የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደማይቻል ኢህአዴግ አስታወቀ

በስብሰባ ተወጥሮ የከረመው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ በቡድንም ሆነ በተናጠል መንቀሳቀስ እንደሚከለከል አስታወቀ፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አገዛዙ ስልጣን እንዲለቅ የሚጠይቁ የቡድንም ሆነ የተናጠል እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ በሚገኙበት በዚህ ሰዓት፤ በቀጣይ ቡድናዊም ሆነ ተናጠላዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደሚከለከል ፓርቲው ይፋ አድርጓል፡፡ ፓርቲው ስብሰባውን ከመጀመሩ በፊትም ሆነ በስብሰባው መሐል፣ ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ ከዚህ በፊት ተሰምተው የማይታወቁ የመፍትኤ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ገልጾ የነበረ ቢሆንም፤ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎ የወጣው መግለጫ ግን፣ ዜጎች በቡድንም ሆነ በተናጠል እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይችሉ ያስጠነቅቃል፡፡

ይህ ማስጠንቀቂያ፤ ዜጎች በጋራ ወይም በቡድን የሚያደርጓቸውን የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ጭምር እንደሚያካትት ታውቋል፡፡ ፓርቲው፣ አድሮ ቃሪያ ከመሆን ውጭ የመለወጥ አቅምም ሆነ ፍላጎት እንደሌለው ከመግለጫው መረዳታቸውን የገለጹ ታዛቢዎች፤ በቡድንም ሆነ በተናጠል የሚደረጉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ለመከልከል፣ ፓርቲው አስራ ስምንት ቀናት ሙሉ በር ዘግቶ ስብሰባ ማካሄዱ እንዳሳዘናቸውም ታዛቢዎቹ አክለዋል፡፡

የድርጅቱ መግለጫ ይቀጥልና፣ በድርጅታችን ውስጥ የበላይም ሆነ የበታች ፓርቲ የለም ይላል፡፡ ዛሬ ቅዳሜ ታህሳስ 21 ቀን 2010 ሲያካሂድ በሰነበተው ስብሰባ ዙሪያ መግለጫ ያወጣው የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ በኢህአዴግ ውስጥ የበላይነት ያለው ወይም የበታች ሆኖ የሚኖር ፓርቲ የለም ብሏል፡፡ የድርጅቱ መግለጫ፣ የስርዓት ለውጥ ከተደረገበት ከ1983 ጀምሮ እስከ ዛሬ የዘለቀውን የህወሓት የበላይነት አስተባብሏል፡፡ የአንድ ሀገር ወሳኝ የስልጣን ቦታዎች የሆኑትን መከላከያ፣ ደህንነት እና ሌሎች የጸጥታ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ የያዘው ህወሓት ቢሆንም፣ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያወጣው መግለጫ ግን ይህን የበላይነት ማስተባበሉን የፖለቲካ ተንታኞች አልተቀበሉትም፡፡

ድርጅቱ ባወጣው በዚሁ መግለጫ ላይ፣ የተለያዩ ጉዳዮችን የነካካ ቢሆንም፤ አብዛኛው የመግለጫው ክፍል ግን ከዚህ ቀደም ድርጅቱ ከተናገራቸው አባባሎች ተመዘው የመጡ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን እያካሄደ ባለበት ሰዓት በመሐል ባወጣው መግለጫ ላይ፣ በሀገሪቱ ለተፈጠሩ ፖለቲካዊ ቀውሶች እና ግጭቶች ተጠያቂው እኔ ነኝ ብሎ ነበር፡፡ ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ ዛሬ የወጣው መግለጫ፣ አዲስ ነገር ያልታየበት እና ፓርቲው ራሱን ጥፋተኛ አስመስሎ ለሌላ የሰልጣን ዘመን መሰናዳቱን የሚያሳብቅ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ቀውስ ‹‹ጊዚያዊ›› ሲል አሳጥሮ ጠርቶታል፡፡ ሆኖም ህዝብ ሲጠይቅ የቆየው የፖለቲካ ለውጥ፣ የአጭር ጊዜ ሳይሆን ለረዥም ጊዜ ሲንከባለል የመጣ መሆኑን ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡

‹‹ኢህአዴግ አገራችንን ከመበታተን ቋፍ አውጥቶ አዲስ አይነት ዴሞክራሲያዊ አንድነትና የእኩልነት ትስስር በመገንባት ረጅም ርቀት ተጉዟል፡፡›› ሲል በራሱ መግለጫ ራሱን ያሞካሸው ፓርቲው፤ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለመገንባት ብዙ ስራዎች መሰራታቸውንም በመግለጫው አትቷል፡፡ በተከተለው ፖለቲካዊ አካሄድ፣ ለዘመናት አንድ ሆነው በኖሩ ህዝቦች መካከል ጥርጣሬ እና አለመተማመን የፈጠረው ኢህአዴግ፣ ሀገራችንን ከመበታተን ቋፍ ታድጊያታለሁ ማለቱ እንዳስገረማቸው፣ የድርጅቱን መግለጫ የተከታተሉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በመግለጫው አንደኛው ክፍል፣ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለመገንባት ደፋ ቀና ሲል መክረሙን ይናገርና፤ ‹‹ብሄረሰባዊና አገራዊ ማንነትን አስተሳስሮ በመገንባት በኩል የታየውን ጉድለት በአፋጣኝና በአስተማማኝ መንገድ መፍታት እንደሚኖርብን ታምኖበታል፡፡›› በማለት በፖለቲካዊ ሴራዉ ምክንያት በአንድ ሀገር ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን መለያየት ለመጥቀስ እንደሞከረ ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡ የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ላይ የተለያዩ ጉዳዮችን የጠቃቀሰ ቢሆንም፤ ባጠቃላይ ግን ምንም አዲስ ነገር ያልታየበት፣ ፓርቲው ስልጣን የመልቀቅም ሆነ ራሱን የመለወጥ ፍላቶት እንደሌለው ያረጋገጠ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ገልጸዋል፡፡ ተንታኞቹ አክለውም፤ መግለጫው በርዝመቱም ሆነ በተደጋጋሚ በተገለጹት ቃላቱ አሰልቺ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

BBN Daily News December 30, 2017

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s