ዳኛ ዘርዐይ ወልደሰንበት ዛሬ ማሕሌት ፋንታሁንን በችሎት መሐል በወቀሳ አስጠነቀቋት | ጌታቸው ሽፈራውም….

ጌታቸው ሽፈራው

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን “አክላቸው ወንድወሰን” በተባለ የፌስቡክ አድራሻ የዳኛ ስም ተጠቅሶ የተፃፈ የፍርድ ቤቱን ክብር የሚነካ ፅሁፍ አጋርተሻል በሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

አሚር በፌስቡክ የተፃፈ ፅሁፍ ስር አስተያየት እንደሚሰጥ፣ እንዲሁም እኔ (ጌታቸው ሺፈራው) የምፈልገውን የፍርድ ቤት ውሎ ብቻ ቆርጬ እንደምዘግብ ይህም ምን “ሸንቆጥ” ለማድረግ እንደተፈለገ ፍርድ ቤቱ እንደሚረዳው፣ ለሌላ ሰውም መረጃ እንደምልክ ፍርድ ቤቱ ገልፆአል። ፍርድ ቤቱ ለሌላ ሰው መረጃ ትልካለህ ሲል የጠቀሰው ማስረጃም ሆነ የሰው ስም የለም።

ናትናኤል (የአባቱ ስም ያልተጠቀሰ)፣ አንገቱ ላይ “ሻርፕ” ያደርጋል የተባለና በችሎት ያልነበረ ግለሰብም ስሙ በችሎት ተጠቅሷል።

ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን በችሎት ቀርባ አጋርተሽዋል ስለተባለው ፅሁፍ የተጠየቀችው በጠዋቱ የፍርድ ቤት ጊዜ ሲሆን ለከሰዓት ተቀጥሮ ከአሁን ቀደም የምትፅፋቸው ፅሁፎች አጋራችው የተባለውን አይነት ይዘት እንደሌለው በመጥቀስ በተግሳፅ እንደታለፈች ፍርድ ቤቱ ገልፆአል።

ፌስቡክ ላይ የተፃፉ ፅሑፎችን ዳኞች እንደሚያነቡ የገለፀው ፍርድ ቤቱ ይህን የምናደርገው የፍርድ ቤቱን ክብር ለማስጠበቅ ነው ብሏል። ፍርድ ቤቱ “እንዲህ የምናደርገው እናንተን ሃራስ ለማደረግ አይደለም” ቢልም ለሌላ ሰው መረጃ መላክና መሰል ጉዳዮች ላይ ተላከለት የተባለ ሰው ስም፣ ምን እንደተላከ እና እንዴት እንደተላከ ሳይጠቅስ ማስጠንቀቂያ መሰል ምክር ሰጥቶ አልፏል።

በሌላ በኩል የፌደራል ፖሊስ አክላቸው ወንድ ወሰን የሚል የፌስቡክ አድራሻን አጣርቶ ለፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተላልፏል።

ከአሁን ቀደም በዚሁ ችሎት መሃል ዳኛው “የተቀረፀ በሚመስል መልኩ ቃል በቃል እየተዘገበ ነው” እንዲሁም የግራ ዳኛው የተዛቡ ዜናዎች በፌስቡክ እየተላለፉ ነው በሚል ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ የሚታወስ ነው።

______________
ዳኛ ዘርዐይ ወልደሰንበት ዛሬ ማሕሌት ፋንታሁንን በችሎት መሐል በወቀሳ አስጠነቀቋት

በፍቃዱ ዘ-ኃይሉ እንደጻፈው

ዳኛ ዘርዐይ ወትሮም ትዝብት የማያጣው የፌ/ከፍ/ፍ/ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ዳኛ ሆነው ከመጡ ጀምሮ ሌላ የውዝግብ መንስዔ ሆነዋል። ታዳሚውን በጥርጣሬ ይሁን በጥላቻ በማያስታውቅ ሁኔታ የሚገረምሙት እኚህ ዳኛ ከመጡ ወዲህ ችሎቱ ቁጡ እና ለተከሳሽ ቀርቶ ለታዳሚ አስፈሪ ሆኗል። በሚገርም ሁኔታ እሳቸው ገጽታ ላይ የሚነበበው ቁጣ ሌሎቹ ዳኞች ላይ አይነበብም። የችሎቱ ዳኞች ባለፈው ግዜ (ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራውን ጨምሮ የአውሮጳ ኅብረትን ወክለው ችሎቱን የሚታዘቡ) ታዳሚዎችን በማስነሳት “እነማን ናችሁ? ለምንድን ነው የመጣችሁት?” ብለው ጠይቀዋል። ይህ በሕግ አግባብ ተገቢ ይሁን አይሁን የሕግ ባለሙያዎች አስተያየት የሚሰጡበት ነው። ችሎቱን ለሚታደሙት እና በራሳቸው ከደረሰባቸው ኢፍትሐዊነት በመነሳት የሰብኣዊ መብት ጥሰት አቤቱታዎችን አድምጦ ለሕዝብ ለማጋለጥ እና የፍርድ ቤት ውሎዎችን በመዘገብ፣ ችሎቱን አክብረው፣ የሕግ የበላይነት እና የችሎቱ ነጻነት ላይ ያላቸውን ሁሉ ጥርጣሬ ቀብረው፣ ለፍትሕ ስርዓቱ የግልጽነት ድባብ ለማላበስ የለት እንጀራ ሳያምራቸው በብዙ መስዋዕትነት ለሚከፍሉት ወዳጆቼ ምን ያህል አስደንጋጭ እና የማስፈራራት ስሜት እንዳለው አውቃለሁ። በመሆኑም በጣም አዝኛለሁ!

ችሎቱ በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት የተለያየ ሰበብ ተለጥፎባቸው የተከሰሱ ሰዎች የሚበዙበት እንደመሆኑ ብዙ ቅሬታዎች ይቀቡበታል። ለዚህ ደግሞ ችሎቱ ማድረግ የሚችለው ዝቅተኛው ነገር ቅሬታዎቹን ማድመጥ ነው። ከዚህ በፊት የነበሩት ዳኞች ቢያንስ ይህንን ሞክረው ነበር። ነገር ግን እኚህን ዳኛ ጨምሮ አዲሶቹ ከመጡ ጀምሮ ችሎቱ የተከሳሾችን ቅሬታ ማቅረብ እንደጠብ ማጫር ነው የሚመለከተው። ተከሳሾቹ በችሎቱ ላይ ጭላንጭል እምነት እንኳ እንዳይቀራቸው በተለይ ዳኛ ዘርዐይ በተግሳፅ እና ቁጣ ያሸማቅቋቸዋል። እኚህ ዳኛ በወልቃይት ጉዳይ ላይ ያላቸውን አቋም በጦማር ላይ የጻፉ በመሆኑ ብዙ ተከሳሾች በገለልተኝነት ጉዳያችንን ያያሉ ብለን አናምንም ብለው እንዲነሱ ጠይቀዋል። አቶ ዘርዐይ ግን ይበልጥ እልህ የተጋቡ ይመስላሉ።

ዛሬም የችሎት ታዳሚውን ማስደንገጣቸውን ቀጥለውበታል። ማሕሌትን አስነስተው አንድ ራሷ በጻፈችው እና ሌላ ደግሞ የሰው ‘ሼር’ ባደረገችው ጽሑፍ ሳቢያ ወቅሰዋታል። ነገሩን “የችሎቱን ክብር ከመጠበቅ” ጋር አያይዘው፣ “harass ለማድረግ አይደለም” ብለው ቢያቃልሉትም፤ የሚሰጠው ስሜት ግን የማሸማቀቅ ነው። ማሕሌት ‘ሼር’ ያደረገችው ጽሑፍ ላይ “ፍርድ ቤቱን የበቀል ቤት” በሚል የሚገልጸውን ሳታስተውል ማጋራቷን ገልጻለች። ነገር ግን ለብዙ ሰዎች የፍርድ ቤቱ ነጻነት እና ለሕግ የበላይነት ተገዢነት ሁሌም አጠራጣሪ ነው። ይህንን በሐሳብ መግለጽ ለምን የፍርድ ቤቱን ክብር መንካት እንደሚሆን አሁንም ለሕግ ባለሙያዎች አስተያየት እተወዋለሁ። በተጨማሪም፣ ዳኛ ዘርዐይ እነ ጋዜጠኛ ጌታቸውንም አስነስተው “የምትጽፉትን ነገር እናያለን” ብለዋቸዋል። አሚር የተባለ የመብት ተቆርቋሪንም እንዲሁ “የምትጽፋቸውን ‘ኮሜንቶች’ እናያለን” ብለውታል።

ከአንድ ዓመት በፊት፣ ብሌን መስፍን አስቸኳይ ግዜ አዋጁን አስታክኮ የታሰረች ግዜ፣ የጉለሌ አንደኛ ደረጃ ችሎት የፈቀደላትን በዋስ የመፈታት መብት፣ በዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ባይነት፣ የከለከሏት ዳኛ ዘርዐይ ነበሩ። የዛን ዕለት ይህን ሁሉ ዓመት ሳውቃት የማላውቀውን፣ ማሒ ስታለቅስ አይቻታለሁ። የዳኛ ዘርዐይ ውሳኔ ነበር ያኔም ያስለቀሳት። አሁንም ተግሳፃቸው ተከትሏት ልደታ መጥቷል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s