አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ሃጎስን ያሳሰረ የስኳር ፋብሪካ ጦስ! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

ዳዊት ከበደ ወየሳ

kuraz sugar corporation

የመንገድ ስራዎች ባለስልጣን ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ሃጎስ በትላንትናው እለት በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል። አቶ ዛይድ የመንገድ ስራዎችን ኮንትራት ለቻይና ድርጅቶች በመስጠት፤ ምናልባትም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሙስና ውስጥ እንደገቡ ተደርጎ በተደጋጋሚ ስማቸው ሲነሳ ቆይቷል። ትንሽ ውስብስብ የሚመስለውን የሙስና እንቆቅልሽ ለመፍታት ግን፤ ይህን በአገር ላይ የሚደረግ ድራማ ከስር መሰረቱ መፈተሽ ያስፈልጋል።

ዝርዝር ጉዳዮችን ወደጎን በመተው በቀጥታ ወደ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ እንሄዳለን። የስኳር ፋብሪካው የግቤ ግድብን ተከትሎ የተሰራ፤ በአቶ አባይ ጸሃዬ የሚመራ ፕሮጀክት ነው። ለአቶ አባይ ጸሃዬ እንደጉዳይ አስፈጻሚ ሆነው፤ የሚወከሉት ደግሞ የስኳር ፋብሪካው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ደስታ ነበሩ። (ባለፈው አመት ከስልጣናቸው ከተነሱ በኋላ፤ ትላንት ምሽት ላይ በሙስና ተጠርጥረው መታሰራቸው ተሰምቷል)

የመንገድ ስራዎች ባለስልጣኑ መስሪያ ቤት ሌሎች አስቸኳይ ስራዎች ቢኖሩበትም፤ በ2014 ዓ.ም ግን አስቸኳ ትዕዛዝ፤ ከትራንስፖርት ሚንስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ቢሮ ደረሰው። በደቡብ ክልል ወደ ኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ የሚወስድ 79 ኪሎ ሜትር መንገድ ባስቸኳይ እንዲሰራ አስቸኳይ ትዕዛዝ ተላለፈ።

በውሳኔውም መሰረት አቶ ዛይድ፤ ሃሙስ እለት… ኦክቶበር 30፣ 2014 ዓ.ም ከቻይናው “ሲኖሃይድሮ” ድርጅት ጋር እንዲፈራረሙ ተደረገ። ይህም በአንድ ኪሎሜትር – 21 ሚሊዮን ብር ክፍያ መሆኑ ነው። ይህንን ውል በተፈራረሙ በማግስቱ፤ አርብ እለት አቶ ዛይድ በተወካዮች ምክር ቤት፤ ከትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ስብሰባ ላይ ነበሩ። ስብሰባው አልተገባደደም። ሰኞ እለት ቀጣዩን ስብሰባ ለማድረግ ተወያይተው፤ ከተወካዮች ምክር ቤት ወጡ። ሆኖም አቶ ዛይድ ከስብሰባ ወጥተው ወደ ስራ ሲመለሱ፤ በጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ፊርማ፤ የስንብት ደብዳቤ ነበር የጠበቃቸው።

እንግዲህ ለስኳር ፋብሪካው 79 ኪ.ሜ መንገድ ማሰሪያ፤ የ21 ሚሊዮን ብር ክፍያ እንዲደረግ ካስፈረሟቸው በኋላ በንጋታው፤ በእንዲህ አይነት ድራማ፤ ለአስር አመታት የባለስልጣኑ መስሪያ ቤት ዳይሬክተር ሆነው ከሰሩበት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መስሪያ ተባረሩ። ከወያኔ ቁልፍ ሰዎች ጋር በመስራት የሚታወቀው “ሲኖሃይድሮ” በዚህ አይነት የውል ወረቀቱን እጁ ካስገባ በኋላ፤ አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል በንጋታው፤ ያውም በጠቅላይ ሚንስትሩ ፊርማ ከስልጣናቸው ተነሱ። በምትካቸውም ሌላኛው የትግራይ ተወላጅ የሆኑት አቶ አርአያ ግርማይ ተተክተው እንዲሰሩ ተደረገ። (አቶ አርአያ ግርማይ አሁንም የባለስልጣኑ መስሪያ ቤት ዳይሬክተር ሆነው እየሰሩ ነው)

ወደ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ የሚወስደው መንገድ ከመጀመሩ በፊት፤ የአቶ ዛይድ ከመስሪያ ቤት ጀምሮ እስከ ተወካዮች ምክር ቤት መነጋገሪያ ሆነ። በእርግጥም ለሲኖሃይድሮ ድርጅት የተከፈለው ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑ አንደኛው መነጋገሪያ ነው። ነገር ግን ከአለም ባንክ የሚገኝ ገንዘብ ያለአግባብ ሲመነዘር እና ሲበተን ይህ የመጀመሪያው አልነበረም።

ቀደም ብሎም በትግራይ መንገድ ላይ ከዚህ የበለጠ ገንዘብ ወጪ ሆኖ ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኗል።  ይህ የሆነው …ከ3 አመታት በፊት፤ ጁን 24 ቀን 2014 ዓ.ም ነው። በትግራይ ለተገነባ መንገድ በ1 ኪሎ ሜትር 39.6 ሚሊዮን ብር እንዲከፈል የተደረገበት አጋጣሚ ነበር። በዚህ አገር ስሌት… አንድ ማይል ለማይሞላ መንገድ፤ 2ሚሊዮን ዶላር (በወቅቱ የብር ምንዛሪ)  ክፍያ ማድረግ ማለት ነው። ኪሎ ሜትር በጨመረ መጠን ምን ብዙ ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ይታወቃል። ይህ ለትግራይ መንገዶች የተከፈለው የክፍያ መጠን ታይቶ እና ተሰምቶ የማይታወቅ፤ በህዝብ ስም ከአለም ባንክ የሚገኘው ገንዘብ በምን ያህል መጠን እንደሚባክን አመላካች መሆኑን ገልጸን እንለፈው።

ወደ አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ጉዳይ እንመለስ። አቶ ዛይድ ከሃላፊነታቸው በተነሱ ማግስት፤ ጉዳዩ በሰራተኛውና በሚያውቋቸው ሰዎች ዙሪያ መነጋገሪያ ሆነ። ወሬው ከመጠንከሩ በፊት ግን፤ ለአቶ ዛይድ አዲስ የስራ ሃላፊነት ተሰጣቸው። በተባበሩት መንግስታት ስር በሚገኘው – ሞንትሪያል ካናዳ International Civil Aviation Organization (ICAO)፤ የኢትዮጵያ መንግስት የሲቪል አቪዬሽን ቋሚ ተወካይ ተደርገው ተሾሙ። አቶ ዛይድ በኢኮኖሚክስ ያገኙት ማስተርስ ዲግሪ፤ ለዚህ የሲቪል አቪዬሽን ስራ  ብቁ የሚያደርጋቸው አልነበረም። ነገር ግን በወቅቱ አቶ ዛይድን ማራቅ አስፈልጎ ነበርና፤ የማይመጥናቸው ትልቅ ሃላፊነት ተሰጥቷቸው በሞንትሪያል እንዲቆዩ ተደረገ። (በነገርዎ ላይ ICAO በ1944 ሲመሰረት ኢትዮጵያ ከመስራቾቹ አገሮች አንዷ ነበረች)

አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ሃጎስ በቁጥጥር ስር ይዋሉ እንጂ፤ አሁንም በካናዳ የሚገኘው ICAO ከኢትዮጵያ የተሾመበት ባለሙያ የለም።ከሳቸው በፊት በጊዜያዊነት ይሰሩ የነበሩት አቶ ነብያት መኮንን ቀደም ብለው ስራውን ለቀዋል። ከዚያ በፊት የነበሩት አቶ ተፈራ መኮንን ደግሞ በናይሮቢ የድርጅቱ ICAO ዋና መስሪያ ቤት እየሰሩ ይገኛሉ። ከነሱ ሁሉ ቀድመው የ ICAO ተወካይ የነበሩት አቶ መሸሻ በላይነህ ደግሞ በሂሳብ ሊቅነታቸው የሚታወቁ፤ በአሁኑ ወቅት በ ICAO የድርጅቱ የቴክኒክ ትብብር ምክትል ዳይረክተር ናቸው። አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ሃጎስ ግን የተሰጣቸውን አዲስ ሹመት አጣጥመው ሳይጨርሱ፤ ከሁለት አመት በኋላ አገር ሰላም ብለው በተመለሱባት ኢትዮጵያ፤ ትላንት ምሽት በቁጥጥር ስር ውለው የሰሞኑ ዜና ለመሆን በቅተዋል።

ከሳቸው ጋር ደግሞ አቶ ኪሮስ እና አቶ አለማየሁ ጉጆ ታስረዋል። አቶ አለማየሁ ጉጆ ከአስር አመት በፊት በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር በአቶ መለስ ዜናዊ የተሾሙ የፋይናንስ ባለስልጣን ናቸው። በቁጥጥር ስር በዋሉ ግዜ ደግሞ የኢኮኖሚና ትብብር  ሚንስትር ደኤታ ነበሩ። ፈረንጆች ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ወንጀል ሲሰራ “Follow the Money” ይላሉ። ተፈጠረ የተባለውን የገንዘብ ብክነት ሲከታተሉ፤ አቶ አለማየሁ ጉጆ ላይ ደርሰዋል። ይህ ገንዘቡን የመከተል ስራ በትክክል ከቀጠለ፤ የስንቱ ባለስልጣን ቤት ሊንኳኳ እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

የተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ “ያለመታሰር መብት”ን በመግፈፍ፤ እነ አቶ አለማየሁ ጉጆ ወደ እስር ቤት ሲገቡ አይተናል። በነአቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ላይ የተሰራው ድራማ የሚገርመንን፤ ጄነራሎቹ፣ የጄነራሎቹ ሚስቶች፣ እነአባይ ጸሃዬ፣ አዜብ መስፍን፣ አቦይ ስብሃት ነጋ እና ሌሎችም ህዝብ የሚያውቃቸው ሙሰኞች አሁንም ቆመው መሄዳቸው ይበልጥ ይደንቀናል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s