ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ ማለት አይቻልም (ሸንቁጥ አየለ)

አንዳንድ ሰዎች ለምን ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመስራት አትታገሉም ሲባሉ ከአማራ ትምክህተኞች ጋር ለመስራት ይከብዳል ይሉሃል::ሌሎቹ ደግሞ የትግሬ ወያኔ አሁን እኮ ኢትዮጵያ የሚለዉን ነገር አፍርሶታል ይሉሃል:: አንዳንዶችም ከአክራሪዎቹ የኦሮሞ የኦነግ ቡድኖች ጋር እንኳን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር አንድ ማህበር በጋራ መርተህ ግብ አታደርሰዉም ይሉሃል:: ሌሎች ደግሞ ሌላ ምክንያት ይደረድሩና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር ከቶም አይቻልም ብለዉ በዉጫዊ ሁኔታዎች ላይ የኢትዮጵያን አንድነት ጉዳይ አንጠልጥለዉ የዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ጉዳይ ገፋ አድርገዉት ዘወር ይላሉ::
ሆኖም ሰዉ አይቶ ወይም ፓርቲ አይቶ ወይም ቡድን አይቶ አላማ አይነደፍም :: ሁኔታዎች ምቹ ስለሆኑ ወይም ስላልሆኑ ሀገር ይፍረስ ይቀንጠስ አይባልም:: ትግልም በሌሎች አስተሳሰብ ላይ ተንጠልጥሎ እና ተቃኝቶ የለም::ስለዚህ ስለሌላዉ ቡድን ሲባል የሚነደፍ የፖለቲካ ትግል ካለ እርሱ ትግል እና አላማ ሳይሆን እቃ እቃ ጨዋታ ነዉ ማለት ነዉ:: ወይም ፋሽን እንደ መከትል አይነት የትግል ፍልስፍና ነዉ::
ዋናዉ ጥያቄ መሆን ያለበት አንድ ነዉ:: ጥያቄዉ የዉስጥ እምነትህ ምንድን ነዉ? የሚለዉ ነዉ:: “ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ : ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያ ናት” የሚል ከሆነ መልስህ ከየትኛዉም በኩል ይሄን ሀሳብ የሚጋፋ ቢነሳ በቁርጠኛ የትግል አላማ ማስተካከል እንጅ የኢትዮጵያዊነትን ህልዉና ጥያቄ ምልክት ዉስጥ ማስገባት ከቶም አይታሰብም::
ቡድኖች እና አስተሳሰባቸዉ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሎም ገዥዎች ሁሉ ይለዋወጣሉ::የሀገር ህልዉና እስከተጠበቀ ድረስ ግን አንድን ሀገር ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን በጠራ የትግል መስመር መቃኘት ይቻላል:: ስለዚህ የትግሬ ገዥዎች: የአማራ ትምክህተኞች: የኦሮሞ አክራሪዎች እና የእንቶኔ ምናምኖች እንዲህ ስለሚሉ ወይም እንዲህ ስለሚያዉኩን ወይም ስለሚዋጉን  የዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ስራ ልንወጣዉ አንችልም ማለት መዠመሪያዉንም በዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ላይ እምነት የለህም ብሎም በሀገሪቱም ቀጣይነት ላይ የሚያነክስ ልብ አዝለህ ትዞራለህ ማለት ነዉ::
ትግሉ እዉነት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ደህንነት: ምቾት እና ሰላም ከሆነ መፍተሄዉ አንድ ነዉ::በሁለት እግር ቆሞ በጋራ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚፈጠርበትን ትግል ማድረግ ነዉ::ዘላቂዉ እና ብቸኛዉ መፍተሄ ይሄዉ ነዉ::ሌላዉ ሰበብ የናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ አገርም አያድን : ዘላቂም መፍትሄ አያመጣ::ለራስ ማህበረሰብም ወንዝ የሚያሻግር ጥቅም የለዉም:: በትንሹ እንኳን ከወያኔዎች ድል እንደተማርንዉ የአንድ ማህበረሰብ ብቻ ድል ለራሱ ለማህበረሰቡም እራሱ አጣብቂኝ ነዉ:: መዉጫ የለዉም::ዛሬ ወያኔ የሌላዉ ኢትዮጵያ ህዝብን አጣብቂኝ ዉስጥ ቢጥለዉም ከማንም በላይ ግን ከፍተኛ አጣብቂኝ ዉስጥ የገባዉ የትግራይን ህዝብ ነዉ::
እናም ምን ለማለት ነዉ ? ኢትዮጵያን ለማዳን ብሎም ዲሞክራሲያዊት ለማድረግ እያንዳንዱ ማህበረሰብ እና ግለሰብ ሌላዉን ወገን ሳይመለከት በሙሉ የባለቤትነት ስሜት ይነሳ እንጅ ሰበብ እና የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ፈሊጥን ሊተዉ ይገባል:: አንዳንዱ ከኢትዮጵያ መነጠያ ሰበብ ሲፈልግ “ኢትዮጵያዊ ሆኜ መኖር የምፈልገዉ መብቴን ሌላዉ ወገን የሚያከብርልኝ ከሆነ ነዉ” ብሎ ጣቱን ወደ ሌላዉ ከቀሰረ ብኋላ የመለዬት ፍላጎቱ ላይ ይጣበቃል:: ሆንም ማንም መብት ሰጭ ወይም መብት ነሽ አካል የለም::
ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የምትሰራዉ በጋራ ነዉ:: መብቶችም ሁሉ የጋራ  ናቸዉ:: ብሎም  የህግ የበላይነት ሲዘጋጅም ለዚህኛዉ ወይም ለዚያኛዉ ማህበረሰብ ተብሎ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሰማይ እና ግዛት ስር ላሉ ግለሰቦች: ቡድኖች እና ማህበረሰቦች ብሎም ዜጎች እኩል የሚሰራ እና ከፍተኛዉ የስልጣኔ ደረጃ ላይ የደረሰዉ የህግ ጽንሰ ሀሳብ እንዲሆን ተደርጎ ነዉ:: ይሄም ሁሉ ሂደት በጋራ እና በእኩል ታግሎ በጋራ እንዲተገበር ይደርጋል እንጅ እንደ ህጻን ልጅ እከሌ መብቴን ከነሳኝ ወይም መብቴን ካላከበረልኝ እንዲህ አደርጋለሁ ወይም እንዲህ አላደርግም ማለት አስቂኝ ነዉ::
በያገባኛል ባይነት : ሀገሩ ህልዉናዉ መጠበቅ አለበት ብሎም የግድ ደግሞ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መፈጠር አለበት ብሎ መነሳት እንጂ ወደ ሌላዉ ጣት በመቀሰር እና ሌላዉ እንዲያባብለዉ በመጠበቅ ዉስጥ በሚዋኝ የአስተሳሰብ መንፈስ እና ቅኝት ዉስጥ ተመስጎ የሚከወን አንድም ሀገራዊ ጉዳይ አይኖርም:: እንዲህ አይነቱ ሰበብ ድርደራ እነ እከሌ የጠዬቅሁትን መብቴን ስላላከበሩልኝ እገነጠላለሁ ከህብረቱ እለያለሁ የሚል አስመሳይ ተጠይቅ ለማደላደል የሚሸረብ አካሄድ ነዉ:: በአላም ላይ እንዲህ አይነት ቀልዳቀልድ ሀገራዊ ስራም ተሰርቶም አያዉቅም:: እናም ጥያቄዉ አንድ ነዉ::እምነትህ ምንድን ነዉ? የኢትዮጵያ ህልዉና ላይ ሙሉ እምነት አለህ? ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትሰራ ዘንዳ ቁርጠኛ አቋም አለህ? የሚል ሆኖ ይወጣል::
ኢትዮጵያን በጥቅል ማዳን ካልተቻለ ብሎም ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር እዉን ካልሆነ በርግጠኝነት ከዳር እስከዳር ያለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ከፍተኛ ትርምስ ዉስጥ እና ቀዉስ ዉስጥ ይገባል::አንዳንዶች አሁን ለጊዜዉ ወያኔ እንዳደረገዉ ከሌላዉ ማህበረሰብ በአንጻራዊነት የመደራጀት እና የመሰባሰብ ደረጃ ላይ ስለሆንን ብሎም ጉልበት ስላለን የራሳችንን ማህበረሰብ ማዳን ስለምንችል ኢትዮጵያ ብትድንም ባትድንም ግድ የለንም የሚል መንፈስ ዉስጥ ስለሚዳክሩ ነዉ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ ማለት ጨዋታን እንደ ታላቅ ብልጠት የያዙት:: ዋናዉን ቁም ነገር በድጋሚ መዞ ለማሳሰብ ደግሜ ለአስጽንኦት እዚህ ልድገመዉ:: ኢትዮጵያን በመላ ማዳን ካልተቻለ ማንም የሚድን የለም::ሁሉ በጋራ እኩል እሳቱ ዉስጥ ተያይዞ ይገባል::
Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s