ከብሔራዊ እርቅ ባሻገር! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

በዳዊት ከበደ ወየሳ

Ethiopian political prisoner Eskinder Nega released.

እድሜያችን ገና በሃያዎቹ ውስጥ እያለ፤ ከነእስክንድር ጋር ደጋግመን የምንጫወተው፤ ነገር ግን ሁሌም አድማጭ እና መፍትሄ የማናገኝለት ጉዳይ ቢኖር፤ የብሔራዊ እርቅ ርዕሰ ጉዳያችን ነበር። ያ ሁሉ ግዜ አልፎ… እኛም ተሰደን፤ እስክንድርም ታስሮ ሲፈታ… የ”ብሔራዊ እርቅ” አጀንዳችን ታወሰን። እናም የወጣትነት ጓደኛችንን የእስክንድር ነጋን ንግግር እያደመጥን በደስታ እና በተመስጦ እንባችን ወደ ውስጥ ፈሰሰ። እነሆ ከሰላማዊ ትግሉ ማዶ በኢትዮጵያ ሊነግስ የሚገባውን ብሔራዊ እርቅ በማሰብ… ይህንን አልነ።

“ድል ለሰላማዊ ትግላችን!” ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

ባለፈው ሳምንት የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን የመፈታት ዜና ሰምተን፤ ደስታችንን አጣጥመን ከመጨረሳችን በፊት… “ይቅርታ ጠይቃችሁ ትፈታላቹህ” መባላቸውን አረዱን። ሆኖም እነዚህ የዘመናችን ጀግኖች… “ያለጥፋታችን መታሰራችን ሳያንስ፤ ‘ይቅርታ ጠይቁ’ መባላችን ትክክል አይደለም” ብለው፤ ዳግም ወደ ቃሊቲ ተመለሱ። ይህንን ሁሉ የጀግኖች መዋዕለ-ዜና እየሰማን ሰንብተን፤ ዛሬ ላይ በድንገት “ጓደኛችን ተፈታ!” የሚለውን የምስራች ዜና ሲበሰርልን፤ የልባችን ንዝረት ሃያል ነበር። እኛ የሰማነውን ዜና ባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል እና ናፍቆት እስክንድር ሲሰሙ ደግሞ ምን ያህል ሊደሰቱ እንደሚችሉ በማሰብ ህሊናችን በሃሴት ይባቤ ለፈጣሪ ምስጋና አቅርባለች።

ልክ እንደ’እስክንድር ሁሉ… የአንዷለም አራጌ፣ የበቀለ ገርባ፣ የነውብሸት ታዬ፣ የነአህመዲን ጀበል፣ የነቀስቶ እና የሌሎቹም ታሳሪ ቤተሰቦች የደስታቸው መጠን የላቀ እንደሚሆን ለአንድ አፍታ ጥርጣሬ አይገባንም። ከምንም በላይ ደግሞ ላለፉት በርካታ አመታት በሰላማዊ ትግል አምነው ሲታገሉ የነበሩ፤ አሁንም  በሰላማዊ ትግል ውጤት ያስመዘገቡ ኢትዮጵያውያን… ሁሉም ሊመሰገኑ ይገባል።  ለዚህም ነው… ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንደተፈታ…

“ድል ለዲሞክራሲ!”

“ድል ለህዝባችን!”

“ድል ለሰላማዊ ትግላችን!” ሲል፤ በውስጥ አዋቂ የሰላማዊ ትግል አርበኞችን እያመሰገነ ለመሆኑ ሳይገባን የሚቀር አይመስለንም።

ዛሬ ከእስር የተፈቱት ጀግኖቻችን… ትላንት ለፍትህ እና ለእኩልነት ስለቆሙ፤ በፍትህ ሽፋን “አሸባሪ” ተብለው መቀመቅ እንዲወርዱ የተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው። ከዚያም አልፎ… ትላንት በግፍ የተገደሉት ኢትዮጵያውያን ደም ፈ’ሶ አልቀረም። በዚህ ሁሉ ግፍና በደል ላይ ለዘላለም የማይጠወልግ የዲሞክራሲ ችግኝ፤ እዚህም እዚያም እንደአደይ አበባ ፈነጠቀ። እነሆ የትግሉን መጀመር የሚያበስረው ነጋሪት ከዳር እስከዳር አስተጋባ። በ’ነዚህ ዜጎች ላይ የተፈጸመው ግፍ…  እስላም እና ክርስቲያኑ፤ አማራና ኦሮሞው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንዲት ኢትዮጵያ ስም እንዲማማል አደረገው።

ዛሬ ላይ የምናየው… የእስረኞች መፈታት የሰላማዊ ትግሉ አንደኛው ውጤት ቢሆንም፤ በዚህ ተመጻድቀን የሰላማዊ ትግሉን መጋረጃ የምንዘጋበት ምዕራፍ ላይ… ገና አልደረስንም። እኛ የትግሉን የመጀመሪያ ምዕራፍ በተመስጦ በምናይበት ቅጽበት፤  ኢህአዴግ ደግሞ በመንታ መንገድ ላይ ሆኖ ቁልቁል ወደ አዘቅት ለመውረድ ወይም ደግሞ ዘላቂውን የኢትዮጵያ ሰላም ለማውረድ፤ ብዥ ባለ መንፈስ ውስጥ ተጠምዷል። ቁልቁል ወደ አዘቅት የሚወርድበት መንገድ ቅርብ የመሆኑን ያህል፤ ሰላም የሚወርበት ጎዳና ደግሞ በብሔራዊ የእርቅ ጉባዔ ጥቂት መንገድ ሊያስኬደው ይችላል። ጥያቄው… “ኢህአዴግ በብሔራዊ እርቅ አገሪቱን ወደ አንድነት ያመጣታል? ወይስ ዶሮ እንደጫረው ጥሬ ይበታትናታል?” የሚለው ይሆናል።

ብዙዎቻችን እንደምናውቀው… ኢህአዴግ እራሱን ለብሔራዊ እርቅ አዘጋጅቶ አያውቅም። የበደለውን የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ፤ በውሸት ፕሮፓጋንዳ እራሱን ሰማይ አድርሶ ሌላውን መወንጀል እና በጠላትነት መፈረጅ እንደሙያ የሚከተለው አብዮታዊ ፖለቲካው ነው። በዚህም ምክንያት የህዝቡን እንባ ከማበስ ይልቅ ይብስ ሲያባብሰው ሰንብቷል።

ዛሬ በሺህ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞች በመላ አገሪቱ ድምጻቸውን  የሚያሰሙት፤ የበደል ጽዋው ሞልቶ ስለፈሰሰ እንጂ፤ በቀን ሶስት ግዜ መብላት በመቻላቸው አይደለም። ይህን የህዝብ ጩኸት በጠመንጃ ለማፈን መሞከር ትርፍ-አልባ የፖለቲካ ኪሳራ የመሆኑን ያህል፤ ዜጎችን በሃሰት ወንጅሎ ወህኒ መወርወር… ውጤቱ የዜሮ ብዜት ለመሆኑ የዘመናችን ተሞክሮ አሳይቶናል።

በመሆኑም መንበረ ስልጣኑን የጨበጠው ኢህአዴግ… አንድም ታሪካዊ ሞት መሞት ወይም እራሱን ለብሔራዊ እርቅ ማዘጋጀት አለበት። ብሔራዊ እርቅ ስንል ደግሞ… በወልም ሆነ በግል በደል የደረሰባቸው ሊካሱ ይገባል። በቅርብ ከምናውቀው ተነስተን አንዳንድ ነገሮችን እንደዋዛ እንጨዋወት። ለምሳሌ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በሃሰት ውንጀላ ለእስር ሲዳረግ፤ ቤትና ንብረቱ እንዲወረስ ፍርድ ቤቱ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሰጥቶበታል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ቤተሰቡም ለስደት ተዳርጓል። በፍትህ ሽፋን እንዲህ አይነት በደል የደረሰባቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አሉ። እናም ኢህአዴግ እነዚህን ዜጎች በይፋ ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን፤ ለባከነው ግዜና ንብረት ካሳ የመክፈል የሞራልም የህግም ግዴታ ይኖርበታል። እንግዲህ ብሔራዊ እርቅ ከዚህ ይጀምራል።

ከዚህ የሚጀምረው ብሔራዊ እርቅ… በወል እና በአገር ደረጃ ሰፍቶ፤ በመንታ መንገድ የቆመችውን አገር በሰላማዊ ጎዳና መውሰድ ይቻላል። እናም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ “ሰላማዊ ትግላችን ይቀጥላል!” ሲል፤ ትላንት የቆመለት ‘የህዝብ አንድነት፣ የነጻ ፕሬስ ነጻነት፤ የመደራጀት፤ የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ይከበር!’ ማለቱ ነው። ታላቂቱን ኢትዮጵያ ለመገንባት የምንሄድበት መንገድ ግን… የጠመንጃ ጋጋታ እና የሃሰት ፕሮፓጋንዳ አያሻውም። ታላቂቱ ኢትዮጵያ የምትገነባው… የመሰረት ድንጋይዋም የሚጣለው በብሔራዊ እርቅ እና እርቅ ላይ ብቻ ሊሆን ይገባዋል።

ዛሬ በመንታ መንገድ ላይ ቆሞ አገሪቱን በመንታ መንገድ ላይ እንድትዋዥቅ ያደረጋት ኢህአዴግ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ሊጠቀምበት የሚችለው፤ የመጨረሻ ካርድ  ቢኖር… ተከታታይ የብሔራዊ እርቅ ጉባዔዎችን በማድረግ በመላ አገሪቱ እርቅ ማስፈን ብቻ ይሆናል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ… ድንበር መጠበቅ የሚገውን ወታደር መሃል ከተማ አስገብቶ ህዝብን የመፍጀት ስራውን የሚቀጥል ከሆነ ግን፤ በማንኛውም ግዜ የጠመንጃው አፈ ሙዝ ወደርሱ ሊዞር እንደሚችል ማመን ይኖርበታል። አሁን በትግሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ሆነን የኢህአዴግን የመጨረሻ እድል፤ በጨለማ ጭላንጭል ውስጥ እያየን ነው። እነሆ የግዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ብሔራዊ እርቅን የማይከተል መንግስት አይሞቱ ሞት ይሞታል። ያን ግዜ የወላጁን የአቶ መለስ ዜናዊን ያህል ፍታተ-ጸሎት ሊያገኝ ቀርቶ፤ የቀብር ስርአቱ እንደሰዶም እና ገሞራ የፈጠነ ይሆናል።

እመኑን! በብሔራዊ እርቅ ይህች አገር ዳግም ካልቆመች በቀር… ኢህአዴግ ከሞተም በኋላ፤ የፈጀውን ያህል ግዜ ፈጅቶ… የሞተውንም ያህል ሰው ሞቶ ታላቂቱ ኢትዮጵያ፤ በኢህአዴግ መቃብር ላይ ትገነባለች!

“ድል ለሰላማዊ ትግላችን!”

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s