በሞያሌ በግፍ ስለ ተጨፈጨፉት ወገኖቻችን የተሰጠ የኃዘን መግለጫ

መቆሚያ ያጣው የኢትዮጵያ እንባ

በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ከአውስትራልያ ሀገረ ስብከት

የሚያጽናናኝ ነፍሴንም የሚያበረታት ከእኔ ርቋልና ፥ ስለዚህ አለቅሳለሁ  ዓይኔ  ዓይኔ ውኃያፈስሳል  ጠላት በርትቶአልና ልጆቼ ጠፍተዋል  ሰቆቃ ኤር 116

ይህ ጩኸት የኢትዮጵያ የእየለቱ ጩኸት ሁኖ ሲቀጥል ዓመታት ተቈጠሩ። ያለፈውን የወገኖቻችን እልቂት ሰምተን እንባችን በወጉ ሳንጠርግ አሁንም በየቀኑ ከሚፈሰው የንጹሐን ደም ባለፈ በሰላማዊ መንገድ በሥራ ቦታቸው ያሉ ወገኖቻችንን በጅምላ ጨፍጭፎ በስሕትት ነው እያለ  የሚንቅና  የሚቀልድ  አካል ልባችንን አድምቶታል። ይህ ተግባር አንድ አገር እመራለሁ ከሚል አካል ይቅርና በሰው ደረጃ ከሚንቀሳቀስ ጤናማ አእምሮ የሚከናወን ድርጊት አይደለም።Ethiopian orthodox church cross

ኤርምያስ በነበረበት ዘመን መከራና ስቃይ ለሚደርስበት ሕዝብ የጮኸው የኃዘን ጩኸት ፣ ዛሬም በኢትዮያ ምድር የሚጮኽ ጩኸት ነው ። ነቢዩ የሕዝቡን መከራ እያየ ዝም ማለት አቅቶት ይህንን የመከራ እሮሮ አንጎራጎረ ። እኛም ዛሬ በባዕድ ምድር ሁነን የወገኖቻችንን እልቂት ስንሰማ የመረረ ኃዘን ውስጥ ሁንን ነው ይህን አጭር የልብ ስብራታችንን የሚገልጥ መግለጫ ያወጣነው።

ጉዳዩን አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ “በስሕተት ነው” የሚለው ቀልድ ነው ።  አንድ የታጠቀ ኃይል በጦር ሜዳ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት ይህን ያህል ሰው ለመግደል እንዴት ሊሳሳት ይችላል ? ይህ ከሆነ አእምሮው የተነካ ሰው መሆን አለበት ፣ በሠለጠነው ዓለም እንዲህ የሚያደርግ ሰው አእምሮው የተነካ ይባላል ። በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ሰው ማኅበረሰቡን እንዳይጎዳ ወደ ጥብቅ የእሥር ወይም የጥበቃ ቦታ ይገባል ። መሣሪያ ከእጁ እንዳይገኝ ጥንቃቄ ይደረጋል ። በኢትዮጵያ አእምሯቸው የተነካው የሚባሉት ታዘው የተኮሱት ሳይሆኑ ፣ አዛዦቹና ሰው እንዲገድሉ ሥልጣን የሚሰጠውን “የአስቸኳይ ጊዜ” የተባለውን የጥፋት አዋጅ ያወጡት ግለሰቦች ናቸው ። መሣሪያቸውንና የሚገለገሉበትን አዋጅ መነጠቅ ያለባቸው እነሱ ናቸው።

አሁን በኢትዮጵያ በሕወኃት የሚመራ ሥርዓት ፥ በሥልጣን ወዳድነት የአዕምሮ መቃወስ የገጠማቸው ግለሰቦች የተጠራቀሙበት ስለ ሆነ ለአገርና ለሕዝብ አደጋ ነው ። ስለሆነም መታሰር ያለበት ይህ ሥርዓት ነው።

ሥር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሳይሆን በሥልጣን አጣለሁ በሽታ የተያዘ ፥ ከጤናማ ሰው አእምሮ ውጭ እንደ አውሬ የሚያስቡ የግለሰቦች ስብስብ እንጂ መንግሥትን በመንግሥትነት ሊመራ የሚችል ሥርዐት አይደለም።

ይህን የምንልበት ምክንያት ሰውን ያህል ፍጡር ትንፋሽን የሚቈጣጠር አዋጅ አውጥቶ ዘወትር ሰዎችን እያስገደለ “በስህተት ነው” የሚለው አባባል ተቀባይነት ሊያግኝ የሚችለው የእእምሮ ጤና በጎደላቸው ሰዎች ዘንድ ብቻ መሆን አለበት እንጂ ፤ በትክክለኛና በጤናማ አእምሮ የሚያስብ ማኅበረ ሰብ ይህን የዕብዶች ሥርዓት አይቀበልም ። እንዲያውም ሊያውግዘው ይገባል።

ከሁለት ሰው በላይ በአንድ ቦታ ላይ መቆምና መሄድ አትችሉም የሚለውን አዋጅ ያወጅኩት ለሕዝብ ነጻነት ስል ነው የሚለው አባባል በተጨባጩ ዓለም ላይ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ። በዚህ አዋጅ መሠረት በትዳር የሚኖሩ ጥንዶች ከትዳር ጓደኛቸው ጋር መሄድ አይችሉም ፥ ሁለት ልጆች ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለማድረስ ሁለት ጊዜ መመላለስ አለባቸው ፣ አባት ወይም እናት ከሁለቱ ልጆቻቸው ጋር ሲሄዱ ቢገኙ አዋጁን ጥሳችኋል ተብለው ሊገደሉ ወይም ተደብድበው ሊታሰሩ ይችላሉ። ምክንያቱም ሕጉ ይህን አዋጅ የሚያስከብሩት አካላት የፈለጉትን እንዲያደርጉ ይፈቅድላቸዋልና ነው።

እነዚህ ወታደሮችም ይህን የመግደል አዋጅ ተጠቅመው ነው ንጹሐን ወገኖቻችንን በጥይት ጨፍጭፈዋል ።  በመሆኑም ነፍሰ ገዳዮች መባል ያለባቸው ወታደሮቹ ሳይሆኑ አዋጁን ያወጀው አካል ነው። መታሰርና መሣሪያውን መቀማት ያለበትም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እያሉ የሚቀልዱበት ወያኔ የሚመራው ሥርዓትና መንግሥት ነው ። ስለዚህ በሞቱ ወገኖቻችን መሪር ኀዘናችንን እየገለጥን ፣ የሕወኃት የጦር አዛዦችና ባለ ሥልጣኖቹ ለፍርድ እዲቀርቡ ፥ በአውስትራልያ ሀገረ ስብከት ስም እንጠይቃለን።

በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም ዙሪያ የምትኖር ኢትዮጵያዊ ወገናችን ሆይ ! የትኛውንም ቋንቋ የምትናገር ፥ በየትኛውም ነገድ የምትጠራ ፥ በየትኛውም ሃይማኖት የምታመልክ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ዛሬ በሞያሌና በሌላውም የኦሮሞኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን እየፈሰሰ ያለው ደም ያንተ ደም ነው ። ሞታቸው ሞትህ ነው ፣ ስደታቸው ስደትህ ነው ፣ እየተንገላታ ያለው የአንተ አካል መሆኑን እወቅ ። መቃብር የገባው የአንተ የራስህ አካል ነው ። ስለዚህ ዛሬ አንተ ስላልሞትክ ለነገ ዋስትና ያለህ አይምሰለህ ። ነገ ጧት ስትወጣ ከአንድ ጓደኛህ ጋር ስትገናኝና ሁለት ሁናችሁ ትምህርት ቤት ወይም ሥራ እንዲሁም ገበያ ልሂድ ብትል አንተም ሞያሌ እንደ ሞቱት ወገኖችህ ትሞታለህ ፥ እነርሱም አንተን ናቸው ፥ አንተም እነርሱን ነህ።

ስለዚህ ይህን የኢትዮጵያን ሕዝብ በማያቋርጥ ኀዘን ውስጥ እንዲገባ ያደረግ ሥርዐት ለአንዴና ለመጨረሻ እንዲያበቃ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ እንዲተባበር ፣ የተሰደዱት በያሉበት እርዳታ እንዲያገኙ እንድታደርጉ በግፍ በተጨፈጨፉት ወጎኖቻችን ስም ጥሪ እናቀርባለን።

የሞቱትን ነፍሳቸውን እንዲምር ለወገኖቻቸውና እንዲሁም ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብርታትን ጽንአትን ኅብረትን እንዲሰጥ ወደ አምላክችን እንጸልያለን ። የፖለቲካ መሪዎች ፥ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ፥ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ አቀንቃኞች ሁሉ የሕዝባቸውን መከራ ለማሳጠር ሲሉ እንዲተበባበሩና ይህን ሰላማዊ የሕዝብ ትግል ከዳር እንዲያደርሱ በቤተ ክርስቲያን ስም በታላቅ ጩኸት ጥሪ እናቀርባለን።

አባ ጴጥሮስ

የአውስትራልያና የኒውዝላንድ ሊቀ ጳጳስ ።

ሜልቦርን አውስትራልያ

Leave a comment