“መደመሩን” ከቀኝ ጅቦች ለማዳን – ፀረ-ቅልበሳ ኃይሎችን ማደራጀት – B.K

 

1966 ዓም ተጠናክሮ የመጣው የለውጥ ማዕበል ቤተመንግስቱን ሳይቀር አንቀጠቀጠ። ንጉሡ የሕዝቡን ተቃውሞ መቋቋም አቃታቸው። በዚህን ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስቴር አክሊሉ ሃብተወልድ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀቁ። ይህ ለመጀመርያ ጊዜ የተደረገ በሳል የፖለቲካ ርምጃ ነበር። ንጉሡ የሕዝቡን ንቅናቄ በጥገናዊ ለውጥ ለማስተካከል ሞክረው ልጅ እንዳልካቸው መኮንንን ጠቅላይ ሚኒስቴር አድርገው ሾሙ። ሕዝቡ አሁንም ተቃውሞውን ገፋበት። የንጉሡ አስተዳደርር ለፖለቲካ ፓርቲ እውቅና የማይሰጥ ስለነበር ሃገሪቱ ጠንካራ ድርጅት አልነበራትም። በወቅቱ የተደራጀውና የታጠቀው ኃይል ወታደሩ ስለነበር ሥልጣኑን በቀላሉ ቀርጨም አደረገ። ይህ ኃይል “የጊዜአዊ ወታደራዊ አስተዳደርር ደርግ” ይባላል። ወድያውኑ በአስቸኳይ የተደራጁት ኢሕአፓና መኢሶን ሥልጣኑን አንደኛው በትጥቅ ትግል ሌላኛው ደግሞ በሠላማዊ መንገድ ለመንጠቅ ትግላቸውን በየፊናው ተያያዙት። ኢሕአፓና መኢሶን በርዕዮተ ዓለም የበሰሉ ለዴሞክራሲ ሲሉ ደርግን ለማስወገድ በቆራጥነት የተሰለፉ የምሁራን ድርጅት ነበሩ። እነዚህ ቡድኖች አንዳች የግል ጥቅም አልነበራቸውም። በብስለት መራመድ ባለመቻሉ ምክንያት ኢትዮጵያ ይህ እድል ተበላሸባት።

ደርግ በራሱ ድክመት ሲገረሰስ እሚኒልክ ቤተመንግሥት መግባት የቻለው ባለጊዜው ወያኔ–ኢሕአዴግ ኢሕአፓና መኢሶንን ይቅርና የደርግ ያህል የርዕዮተ ዓለም እውቀት አልነበረውም። አውራ መሪዎቹ እንደውም አንዳች ፍንካች ኢትዮጵያዊነት አልታደሉም። ይኸው አውራ ቡድን ፍላጎቱ የቅርብ ቤተሰቦቹን ማበልጸግና ቢቻል ጨረቃ ላይ ማሳረፍ፣ ቀጥሎም አካባቢውን በልማት ጭላንጭል በመደለል ነዋሪውን የክብሩ ጠባቂ አድርጎ በተስፋ እያማለለ እድሜውን ዘላለማዊ ማድረግ ነበር። ደርግ ሲወድቅ፣ ከታማኝ በየነና ጥቂቶች በቀር፣ ሕዝቡ በቂ ተቃውሞ አላደረገም። አውራው ቡድን አንዳች ተቃውሞ ያላሳየውን ጨዋ ሕዝብ ሥነ–ልቦና እያደር መቆጣጠር በመቻሉ ለሃያ ሰባት ዓመት ደሙን ካለርኅራሄ መጠመጠ፣በርካቶችን አስደደ የሚችለውን ገደለ። ሥርዓቱ በሙስና ያባለጋቸው እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ባለጌ ኃይል አለው። ችግሩ እዚህ ላይ ነው። ልብ በል።

አውራው የማፍያ ቡድን ሃያ ሰባት አመት በስርቆት ሲገዛ ጉምሩኩን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን፣ የፍተሻ ኬላዎችን፣ ወደብ ላይ ሠራተኞችን፣ ደህንነትና ወታደራዊ እና ዘርዝሬ የማልጨርሰው ሌሎች ባለፉት መንግሥታት የተቋቋሙ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሙስና ባለሙያዎችንና ዘራፊ ባለጌዎችን አስቀምጧል። ልብ በሉ እንደ ደርግ ጊዜ አብዮቱን የሚወዱ ካድሬዎች ሳይሆን የተቀመጡት ለዝርፍያ የተዘጋጁ ቦዘኔ መሃይም ሌቦች ናቸው በየወንበሩ ፊጥ ያሉት። እነዚህን ባለጌዎች ማንም በድፍረት መናገር አይችልም። አንዱን ባለጌ መናገር ማለት ሄዶ ሄዶ ወደ ላይ አውራ ሌባውን መድፈር እንደ ማለት ነው። ይህ በደል ያንገሸገሸው ሕዝብ በደሉን አምቆ ሲገዛ ኖረ። ብልግናው ከየቢሮው አልፎ አካባቢውን ሲበክል ብሶት የወለደው ቄሮ፣ ፋኖና ዘርማ የሞት የሽረት ትግል አደረጉ። የነለማ ቡድንን በሳል ሚና ጨምሮ የዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን መምጣት ይህ የሃያ ሰባቱ ዓመት ብሶት የወለደው ነባራዊ ሁኔታ ነው።

ለመሆኑ የቀኝ ጅቦች እነማን ናቸው – በዶክተር አብይ የሚመራውን የመደመሩን ፍልስፍና የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያን አሉ ማለት ይከብዳል። ደርግ ሙስናን እንደ ርዕዮተ ዓለም ስለማያራምድ በጥቅማ ጥቅም የገዛቸው ኃይል አልነበሩትም። ኢሕአዴግ ግን ሙስናውንና ዝርፊያውን የሚያስፋፉ በማፍያው አውራ ቡድኖች የተሾሙ አገልጋዮች አሉት። ሥርዓቱ በንግዱም ይሁን በአስተዳደር ቢሮው በርካታ ተጠቃሚዎችን አፍርቷል። ሌላም ጉዳይ አለ። አስተሳሰብ ያድጋል በመሆኑም የሥርዓቱን አሳፋሪ ጥፋቶች ተገንዝበው ወደ መደመሩ ፍልስፍና ራሳቸውን የመለሱ የኢሕአዴግ አባላትም አይኖሩም አይባልም። ይህንን ሁኔታ ሰው በአንክሮ ሊመዘግበው ይገባል። የቀኝ ጅቦች ማለት አውራው የሙስና ኃይል በዘረጋው የዘረፋና የሌብነት ሥርዓት ተጠቃሚ የሆኑ ዛሬ ከመደመሩ ፍልስፍና ጋር መጓዝ ያቃታቸው የደነገጡ ግለሰቦች ማለት ነው። እነዚህ ፈሪ ግለሰቦች የቅልበሳ ሥራ ለማድረግ ከመሞከርና ግድያ ከመፈጸም አይቦዝኑም።

ሥልጣንን ተገን ያደረጉ ግለሰቦችና አብረዋቸው የሚሠሩት ነጋዴና ሸሪኮች ካላንዳች እፍረት በከፍተኛ ፍጥነት ዝርፊያና ሌብነት ሲፈጽሙ የቆዩት – ሥርዓቱ አንድ ቀን እንደሚወድቅ ያውቁ ስለነበር ነው። አውራ ሌቦቹ ቤተሰቦቻቸውን ወርቅ አልብሰው ወርቅ መኪና ይነዳሉ። በየመሥሪያ ቤቱ የተጎለቱ ባለጌዎች ዘመዶቻቸውን ሳይቀር አውሮፓና አሜሪካ ልከዋል። አንዳንዱ በህገ ወጥ ዶላር እያሸሸ ለዘመዱ አሜሪካ ውስጥ ቪላ ገዝቷል። ይህን ያህል ነው ኢትዮጵያ የተመዘበረችው። የዝርፍያው ፖለቲካ በፈጠረው ችግር ምክንያት ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ መብላት፣ መጠጣት እማይችልበት ደረጃ ደርሰው ሳለ ነው የብዙ ታጋዮች ውጤት የሆነው የመደመሩ ፍልስፍና ድንገት የበራው። ብርሃኑ ባለጌዎችን አሳውሯል። አውራ ሌቦቹም ከፍርሃት የተነሳ በተወሰነ አካባቢ ለመመሽግ ተገደዱ።

ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ “የቀን ጅቦች” ያሏቸው ቀልባሾች አስቀድመው የተደራጁ የማፍያ ቡድኖች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ሌቦች በርካታ ገንዘቦች፣ ትጥቆች፣ ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎችና በየቦታው በጥቅም የገዟቸው አጋዥ ባለጌዎችን አቅፈዋል። ይህ የቅልበሳ ቡድን በወታደራዊ ሙያ የሠለጠኑ ግለሰቦችንና መቺ ኃይሎችንም አደራጅቷል። ዛሬ አይደለም የተደራጀው ገና አስቀድሞ “ነገም ሌላ ቀን ነው – ሳንቀደም እንቀድማለን” ብሎ ነው የተሰባሰበው። ፈላስፋው ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይላቸው በመደመሩ ዙርያ የተሰለፈው ሕዝብና ፍቅር ነው። ታላቁ መሪያችን ፍርሃታቸው ደግሞ ሕዝቡ የቀመሰው ፍቅርና ሕብረት እንዳይዛነፍ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከፍ ያለችው ኢትዮጵያ ዳግም እንዳትቆዝም ነው። ትላንት መስቀል አደባባይ ላይ ቦንብ ያፈነዱ ዛሬ ደግሞ የሕዝብ ኃብት የሆኑትን ታላቁን ምሁር ኢንጂነር ስመኘው በቀለን የገደሉት የቀን ጅቦች ጥቃታቸውን በዚህ ያቆማሉ ማለት አይደለም። ስለሆነም፤

፩. ዶክተር አብይ በሂደት በየቢሮው የተሰገሰጉትን ሌቦች ማጥራት አለባቸው። በርካታ የተማረ ኃይል ስለሚኖር ሌቦቹ መሥፈርቱን ጠብቆ በሚቀጠሩ የሠራተኛ ኃይሎች ሊተኩ ይገባል። ይህ ድልድል እላይ በየደረጃው እስከተቀመጡት ባለስልጣኖች ዘንድ ሊደርስ ይገባል። እርሳቸው ይህን ሲያደርጉ የቀኝ ጅቦቹ በአስተዳደሩ ላይ ጥፋቶችን ሊፈጽሙ ስለሚችሉ በየቢሮው ያሉት አገልጋዮች ይህን ክፋት ሊቆጣጠሩ ይገባል።

፪. ሌላው ትልቁ ሥራ የሕዝብ ነው። ሕዝቡ በየቀበሌው በአዋቂዎች የሚመራ “የቀኝ ጅቦችን ውር ውር የሚቆጣጠር፣ “የመደመሩ ፍልስፍና አራማጆችና ፀረ–ቅልበሳ ኮሚቴ” ሊያቋቁሙ ይገባል። ይህ ትልቅ ጉዳይ እንደውም ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቢታገዝ አባላቱ ከወንበሩ ይልቅ ለሃገር ደህንነት ቅድሚያ መስጠታቸውን ያሳያል። ሁሉም ነገር በስሜት ሳይሆን በጥበብ የሚራመድ ሊሆን ይገባል። ስሜት ብቻዋን ተሸናፊ ታደርጋለች። ሕዝቡ በጥበብ ከተደራጀ ዶክተር አብይ እንዳሉት ጸጉረ ለውጦችን መለየትና እንቅስቃሴአቸውን በአንክሮ መከታተል ይችላል። ፖሊስ በሕዝብ ተሳትፎ እየታገዘ እንደ መርካቶና ፒያሳ ያሉትን ሕዝብ የሚበዛባቸውን ቦታዎች ሠላም ለመጠበቅ በሙያ የታገዘ ሥራ ሊከውን ይችላል።

፫. የቀኝ ጅቦቹን ማንነት መለየት ዋናው ትኩረት መሆን ይገባል። ይህ በሙያዊ ክህሎት መመራት አለበት። ፖለቲካው ከብርሃን ፍጥነት ቀድሞ ኃብታም ያደረጋቸው ሰዎች ለቀኝ ጅቦቹ ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ። የቀኝ ጅቦች የዝርፊያው መቋረጥ ባስደነገጠው ባለሥልጣንም ሊታገዙ ይችላሉ። ይህን ሁኔታ እንደምን መቆጣጠር እንደሚቻል ምክክር ማድረግ ያስፈልጋል። የቀኝ ጅቦቹ በቂ ገንዘብ፣ ተሽከርካሪዎችና የጦር መሳርያዎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ መገልገያዎች ስለሚኖሯቸው ከከተማ ከተማ መዞር ብቻ ሳይሆን በከፍተኛና ትናንሽ ሆቴሎች ውስጥም ሆነ ምስጢራዊ ቦታዎች እያደሩ ደብዛቸውን መሰወር ይችላሉ። የቀኝ ጅቦቹ የጦር መሳርያዎችንና ቦንቦችን ሊደብቁ ይችላሉ። ሕዝቡ በቡድን በቡድን ተደራጅቶ ፎቶግራፎችን ከማንሳት ጀምሮ የጠረጠርውን በጨዋ ሥርዓት አቁሞ መጥየቅ ይገባል። የቀን ጅቦቹ የሚፈልጉትን እቅድ እምሽት ላይ ሊነድፉ ስለሚችሉ ይህን የመከታተል ልዩ አቅምም ሊገነባ ይገባል። ሕዝቡን መደመሩን ከቅልበሳ ለማዳን ጥበባዊ እቅዶችን ከነደፈና በአመክኖዖ ከተመራ የቀኝ ጅቦቹ ሊጋለጡ ይችላሉ።

፬. ሕዝብ ዘራፊዎቹና ሌቦቹ የቀደዱትን የተንኮል ቦይ ተከትሎ አብሮ መፍሰስ የለበትም። ተንኮስ አድርገው ሕዝብ በስሜት ተነሳስቶ ጎጂ ነገሮች እንዲፈጽም ነው ፍላጎታቸው። የመደመሩ ፍልስፍና እንዲቀለበስ የቀኝ ጅቦቹ ሠላምን ለማደፍረስ በርካታ መላዎችን መንደፍ ይችላሉ። ልምላሜን ለማምጣት እውቀት ባይኖራቸውም እንኳን ድርቀትን ለማስፈን መላን አያጡም። የቀኝ ጅቦቹ አውራ አለቆች አንዳንዶቹ በልዋጭ ልዋጭና የልመና የሠፈር ስለላ ረገድ በቂ ሙያን ያካባቱ አልፎ ተርፎም በባለስልጣን ቤት ዘበኛ ሆኖ ተቀጥሮ በመስራትና ምስጢር በመጥለፍ ሥራ ከማንም በላይ የተካኑ ኋላም ለሃ ሰባት ዓመት “አንድ ላምስት በሚለው ጥርነፋና ከፋፋይ የክልል ፖለቲካ ታግዘው በማጋጨትና በማናቆር ሙያ ህዝብን ምን ያህል እንዳስጨነቁ የሚረሳ አይደለም። እነዚህ አውራ ሌቦች የመደመሩን ፍልስፍና ለማደናቀፍ የክፋት መላ በማውጠንጠን ረገድ አሁንም ቢሆን የማይናቅ እምቅ ችሎታ እንዳላቸው መዘንጋት አያስፈልግም።

የቀን ጅቦቹን ሻጥርና የግድያ ሤራ ማክሸፍ የሚቻለው የእነርሱን የክፋት ሥራዎች ተረድቶ ብሎም በጥበብ በልጦ በመገኘት ንቃትና በጠነከረ ህብረት ብቻ ነው። የቀኝ ጅቦች የሙስናውና ብልግናው ሥርዓት ልጆች ናቸው። ሥርዓቱን ለመመለሰ ቅልበሳ ማድረግ የሞት የሽረት ትግላቸው ነው። ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ የሚከወነው ኢትዮጵያን የማንሳትና ፍቅርን የማጎልበት ቅን ሥራ ለቀኝ ጅቦቹ ምን ያህል ውርደትና እፍረት መሆኑን ለማወቅ አንዳች ምርምር አያስፈልግም። የመደመሩ ፍልስፍና ለቀኝ ጅቦቹም ሆነ ለአውራ ሌቦቹ – በህይወት ሳሉ ሺህ ጊዜ መሞት – ማለት ነው። የቀኝ ጅቦቹ ምንም ነገር ከማድረግ አይመለሱም። ይሁንና ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ አሸንፈው ዳግም የጨለማውን ዘመን መመለስ ከቶ አይችሉም። አርፈው ቢቀመጡ ለነሱም ሆነ ቤተሰቦቻቸው መልካም ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s