርስ ተወታትበዋል……………….. የግል ኢንቨስተሮች ሊሰማሩባቸው የሚገቡ (የሚችሉ) አብዛኞቹ የስራ ዘርፎች በፖለቲካ ፓርቲዎች የንግድ ድርጅቶች ተይዘዋል፤ የነዚህ በፖለቲካ ፓርቲዎች የሚተዳደሩት የንግድ ድርጅቶ ስትራቴጂ ነው የፖለቲካ ውሳኔን የሚቀድመው (የሚወስኑት)? ወይንስ የመንግስት ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው የንግድ ድርጅቶችን ስትራቴጂ የሚወስነው? የሚለው ብዙ ጊዜ ግልጽ ሁኖ አይታይም:: ” (ገጽ 29)
ይሄው ጥናት እንደሚያመለክተው ሼክ መሃመድ አላሙዲንን ጨምሮ የተወሰኑ ባለሃብቶች ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በንግድ ሽርክና እና ሎሎች እንዲህ ነው ተበለው ሊጠቀሱ በማይችሉ (ለህዝብ ግልጽ ባልሆኑ) ጥቅማጥቅሞች መተሳሰራቸውን ጠቅሶ እነዚህ አካለት ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል የበለጠ የኢኮኖሚ ነጻነት እንዳላቸው ይገልጻል::

“Business, Politics, and State in Africa: Challenging the Orthodoxies on Growth and Transformation” በተሰኝው መድብል ውስጥ ተካቶ “Ethiopia: Rent-seekers and Productive Capitals” በሚል ርዕስ የወጣው የቲም ኬልሴል (Tim Kelsall) ጥናት ከላይ የተጠቀሰውን የቲልማን አልቴንበርግን መደምደሚ ያጠናክረዋል:: የቲም ጥናት የህውሓት ንብረት የሆነውን የEFFORT አመሰራረትና ሂደት በስፋትና በጥልቀት ከተነተነ በኋላ EFFORTትን በተለየ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች አይወሰኑም ማለት አይቻልም ሲል ይደመድማል:: ለቲም ከልሴል ጥናት ማረጋገጫ የሚሆነው የዛሬ ሶስት የአመት ገደማ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ነው:: በዚህ ቃለ መጠይቅ በዛን ወቅት የEFFORT ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ወ/ሮ አዜብ መስፍን “መለስ ከመሰዋቱ በፊት የአምስት ዓመት የትግራይ ኢንደስትሪ በEFFORT እንዴት መፈጸም እንዳለበት የጻፍው ስትራቴጂ ነበር” ማለታቸው ፖለቲካዊ ውሳኔዋት ለEFFOR እና EFFORትን ለመሳሰሉ ተቋማት ያደሉ ናቸው ወደሚለው መደምደሚያ ይወስዳል::

በሌላ በኩል አክሴል ቦርችግሪቪንክ (Axel Borchgrevink) የተሰኙ ምሑር “Emerging Economies and Challenges to Sustainability: Theories, Strategies, Local Realities” በተሰኘው መድብል “Ethiopia: Rapid and Green Growth for All?” በሚል ርዕስ በ2014 እ.ኤ.አ. ባሳተሙት የጥናት ጽሑፍ ገዥው ፓርቲ የሚከተለውን የኢኮኖሚ ሞዴል ዜጎችን በእኩል ደረጃ ተሳታፊ ማድረግ እንደተሳነው አሳይተው ይህም በዜጎች መካከል ያለውን የገቢና የሃብት ልዩነት እንዳሰፋው አትተዋል::

ከላይ ከተጠቀሱት ጥናቶች መረዳት እንደሚቻለው የገዥው ፓርቲ፣ የመንግስት ባለስልጣናትና ደጋፊዎች በተሰማሩበት የንግድ ዘርፍ በነጻ ገበያ ስርዓት ተወዳዳሪ ሆኖ መዝለቅ አዳጋች ነው:: በገዥው ፓርቲ ስር ለተሰበሰቡት ነጋዴዎች የሚደረግላቸውን የተለየ መድሎን ተቋቁሞ ገበያ ውስጥ መዝለቅ የቻለ ነጋዴ የፖለቲካ ስልጣንን ተገን ባደረገ አሻጥር (የግድያ ዛቻንና እስርን ይጨምራል) ከገበያ እንዲወጣ ይደረጋል:: ይህ አይነት ፖለቲካዊ ደባ ከተፈጸመባቸው ባለሃብቶች መካከል የኢተዮጵያ አማልጋ ሜትድ ሊሚትድ ባለቤት የነበሩትን አቶ ገብረየስ ቤኛን መጥቀስ ይቻላል:: አቶ ገብረየስ ተሰማርተውበት የነበረው ዋነኛው የንግድ መስክ በአሁኑ ወቅት በገዥው ፓርቲ ድርጅቶች (ጉና፣አምባሰል፣ ወንዶ እና ዲንሾ) በሞኖፖል የተያዘው የማዳበሪያ ንግድ ነው:: አቶ ገብረየስ ቤኛ በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ESAT) ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለ መጠይቅ በፖለቲካ አሻጥር ለ1 ቢሊዮን 700 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ተዳርገው በመጨረሻም የሃሰት ውንጀላ እና ዛቻ በመበርታቱ ንግዳቸውን ዘግተው በስደት ይኖሩባት ወደነበረችው አሜሪካ መመለሳቸውን አስረድተዋል::

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት የኢኮኖሚ ነጻነት የግለሰብን ብሎም የማህበረሰብንና የህዝብን ገቢና የኑሮ ደረጃን በየውቅቱ እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጾ ያደርጋል:: የኢኮኖሚ ነጻነት በተከበረበት ሃገር ዜጎች ለስራ ቅጥር የሚታጩት በትምህርት ደረጃቸው፣ በስራ ልምዳቸውና በችሎታቸው ነው:: ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ነጻነት በታጣበት ሃገር ዜጎች ለስደት ይዳረጋሉ:: የዜጎቻችንን ህይወት እየቀጠፍ ላለው ስደት ዋነኝው ምክንያት የኢኮኖሚ ነጻነት እጦት መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው:: የስርዓቱ ባለስልጣናት “ለዜጎች ሰደት መንስሄው የግንዛቤ እጦት ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርቶ መቀየር ይቻላል” ሲሉ ድንበር በማቋረጥ ላይ ያሉ ዜጎች በበኩላቸው “ሃገራችን ውስጥ ሰርተን መቀየር ይቅርና በነጻነት ሰርተን መብላት አልቻልንም” በማለት ያማርራሉ:: የጀርመን ራዲዮ የአማረኛው ፕሮግራም ክፍል “መፍትሄ የሚያሻው የስደት አባዜ” በሚል ርዕስ ጥቅምት 28, 2008 ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ተሳታፊ የነበሩት ከሳውዲ ተመላሽ ኢትዮጵያዊ ይህንኑ ነው ያረጋገጡት::

የኢኮኖሚ ነጻነት ባልተረጋገጠባት ሃገር ህዝቦች በእኩልነት ተሳታፊና ተጠቃሚ የሆኑበት ልማት ሊመጣ አይችልም:: የዜጎች የኢኮኖሚ ነጻነት ባልተከበረበት ሃገር ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች (ነጻነቶች) ይከበራሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው:: እንደዘርፉ ምሁራን ገለጻ ኢኮኖሚውን የተቆጣጠረ እና የህዝቦችን የኢኮኖሚ ነጻነት የደፈጠጠ መንግስት የህዝብን ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ጭምር እንደተቆጣጠረ ይገልጻሉ:: ዜጎች በፖለቲካ ፓርቲ አባልነታቸውና ደጋፊነታቸው ሥራ የሚቀጠሩ፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው ከሥራ የሚሰናበቱበት ሃገር ሰባዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ይከበራል ተብሎ አያታሰብም:: ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን ከገዥው ፓርቲ የንግድ ድርጅቶች (ከጉና፣አምባሰል፣ ወንዶ እና ከዲንሾ) ብቻ እንዲገዛ የተገደደ ገበሬ የልቡን ይናገራል ተብሎ አይጠበቅም:: የኢኮኖሚ ነጻነት የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዳይሽራረፉ የሚረዳ ትልቁና ዋነኛው መደላድል ስለሆነ ፖለቲካኞችም ሆኑ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች እና ተቋማት ለዜጎች የኢኮኖሚ ነጻነት ቅድሚያ ሰጥተው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል::

Facebook page: https://www.facebook.com/kassa.anbessaw.733

እፉኝቶቹን ተሸክመን የመጓዝ ግዴታ የለብንም – መስቀሉ አየለ

አጼ ኃይለስላሴ በአንድ ወቅት ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር። ወቅቱ የፓን አፍሪካኒዝም ስሜት ጣራ የነካበት፤ ባሪያ ፈንጋዮቹ አፍሪካን ጥለው መፈርጠጥ የጀመሩበት፣ አፍሪካውያን በንስሮቹ ባለራእይ ወጣት መሪዎች ኩዋሚ ንክሩሁማን፣ ጁሊየስ ነሬሬ፣ ጆሞ ኬንያታ ወዘተ መመራት የጀመሩበት፣ ለሶስት ሺህ ዘመን የአፍሪካ ሳይሆን የመካከለኛው ምስራቅ አካል ሆና ታሪኳን፣ ወግ፣ ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖቷን ጭምር ከቤተ እስራኤል ስትዋረስ የኖረችው አገራችን ለመጀመሪያ ግዜ ፊቷን ወደ ጎረቤት አፍሪካውያን የመለሰችበት እና ይልቁንም በባርነት ለኖሩት አፍሪካውያን የነጻነት ቀንዲል በመሆን የአፍሪካ ህብረትን በመናገሻዋ ያኖረችበት በዚህም እስከ ካረቢያን ያሉ አገሮች ሳይቀር ባንዲራችንን ባንዲራቸው እስከማድረግ የሔዱበት ወርቃማው የአፍሪካውያን ትንሳኤ ዘመን ነበር አስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ ፤

አንድ በሁኔታው የተደመመ የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ ንጉሱን እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ “ለመሆኑ ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? ”
እርሳቸውም ቆፍጠን ባለ አነጋገር “ኢትዮጵያዊነት ኩራትና ትህትና ነው” አሉት።
ጋዜጠኛውም ቢሆን የዋዛ አልነበረምና “ይቅርታ ያድርጉልኝ ጃንሆይ ይሄ ሃምብልነስ እና ፕራውድነስ የሚሉት ነገር እራስ በርሱ የሚጣረስ ማንነት አይመስልዎትም ወይ” የሚል ጥያቄ ያስከትላል። ንጉሱም እንዲህ አሉ፤ “አየኽ አንድ በጣም ተራ የምትለው ገበሬ ቤት በእንግድነት ብትሄድ ያለውን እራት አብልቶ፣ እግርህን አጥቦ፤ ያጠበውን እግርህን ስሞ፣ አልጋውን ላንተ ለቆ እርሱ ግን መሬት ላይ ይተኛል። በዚያው ልክ በሚስቱና በርስቱ ላይ ብትመጣበት ደግሞ በግንባርህ ላይ ጥይት ይቆጥርለሃል፤ ስለዚህ አይጋጭም፤ ነገር ግን ይሄንን ነገር ለመረዳት አንተ ራስ ህ ኢትዮጵያዊ መሆን አለብህ” ነበር ያሉት።

የዘመኑ ጭንጋፎች ነፍጠኛ የሚሉት እንዲህ አይነቱን ስነ ልቦና ነው። ጻድቁ ፕሮፌሰር አስራት “ነፍጠኛ ነኝ፤ ሃኪም ነኝ፤ አውሮፕላንም አበራለሁ” ሲሉ ገና በጠዋቱ አፈፍ ብለው የተነሱት የዘፈን ዳርዳሩ ስለገባቸው እንደነበር ዛሬ ላይ ቆሞ ወለል ብሎ የማይታየው የለም። ወንጀል ሆኖ ዋጋውን በህይወት ያስከፈላቸው ይሄው በውስጣቸው የተጻፈው ኪዳን ነበር።ክርስቶስ በደሙ ዋጋ ቤተክርስቲያንን እንዳነጻት ሁሉ ይህ በነፍጠኛው ደም የተጻፈው ኪዳን አገሪቱን ከነሙሉ ታሪኩዋና መንፈሳዊ እሴቷ ጠብቆ ለማቆየት የተከፈለው ዋጋ ነው። የዚህች አገር እጣ ፋንታም የሚያሳስበው፣ እዳዋም ከትከሻው የማይወርደው ይኼው የባለቤትነት ውርስ ነው።ምንም እንኳን ዛሬ ከውጭ ከመጣ ወራሪ መንጋ ጋር እያበሩ ይኽችን አገር ሲያደሙ የኖሩት የባንዳ ልጆች የቀዝቃዛውን ጦርነት ማለቅ ተከትሎ የደፈረሰው የታሪክ ወንዝ አምጥቶ አራት ኪሎ አምጥቶ ስለደፋቸው አገሪቷን ለመበቀል ከመቸውም ግዜ በላይ የተሻለ እድል ማግኘታቸው እሙን ቢሆንም ቅሉ ከነሱ የረጅም ግዜ ክፉ ምኞት በላይ ትልቁ ማነቆ የሆነው ግን ዛሬም ድረስ ከክህደት ታሪካቸው ባለመማር እነዚህ የእፉኝንት ልጆች በግድ ኢትዮጵያዊ አድርገን የመቀጠላችን ኩነት ነው።

ለመሆኑ ኢትዮኦጵያዊነት ለዚህ ትውልድ ምንድን ነው?

ኢትዮጵያዊነት እንጀራ መብላት ከሆነ ዛሬ አበሻ በተሰደደበት አገር የጤፍ እንጀራውም ተሰዶ ከቤጂንግ እስከ ሳንፍራንሲስኮ ከኖርዌይ እስከ ደቡብ አፍሪካ የውጭው አገር ዜጋም እየለመደው ነው። አገርኛ ቋንቋ መናገር ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው ያደጉ ብዙ አርመኖች፣ ግሪኮችና የዛሬ ኤርትራውያን ኢትዮጵያዊ ሆነው አልቀጠሉም። ይልቁንም ኢትዮጵያ ብትሞት ሌላ አገር አላቸውና። ኢትዮጵያ ውስጥ ትንሽ ህንጻ ማቆም የኢትዮጵያዊነት መለያ ቢሆን ቢሆን ኖሮ ጣሊያን የተሻለ ኢትዮጵያዊ ይሆን ነበረ። ኢትዮጵያዊነት ማለት የዚህችን አገር ህመም መታመም ነው። በደስታዋ መስከር ነው። ለክብሯ መሰዋት ነው። በስሟ ማህሌት መቆም፣ጸሎተ እጣን ማሳረግ ነው። በዚህ ስሌት ከሄድን የተከዜ ማዶ ተውሳኮች እጣ ፋንታ ግልጽ ነው። በዚህች አገር ወርድና ቁመና ስር ሊገቡ የማይቻላቸውን እኒህን ጋንግሪኖች ይዞ በታሪክ ስም መገዝገዙ ሊበቃን ይገባል።ኖረው ቀርቶ ሞተው እንኳን መቃብራቸው ላይ የሚበቅለው እሾን ምን ያህል ጋሬጣ እየሆነ እረፍት እንደሚነሳ መለስ ዜናዊ ከተባለ ልቡሳነ ስጋ ያየነው ሃቅ ነው። ታሪክ ማለት እንደነዚህ ካሉ የደደቢት ተውሳኮች ጋር “አብሮ መኖር” ከሆነ ታሪክ ገደል አባቱ ይግባ።

የአፍሪካ ሕብረት ለሁለት የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች መታሠቢያ ሃውልት ሊያቆም ነው

29ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ለቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴና ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመታሰቢያ ሃውልት እንዲቆምላቸው መወሰኑ – ተገልጿል፡፡

ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት እንዲሁም ለአፍሪካ ሕብረት መጠናከር በየወቅቱ ላደጉት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ነው ለቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች እውቅናው እንዲሰጥ መወሰኑ የተገለፀው፡፡ የዕውቅናው ሃሳብ ያቀረቡት የጋናው ፕሬዚዳንት ናና ኩፉ ኦዶ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ስለተሰጠው እውቅና ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ ተከታዩን ብለዋል፡፡

 

” ነጭ ኑግ ጥቁር ወተት ውለዱ ” 25 አመታት የሌላውን ሁሉ ውጣ የማትጠረቃው ክልል! ! [ቬሮኒካ መላኩ]

ትናንት ነበር ሌላም ጊዜ እንደማደርገው ለአመታት የጆሮዬ ጓደኛ የሆነውን የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ሰአቱን ጠብቄ ከፍቸው ነበር። የእለቱ የራዲዮ ፕሮግራሙ አስተዋዋቂ ” አድማጮቻችን በዛሬው የፕሮግራማችን ሁለተኛ ክፍል ላይ ኢትዮጵያ በኤርትሪያ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ በትግራይ ክልል እየፈጠረ ያለውን ችግር የሚያስረዱ ሁለት እንግዶች ስለሚቀርቡ ይሄን ዝግጅት እንድታዳምጡ እንጋብዛለን> > በማለት ፕሮግራሙን አስተዋወቀ።
እኔም ሰአቱን ጠብቄ ፕሮግራሙን መከታተል ጀመርኩኝ ።

የፕሮግራሙ አዘጋጅ የሆነችው አንጋፋዋ ጋዜጠኛ አዳነች ፍስሃዬ ስትሆን የጋበዘቻቸው ሰዎች ደሞ ከወደ ትግራይ እንደሆኑ በሚናገሩት አማርኛ በደንብ መረዳት ይቻል ነበር። ሲጀመር ይሄ ፕሮግራም መቅረብ የነበረበት በቪኦኤ የትግርኛ ፕሮግራም ነበር በአማርኛው ክፍለ ጊዜም ይቅረብ ከተባለ ቢያንስ አንድ አይነት አመለካከት ፣አንድ አይነት አስተሳሰብ ያላቸውን እንግዶች ከማቅረብ በጉዳዩ ላይ የተለየ አመለካከት ያላቸው እንግዶች ቢቀርቡ ፕሮግራሙን ሚዛናዊ ማድረግ ይቻል ነበር።

በነገራችን ላይ አንጋፋውና ተወዳጁ የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ በአንድ ክልል እና ብሄር የእጅ አዙር ቁጥጥር ስር የገባ ይመስላል። ቪኦኤ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በተለየ ከትግራይ ክልል የሚዘግብ ዘጋቢ አለው ፣ በትግሪኛ ቋንቋ የሚያሰራጨው በክልሉ ፖለቲካዊ ፣ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና እና ሌሎች ጉዳዮች ብቻ አትኩሮ የሚሰራ የ30 ደቂቃ ፕሮግራም አለው ። ይሄ ሁሉ አልበቃ ብሎ የአማረኛውም ፕሮግራም ብዙ ጊዜውን የሚያጠፋው ስለትግራይ በመዘገብ ነው።

ወደ ዋናው የትናንቱ የቪኦኤ ፕሮግራም ይዘት ስገባ ፕሮግራሙ በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር: ። በፕሮግራሙ የቀረቡት እንግዶች ጥያቄያቸውን ለጠ/ሚ ሀይለማሪያምና ፌደራል መንግስት ማቅረባቸውንና በጎ ምላሽ እንደሚጠብቁ ገልፀዋል … ሁለቱ የፕሮግራሙ ይዘቶች

1~ ትግራይ የጦርነት ቀጠና ሆና በልማት እየተጎዳች ስለሆነ ከፌደራል መንግስት ድጎማ እንድደረግላት የሚጠይቅ ሲሆን…

2~ ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የምትከተለው No war No peace ፖሊሲ ተቀይሮ ወደ ጦርነት እንድገባ የሚገፋፋ አንድምታ ያለው ነው ።

በሁለቱም ጉዳዮች ላይ ያለኝን አመለካከት አጠር በማድረግ ላስቀምጥ:
…..
1~ “ትግራይ በልማት እየተጎዳች በመሆኑ የፌደራል መንግስት ድጎማ ያስፈልጋታል ”
…..
እንግሊዛዊው ባለቅኔና ገጣሚ ዊሊያም ሸክስፒር ” ሀምሌት ” በተባለው ዘመን አይሽሬ ተውኔቱ የሰውን ስግብግብነት ፣ አልጠግብ ባይነት ፣ክፋት ፣ ተንኮል እና ፈጣጣነት በአንድ አረፍተ ነገር ገልፆት ነበር … << O shame, where is thy blush ? Proclaim no shame !! …>>
” ሃፍረት ሆይ !! ይሉኝታ ቢስ ሆይ!! ቅላትሽ ወደት አለ? … አንተ ሀፍረተ ቢስ!! እናንተ ይሉኝታ የለሾች! ! ሃፍረት የሌለህ እንደሆንከ አዋጅ ተናገር >> እያለ ይቀጥላል ።
እዚህ ላይ የዊሊያም ሸክስፒርን አባባል መጥቀሴ ለእነዚህ ሰዎች ተገቢና ገላጭ አባባል ሆኖ ስላገኘሁት ነው ።

ይች ኢትዮጵያ የምትባል አገር እስከ መቼ ነው የትግራይ ጥገት ላም ሆና የምትኖረው? አሁንም ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ አፍ ላይ ተነጥቆ የእነሱ ክልል እንደ ታይዋን እና ሆንግ ኮንግ እንደሆን ይፈልጋሉ ። ብዙዎች በየቀኑ ከኢትዮጵያዊነት መንበር ሸርተት እያሉ ለመሸፈታቸው ዋናው ምክንያት ” ትግሬ እያጋበሰ የሚኖርባት እና ሌላው በችጋር ተጠብሶ የሚያለቅስባት አገር ፣ የተለያዩ ዜጎች እና ክልሎች በእኩል አይን የማይታዩበታ አገር አታስፈልገኝም ” በማለት ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ሌላው ክልል ዜጎች በርሃብ ፣ በእርዛት ፣ በእስር እና በግድያ የሚሰቃዩባት የትራጂዲያ መድረክ ናት ። እንደ ተራ እንስሳ በመከራ የሚጠበሱ ዜጎች ባሉባት አገር ውስጥ የአንድ ክልል ነዋሪዎች ሌላውን ህዝብ << ጥቁር ወተት እና ነጭ ኑግ ውለድ! >> የሚባለው የአልጠግብ ባዮች ልፈፋ በአስቸኳይ መቆም አለበት ። ቪኦኤስ እንደት ስራ ቢያጣ ነው ይሄን አይነት የለየለት የዘረፋ ፕሮጀክት ሊያቀርብልን የቻለው ?
የኢትዮጵያ ምዝብርና ግፉእ ህዝብ ለ25 አመታት የተበዘበዘውና የተመዘበረው አንሶ አሁንም አመታት ቢውጡ ከርሳቸው የማይሞላና የማይጠግቡ ቡድኖች ሲሳይ መሆኑ ማብቃት አለበት ። ይሄ ካልሆነ ግን በአገራችን ይሄ አይነት ሰፍሳፋነትና አልጠግብ ባይነት እስካለ ድረስ በአገራችን ሰላም ሊሰፍን አይችልም ።

2~ የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትሪያ ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ በመቀየር አስቸኳይ እርምጃ እንድወስድ ።

በሁለተኛ ደረጃ የአዳነች ፍስሃዬ እንግዶች ያስረዱትና እና ለፌደራል መንግስት አቀረብነው ያሉት ጉዳይ ” ጦርነት ይደረግልን” የሚል አንድምታ ይመስላል።
ሀበሻ ሲተርት ” የዘንዶ ጉድጓድ በሞኝ ክንድ ይለካል ” ይላል። እነዚህ ሰዎች እቤታቸው ያለውን የዘንዶ ጉድጓድ በሌላው ኢትዮጵያዊ ክንድ ይለካልን እያሉ እየጠየቁ ይመስላል ።
ከአመታት በፊት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ወንዶች ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው ወደ ጦር ሜዳ ዘመቱ። እነዚህ ወጣቶች ወደ ጦርነቱ ሆ ብለው የገቡት በወቅቱ ገንኖ በነበረው የብሔራዊ ስሜት ማዕበል ተነድተው እና አገራችን ተወረረች ብለው ነበር ።ይሁንና ብዙም ሳይቆይ ተገኘ የተባለው ድል ወደ ምሬት ተለወጠ። ሰዎች በዘር እየተለዩ እየተመረጡ የፈንጅ ማምከኛ እንደሆኑ ተረጋገጠ ።ምሽግ ውስጥ ሆነው የሚዋጉት ወታደሮች ብዙም ሳይቆይ እውነታው ግልጽ ሆነላቸው። የፖለቲካ መሪዎች ጉድ እንዳደረጓቸው፣እንዳታለሏቸውና የጦር መሪዎቻቸውም አሳልፈው እንደሰጧቸው ተረዱ።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች “ደስ እያላቸውና በፈቃደኝነት” ለጦርነት የዘመቱት ወድያውኑ ዘመቻው አንድን ቡድን የበላይነት ለመጠበቅ እንደሆነ ተረዱ ። ህዝቡም አወቀ ።የጦርነቱ ነጋሪት ጎሳሚዎች ጦርነት መኖር ያለበት “ተፈጥሮአዊ ግዴታ” ነው ብለው ያመኑ ይመስሉ ነበር ።
BBC በተባለው የዜና ማሰራጫ “Human Wave ” በተባለው የጦርነት ስልት ያለቁትን ብሄሮች ስንሰማ የወያኔ መሪዎች ፊል ዊልያምስ የተባሉት ደራሲ “ማህበራዊ ዳርዊኒዝም” ጦርነት የተወሰኑ ዘሮችን ፣ ብሄሮችን ለማስወገድ” የሚያስችል ትክክለኛ መሣሪያ ነው የሚለውን አስተሳሰብ ተከታዮች እንደነበሩ ተረድተናል ።

ዛሬስ እነዚህ ሰዎች ምን አድርጉ እያሉን ነው? የምን ነጋሪት እየጎሰሙብን ነው? የማሰብ ችሎታ ያላቸው ሰዎች . . . እንዲህ ያለውን እብደት ሊቀበሉ ይችላሉ ወይ?
በእርግጥ ዛሬ ሌላ ቀን ነው ። በእርግጥ ልንማረው የሚገባ አንድ ግልጽ ትምህርት አለ። ባለፉት አመታትት የታዩት አሳዛኝ ሁኔታዎች እንዳይደገሙ ከተፈለገ ሊሳሳቱ ከሚችሉት የሰው ልጆች ፍልስፍናዎች ይበልጥ አስተማማኝ የሆነ መመሪያ ያስፈልገናል። ከታሪክ መማር ።
“ሰዎች ከታሪክ ሊማሩ ቢችሉ ኖሮ እንዴት ያለ ትምህርት ይገኝ ነበር! ነገር ግን በስሜታዊነትና በወገናዊነት ታውረናል። ተሞክሮ የፈነጠቀልን ብርሃን የጋን ውስጥ መብራት ሆኖብናል!”— ሳሙኤል ቴይለር ኮልሪጅ

እንግሊዛዊው ባለቅኔ ሳሙኤል ኮልሪጅ በሰጠው አስተያየት እኔ እስማማለሁ ። ለአንድ የተወሰነ ዓላማ ባለን የጋለ ስሜት ታውረን የቀደሙ ትውልዶች የፈጸሙትን አሳዛኝ ስህተት ደግመን ልንፈጽም አይገባንም ።

ከባዶ ጣሳ ወደ ተቀደደ ጣሳ – አዲስ አበባ ወደ ፊንፊኔ! (ታሪኩ አባዳማ)

ታሪኩ አባዳማ – ሰኔ 2009

የብሔር/ብሔረሰቦች መብት ይከበር ብሎ የተነሳው ኮምኒስታዊ የተማሪ እንቅስቃሴ በትግራይ በኩል ብሔረሰባዊ የትጥቅ ትግሉን በተሳካ ሁኔታ ካገባደደ በሁዋላ መንደሮችንና ከተሞችን ሳይቀር በዘር ግንድ ላይ በተሰመረ ድንበር ክልል (አጥር) ገድቦ አገሪቱን ወዳልታወቀ ጥፋት አቅጣጫ ይዟት መጓዙን ቀጥሏል። ለወያኔ ሹማምንት እና የጎጥ ካድሬዎች የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መሰረታዊው የሰብአዊ መብት መረጋገጥ እና የህግ በላይነት ሳይሆን የትኛው ብሔረሰብ በየትኛው ‘ክልል’ የበላይ እና የበታች ይሆናል የሚለው ጉዳይ ሆኗል።Ethiopia, Addis Ababa

ዜጎች ዘራቸውን ሳይሆን ዜግነት በሚፈቅደው ተፈጥሯዊ እና ህጋዊ መብት ተጠቅመው አገራቸውን ብለው ከትውልድ ትውልድ በቆዩበት ፣ ወልደው ስመው ፣ ድረው ኩለው ፣ አሳድገው ለወግ አብቅተው ባረጁበት ስፍራ ሁሉ ማን አለቃ ማን ምንዝር ፣ ማን ከንቲባ ማን ግብር ከፋይ ፣ ማን መጤ ማን ባላገር ፣ ማን ልዩ ተጠቃሚ ማን ተርታ መንገደኛ… ምን ቀረ? ማን ወርቅ ማን መዳብ እንደሆነ ዘር ላይ የተመረኮዘ ድልድል ቀርቦ ሁሉም በጎጥ መስፈርት እንዲለካ እንዲመዘን ሆኗል። ከህወሀት የፖለቲካ ፕሮግራም ጋር የተዳቀለው የወያኔ ህገ መንግስት ይህ እንዲሆን ግድ ብሏል።

ይህን የምለው አዲስ አበባ የማን ናት ብለው ከፊሉ የዘር ሀረግ እየቆጠሩ ሌሎቹ ጥንታዊ አድባራት ስም እየጠሩ ከሚሟገቱት ካንዳቸውም ጋራ የማልስማማ መሆኔን ለማመልከት ነው። አዲስ አበባ የራሷ የበቃ ታሪክ ያላት የሁሉም ኢትዮጵያውያን የክፉም የደጉም ቀን መናኸሪያ ናት።

አዲስ አበባ ኢትዮጵያዊነት ነው። ወያኔ ከምርጫ 97 አንስቶ በተቀነባበረ ስልት በከተማይቱ የሚያራምደው ፖሊሲ ያንን ኢትዮጵያዊነት ማኮላሸት ነው። ነዋሪዎች በልማት ስም ተፈናቅለዋል ፤ ለብዙ አሰርት አመታት በእድሩም በደጀ ሰላሙም ተቀራርበው የገነቡት መተሳሰር ተበጣጥሷል ፣ ወላጆች ሲፈናቀሉ ልጆች ከትምህርት ገበታቸው ተስተጓጉለዋል ፤ አዛውንት እና አቅመ ደካሞች ጠዋሪ እና ሲታመሙ ጠያቂ እንዲያጡ ተበይኖባቸዋል። ዛሬ ደግሞ እስከናካቴው አዲስ አበባ የሚባል ከተማ የለም ተብለዋል።

አዲስ አበባ ፊንፊኔ ትሆናለች ምክንያቱም ቁምነገሩ ነዋሪዋ ማን ነበር አሁንስ ማን ነው የሚለው ሳይሆን አቀማመጧ የኦሮሞ ህዝብ ዙርያውን ከቦ መኖሩ ግምት ውስጥ መግባቱ ነው። ይህን መሰረት ያደረገ አዲስ አዋጅ ተረቆ በሚንስትሮች ፀድቆ ጨዋታው ወደ ወያኔ 99% ፓርላማ ሜዳ ተልኳል… ሰነድ የጨበጠ ወይንም በአፈ ታሪክ እንኳ ፊንፊኔ የሚባል ከተማ ኖሮ ባያውቅም አዋጁ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ‘መጤ’ የሚባሉ ዜጎችን ለይቶ አድሏዊ ስርዓት ለማስፈን መወጠኑን ያረጋግጣል።

ትንሽ ስለ ‘ፊንፊኔ’

እኔ እሰከማውቀው ድረስ የኦሮሞ ህዝብ አዲስ አበባን ፊንፊኔ በሚል መጠሪያ አያውቃትም። እንደ አንድ ለአቅመ አዳም የደረሰ ኢትዮጵያዊ መናገር የምችለው ፊንፊኔ የሚባል አጠራር የሰማሁት ወያኔ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ወዲህ ነው። በማጠያየቅ እንደተገነዘብኩት ደግሞ ይህን ስያሜ ለከተማይቱ ያወጡት እነ ሌንጮ ለታ የኦነግን ፕሮግራም ሲቀርፁ በነበረበት ሰነድ ነው። እነኝህ ሰዎች ከወለጋ ቄለም እና ደምቢዶሎ መጥተው አዲስ አበባን ፊንፊኔ ናት ሲሉ ምን ታሪካዊ መሰረት ይዘው እንደሆነ የሚነግረኝ አላገኘሁም። ይሁንና ላንድ አፍታ ወጣ ብለው እኔ የተወለድኩበትን አካባቢ ህዝብ ቢያነጋግሩ ኖሮ ፣ እውን ለኦሮሞ ለህዝብ ታሪክ እና ባህል አክብሮት ቢሰጡ ኖሮ ምናልባት እንደ ወትሮው ‘ሸገር’ ይሏት ነበር። የሸዋ ኦሮሞ በራሱ ቋንቋ ሀሳብ ሲለዋወጥ አዲስ አበባን ሸገር ይላታል። የሚያወራው በአማርኛ ሲያነሳት ግን ያው አዲስ አበባ ይላታል።

አፌን በፈታሁበት እና የእረኝነት እድሜዬን ባገባደዱኩበት ጅባትና ሜጫ ፣ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ የኖርኩበት ጨቦ ፣ በቾ እና አመያ ፣ አጠቃላይ የምእራብ ሸዋ ኦሮሞ ህዝብ በራሱ ቋንቋ አዲስ አበባን ‘ሸገር’ እያለ ሲጠራት መቆየቱን የሚያስተባብል የለም። ወግ ያለው ጥናት ቢደረግ የዚህ አጠራር መሰረት ምን እንደሆነ ማውቅ የሚቻል ይመስለኛል። ዛሬ ድረስ ብዙ ያራዳ ልጆች ጭምር አዲስ አበባን ሲያቆላምጧት ሸገር ማለታቸው አለምክንያት አይደለም። አጠራሩ ከኦሮምኛ ተናጋሪ ወገኑ የተወረሰ መሆኑም አይጠፋውም። ይኼ እንግዲህ የህዝብን ባህላዊ እና ታሪካዊ መስተጋብር የሚያንፀባርቅ አሻራ ነው – የህዝብ መፈቃቀር። ይህም ሆኖ የአዲስ አበባን ታሪካዊ መሰረት የጨበጠ ስም መቀየር የሚያስፈልግበት አንዳችም ሰበብ የለም።

እጅግ ሁዋላ ቀር መገናኛ ተንሰራፍቶ በቆየባት አገራችን እያንዳንዱ መንደር ወይንም ቀዬ ፣ አካባቢ እና ሰፈር እዚያው ነዋሪ በሆነው ህዝብ ትርጉም ሊስጠው በሚችል መልኩ ስም ሲወጣ ቆይቷል። ይኼ እኛ አገር ብቻ ሳይሆን የሰው ዘር በኖረባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሚደረግ ነው። መንደሮች ወይንም አካባቢዎች ስም የሚወጣላቸው በጭፍን ወይንም የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ በፓርቲ ምክር ቤት ስብሰባ አልነበረም። ለአካባቢው ነዋሪ ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ስያሜ ይወጣል። አባ ጅፋር ወልቂጤ የሚል ስም ሲያወጡ ያካባቢውን ገበሬ ማማከር አላስፈለጋቸውም።

አዲስ አበባ የተቆረቆረችው ደግሞ በዘመኑ አገር እና ህዝብ የማሳደር ሀላፊነት ትከሻቸው ላይ በወደቀ የራሷ ዜጎች ነው። ያኔ አዲስ አበባ የሚለው ስያሜ ይበልጥ ትርጉም ይሰጥ የነበረው ለነዋሪው እና አከባቢው በቅርብ ርቀት ላለው ህዝብ ነበር ማለት ይቻላል።

ሐረር ወይንም ደምቢዶሎ የሚኖር ኦሮሞ በዚያን ዘመን ስለ አዲስ አበባ ታሪካዊ ስፍራ የሚያውቀው ወይንም እንዲያውቅ የሚጋብዘው ምክንያት አልነበረም። መቀሌ እና ሽሬ የሚኖር ትግሬ ፣ ጎጃም እና ጎንደር ነዋሪ የሆነ አማራ ምናልባትም እድሜውን ሙሉ ያችን አዲስ አበባን ላይጎበኛት ይችላል። ዘመን ሲለወጥ እና የመገናኛ አገልግሎቱ ፣ የልማት አውታሩ እየሰፋ ሲሄድ ዩንቨርሲቲ ለመማር አለበለዚያም ዘመድ ለመጠየቅ ወይንም ስራ ፍለጋ… ምናልባት ይጎበኛት ይሆናል። ለሱ አዲስ አበባ ማለፊያ ማግደሚያ ደማቅ ያገሬ ርዕሰ ከተማ እንጂ ሌላ አልነበረችም። ሲመጣ ተቀብላ ታስተናግደዋለች ፣ ሲሄድ የማይረሳ ትዝታ አስታቅፋ ትሸኘዋለች።

በመሰረቱ ዛሬ አገሪቱን የሚያስተዳድሩት የጎጥ ጦር አበጋዞች አዲስ አበባን የሚያውቋት ቁምጣ እና ሸበጥ ታጥቀው በወረሯት ጊዜ ነበር። ስለ ነዋሪዋ መስተጋብር ፣ ስለ ህዝቡ አኗኗር ፣ ስነልቡና እና ከአካባቢው ህዝብ ጋር ፀንቶ ስለቆየው ማህበራዊ ግንኙነት ያላቸው ግንዛቤ ዚሮ ነበር ማለት ይቻላል። በምርጫ 97 ወቅት የደረሰባቸውን ሽንፈት አስተውሎ መሪያቸው “አዲስ አበባ ውስጥ የዘር ፖለቲካ አይሰራም” ወደሚል ድምዳሜ መድረሱንና ካድሬዎቹ አደረጃጀት ስልት በመቀየር የወጣት ፣ የሴት ሊግ እያሉ እንዲያሰባስቡ ቀጭን መመሪያ መስጠቱ ያስታውሷል። ወቅቱ አዲስ አበባ ለጎጥ ፖሊቲካ አልመችም ብላ ድምፁዋን ከፍ አድርጋ ያስተጋባችብት አጋጣሚ ነበር።

በመሆኑም አዲስ አበባ ስለ ስሟ ማንነት ቆርቁሮት ፣ እንደ ችግር ተቆጥሮ ጥያቄ ያቀረበ ወገን እንዳለ ተሰምቶም አያውቅም። ዛሬ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍ ፋይዳ ያለው ጠቀሜታ እና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ብትሆንም አገሪቱ የምትመራው ደግሞ በዘር ማንነት ላይ በተደራጁ የጦር አበጋዞች ስለሆነ ዘረኛ ልዩ ጥቅም ፣ ልዩ መብት የሚባል ፈሊጥ ተቀስቅሶ ከተማይቱ ላይ ተዘምቷል። ገበያ ፣ ገንዘብ እና ስልጣን ያሰከራቸው የጎጥ ጦር አበጋዞች ለስልጣናቸው ዕድሜ ማርዘሚያ ሌላ የዘር መስፈርት እያዘጋጁላት ነው።

መሰረታዊ ሰብአዊ መብቱን በታጠቀ ወራሪ ጦር የጨፈለቁትን ህዝብ ዛሬ ልዩ መብት ልናጎናፅፍህ ነው የሚል አዋጅ ያስነግራሉ።

አዲስ አበባ ዘር አላት?

አባ ጅፋር ከጂማ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ እርፍት አዳር የሚያደርጉባትን መንደር ‘ወልቂጤ’ ብለው ሰይመዋል። ትርጉሙ ‘እኩል በኩል’ ማለት ሲሆን ይኸውም ያች መንደር በጅማ እና አዲስ አበባ መካከል እኩል ርቀት ላይ መሆኗን ለማመልከት እንደነበር ይታወቃል። ወልቂጤ በመሰረቱ የኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪ መንደር አልነበረችም ፣ አሁንም አይደለችም። ትናንትም ሆነ ዛሬ ነዋሪዎቿ ስሟን ለመቀየር የሚያስገድዳቸው ምክንያት አልታያቸውም። ነገ የሚመጣውን ለመተንበይ ግን የዘመኑ ፖለቲካ አያያዝ አይፈቅድም። አባ ጅፋር እንደ አላፊ አግዳሚ እንግዳ ድንኳናቸውን ተክለው ከማደር በላይ የመንደር ስም ሰጭ ማን አደረጋቸው ብሎ ያኮረፈ ወይንም ጥያቄ ያነሳ ወገን እስከ ዛሬ መኖሩን አላውቅም። እስከ ዛሬ ድረስ የአባ ጅፋርን ነብስ ይማርና ወልቂጤ ለማንም ሳትሸጥ ሳትለወጥ አለች። ያው እንደቀድሞው ለፍቶ አዳሪ እና ታታሪ ህዝብ እየኖረባት ነው።

የወያኔው ረቂቅ አዋጅ እንዲህ ይላል “ከተማዋ ፊንፊኔ ተብላ በመቆርቆሯ…”። እንዲያው በሞቴ ፊንፊኔ የሚባል ከተማ መቼ እና በማን ተቆረቆረ? ብለን ብንጠይቅ እኛ የቅርብ ነዋሪዎቿ የሆነውን ኦሮሞዎች ቀጥቅጠው እየገዙን ባሉት የትግራይ የጦር አበጋዞች ዘንድ ያስገምተን ይሆን?

ትንሽ የቤተሰብ ታሪክ ላክልበት – አያቴ ቀኛዝማች ጉተማ ፊጤ አዲስ አበባ መርካቶ አራተኛ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ1911 አካባቢ አንድ መንደር ቆርቁረዋል። ዘመዶቼ እንደነገሩኝ አውቶቡስ ተራ እስከ ፋሲል መድሀኒት ቤት የነበረው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ንብረትነቱ የአያቴ ነበር። ፋሲል መድሀኒት ቤት ጀርባ ቀበሌ 32 ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት የሚገኘው ግቢ ውስጥ ለራሳቸው መኖሪያ ትልቅ ቪላ እና ዙርያውን ደግሞ የሚከራዩ ቤቶች አንፀዋል።

የዚያ ሰፈር ነዋሪዎች ሊያረጋግጡ እንደሚችሉት (የልማት ተፈናቃይ ሆነው ገሚሱ ጎዳና ላይ እየተኙ ነው) አያቴ ከሰሯቸው ውስጥ አብዛኞቹ ሳር ክዳን ቤቶች ነበሩ። የመጨረሻው የሳር ክዳን ቤት በቆርቆሮ የተተካው ብታምኑም ባታምኑም 1964 እንደ እኛ አቆጣጠር ነበር። የመርካቶን የመጨረሻ ሳር ጎጆ አቶ ሀይሌ ቱሬ የሚባሉ ትጉህ ዜጋ ይኖሩበት ነበር። በመርካቶ የሳር ቤት አሻራ የቆየው እስከ እኛ ዕድሜ ጊዜ ድረስ ነበር ለማለት ነው። ታዲያ  በሰፈሩ ህብረተሰቡን ያሰባሰበው ትልቁ ማህበር ‘ጉተማ ፊጤ’ እድር እየተባለ እስከ ደረግ ዘመን ማብቂያ ድረስ ይጠራ እንደነበር አስታውሳለሁ። ቀኛዝማች ጉተማ አፄ ሀይለስላሴን ተከትለው ሰገሌ ፣ ሁዋላም ማይጨው የዘመቱ ብዙ ቤተዘመድ ጦርነቱ ላይ አጥተው የተመለሱ አገራቸውን የሚወዱ ዜጋ ነበሩ። የሞቱት በ1951 አካባቢ ነው። አዲስ አበባ እያንዳንዷ መንደር ገብታችሁ ብታስሱ የሳቸውን አይነት ተመሳሳይ ታሪክ ታገኛላችሁ።

እንደ እኔ አያት ሁሉ ከሁሉም የኢትዮጵያ መንደሮች የመጡ ዜጎች በሙያቸው ፣ ጥበባቸው እና ባገኙት መስክ ተሰማርተው አዲስ አበባ ላይ አዲስ ህይወት ገንብተዋል። ዘር የማትቆጥረው አዲስ አበባ ዶርዜውን ፣ ትግሬውን ፣ አማራውን እና ኦሮሞውን አጎራብታ በአንድ ማህበር ፅዋ አቋድሳ ፣ በሀዘን ጊዜ ለመፅናናት አቀራርባ ፣ በሰርግ ጊዜ አንድ መድረክ ላይ ዳንኪራ አስረግጣ ፣ በክፉ በደጉ ሁሉ አቅፋ ደግፋ አስተናግዳቸዋለች። ያንን ፅኑ መሰረት ላይ የቆመ ታሪካዊ ማንነት ለማፍረስ ከትግራይ በረሀዎች ጦር ሰብቀው የመጡ ወራሪዎች ዘምተውበታል።

በኔ እምነት አንድን ከተማ ወይንም አካባቢ ላንድ ዘር ልዩ መጠቀሚያ የማድረግ ዝንባሌ የሚመነጨው ፀረ-ኢትዮጵያ ከሆነው የህወሀት ማኒፌስቶ ብቻ ነው። ተጨባጭ ታሪክን ክዶ ፣ የህዝብን በጎ ታሪክ አዋርዶ ለጠባብ የድርጅት አላማ ሲባል አገርን ለጥቃት ማመቻቸት የህወሀት ማኒፌስቶ መርህ ነው። ኢትዮጵያ የህወሀት የጥፋት ኢላማ ሁና ቆይታለች – አሁንም የተቀየረ ነገር የለም።

እንጂ የከተሞች እና ክፍለ አገራት ባለቤትነት ዘር ላይ የተመረኮዘ ታሪካዊ መሰረት አላቸው ከተባለ ከአዲስ አበባ ይለቅ አስመራ ወደ ታሪካዊ ባለቤቷ እንድትመለስ ለምን አይታገሉም። ያቺ ከተማ በማን ተቆረቆረች። ከትግራይ ወይንም ትግርኛ ተናጋሪ ህዝብ ጋር ያላትስ ታሪካዊ ግንኙነት ምንድነው? በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ የኢትዮጵያም ጭምር ገዢ አሳዳሪ የነበሩት ርዕሰ ከተማቸው መቀሌ የነበረው አፄ ዮሐንስ እና ራስ አሉላ አስመራ ላይ ምን ሲያከናውኑ ቆዩ?

ህወሀት ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ሲረዳ እና የትግራይን ድሀ ልጅ ምፅዋ እና ናቅፋ ከሻቢያ ጎን አሰልፎ ሲማግድ ታሪካዊውን የትግራይ ህዝብ አሻራ እና የኢትዮጵያን መሰረታዊ ማንነት እየፋቀ መሆኑን ሹክ ያለው አልነበረም ማለት ነው። እንዲያው ይኼ ጥንት እነ እገሌ ኖረውበት ነበርና ዛሬ ስያሜውም ባለቤትነቱም መቀየር አለበት ሲባል የዚህ አይነቱ አመክንዮ በቅድሚያ ተግባራዊ መሆን ያለበት የተፃፈ ሰነድ ጭብጥ ታሪክ ባላቸው እንደ አስመራ ባሉት ላይ ቢሆን አይሻልም ነበር? ጥያቄዬ ለህወሀት ነው እንጂ ለዛሬዎቹ የአስመራ ልጆች አይደለም።

ልዩ ጥቅም በአዋጅ

አዲስ አበባ ዙርያ ያለው ዜጋ መሰረታዊ አገልግሎት የሚሟላልህ የከተማይቱ ስም ፊንፊኔ በሚል ከተቀየረ በሁዋላ ነው የሚል መልዕክት ያዘለ አዋጅ ነው። የንፁህ ውሀ መጠጥ አገልግሎት የምታገኘው ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎትህ የሚረካው ፣ ሆስፒታል ገብተህ የምትታከመው አዲስ አበባ ወደ ፊንፊኔነት ስትቀየር ነው የሚል መልዕክት አዋጁ ውስጥ ሰፍሯል። በሙስና እና ስግብግብ ዘራፊዎች እጅ ወድቃ ለነዋሪዎቿ ሲኦል የሆነችው አዲስ አበባ ለራሷ አሮባት በዙርያዋ ነዋሪ ለሆኑ ገበሬዎች የተትረፈረፈ አገልግሎት የምታቀርበው ስሟ ሲቀየር ብቻ ነው። ይኼ ነው የአዋጁ ይዘት።

አዲስ አበባ በወያኔ ዘመን እንኳን የአካባቢውን ገበሬ ፍላጎት ልታረካ ለራሷ የተሟላ የትራንስፖርት አገልግሎት የላትም ፣ የኑሮ ውድነት አብዛኛውን ነዋሪ ከሰውነት ተራ አውጥቶት የሚገኝ መሆኑን የዕለት ዘገባዎች ሳይቀሩ ይመሰክራሉ፣ የመብራት መቆራረጡ ፣ የውሀ ወረፋ ፣ የህክምና አገልግሎት እጦት ፣ የትምህርት ቤቶች ጥራት መውደቅ ፣ ከፍተኛ የስራ አጥነት ችግር… ስንቱ ይነገራል። ወያኔ የያዘው ውሀ ከባዶ ጣሳ ወደ ተቀደደ ጣሳ ማገላበጥ ነው።

በዚህ ሳምንት ይፋ የሆነ ሪፖርት የሚከተለውን አስፍሯል…

አዲስ አድማስ ጋዜጣ ባለፈው ቅዳሜ “የትምህርት ጥራቱ በአስደንጋጭ ሁኔታ አሽቆልቁሏል” በሚል ርዕስ ስር እንደዘገበው “… የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ያግዛል በሚል ከእንግሊዙ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በቅርቡ የተደረገው ይሄው ጥናት፤ የተማሪዎችን የአስተሳሰብ አቅም ከሌሎች አገራት ጋር በማነፃፀር ውጤቱን ይፋ አድርጓል፡፡ “በኢትዮጵያ የሚገኙ የ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች አስተሳሰብ፣ አሜሪካና ሲንጋፖር በመሳሰሉ የአደጉ አገራት ከሚገኙት የአንደኛ ክፍል ተማሪዎች አስተሳሰብ ጋር እኩል ነው…” ይላል።

ይህን አይነቱን አሳፋሪ የስራ አፈፃፀም የታቀፈ ስርዓት የአንዲትን ታሪካዊ ርዕሰ ከተማ ስም ለመቀየር አዋጅ ያረቃል። አገሪቱ ወደተረጋጋ ሰላም እና ዕድገት የምትጓዝበትን ትልም ሳይሆን ዜጎች ዋስትና በሌለው ጥቃቅን ጉዳይ ላይ እንዲራኮቱ ተንኮል ይሸርባል።

አናሳዝንም ወይ? ነው ያለው ሙዚቀኛው!

ወያኔ የአዲስ አበባን ስም ለመቀየር ብሎ ባወጣው አዋጅ ሰበብ የተነሳው አተካሮ ሌላው አሳዛኝ ትርኢት ነው። ትርኢቱን በብዙሀን መገናኛ መድረክ ላይ የሚያራግቡት አብዛኞቹ ያው የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ግብረ ሀይል ካድሬዎች ቢሆኑም በዚህ ከፋፋይ መረብ ውስጥ ጥልቅ ብለው አቧራ የሚያስነሱ ቅን ዜጎችም እንዳሉ ማስተዋል ይቻላል። ገሚሱ ለኦሮሞ ህዝብ መብት ተሟጋች ሆነው ግፋ ወደፊት የሚሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ አዲስ አበባ የአማራ እንጂ የማንም አይደለችም በሚል እጅግ አሳፋሪ ሙግት የገጠሙ ናቸው። ሁለቱም ተቃራኒ ወገኖች አርቆ አስተዋይነት የነጠፈባቸው ግን የሚያስከትሉት ጥፋት መዘዙ አገሪቱን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። በመካከሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያወገዙ መስሎ አንድን ህዝብ በጅምላ የሚረግሙ እና የሚያበሻቅጡ ወገኖች አሉ።

አዲስ አበባ ኢትዮጵያዊ እንጂ ምንም ልትሆን እንደማትችል ሁሉም ወገን ጠንቅቆ ሊረዳው የሚገባ ይመስለኛል። አዲስ አበባ ላይ ያነጣጠረው የወያኔ ጥቃት ስም በመቀየር ብቻ የሚገታ መስሎ ከታየን እጅግ አድርገን ተሳስተናል። ጥቃቱ ኢትዮጵያን ከገፀ-ምድር ለመፋቅ ወያኔ የጠነሰሰው የረጅም ጊዜ አላማ አካል ነው። መዋጋት ካስፈለገ ልንዋጋ የሚገባን ህዝብ ላይ የተጫነውን የወያኔ ፖለቲካ ሰነድ ነው። እነሱ በማያሻማ ቋንቋ አላማቸውን ነድፈው አስቀምጠዋል ፤ እያንዳንዷ የሚወስዷት እርምጃ ወደ አላማቸው ግብ የሚወስድ አውራ ጎዳና ነው። ይህን በንፁሀን ዜጎች ደም የበከተ የጥፋት ጎዳና አንድ ላይ ተሰልፈን መዝጋት ካልቻልን አዲስ አበባችን ብቻ ሳትሆን እኛም ማንነታችን ይጠፋል።

የአማራ ህልውናና መብት የሚከበረው በራሱ ትግል እንጅ በሕገመንግሥቱ አይደለም። (ከይገርማል)

ሕገመንግሥት የአንድ ሀገር ገዥ/የበላይ ሕግ ነው። ሌሎች ህጎች የሚወጡትና ተፈጻሚ የሚሆኑት ሕገመንግስቱ ላይ የሰፈሩትን ጽንሰሀሳቦች መሰረት አድርገው ነው። ከህገመንግሥቱ ጋር ተቃርኖ ያላቸው ሌሎች ህጎች ተቀባይነት የላቸውም። ይሁንና እኛ ሀገር እንዲህ አይነት ነገር አይሰራም። እንደሚታወቀው በህወሀት አምባገነንነት ስር በምትማቅቅ ሀገር ውስጥ ነው የምንኖረው። ለሚፈለገው ተግባር ጠቀሜታ ይሰጣል ተብሎ እስከታመነ ድረስ በህገመንግሥቱ ላይ የሰፈሩ መብቶችን የሚጥስ የወያኔ ሀሳብ በአንድ ቀን አዳር ተረቆ ህግ ሆኖ ሊወጣ ይችላል። ወያኔ እንደድርጅት ይቅርና አንድ የወያኔ ሹም ሕገመንግሥቱን የሚጥስ ተግባር ቢፈጽም ምንም ማለት አይደለም። እንዲህ ያሉ ሁኔታወች ብዙ ጊዜ የሚያጋጥሙ በመሆኑ በማናችንም ላይ መደናገር አይፈጥርብንም። ሕገመንግሥቱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሀገሪቱ ዕኩል መብት ያላቸው መሆኑን ይናገር እንጅ ዕውነታው ግን እንደዚያ አይደለም። ለሕገመንግስቱ ከበሬታ መስጠትና ተገዥ መሆን የሚጠበቀው ከወያኔና በላተኞቹ ውጪ ባለው ማህበረሰብ ዘንድ ነው። በተለይ በአማራው ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ በሕገመንግሥቱ አግባብ ለመዳኘት የሚቻል አይደለም፤ ለአማራው ስለማይሰራ። ለ26 ዓመታት ያህል የደረሰውን የሰውና የንብረት ጥፋት በተመለከተ ለሚነሳው የሕዝብ ጩኸት ጆሮ ሰጥቶ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ አማሮች ተለይተው ለምን የጥቃት ሰለባ ሊሆኑ ቻሉ፣ ምን ያህል ሰው ተገደለ፣ ምን ያህል ሕዝብ ተፈናቀለ፣ ሰዎች የተገደሉት በምን እና እንዴት ነበር፣ የጠፋው ንብረት አይነትና መጠን ምን ይመስላል? በሚል ዝርዝር ሁኔታውን ለማወቅ የተደረገ ጥናት የለም፤ በአጥፊወች ላይ ርምጃ ለመውሰድም አልታሰበም። የብሔር ብሄረሰቦችና ሕዝቦችን መብት ያስከብራል ተብሎ የወጣው ሕገመንግሥት ለአማራው አይሰራም።

 

ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ የምታገኘው ልዩ ጥቅም አለ ሲባል ብዙም አልገባኝም ነበር። አሁን እንደተረዳሁት ክልሉ ብቻ ሳይሆን የክልሉ ኗሪም የአዲስ አበባ ልዩ ተጠቃሚ እንደሆነ ነው። ይህም ማለት በአንድ ሀገር እየኖርን በዋና ከተማችን አዲስ አበባ የዜጎች የጥቅም መበላለጥ ተፈጠረ ማለት ነው። የጥቅም መበላለጥ ማለት ዕኩል መብት አለመኖር ማለት ነው። በመሰረቱ የአንድ ሀገር ዜጎች የተለያየ መብትና ጥቅም ሊኖራቸው አይገባም። ክልሎች በራሳቸው ሰዎች የመተዳደር አስፈላጊነት በህግ በተሰጣቸው ኃላፊነቶች በስራቸው የዋሉትን ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሐብቶች ለማስተዳደር፣ ለማሳደግና ሕዝባዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ፣ በክልሉ የሚኖረው ሕዝብ የዴሞክራሲያዊ መብቱ እንዲጠበቅ፣ በክልሉ ሀብትና አገልግሎት ፍትሀዊ ተጠቃሚ እንዲሆን (እኩል እድል እንዲያገኝ)፣ በቋንቋው እንዲማር/እንዲዳኝ፣ ባህልና ወጉን እንዲያጎለብት፣ እና ሰላሙ እንዲረጋገጥ ለማስቻል እንጅ በሀገሪቱ ዜጎች መሀል ልዩነት ለመፍጠር መሆን አልነበረበትም።

 

ይቅርታ ይደረግልኝና የአንዳንድ ሰዎች ሁኔታ ምኑም አይገባኝም። ስለፍላጎትና አቅርቦት (demand and supply) አንስተው ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ልዩ ተጠቃሚ የመሆን መብት ሊኖረው እንደሚገባ ሊያስረዱ የሚሄዱበት መንገድ በጣም ግራ የሚያጋባ ነው። በመሰረቱ አዲስ አበባ የሚመረት የእርሻ ምርት የለም ቢባልም አዲስ አበባ የሚመረት የፋብሪካ ውጤት ግን አለ። ኦሮሚያ የግብርና ምርት አቅራቢ ስለሆነች ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ሊጠበቅላት ይገባል ከተባለ አዲስ አበባ አምርታ ወደኦሮሚያ ለምትልከው የፋብሪካ ውጤትም ልዩ ጥቅም  የመጠየቅ መብት አላት ማለት ነው። ለነገሩ ያህል ነው እንጅ ለአዲስ አበባ የግብርና ምርት የሚቀርበው ከኦሮሚያ ብቻ አለመሆኑን ማንም ያውቃል። ሊሆን የሚገባው በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖሩ የኦሮሚያ ክልል ኗሪወች ቢፈናቀሉ ተመጣጣኝ ካሣ የማግኘት መብት እንጂ ማንም ዜጋ በሀገሩ ላይ የበለጠ ተጠቃሚና ዝቅተኛ ተጠቃሚ የሚያደርግ የተለያየ መብት አይደለም። በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ዕኩል መብት ያላቸው ናቸው። ዜጎቹ በፈለጉበት ቦታ ተዘዋውረው የመኖር፣ የመስራትና ሐብት የማፍራት መብት አላቸው። በርግጥ ክልሎች ሕገመንግሥቱን ተከትለው በሚያወጧቸው አካባቢያዊ ህጎች የመገዛትና እንደማንኛውም የክልሉ ዜጋ በማህበራዊ ጉዳዮች የመሳተፍ ግዴታ ሊኖርባቸው ይችላል።

 

“ለኦሮሚያና ለኦሮሞ ሕዝብ ተሰጠ የተባለው ልዩ ጥቅም እዚህ ግባ የማይባል ተራ ነገር ነው፤ ወያኔ በኦሮሚያ የተነሳበትን የሕዝብ አመጽ ለማብረድ ሲል እንደደነበረ የወሰደው ርምጃ ነው” ብለው የሚያስቡም አሉ። እኔ ግን እንደዚያ አላስብም። የማምነው ነገር ቢኖር አማራውን አቅም አልባ ለማድረግ እየወሰዱ ያሉት ቀደም ብሎ የተጠና ዕቅድ እንደሆነ ነው። መጀመሪያ ወልቃይትንና ራያን ከአማራው ለመንጠቅ ሲያስቡ የኦሮሞ ድጋፍ እንዲኖራቸው አዲስ አበባን ጨምሮ እጅግ ሰፊ አካባቢ ለኦሮሚያ ሰጡ፤ በከሚሴና በባቲ የሚኖሩት ኦሮሞወች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በሚል በልዩ ዞን እንዲደራጁ እንዲደረግ ለጉዳይ አስፈጻሚው ብአዴን ትዕዛዝ አስተላለፉ። አማሮች በዛ ብለው በሚገኙባቸው ሌሎች ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ቀርቶ በቋንቋቸው እንዲማሩ፣እንዲዳኙ፣ ይባስ ብሎ እንደወልቃይትና ራያ ባሉት አካባቢወች በቋንቋቸው እንዲናገሩ እንኳ ዕድሉ አልተሰጠም፤ እንዲያውም መሬታችሁን እንጅ እናንተን ስለማንፈልጋችሁ ወደክልላችሁ ሂዱ ተብለው ከሞት የተረፉት እየተፈናቀሉ ግፍ ተፈጸመባቸው እንጂ። ሰው ያልገባው ከምንም በላይ የጎሠኞች የተጠናከረ ትብብር መኖሩን ነው። የሚለያዩት በመለስተኛ ፍላጎቶች ሲሆን ዋና ጠላት ነው ብለው ሁሉም የሚስማሙበት ደግሞ አማራውን ነው። በአንዳንድ ልዩነቶች ሲናቆሩ ይቆዩና አማራው በእግሩ ለመቆም ቻቹ ችግራ/ወፌ ቆመች ለማለት ሲጀምር ልዩነታቸውን ትተው ሁሉም በአንድ ላይ ይነሱበታል፤ ወፌ ቆመች ሳይሆን ወፌ ላላ ነው የሚገባህ ብለው ስቃዩን ያበሉታል። ጎሠኞች እንደውሻ እርስ በርስ ቢነካከሱም ጠላት ነው ብለው የፈረጁት አማራ ላይ ግን ተባብረው ሊያጠፉት ይነሳሉ።

 

ወያኔወች አንድ ነገር ለማድረግ መጀመሪያ መምከር ከዚያ መወሰን፣ ውሳኔውን በሀይልም ቢሆን ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀስ፣ በመጨረሻም የሚቃወሙትን በተለያየ መንገድ ማስታገስ ከተቻለ ሕዝባዊ ጩኸቱ የአንድ ሰሞን ይሆንና ቀስ በቀስ እየተለመደ ይሄዳል የሚሉት ስልት አላቸው። ይህ ስልት ጠላት ነው ብለው የፈረጁትን አማራ አናሳና ከፉክክር የራቀ በማድረግ በሂደት ጭራሹን እንዲጠፋ ያቀዱትን እቅድ ለማሳካት የሚከተሉት የአሰራር ዘዴ ነው።

 

የወቅቱ አማራን የማዳከሚያ ስልታቸው ከአዲስ አበባ ጋር ያለውን ታሪካዊ ቁርኝት ጨርሶ መበጠስ ሆኗል። በዚህም መሰረት በአባቶቻችን ከተማ አማራው እንደሌላ ሀገር ዜጋ እንዲቆጠር ሲደረግ ባለቤት ነው ለተባለው ኦሮሞ ልዩ ጥቅም ሰጠን ብለው አውጀዋል። ብአዴን እንደለመደው ውሳኔውን አብሮ አጽድቋል። የኦነግ ጀሌወች በደስታ ጮቤ እየረገጡ “ገና ብዙ ይቀራል” እያሉ ነው። ዕውነታቸውን ነው፤ ገና ብዙ ይቀራል። የኦሮሞ ድርጅቶች የወያኔ የክፉ ቀን ደራሽ ሆነው የሚቃጣበትን ሁሉ ለመመከት የተቀመጡ ኃይሎች መሆናቸውን ማንም የተገነዘበ አይመስልም። በአንዳንድ ልዩነቶች ተጣላን ብለው በተኳረፉ ጊዜ የኦነግ አመራሮች ወደየሚፈልጉት ሀገር የተጓዙት በቦሌ በኩል ነበር። ውጭ ከወጡ በኋላም በወያኔ ላይ የተባበረ ኃይል እንዳይነሳ የብተና ስራ በመስራት ላይ ናቸው። አንዳንድ የኦነግ አመራሮች እንደነ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚፈለጉ ስላልሆኑ  አሁንም ቢሆን ሰበብ እየፈጠሩ ወደ ኢትዮጵያ ወጣ ገባ ማለታቸውን አላቆሙም።

 

የአማራው ችግር ብዙ ነው። አሁን ደግሞ በዋና ከተማው ባህርዳር ህልውና ላይ ያንዣበበ አደጋ ተከስቷል። አደጋው ለከተማዋ ህይወት የሆነው ጣና በእምቧጮ አረም መወረር እና ሆን ተብሎ ወደሀይቁ በሚለቀቅ ፈሳሽ መበከል ምክንያት የመጣ ነው። ወደሀይቁ የሚፈሰው ቆሻሻና ጎጂ ኬሚካል ሀይቁን ቤታቸው አድርገው በሚኖሩ እንስሳት ላይ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል የሚያጠያይቅ አይደለም። የክልሉ መንግሥት በከተማው ቁጭ ብሎ ይህን ብክለት ለምን ዝም ብሎ እንደሚመለከት የሚታወቅ ነገር የለም። ጣናን የወረረው ባዕድ አረም እንዴት መጣ? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ያለ አይመስለኝም። ቢኖርም አረሙ በሌሎች አካባቢወችም የተከሰተ አመጣጡ በውል ያልታወቀ ነው የሚል ሊሆን ይችላል። ወያኔ በተንኮል ሰይጣንን የሚያስንቅ፣ የሚያስቀና መሆኑን ላልተረዳ የሚናገሩትን ሊያምን ይችላል። አረሙ እንዴት ጣና ላይ ብቻ ተከሰተ የሚል ጥያቄ እንዳያስነሳ በሌሎች ሀይቆች አካባቢም በስሱ በተን አድርገው ጣና ላይ አፍስሰውብን ቢሆንስ! አዎ እንደዚያ ነው! እኛ ጣናን የወረረውን አረም ስናርም እነሱ ደግሞ ሌላ የቤት ስራ ሊሰጡን ይዶልታሉ።

 

ከማን ጋር ነው የሚዶልቱት ቢባል መልሱ ከኦነግና መሰል የጎሣ ድርጅቶች ጋር የሚል ይሆናል። የጎሳ ድርጅቶች የተመሰረቱበት መሰረታዊ ፍላጎት ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ለማስቻል ነው የሚል ቀና የመሰለ ሀሳብ የያዘ ይምሰል እንጂ በውስጡ ተሸፍኖ የተቀመጠ የአማራውን መጥፋት ለማቀላጠፍ ሁሉንም ባለድርሻ የማድረግ እና የአንድነት ኃይሉን ቦታ የማሳጣት እጅግ አደገኛ ሀሳብ አለው። የጎሣ ድርጅቶች አንድ ናቸው ስንል ዝም ብለን ከመሬት ተነስተን አይደለም። በአማራው ላይ የሚደርሰው ማሳደድ እና ግድያ የተለየ እንዳይመስል አልፎ አልፎ የሌሎች ጎሣወች የርስ በርስ ግጭት ቦግ ብሎ እልም እንዲል ይደረጋል። እንዲህ ያለው ነገር በአማራ ላይ ለሚደርሰው መከራ ሽፋን ተብሎ የሚፈጸም የክፋት ስራ ነው። በዚህ ወቅት የሚጠፋው የሌሎች ጎሣ አባላት ህይወት የጠላትን ጦር ለመምታት እንዲያስችል መተላለፊያውን ከፈንጂ በማጽዳት ተግባር ተሰማርተው መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ ወታደሮች የሚቆጠር ነው።

 

አማራው ህልውናውን ለመከላከል ይደራጅ ስንል የዘር ማጥፋትን እንከላከል ማለታችን ነው። በዚህ ያልተደሰቱ ወገኖች አማራ ዘረኛ ሆነ በሚል ከብዙ አቅጣጫ ጦርነት ከፍተዋል። አማራ በዘሩ ከተደራጀ ከወያኔ ምኑን ተለየ ብለው ይከራከራሉ። “የተደራጀነው ራሳችንን ከጥቃት ለመከላከል እንጂ ዘረኛ ለመሆን አይደለም። ለ26 ዓመታት ያህል እንደ አውሬ ስንታደን ማንም የተቆረቆረልን አልነበረም።” ብለው መከላከያ ለሚያቀርቡት አማሮች የሚሰጠው መልስ የአማራው ችግር የሚፈታው የመላው ኢትዮጵያ ችግር ሲፈታ ብቻ ነው የሚል ነው። እኒህ ሰዎች ያልገባቸው ነገር በኢትዮጵያዊነት እንደራጅ ቢሉም የሚቆሙት ብቻቸውን መሆኑን ነው። በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር ብዙሀኑ የሌላ ጎሣ አባላት ያሉት እናት በየሚሏቸው በየጎሣ ድርጅቶቻቸው ውስጥ ነው። በአንድነት ስም ከተሰባሰቡትም መሀል ምን ያህል ተልዕኮ ተሰጥቶት እንደመጣ መገመት ይከብዳል። ጎሰኝነትን አውግዘው ለኢትዮጵያ እንሟገታለን ብለው ከልብ የተሰለፉ የሌላ ጎሣ አባላት ምን ያህል ናቸው? “እዚያ ቤት የሚደረገውን ሂዳችሁ እዩ!” የተባሉትስ?

 

ከዚህ በፊት በነበሩት የአንድነት ድርጅቶች ላይ ምን ደረሰ? ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ መልሱ የአንድነት ድርጅቶች የነፍጠኛውን ስርአት ለመመለስ የሚያልሙ ናቸው ተብለው እንደተወገዙ ነው። እነ መኢአድ፣ አንድነት፣ ቅንጅት እንዲዳከሙ የተደረጉት የነፍጠኛ ስርአት አራማጆች ናቸው በሚል አይደለም? በኢትዮጵያዊነት በተደራጁት ሰላማዊ ድርጅቶች ውስጥ ተመልካችን እንዳይከፋው በሚል አማራው ከአመራር ቦታ እንዳይደርስ ተወስኖ ከታች ሆኖ ቢደግፍም “አማራ የታየበት ሁሉ የተወገዘ ነው” በሚል ስሜት የነፍጠኛ ድርጅት ነው እየተባለ ሲከሰስና በተንኮል እንዲፈርስ ሲደረግ ነው የምናውቀው።

 

በ1997 ዓ ቅንጅት ሲያሸንፍ የነፍጠኛው ስርአት አንገቱን ቀና እያደረገ ነው ተብሎ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ታግለን የስርአት ለውጥ ለማምጣት ነው የተደራጀነው ሲሉ የነበሩት በጎሣ የተደራጁ ተቃዋሚ ኃይሎች ጭምር ክተት እንዳወጁበት መርሳት አይኖርብንም። ሻዕቢያም በበኩሉ በቅንጅት ማሸነፍ ደስታ እርቆት ብዙ ሲቀሰቅስ እንደነበረ የምናስታውሰው ዕውነት ነው። በደርግ ጊዜ ኢሕአፓን ከላይ ሆነው ይመሩት ከነበሩት ውስጥ ዋናውን ቦታ በመያዝም ሆነ በብዛት ከአማራው ይልቅ ትግሬወች ይበልጡ ነበር። ነገር ግን አማሮች ስለታዩበት ነበር በፓርቲው ውስጥ የነበሩትን ትግሬወች የአማራ አሽከር እያሉ ሲያዋርዷቸው የነበሩት፤ ከትግራይ ክልል ውጡ ተብሎ ድርጅቱ ውጊያ የተከፈተበት! እናሳ! ምን ሁኑ ነው የሚባለው? ለአማራው ማን ይታገል? ሳይደራጅ ብትንትን ብሎ ይጥፋ!

እንዲህማ አይሆንም!! እጅና እግሩን አጣጥፎ መከራን መቀበል ሳይሆን ተደራጅቶ እየታገለ መስዋዕት መሆንን ለተተኪወቹ ማውረስ መተኪያ የሌለው የህይወት መድኅን ነው። አማራው የራሱን ልጆች ድምጽ ብቻ ያድምጥ! ጨርሶ ላለመጥፋት መውተርተር የራሱ እንጅ የሌላ የማንም ድርሻ አይደለም። “ለእኛው ያለነው እኛው ስለሆንን ህልውናችንን ለመከላከል እንደራጅ” ብለው የተነሱትን አማሮች ትግላቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ እንቅፋት መፍጠር ሳይሆን መደገፍ የማንም በፍትህ እና በዕኩልነት የሚያምን ዜጋ ሁሉ ኃላፊነት ነው።

 

አንዳንዴ ራሳችን የምናውቀውን ዕውነትም ቢሆን በሌላ ሰው አንደበት ሲነገር ስንሰማው ክብደቱ የበለጠ ሊገለጽልን ስለሚችል በድጋሚ የምክር ሀሳቤን እንድሰነዝር ይፈቀድልኝ። “ብአዴን ውስጥ ያላችሁ አማሮች ልብ ግዙ! ትግሉ እናንተን ጨምሮ መላ አማራውን ነጻ ለማድረግ የሚደረግ ትግል ነው። የአማራ ታጋዮች የናንተን መብት ጭምር ለማስከበር ነው እየታገሉ ያሉት። የነርሱን ትግል መደገፍ የራሳችሁንና የቤተሰባችሁን ህልውና ማረጋገጥ ነው። አማራን ለማጥፋት የሚደረገው ደባ እናንተን የሚምር አይሆንም። በአንድ ወቅት አንድ የሽግግር መንግስቱን ቻርተር በማጽደቅ ሂደት የተሳተፈ ሰው ጋር ስናወራ፦

 

“የድርጅት አባል የሆንሁበትን ቀን መርገም የጀመርሁት በሽግግር መንግስቱ ቻርተር ተሳታፊ በነበርሁበት ጊዜ ነበር። ማንም እየተነሳ ‘አማራ ልብ የለውም። ዱሮም በስልጣን ላይ እንዲቆይ ያስቻለው ጀግንነቱ ሳይሆን ቀድሞ የነቃ ስለነበረ ብቻ ነው። ይህንን ዕውነታ እዚህ ያላችሁት አማሮችም አትስቱትም። አሁን ግን ሁላችንም ነቅተናል’ ሲሉን አለቆቻችንንም በመፍራት በየተቀመጥንበት ወንበር ተሸማቀን ጭብጥ አክለን ነበር የምንቀመጠው። ሁኔታው ሲታይ የአንድን ሀገር ጊዚያዊ መተዳደሪያ ህግ ለማጽደቅ ሳይሆን አንድን ሕዝብ ለመወንጀልና ለማዋረድ ሆን ተብሎ የተሰናዳ ስብሰባ ነበር የሚመስለው። እየነገርሁህ ያለሁት የአንድን ሀገር ጊዜያዊ ሕግ ለማውጣት በተሰበሰበ ከፍተኛ ጉባዔ መባል ያልነበረበትን በእኛ ላይ ያነጣጠረ የብልግና ንግግሮችን ቀንሼ ነው” ብሎኛል ከልቡ እያዘነ።

 

የአማራ ልጆች ተጋድሎ ይህንን ሁሉ ሸክማችሁን ለማቅለልም ስለሆነ በዕኩል ዐይን ታይተን መብታችን እንዲከበር ለሚደረገው ትግል የበኩላችሁን ድርሻ መወጣት ይኖርባችኋል። ይህ ትግል የእናንተ የክብር አካል ነው። የአማራው ትግል ከተኮላሸ በስድብ ብቻ ሳይሆን በአለንጋም እየገረፉ እንደሚያሰሯችሁ ልትገነዘቡት ይገባል። ስለዚህ በመጀመሪያ ድርጅታችሁን ከሰርጎ ገቦች ለማጽዳት ውስጥ ለውስጥ ተነጋገሩ። የእኛ ባልሆኑ ሰዎች አንመራም የሚል ጽኑ አቋም ይኑራችሁ። በረከት ስምዖንም ሆነ ተፈራ ዋልዋ ወይም አዲሱ ለገሰ የታገሉት ለህብረ ብሄራዊ ድርጅቱ ኢሕዴን እንጅ ለአማራው አልነበረም፤ ደግሞም አማራ አይደሉም። ስለዚህ የነርሱን አመራርም ሆነ ምክር አንፈልግም ብላችሁ ከድርጅት አባልነት ሰርዟቸው። ከዚያም በየቀበሌው የማደራጀት፣ በአካባቢ ሚሊሽያ ስም ወታደራዊ ስልጠና የመስጠት፣ የማስታጠቅና የተከፈተባችሁን የዘር ጥቃት ለሕዝባችሁ በማስገንዘብ ራሳችሁን ለመከላከልና በጉልበት የተነጠቃችሁትን ታሪካዊ ይዞታችሁን ለማስመለስ በጽናት መቆም ይገባል። ዛሬ በእጃችሁ ያለውን ዕድል ካልተጠቀማችሁበት ወደፊት እንደምትጸጸቱበት አትጠራጠሩ። አማራነት እኮ መከበሪያም ማስከበሪያም ነው፤ የጥቁር ዘር ኩራት፣ የነጻነት ምልክት፣ የጀግንነት ምሳሌ ነው። ዛሬ በናንተ ጊዜ ከመሬት ወድቆ ማንም ሲረጋግጠው ዝም ብላችሁ ስትመለከቱ፣ ያም አልበቃ ብሏችሁ ከጠላት ወግናችሁ የጥፋቱ ተባባሪ ስትሆኑ በልጅ ልጆቻችሁ እንዴት ትታወሱ ይሆን! አሁንስ ህሊናችሁን አይቆረቁራችሁም! ብትሞቱስ ነፍሳችሁ እረፍት ታገኛለች! “እንዲያው ከምኑ ነው የተፈጠሩት!” መባሉ ብቻውን አያሸማቅቅም!”

 

አዲስ አበባ ፊንፊኔ የሚለው ስም በተለዋጭ ተይዞላታል። መንገዶቿም፣ አደባባይዋም እንደአስፈላጊነቱ ዲማ ነገዎ ጎዳና፣ ሌንጮ ለታ አደባባይ እየተባለ ይሰየምላታል። በአማራ ስም የሚጠሩ ኦሮሞወች ምን እንዳሰቡ አይታወቅም። ወደፊት ዶሮ ግብር ድረስ ያለውን የአማራ መሬት ወደትግራይ ለማካለል ሲታሰብ የኦሮሚያን ድጋፍ ለማግኘት ሲባል የከሚሴ ኦሮሞወች ወደኦሮሚያ መካለል አለብን የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ ይደረግና ቆቦ በጉልበት፣ ከሚሴ የሕዝብ መብት መከበር አለበት በሚል ሽፋን አማራን ይሰናበታሉ። እንዲህ እንዲህ እየተኮረኮመ አማራ ወደነበር ይሸጋገራል።

 

የአማራ ህልውናና መብት የሚከበረው በራሱ ትግል እንጅ በሕገመንግሥቱ አይደለም።  መፍትሄው ቆፍጠን ማለት ነው፤ ንፋስ ሳያስገቡ እጅ ለእጅ ተያይዞ መፋለም ነው። ያን ጊዜ አማራ እንደአውሬ መታደኑ ይቀርና ሁሉም ሰው መሆኑን አምኖ ይቀበላል። አሁን የሚንቀው ሁሉ ያከብረው ይጀምራል። የሚናገረው በቁምነገር ይደመጣል። ከሚሸሸው የሚቀርበው ይበዛል። የያዘው ይበረክታል የሄደውም ይመለሳል።

 

ትንሳኤ ለአማራ!

ትንሳኤ ለኢትዮጵያ!

እንደ ታሪኳ ያልታደለች አገር | “እኛ ያለንበትን ጉስቁልና …ታያላችሁ” (ነህ.2፡17)

ጸጋ አብ በቀለ

ከሰኔ 21-23/2009 ዓ.ም ለአገልግሎት ወደ ጎንደር ባቀናሁ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ ስለ ጎንደርና ስለአጠቃላይ ኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ ሸክምና መንፈስ ውስጥ አስገብቶኝ በፊቱ በጸሎት ሆኜ በብዙ አነባ ነበር፡፡

 

ጥቂት ስለ ጎንደር

በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን የሚትገኘ የዞኑ ዋና ከተማ ናት፡፡ ጎንደር፡- የኢትዮጵያ ቀደምት ነገሥታት መናገሻ መንበር፣ የዕውቀትና የስልጣኔ ማዕከል፣ ለብዙ ዘመናት የጦርነት አውዱማ ሆና የዘለቀች ምድር፣ በዩኒስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ በሥነ-ሕንፃ ዲዛዬን እጅግ የመጠቁ፣ የረቀቁ ዛሬም አጅግ ውብ የሆኑ ከ300 ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ የኢትዮጵያ ነገሥታት ቤተመንግሥት የታነፁባት፣የጠንካራና ትጉህ ሕዝብ መኖሪያ፣ …ድንቅ ምድር ናት፡፡ ጎንደር ያለ ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያም ያለ ጎንደር ሙሉዕ ታሪክ አይኖራቸውም፡፡ ጎንደር ውብ ናት፡፡ እንደ እ.ኤ.አ 2007 ቆጠራ ከሆነ የጎንደር ሕዝብ 207,044 ሲሆን የሃይማኖት ስብጥር ደግሞ 84.2% የኦርቶዶክ፣ 11.8% ሙስሊም፤ 1.1 የወንጌላውያን አማኞች እንደሆኑ ያመለክታል፡፡

ጥቂት ስለኢትዮጵያ

በአጠቃላይ ጎንደርን ጨምሮ የድንቅ መልክአ ምድር፣ የቀለመብዙ ቱባ ባሕል፣ ከ80 በላይ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች፣ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መኖሪያ፣ ባለብዙ ገድልና ታሪክ ባለቤት የሆነች አገራችን ኢትዮጵያ ያለፈ የቀደመ ታሪኳ በዓለም ላይ ቀዳሚ አላደርጓትም፡፡ የትላንት ድንቅ ታሪካችን ለዛሬ ለላቀ ራእይ፣ ሥራና ብዙ ፍሬዎች ባለቤት ካላደረገን፣ ወደ ኋላ ብቻ እያየን ለራሳችን ምንም ሳንሠራ የምንደነቅና የምንደመም ከሆነ ዋጋ የለምው፡፡ መልካም ታሪካችን እንደ መሰላል ወደ ላይ መውጫ ሳይሆን የማሰናከያ አለት ሆኖብናል ማለት ነው፡፡ እኛ ሁሌ የምንፎክርበት ጀግንነት፣ በባዕድ ኃይል ያለመገዛታችን፣ ቱባ ባሕላችን፣ ሃይማኖታችን፣ የአፄ ፋስል፣ የላሊበላና የአክሱም ድንቅ ኪነ ሕንፃና ሐዊልቶች…ከረሃብ፣ ከድህነት፣ ከእርስ በርስ ጥላቻ፣ ከጠባብነት፣ ከስደት እንድናመልጥ አላደረጉንም፡፡ በዓለም ላይ ከታሪኩ ጋር የማይመሳስል ምስኪን ሕዝብ ከመሆንም አልታደጉንም፡፡ በእኛና ባለፈው ታሪክ መካከል የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ሳይሆን በቅጡ ለማወቅ እንኳ ጊዜ ያለን አንመስልም፡፡ የት እየሮጥን እንደሆነ ግባችንን በትክከል አውቀን ለመናገር ባንችልም ፋታ በማይሰጥ ብርቱ ሩጫ የተጠመድን እንመስላለን፡፡

ለኢትዮጵያ መፍትሔ እግዚአብሔር ነው

መፍትሔው፡- እግዚአብሔር ነው፡፡ መፍትሔው፡- እውነተኛ ወንጌል ነው፡፡ መፍትሔው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ መፍትሔው፡- ብርቱ የእምነት ፀሎት ነው፡፡ መፍትሔው፡- ግልጽና ትልቅ ራእይ ያነገበ፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለብርቱ ሥራ የጨከነ ትውልድ መነሣት ነው፡፡ መፍትሔው፡- በእውነተኛ ወንጌል ልቧ የተለወጤ የሃይማኖትና የሥርዓት ማዕከል የሆነች ሳይሆን የዓለም ብርሃንና ጨው እንዲትሆን የተላከች እውነተኛ የክርስቶስ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን/ተለውጠው የለውጥ መሣሪያ ለመሆኑን የተዘጋጁ የቅዱስን ሕብረት/ በሙላት በኢትዮጵያ መገለጥ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ 97% ሃይማኖተኛ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እኔ እያወራሁ ያለው ስለሃይማኖት ሳይሆን እርግማን፣ ጨለማን፣ ኃጢአትን፣ ክፋትን፣ ያለመሥራትን፣ መደንዘዝን፣ ራእይ አልባነትን፣ ጥላቻን፣ የእርስ በርስ ጦርነትን፣ ያለመቀባበልን፣ መናናቅን፣ ጠባብነትን፣ መንደርተኝነትን፣ ያለማደግን፣ …ጽልመት ከላያችን፣ ከምድራችንና ከዓለም ሁሉ ላይ ለመግፈፍ ከላይ ከሁሉ በላይ ሆኖ ስለመጣው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስለኢየሱስ የሚያወሩ፣ ኢየሱሰን በአፍ የሚከተሉ፣ ኢየሱስን ሃይማኖታቸው ያደረጉ፣ የኢየሱስ ደጋፊዎች …ሳይሆን በኢየሱስ ወንጌል በእውነት ተለውጠው እርሷንም በሁለንተናዊ መልኩ የሚለውጧት የኢየሱስን ልጆች /ልበ-ክርስቲያኖችን/ ትፈልጋለች፡፡

ለመፍትሔነት ከእግዚአብሔር የተላከ ሕዝብ

“በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ፥ ከክፉ መንገዳቸውም ቢመለሱ፥ በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር እላለሁ፥ ምድራቸውንም እፈውሳለሁ”(2ዜና.7፡14)፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለተባለ፣ ስለሆነም መፍትሔ አይሆንም፡፡ የመጀመሪያ የሰማይ መዘጋት፣ የውስብስብ ችግሮች መኖር መከሰት በማመን፣ በማየት፣ 1. ሰውነታቸውን ማዋረድ፡- ራስን በእግዚአብሔር ፊት መጣል፣ ከጊዜው እጁ ከፍ እንድታደርገን አውቀን ራስን ማዋረድ፣ 2. መፀለይ፡- በፀሎት ሁሉ ይቻላልና 3. ፊቱን መፈለግ፡- እግዚአብሔርን ስለምድራችን ፊቱን መፈለግ፡፡ 4. ከክፉ መንገድ መመለስ፡- የእግዚአብሔር ሕዝብ ከክፉ መንገዱ ካልመለሰ አገርን ከክፉ መንገድ መመለስ አይችሉም፡፡ ቃሉም የእግዚአብሔርን ምላሽ ሲገልጽ፡- 1. በሰማይ ሆኜ እሰማለሁ፡፡ 2. ኃጢአታቸውን ይቅር እላለሁ፡፡ 3. ምድራቸውን እፈውሳለሁ፡፡ ይላል፡፡

በዚህ ልክ እንዳንገለጥ የማያስጨክነንና ለዚህች አገር መፍትሔ እንድንሆን የማያደርግን ክርስትና፣ መንፈሳዊነት፣ የወንጌል ስብከት፣ የቤተእምነትና የሚንስትሪ የስም ብዛት፣ የተወሰኑ ሰዎች መነቃቃት፣ መንፈሳዊ ግርግር፣ በፍርሽራሽ መካከል ሆነን “የእኔ እበልጣለሁ” ባዶና ከንቱ ያላዋቂዎች ፉኩኩር፣ …ሁሉም የክንቱ ከንቱ ናቸው፡፡ ወገኖቼ፡- ለራሳችንና ለአገራቸን ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን በተሰበረ ልብና መንፈስ፣ በጥልቅ ንስሐና በእንባ እንፈልግ፡፡ እንደ እስኮትላንዳዊው ሰባኪ “ኢትዮጵያን ወይም ሞቴን ስጠኝ” የሚሉ ማላጆች እንድንሆን ጌታ እየጠራን ነው፡፡ ጥሪውን ሰምተን እንመልስ ይሆን? መልሱ ከእያንዳንዳችን ለጌታ! ተባረኩ፡፡

ኅልውናዋ በማኅበረሰቦች ግጭት የተንጠለጠለ የሕወሓት ነፍስ – ምሕረት ዘገዬ

ሰሞነኛው ሕወሓታዊ  የዕውር ድምብር እንቅስቃሴ ብዙ ነገሮችን እንዳስታውስ አድርጎኛል፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህንን አዲስ አበባን ለኦሮሞ የመስጠት ጉዳይ በዩቲዩብ ስመለከት ከመደንገጥም አልፌ ከሦስት ቀናትም በኋላ አሁን ድረስ ላልተወኝ ራስ ምታት መጋለጤን ልደብቅ አልፈልግም፡፡ የዕብድ ሥራም አንዳንዴ ያስደነግጥና እስኪለቅ ድረስ መቸገር ይኖራል፡፡ የድንጋጤየ ዋና መነሻ ግን የወያኔው ዕብደት የወለደው ይህ ሕዝብን የማተረማመስ ሥልት ከቁም ነገር የሚጣፍ ሆኖ ሣይሆን ከወያኔው ታሪክ በመነሣት ብዙ “አይሆኑም” የሚባሉ ነገሮች በመሆናቸው እነዚህ ውሉዳነ አጋንንት የቆይታ ዕድል ካገኙ ይህም ቅዠት እውን ሊሆን እንደሚችል በመጠራጠር ነው፤ “ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር” ይባላልም እኮ፡፡ እንጂ እንዲህ ያለ ዘመኑን ያልዋጀ የዕብደት ዐዋጅ ኢትዮጵያን ያሰጋታል ብዬ ከልቤ አምኜበት አይደለም፡፡(በነገራችን ላይ ኤርምያስ ለገሠ በዚህ ነገር ዙሪያ የጻፈው ግሩም ወቅታዊ  ሀተታ አለና ያላነበበ ሰው ቢያነበው ጥሩ ነው እላለሁ፡፡)

ይህ ክስተት ከሚያስታውሱኝ በጣም በርካታ ነገሮች ውስጥ አንድ ሁለቱን ያህል ላስታውሳችሁ፡፡

ከምድራዊው ልጀምር፡፡ በትዳር ሕይወቷ ብዙ ልጆችን ያፈራች አንዲት የቤት እመቤት በጠና ትታመምና ንስሃ ለመግባት በዚያውም የኑዛዜ ቃሏን በእማኞች ፊት ለመስጠትና ይህችን “ቆሻሻ” ምድር ለመሰናበት ሁለት ሽማግሌዎችንና የነፍስ አባቷን ታስጠራለች (አሉ)፡፡ የተባሉት ሰዎች መጥተው ያችን እንደወያኔ በፅኑ ጣዕር ወህማም ላይ የነበረችን ሴትዮ በመክበብ ማዳመጥ ይጀምራሉ ፡፡ የአሥራ አንድ ልጆች እናት የሆነችው ወይዘሮ በቅድሚያ ንስሃዋን ማውረድ የፈለገች ይመስላል፡፡ እናም ቀጠለች – “መምሩ ደህና አድርገሁ ይፍቱኝ፤ በደምብ ይጸልዩልኝ፡፡ በቁርጥ ስለተያዝሁ እውነቱን ብቻ ነው የምናገረው፡፡ ለትዳሬ ታማኝ አልነበርሁም፡፡ … የመጀመሪያው ልጄን የወለድሁት ከጎረቤታችን ከአቶ አውግቼው ነው፤ ሁለተኛውን ልጄን የወለድሁት ከአጥቢያ ዳኛው ከአጋፋሪ እንደሻው ነው፤ ሦስተኛውንና አራተኛውን ልጆቼን የወለድሁት ከባለቤቴ ነው፤ … አምስተኛውን ልጄን የወለድሁት ከርስዎ ከራስዎ ከመምሩ ነው፡፡…” በእግዜር እጅ የተያዘችው እመቤት ንስሃዋን አልጨረሰችም፤ የሕይወት ድርሣኗን ከፍታ እውነትና እውነቱን ብቻ እየተናዘዘች ነበር፡፡ ሴትዮዋ በመጨረሻ የተናገረችውን ያልሰሙ በመምሰልና ለማመንም በመቸገር ጭምር ሽማግሎቹ ተደናግጠው “ምን አለች፣ ምን አለች?” ብለው እርስ በርስ ይጠያየቃሉ፡፡ ይህችን ጠባብ ዕድል ያገኙት የንስሃ አባት “ኧረ ገና ብዙ ትዘባርቃለች!” በማለት ሰዎቹ በቄሱ ላይ ያሳደሩትን ጥርጣሬን የተሻገረ የውስልትና ሥራ ለማስቀየስ ይሞክራሉ፡፡ ይህን ለማለት ያበቃቸው አለሥራቸው ታምተው ሣይሆን “ሴትዮዋ በጣር ስላለች የምትለውን አታውቅም” ለማለት ፈልገው ነው፡፡ አለቃ ገ/ሃናም ያመለጣትን እውነተኛ ፈስ እንዳልፈሳች ለማስመሰል ስትል በአፏ “ጡጥ!” ያደረገችዋን መንገደኛ “ይቺ ሌላ፣ ያቺ ሌላ” ሲሉ እንደነቁባት መግለጻቸውን እዚህ ማስታወስ ሳይገባኝ አይቀርም፡፡ የምትደበቅ እውነት እንደጭስ ናት – እንደምንም ብላ መውጣቷ አይቀርም፡፡

ለማንኛውም ወያኔ ገና ብዙ ይዘባርቃልና በጥንቃቄ መከታተል ተገቢ ነው፡፡ እነሱ ፈንጂ ባጠመዱ ቁጥር፣ እነሱ ወጥመድ በዘረጉ ቁጥር፣ እነሱ ጉድጓድ በቆፈሩልን ቁጥር እየዘለልን የምንገባ ከሆነ ስህተቱ የኛ እንጂ የነሱ አይደለምና በሚያልፍ መጥፎ ዘመን የማያልፍ ጠባሳ በታሪክ ስንክሳር ላይ ላለመተው ብዙ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን እኛ ብዙኃኑ ነን፡፡ እመለስበታለሁ፡፡

ሰማያዊውን ልቀጥልና ወደ ቁጭቴ(ማጠቃለያየ) ላምራ፡፡ በክርስትናው እምነት እንዲህ ያለ ታሪክ አለ፡፡ መላእክት ፈጣሪን – ማለትም – ቅዱስ እግዚአብሔርን በመንበሩ ያጡታል፡፡ ይደናገጣሉ፡፡ ያኔ የመላእክት አለቃ የነበረው ሊቀ ሣጥናኤል የመላእክቱን መደናገጥና የተፈጠረውን ክፍተት በመረዳት በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ሄዶ ይቀመጣል፡፡ ዱሮም ይቀና ነበር ማለት ነው፡፡

መላእክቱ “ማን ነው የፈጠረን?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ሊቀ ሣጥናኤልም “እኔ ፈጠርኳችሁ!” ይላቸዋል፡፡ ያመኑት አመኑ – በርሱም “ቆርበው ዳኑ”፡፡ ያላመኑት ግን “ፈጣሪያችንን እስክናገኝ በያለንበት (በጽናት) እንቁም!” ብለው ይወስናሉ፡፡ በወቅቱና አሁንም ቢሆን በኃያልነቱና በእልኸኝነቱ የማይታማው ሊቀ ሣጥናኤል እንደተነቃበት ሲረዳ እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ/ጦርነት ውስጥ ይገባና በየዋህነትም ይሁን በክፉ መንፈስ ተነድተው ፈጣሪያቸውን የካዱ መሰል መላእክት ጋር በመሆን በዓላማቸው ጸንተው ለፈጣሪያቸው ከቆሙት እነቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል ጋር ክንፋቸውን እየተነጫጩ በጨበጣ ይተጋተጉ ያዙ፡፡ በዚያ ታላቅ መንፈሣዊ ጦርነት እግዚአብሔር ባይደርስላቸው ኖሮ አሁን ዓለማችንን በታላቅ ግዳይነት አጋድሞ እየተጫወተባት የሚገኘው ሊቀ ሣጥናኤል ሊያሸንፋቸው ተቃርቦ እንደነበር የሃይማኖት አባቶችና መጻሕፍት ያስተምሩናል፡፡ ግን ያቺ የፈተና ጊዜ አልፋ ዳፋዋ ግን ለአዳምና ሔዋን ደርሳ በነሱም ሳቢያ ወደኛ ተላልፋ ይሄውና በሕወሓት አማካይነት ሌላ ኢትዮጵያዊ የመጨረሻ ፍልሚያ ውስጥ ገብተናል፡፡

አንደናገጥ፡፡ ብዙ ሰው የተደናገጠ ይመስላል፡፡ ብዙ ሰው ደግሞ እንደቀልድ እያዬ ይዝናናበት ጀምሯል፡፡ እንዳንደናገጥ የምመክረው ወያኔ ካርዶቹን ሁሉ አሟጦ ተጠቅሞ( አብዛኛውን በድርቅናና ሳናምንለት ነው) እዚህች የማትረባ ካርድ ላይ በመድረሱና ይህችም ካርድ እርባናቢስ በመሆኗ ነው፡፡ ወያኔና እግዚአብሔር፣ ወያኔና የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ወያኔና እውነት፣ ወያኔና ሰብኣዊነት… በቅጡ ሳይተዋወቁ እነዚህ እርጉሞች ሊሰናበቱ መቃረባቸው ግን በእውነቱ ያሳዝነኛል – “ሰው”ነትን አውቀውና ሆነውም ቢያዩት ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ከጉርምስና እስከ ጉልምስና፣ ከወመሽነት(ወጣት መሳይ ሽማግሌነት) እስከ ጅጅትና ፈጣሪንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ማወቅ አለመቻል የአለመታደል ሁሉ ጫፍ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የዐዋጅ ጋጋታም አንዱና ምናልባትም ትልቁ የድንቁርናቸው ምልክት ነው፡፡ አንድ ሰው እየሞተ እንኳን ልብ ካልገዛና ወደሰውነቱ – ወደኅሊናው ካልተመለሰ – በስም እንጂ በግብር ሰው መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ ለምሣሌ ወያኔዎች አዲስ አበባ እንደገቡ ሰሞንና ከዚያም በኋላ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የዘረፉትን የጥቁር አንበሣ ጄኔሬተር፣ የጎንደር ከተማ (ሆስፒታል?) ጄኔሬተር፣ የአዲስ አበባ ዳቦ ቤቶች(ከኤርምያስ ሁለተኛው መጽሐፍ እንዳነበብኩት)፣ በቢሊዮኖች ብር የሚገመት የመንግሥትና የግል ድርጅቶችን ሀብትና ንብረት … ቢቻል መመለስ ባይቻል ደግሞ መጸጸትና ለመካስ መሞከር ካልቻሉ በርግጥም እንደተወለዱ ሞቱ ሊባሉ የሚገባቸው የሰው ጭንጋፍ ናቸው፡፡ ይህን የቤት ሥራ ለትግራይ ክፍለ ሀገር ብንሰጥ የሚሻልና የምንችልም ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የሌባ ተቀባይም ከሌባው ባልተናነሰ የወንጀሉ ተካፋይ፣ በወንጀል ተግባሩ ከሚገኘው ማናቸውም ጥቅም ተጋሪና በወንጀሉም ተጠያቂ ነውና፡፡ የአሁንን ጥቅምና ፍላጎት ሳይወዱም ሆነ በግድ ማሟላት ብቻ ሳይሆን የነገን ኃላፊነትና ተጠያቂነትም ማሰብ አስፈላጊና ተገቢም ነው፡፡ እንዳለ የሚኖር ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር ተለዋዋጭ ነውና፡፡

አዲስ አበባ መተተኛ ከተማ ናት፡፡ አዲስ አበባ ልትለውጣቸው ያልቻለቻቸው ሕወሓትን የመሰሉ የጨለማው መንግሥት ወኪሎችን እንጂ ተራ ዜጋን በደቂቃዎች ውስጥ ለውጣ ክፉዎችን ገር፣ ተንኮለኞችን የዋህ የምታደርግ ግሩም ከተማ ናት፡፡ አንድ ሰው ከየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ይምጣ፣ የትኛውንም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ይናገር አዲስ አበባ ሲደርስ አዲስ አበቤ እንጂ ጎጃሜ ወይም ሸዌ፣ ወሎዬ ወይም ጎንደሬ፣ ወለጌ ወይም ሐረሬ … አይሆንም፡፡ ለልጆቿ ልዩ ፍቅር ያላት፣ ገዢዎች ጣልቃ እስካልገቡባት ድረስ በተቻላት መጠን ሁሉንም ልጆቿን በእኩል ዐይን የምታይ፣ ልዩ መስተጋብር ያላት፣ ልዩ የመቻቻልና የመደጋገፍ፣ የመተሳሰብና የመተዛዘን መንፈስ ያረበበባት በውነትም ልዩ ከተማ ናት – የኔ አዲስ አበባ፡፡ ሁሉንም ሆና፣ ስለሁሉም ተጨንቃና ተጠባ የሁሉንም ስሜት ገዝታ ከክፉዎቹ ገዢዎቿ መዳፍ ምሥኪን ልጆቿን ለመጠበቅ እየተጋች የምትኖር ከተማ ከአዲስ አበባ ውጪ ብዙም አላውቅም፡፡ ይህች ከተማ የሰውን ዘር በሙሉ እቅፍ ድግፍ አድርጋ ሳታስርብና ሳታሳርዝ የምታኖር ድንቅ ዓለም አቀፍ ከተማ ናት፡፡

አንድ ወቅት እንዲህ ሆነላችሁ፡፡ አንድ ሽማግሌ ከሰሜን ሸዋ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡበት የፍርድ ቤት ሙግት ነበራቸው፡፡ ቀጠሯቸው እየተራዘመ ሲሄድ አንድ ችግር ገጠማቸውና ለችሎቱ አቤት አሉ፡፡ “ክቡር ፍርድ ቤት፣ ውኃየ አልቆብኛልና በእግዜር ይሁንባችሁ ዛሬ ፍረዱልኝ ወይም ፍረዱብኝ!” ብለው ያመለክታሉ፡፡ የመሃል ዳኛውም “የምን ውኃ ነው ያለቀብዎት?” ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ እርሳቸውም “‹የአዲስ አበባ ውኃ አይለቅም‹ ሲባል ሰማሁ፤ ቤት ንብረቴን የትሚናቸውን ጥዬ እዚሁ መቅረት ስላልፈለግሁ የምጠጣውን ውኃ ታገሬ ተመንዝ ነው ይዤ የመጣሁት፡፡ የዚህን አገር ውኃ እዚሁ እንዳያስቀረኝ በመፍራት አልጠጣም፡፡…” አዎ፣ ዳኞቹ ተሳስቀው ወዲያዉኑ ወሰኑላቸው ይባላል፡፡ አዲስ አበባ ፍቅሯ እስከዚህ ነው፡፡

የአዲስ አበባን ባለቤትነት እንኳንስ ሕወሓት ዋና አዛዡ ዲያብሎስም አያገባውም፡፡ እንኳንስ ተላላኪው ሕወሓት የርሱ አለቆች ነጫጭባዎቹም አይመለከታቸውም፡፡ ይህች ታሪካዊት ከተማ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት እንጂ፣ የአፍሪካውያን የጋራ ንብረት እንጂ፣ የዓለማችን ሕዝብ የወል ገንዘብ እንጂ ከ90 ጎሣና ነገድ ለአንዱ ወይ ለሌላው በገጸ በረከትነት የምትሰጥ ቁስ አካል አይደለችም፡፡ የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ …. የለም … የለም… ተረቱ ልክ አይደለም – ባይሆን “በሰው ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” ቢባል ይሻላል፡፡ ለማንኛውም ወያኔዎች ስለተጨነቁ አይደለም እንዲህ ያደረጉት፡፡ ወያኔዎች ይህን ያደረጉት በተለይ ኦሮሞንና አማራን፣ በአጠቃላይ ደግሞ ኦሮሞንና ሌላውን ኢትዮጵያዊ ለማባላት ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተበላ ዕቁብ ው፡፡ አንዳንድ ጅላጅሎችና ወያኔ-ተከል መሠሪዎች ግን እዚህና እዚያ እንደማይጠፉ መጠቆም ብቻ ሣይሆን በርግጠኝነት እንዳሉ ተረድተን ምንም ኃይልና ጉልበት ሳናባክን በጥርሳችን ብቻ እየሳቅንባቸው ቀኒቷን እንጠብቅ፡፡ እኛ ግን አደራችሁን በከፍተኛ ደረጃ እንጠንቀቅ፡፡ “እንዲህ ልጠግብ በሬየን አረድሁ” እንዳለችው ነፈዝ ሴት ላለመሆን የምንሠራውንና የምንሆነውን እያሰብን እንሥራ፣ እንሁንም፡፡ ሲያልፍ ለሚቆጭ ነገር እንዳንዳረግ እንትጋ፡፡

የኢትዮጵያ ነፃነት አንድ ቦታ እየተሠራች ነው፡፡ ያገሬ ገበሬ “ሳለ ፈጣሪ አሟጠሸ ጋግሪ!” የሚለው በፈጣሪው ዕፁብ ድንቅ ተዓምራዊ ሥራ ስለሚተማመን ነው፡፡ ስለዚህም በሰብኣዊ የውሱንነት ባሕርይ ምክንያት የመምጫዋን ጊዜና የምትመጣበትን አቅጣጫ ለይቼ ማወቅ ባልችልም ነፃነታችን እጅግ ቀርባለች፡፡ ንፋሷ አልባብ አልባብ በሚለው መለኮታዊ መዓዛው እያወደኝ ነው፡፡…

እመለስበታለሁ ወዳልኩት ነገር ልመለስ፡፡ ወገኖቼ! “ዐይጥ ወልዳ ወልዳ ጅራቷ ሲደርስ ሲጥ አለች” ይባላል፡፡ “ጦም ጧሚና ሰው ጠባቂ” ሲባልም ሳትሰሙ አትቀሩም፡፡ ያልተነካካችሁ፣ የሰው ላብ፣ የሰው ደም፣ የሰው ሃቅ… የሀገርና የወገን ዕንባ… በእጃችሁ የሌለባችሁ ወገኖች ይበልጥ ተጠንቀቁ፡፡ በነፃነት ቀን የምናፍርበት መጥፎ ሥራ ይዘን እንዳንዋረድ አሁኑንና ከአሁኑ እውነተኛ ንስሃ እንግባ፡፡ ሀገራችን ስትፀዳ የሚወጣ ዕድፍና ቆሻሻ ይታየኛል፡፡ ከቤተ መንግሥት ተጠራርጎ የሚጣል እጅግ የሚገማና የሚሰነፍጥ ቆሻሻ ይታየኛል፡፡ ዲያቆናት፣ ደባትር፣ ካህናትና ጳጳሣት ከየቤተ ክርስቲያናት እንደቁንጫና ትኋን በፍሊት ተጠራርገው ሲወገዱና ዲያብሎስ በነሱ ውስጥ ሲወገር ይታየኛል፡፡ ቤተ እግዚአብሔርን መጫወቻና መሣቂያ መሣለቂያ እንዳደረጉት ሁሉ ማጣፊያው ለሚያጥራቸው መከራና ስቃይ ይዳረጋሉ፤ ያም ቀን ቀርቧል፡፡ በቤተ ክርስቲያናት አካባቢ የሚደረጉ ወንጀሎችንና ነውሮችን በሚመለከት ዝርዝሩን ብንናገር ቤተ ክርስቲያን የሚሄድን ሰው ተስፋ ማስቆረጥ ይሆናል፡፡ በጎቹን ቀበሮና ተኩላ የሚያስበላ እረኛ ዋጋውን ከጌታው ያገኛል፡፡

አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት፤ ያን ማን ካደ? አዲስ አበባ የአማራም ናት፤ አዲስ አበባ የትግሬም ናት፤ አዲስ አበባ የሁሉም ናት፡፡ ከመነሻውስ አዲስ አበባን ስጡን ብሎ በሰላማዊ ሰልፍም ይሁን በወረቀት አቤቱታ ያቀረበ ወገን አለ ወይ? አንዱ “ና አልመታህም!” አለው አሉ አንዱን፡፡ “ና አልመታህም”ን ምን አመጣው? አለና አልመታህም ተባዩ ሸሸው አሉ፡፡ እናስ! “አዲስ አበባን ለኦሮሞ ሰጠን፤ በኦሮምኛ የሚያስተምሩ ት/ቤቶች እንዲከፈቱ… ኦሮሞዎች ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ … ቋንቋቸው የሥራ ቋንቋ እንዲሆን…” ቲሪሪም ቲሪሪምን ምን አመጣው? ወያኔዎች ጊዜ ካገኙ ገና ብዙ ይዘባርቃሉ፤ እንኳን ከፎከረ ከወረወረም የሚያድነው አምላከ ኢትዮጵያ ይሠውረን እንጂ ብዙና ብዙ የሚያጨራርሱን ዕቅዶች በመጋዘናቸው ውስጥ አሉ፡፡ በኦሮምኛ ይቅርና በጋፋትኛስ ቢሆን አንደኛ ትምህርት ቤት ይቅርና በዩኒቨርስቲ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዳይከፍት የተከለከለ ወገን አለ ወይ? የምን ቅቤ አንጓችነት ነው? ማነው ሰጪ? ማንስ ነው ተቀባይ? ማን ነው መፅዋች? ማንስ ነው ተመፅዋች? የሚካኤል ሥሁል ልጆች ምንኛ ማረጡ በል!

ኦሮሞዎችና አማሮች ስሙኝ፡፡ በልጅነቴ ልጆችን የምናጣለበትንና እኔም ሕጻን ሳለሁ እያጣሉኝ ትልልቆቹ የሚዝናኑብኝን አንድ ጨዋታ ላስታውሳችሁ፡፡ ጎርመስ ጎርመስ ያሉት ነፍስ ያላወቁ ትናንሽ ልጆችን ያመጡና በእጃቸው መዳፍ ላይ ምራቃቸውን እንትፍ ይላሉ፡፡ ከዚያም ወደ ሁለት ልጆች መሀል ይዘረጉና “የማን አባት ገደል ገባ፤ የማን አባት ገደል ገባ!” ይላሉ፡፡ አባቱ ገደል እንዳይገባበት በመሥጋት ቀድሞ “የጀገነው” ልጅ ያን ምራቅ በማበስ ለመቅደም ፈራ ተባ ይል የነበረውን ሌላውን ልጅ ይቀባዋል፡፡ ያ ተደፈርኩ ያለው ልጅ ምራቅ የቀባውን ልጅ በዱላ ማቅመስ ወይም  የባላንጣውን ወገብ በትግልመሰቅሰቅ ይጀምራል፡፡ ጠቡ እየከረረ ይሄዳል፡፡ ልጆቹ በእልህ ሲፋለሙ የጠቡ አነሳሾች አንድ ጥግ ጥላ ላይ ቁጭ ብለው እየተደሰቱ ይዝናናሉ – እንደወያኔ በሰው ስቃይ መደሰት፤ ዘመነ ግላዲያተር በሉት፡፡  በሰባና በሰማንያ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት እፍኝ የማይሞሉ ወያኔ ትግሬዎች በነዚህ ኆልቁ መሣፍርት በሌላቸው አማሮችና ኦሮሞዎች መሀል በሚፈጥሩት አርቲፊሺል ጠብ ሊዝናኑና ሂትለራዊ አገዛዛቸውን ሊቀጥሉ መሆኑን የማይረዳ ዜጋ ካለ በርግጥም በትንሹ የዋህ ነው፡፡ የተደገሰለትን የዕልቂት አታሞ በራሱ ጊዜ እየደለቀ ወደ መቀመቅ ለመውረድ የተዘጋጀ የለዬለት በግ ነው፡፡ መቶና ዘጠና ሚሊዮን በግ ደግሞ ሊኖር አይገባም፡፡ የእስካሁኑ ይብቃን፡፡ ለራሳችን ስንል ነው የሚበቃን ደግሞ፡፡

ስለዚህ የትኛውም ከተማ ለማንም ተሰጠ ይባል፤ ግዴለም፡፡ ኢትዮጵያም ከነነፍሷ ለጭዳነት ቀርባ ባወጣች እየተቸበቸበች አይደለም እንዴ ? በነዚህ ማፊያዎች ያልተሸጠ ነገር፣ በወያኔ ያልተጓጓዘ ነገር፣ ሕወሓት ያላደረሰው ጥፋት ከፀሐይ በታች ምን አለ? ስለዚህ ለማይቀረው ነፃነታችን ወደፊት ከሚገለጥልን አቅጣጫ የሚመጣውን መልካም ንፋስ ከመጠበቅና የበኩላችንን አስተዋፅዖ በምንችለው ከማበርከት ባለፈ በነዚህ ያበቃላቸው የሰይጣን ሽንቶች እንዳንታለል የዜግነቴን አደራ እላለሁ፡፡

ለመሆኑ የኦሮሞው ችግር የስም ለውጥና በራስ ቋንቋ መናገር አለመቻል ነው እንዴ? አለቃ ገ/ሃና ምን አሉ? “ይቺ ሌላ፣ ያቺ ሌላ!”  አዳማና ናዝሬት፣ ቢሾፍቱና ደብረ ዘይት፣ ፊንፊኔና አዲስ አበባ፣ ጂጂጋና ጂግጂጋ፣ አለማያና ሀሮማያ፣ አዋሳና ሀዋሳ፣….  በራሳቸው ዳቦ የሚያስገኙ ቢሆን፣ ዴሞክራሲና ነፃነት የሚያመጡ ቢሆን፣ ስደትን የሚያስቀሩ ቢሆን፣ በመቶ ሺዎች በረንዳ የሚያድሩ ዜጎቻችንን ቤት ውስጥ የሚያሳድሩ ቢሆን፣ የወያኔን የመሬት ዘረፋና የሕወሓታውያንን ጋጠወጥነት የሚከላከሉ ቢሆን፣ የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብት ከሕወሓት ዘረፋና ንጥቂያ የሚታደጉ … ቢሆን ኖሮ የኔም ስም ከምሕረት ወደ ሥምረት ይቅርና ወደጄምስና ዊሊያም ቢለወጥ ግድ ባልነበረኝ፡፡ ችግሩ ያ አይደለም፡፡ ችግሩ ራስን እያሳከከን እግርን በማከክ ለመርዳት የመሞከር ጉዳይ ነው – ያልተገናኝቶ፡፡ ግን ግን ከዚያች ሴተኛ አዳሪ የምንማረውና ልብ የምንገዛው መቼ ይሆን? እንደወያኔ ያለ ሞላጫ አጭበርባሪ በ“ነገ እሰጥሻሁ” የማያልቅ ነገ  እያታለለ ቢያሰለቻት ጊዜ “አጭበርባሪ ‹አይበልጠኝም›!” አለቻ! ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ ሆኖ ሳለ ወያኔ ቤተ መንግሥት ውስጥ ቁጭ ብሎ ያሻውን እያደረገ በዚህ በጣም ትንሽ ነገር ያጨራርሰናል፤ ለነገሩ እነሱ ምን አጠፉ? ገልቱዎቹ እኛ! በ“ማን አባት ገደል ገባ!” የሕጻናት ጨዋታ ተሸንፈን ሀገራችንን ከኛ ላነሱ ደናቁርት የሰጠን እኛው ነንና there is no one to blame. ዓለማችን ውስጥ ከ7106 የማያንሱ ቋንቋዎች ይነገራሉ፡፡ አንዱ አንዱን ይውጣል፤ አንዱ ከአንዱ ማሕጸን ይወጣል፡፡ በዚህ ሰው ይተላለቃል? ወይ ሞኝነት! በጀመርኩት እንግሊዝኛ ባወራ፣ በኦሮምኛ ባወራ፣ በአማርኛ ባወራ፣ በትግርኛ ባወራ፣ በጉራግኛ ባወራ፣ በሱማሌኛ ባወራ፣… ሃሳቤን ገለጥኩበት፣ ከሰው ጋር ተገናኘሁበት እንጂ ቋንቋ እኔን ፈጠረኝ እንዴ? ኢንሻኣላህ – እመለስበታለሁ፡፡ ግን ልድገመው – የቀጣፊ ሲሳይ አንሁን!! ችግራችን የሀገር ማጣት እንጂ የቋንቋና የቦታ ስም አይደለም፡፡ ወያኔዎች ዳቢትና ወርቹን፣ ፍሪምባና ጭቅናውን ይዘው እኛን በባዶ ጭራና ለዋገምትና ለዋንጫ እንኳን በማይውል ጠማማ ቀንድ ሲያጣሉን ማየት እጅግ ያማል፤ እናንተንስ አያማችሁም? mz23602@gmail.com

ባህር ዳርና ደብረ ታቦርን ጨምሮ በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች አመፅ አደራጅተዋል የተባሉ ተከሰሱ – ታምሩ ጽጌ

መንግሥትን በኃይል የመለወጥ የፖለቲካ ዓላማ በመያዝ ታኅሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በአማራ ክልል በሚገኙ የባህር ዳርና የደብረ ታቦር ከተሞችን ጨምሮ፣ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች አመፆችና ረብሻዎች እንዲፈጠሩ የማደራጀትና የማንቀሳቀስ ተግባር ሲፈጽሙ ነበር የተባሉ 17 ሰዎች በሽብር ተግባር ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የወንጀል ሕግ አንቀጽ 35፣ 38፣ 32(1ሀ) እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001  አንቀጽ (4) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ የተባለው አርበኞች ግንቦት ሰባት ክንፍ (ሴል) የሆነውን ‹‹የአማራ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ›› (አሕነን) በሟቋቋም፣ አባላትን ሲመለምሉና ሲያደራጁ ቆይተው ዓላማቸውን ለመፈጸምና ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡

በአማራ ክልል እየተፈጠረ ያለውን ግጭት ያመጡት የመንግሥት ባለሥልጣናት መሆናቸውን በመነጋገር፣ ሥልጣን ያለውን መንግሥት በማስወገድ ሌላ መንግሥት ማቋቋም እንዳለባቸው ወስነው ቡድኑን ማቋቋማቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

‹‹መንግሥትን በኃይል በማስወገድ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር አብሮ መታገል ነው፤›› በማለት ውይይት አድርገው በርካታ አባሎችን በመመልመል፣ በማሠልጠንና በማስታጠቅ ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉት ተከሳሾች ታደሰ መሸሻ፣ አዱኛው ካሳዬ፣ ዮናስ ጋሻው፣ ይስማው ወንድሙ፣ ጌታ አስረዳ፣ ክንዱዓለም አስፋው፣ አቻምየለህ ደሴ፣ ደባሱ ቦጋለ፣ ዓለማየሁ ደሴ፣ አበባው መኮንን፣ ቀለምወርቅ ዘለለ፣ ሙላት ጥላሁን፣ ታፈረ መኮንን፣ መልካለም ጌጡ፣ ደረጀ አብርሃም፣ ቄስ ደመቀ ዓለሜና ነብዩ ሉሌ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ ታኅሳስ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በደብረ ታቦር ከተማ የሽብር ድርጅት ክንፍ አመራር የሆኑት ጌታ አስረዴ፣ ይስማው ወንድሙና አዱኛው ካሳ ተሰባስበው ታኅሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች ጦርነት ለመጀመር መስማማታቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

በመሆኑም በክልሉ የሚገኙ ዋና ዋና መንገዶችን መዝጋት፣ ጥይት ለቡድኑ ታጣቂዎች ማሠራጨትና ማከፋፈል ተቀዳሚ ሥራቸው ቢሆንም በዋነኛነት የክልሉን መንግሥት ፖሊስ ልዩ ኃይል አዛዥ ላይ ዕርምጃ መውሰድ፣ በፖሊስ ጣቢያ፣ በመከላከያ ካምፕና በማረሚያ ቤቶች ላይ ጥቃት ማድረስ ተቀዳሚ ዕቅዳቸው እንደነበር ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ ያብራራል፡፡

ተከሳሾቹ እንዲዘጉ ትዕዛዝ ያስተላለፉባቸው መንገዶች ፍኖተ ሰላም፣ ባህር ዳር፣ ጣራ ገዳም፣ ጎንደር፣ ጋይንትና ጭስ ዓባይ መሆናቸውንና ሌሎች ቦታዎችንም እንደሚያካትት ክሱ ይዘረዝራል፡፡

በስማ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያና ማረሚያ ቤቶች ላይ ታጣቂዎችን በማሰማራት ጥቃት እንዲፈጽሙ የግንቦት ሰባት ሴል የሆነው የአሕነን ቡድን እስከ 3,000 ጥይቶችንና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን አስታጥቆ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ በደቡብ ጎንደር ውስጥ ያሉ የሴሉ አባላትን በማደራጀትና በደብረ ታቦር ከተማ ውስጥ በትጥቅ የታገዘ አመፅ በማቀድና በማነሳሳት፣ 40 ሰዎችን ማዘጋጀታቸውንና በደቡብ ጎንደር ዞን ከተሞች ውስጥ አመፅ ለሚያደርጉ 1,000 ጥይቶች መላካቸውን ዓቃቤ ሕግ አክሏል፡፡

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የሴሉ መሪና አደራጅ በመሆንና ተልዕኮ በመስጠት፣ ታኅሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. አመፁ እንዲካሄድ ማድረጋቸውን ጠቁሟል፡፡ አመፁ በጎንደርና በወረታ በመጀመሩ በምድር ድንጋይ፣ በመካነ ኢየሱስና በንፋስ መውጫ ከተሞች ወጣቶች የአመፁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ በባህር ዳር፣ በፍኖተ ሰላምና በሌሎችም አካባቢዎች ላይ ረብሻውና አመፁ በመነሳቱ የሰው ሕይወት እንዲጠፋና ከፍተኛ የንብረት ውድመት እንዲከሰት ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ በተመሠረተባቸው ክስ ላይ መቃወሚያ እንዳላቸው የተጠየቁት ተከሳሾቹ እንዳላቸው በመግልጻቸው፣ በጠበቃ ተወክለውና መቃወሚያቸውን ይዘው ሰኔ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡