የጎንደር ህዝብ የተቃጣበትን የመከፋፈልና የህልውና አደጋ ለመመከትና አንድነቱን ለማስከበር በታላቅ ስብሰባ ወሰነ!

ከሙሉነህ ዮሐንስ

(ነሃሴ 29 2009) በራሰ ተነሳሽነት የአርማጭሆ፣ የደንቢያ እና የጭልጋ ህዝብ ተጠራርቶ የወያኔን ጎንደርን የማፈራረሰ የቀቢፀ ተስፋ እኩይ ሴራ ለማክሸፍ በአንድነት እንደሚመክቱና ጎንደርን እንደሚታደጓት ስምምነት ተደርሷል። ስብሰባው የህዝብ ተወካይ ሽማግሌወች፣ የጎበዝ አለቆችና ብዛት ያለው ወጣት ህዝብ የተሳተፈበት ነው። የስብሰባው ሂደትና እጅግ ስሜት ቀስቃሽ ከሆኑ ግጥሞች ጋር እጃችን ገብቷል። ነገር ግን የህዝቡን ዝርዝር ሚስጥራዊ ስምምነት ለጠላት አሳልፎ ላለመስጠት፣ የተሰብሳቢውን ህዝብ ማንነት ላለማጋለጥ ስንል የስብሰባውን ልዩ ቦታና የድምፅ ፋይሉን ይፋ ከማድረግ ተቆጥበናል።

የስብሰባው ዋና የስምምነት ነጥቦች ግን በመግለጫ መልኩ ስለመጡ አጋርተናል፦

1) ጎንደር አትከፋፈልም። ህዝባችንን ባልጠየቅነው አዲስ ዞኖች መከፋፈል አጥብቀን እናወግዛለን አንቀበለውም። ይህ ከሃገር ተለይቶ ለምን ጎንደር ላይ ለምን በዚህ ሰአት ቢባል ዋናውን የነፃነት ጥያቄያችንን ለማዳፈን እኛን ከፋፍሎ ለማዳከም የታለመ የትግሬ ወያኔ ሴራ ነው።

2) የጎንደር ህዝብ በቅማንትና በአማራ ተብሎ አይከፋፈልም አንቀበለውም። ያልጠየቅነውን የህዝበ ውሳኔ የጫነው ከፋፋዩ የወያኔ ቡድንና ሆድ አደር ተላላኪወቹ ናቸው።

3) ሰፊውን ከሱዳን ድንበር ጋር የሚያዋስነውን በጎንደርና በጎጃም ያለውን ደንበራችንን ለረዥም አመታት በተግባር እየቆራረሰ ሲሰጥ የቆየው ወያኔ የመጨረሻ ደረጃ እቅዳቸው የሆነውን ጎንደርን ሙሉ ለሙሉ ከሱዳን ድንበር ነጥሎ በቤንሻንጉል ስም ሰይሞ ወደ ትግራይ ለመጠቅለል ያሴሩትን ሴራ ያጋለጠ ካርታ ሰሞኑን በይፋ በቴሌቪዥን አይተን እጅግ ተቆጥተናል። እልፍ አእላፍት ወገኖቻችን ባሻ ጥጋቡን ጨምሮ ህይወታቸውን የሰጡትን ድንበራችንን! የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አሳልፈን አንሰጥም።

4) የተፈጥሮ ድንበራችንን ተከዜን ተሻግሮ ጊዜ ሰጠኝ ብሎ ወያኔ በማናለብኝነት የወሰዳቸውን የሁመራ፣ የወልቃይት፣ የጠገዴና የጠለምት መሬቶች ወደ ታሪካዊ የጎንደር ግዛት እንዲመለሱ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን። ወልቃይት መሬቱ የጎንደር ህዝቡም አማራ ነው!

5) የኢትዮጵያ ህዝብ ለፀረ ወያኔ ትግሉ በሚያደርገው እርብርቦሽ በጋራና በህብረት መሰራቱ ከመቸውም ጊዜ አሁን ወሳኝ ምእራፍ ላይ ነንና በጋራ እንታገል የሃገራችንን መፃኢ እድል አብረን እንወስን እያልን ጥሪያችንን በድጋሚ እናስተላልፋለን።

ስብሰባውን የነሃሴ ገብርኤል ጨርሰናል። ይህ መግለጫ በጣምራ ኮሚቴ አመራሩ የነሃሴ መድሃኒአለም እለት ለህዝብ ተልኳል።

የግርጌ ማስታወሻ…የአቋም መግለጫውን ከቦታው ያደረሱን የህዝብ ተወካዮች ተከታታይ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል እኛም ወደ ህዝቡ መልእክቱን እናደርሳለን።

ትግራይ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ ከሀገርም በታች (የታላቋ ትግራይ ሀገራዊ የሟቹ ራእይ) -ሰሎሞን ይመኑ

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እንደ ትግራይ ነፃ አውጭው ግምባር የወንበዴ ቡድን ያሰበውን ያሳካ የለም፡፡

የተከዜ ማዶ ነፃ አውጭ የወንበዴው ቡድን፤የስልጣን ጥመኞች እና ነብሰ በላው ወታደራዊ አገዛዝ የመከራ ቀን ሰልፈኞች ጥርቅም ታላቋን ትግራይ ለመመስረት ያለውን ፍላጎት ለማሳካት ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር እጅ እግሯን አስሮ፤ወገቧን አጉብጦ የቁም እስረኛ ካደረጓት ሶስት አስርተ አመታት ቢጠጉም ለሀገር ወዳዱ ሀገር አልባ ህዝብ ግን ያሳዝናል፡፡ የተከዜ ማዶ ሽፍቶች ታላቋን ትግራይ ለመመስረትም የአማራ ለም መሬቶችን መዝረፍና የኢትዮጵያን ድንበርም ሉዓላዊነቷን አሳልፎ መስጠት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡


በተከዜ ማዶ አምባገነኖች የስልጣን ዘመን ይህ ሆነ፦
1-የትግራይ ክልል ለዘመናት ተራቁቶ የነበረው አካባቢውን መልሶ ለማልማት ባወጣው ፖሊሲና ባደረገው ጥረት ለተገኘው ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድሮ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ለመሆን መብቃቱን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በረሀማነት እንዳይስፋፋ የሚሠራ ቢሮ የገለፀ ሲሆን። ልማቱ ላይ ተቃውሞ ባይኖረኝም ታላቋ ትግራይ የምትባለው የኢትዮጵያ ጎረቤት ሃገር ከሌሎች የአለም ሃገራት ጋር ከሆነ እንግዲህ ውድድሩ በርግጥ በድርቅ ምክንያት 10 ሚሊዮን የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የሚፈልገው የኢትዮጵያ ህዝብ ለተከዜ ማዶ አምባገነኑ አይመለከትም ማለት ነው ምክንያቱም ሽልማቱን ለማሳየት የተጠቀመበት ካርታ ትክክለኛው የትግራዩ ነፃ አውጭ ግንባር የመሰረተውን እና እየመሰረተ ያለውን የታላቋን ትግራይ ካርታ እና ከአማራ ክልል የተወሰዱ መሬቶችን በግልጽ አሳይቶናል ይህም ወያኔ ከተመሰረተበት የደደቢት በርሃ እና ከማህበረ ገስገስቲ ትግራይ ጀምሮ ሟቹ ባለራእይ የተንኮል ሊቅ ያቀደውን ካርታ እንዳሳካ በልማታዊ ሚዲያው ሲያሳየን የህዝቡን ትርታ ለማወቅ እንጅ ያለቀ ካርታ እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ በመሆኑ ታላቋ ትግራይም ሽልማቱን እንደሃገር አሸንፋለች፡፡

* ከዚህም በተጨማሪ በአቢጃታ ሃይቅ በተከሰተው ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ እንዲሁም ድርቅ ምክንያት ከነበረው 100 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ውስጥ 50 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ደርቆ ልጆች ድሮ ሃይቅ በነበረው ቦታ ላይ ኳስ ሲጫወቱበት የተከዜ ማዶዎች ማፊያ መርዶ ነጋሪ የሆነው ኢቢሲ ዘግቦታል ሊንኩን ይጫኑ (https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1624508107581059&id=541629952535552)ታዲያ ይሄ ምን ማለት ነው? በአንድ ሃገር ውስጥ ብንሆን ኑሮ ይሄ ልዩነት ባልኖረ ነበር፡፡

***ሌላው ጉዳይም ጣና ሃይቅ እምቦጭ በሚባል መጤ አረም ሲወረር ህዝቡ ራሱን ሃይቁ ውስጥ አስገብቶ ለማጽዳት እየሞከረ ቢሆንም በተከዜ ማዶ ሰዎች እይታ ግን ለታላቋ ትግራይ ግንባታ ጥቅም የሌለው በመሆኑ እና የማይዘረፍ ሃብት በመሆኑ እንደ አቢጃታ ሃይቅ ሁሉ ጣና ሃይቅም እንዲደርቅ ወያኔ የበኩሉን እየሰራ ይገኛል፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ ሃይቁ ያጋጠመውን አደጋ ለመታደግ ከህዝቡ ገንዘብ እየተሰበሰበ ስለመሆኑ እና አሁንም ሃይቁን የማዳን ስራ በህዝቡ ላይ እንጅ በተከዜ ማዶ ባለስልጣኖች ዘንድ ምንም ሃሳብ ውስጥ እንዳልገባ በኢቢሲ ድጋሚ ሰማን ሊንኩን ይመልከቱ(https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1634962746535595&id=541629952535552)

የደስታ መግለጫ፦ የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግስታት ለታላቋ ትግራይ እና ለተከዜ ማዶ የስልጣን ጥመኞች ሽልማቱን አስመልክቶ የደስታ መግለጫ ላከ የሚል ዜና ሰማን ወይ የጉድ ሀገር ለካ እኛ ሳናውቀው ታላቋ ትግራይ እንጅ ኢትዮጵያ አልነበረችም የኢጋድ አባል፥
ለካ በአለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያ የምትወከለው በአዲሲቷ ሀገር በታላቋ ትግራይ ነው፡፡ የጉድ ሀገር ህዝቦች አቤት ስናሳዝን ሀገር ከአንድ ሰፈር ሲያንስ ይገርማል፡፡ ይህ ነበር የሟቹ ራእይ ለዚህም ነው ያሰቡትን አሳክተዋል ያልኩት፡፡

2ኛ-አሁንም ታላቋ ትግራይ ከአለም ሀገሮች ጋር ተወዳድራ የሲጋራ አጫሾችን ቁጥር በመቀነስ ከአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ሽልማቱን በአለም የጤና ድርጅት ካሸነፉ ሀገራት ውስጥ፦
1ኛ -የትግራይ ክልል
2ኛ -ጋምቢያ
3ኛ-ካሜሮን
4ኛ -ጋና
ዝርዝር ዜናው እዚህ ሊንክ ላይ ይገኛል(https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1395858750513482&id=907126906053338)ይህ እንግዲህ የትግራይ ሪፑብሊክን ለአለም የማሳወቂያ አንዱ ዘዴ ነው፡፡ አንድ ሀገር ውስጥ ብንሆን ኑሮማ የሚቀድመው ከሰፈር ስም የሃገር ስም ነበር፡፡ ግን እንዴት ነው ሌሎች ክልሎች የሲጋራ ፍብሪካ አላቸው እንዴ ያልተሸለሙት?

ይህ እንግዲህ ትግራይን እንደ ሃገር የማቆሙ ስራ ድብቅ ሳይሆን በግልፅ የአማራ ለም መሬቶችን በመዝረፍ እና በወያኔ የብሔረሰብ ጭምብል አዲስ የከፋፍለህ ግዛ መርህ እቅዱን አሳክቷል፡፡ ይህም መጀመሪያ የአማራ ክልልን በሱዳን በኤርትራ እና ጅቡቲ አዋሳኞችን መዝጋት ጀምሮ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ከ1961 እስከ 1991 ድረስ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ካበቃበት ከ1991 ጀምሮ እና ኤርትራም እንደ ሃገር ከቆመች ከ1993 ጀምሮ ወያኔም ጫካ ላይ የነበረውን ካርታ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ፡፡(ካርታ 1 ከ1991 በፊት የነበረው የአማራ ክልል ካርታ ይመልከቱ)በዚህ ካርታ ላይም የአማራ ክልል ከሱዳን ከኤርትራና ከጅቡቲ ጋር ያለውን የድንበር አዋሳኝ የሚያመላክት ሲሆን ካርታ 2 ላይ በግልጽ እንደሚታየውም ወሎ ሙሉ በሙሉ ከጅቡቲ ድምበር ባማውጣት እና በጎንደር በኩል ያለውን የኤርትራ ድምበር ለመዝጋት የተሞከረ ሲሆን አሁንም በሱዳን በኩል ያለውን አዋሳኝም ለመዝጋት ከአማራ ክልል የተዘረፉ ለም መሬቶችን በካርታ 3 ላይ ማየት ይቻላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አሁን ባለው የሰሜን ጎንደርን የመከፍፈል ሴራ የቅማንትን ህዝብ እንደመሳሪያ በመጠቀም የሱዳን ሰፊ አዋሳኝ የሆኑትን ቋራንና መተማን በብሔሩ ስም በማካተት አዲሲቷን ትግራይ የቤንሻጉል ለም መሬቶችን እና ሌሎች ድምበር ላይ ያሉትንም በመጨመር ሙሉ በሙሉ አማራ ክልልን ከሱዳን ድንብር የማጥፍቱ ስራ እየተሰራ መሆኑን ሰሞኑን ይቅርታ የተጠየቀበት ካርታ ማሳያ ነው፡፡

የሃገሪቱን የድምበር አዋሳኞችም በተለይ በሱዳን በኩል ያለውን መሬት ወያኔ ለሱዳን ለመስጠት የሚያደርገውን ጥረት እና የስጋት ቀጠና ብሎ የከለለውን ድምበር ገበሬው ከወያኔ ወታደር እና ከሱዳን ወታደር ጋር ጦርነት ከጀመረ አመታት ያለፉ ሲሆን ነገር ግን ሀገራዊ ትኩረት ባለማግኘቱ እና ድምበሩን የማስመለስና የማስከበር ሂደትም ክልላዊ ይዘት ተላብሷል ይህም የከፋፍለህ ግዛው መርህ በመስራቱ ነገም ቤንሻንጉልን በእድሜ ትንሿ መንግስት ደቡብ ሱዳን ጠቅልላ መውሰዷን ጉዳዩ ካለቀ በሗላ ልንሰማ እንችላለን ልክ ኢትዮጵያ የምትወከለው በታላቋ ትግራይ መሆኑን ከሰሞነኛ ሽልማቶች እንደሰማነው፡፡ ይህ ነው የሟቹም ራእይ፡

ሰሎሞን ይመኑ

ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ ማለት አይቻልም (ሸንቁጥ አየለ)

አንዳንድ ሰዎች ለምን ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለመስራት አትታገሉም ሲባሉ ከአማራ ትምክህተኞች ጋር ለመስራት ይከብዳል ይሉሃል::ሌሎቹ ደግሞ የትግሬ ወያኔ አሁን እኮ ኢትዮጵያ የሚለዉን ነገር አፍርሶታል ይሉሃል:: አንዳንዶችም ከአክራሪዎቹ የኦሮሞ የኦነግ ቡድኖች ጋር እንኳን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር አንድ ማህበር በጋራ መርተህ ግብ አታደርሰዉም ይሉሃል:: ሌሎች ደግሞ ሌላ ምክንያት ይደረድሩና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር ከቶም አይቻልም ብለዉ በዉጫዊ ሁኔታዎች ላይ የኢትዮጵያን አንድነት ጉዳይ አንጠልጥለዉ የዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ጉዳይ ገፋ አድርገዉት ዘወር ይላሉ::
ሆኖም ሰዉ አይቶ ወይም ፓርቲ አይቶ ወይም ቡድን አይቶ አላማ አይነደፍም :: ሁኔታዎች ምቹ ስለሆኑ ወይም ስላልሆኑ ሀገር ይፍረስ ይቀንጠስ አይባልም:: ትግልም በሌሎች አስተሳሰብ ላይ ተንጠልጥሎ እና ተቃኝቶ የለም::ስለዚህ ስለሌላዉ ቡድን ሲባል የሚነደፍ የፖለቲካ ትግል ካለ እርሱ ትግል እና አላማ ሳይሆን እቃ እቃ ጨዋታ ነዉ ማለት ነዉ:: ወይም ፋሽን እንደ መከትል አይነት የትግል ፍልስፍና ነዉ::
ዋናዉ ጥያቄ መሆን ያለበት አንድ ነዉ:: ጥያቄዉ የዉስጥ እምነትህ ምንድን ነዉ? የሚለዉ ነዉ:: “ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ : ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያ ናት” የሚል ከሆነ መልስህ ከየትኛዉም በኩል ይሄን ሀሳብ የሚጋፋ ቢነሳ በቁርጠኛ የትግል አላማ ማስተካከል እንጅ የኢትዮጵያዊነትን ህልዉና ጥያቄ ምልክት ዉስጥ ማስገባት ከቶም አይታሰብም::
ቡድኖች እና አስተሳሰባቸዉ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሎም ገዥዎች ሁሉ ይለዋወጣሉ::የሀገር ህልዉና እስከተጠበቀ ድረስ ግን አንድን ሀገር ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን በጠራ የትግል መስመር መቃኘት ይቻላል:: ስለዚህ የትግሬ ገዥዎች: የአማራ ትምክህተኞች: የኦሮሞ አክራሪዎች እና የእንቶኔ ምናምኖች እንዲህ ስለሚሉ ወይም እንዲህ ስለሚያዉኩን ወይም ስለሚዋጉን  የዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ስራ ልንወጣዉ አንችልም ማለት መዠመሪያዉንም በዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ላይ እምነት የለህም ብሎም በሀገሪቱም ቀጣይነት ላይ የሚያነክስ ልብ አዝለህ ትዞራለህ ማለት ነዉ::
ትግሉ እዉነት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ደህንነት: ምቾት እና ሰላም ከሆነ መፍተሄዉ አንድ ነዉ::በሁለት እግር ቆሞ በጋራ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚፈጠርበትን ትግል ማድረግ ነዉ::ዘላቂዉ እና ብቸኛዉ መፍተሄ ይሄዉ ነዉ::ሌላዉ ሰበብ የናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ አገርም አያድን : ዘላቂም መፍትሄ አያመጣ::ለራስ ማህበረሰብም ወንዝ የሚያሻግር ጥቅም የለዉም:: በትንሹ እንኳን ከወያኔዎች ድል እንደተማርንዉ የአንድ ማህበረሰብ ብቻ ድል ለራሱ ለማህበረሰቡም እራሱ አጣብቂኝ ነዉ:: መዉጫ የለዉም::ዛሬ ወያኔ የሌላዉ ኢትዮጵያ ህዝብን አጣብቂኝ ዉስጥ ቢጥለዉም ከማንም በላይ ግን ከፍተኛ አጣብቂኝ ዉስጥ የገባዉ የትግራይን ህዝብ ነዉ::
እናም ምን ለማለት ነዉ ? ኢትዮጵያን ለማዳን ብሎም ዲሞክራሲያዊት ለማድረግ እያንዳንዱ ማህበረሰብ እና ግለሰብ ሌላዉን ወገን ሳይመለከት በሙሉ የባለቤትነት ስሜት ይነሳ እንጅ ሰበብ እና የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ፈሊጥን ሊተዉ ይገባል:: አንዳንዱ ከኢትዮጵያ መነጠያ ሰበብ ሲፈልግ “ኢትዮጵያዊ ሆኜ መኖር የምፈልገዉ መብቴን ሌላዉ ወገን የሚያከብርልኝ ከሆነ ነዉ” ብሎ ጣቱን ወደ ሌላዉ ከቀሰረ ብኋላ የመለዬት ፍላጎቱ ላይ ይጣበቃል:: ሆንም ማንም መብት ሰጭ ወይም መብት ነሽ አካል የለም::
ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የምትሰራዉ በጋራ ነዉ:: መብቶችም ሁሉ የጋራ  ናቸዉ:: ብሎም  የህግ የበላይነት ሲዘጋጅም ለዚህኛዉ ወይም ለዚያኛዉ ማህበረሰብ ተብሎ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሰማይ እና ግዛት ስር ላሉ ግለሰቦች: ቡድኖች እና ማህበረሰቦች ብሎም ዜጎች እኩል የሚሰራ እና ከፍተኛዉ የስልጣኔ ደረጃ ላይ የደረሰዉ የህግ ጽንሰ ሀሳብ እንዲሆን ተደርጎ ነዉ:: ይሄም ሁሉ ሂደት በጋራ እና በእኩል ታግሎ በጋራ እንዲተገበር ይደርጋል እንጅ እንደ ህጻን ልጅ እከሌ መብቴን ከነሳኝ ወይም መብቴን ካላከበረልኝ እንዲህ አደርጋለሁ ወይም እንዲህ አላደርግም ማለት አስቂኝ ነዉ::
በያገባኛል ባይነት : ሀገሩ ህልዉናዉ መጠበቅ አለበት ብሎም የግድ ደግሞ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መፈጠር አለበት ብሎ መነሳት እንጂ ወደ ሌላዉ ጣት በመቀሰር እና ሌላዉ እንዲያባብለዉ በመጠበቅ ዉስጥ በሚዋኝ የአስተሳሰብ መንፈስ እና ቅኝት ዉስጥ ተመስጎ የሚከወን አንድም ሀገራዊ ጉዳይ አይኖርም:: እንዲህ አይነቱ ሰበብ ድርደራ እነ እከሌ የጠዬቅሁትን መብቴን ስላላከበሩልኝ እገነጠላለሁ ከህብረቱ እለያለሁ የሚል አስመሳይ ተጠይቅ ለማደላደል የሚሸረብ አካሄድ ነዉ:: በአላም ላይ እንዲህ አይነት ቀልዳቀልድ ሀገራዊ ስራም ተሰርቶም አያዉቅም:: እናም ጥያቄዉ አንድ ነዉ::እምነትህ ምንድን ነዉ? የኢትዮጵያ ህልዉና ላይ ሙሉ እምነት አለህ? ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትሰራ ዘንዳ ቁርጠኛ አቋም አለህ? የሚል ሆኖ ይወጣል::
ኢትዮጵያን በጥቅል ማዳን ካልተቻለ ብሎም ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር እዉን ካልሆነ በርግጠኝነት ከዳር እስከዳር ያለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ከፍተኛ ትርምስ ዉስጥ እና ቀዉስ ዉስጥ ይገባል::አንዳንዶች አሁን ለጊዜዉ ወያኔ እንዳደረገዉ ከሌላዉ ማህበረሰብ በአንጻራዊነት የመደራጀት እና የመሰባሰብ ደረጃ ላይ ስለሆንን ብሎም ጉልበት ስላለን የራሳችንን ማህበረሰብ ማዳን ስለምንችል ኢትዮጵያ ብትድንም ባትድንም ግድ የለንም የሚል መንፈስ ዉስጥ ስለሚዳክሩ ነዉ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ ማለት ጨዋታን እንደ ታላቅ ብልጠት የያዙት:: ዋናዉን ቁም ነገር በድጋሚ መዞ ለማሳሰብ ደግሜ ለአስጽንኦት እዚህ ልድገመዉ:: ኢትዮጵያን በመላ ማዳን ካልተቻለ ማንም የሚድን የለም::ሁሉ በጋራ እኩል እሳቱ ዉስጥ ተያይዞ ይገባል::

ለብቻው ቤተ-መንግስቱን ያንቀጠቀጠ ብላቴና፣ ቴዲ አፍሮ (ክንፉ አሰፋ)

ክንፉ አሰፋ

Teddy Afro the best Ethiopian singer

በነዚያ የነጠቡ ብዕሮች “ተራራውን ያንቀጠቀጠ” እየተባሉ ሲወደሱ የነበሩ ሁሉ እነሆ በአንድ ብላቴና ሲንቀጠቀጡ ከማየት የበለጠ ምስክር ከየትም ሊመጣ አይችልም። የ”ኢትዮጵያ” ስም ሲጠራ ብርክ እንደያዘው የሚሽመደመዱ፤ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት እየልን በጣት የምንቆጥራቸው የጥላቻና የበቀል ጉግማንጉጎች ለመሆናቸውም ትውልድን ደፍሮ ይናገርላቸዋል።  የዚህ ቡድን አባላት  ከመጠን ያለፉ ጭቃዎች መሆናቸውን እንኳ ለማወቅ ራሳቸውን በመስታወት የሚመለከቱ አይመስልም።

100 ሚሊዮን ሕዝብ እየመራ ያለው ይህ  ቡድን በየትኛውም መመዘኛ ቢለካ አርቆ ማሰብ እና አስተዋይነት ይጎድለዋል። አስተዋይነት ደግሞ የታላላቆች ውድ ስጦታ ስለሆነ ከርካሽ ሰዎች አይጠበቅም።

አበው ትተውልን ያለፉት አንድ ቅርስ፣ ያቺ የቀስተደመና ተምሳለት፣ ያቺ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ባንዲራ ስትነሳ አጋንንት እንደለከፈው እርያ የሚክለፈለፉ የዘመናችን ጉዶች…. አንድ ነገር እንዳላቸው አንክድም። የበተ-መንግስቱ ታራ ደርሷቸው የተቀመጡት ትንሾች ያላቸው አንድያ ነገር መሃይምነት ብቻ ነው።ግና ኮንሰርት በመከልከል ቴዲን የጎዱ እየመሰላቸው ይልቅ ተወዳጅነቱን በእጥፍ ጨመሩለት።

አንድ ኢትዮጵያዊ፣ ቴዲ አፍሮ ሲያርበተብታቸው አየን። በጩኸት ሳይሆን በዝምታ፣ በሰይፍ ሳይሆን በዘለሰኛ፣ በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር ብቻ የሚሰባብራቸው፣ ሰባብሮም ድል የሚያደርግ ጀግና። እንግዲህ በዚህ አይነት እጅግ በወረደ ተራ ነገር ይህን ድምጻዊ በገንዘብ ሊጎዱት ይችሉ ይሆናል። የህይወት ስንቅ የሆነው ፍቅር ግን ወዲህ ነው። የማይለወጥ የሚሊዮኖችን ፍቅር። እነ ደብረጽዮን አቅሙ ኖሯቸው ይህንን  ቢነፍጉት ኖሮ ቴዲ ሊጎዳ ይችል ነበር።  አንድ በቀነሱበት ቁጥር፣ በመቶ እጥፍ እንደሚጨመርበት ግን መቼም ሊያስተውሉት አይችሉም።

አያሌ እንቅፋቶችን አልፎ ዛሬ ምሽት ላይ በሂልተን ሆቴል ሊደረግ የነበረው የ”ኢትዮጵያ” አልበም ምረቃ  ባይስተጓጎል ነበር የሚገርመን። ምክንያቱም አልበሙ “ኢትዮጵያ”፣ መልእክቱም ፍቅር እና አንድነት ነዋ!  ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ሳይወድዷት ለሚገዙዋት ራስ ምታት ነው። ባንዲራዋን የሚጠሉ ሁሉ የሶስቱ ቀለማት መውለብለብ ያሳምማቸዋል።

ቴዲ አፍሮ፣ ፓርቲ ሳያቋቁም፣ በሶስትም ሆነ ባራት ሳይደራጅ፣  በአንዲት አልበም ብቻ ቤተ-መንግስቱን ያሸበረና የነቀነቀበት ምስጢር ይኸው ነው። የፈሪ ዱላቸውን የመምዘዛቸው ምስጢርም ኢትዮጵያዊነትን የመስበኩ ወንጀል ነው።  አንድ ዜማ ወደ ፍርሃት ጥግ ሲገፋቸው የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ አሳጣቸው። ኮንሰርቱን ሲያግዱ፣ የምርቃቱን ዝግጅት ሲከለክሉ፣ የባንዱን አባል ከሃገር ሲያባርሩ…

እርግጥ ነው። ብላቴናው ላውንቸር ወይንም ሚሳየል ሳይሆን ኢትዮጵያን ከጀርባው ይዟል። ዛሬ በዙፋን ሆነው ይፈርዳሉ። የግዜ ጀግኖች አሁንም በንጹሃን ዜጎች በድፍረት ፍርደ-ገምድል ውሳኔ ይበይናሉ። በዚህ ሁኔታ ለዘልዓለም የሚዘልቁም ይመስላቸዋል። ይህንን ሲያድደርጉ  የሚተማመኑበት አንድ ነገር አለ። ፋጣሪን አይደለም። ሕዝብንም አይደለም። ጠመንጃቸውን ነው የታመኑበት።   “የቆሙ የመሰለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” ይላልና ቃሉ የዛሬ ፈራጆች ነገ እንደማይወድቁ ምንም ዋስትና የለም። በእርግጠኝነት የምንናገረው አንድ ነገር አለ። ትውልድ አምጿል። ልብ በሉ! በመጭው አመት አንድ አዲስ ነገር እናያለን።  ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ይጠብቅ።