ሶስተኛውን መስቀለኛ መንገድ እንዴት እንሻገረው? ክፍተቱን ለመሙላት እንዳይረፍድብን.. 

መስቀሉ አየለ
አንጻራዊ በሆነ መልኩ ለግማሽ ምእተ አመት አገሪቱን አረጋግተው መግዛት የቻሉት ንጉስ ሃይለስላሴ ነበሩ። ገና ወደ ስልጣን መንበር ሲመጡ አገሪቱ የነበሩዋት የተቋማት ደረጃ እዚህ ግባ በማይባሉባትና የህዝቡም አስተሳሰብ ገና ፊውዳላዊ በነበረበት በዚያ የጨለማ ዘመን ደረጃቸውን የጠበቁ የአየር መንገድ፣ አለማቀፋዊ የሆነ የፍታብሔር እና የወንጀለኛ መቅጫ ድንጋጌዎችን ፣የመጀመሪያውን ህገመንግስታዊ ፓርላማ፣ የባህር ሃይል፤ የአየርና የምድር መከላከያ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የመሳሰሉትን መዋቅሮች ወዘተ ለማቆም ችለው ነበር። ያም ሆኖ በመጨረሻ ላይ ወቅቱ ይዞት በመጣው የሶሻሊዝም አስተሳሰብ ያስከተለውን ተጽእኖ ተቋቁሞና አገሪቱ እንደ ሃገር ካቆሟት ማንነት ጋር አቻችሎ ወደ ፊት ይዞ ለመሄድ ንጉሱ የደረሱበት የእድሜና መሰል ሁኔታዎች ተደማምረው ሂደቱን ማስቀጠል ባለመቻላቸው እንዲሁም ለውጥ ፍላጊ ሆኖ ብቅ ያለው የፊደል ሰራዊት የሚል ቅጽል ስም ያነገበው ትምህርት ቀመስ የሆነው ወጣት የዚያኑ ያህል ጠንካራ አደረጃጅት ኖሮት ስልጣኑን ለመረከብ ባለመቻሉ በተፈጠረው ክፍተት ጥቂት አስር አለቆች አጀንዳውን በመጠምዘዝ የዙፋኑን ስር ምንጣፍ ለመጎተት በቁ። የለውጥ አብዮቱ እርሾ የነበረውን አንድ ሙሉ ወርቃማ ትውልድ በልቶም ጥሎት ያላፈው ጣጣ ዛሬ ድረስ መልኩን እየቀያየረ አሁን ላለንበት ውስብስብ ችግር መዳረጉ ብቻ ሳይሆን አሉ የተባሉት የአገር ምልክቶች ሁሉ በሂደቱ ውስጥ በማለቃቸው በመጨረሻም እንደ ወያኔ ላሉ የጃርት ስብስቦች ትልቁን በር ከፍቶ እንደሰጣቸው ግልጽ ነበር። የደደቢቶቹ መርዛማ ፍሬዎች አዲስ አበባ ሲገቡ ካለ ፕሮፌሰር መስፍን፣ ፕሮፌሰር አስራትና መሰል ጥቂት አረጋውያን በስተቀር ይኽ ነው የሚባል ታዛቢ ሽማግሌ ነበር ማለት አይቻልም።
በሌላ በኩል ደግሞ እየወደቀም እየተነሳም፣ ሂደቱ ከሚፈጥራቸው ባንዳና ከሃዲ አስመሳይ ተቃዋሚዎች ጋር እየታገለም፣ ነገር ግን ባንድ እጁ ከወያኔ በሌላኛው እጁ ወያኔ ጋር አብረው ከሚያሴሩ ሃያላን መንግስታት ጋር ግብ ግብ ገጥሞ እዚህ የደረሰው የጸረ ወያኔው ንቅናቄ ይኽ ነው የሚባል ተጽእኖ ሳያሳድር ሩብ ክፍለ ዘመን አስቆጥሯል። የቀዝቃዛውን ጦርነት ማለቅ ተከትሎ የመጣው የሰላማዊ ፖለቲካ ፋሽን ለወያኔ መሰሪ ተፈጥሮ የማይመጥን መሆኑን ብዙ ግዜና ጉልበት አጥፍቶም ቢሆን ኩነቱን የተረዳው ህዝብ ዛሬ በራሱ ግዜ እየወጣ መገዳደር መጀመሩ የትግሉን ባህሪ ሌላ መልክ ሰጥቶታል። በዚህ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮ ከፍቶ ይኽ ትግል የኔ ነው ብሎ ለመናገር የሚደፍር ከረባት አሳሪ የትርፍ ሰአት ተቃዋሚ የሌለውም ለዚሁ ነው።
አሁን አንድ ሃቅ ፍንትው ብሎ ወጥቷል። ክፍተት ተፈጥሯል። ወያኔ በራሱ ግዜ ከውስጥ መርቅዞና እራሱን በራሱ መርዞ በሞት ደጃፍ ላይ ስለመሆኑ የራሱ ድኩማን አለቆች ሳይቀሩ መደበቅ የማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል። ይኽ ደግሞ ከፍጹም አልጠግብ ባይነት እና ኢትዮጵያ ላይ ካላቸው ስር የሰደደ የጥላቻ ደዌ የመጣ በመሆኑ ስርአቱ ከዚህ መዳን አይቻለውም። የችግሩ አሳሳቢነት ደግሞ በዚህ አጋጣሚ የተፈጠረውን ክፍተት ሊሞላ የሚችል በአደጋው ስፋት ልክ የተዘረጋ መዋቅር ያለው ማነው የሚለው ቁልፍ ጥያቄ ዛሬ ህዝቡ በደመነፍሱም ቢሆን የሸተተው አደጋ ነው። በመሆኑም ምንም እንኩዋን ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመርጡ ቢሆንም ቅሉ ዛሬ አንዳንዶች ከውጭ የሚያዩት ሲያጡ እራሱ የደደቢቱ ጋንግሪን ይኽችን አገር በዚህ ደረጃ ለማፍረስ እንደ ትሮይ ፈረስ ሲጠቀምባቸው የኖሩትን ኦህዴድና ብአዴን እንኳን ሳይቀር ምናልባት አንድ ነገር ቢያደርጉ ብሎ ተስፋ እስከማድረግ ድረስ የተሄደበትን ኩነት መሸሽ አይቻልም። ያም ሆኖ ግን አንድ ነገር ግልጽ ሆኖ ሊሰመርበት ይገባል። አርባ አመት ሙሉ በብሄረሰቦች ነጻነት ስም ሲዘራ የኖረውን የዘረኝነትና የቂም ፖለቲካ የፈጠረውን ሸለቆ ከራሱ ከወያኔ የወጡ መጋዣዎች ሞልተው ያሻግሩናል ብሎ ማሰብ እንደ ነቢዩ ሙሴ ቀይ ባህርን በበትር ከፍሎ የማሻገር ያህል ተአምር ይጠይቃቸዋል።
በመሆኑም ዛሬ ወያኔ የመጨረሻውን ካርድ ለመጣል እየሞከረ ነው።ለዚሁም አንዱ አስረጅ ነገር አገሪቱን ዳር እስከዳር የወረሯት መዥገሮች የዘረፏትን እያንዳንዷን ቁራጭ ሳንቲም ሳትቀር በትግራይ ልማት ማህበር በኩል በሚሰጣቸው የሚስጥር ኮድ ወደ ውጋገን ባንክ በሚባል የጎተራ አይጥ በኩል እየቀረቡ ወደ አሜሪካን ዶላር ቀይረው በቀጣይ የሚሆነውን ነቅተው እየተበቁ ነው።ዶንቆሮ የሰማ ለት ያብዳል እንዲሉ አሁንም የተኛው ነገር ግን ትልቁን አደጋ የተጋረጠው ግን ሌላው ህዝብ ነው። ስርአቱ ባሉት መዋቅሮች ሁሉ ተጠቅሞ አንዳንድ የውስጥ ለውጥ በማድረግ ስልጣኑን ለማስጠበቅ ካልቻለ እንደገና ወታደራዊ አገዛዝ በመመስረት የትጝራይን የበላይነት አስጠብቆ ለማቆየት ይሞክራል፤ ያም ሊሆን የማይችልበት ሁኔታ ላይ ከደረሰ ግን እስከዛሬ ሲዝትና ሲገዘት እንደኖረው አገሪቱን አፍርሶና የጀኖሳይድ እሳት ለኩሶ ወደ ደደቢት ለመመለስ ጫፍ ላይ መድረሱን ከክራሞታችን እያየነው ነው።ምንም ይሁን ምን ግን በርግጥ ተሳክቶለት ይህን ነገር በተወሰነ  ደረጃ  የተወሰነ ያህል እርቀት ይዞ መሄድ ከቻለ ኋላ እሳቱ በማን እንደሚከፋ አብረን የምናየው ይሆናል።
የፕሮፌሰር ጌታቸውና የሻለቃ ዳዊት ወልደጊዎርጊስ ሩጫ

ሁለቱ ጉምቱ የፖለቲካ ልሂቃን አማራውን በዘሩ ለማደራጀት ላይና ታች እያሉ መሆኑ ይሰማል። ይኽ እንግዲህ ዛሬ ተሸምቶ ዛሬውኑ ተፈጭቶና ተቦክቶ ለዛሬ የሚደርስ እንጀራ መሆኑ ነው። በሽዎች አመታት ሂደት እየጣለና እየወደቀ የዚህችን አገር ግማደ መስቀል ተሸክሞ እዚህ የደረሰ ከማንነቱ በላይ አልፎ ሰው ለመሆን የበቃን ህዝብ እንደገና በአንድ ቀን ጀምበር ጠፍጥፎ ወደ ጭንጋፉ የወያኔ የዘር ፖለቲካ ቁመና ማድረስ ይቻላል የሚል ነው። አንድ ግልጽ የሆነው ሃቅ ወያኔም ሆነ በአጠቃላይ በድፍን ኢትዮጵያ ውስጥ የተኮለኮሉት ብሄርተኛ ድርጅቶች ሁሉ የብሄርተኝነት ስሜታቸው የቆመው በአማራ ጥላቻ ላይ መሆኑ ነው።ትናንት በዋለው የፍርድ ቤት ችሎት እንደሰማነው የጉጅሌው መርማሪ አማራውን እስረኛ …”ምን ያህል ተምረሃል…”… ዕስንት ግዜ ወድቀሃል….”….”አማራ ደደብ ሆኖ ሳለ እንዴት አልወድኩም ትላለህ…”…እያለ ሲመረምረው እንደነበር ለችሎቱ አስረድቷል። በትክክክል ላጤነው ሰው እኒህ ሰዎች አማራውን ሲያስቡት የሚሰማቸው የበታችነት ቀውስ ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ ከዚህ የቀለለ አስረጅ ምሳሌ የማይኖረውን ያህል በዚያው ልክ የብሄርተኝነት ልክፍት ያለበት ሁሉ ደግሞ በየደረጃው እድሉን ቢያገኝ እጁን በዚህ ህዝብ ላይ ማንሳቱ ሳይታለም የተፈታ ነው። የዚያኑ ያህል አማራው አንድ ግዜ እረጅምና ውስብስብ በሆነ የታሪክ ሂደት ውስጥ በደረሰበት የመንፈስ ከፍታ የተነሳ ዛሬም ድረስ እታች ድረስ ወርደን ብናየው እንደሰው ደረሰብኝ ከሚለው ጥቃት በታች ይኽ ሁሉ ጥቃት የሚደርስብኝ በማንነቴ ነው ብሎ ሌሎቹ ድኩማኖች እንደሚሰማቸው የማንነት ጥቃት ለሰከንድ ማሰብ አልቻለም ብቻ ሳይሆን አይችልም። የማንነቱ ጥቃት ሰለባ መሆኑ ቢሰማው ደግሞ እነርሱው በሄዱነት መንገድ ለመምጣት ቀስቃሽ አያስፈልገውም ነበር እና።አሁንም እላለሁ፤ ስለዚህ አማራነት ከብሔርተኝነት በላይ ወደ ሰውነት ያደገ መሆኑ ከዚህ በላይ አስረጅ ነገር ሊኖር አይችልም። በመሆኑም ዛሬ የሁለቱ ልሂቃን ጥረት ከዚህ መሰረታዊ እውነት ሊያመልጥ የሚችልበት ቀመር ይኖራል ብሎ ማሰብ ለትግሉ የምናበረከተውን በጣም እንቁ የሆኑ ሰአቶች ከማባከን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም።መቸም ሰውን በዘሩና በሃማኖቱ ከመቀስቀስ ብሎም ከማደራጀት በላይ በጣም ቀላል የሆነ ነገር የለም።ምክንያቱም በዘር ማሰብ እውቀት አይፈልግም። በሃይማኖትም ቢሆን እንዲሁ። እንደሰው መደራጀት ግን ጥልቅ የሆነ ሃሳብ እና የጠራ ግንዛቤ እንዲሁም ለዚሁ የሚመጥን ትጋት ይጠይቃልና። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ዋነኛው ቁልፍ ነጥብ የነዚህ ሰዎች ጥረት ተሳክቶና አማራው በዘሩ ተደራጅቶ በጸረ ወያኔ ትግሉ ላይ የራሱን ድርሻ ቢወጣ ወያኔን ጠራርጎ ለማውጣት በጣም ቀላሉ መንገድ የሚሆነውን ያህል ዛሬ በዘሩ የተደራጀ አማራ የትግራይን ብሄርተኞች መቃብር ሲገነባ የራሳቸው የትግሬዎች የዘረኛ አይዲዮሎጅ ሰለባ ሆኖና ተሸንፎ እንጅ እንዲሁ ያለዋጋ በነጻ የሚደረስበት አለመሆኑ ነው። በርግጥ ማንም ጤነኛ አይምሮ ላለው ሰው ዘር ለሚለው የትግሬ አይዲዮሎጅ ተሸንፎ ነገር ግን የጦር የበላይነት ቢያግኝ ምን ያህል ኪሳራ እንደሚሆንበት ውጤቱን ሲደርስ ነው የሚያየው። አናሳዎቹ በዘራቸው ተደራጅተው ይኽን ያህል ኪሳራ ካደረሱ በአንጻሩ ደግሞ ዋነኛው አገሪቱን ያቆመው ዋርካው አማራ በዚህ ሁሉ ግዙፍ ቁመናውና ባለው ፈርጀ ብዙ እሴቱ በነሱ ቁመና ጨንግፎ ማሰብ ቢጀምር አገሪቱን የሚያስከፍላትን ዋጋ በቀላሉ ማስላት የሚቻል አይመስለኝም።ቢጀምር አገሪቱን የሚያስከፍላትን ዋጋ በቀላሉ ማስላት የሚቻል አይመስለኝም።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s