ለክቡር የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

July 26 2018

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር

ከዛሬ ነገ ኢትዮጵያ በእርስ በርስ ጦርነት በደም ትጥለቀለቃለች ተብሎ ሕዝብ የተጨነቀባቸዉ ቀናቶቸ ነበሩ፡፡ የአገዛዙ ክፍልም ኢትዮጵያ እንደ ሶርያ ትሆናለች በማለት ሕዝቡን ያስፈራሩት ነበር፡፡ ነገር ግን አንድ ተዓምር ተፈጠረ፡፡ ይህም ለዉጥ የአንድ ብልህ መሪ መፈጠር ነበር፡፡ የሕዝቡ እምነት በአንድ ጊዜ ተቀየረ፡፡ አንድነት፣ ፍቅር፣ ይቅርታ፣ ዴሞክራሲ፣ ሥልጣኔ፣ መደመር፣ እነዚህ የመሳሰሉ ያልታወቁ አዲስ ፍልስፍናዎች በመሆናቸዉ በሕዝቡ ላይ ከዳር እስከ ዳር ብዙ ተስፋና አዲስ ያልነበረ እምነትን ተፈጠረ፡፡ ይህም በሰላምና በትዕግስት የተገኘ ድል ዓለምን አስደነቀዉ፡፡ ወድቆና ተንኮትኩቶ የነበረዉ የኢትዮጵያ ገበና በአንድ ጊዜ ከአድማስ ባሻገር ለሚገዉ ዓለም ጭምር ከአድንቆት በላይ ያልተጠበቁ ተስፋዎችና እምነቶችን ቀሰቀሰ፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ ብቻ ሳይሆን የመላዉ አፍሪካ መብራት ነች የሚል አነጋገርም ከብዙዎች ቦታ ተሰሙ፡፡ የጎሣ ትግልና ጦርነት ቀርቶ ኢትዮጵያ አንድ የምትሆንበት መፍትሔ ተገኘ፡፡ ተአምሩ በዚህ ብቻ አላከተመም፤ የብዙ ሺ ሕይወት የተከፈለበት የኤርትራና የኢትዮጵያ ጦርነት ከሃያ ዐመት ጠላትነት፣ ጥላቻና ጭካኔ በኋላ ካለ አንድ አሰታራቂና ሽማግሌ መሪዎች ተቃቅፈዉና ተሳስመዉ ማየቱ ያላስደነቀዉ ሕዝብ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ብዙ ፖለቲከኞችም መደነቅ ብቻ ሳይሆን ቅናትም የተሰማቸዉ ነበሩ፡፡ ይህ ሁሉ በአጭር ጊዜ የተፈጸመ ለዉጥ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ አቋም ሳይሆን የአንድ ሰዉ ብቻ ትግል ያመጣቸዉ ዉጤቶች ናቸዉ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ይህ ከላይ የተዘረዘሩት የስኬታማ ለዉጦች ባለቤት በመሆንዎ እኛ በእስራኤል የምንገኝ የቤተ እስራኤል ተወላጆች በጣም እናደንቆታለን የወደፊት ዕቅዶችዎ በሙሉ እንዲሳኩና ኢትዮጵያን ከከፍተኛ ግብ እንዲያደረሷት እንጸልይሎታለን፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል የተገባለትን ሁሉ በተግባር ለማየትና በአፈጻጸሙም በሙሉ ልብ ተባባሪ እንደሚሆንና ለነፃነት፤ ለአንድነትና ለኢትዮጵያ እርምጃና ግሥጋሤ የተቻለዉን ያህል ለመካፈል ምኞት እንዳለዉ አንጠራጠርም፡፡ የአዲስ አበባና የሓዋሳ ኗሪዎች ለመሪያቸዉ  ያላቸዉን ፍቅርና እምነት የኢትዮጵያን ሕዝብ ወክለዉ ለፕሬዝዴንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተደረገላቸዉ አቀባበል በአደባባይ ወጥተዉ አስመስክረዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል የተገባለት ብዙ ነገር አለ፡፡ በከፊል ረጅም ጊዜ የሚፈጁ ሲሆን የተቀሩትም በአጭር ጊዜ ለመፈጸም የሚችሉ አሉባቸዉ፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ብዙ ጊዜ ሳይፈጅ በሥራ ላይ ሊዉሉ የሚችሉት ለዉጦች በተሳካ ሁኔታ በሥራ ላይ እየዋሉ ቢሔዱ መላዉ ዜጋ እምነቱ እየጨመረ እንደሚሔድና በሌላ በኩልም ታማኝነቱ እየጠበቀ እንደሚሔድ ጥርጥር የለበትም፡፡

እኛ በእስራኤል የምንገኝ የቤተ እስራኤል ተወላጆች የኢትዮጵያ ታሪክ ሊቃዉንቶች እንደመዘገቡት ከኢየሩሳሌም ከሁለት ሺ አምስት መቶ በፊት መምጣታችንና የአንድ አምላክ እምነትንም ይዘን በአክሱም በቤተ መንግሥቱና በአካባቢዉ ለነበረዉ ኗሪ ሕዝብ በማሳመን በጊዜዉ የነበረዉን ሥልጣኔ በአክሱም ግዛት አካባቢ በማሰራጨት የቅድም አያቶቻችን ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዉ አልፈዋል፡፡ በታሪክም ለረጅም ዘመን የአክሱም ገናናነት በዘመኑ በነበሩት ኃያላን መንግሥታት እንደ ግሪክ፣ ግብጽ፣ ኢራን(ፋርስ) ሮማ ከተባሉት አገሮች ጋር የምትወዳደር እንደነበርና በንግድም ስመጥር እንደነበረች ይዘረዝራሉ፡፡ እስከ አራተኛዉ ክፍለ ዘመን (ከክርስቶስ ልደት በኋላ ድረስ የአክሱም መንግሥት በኦሪት  ሲያመልክ ከቆየ በኋላ የክርስትና እምነት ወደዚሁ ግዛት በገባ ጊዜ ቤተ መንግሥቱ የክርስትናን እምነት በመቀበሉ የሃገሪቱም ሃይማኖት ክርስትናን እንዲቀበል ታወጀ፡፡ በዚህ መኻል በኦሪት አማኞችና በክርስትና አማኞች መካከል የሃይማኖት ግጭት ተፈጠረ፡፡ በዚህም ጦርነት ምክንያት የኦሪትን ሃይማኖት አንለቅም ያለዉ አነስተኛዉ ክፍል አክሱምን ለቆ በስሜን፣ በወገራ፣ ባርማጭሆ፣ በወለቃይት፣ በጠገዴ፣  በደንቢያ፣ በጭላጋ፣ በአቸፈር፣ በቋራ በመሳሰሉት አካባቢዎች ተበታተነ፡፡ እነዚህ አዉራጃዎች ከጊዜ በኋላ የቤተ እስራኤሎች ግዛት በመባል ታዉቀዉ ጌድዮን በሚባሉ የቤተ እስራኤል መሪዎች የሚገዙ ነበሩ፡፡ ይኽም ግዛት እራሱን የቻለ (ኦቶኖሚ) ስለነበር የአክሱም ንጉሥ አያዝበትም ነበር፡፡ በአሥረኛዉ ክፍለ ዘመን የአክሱም መንግሥት በደከመ ጊዜም ይሁዲት የተባለችዉ የቤተ እስራኤል መሪ (የጌድዮን አራተኛዉ ልጅ) ጠንካራና ኃይለኛ ሥልጣን ስለነበራት የአክሱምን መንግሥት ድል አድርጋ (960) ጠቅላላዉን የአክሱምን ግዛት ጨምራ ለአርባ ዓመት እንደገዛች የኢትዮጵያ ታሪክ ይዘረዝራል፡፡ በነዚህ ዘመናት የኢትዮጵያ ግዛት በአሰዋን አካባቢ ከሚገኘዉ ግዛት ጀምሮ ሱዳንን በማጠቃለል የመንን ሱማልያንና ኬንያን ያጠቃልል ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ነገሥታትና በቤተ እስራኤሎች መካከል በተካሄዱት የአራት መቶ ዓመት የሃይማኖት ጦርነቶች በዐፄ ይስሐቅ ዘመነ መንግሥት (1414-1429) ቤተ እስራኤሎች ድል ሆነዉ የክርስትናን ሃይማኖት አንቀበልም በማለታቸዉ ‹‹ፈላሻ›› የሚባል ስም ተሰጥቷቸዉ ገባር እንጅ ባለ ርስት እንዳይሆኑ የንጉሥ አዋጅ ታወጀባቸዉ፡፡ ቤተ እስራኤሎች በዚህ አዋጅ መሠረት ዘመንና ንጉሥ ድንጋጌዉን ሳይቀይረዉ በገባርነት እንጅ ባለ ርስት ሆነዉ ኣያዉቁም፡፡ ይህም ማለት እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ምንም ዓይነት መብት አልነበራቸዉም በፍርድ ቤትም ምንም ዓይነት ጉዳይ ቢኖራቸዉ መብታቸዉ የተጠበቀ ባለመሆኑ ብዙ ግፋና ጭቆና ይፈጽምባቸዉ ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ቤተ እስራሎች ባላቸዉ የእጅ ጥበብ ሟያ አገልግሎታቸዉን በተፈለጉበት ቦታ ሁሉ በመሔድ ያሟሉ ነበር፡፡ ይኸዉም በኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞችና ገጠሮች የሠሯቸዉ ቤተ መንግሥቶች ቤተ ክርስቲያናትና ገዳማት እሰከዛሬ ድረስ የታሪክ ምስክሮች ናቸዉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከዉጭ ወራሪ ጠላት ተነስቶ አገሪቷን ለማጥቃት በተነሣ ጊዜ ግንባር ቀደም በመሆን ከጀግኖች የጦር መሪዎች ጋር ለአገራቸዉ ነፃነትና ድንበር የተዋጉና ብዙዎችም ሕይወታቸዉን ማሳላፈቸዉ ጥርጥር የለዉም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ አባቶቻችን ያሳለፉትን ታሪክ በአንድ ደብዳቤ ለመዘርዘር አይቻልም፡

፡ የቤተ እስራኤሎች የጥንትና አዲሱ ዘመን ታሪክ በጣም ሰፊና በኢትዮጵያ ታሪክ በጣም ከፍተኛ ቦታ ያለዉ ከመሆኑም በላይ በብዛት በአገሮቹ ተወላጆች ሳይሆን በዉጭ ተወላጆች የተጠናና የተጻፈ በመሆኑ እዉነተኛዉና ትክክለኛዉ ታሪክ በኢትዮጵያኖች ተጠንቶ አልቀረበም፡፡ አብዛኛዉ የታሪክ መረጃዎችም በቤተ ክርስቲያንና በገዳማት የነበሩ ሲሆን በተለያዩ መንገድ ለባዕድ ተሸጠዉ ከአገሪቱ ዉጭ ዩኒቨርሲቲዎችና ሙዚየሞች ተሰራጭተዉ ይገኛሉ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ታሪክን በተመለከተ ያለፈዉ መንግሥት ምን ያኽል ጥፋት እንዳደረሰ ከኛ ይበልጥ ክቡርነትዎ ከቦታዉ የሚገኙ ስለሆነ ከኛ ይበልጥ ስለሚያዉቁ ስለሆነ መረጃዎች ማቅረቡ ተፈላጊ መስሎ አልታየንም፡፡ ይሁን እንጅ በተወለድንባትና ባደግንባት አገራችን ጥለነዉ የመጣነዉ የሚያኮራ ታሪካችን እንዳልነበር ሁኖ ከመጥፋቱ በፊት ከስርቆት የተረፉት ቅርሶች እንዳይጠፉና በጥንቃቄ እንዲያዙ አደራችንን እናቀርባለን፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ልመናችንም ከላይ እንደጠቀስነዉ በተለያዩ ጦርነቶች አንድነትና  ሰላም የሐገር ዋስትና መሆኑን የተረዱት አባቶቻችን መሪዎቻችንና ቀሳዉስቶቻችን አገርን ለማጥፋት ከመጣ ጠላት ጋር ተዋግተዉ ለአገራቸዉ የተሰዉት አባቶቻችን፤ እናቶቻችንና ወንድሞቻችን የተቀበሩባቸዉና የጻድቃን መቃብር በግንብ አጥር አሠርተን ዘበኛ ቀጥረን ልናስከብር ብንሞክር በጉልበት የነበሩትን ዛፎች በመቁረጥና ጫካዉን በማዉደም ካልጠፋ የኢትዮጵያ ቦታ አዉድመዉታል፡፡ በኢትዮጵያ ባህል መቃብር ቤት ሲታረስ ሰምተን አናዉቅም ነበር፡፡ እንዴት መቃብር ይታረሳል? ክቡርነትዎ ለክልል መሪዎች የተረፉት የመቃብር ቦታዎቻችን  እንዲከበሩልን አጥብቀን እንለምናለን፡፡

ከታላቅ አክብሮት ጋር

Yonaze1@gmail.com

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s