የኢትዮጵያ ውስጥ መኖር መሠረታዊ የዜግነት መብት እንጂ በጎሰኛ ፓለቲከኞች የሚሰጥ ችሮታ አይደለም! – የኢትዮጵያ ክፍለሀገሮች ሕብረት አስተባባሪ ኮሚቴ

ኖቬምበር፣ 4, 2017

ኢትዮጵያ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገሩባት፣ በርካታ ባህሎች የሚንጸባረቁባት፣ ልዩ-ልዩ እምነቶች የሚስተናገዱባት የጋራ አገር ናት። ሀገራችን ለረጅም ዘመናት፣ ከብዙ አገራት በፊት በነጻነትና በመንግስታዊ ስርዓት ስትተዳደር መኖሯ በታሪክ የተመሰከረለት መሆኑ የሚካድ አይደለም። በሕዝቧ የአሰፋፈርና የተፈጥሮ መልከአ-ምድራዊ አቀማመጥ አኳያ ለአስተዳደር አመቺ እንዲሆን በታሰበበት መልክ በክፍለሀገሮች ደረጃና በኋላም ራስ-ገዝ አውራጃዎችን በጨመረ አወቃቀር የስልጣን ተዋረድ በነበረው ስርዓት ትተዳደር የነበረች አገር ናት።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በመካከሉ ያሉ ባህላዊና ልማዳዊ ልዩነቶች ሳይገድቡት፣ ተስማምቶና ተቀላቅሎ፣ በጋብቻ ሰንሰለት ተሳስሮ፣ ጎሰኝነትን ስሜት አመንምኖና ሰብሮ፣ የብሔራዊ ስነ-ልቦናን አዳብሮና ተከባብሮ የኖረባት፤ ለብዙ አገሮችም የነጻነት ቀንዲልና መልካም ምሳሌ የሆነች አገር መሆኗም ይታወቃል።

ሕዝቧም የሰሜኑ ደቡብ፣ የደቡቡ ሰሜን፣ የምስራቁ ምዕራብ፣ የምዕራቡ ምስራቅ፣ የመሃሉ ዳር፣ የዳሩ መሃል እንደልቡ ተንቀሳቅሶ በፈለገውና በመረጠው ቦታ እየኖረ ከወደደው ማህበረሰብ ተወላጅ ጋር ተጋብቶ፣ የፈለገውንና የመረጠውን እምነት ተቀብሎ የኖረባትና የሚኖርባት አገር ናት። እንግዳ ተቀባይ የሆነው ሕዝቧ የሌላ አገር ዜጎችን ሳይቀር በፍቅርና በክብር ተቀብሎ አብሮ የኖረ ነው።

ይህችን ኢትዮጵያ የምትባል የጋርዮሽ አገር ህልውናዋን ለማጥፋት የውጭ ወራሪ ሃይሎች ያደረጉትን ተከታታይ ሙከራ የየክፍለሃገራቱ ተወላጆች የየራሳቸውን ስንቅና ትጥቅ በመያዝ እንደ ንብ ሰራዊት መሪዎ ቸውን አጅበው በጦር ሜዳ በመሰለፍና አይከፍሉ መስዋእት በመክፈል አገራቸውን የተዳፈሩትን ሁሉ አሳፍረው በመመለስ የአኩሪ የጋራ ድል ባለቤቶች መሆናቸውን የባዕዳን ታሪክ ጸሃፊዎች ሳይቀሩ የመሰከሩት ሃቅ ነው።

ከየት መጣህ?ለምን መጣህ?መቼ ትመለሳለህ?የሚል ጥያቄ ሳይቀርብበት በሄደበት ያገሩ መሬት በነጻነት ሲኖር የነበረ ሕዝብ እንደመጤና እንግዳ ተቆጥሮ ለጥቃት የተጋለጠበት ጊዜ ቢኖር ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በውጭ ሃይሎች ድጋፍና ምክር ተደራጅቶ ከሃያ ሰባት ዓመታት በፊት በጉልበት ስልጣኑን በጨበጠው የጎሰኞች ስብስብ በዘረጋው ስርዓት ስር ነው። ባዕዳን በወረራ ያልተሳካላቸውን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዓላማ አገር-በቀሉ የባንዶች ስብስብ ለጎሳ መብትና ነጻነት በሚል ሽፋን ተስማምቶ፣ተሳስቦና ተቀላቅሎ የኖረውን ሕዝብ ድንበር ሸንሽነው እርስ በርሱ እያጋጩ የብዙ ንጹሃን ዜጎች ደም በከንቱ እንዲፈስ አድርገዋል አሁንም እያደረጉ ነው። የሚያስቆማቸው ከሌለ ወደፊትም ይቀጥላል።

ቀደም ሲል በተለያዩት የሀገሪቱ ክፍሎች የተደረገው የእርስ በእርስ ፍጅት አሁን በቅርቡ ደግሞ በኦጋዴን፣በሓረርና በባሌ በሚኖሩት የሶማሌና የኦሮሞ ማህበረሰብ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው የማጫረስና የማፈናቀል ወንጀል ሳይበርድ ሰሞኑን በኢሊባቦርና ቤኒሻንጉል ውስጥ በሚኖሩት በተለይም በአማራው ማህበረሰብ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ያለው የማጥቃት ዘመቻ ለብዙ ንጹሃን ዜጎች ህይወት መጥፋት፣ ለአካል ጉድለት፣ንብረት መውደምና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

ይህንን መሰሪ፣ ኢ-ሰብአዊ፣ ጸረ አንድነትና ጸረ ሰላም ድርጊት ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ድርጊቱን ለመቋቋምና ለማክሸፍ የሚያስችል ስራ መሰራት እንዳለበት ወቅቱ የግድ ይላል። ለዚህ ሕዝብና አገር-አድን ተልእኮ ሁሉንም አስተባብሮ መልስ ለመስጠት የሚችለው በቅርቡ የተቋቋመው የክፍለሃገራት ህብረት እንደሆነ ታምኖበታል። ይህ የክፍለሀገራት ህብረት የየአካባቢው ሕዝባዊ ብሶቶች ተገቢ ትኩረት እንዲያገኙ በማድረግ፣ የጋራ ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ይቻል ዘንድ ጎሰኝነትን በማምከንና ኢትዮጵያዊነትን በማጉላት የሕዝቡን ብሔራዊ ድርሻ አዳብሮና መብቱን አስከብሮ አገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ በጋራ መቆምን ዓላማ አድርጎ የተነሳ ብሔራዊ መድረክ ነው። በዚህ መልክ መደራጀቱ ለአገሪቱ አንድነት ዋስትና ከመሆኑም በላይ የተከሰቱትንና ወደፊትም ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋና ችግሮችን ለመከላከልና ለማስወገድና የተሻለ በመሆኑ

 

በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል። በክፍለሀገር የመደራጀቱ ሂደት እየሰፋ በመምጣት ላይ ሲሆን ሌሎቹም ያልተደራጁት ተደራጅተው እንዲቀላቀሉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ያደርጋል።

በተለያዩ ክፍለሀገሮ የተወለድንና የምንኖር ለሰብአዊ መብት መከበር፣ለአንድነትና ለሰላም የቆምን፣በኢትዮጵያዊነታችን የምናምን ሁሉ በየአካባቢያችን ሕዝብ ከፋፋይ በሆነ የጎሳ ፖለቲካ ላይ የተሰማሩ ክፍሎች ከአጥፊ ተግባራቸው እንዲታቀቡና እስከ አሁን ድረስ በሕዝቡ ላይ በደል የፈጸሙትም በድርጊታቸው ተጸጽተው እንዲመለሱ አጥብቀን ስናሳስብ፣ከእንደዚህ መሰል አጥፊ ተግባር ለማይቆጠቡት ግን ከሕግና ከታሪክ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ልናስገነዝባቸው እንወዳለን።

ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት መስፈን፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለሰብአዊ መብት መከበር የቆሙና የጎሳን ፖለቲካና አደረጃጀት የሚቃወሙ የፖለቲካ ድርጅቶች ለሃገር ህልውና ቅድሚያ በመስጠት ከራሳቸው ሳጥን ውስጥ ወጥተው የክፍለሃገራቱ ማህበር ለሚያደርገው አገር አድን ትግል ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉና በአንድነት ሃይሉ ግንባታ ስራ ላይ እንዲተባበሩ ጥሪ እናደርጋለን። የአንድነት ሃይሉ በዚህ መልክ ከተዋቀረ አገራችንን ከተደቀነባት የመበታተን ስጋትና አደጋ ያወጣታል ብለን እናምናለን።

የክፍለሀገር ማህበራት ሕብረት የሚከተሉትን ጥያቄዎች በማቅረብ ፍጻሜ እንዲያገኙ ሕዝቡ ድጋፉን እንዲሰጥና እንዲተባበር ጥሪ እናደርጋለን።

  1. በወያኔ አጋዚ ሚሊሽያ በግፍ ለተጨፈጨፉትና ለተፈናቀሉት ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን አቅማችን በፈቀደው ሁሉ እስከ ድል ድረስ ከጎናቸው እንደምንሰለፍ እናረጋግጣለን።
  2. በወገኖቻችን ላይ የግድያ፣የማቁሰልና የማፈናቀል ወንጀል የፈጸሙት በሕግ እንዲጠየቁ
  3. ጥቃት የደረሰባቸውና የተፈናቀሉት ወገኖቻችን ለወደመባቸው ንብረትና ለደረሰባቸው ጉዳት ተገቢውን ካሳ ተክሰው ወደ ነባሩ መኖሪያቸው ተመልሰው በሰላም የመኖር ዋስትና እንዲሰጣቸው፣
  4. የጎሳ ፖለቲካ ተወግዶ ሁሉም ነዋሪ በአንድ አገር ዜግነቱ ማለትም በኢትዮጵያዊነቱ ለሚኖርበት አካባቢ እኩል የባለቤትና ወሳኝ ድርሻ እንዳለው የሚረጋገጥበት አሰራር እንዲፈጠር
  5. የክፍለሀገር አስተዳደሮች በአንድ አገራዊ ሕገመንግስት ስር ተሳስረው አካባቢያቸውን በሚመለከተው ተግባር የሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎና ቁጥጥር ያለበት አስተዳደርና ደንብ አውጥተው የሚወስኑበት ከአጠቃላዩ አገራዊ ጥቅምና አንድነት ጋር የማይጋጭ አሰራር እንዲፈጠር፣
  6. ለወደፊቱ ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት በጎሳና በእምነት ላይ መሰረት ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጀትና ድርጅት በሕገ-መንግሥት እንዲታገድ እየጠየቅን፤ አገር አጥፊ የሆነውን የወያኔን ሕገ መንግስት ተብዬ የተቀበሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አቋማቸውን እንዲመረምሩና እንዲያስተካክሉ ለማሳሰብ እንወዳለን። የወያኔን ሕገ-መንግሥት መቀበል ማለት ሕዝብ በነጻ ያልተሳተፈበትንና የአገሪቱን መበታተን የሚፈቅደውን ሕግ መቀበል ማለት ነው።

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመኖር ነጻነቱ በጎሰኞች ፈቃድ የሚያገኘው ችሮታ ሳይሆን መሠረታዊ የዜግነት መብቱ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!!

የኢትዮጵያ ክፍለሀገሮች ሕብረት አስተባባሪ ኮሚቴ

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s