“ሰው እየሳቀ መሞት እንደሚችል አሳያችኋለሁ ነበር ያልኳቸው” አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ

BBC Amharic:  በሽብርተኝነት የተፈረጀው የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ዋና ፀሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በልዩ ይቅርታ እንደሚፈቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቅዳሜ እለት መግለፁን ተከትሎ ከትንናት ሰኞ ጀምሮ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው መፈታታቸውን ሲጠብቁ ቆይተው ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ተለቀዋል።

በቤተሰባቸው ቤት ከቅዳሜ ጀምረው ሲጠባበቁ ለነበሩት ወዳጆቻቸው ባደረጉት ንግግር አቶ አንዳርጋቸው ”እኔ ተፈትቻለሁ ኢትዮጵያ ግን ያልተፈቱ ብዙ ችግሮች አሉባት” ብለዋል።

ከእስር ተፈተው ቤታቸው ሲደርሱ የተመለከቱት ነገር ያልጠበቁት እንደሆነ የተናገሩት አቶ አንዳርጋቸው። “ምንም መረጃ ባይኖረኝም ኢትዮጵያዊያን እኔን ለማስፈታት ጥረት እንደሚያደርጉ ይሰማኝ ነበር” ብለዋል።

ለዚህ ቀን መምጣት ለደከሙ ለሁሉም ሰዎች ከፍተኛ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ገብቶበት ካለው አስቸጋሪ ሁኔታ አንፃር፤ እንዲህ አይነት ሃገር ከማየት ፍርድ ቤታችሁ የወሰነውን የሞት ቅጣት ተግባራዊ አድርጉ” በማለት ለመርማሪዎች መናገራቸውን ገልፀዋል።

ከዚህ በፊት በቴሌቪዥን ተቆራርጦ ነው የቀረበው ያሉትን ምስል እንዳዩት የተናገሩት አቶ አንዳርጋቸው “ሰው እየሳቀ መሞት እንደሚችል አሳያችኋለሁ ነበር ያልኳቸው፤ ነገር ግን ቆራርጠው ነው ያቀረቡት።”

ጨምረውም “ፍቱኝ ብዬ አልጠይቃችሁም አብሬያችሁ የሰራሁበትን ጊዜ እንደውለታ ቆጥራችሁ የሞት ፍርዱን ተግባራዊ አድርጉ ብዬ ጠይቄያቸዋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርግ የቆየው ሪፕሪቭ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም እንዳለው አቶ አንዳርጋቸው ለንደን ከሚገኙት የህይወት አጋራቸው የሚ ኃይለማሪያም ጋር ከአራት ዓመት በኋላ ለአጭር ጊዜ በስልክ ተነጋግረዋል።

የሪፕራይቭ ዳይሬክተር ማያ ፎአ ስለአንዳርጋቸው መፈታት በሰጡት አስተያየት “ቤተሰቡ፣ ልጆቹና ደጋፊዎቹ የሚደሰቱበት አስደሳች ዜና ነው። በቅርቡም ወደ ለንደን መጥቶ ለረጅም ጊዜ ተለይቷቸው የቆዩትን ልጆቹን ያገኛቸዋል ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ” ብለዋል።

ሰኞ ጠዋት የእንግሊዝ ኤምባሲ መኪኖች በማረሚያ ቤት አካባቢ ተገኝተው ነበር፤ የአቶ አንዳርጋቸው እህት በስፍራው ከኤምባሲ ሰዎች ጋር የነበረች ሲሆን ለቤተሰቦቿ ደውላ ማለዳ እንዳገኘችውና ወደቤት እንደሚመጣ ነግራቸው ነበር።

ከሰኞ እለት ጀምሮ አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ የሚገኘው የቤተሰቦቹ ቤትና አካባቢው በመፈታቱ የተሰማቸውን ደስታ በሚገልጡ መልዕክቶችና በፎቶዎቹ አሸብርቆ ውሏል።

የአንዳርጋቸው ደጋፊዎች የእርሱን ምስል የታተመበት ቲሸርት ለብሰው በአካባቢው ተገኝተው ሲጨፍሩ እና ደስታቸውን ሲገልጡ እንደነበር ተመልክተናል።

በለንደን የምትኖረው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የህይወት አጋር ወ/ሮ የምስራች ኃይለማርያም (የሚ) በባለቤቷ ሊፈታ በመሆኑ እጅግ መደሰቷን እና እስካሁንም የተፈጠረውን እንዳላመነች ለቢቢሲ ተናግራለች።

”ከአንድ ሰው ህይወት 4 አመት የሚሆነውን በእስር ማሳለፍ ምን አይነት ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ይከብዳል። ነገር ግን ባለቤቴ ከዚህ በኋላ ወደ ፀሃፊነት ያዘነብላል ብዬ አስባለሁ” ትላለች ወ/ሮ የሚ።

ለልጆቼ ዜናውን ስትነግራቸው በደስታ አልቅሰው ነበር የምትለው የሚ፤ እስካሁን አንዳርጋቸውን ለማነጋገር እየጠበቁ እንደሆነ ገልጻለች።

ባለቤቷ በሽብርተኝነት በተፈረጀው ግንቦት ሰባት ድርጅት ስለነበረው ኃላፊነት እና ስለቤተሰቡ ሁኔታ የተጠየቀችው የሚ፤ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከመንግሥት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ይታወቃል፤ ስለዚህ ሁሌም ቢሆን የሆነ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል እገምት ነበር ብላለች።

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ቀን ጀምሮ እንዲለቀቁ ሲወተውት የነበረው ሪፕራይቭ የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ዋና ኮሚሽን የሆኑት አዳም ስሚዝ እስካሁን ድረስ አለመለቀቃቸውን ገልጾ ዛሬ ብሔራዊ በዓል ስለሆነ ላይለቀቁ ይችላሉ ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

አክለውም የእንግሊዝ ኤምባሲ አስቸኳይ የጉዞ ሰነዶችን ሊያዘጋጅ ይገባል፤ አንዳርጋቸውም አባቱን ማየት ሊፈልግ ይችላል ብለዋል።

የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ አንዳርጋቸው፣ በሽብር ወንጀል ሁለት ጊዜ ክስ ተመሥርቶባቸው በዕድሜ ልክና በሞት እንዲቀጡ እንደተፈረደባቸው ይታወሳል።

Grey line
  • አቶ አንዳርጋቸው የተወለዱትና ያደጉት አዲስ አበባ ነው። የቀለም ትምህርት ከቀመሱበት ተፈሪ መኮንን ሲወጡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኤሌክትሪክ ምህንድስና ማጥናት ጀመሩ። በዩኒቨርስቲ ቆይታቸውም በተማሪዎች ንቅናቄ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ።
  • የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ወድቆ ደርግ ስልጣኑን ሲይዝ ኢህአፓን ተቀላቀሉ። በወቅቱ የኢህአፓ አባል የነበሩ ወጣቶች እንደሚያደርጉት በፓርቲው በህብዕ አደረጃጀት ውስጥ በመሆን የደርግ መንግሥትን መታገል ጀመሩ።
  • አቶ አንዳርጋቸው የደርግ መንግሥት የቀይ ሽብር አውጆ በርካታ ወጣቶች ላይ እርምጃ ሲወስድ ወንድማቸውን አጥተዋል። ያኔ አንዳርጋቸው ሀገር ጥለው ተሰደዱ። በወቅቱ ከኢህአፓ ጋርም በነበራቸው የርዕዮተ ዓለም ልዩነትም ከፓርቲው ተለይተው በሱዳን በኩል እንግሊዝ በመግባት ጥገኝነት ጠየቁ። በኋላም ዜግነት አግኝተዋል።
  • በ1983 የደርግ ከስልጣን ሲወገድ አዲስ የተመሰረተውን መንግሥት ለማገዝ ወደ ሀገር ተመለሱ። ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ ተመልሰው ወደ እንግሊዝ ሄዱ።
  • በጥር ወር 1997 ዓ.ም እንደገና አንዳርጋቸው ጽጌ አዲስ አበባ ገቡ። የመጡት በምርጫው ቅንጅትን ለመርዳት ነበር፤ ወዲያውኑም የቀስተ ዳመና አባል ኾነው የፓርቲ ሥራ ጀመሩ።
  • 1997 ሰኔ ወር ላይ አቶ አንዳርጋቸው በዝዋይ እስር ቤት በሺህዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ታስረው ለሁለት ሳምንታት ቆዩ። ከእስር ቤት እንደወጡ ሐምሌ 1997 ወደ እንግሊዝ ተመለሱ።
  • በግንቦት 2000 ዓ.ም ከዶክተር ብርሃኑ ነጋ ጋር በመሆን ግንቦት ሰባት ንቅናቄን መሰረቱ። አንዳርጋቸው የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ ሆነው ተመርጠው ነበር።
  • ሚያዚያ 2001 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥት “በግንቦት ሰባት የተቀነባበረ መፈንቅለ መንግሥት አከሸፍኩ” ሲል ገለጸ። ግንቦት ሰባትንም አሸባሪ ሲል ፈረጀ። በዛው ዓመት አቶ አንዳርጋአው ጽጌ በሌሉበት የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው።
  • ሰኔ 2006 ዓ.ም አንዳርጋቸው የግንቦት ሰባትን ሥራ ለማካሄድ ዱባይ ገቡ። ከዱባይ ተነስቶ በየመን በኩል ወደ ኤርትራ ሊጓዙ ሲሉ ሰንዓ ላይ በየመን የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው ለኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፈው ተሰጡ።
  • በ2007 የእንግሊዝ መንግሥት አንዳርጋቸው ከእስር እንዲፈታ የኢትዮጵያ መንግሥትን መጠየቅ ጀመረ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s