የአስቴር (ቀለብ) ስዩም ይግባኝ በሌላ ግለሰብ የስልክ መረጃ እንደተፈረደባት ተገልፆአል።

የአስቴር (ቀለብ )ስዩም ይግባይ

( በሌላ ግለሰብ የስልክ መረጃ እንደተፈረደባት ተገልፆአል።
#የተጠቀሰው ስልክ መስመር (ለፍርዱም መነሻ የሆነው) ተጠቃሚ ቀለብ ስዩም አስፋው ሲሆን የይግባኝ ባይ ሙሉ መጠሪያ ደግሞ ቀለብ ስዩም አበራ ነው።

#ወንጀሉ” ተፈፀመ ከተባለ እንኳ፣ በግሏ ጥቅም ተነሳስታ ሳይሆን፣ ከፍ ባለ፣ በአገሯ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲጎለብት ካላት የከበረ ራዕይና በጎ አመለካከት የሚታይ በመሆኑ፣ “ወንጀሉ” ተፈፀመ ለተባለበት ምክንያት የሆነውን ህዝባዊ ዓላማ ፍ/ቤቱ ከግምት ውስጥ አስገብቶ፣ የስር ፍ/ቤት ቅጣቱን እንዲያቀልልን)

በፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ለወንጀል ይግባኝ ሰሚ ችሎት

አዲስ አበባ

ይግባኝ ባይ ……….. ወ/ሮ ቀለብ ስዩም አበራ

መልስ ሰጪ………. የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ.185(1) መሠረት የቀረበ የይግባኝ ማመልከቻ፤

መግቢያ

ይግባኙ የቀረበው የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በወ/መ/ቁ. 171660 በግንቦት 04 ቀን 2009 ዓ.ም በሰጠው የጥፋተኝነት እና በግንቦት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው የቅጣት ውሳኔ ላይ ቅር በመሰኘት ነው፡፡

መልስ ሰጪ በሚያዝያ 14 ቀን 2008 ዓ.ም አሻሽሎ በሥር ፍ/ቤት በይግባኝ ባይ እና ሌሎች አምስት ተከሳሾች ላይ የወ/ሕ/ቁ. 32(1)(ሀ) እና የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 አንቀጽ 7(1) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ እራሱን አርበኞች ግንቦት ሰባት ብሎ በሚጠራው ሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ ከግንቦት 2007 ዓ.ም ጀምሮ አባል በመሆን እና በመሳተፍ ወንጀል ተከሰዋል የሚል ነበር፡፡
ፍ/ቤቱም በአብላጫ ድምጽ ይግባኝ ባይን ጥፋተኛ በማለት የአራት ዓመት ጽኑ እስራት ቅጣት አስተላልፏል፡፡ ይግባኙም የቀረበው በዚህ የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ ቅር በመሰኘት ሲሆን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

የጥፋተኝነት ውሳኔውን አስመልክቶ፤

በተስተባበለ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ላይ የቀረበ ቅሬታ፤
ይግባኝ ባይ በስር ፍ/ቤት፣ መልስ ሰጪ የአርበኞች ግንቦት ሰባት የተባለው የሽብር ድርጅት አባል ናት ብሎ ክስ ያቀረበ ሲሆን ይግባኝ ባይም ክሱን ክጄ ስለተከራከርኩ ዐቃቤ ሕግ 6 የሰው ምስክሮች እና ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተጠናቅሮ የመጣ የመረጃ ሪፖርት አቅርቧል፡፡

በሰኔ 28 ቀን 2008 ዓ.ም እና በሐምሌ 22 ቀን 2008 ዓ.ም ዐቃቤ ሕግ ስድስት ምስክሮች አስቀርቦ ያስደመጠ ቢሆነም አንዳቸውም በይግባኝ ባይ ላይ አልመሰከሩም፣ ቃላቸውም ሳይነካቸው ምስክሮች ተመልሰው ሄደዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ሌላ ያቀረበው የሰነድ ማስረጃ የደህንነት ሪፖርቱ ሲሆን እርሱም ባጭሩ የሚለው፣ ይግባኝ ባይ በአራት ተንቀሳቃሽ ስልክ ቁጥሮች ተጠቅማ የተለያዩ የሽብር መልዕክት ልውውጦችን አድርጋለች የሚል ቢሆንም፣ ሶስቱ መስመሮች ይግባኝ ባይ የማያውቋቸው እና በእሳቸው ስም ጭራሹንም ያልተመዘገቡ መሆኑን በመከላከያችን ከኢትዮ- ቴሌኮም ጠይቀን በመጋቢት 27 ቀን 2009 ዓ.ም የቀረበው መልስ እና ማስረጃ ያስረዳል፡፡ የስር ፍ/ቤትም ሶስቱን ያስረዳች ቢሆንም የሞባይል ስልክ ቁጥር 096306……የይግባኝ ባይ መሆኑን ኢትዮ-ቴሌኮም አረጋግጧል፣ የስልኩ ተጠቃሚ መሆኗ ግልጽ ነው፣ በዚህ ከ”አሸባሪው” ቡድን ጋር እንደምትገናኝ በመገለጹ የይግባኝ ባይ መከላከያ የዐቃቤ ሕግን ክስ የሚያጠናክር እንጂ የሚያስተባብል አይደለም ሲል የሰጠው ውሳኔ ከፍተኛ ቅሬታን ፈጥሮብኛል፡፡

በቅድሚያ ከኢትዮ-ቴሌኮም የመጣው አራተኛው፣ ከላይ የተጠቀሰው ስልክ መስመር ተጠቃሚ ቀለብ ስዩም አስፋው ሲሆን የይግባኝ ባይ ሙሉ መጠሪያ ደግሞ ቀለብ ስዩም አበራ በመሆኑ፣ ግልጽ የአያት ስም ልዩነት እያለው ፍ/ቤቱ ግን እንደ ተራ ነገር በፍርዱ ላይ ገልጾ ማለፉ ፍትህን የሚያጓድል ጉዳይ አድርጎታል፡፡

ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የስር ፍ/ቤት እንዳለው ስልኩ የይግባኝ ባይ መሆኑ ቢረጋገጥ እንኳን፣ በአገሪቱ ብቸኛ የሞባይል አገልግሎት ሰጪ የሆነው ኢትዮ-ቴሌኮም በመስመሩ ምንም አይነት መረጃ ልውውጥ እንዳልተካሄደበት እና ቋቱ ባዶ መሆኑን ባቀረብነው መከላከያ ማስረጃችን አስረድተን ሳለን፣ የስር ፍ/ቤት፣ የመስመሩ ባለቤት ከመሆን ባለፈ ምንም አይነት ልውውጥ አለመደረጉን ማስረጃውን እያየ፣ ከአሸባሪው ቡድን ጋር ተገናኝታበታለች በማለት በመረጃ መመዝገቢያው ሲስተም ላይ ያልተመዘገበን መረጃ እንደተመዘገበ አድርጎ የሰጠው ውሳኔ ታላቅ የፍትህ ጉድለት በመሆኑ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ሊያርመው ይገባል፡፡

የደህንነት ሪፖርት ማስረጃን አስመልክቶ የቀረበ የሕግ ክርክር፤

በይግባኝ ባይ ላይ ዐቃቤ ሕግ በማስረጃነት ለማስረዳት ያቀረበው ብቻኛ ማስረጃ የብሔራዊ ደህንነት እና መረጃ አገልግሎት ከስልካቸው ተጠልፎ ተገኘ በማለት ያቀረበውን የመረጃ ሪፖርት ነው፡፡ ይህ ማስረጃ ሕጉን ተከትሎ ያልቀረበ ስለሆነ ተቀባይነት ሊያገኝ አይገባም (Inadmissible evidence) ስንል በስር ፍ/ቤት ክርክር ብናቀርብም እና ዐቃቤ ሕግም ባይከራከርበትም፣ የስር ፍ/ቤት ክርክራችንን እንዳላቀረብን አድርጎ በዝምታ ማለፉ ቅሬታን ፈጥሮብናል፡፡
ይግባኝ ባይ የተከሰሱበት አ/ቁ. 652/2001 አንቀጽ 14(1) በደህንነት ተቋማት የሚደረጉ የመረጃ ክትትሎች “ከፍርድ ቤት ፈቃድ በመውሰድ” መሆን እንዳለባቸው በግልጽ ደንግጓል፡፡ መልስ ሰጪ በማስረጃነት፣ ይግባኝ ባይ ከተገለገሉበት የስልክ ልውውጦች ተወስዶ ቀረበ ያለውን የደህንነት ማስረጃ እንደ ሕጉ ድንጋጌ በፍ/ቤት ፈቃድ ስለመገኘቱ ያቀረበው አንዳችም ማስረጃም ሆነ ክርክር አልነበረም፡፡

ይሄ ደግሞ በአዋጁ መሠረት ሊቀርብ ይችላል በማለት በአንቀጽ 23(1) ላይ የሚገኙት የማስረጃ አይነቶች፣ እራሱ የአዋጁ አንቀጽ 14 እና ከሕገ መንግስቱ የግል ነጻነትን ጥብቅነት ከሚያስቀምጠው አንቀጽ ጋር እንዲጣጣም ታስቦ፣ ጠበብ ተደርጎ ለግል ነጻነት መብት የበለጠ ጥበቃ በሚያደርግ መልኩ ተግባብቶ መተርጎም ሲገባው አንቀጹን ትርጉም በሚያሳጣው መልኩ መተርጎሙ የሰብዓዊ መብት ጥበቃን የሚያጣብብ ነው፡፡ ስለሆነም፣ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ የሰጠው፣ የሕጉን አስገዳጅ መጠይቅ ተከትሎ ባልቀረበ ማስረጃ ተመስርቶ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም እንዲባልልን፡፡

ይግባኝ ባይ በተጨማሪ የማነሳው የሕግ ትርጉም ቅሬታ፣ በአዋጁ አንቀጽ 23(1) መሠረት የሚቀርብ የደህንነት ሪፖርት ማስረጃ ብቻውን ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በጸዳ መልኩ ጥፋተኛ ለማስባል በቂ አይደለም(weak probative value) የሚል ነው፡፡ አዋጁ፣ በዚህ አንቀጽ ስር ተቀባይነት የሚኖራቸውን ማስረጃዎች ዝርዝር(List of admissible evidence) አስቀመጠ እንጂ፣ ከእነዚህ ማስረጃዎች ውስጥ ዐቃቤ ሕግ አንዱ ብቻ ስለቀረበ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ክሱን አስረድቷል ወደሚል ደፋር የጥፋተኝነት ድምዳሜ የሚያደርስ ግን አይደለም፡፡ ለዚህም ነው በስር ፍ/ቤት ውሳኔ ላይ አናሳው ድምጽ “ይህ ማስረጃ ከመንግስት ተቋም የተገኘ በመሆኑ እውነተኛ የመሆኑ ነገር ግምት ሊያዝበት ቢችልም ያለምንም ጥርጣሬ ሙሉ በሙሉ እውነተኛ አድርጎ ለመውሰድ ግን ለሪፖርቱ መሠረት የሆነውን የስልክ ንግግር አስቀርቦ መመርመሩ በሪፖርቱ ላይ ሊነሳ የሚችለውን ምክንያታዊ ጥርጣሬ ስለሚያስወግድ ከብይኑ በፊት ተጠቃሹ የስልክ ንግግር ሊቀርብ ይገባ ነበር”፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤትም ይህን የስር ፍ/ቤት የልዩነት ሃሳብ በመቀበል፣ የደህንነት ሪፖርቱ፣ ዋናው የጠለፋው ማስረጃ ይልቁንም፣ ተጠይቆ የሌለ መሆኑ በተገለጸበት ሁኔታ ጭምር፣ ብቻውን ክሱን ለማስረዳት በቂ አይደለም በማለት የስር ፍ/ቤትን የጥፋተኝነት ውሳኔ በመሻር እንዲያሰናብተን፡፡

የቅጣት ውሳኔን በተመለከተ የቀረበ የይግባኝ ቅሬታ፤
የሥር ፍ/ቤት ይግባኝ ባይን በአ/ቁ. 652/2001 አንቀጽ 7(1) ስር ጥፋተኛ በማለት በአራት ዓመት ጽኑ እስራት ሲቀጣት አለአግባብ ሁለት የቅጣት ማቅለያዎችን አልፎብናል፡፡ በመጀመሪያው ያቀረብነው የቅጣት ማቅለያ፣ ይግባኝ ባይ “አንድነት ለፍትህና ዴሞክራሲ” ተብሎ ሕጋዊ ፈቃድ በተሰጠው ፓርቲ ውስጥ አባል በመሆንና በሚኖሩበት አካባቢ ንቁ ተሳታፊ ሆነው ለአገራቸው የዴሞክራሲ ሰርዓት ግንባታ በወጣትነት እድሜጣቸው ያበረከቱት አስተዋጾ እንደ አንድ የቅጣት ማቅለያ እንዲያዝልን የሚገልጽ ቢሆንም፣ የስር ፍ/ቤት ግን ሕጋዊውን ፓርቲ ለሽፋን ነው የተጠቀሙበት በሚል ማለፉ ሊታረም የሚገባው ነው፤ ምክንያቱም፣ ይግባኝ ባይ በክሱ ላይ ዐቃቤ ሕግ እንደጠቀሰው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅት አባል ሆነች የተባለው፣ በግንቦት 2007 ዓ.ም ሲሆን የአንድነት ፓርቲ አባልነቷ ግን (በስር ፍ/ቤት ማስረጃ እንዲመጣልን ጠይቀን ሳይመጣልን የተወሰነ ነው) ከዛ በፊት የነበረ በመሆኑ ማቅለያውን ያልተቀበለበት ምክንያት በማስረጃ ያልተደገፈ ነው እንዲባልልን፡፡

በሁለተኛ ደረጃ፣ ይግባኝ ባይ እንደ የወ/ሕ/ቁ. 82(1)(ለ) ድንጋጌ መሠረት ጥፋተኛ የተባለችበት ድርጊት ፈፀመች ከተባለ እንኳ፣ በግሏ ጥቅም ተነሳስታ ሳይሆን፣ ከፍ ባለ፣ በአገሯ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲጎለብት ካላት የከበረ ራዕይና በጎ አመለካከት የሚታይ በመሆኑ፣ “ወንጀሉ” ተፈፀመ ለተባለበት ምክንያት የሆነውን ህዝባዊ ዓላማ ፍ/ቤቱ ከግምት ውስጥ አስገብቶ፣ የስር ፍ/ቤት ቅጣቱን እንዲያቀልልን ይህን በጽሁፍ ያቀረብነውን አስተያየት ማለፉ ተመልክቶ ቅጣቱን ሊያቀልልን ይገባዋል እንላለን፡፡

ይግባይ ባይ

የይግባይ ባይ ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s