አዲሷ የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊ በማስፋፊያ ሥራዎች ይጠበቃሉ (ዳዊት ታዬ)

የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊዎች ብሔራዊና ሌሎች በዓላትን አስታከው ለደንበኞቻቸው የእንኳን አደረሳችሁ ወይም እንኳን ደስ አላችሁ የሚሉ የጽሑፍ መልዕክቶችን በደንበኞች ስልክ ማስተላለፋቸው የተለመደ ነው፡፡ ከአንድ ወር ተኩል በፊት ኢትዮ ቴሌኮምን እንዲመሩ የተሰየሙት የመጀመርያዋ እንስት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩም በስማቸው የእንኳን አደረሳችሁ አጭር የጽሑፍ መልዕክት የአረፋን በዓል አስታከው አስተላልፈዋል፡፡

Frehiwot Tamiru

ይህንን መልዕክት ባስተላለፉ በቀናት ውስጥ የመጀመርያቸውን ጋዜጣዊ መግለጫ ረቡዕ፣ ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም የቴሌኮም ታሪፍ ከ40 በመቶ በላይ ቅናሽ እንደተደረገበት አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ወደ ኃላፊነት የመጡበት ወቅት ከፍተኛ የኔትወርክ መጨናነቅ የተፈጠረበት በመሆኑ፣ በቴሌኮም መስክ የአገልግሎት ጥራት ችግር እንደሚኖር በይፋ ተናግረዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በአንድ ወር ተኩል የኃላፊነት ቆይታቸው፣ የሚመሩት ተቋም እንዲህ ያለውን ዕርምጃ እንዲወስን ያበቁትን ምክንያቶች አብራርተው ነበር፡፡  በሞባይል የድምፅ አገልግሎት ላይ የ40 በመቶ፣ በሞባይል ኢንተርኔት የ43፣ የሞባይል አጭር መልዕክት ላይ የ43 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ተደርጓል፡፡ እንደ ብሮድባንድ ያሉ አገልግሎቶችም እስከ 53 በመቶ ቅናሽ ተደርጎባቸዋል፡፡ በሌሎች አገልግሎቶች ላይ ተመሳሳይ ቅናሽ ተደርጓል፡፡አዲሷ የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊ

የታሪፍ ቅናሹ ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ፣ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ያደረገበት ሆኗል፡፡ የሞባይል አገልግሎት ሲጀመር፣ ለድምፅ የሚከፈለው 1.50 ብር በደቂቃ ነበር፡፡ እስካሁኑ የታሪፍ ለውጥ ድረስ ለሞባይል ድምፅ አገልግሎት ሲከፈል የቆየው በደቂቃ 83 ሳንቲም ነበር፡፡ በአዲሱ ታሪፍ ደግሞ ይህ ወደ 50 ሳንቲም ወርዷል፡፡ ይሁንና አሁንም ቢሆን ታሪፉ ከፍተኛ ስለመሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡

በቅናሹ ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ማሻሻያው ካስፈለገባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ አንደኛው እስካሁን የነበረው የአገልግሎት ትርፍ የደንበኞችን አቅም አለማገናዘቡን ነው፡፡ 41 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን በቋሚነት እየተጠቀሙ ካሉት ውስጥ አብዛኞቹ የኩባንያው ታሪፍ ውድ ስለሆነባቸው በተገቢው መንገድ እንደማይጠቀሙ ገልጸዋል፡፡

ለታሪፍ ቅናሹ ምክንያት ሆኗል ብለው ያስቀመጡት ሌላው ነጥብ፣ እስካሁን ደንበኛ ሊሆኑ ያልቻሉ ዜጎች፣ አገልግሎቱ የመክፈል አቅማቸውን ባለማገናዘቡ እነሱንም ለማካተት ታስቦ ቅናሽ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ እስካሁን የነበረው ታሪፍ በዓለም አቀፍ መሥፈርት ሲታይም፣ የኢትዮጵያ ዋጋ ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱ ለታሪፍ ቅናሹ መነሻ ስለመሆኑ ከዋና ሥራ አስፈጻሟ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ የቴሌኮም ታሪፍ  ውድ ተብሎ በተቀመጠው ክፍል ውስጥ እንደሚመደብና ይህንን ለመቅረፍም የዋጋ ማሻሻያ ማድረግ እንዳስፈለገ አስታውቀዋል፡፡

የዓለም ቴሌኮም ዩኒየን ካስቀመጣቸው መሥፈርቶች ውስጥ፣ አንድ ግለሰብ በወር በአማካይ ከሚያገኘው ገቢ ውስጥ ለቴሌኮሙዩኒኬሽን ወጪ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ የተቀመጠው ከጠቅላላ አገሪቱ ብሔራዊ ገቢ ውስጥ ከአምስት በመቶ መብለጥ የለበትም የሚለውን በመጥቀስ፣ በዚህ መሠረት የኢትዮ ቴሌኮም ታሪፍ ከአምስት በመቶ በላይ እንደነበር ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡ ይህም የቴሌኮም ዋጋ ውድ መሆኑን በማመላከቱ የታሪፍ ቅናሹ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የዋጋ ቅናሽ መደረጉ በጎ ቢሆንም፣ የኔትወርክ መቆራረጥና እየተከሰተ ያለው የአገልግሎት ጥራት መጓደል አዲሷን ሥራ አስፈጻሚ የሚፈትን ሥራ መሆኑ አይቀርም፡፡ የኔትወርክ ጥራት መጓደል ተቋሙን ተጨማሪ ኢንቨስትመንት  እንዲያካሂድ ማስገደዱ አይቀሬ ነው እየተባለ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ለሚከሰተው የኔትወርክ መጨናነቅ ዋናው ምክንያት ለ1.5 ሚሊዮን ተገልጋይ የተዘረጋው ኔትወርክ ለ2.8 ሚሊዮን ተገልጋይ መዋሉ በመሆኑ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ይጠይቃል ተብሏል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባና በዋና ዋና የክልል ዋና ከተሞች ከፍተኛ የሆነ የኔትወርክ መጨናነቅ እንደሚታይ በግልጽ የተናገሩት ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ይህ የሆነበት ምክንያት በተለይ አዲስ አበባ ላይ ያለው የኔትወርክ መሠረተ ልማት ከሚሸከመው በላይ እያስተናገደ ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡ ይህንን በመገንዘብ ማሻሻያዎች ሲደረጉ እንደነበርም፡፡ ነገር ግን መጨናነቁን ለመቀነስ የማስፋፊያ ሥራ ማስፈለጉን ጠቁመዋል፡፡ ሁለተኛው የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ፕሮጀክትን ለመተግበር እየተሰናዳ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

ለማስፋፊያው ግዥዎችን መፈጸም ስለሚያስፈልግ፣ የግዥ ጥያቄው ስለመፅደቁም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ኔትወርክ አብዛኛው ክፍል በቻይናው ሕዋዌ ኩባንያ የተገነባ በመሆኑ፣ ለማስፋፊያውም ከኩባንያው ጋር ድርድር መካሄዱን ገልጸዋል፡፡ ይህ እስኪሆን ድረስ በአንዳንድ አካባቢዎች የተደራሽነት ችግር እንደሚከሰት ያመለከቱት ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ዓለም ገና፣ ለገጣፎ፣ ቡራዩ፣ ጀሞና ዓለም ባንክ ለተደራሽነት ችግር ከሚጠቅሱት ውስጥ ናቸው፡፡

የተደራሽነቱ ችግር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እንደ በቦሌ መድኃኔዓለም፣ ሃያ ሁለት ከጎላጎል ሕንፃ እስከመገናኛ ድረስ ከፍተኛ የሆነ የስልክ መቆራረጥን የአገልግሎት ጥራት መጓደል ይታያል፡፡ በክልል ዋና ዋና ከተሞች ላይም በተመሳሳይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ መጠነኛ ማስፋፊያ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ጥረት በሚደረግበት ወቅት ኅብረተሰቡ በትዕግሥት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል፡፡ ለሚታይ የጥራት መጓደል ግን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ አዲሷ ሥራ አስፈጻሚ ከአንድ ዓመት በፊት ተግባራዊ እንዲደረግ ተወስኖ የነበረው አሠራር እንደተሻረ አስታውቀዋል፡፡

አስገዳጁ አሠራር ማንኛውም ሲም ካርድ የሚቀበል የቴሌኮም መሣሪያ አገልግሎት ላይ ከመዋሉ በፊት መመዝገብ አለበት ተብሎ ይኼው ሲተገበር ቆይቷል፡፡ ማንኛውም የሞባይል ስልክ ለአገልግሎት ከመዋሉ በፊት ደንበኛው ወደ ኢትዮ ቴሌኮም በመሄድ ስልኩን በኔትወርክ ለማገናኘት መስመሩን ማስከፈት ይጠበቅበታል፡፡

ይህ አሠራር ብዙዎችን ሲያማርር ቆይቷል፡፡ የውጭ ዜጎች በገቡ ቁጥር ስልክ ለማስመዝገብና ኔትወርክ ለማስከፈት ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡ በቴሌኮም ቅርንጫፎች ለዚህ ሲባል የሚያጠፉት ጊዜና የሚደርስባቸው መጉላላት ከፍተኛና ቅሬታ ማሳደሩም ይታወሳል፡፡

ይህ አሠራር መቋረጡን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡ የሞባይል ምዝገባ  ሥራ ላይ የዋለው የአገር ውስጥ ሞባይል አምራቾችን ለማበረታታት፣ የሕገወጥ የሞባይል ስልኮች ግብይት ለመከላከልና ለመሳሰሉት ተግባራት ነበር፡፡ ይሁንና ከጥቅሙ ጉዳቱ በማመዘኑ እንዲቋረጥ ተደርጓል ተብሏል፡፡ ‹‹አሁን ላይ ቆም ብለን አሠራሩን ስንፈትሽ ከውጤታማነቱ ይልቅ ብዙ ክፍተቶች ታይተውበታል፤›› በማለት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s