ከአድዋ ድል ማግስት፤ አጼ ምኒልክ እና ኤርትራ (ከ ሙሉጌታ ገዛኸኝ)

 

የአድዋውን ጦርነት ድባብ በርካታ የውጭ ጸሓፍት በስፍራው ተገኝተው የዘገቡት ቢሆንም ከአገሬው ዐይን እማኝ ታዳሚዎች መካከል የአጼ ምኒልክ መዋእለ ዜና አሰናጁ ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሤ ወልደአረጋይ ለዛ ባለው አገላለፅ ሲፅፉት ያስደምማል፡-« እንዲህም እስኪሆን ድረስ  ከሌሊቱ በ11 ሰዓት የጀመረ እስከ 4 ሰዓት ድረስ ተኩስ አላባራም፣ ድምፁም እንደ ሐምሌ ዝናብ እንደያማባራው ነበረ፤ በኖኅ ሰማዩ ተነድሎ መሬቱን አጠፋው እንደሚባለው እንደዚያ ይመስላል እንጅ በሰው እጅ የተተኮሰ አይመስልም፡፡ መድፉም ሲተኮስ ጢሱ የቤት ቃጠሎ መስሎ ይወጣ ነበር፡፡… ነገር ግን ከብዙ በጥቂቱ ጻፍን እንጅ የአድዋን ጦርነት በዐይናችን እንዳየነው በጆሯችን እንደሰማነው መጻፍ አይቻለንም፡፡» በማለት ከትበዋል፡፡

በጦርነቱ ስለወደቁ ጀግኖች አርበኞችም እጅግ አጥብቆ ኅዘን ሆነ፡፡ ከአድዋው ጦርነት ላይ የሚሞተው ይህ ሁሉ ሰው ለአገርና ለንጉሱ ፍቅር ሲያልቅ ያዩት አጤ ምኒልክ ልባቸው በእጅጉ ተነክቶ አዘኑ፡፡ እቴጌይቱም ስለአሽከሮቻቸው፣ ስለወዳጆጃቸው ማለቅ (ስለ ዘማቹ አርበኛ መስዋዕትነት) መሪር ኀዘን አዘኑ፡፡ ብርሃን የመሰለ ፊታቸው አጥላስ እስኪመስል አለቀሱ፡፡ ነገር ግን እንደተኩሱ ብዛት እንደቀኑ ርዝመት የሞተው ሰው ኀዘን መሪር ቢሆንም ስለቆመው ባንዲራና አገር ሲሉ ተፅናኑ፡፡ በማለት ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሤ ያወሳሉ፡፡

ለመሆኑ ከአድዋው ድል የምንማረው በጎ ነገር ምንድነው? ኢትዮጵያውን በጋራ አንድነትና ኅብረት ብረታት ፍቅርን ተላብሰው የውጭ ጠላትን ለመመከት በጀግንነት ወላፈን መተባበራቸውን እንጅ በጥላቻና በዘር የመከፋፈል አባዜን አይደለም፡፡

አሜሪካኖች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተቃጣባቸውን ጥቃት ለመከላከልና ኅብረት ለመፍጠር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን “United we stand/strong divided we fall” በሚገባ እንዳጤኑት ልብ ይሏል፡፡ «እርስ በርሷ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፤ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም፡፡»ማቴ 12፡ 25 «መንግሥትም እርስ በርሷ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤ ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ቤት ሆኖ ሊቆም አይችልም፡፡»ማር 3፡25 ፡፡

ስለመረብ ምላሽ የኢትዮጵያ አካል ለጊዜው ተቆርጦ መቅረት ንጉሠ ነገሥቱ ቁጭት ያሳደረባቸው መሆኑን ልዩ ልዩ የሰነድ ማስረጃዎች ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በአንዳንድ ፀሐፍት ዘንድ ከሚቀርቡት ትችቶች መካከል አጼ ምኒልክ ኤርትራ በኢጣልያ እጅ እንድትቆይ ሆነ ብለው የፈፀሙት ደባ ነው የሚለው አስተሳሰብ ተጠቃሽ ነው፡፡ ምክንያቱን ሲብራሩ ደግሞ ኢጣልያ የመረብ ምላሽ ግዛትን “ኤሪትሪያ” ብላ ሰይማ ቅኝ የምትገዛውንም ህዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲነጠል በፀረ-ኢትዮጵያዊነት ጥላቻ ፕሮፖጋንዳ እንዲፈጠለፍ በማድረጓና ኤርትራውያንም በዚሁ ቅሬታ ውስጥ በመቆየታቸውን ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ማረጋገጣቸው ነው ይላሉ፡፡ ይህ አተያይ እውነታው ግልፅ ቢመስልም አጼ ምኒልክ ወደ ፊት ገፍተው እንዳይሄዱ አጣብቂኝ ውስጥ የከተታቸው የስንቅና ውሀ ተያያዥ ችግሮች ያላቸውን የሰው ሀይል አቅም ለጊዜው በመፈታተኑ ምክንያት ብቻ እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ ጥንት ኢትዮጵያ የነበራትን የሰሜኑን የባሕር በር ስትራቴጂያዊ ይዞታ ጠቀሜታውን አብጠርጥረው የሚያውቁት ዳግማዊ ምኒልክ ይቅርና በማናቸውም ዜጋ ህሊና ዘንድ የማይዘነጋ ነው፡፡ የአድዋ ጦርነት የተቋጨው ንጉሠ ነገሥቱ የመረብ ምላሽ ግዛታቸውን ከወራሪው ኢጣልያ ጦር መንጋጋ ለማስለቀቅ ከፍተኛ ቁጭት እንዳዘሉ መሆኑን በቀላሉ ለመረዳት አያዳግትም፡፡

ጦርነቱ በተጠናቀቀ በነጋታው አጼ ምኒልክ ከሰኞ እስከ ሀሙስ ውሎ አድርገው የሞቱትን ሲያስቀብሩና የቆሰለውንም እያነሱ በአድዋና አክሱም ሲያመሩ፣ መድፉን ነፍጡን የመድፉን አረር ሲያሰባስቡ ሰንብተው በ28 ቀን ሐማሴን ለመሻገር ወደ እንትጮ ተጓዙ፡፡ እንትጮ ሰፍረው ወደ ሐማሴን የሚያስከደውን መንገድ ሲያሰልሉ መሰንበቻ ሆነ፡፡ እዚያም ላይ እንደሰፈሩ የኢጣልያ ሹም በጦርነቱ ያለቁትን ኢጣልኖች ልቅበር ብሎ አጼ ምኒልክን ለማስፈቀድ መጣ፡፡ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ቀርቦ የኢጣልያ መንግስት ከግርማዊነትዎ ጋር እርቅ ወዷልና ከንጉስ ኡምቤርቶ ዘንድ ባለማኅተም ደብዳቤ እስኪመጣ ድረስ ወደ ሐማሴን አይሻገሩ ጦርዎን ያስቁሙልን ብሎ ለመነ፡፡ እሳቸውም እስከዚያው ድረስ ጦርነት ማድረግ እንዲቆይ ሲሉ ፈቃዳቸው ሆነ፡፡

ሆኖም አጼ ምኒልክ ኢጣልያኖችን ተዋግተው አድዋ ላይ አስደናቂ ድል ተቀዳጅተው ወቅቱ በፈቀደው የሞራል ብርታት አዲኳላን ተሻግረው እንዲሰፍሩና እዚያው እንዲቆዩአቸው የትግሬውን ገዥ ልዑል ራስ መንገሻን፣ የሐረርጌውን ገዥ ልዑል ራስ መኰንን፣ ፊታውራሪ ተክሌን፣ ሊቀመኳስ አድነውን እንዲሁም ሌሎችን ሰደዷቸው፡፡ እነሱም በታዘዙት መሰረት ወደ አዲኳላ ተሻግረው ቢወርዱም የመረብ ወንዝ ውሀ ደርቆ ስላገኙት እንኳን አካባቢው የአጼ ምኒልክን ጦር ሊያሰፍር ቀርቶ  ጥቂቱን ጋሻ ጃግሬ እንኳ በውሀ ጥም ተጨንቆ መክረሙን አሳወቋቸው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም የወንዙን ውሀ መድረቅ ቢሰሙ የእግዚአብሄር ፈቃድ ባሆን ነውና ተመለሱ ብለው ላኩባቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አጼ ምኒልክም ወደ ሐማሴን ለመሻገር እያሰላሰሉ ከገንደብታ ተጉዘው አባገሪማ ጉልት ላይ ሰፍረው ሰነባበቱ፡፡ እዚያም ረቡዕና ሐሙስን ሲመክሩ ቆይተው ኢጣልያ ከያዘችው የመረብ ምላሽ አቅጫጫ ብትወጣም ባትወጣም ወደ ሐማሴን እንጓዝ ተብሎ በመኳንንቱ ዘንድ ቁርጥ ምክር ተመከረ፡፡  በሌላ በኩል ጆርጅ በርክሌይ ይህንኑ አስመልክቶ የአድዋ ዘመቻና የአጼ ምኒልክ አነሳስ በሚል በተተረጎመው መጽሐፉ ሲብራራ ከሁለቱም ወገን በጦርነቱ ያለቀው ሰው ቁጥር ቀላል ስላልነበረ አጼ ምኒልክም ለሠራዊታቸው የሚቀርቡት ስንቅ መመናመን እንዲሁም ኢጣልያ ተጨማሪ ሀይል ለማሰለፍ ብታደርግ በነበረው ሙከራ ከመረብ ወዲያ ያለውን ግዛታቸውን ለማስመለስ ለጊዜው ዘመቻው ፈታኝ መሆኑን አስቀድመው የተገነዘቡት ይመስላል፡፡  ቸር ይግጠመን!!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s