ግልጽ ደብዳቤ – ክቡር ዶ/ር አቢይ አሕመድ (ትብብር)

ይድረስ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር

ክቡር ዶ/ር አቢይ አሕመድ

ትብብር የተሰኘው የ ፳፮ የኢትዮጵያ ማኅበረ-ሰባዊ ድርጅቶች ማዕከል፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ቦታ በመያዝዎ የደስታ መልዕክቱን ያስተላልፋል።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ስልጣን በተረከቡበት ዕለት በንግግርዎ “ዲሞክራሲ ያለነጻነት አይታሰብም” ማለትዎን፤ በጽንሰ-ሃሳብ ደረጃም ቢሆን፤ አቀራረብዎ ለዘመናት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲመኝ የነበረውን የነጻነት ተስፋ ጭላንጭል የሚከፍት ሆኖ አግኝተነዋል።

በነጻነት መኖርን በመፈለግ፤ በሺ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ተሰደዋል፤ ታስረዋል፤ ተሰውተዋል እንዲሁም በመላው አለም ተበታትነዋል። ከሚሊየን በላይ የሚገመቱ ወገኖቻችን ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ቁጥራቸው በቅጡ ባይታወቅም፤ በየቀኑ ብዙ ወጣቶች ከአገራቸው መሰደዳቸው ቀጥሏል።

“ዲሞክራሲ የለነጻነት አይታሰብም” ብለው ያስቀመጡት አቢይ አነጋገር፤ በተግባር ሊፈጸም ይችል ዘንድ የአስተዳደርዎ ተቀዳሚ መርህ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። ወደ ዲሞከራሲ የሚደረገው ጉዞም የሚከተሉትን ተግባራት ሊያጠቃልል ይገባል ብለን እናምናለን፤–

1. በኢትዮጵያውያን ላይ የተደነገገውን ጊዜያዊ አዋጅ በፍጥነት ማንሳት
2. ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ያለ ቅደመ-ሁኔታ መፍታት
3. ከዚህ ቀደም “ሽብርተኞችን መከላከል” በሚል ሽፋን፤ በጋዜጠኞች፤ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የተጫኑትን “ሕግጋት” በአስቸኳይ መሻር
4. በግፍ ሰላማዊውን ሕዝብ የገደሉ፤ ያቆሰሉ እና ያፈናቀሉ ግለሰቦችንም ሆነ ተቋሞችን ለፍርድ በማቅረብ ከፍትሕ ጎን መቆም
5. በመላው ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያውያን በግለሰብም ሆነ በድርጅት በነጻነት በመንቀሳቀስ ብሔራዊ ውይይት የሚያደርጉበትን ጎዳና መጥረግ፤ መድረኩንም ማምቻቸትና ሕዝቡ የፖለቲካ ሥልጣኑ ባለቤት እንዲሆን ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት።

ከዚህ በላይ ያሉት ከብዙው ጥቂቶቹ አሰራሮች ተአመኔታ ከመስጠት ባሻገር ለሃገራችን ዲምክራሲያዊ ግንባታ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ ብለን እናምናለን። ከዚህ ባነሰ የሚደረጉ ጥገናዊ እርምጃዎች፤ በንግግርዎ ያቀረቡትን ፅንሰ-ሃሳብ ግብር-አልባ ከማድረጉ ሌላ የኢትዮጵያን ሕዝብ ትግል ላማጨንገፍ እና ያለውን ስርአት እድሜ በሌላ አቀራረብ እንዲቀጥል ለማድረግ የታሰብ ዕኩይ እርምጃ ያስመስለዋል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

ለእርስዎ የጠቅላይ ሚኒስቴር ቦታ ማግኘት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል፤ በተለይ የወጣቱ ትውልድ መስዋዕትነት፤ አስተዋፅዖ እና ውጤት ነው ብለን እናምናለን። ጥንካሬዎ ሊገነባ የሚችለው በኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍና መልካም ፈቃድ መሆኑን በማመን አገልግሎትዎ ከልብ የሕዝብን ጥቅም ያማከለ ብቻ ሊሆን እንደሚገባው እናሳስባለን።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንክሮ የዕለት በዕለት እርምጃዎን በማየት ላይ ነው። ፊትዎን እንደማያጥፉበት ተስፋ እናደርጋለን።

እግዚአብሔር ከርስዎ ጋር ይሁን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ

በትሩ ገብረእግዚአብሔር፤
የትብብር ሊቀመንበር፤

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s