የቤተ ክርስቲያንን ነጻነትና ተደማጭነት ለመመለስ ያለመ የማኅበረ ካህናት አንድነት ተመሠረተ

  • ጅምሩን በአሜሪካ ቢያደርግም በመላው ዓለም ኦርቶዶክሳውያን ካህናትን ለማቀፍ ይንቀሳቀሳል
  • ቤተ ክርስቲያን በሚገባት ክብርና ልዕልና እንዳትገኝ የካህናት ግድየለሽነት አስተዋፅኦ አድርጓል
  • በጎሠኝነትና ምንደኝነት፥ ከዓለም በከፋ ኹኔታ ተከፋፍለን፤ መተማመን ጎድሎናል፤ ተራርቀናል
  • ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ ጎድቷታል፤ መከራዋንም አብዝቶታል፤ በአንድነት ልንፈታው ይገባል
  • አባላቱ፣ ከግለኝነት እና ጎሠኝነት የጸዱ ሊኾኑ ይገባል፤ የአስተዳደር ልዩነቱ አይገድበውም፤

†††

  • አንድነት ሲኖረን እግዚአብሔር ይሰማናል፤ምእመናኑን ወደ አንድነት ማምጣቱም አይከብድም
  • ቅ/ሲኖዶሱ ሚናውን በነጻነት እንዲወጣ፤ ፓትርያርኩ ሓላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲተገብሩ…
  • የቤተ ክህነት ሓላፊዎች ለሁለት ጌቶች ሳይገዙ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ብቻ እንዲፈጽሙ…
  • መንግሥት ተገዶም ቢኾን ያደምጠናል፤ ተቋማት ያከብሩናል፤ሉዓላዊነትና ነጻነት ይመለሳል፤
  • “እንችላለን” በሚል እምነት የሌሎችንም ችግር የሚቀርፍ ሙሉ አቅም ለመፍጠር ያስችላል፤

†††

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ከየትኛውም አካል የሚደርስባትን ትንኮሳና ጥቃት በመመከትና በመከላከል ዘርፈ ብዙ ፈተናዎቿን በጋራ የመፍታት ዓላማን ያነገበ የካህናት አንድነት ማኅበር በሰሜን አሜሪካ ተመሠረተ፡፡

የአንድነት ማኅበሩ የተመሠረተው፣ ከአሜሪካ እና ከካናዳ አህጉረ ዓለም የተሰበሰቡ ሊቃውንት፣ ካህናትና ዲያቆናት፣ቤተ ክርስቲያናችንን እንታደግበሚል መሪ ቃል ለሦስት ቀናት በሲያትል ከተማ ባደረጉት ጉባዔ ነው፡፡

ከመላው የአሜሪካ ግዛትና ከካናዳ የመጡ በቁጥር ከ70 በላይ የኾኑ ልኡካን፣ ከሚያዝያ 25 እስከ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. (May 3 – 5, 2018) በዋሽንግተን ሲያትል ከተማ ያካሔዱት ይኸው የካህናት አንድነት ማኅበር ምሥረታ ጉባዔ፣ታሪካዊ እንደኾነና ፍጹም መንፈሳዊነት ባልተለየው ኹኔታ በጸሎት፣ በፍቅርና በእንባ ጭምር እንደተከናወነ፣ በመርሐ ግብሩ ፍጻሜ የወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

በምሥረታ ጉባኤው፣ ቤተ ክርስቲያናችን በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትገኝበትን ወቅታዊ ኹኔታ የዳሰሰ ጥናታዊ ጽሑፍ እንደቀረበና ጥልቅ ውይይት እንደተደረገ ተገልጿል፡፡ እውነትን የያዘችው ቤተ ክርስቲያናችን በሐሰተኛው ዓለም ውስጥ የምትጓዘው በእሳት መካከል እንደኾነ የጠቀሰው መግለጫው፣ ከፖሊቲካ ኃይሎች የሚደርስባት ፈተና ግንባር ቀደሙ ነው፤ ብሏል፡፡

መንግሥታት ሥልጣናቸውን ለማደላደል ተቋማዊ ነጻነቷን በዓምባገነንት እየተጋፉ፣ አስተዳደራዊ መዋቅሯን በመቆጣጠር በሥርዐቷና በሕጓ እንዳትመራ፤ በሀብቷና በንብረቷ በአግባቡ እንዳትጠቀም ያደረሱባትን በደሎች አብራርቷል፡፡ ተጽዕኖው በፈጠረው ተጋላጭነት ተጠቅመው በውስጧ የተሰገሰጉ ግለሰቦችም፣ አስከፊ ምዝበራ እየፈጸሙባት እንደቆዩና በአሁኑ ወቅት ሌብነቱን ነውር አልቦ ልማድ በማድረግ ያለኀፍረት እያንሰራፉት እንደሚገኙ አስፍሯል፡፡

በውጤቱም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታምንበትን እንዳትናገር፣ እውነቱን በዐደባባይ እንዳትመሰክር፣ አጥፊዎችን እንዳትገሥጽና እንዳትመክር፣ መተኪያ የሌለው የሸምጋይነት ሚናዋንም እንዳትወጣ ከማሳነስም በላይ አስተዳደሯ እንዲዳከም፣ ተደማጭነቷ እንዲጠፋ፣ ከዚህ አልፎ ያለስሟ ስም፣ ያለግብሯ ግብር እየተሰጣት ጥቂት በማይባሉ የሀገራችን ኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ በጠላትነት እንድትፈረጅ እንዳደረጋት አትቷል።

የውስጥ ችግሩንና የውጭ ተግዳሮቱን በዋናነት መከላከልና ማስወገድ የሚገባቸው፣ የኖላዊነቱ ሓላፊነት የተሰጣቸው አዕይንተ እግዚአብሔር ካህናትቢኾኑም፣ ለዓመታት አንቀላፍተው በመቆየታቸው ከዚያም አልፎ ከዓለማውያን በከፋ መልኩ በጥቅመኝነትና ጎሠኝነት መከፋፈላቸውና መራራቃቸው፣ ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ እንደጎዳትና መከራዋን እንዳበዛው መግለጫው ተችቷል፡፡

“በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተለያየ ጊዜ የመከራ ዶፍ ሲወርድ እጃችንን አጣጥፈን በመቀመጥ፣ ለፖለቲካ ኃይሎች በማጎብደድና በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ እንዲገቡ በመጋበዝ፣ በመፍቀድና በመተባበር፣ በጎሠኝነት በመከፋፈል፣ በጉቦ ቅብብል፣ በምዝበራውና በዘረፋው በመሳተፍ፣…ወዘተ የብዙዎቻችን እጅ እንዳለበት መካድ አንችልም፤” ያለው መግለጫው፣ ለችግሩ መባባስ በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የእያንዳንዳችን አስተዋፅኦ እንዳለበትና ለዓመታት ማንቀላፋታችንን ከማመን መነሣት እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡

31958247_1818206608475844_7227731421392011264_n

መፍትሔው፣ ችግሩን በግልጽ ተነጋግሮ በመተማመን እንደሚገኝ የጠቆመው መግለጫው፣ ለዚህም ካህናት ከግዴለሽነት፣ አድርባይነት፣ ምንደኝነትና ጎሠኝነት ክፉ ልማድ ርቀው ለሌላው የሚያስተምሩትን ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት በራሳቸው በመተግበር ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅባቸው አሳስቧል፡፡ ጥቂት አባቶችና ወንድሞች፣ምእመናን በተለይም ወጣቶች፣ በተለያየ ጊዜ በተናጠል የሚያደርጉት ተጋድሎ በቂ እንዳልኾነና በኖላዊነት የሚመሩት ካህናት አንድነት በእጅጉ አስፈላጊ እንደኾነ አሥምሮበታል፡፡

በአንድነት መንቀሳቀስ ከቻልን፥ እግዚአብሔር ይሰማናል፤ የምንመራቸውን ምእመናን ወደ አንድነት ማምጣቱ ከባድ አይኾንም፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የሲኖዶስነት ሚናውን በነጻነት እንዲወጣ፤ ፓትርያርኩ የፓትርያርክነት ሓላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲተገብሩ፤ በየደረጃው ያሉ የቤተ ክህነት ሓላፊዎች ለሁለት ጌቶች ከመገዛት ተላቅቀው የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልእኮ ብቻ የሚፈጽሙ እንዲኾኑ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ መፍጠር እንችላለን፤ መንግሥትም ቢኾን ተገዶ ያደምጠናል፤ ተቋማትም ያከብሩናል፤ ብሏል፡፡

“የቤተ ክርስቲያንን ችግር መፍታት አይቻልም፤” የሚል የቀቢጸ ተስፋ ድምዳሜ፣ የዓለም ብርሃን መኾን የሚገባትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በድቅድቅ ጨለማ እንድትጓዝ ከመፍረድ ተለይቶ እንደማይታይና በምትኩ “እንችላለን” የሚለውን እምነት በመያዝ ከራሳችን አልፈን የሌሎችን ችግር የምንቀርፍበት ሙሉ አቅም ለመፍጠር፣ ከራስ ክብርና የግል ጥቅም ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን ህልውናና ክብር ቅድሚያ ሰጥቶ መቀናጀት እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል፡፡

32073061_1818207351809103_4640285862054068224_n

በመንፈሳዊውም በዓለማዊውም ዕውቀት የተራቀቁና የመጠቁ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ካህናትና ምእመናን፣ በትክክለኛው መንገድ የሚመራቸው እስካገኙ ድረስ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን ብቻ ሳይኾን ሕይወታቸውንም ለመስጠት የማይሰስቱ ወጣቶች እንዲሁም እምቅ አቅምና ሀብት ያላት ታላቅ ቤተ ክርስቲያን፣ ምንም እንደሌላትና ምንም ማድረግ እንደማትችል ሁሉ የማንም መፈንጫና መዘባበቻ የኾነችበትን የዘመናችንን ክፉ ታሪክ በመቀየር በቀላሉ የማይተነኩሷትና የማይገዳደሯት ሉዓላዊ፣ የተከበረች፣ ነጻና ተደማጭ ለማድረግ፣ በአንድነትና በቁጭት ከመንቀሳቀስ በቀር አማራጭ አለመኖሩን አሳስቧል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመሠረተው ይኸው የማኅበረ ካህናት አንድነት፣ በሲኖዶሳዊ አስተዳደር የተፈጠረው ልዩነት እንደማይገድበው መግለጫው ጠቅሶ፣አባል የሚኾኑ ካህናትም፦ የሃይማኖት ሕጸጽ የሌለባቸው፣ ጎሠኝነት ያልተጠናወታቸው፣ ከግለኝነት ይልቅ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ የሚያስቀድሙ፣ አቅም በፈቀደ ሁሉ ሃይማኖታዊ ተጋድሎ ለማድረግና መሥዋዕት ለመክፈል ቁርጠኝነት ያላቸው ሊቃውንት፣ መነኰሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ ሰባክያነ ወንጌል ሁሉ እንደኾኑ ገልጿል፡፡

የማኅበሩን ዓላማና ጥቅም የተገነዘቡ ሁሉ በየአጥቢያው ለሚያውቋቸው ካህናት በትጋት በማስረዳት፣ በቀላሉና በአጭር ጊዜ ዓለም አቀፍ አንድነቱን ማምጣት እንደሚቻል ያመለከተው መግለጫው፣ የማኅበራዊ መገናኛው ለቅስቀሳው ያለውን አመቺነት በአማራጭነት ጠቁሟል፡፡

የካህናት አንድነቱ፣ ጅምሩን በሰሜን አሜሪካ ያድርግ እንጅ፣ በሒደት በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትን ሁሉ በአባልነት ለማካተት ዕቅድ ይዞ በከፍተኛ ኹኔታ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቋል – ቆጭቶናል ብለን ከተነሣን በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን የቤተክርስቲያናችንን ጉዳይ ማስቀደም ይገባናል። ሁሉም ካህናት ወደዚህ አንድነት ይመጣሉ። የሚመጡበት ጊዜ ግን የተለያየ መኾኑ የሚጠበቅ ነው።

በመጨረሻም ጉባዔው፣ ባለዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣትና የሚቀጥለውን ዓመት ጉባኤ በዋሽንግተን ዲሲ ለማድረግ በመወሰን ተጠናቋል!

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

ሙሉ የአቋም መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል::

ማኅበረ ካህናት ዘሰሜን አሜሪካ

መግቢያ

የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው። /2ኛቆሮ.11፥28

ቅዱስ ጳውሎስ ከላይ በተጠቀሰው መልእክቱ፣ ክርስቶስን በመስበኩ ምክንያት ብዙ ጊዜ እንደታሰረ፣ እንደተገረፈ፣ በየብስም በባሕርም፣ በከተማም በበረሓም ለሞት እስኪደርስ ድረስ ብዙ መከራና ሥቃይ እንደጸናበት፣ ረኀቡና ጥማቱ፣ ቍሩና ዋዕዩ እንደተፈራረቀበት ከዘረዘረ በኋላ ነው፣የቀረውንም ነገርሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው፤ የሚለው፡፡

በመድኃኔዓለም ክርስቶስ ደም ተመሥርታ በየዘመናቱ በተነሡ ቅዱሳን ተጋድሎና ጥብዓት ዘመናትን ተሻግራ ወደኛ የደረሰችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የተከፈለላት መሥዋዕት የቱን ያህል እንደኾነ ከላይ የተጠቀሰው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ትልቅ ማሳያ ነው። ተጋድሎ የሚያስፈልገው መከራ ስላለ እንደኾነ እሙን ነው። እውነትን የያዘችው ቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ በሐሰተኛው ዓለም ውስጥ ጉዞዋ በእሳት መካከል እንደኾነ ጥርጥር የለውም።

መሪ ቃል፦ ቤተ ክርስቲያናችንን እንታደግ

የአንድነት ምሥረታው የመነሻ ሐሳብ አሁን ያለበት ደረጃ፤

በክርስትና ታሪክ ጥንታውያት ከሚባሉት አብያተ ክርስቲያናት አንዷና ዋነኛዋ የኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በረዥም ጊዜ ታሪኳ፣ በቅድስናቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ተቀባይነትና ዕውቅና ያገኙ ብዙ ቅዱሳንን ያፈራች፣ በዓለማችን ላይ ከሚገኙት የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትና በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት እምነቶች በአማኞች ብዛት ግንባር ቀደም የኾነች ስመ ጥርና ገናና ቤተ ክርስቲያን ናት።

የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ ጠብቃ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያሸጋገረች የሀገር ባለውለታ ቤተ ክርስቲያን ናት። ስለሀገር ሰላምና ደኅንነት፣ ስለሕዝብ አንድነት ስትጸልይና ስታስተምር ከመኖሯም በላይ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን፣ ክብርንና ነጻነትን የሚያሳጣ፣ ሃይማኖትንና ማንነትን የሚያጠፋ የውጭ ወራሪ ሲመጣ በግንባር ቀደም እየተሰለፈች መሥዋዕትነት የከፈለች፣ የውስጥ ዓምባገነን ሲነሣ ደግሞ በግልጽ የሚገሥጹና የሚያወግዙ ቆራጦችና ጥቡዓን አባቶች የነበሯት በብዙዎች ዘንድ የምትወደድ፣ የምትከበርና የምትፈራ ባለግርማ ሞገስ ቤተ ክርስቲያን ናት።

ይኹንና ከጊዜ በኋላ ክብሯና ልዕልናዋ እየኮሰሰ፣ ተደማጭነቷና ተፈሪነቷ እየቀነሰ ዛሬ መሸምገል እንኳን የማትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች።አሁን አሁን ከዚህም አልፎ የትንሹም የትልቁም መዘባበቻና መሣለቂያ ወደ መኾን እየተሸጋገረች ትገኛለች። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ዘመን ብዙ ዓይነት ፈተናዎችና በርካታ ውስብስብ ችግሮች ያሉባት ብትኾንም ጥቂቶቹን ብቻ ለመጥቀስ እንሞክራለን።

1ከፖለቲካ ኃይሎች የሚደርስባት ተጽዕኖ፤

ይህ ችግር በአሁኑ ጊዜ በግንባር ቀደም የሚጠቀስና ለአብዛኞቹ ችግሮችም እንደ ዋና መንሥኤ የሚጠቀስ ነው። ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ ያለውን ብቻ እንኳን ብንመለከት፣ ለዓምባገነናዊ አገዛዙ እንደማትመች አስቀድሞ የተረዳው የደርግ መንግሥት፣ የፖለቲካ ሥልጣን በያዘ ማግሥት፥ ፓትርያርኳን ገድሎ፣ ጳጳሳቷን አስሮ፣ ሀብት ንብረቷን በግፍ ወርሶ፣ ነጻነቷን ቀምቶ እስረኛ በማድረግ ነው ሥልጣኑን ያደላደለው።

በእሳት ውስጥ ማለፍ የምትችልና የማትሞት ቤተ ክርስቲያን ስለኾነች ነው እንጅ፣ ደርግ እንዳደረሰባት በደልና እንደሚከተለው ርእዮተ ዓለም/ኮሚኒዝም/ ቢኾን ኑሮ አሁን የደረሰችበት ደረጃም ባልደረሰች ነበር። ኾኖም ግን በቀላሉ የማይተኩትን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ከማጣቷና የዕድገት ግሥጋሴዋ ከመገታቱ በተጨማሪ፣ ሥርዓቱ በርካታ አማኞቿ ከሃይማኖት እንዲወጡ ወይም ለሃይማኖታቸው ግዴለሽ እንዲኾኑ ስላደረጋቸው የደረሰባት ጉዳት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ቢኾን ገና ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ነበር ይህችን ቤተ ክርስቲያን ለማዳከም ዓላማ አንግቦ፣ ዕቅድ አውጥቶ መንቀሳቀስ የጀመረው። /የዶክተር አረጋዊ በርሄን መጽሐፍና የሌሎች ግለሰቦችን ምስክርነት መጥቀስ ይቻላል/ ሀገሪቱን እንደተቆጣጠረም፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን በጀት በማገድና በወቅቱ የነበሩትን ፓትርያርክ ከመቀየር ጀምሮ ቁልፍና ወሳኝ የኾኑትን የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅሮች በራሱ ካድሬዎች በማስያዝ ነበር ቤተ ክርስቲያኒቱን በመዳፉ ውስጥ ያስገባት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታምንበትን እንዳትናገር፣ እውነቱን በዐደባባይ እንዳትመሰክር፣ አጥፊዎችን እንዳትገሥጽና እንዳትመክር፣መተኪያ የሌለው የሸምጋይነት ሚናዋንም እንዳትወጣ ከመደረጓም በላይ አስተዳደሯ እንዲዳከም፣ ተደማጭነቷ እንዲጠፋ እንዲያውም ከዚህ አልፎ ያለስሟ ስም፣ ያለግብሯ ግብር እየተሰጣት ጥቂት በማይባሉ የሀገሪቱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ በጠላትነት እንድትፈረጅ አድርጓታል።

ይህ ዘመን በፓትርያርክና በጠቅላይ ሚኒስትር፣ በቀበሌና በደብር ጽ/ቤት ያለው ልዩነት እስኪጠፋብን ድረስ መደበላለቅ የተፈጠረበት ዘመን ነው። “ፖሊስ ጠርቼ አሳስርሃለሁ፤ ደኅንነት አምጥቼ አስገርፍሃለሁ” የሚሉና ራሳቸውም የጦር መሣሪያ የታጠቁ የቤተ ክህነት ሓላፊዎች፣ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች የተፈጠሩበት፣ የቤተ ክህነቱ ቅልብ ወንበዴዎች የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን የመኖሪያ ቤት በሮች እየገነጠሉ፣ መስኮቶችን እየሰበሩ ጳጳሳትን የመደብደብ ሙከራ ሲያደርጉ ከልካይ እንደሌላቸውና ወንጀል ኾኖ እንደማይቆጠርባቸው የታየው በዚሁ ዘመን ነው። ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤዎች እየተገኙ መመሪያ እስኪሰጡ ድረስ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ዐይን ያወጣና ቅጥ ያጣ ጣልቃ ገብነት የተፈጸመውም በዚሁ በእኛው ዘመን ነው።

2ኛ. የአስተዳደር ችግር

ከላይ ከተገለጸው ጋራ ተያይዞ የቤተ ክርስቲያናችን የአስተዳደር ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል። በአሁኑ ጊዜ፥ ጉቦኝነት፣ ዘረፋ፣ምዝበራ፣ ዘረኝነት/ጎጠኝነት፣ አድሏዊነት፣ የአስተዳደሩ ዋና ዋና መገለጫዎቹ ኾነዋል። እነዚህ አስጸያፊ ተግባራት እንደነውር የማይቆጠሩበት ደረጃም ተደርሷል። በቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ መዋቅሮች የተሠገሠጉ አምባገነኖች ለሚፈጽሙት ግፍና ጭቆና ጠያቂ የላቸውም።

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት ችግራቸውን በአግባቡ የሚፈታ የአስተዳደር አካል በማጣታቸው ምክንያት በተረጋጋ መንፈስ አገልግሎት ለመስጠት ካለመቻላቸውም በላይ ለከፍተኛ መጉላላት፣ እንግልትና መከራ ተዳርገዋል። የሕግና የሥርዓት መሠረት የኾነችው ታላቋ ቤተ ክርስቲያን፥ሕገ ወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት የነገሠባት፣ ፍትሕ ርትዕ የተጓደለባት ኾናለች፤ ምእመናኗም በመሪዎቻቸው አባቶች ጳጳሳትና ካህናት እንደዚህ ዘመን ያፈሩበትና የተሸማቀቁበት ጊዜ ታይቶ አይታወቅም፤ በርካቶችም ተስፋ እየቆረጡ እረኛ እንደሌላቸው በጎች እየተቅበዘበዙ ይገኛሉ። በዚህ ምክንያት ከበረቱ ብዙዎች እንደወጡ መረጃዎች እያመላከቱ ነው።

በመሠረቱ አሁን በቤተ ክርስቲያናችን እየታየ ያለው ትርምስ፣ድንገት ዛሬ የተፈጠረ አይደለም። በአጋጣሚ የኾነም አይደለም። ከ30 እና 40 ዓመታት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማዳከም በዕቅድ የተነደፈ ነው እንጅ። ለዓመታት የተዘራው ክፉ ዘር አሁን ለፍሬ ደርሶ ቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ አደጋ እንዲያንዣብባት አድርጓል።

ክፉዉ ዘር ዛሬም እየተዘራ ነው። እጃችንን አጣጥፈን ከተቀመጥን ደግሞ ከ20 እና 30 ዓመታት በኋላ ቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ብቻ ወደ መኾን የማትሸጋገርበት ምክንያት አይኖርም። አንዳንዶቻችን፣ “ቤተ ክርስቲያን እስከ ዓለም ፍጻሜ ትኖራለች፤” ሲባል እንዲሁ በረድኤተ እግዚአብሔር ተጠብቃ ብቻ ይመስለናል። እውነቱ ግን ይህ ብቻ አይደለም። ጉዞዋ በእሳት መካከል ነው። ከሐዋርያት ጅምሮ ብዙ ቅዱሳን ተጋድለውላታል፤ ተሠውተውላታል። ዛሬም ወደፊትም የሚጋደሉላት የሚሠዉላት ያስፈልጓታል። የትላንቶቹ በተጋድሎአቸው ለእኛ አስረክበዋል። ዛሬ ተራው የኛ ነው። ነገ ደግሞ እኛ የምናስረክባቸው ይኾናል። ምንድን ነው የምናስረክባቸው? የሚለው ጥያቄ ግን መመለስ ይኖርበታል – ቁጭት!!

በአሁኑ ጊዜ ወደ 195 ገደማ ከሚኾኑት የዓለም ሀገሮች ወስጥ ከ45 ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ብዛት ያላቸው ሀገሮች ከ30 አይበልጡም፡፡ ከ45 ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ አማኞች ያሏት ቤተ ክርስቲያናችን፣ ከቀሪዎቹ 165 ሀገሮች የበለጠ የሕዝብ ብዛት ያላት ተቋም ናት ማለት ነው፡፡ ከእኒህም ውስጥ፣ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ካህናት፣ በመንፈሳዊውም በዓለማዊውም ዕውቀት የተራቀቁና የመጠቁ ካህናትና ምእመናን፣ በትክክለኛው መንገድ የሚመራቸው እስካገኙ ድረስ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን ብቻ ሳይኾን ሕይወታቸውን ጭምር ለመስጠት የማይሰስቱ ወጣቶች እንዲሁም ዘርዝረን የማንጨርሰው እምቅ አቅምና ሀብት ያላት ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ኾኖም ምንም እንደሌላትና ምንም ማድረግ እንደማትችል ተቆጥራ ማንም እንደፈለገ የሚፈነጭባት፣ የትንሹም የትልቁም መዘባበቻ ኾና ከማየት የበለጠ ምን የሚያንገበግብ ነገር ይኖራል?

በስደት በምንኖርበት ሀገር እንኳን፣ አውራ ጎዳናዎች እየተዘጉ በሞተረኛ ፖሊሶች እየታጀብን ሃይማኖታዊ በዓላትን በነጻነት ለማክበር መቻላችንን አስበን፣ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶቻችን በገዛ ሀገራቸው በየከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በሃይማኖታቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን ወከባና እንግልት ስንሰማ ካልተቆጨን ምን ሊያስቆጨን ይችላል?በማይመች ኹኔታ ውስጥ እያለፍን እንድናንቀላፋ አዚም ያደረገብን ማን ነው? ለመሆኑ እኛ የዚህ ዘመን ካህናት የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ምን ያህል ያሳስበናል?ካሳሰበን በተግባር ምን አድርገናል? ስለ ቤተ ክርስቲያን ስንል ምን ያህል መከራ ተቀብለናል? ስንት ጊዜስ ታግሠናል?

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ ጥቂት አባቶችና ወንድሞች፣ በተናጠል ከሚያደርጉት ትግል እንዲሁም አልፎ አልፎ ምእመናን በተለይም ወጣቶች በተለያየ ጊዜ ለሃይማኖታቸው ካደረጓቸው ተጋድሎዎች ውጭ፣ እኛ ካህናቱ ለብዙ ዓመታት አንቀላፍተናል። የእኛ ማንቀላፋት ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችንን በእጅጉ ጎድቷታል፤ መከራዋንም አብዝቶታል። መነሣት ያለብን ማንቀላፋታችንን በማመን ነው። ለችግሩ መባባስ በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የእያንዳንዳችን አስተዋፅኦ አለበት። በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተለያየ ጊዜ የመከራ ዶፍ ሲወርድ እጃችንን አጣጥፈን በመቀመጥ፣ ለፖለቲካ ኃይሎች በማጎብደድ፣ መንግሥት በቤተ ክርስቲያናችን ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ በመጋበዝ፣ በመፍቀድና በመተባበር፣ በጎጥ በመከፋፈል፣ በጉቦ ቅብብል፣ በምዝበራውና በዘረፋው  በመሳተፍ፣…ወዘተ የብዙዎቻችን እጅ እንዳለበት መካድ አንችልም።

ታላቋ ቤተ ክርስቲያናችን፣ በዚህ ዘመን መገኘት በሚገባት ክብርና ልዕልና እንድትገኝ እኛ ካህናቱ ምን እናድርግ? ያልሠራነው ነገር ከመብዛቱ የተነሣ ለዚህ ጥያቄ የሚኖረን መልስ ብዙ እንደሚኾን አያጠራጥርም። ነገር ግን በእኛ አሳብ፣ ከዚህ በታች የተቀመጡትን ሁለት ጉዳዮች ማከናወን ከቻልን፣ ከእግዚአብሔር ፍርድና ከታሪክ ወቀሳ እንድናለን ብለን እናምናለን።

የካህናት አንድነቱ ዓላማዎች፤

1ኛ. ቤተ ክርስቲያናችንን ከፖለቲካ ኃይሎችና ከማንኛውም አካል ተጽዕኖ ነጻ እንድትወጣ፣ ወደ ቀደመ ክብሯና ልዕልናዋ እንድትመለስ፣ ሃይማኖቷንም በነጻነት እንድታስፋፋ ማስቻል፤ እንዲሁም ከፍተኛውን የሀገሪቱን የሕዝብ ቁጥር በሃይማኖት የምትመራ እንደመኾኗ መጠን በሀገር ጉዳይ ላይ ሊኖራት የሚገባው ተደማጭነት እንዲመለስ፣ የሰላም የፍቅር የአንድነት ሰባኪነትዋ፣ ሸምጋይነትዋና አስታራቂነትዋ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መታገል፤

2ኛ. አስተዳደሯን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ ሃይማኖታዊ ድንጋጌዎችና ቀኖናዎች ብቻ እንድትመራ፤ ሀብቷን፣ ንብረቷንና ቅርሷን ከምዝበራ እንድትጠብቅ እገዛ ማድረግ፤

3ኛ. ለወደፊቱም በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ከማንኛውም አካል የሚመጣውን ጫና እና በደል በመመከት ለነጻነቷ፣ ለመብቷና ለጥቅሟ ጥብቅና መቆም ናቸው፡፡

አባልነት፦ የሃይማኖት ሕጸጽ የሌለባቸው፣ የዘረኝነት/የጎጠኝነት በሽታ ያልተጠናወታቸው ወይም ከበሽታው የተፈወሱ፣ ከግል ጥቅማቸው ይልቅ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ የሚያስቀድሙ፣ አቅማቸው በሚፈቅደው ሁሉ ሃይማኖታዊ ተጋድሎ ለማድረግና መሥዋዕት ለመክፈል ቁርጠኝነት ያላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ያለው የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር መለያየት ሳይገድባቸው በመላው ዓለም የሚገኙ ሊቃውንት፣ መነኮሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ ሰባክያነ ወንጌል ሁሉ የማኅበረ ካህናቱ አባል መኾን ይችላሉ።

አንድነቱ ለምን ያስፈልገናል

ወደ መፍትሔው መድረስ የምንችለው ችግሩን በግልጽ ተነጋግረን ስንተማመን ብቻ ነው። በተለይ ባለፉት ጥቂት ዐሠርት ዓመታት ውስጥ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት በጎጥና በሌሎች ምክንያቶች ከዓለማውያን በከፋ ኹኔታ ተከፋፍለን ብዙ ሽኩቻ አሳልፈናል።መተማመን ጎድሎናል፤ ተራርቀናል፤ ተገፋፍተናል፤ ተቆሳስለናል፤ የኛ ፍቅር መጉደል እኛን ራሳችንንም ጎድቶናል፤ ቤተ ክርስቲያናችንንም ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ይገኛል። ከሃይማኖት ቤተሰቦች የማይጠበቅ ይህን ክፉ ባህል በመተው አንድ ኾነን ለቤተ ክርስቲያናችን በጋራ የምንቆምበት፣ ለሌሎች የምናስተምረውን ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት እኛም የምንተገብርበትና አስደናቂ ለውጥ የምናመጣበት ወሳኝ ጊዜ ላይ በመድረሳችን አንድነቱ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ ኾኗል።

ብዙዎቻችን የቤተ ክርስቲያናችንን ችግር ሌላ አካል እንዲፈታልን እንጠብቃለን። እውነታው ግን ከእኛ ውጭ ማንም ሊፈታልን የማይችል መኾኑ ነው። እኛም ብንኾን አንድነት ከሌለን ልንፈታው አንችልም። አንድነት ሲኖረን እግዚአብሔር ይሰማናል፤ መንግሥት ተገዶም ቢኾን ያደምጠናል፤ ተቋማት ያከብሩናል። ካህናት ለቤተ ክርስቲያኒቱ የጀርባ አጥንት/ከእኛ በላይ ላሉት ሊቃነ ጳጳሳት ጉልበት፣ ከእኛ በታች ላሉት ምእመናን መሪ/ እንደመኾናችን መጠን እኛ በአንድነት መንቀሳቀስ ከቻልን፥ ቅዱስ ሲኖዶሱ የሲኖዶስነት ሚናውን በነጻነት እንዲወጣ፣ ፓትርያርኩ የፓትርያርክነት ሓላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲተገብሩ፣ በየደረጃው ያሉ የቤተ ክህነት ሓላፊዎች ለሁለት ጌቶች ከመገዛት ተላቅቀው የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልእኮ ብቻ የሚፈጽሙ እንዲኾኑ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ መፍጠር እንችላለን።

እኛ አንድ መኾን ከቻልን በአባትነት፣ በእረኝነት የምንመራቸውን ምእመናንን ወደ አንድነት ማምጣቱ ከባድ አይኾንም። የካህናቱና የምእመናኑ አንድነት ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋራ ተደምሮ የቤተ ክርስቲያናችንን ሉዓላዊነትና ነጻነት ይመልሳል፤ ያስከብራል።መንግሥት አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደር እንዲታቀብና ከቤተ ክርስቲያናችን ላይ እጁን እንዲያነሣ ይገደዳል። ካህናቱ ጥቃቅን የልዩነት ምክንያቶችን አስወግደን፣ ከእንቅልፋችን ነቅተን፣ ግዴለሽነታችንንና ምንደኝነታችንን አሽቀንጥረን ጥለን በአንድነት መንቀሳቀስ ከቻልን ይህችን ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ማንም በቀላሉ ሊተነኩሳትና ሊገዳደራት ወደማይችልበት ደረጃ እናደርሳታለን።

መቼም ቢኾን መዘንጋት የሌለብን ነገር ቢኖር፣ በዚህ ዘመን የምንፈራው፣ የምንከበረው፣ የምንደመጠው፣ ሃይማኖታዊ መብታችንን ማስጠበቅና የምንፈልገውን ለውጥ ለማምጣት የምንችለው ብዙ ኾነን አንድ ስንኾን ብቻ መኾኑን ነው።

እንዴት ወደ አንድነት መምጣት እንችላለን

ይህ የካህናት አንድነት ጅምሩን በሰሜን አሜሪካ ያድርግ እንጅ በሒደት በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትን ሁሉ በአባልነት ለማካተት ዕቅድ ይዞ በከፍተኛ ኹኔታ እየተንቀሳቀሰ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ በሺሕ የሚቆጠሩ ካህናትን እንዴት አድርጎ ወደ አንድነት ማምጣት ይቻላል? በማለት የሚተይቁ አሉ፡፡ ጉዳዩ ከባድ ቢመስልም በቀላሉና በአጭር ጊዜ ሊተገበር የሚችል መኾኑን በምሳሌ ማሳየት እንችላለን።

ለምሳሌ፦ ከኢትዮጵያ ውጭ 200 የሚኾኑ አጥቢያዎች አሉ ብንልና በእያንዳንዱ አጥቢያ በትንሹ በአማካይ 3 አገልጋዮችን መመልመል ቢቻል ከኢትዮጵያ ውጭ በአንድ ጊዜ ከ600 በላይ ካህናትን የዚህ ማኅበር አባላት ማድረግ ይቻላል ማለት ነው። ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ ለምሳሌ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ወደ 130 ገደማ የሚኾኑ አጥቢያዎች አሉ። በእያንዳንዱ አጥቢያ በትንሹ 10 ካህናትን መመልመል ቢቻል በአንድ ጊዜ 1300 ካህናትን ወደ አንድነቱ ማምጣት ይቻላል ማለት ነው። ከአዲስ አበባ ውጭ የሚገኙ አጥቢያዎችንም በተመሳሳይ መንገድ በመሔድ በሺሕ የሚቆጠሩ ካህናትን ወደዚህ አንድነት ማምጣት ይቻላል ብለን በጽኑዕ እናምናለን። ዘመኑ ደግሞ ለዚህ የተመቸ ነው። ማኅበራዊ መገናኛዎቹ በአንድ ጊዜ ብዙዎችን መድረስ ያስችላሉ።

ይህ ማኅበረ ካህናት ነገ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የማኅበራዊ መገናኛ ተከታዮች እንደሚኖሩት አንጠራጠርም። ይህ ስሌት ተግባራዊ መኾን የሚችለው ግን የካህናት አንድነቱን ዓላማና ጥቅም የተረዳን ሁላችንም በመላው ዓለም ለሚገኙ፣ ለምናውቃቸውና ለምንቀርባቸው ካህናት ሁሉ በትጋት ማስረዳትና መቀስቀስ ስንችል ብቻ ነው። ቆጭቶናል ብለን ከተነሣን በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን የቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳይ ማስቀደም ይገባናል። ሁሉም ካህናት ወደዚህ አንድነት ይመጣሉ። የሚመጡበት ጊዜ ግን የተለያየ መኾኑ የሚጠበቅ ነው።

እንችላለን የሚለው እምነት ጎድሎናል፡፡ ብዙዎቻችን፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ችግር፥ የማይገፋ ተራራ፣ የማይሻገሩት ጎርፍ፣ የማይነጋ ጨለማ አድርገን ወስደነዋል። ሊፈታ የማይችል ነው ብለን ደምድመናል። በእኛ አቅም ልናደርገው የምንችለው ምንም ነገር የለም ብለን ተስፋ ቆርጠናል። የቅዱስ ሲኖዶስ ሰብሳቢና የቤተ ክርስቲያናችን ርእሰ አበው የኾኑት ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች አንዱ ስለኾነው አስተዳደራዊ ብልሽት፣ ስለተንሰራፋው ግልጽ ዘረፋ፣ ጉቦኝነትና ሌብነት ተጠይቀው ሲመልሱ፣ “ከአንበሳ መንጋጋ ሥጋ የማውጣት ያህል ነው”፤ “ምናልባት ቀጣዩ ትውልድ ይቀርፈው ይኾናል“ …ወዘተ በማለት ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል አስከፊ ኹኔታ ውስጥ እንዳለች ብቻ ሳይኾን ከአዘቅቱ መውጣት የማትችል መኾኗንም ጭምር ሊያሳዩን ሞክረዋል።

በርግጥ ይህ ለብዞዎች ተስፋ አስቆራጭ ቢኾን ሊያስደንቅ አይችልም፤ ምክንያቱም ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ብሏልና፤ የሰውነትህ መብራቱ ዐይንህ ነው፥ዐይንህ ብሩህ ቢኾን ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይኾናል። ዐይንህ ግን ታማሚ ቢኾን ሰውነትህ ሁሉ ጨለማ ይኾናል። በአንተ ላይ ያለው ብርሃን ጨለማ ከኾነጨለማህ እንዴት ይበዛ!” /ማቴ.6፥22/

እንግዲህ እናስተውል፤ ዐይን ማለት ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጅምሮ በየደረጃው የምንገኝ ውሉደ ክህነት ነን። አዕይንተ እግዚአብሔር ተብለን የምንጠራ መኾናችንን ልብ ይሏል። እኛ፣ ችግር መፍታት አንችልም፤ ብለን ተቀመጥን ማለት፣ የዓለም ብርሃን መኾን የሚገባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በድቅድቅ ጨለማ እንድትጓዝ ፈረድንባት ማለት ነው። አሁን ጥያቄው፣ሁላችንም ከዚህ ጨለማ እንዴት እንውጣ የሚለው ነው።

መፍትሔው፣ የጎደለንን “እንችላለን” የሚለውን እምነት ማምጣት ነው። ችግራችንን ራሳችን እንፈታዋለን፤ በዘመናችን የሚታየውን ክፉ ታሪክ መለወጥ ይገባናል ደግሞም መለወጥ እንችላለን ብለን ማመን ነው። እንኳን እኛ፣ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ የምናደርገው ሃይማኖተኞቹ አይደለንም፣ ዓለማውያን እንኳን፣ “እንችላለን” ብለው በአንድነት በመነሣታቸው ብዙ ነገር ለመለወጥ እንደ ቻሉ በርካታ ታሪኮችን መጥቀስ ይቻላል። በቅርቡ እንኳን የሀገራችን ርእሰ መንግሥት ከሥልጣን እንዲወርዱ ያስገደዳቸው፣ “እንችላለን” ብለው የተነሡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተቀናጅተው ባደረጉት ትግል እንደኾነ መዘንጋት አይገባንም። ስለዚህ ከእኛ አቅም በላይ የኾነ ችግር የለንም።እንዲያውም ሙሉ አቅማችንን መጠቀም ከቻልን የእኛን ብቻ ሳይኾን የሌሎችን ችግር መፍታት እንደምንችል ማመን ይገባናል።

ምስጋና

በመጨረሻም፣ በተለያዩ የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች የምትኖሩ ካህናት፣ ከቤተ ክርስቲያናችን በላይ የሚበልጥብን ምንም ነገር የለም፤ በማለት ከቤተሰዎቻችሁ ተለይታችሁ፣ ሥራችሁን ትታችሁ፣ ብዙ ገንዘብ አውጥታችሁ፣ እስከ ግማሽ ቀን የሚደርስ የአየር ላይ ጉዞ አድርጋችሁ ወደ ሲያትል ከተማ መምጣታችሁ ለሃይማኖት መቅናት ማለት እንዴት እንደኾነ፣ለቤተ ክርስቲያን መጨነቅ ማለት ምን ማለት እንደኾነ፣ ቆራጥነታችሁንና መንፈሳዊ ወኔያችሁን በቃል ሳይኾን በተግባር ስላሳያችሁን፣ መሥዋዕትነት እንዴት እንደሚከፈል ስላስተማራችሁን ደግመን ደጋግመን እናመሰግናችኋለን! ይህ ቁርጠኝነታችሁ ለሃይማኖታችሁ ስትሉ ወደ የትኛውም ቦታ ለመሔድና ማንኛውንም መሥዋዕት ለመክፈል የተዘጋጃችሁ መንፈሳውያን አርበኞች መኾናችሁን የሚመሰክር፣ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች መኾናችሁን የሚያረጋግጥና በዓለም ላይ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ሁሉ በመልካም አርኣያነቱ የሚጠቀስ በመኾኑ መንፈሳዊ ኩራትና ደስታ ሊሰማችሁ ይገባል።

በሲያትል ከተማ የምትገኙ ካህናትም፣ ዓላማውን ከማመንጨት ጀምሮ ጉባኤው የተሳካ እንዲኾን ከአንድ ወር በላይ ለሚኾን ጊዜ ሥራችሁንና ትምህርታችሁን ሳይቀር እየተዋችሁ የስልክና የአካል ስብሰባዎችን በማድረግ፣ ሓላፊነቶችን በመከፋፈል፣ ገንዘባችሁን፣ ጉልበታችሁንና ጊዜያችሁን መሥዋዕት አድርጋችሁ ያማረ የሠመረ የምሥረታ ጉባኤ ስላዘጋጃችሁ ምስጋና ይገባችኋል።

በአጠቃላይ ይህ ጉባኤ የተሳካ እንዲኾን በሩቅም በቅርብም ኾናችሁ ለተባበራችሁ፣ በጎ አሳባችሁን ለገለጻችሁ፣ ለጸለያችሁ ሁሉ ምስጋናችን ይድረሳችሁ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር                                   

ሚያዝያ 25 ቀን 2010 ዓ.ም.(May 03, 2018)

የሲያትል ማኅበረ ካህናት

ሲያትል ዋሽንግተን

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s