በበረከት ስምዖን ዘመን ኢትዮጵያ ትንሣኤ አልነበራትም (መንገሻ መልኬ)

 • ጥንታዊ ኢትዮጵያና ሕወሀታዊ ኢትዮጵያ፤ (ንጽጽር
 • አቢዮታዊ ዲሞክራሲ ምን ድን ነው ? (ፓለቲካዊ ግንዛቤ፤
 • «ወደ ነበርንበት እንመለስ» አንባሻ እንደ መጋገር ቀላል አይደለም፤
 • የዶክተር ዐቢይ አስተዳደር በሕገ መንግሥቱን በማሻሻል አሻጋሪ መንግሥት ይሁን፤
 • በረከትና ጎንደር፤ በረከት በሁለት በኩል የተሣለ ሰይፍ የአማራ ጠላት፤
 • ፓርቱጋልና ግራኝ አህመድ፤ ህወሀትና አብዲ ኢሌ፣ በረከትና አና ጎሚዝ፤(የታሪክ ምስክርነት
 • ጎንደር ውስጥ የትግሬ መፈናቀል፤ የአልጃ -ዚራ ቴለቭዝን ዜና፤ የበረከት ተቆርቋሪንት፤

ምንም እንኳን «ትንሣኤ ዘኢትዮጵያ» በሚል ርዕስ በበረከት ስምዖን የተጻፈውን መጽሐፍ ባላነበውም ወይም የማንበብ ፍላጎት ባይኖረኝም ሕወሀት  እራሱ ማን ነው የሚለውን በመረዳት፣ እነ በረከት ከመነሻቸው ጀምሮ በኢትዮያ ላይ እንደ ሀገር ያላቸው መሠረታዊ ግንዛቤና ዓላማ ምንድን ነው የሚለውን በመከለስ? በሕወሀት አገዛዝ ዘመን የበረከት ተሳትፎ ከበረኸኝነት እስከ ምንስትርነት፣ እንዲሁም በረከት በቅርቡ በአንድ የቧልት መድረክ ከሰጠው ቃለ ምልልስ አንጻር በመነሳት «ትንሣኤ ዘኢትዮጵያ» በበረከት ስሞዖን ከየት ሊጀምር ይችላል በሚል መጠየቅ፤ መጽሐፉ ሊያስተላልፈው የሚፈልገው መልዕክት ምን ሊሆን እንደሚችል መራዳቱ ብዙ ፍልስፍና የሚጠይቅ ስለማይሆን ይህን በበረከት ስምዖን ዘመን ኢትዮጵያ ትንሣዔ የላትም ባልኩት ርዕስ ወቅታዊና ታሪካዊ ኩነቶችን ያጣመረ አጭር ጽሑፍ ለማቅረብ ወደድኩ።

የጽሑፍን ርዕስ በዝርዘር በማንበብ በቀላሉ ለመረዳት እንዲያስችል፤ ኢትዮጵያ ስንል በሚከተለው ሁለት ጥንታዊት ኢትዮጵያ እና ሕወሀታዊ ኢትዮጵያ በማለት የተሰጠውን ገለጻ ማገናዘቡ ቅድሚያ የሚሰጠው  አርዕስተ ጉዳይ ይሆናል።

 • አንደኛው ብዙዎቻችን የሚያስማማን ኢትዮጵያ እረጅም ታሪክ ያላት ብዙ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፋ፣ ተሰባጥረው ተቀላቅለው ተዋሕደው በሚኖሩ ዜጎች ደምቃ፣ የብዙ ቋንቋዎችና ባህሎች ባለቤት፣ የረጅም ዘመናት መልዕካ ምድራዊ ገጽታ ያላት፣ የተመቻቸ የባህር በር የነበራት በየጊዜው በነበረው ንቃተ ሕሊና ቁሳዊ፣ ማኅበራዊና ፓለቲካዊ አስተሳሰብ የእድገት ደረጃ አንጻር እንደ ሀገር እረጅም ዘመን ያስቆጠረች ኢትዮጵያ ፤ከዚያም አልፎ «ኢትዮጵያ» የሚለው ቃል ብቻውን ፈጣሪውን የሚያመልክ በፈጣሪው ስም የእምነት ገጸ በረከት የሚያቀርብ ሕዝብ የሚኖርባት ቀደምት ሀገር ማለት እንደሆነ ዘመኑ ያራቀቃቸውና ስልጡን የታሪክ ሊቃውንት በምርምር ሥራቸው ያረጋገጧትን ኢትዮጵያ ነው።

 

 • ሁለተኛው የህወሀታዊ ኢትዮጵያ ማለት በአርባ ዓመት ጉዞ ውስጥ የአማራ ብሔረሰብ እና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፊውዳላዊነት ፈርጆ ተቀዳሚ የመደብ ጠላቶች ያደረገ ጽንሰ ሐሳብ በማኒፌስቶ ቀርጾ የተነሳና እነሱን ደምስሰን በትግራይ ትግርኝ የበላይነት የምትመራ በብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ሽፋን በክልል መንግሥታት የተከፋፈለች ቅራኔና የቂም በቀል ኃውልት የታነጸባት፣ መተማመና መረዳዳት በአንድ አሀገር አንድ ሕዝብ ሆኖ መኖር ጠፍቶ መለያየትና በመከፋፈል አጥቂና ተጠቂ፣ አፈናቃይና ተፈናቃይ፣አሳዳጅና ተሰዳጅ፣ አጥፊና ጠፊ ፣ ባሀር በርሯ የተዘጋ፣ መልካ ምድሯ ያነሰ፣ ከቀደምት በጎ የታሪክ አሻራዎች ጋር መፋለስ፣መናናቅ፣ የበዛበት ሕወሀት ከተነሳበት ዘመን ጀምሮ በሕወሀት አስተሳሰብና አመራር ያለችውን ኢትዮጵያን ማለታችን ነው።

በረከት ስምዖን በሕወሀታዊ ኢትዮጵያ አስተሳሰብ ተቀርጾ ያደገ ከመሆኑም በላይ የዚህ ዓላማ አራማጆች ከሆኑት  ግንባር ቀደም ታጋይ እና በዚህ የዓላማ ጥንካሬውና ታማኝነቱ ተመልመሎ በሕወሀት የአገዛዝ ዘመን  ከበረኸኝነት እስከ ምንስትር ማዕረግ የደረሰ መሆኑን በመረዳት በንጽጽር መገምገም ይኖርብናል።

ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት የኢትዮጵያዊነት አገላለጽ በስፋት አበጥረንና ስንመለከት፤ «ትንሣዔ ዘኢትዮጵያ» በበረከት ስሞዖን ከየት ሊጀምር ይችላል ብለን ብንጠይቅ፤ በረከት የሚያውቃት ኢትዮጵያ ከበረኽኝነት እስከ ምንስትርነት ድረስ የደረሰባትን በሁለተኛ ተራ የተገለጸችውን በክልል መንግሥታት የተከፋፈልችውን ሕወሀታዊ ኢትዮጵያ ላይ የሚያነጣጥር መሆኑን ማሰብ ቀላል ስሌት ነው። ከዚህ ስሌት አኳያ ኢትዮጵያ በእነ በረከት ስምዖን ዘመን ትንሣዔ የላትም ብሎ ማስረዳት የቀላል ቀላል ነው።

ምክንያቱም ነባር ጥንታዊ ኢትዮጵያዊ ታሪክ፣አብሮ የመኖር እሴት፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ትውፊት ሁሉ በሕወሀት ዘንድ በጠላትነት የተፈረጀ እንደመሆኑ መጠን ከዚያ በላይ አንድ ኢንች ርቆ ለመሄድ ያሳደጋቸው ሕወሀታዊ ገጸ ባህሪነት  የማይፈቅድላቸው በመሆኑ ከወዲሁ ማረጋገጥ ይኖርብናል። የኢትዮጵያ ትንሣዔ የታየባት ሳትሆን ተከፋፍላ በሕይወትና በሞት መካከል  እያነሰች መጥታ ለመሞት እያጣጣረች ያለች ኢትዮጵያ ከመሆንኗም በላይ በእነ በረከት ስሞዖን እግር የተተኩትም እነሱን አስመስለው ያሳደጓቸው፣ ያሰለጠኗቸው «ቃለ አሚኖዎች» በሙሉ ከሕወሀታዊ ኢትዮጵያ ታሪክ እርቆ መሄድ የማይፈልጉ በመሆናቸው የኢትዮጵያን ሞት ከሚያፋጥኑ መቃብር ከሚቆፍሩ በስተቀር ለኢትዮጵያ ትንሣዔ የሰለጠኑ አለመሆናቸውን ከውዲሁ መረዳት ስለሚቻል ነው።

በመሆኑም «ትንሣኤ ዘኢትዮጵያ» በበረከት ስምዖን የሚለው በምናባችን ስንመለከት አብዛኞቻችን በአንድነት በሕብረት የምንስማማባትን ጥንታዊት ታሪካዊት ኢትዮጵያን ያገናዘበ ሳይሆ፤ ሕወሀታዊ ኢትዮጵያን የሚያቀነቅን፤ ታሪካዊ መሠረት ፋይዳ ሊኖረው እንደማይችል ለመረዳት «ጸሐፊውን» ቀርጾ ካሳደገው ርእዮት ዓለምና መሪ ዓላማ፣ተመልምሎ ከበረኸኝነት እስከ ምንስትርነት የደረሰበትን አቋም፣ በሥልጣን ዘመኑ የነበረውን ሥራ አፈጻጸም ድክመት የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገራት ሕዝባዊ ትችትና ወቀሳን በማነጻጸር ብቻውን ኢትዮጵያ በእነ በረከት ስሞዖን ዘመን ትንሣኤ የላትም ብሎ መልስ መስጠት ባጭሩ አሁን በአሁኑ ስዓት ሕብረተሰባቸን የደረሰበትን የለውጥ ማዕበል የንቃተ ኅሊና ደረጃ ያገናዘበ ከመሆኑም በላይ ሚዛናዊ ፍሩዱንም የጎላ ያደርገዋል።

ህወሀት ከጅምሩ ስንመለከተው ከትምህርት ገበታቸው ፈርጥጠው፣ የአካል ጥንካሬ የአዕምሮ ማስተዋልና የማገናዘብ ብስለትና ብቃት መጠኑ ተፈላጊው የዕድገት ደረጃ ላይ ባልደረሰበት ሁኔታ ጠባብና አናሳነት ወይም የበታችነት በፈጠረው ጨቅላ አስተሳሰብ በአንድ ብሔርሰብ ተዋጽዖ የተመሠረተ ነው።ይህም ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ያገናዘበ መርህ ሳይኖረው አንድን ክልል ከማዕከላዊ መንግሥት አስተዳደር ነፃ አውጣለሁ በሚል ዓላማ የተጸነሰ «የትግሬ ሀርነት» ርእዮት ዓለም ብቻ ያናወዘው ነው። በዚህ የአስተሳሰብ መሠረት ላይ የታነጸ ሀርነት በኢትዮጵያዊ ስሜት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥን ያመጣ ትንሣኤ ነው ብሎ ማሰብ  ፈጽሞ አይቻልም። የለውጥ ኃይልም ነው ብሎ ለመናገርም አያስደፍርም። እራሱ ሕወሀት ዋናውን ስማቸውን እየቀየረ ከሌሎች ብሔሮች ጋር የሚያመሳስል  የዳቦ ስም እየሰጠ፤ አዲስ አበባ በመቆጣጠሩ ዋዜማ «ኢሕአዴግ» የሚል ስያሜ በማውጣት የማዕከላዊ መንግሥቱ ባለቤት ለመሆን ያወጣው የጣዖት ስያሜ እንጅ አብዮታዊ ዲሞክራሲዊነት የሚያንጸባርቅና የኢትዮጵያን ትንሣዔ የሚያሳይ  ምዕራፍ ተብሎ ሊጠቀስ አይገባም።

ይልቁንም የጣዖት ስያሜ  ኢሕአዴግ የራሱ ጠባብ ዓላማ ለማስፈጸም በኢትዮጵያዊነት ስም የኢኮኖሚ ጥገኛ ሆኖ መቆየትና የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት ወደ አንድ ክልል ብቻ በገፍ ማጓጓዝና ማከማቸት፣ የእራሱ ያልነበሩ ክልልሎችን መሬት መቀማት፣ ከክልልሉ የራቁትን ለም መሬቶች በርካሽ ዋጋ ለባለሀብቶች መሸጥ፣ ሥልጣንን መከታ በማድረግ  በዝምደና፣ በአምቻ በጋብቻ ከላይ እስከታች በተያዘ ሰንሰለታዊ ግኑኝነት ከመጠን ባለፈ ዘረፋ ላይ መሰማራት ከፍተኛ ሀብት የማጋበስ ቡደናዊ መዋቅር ሥር የቆየ ከመሆን ተልዕኮ በዘለለ ዛሬ ገሀዱ ዓለም ያገናዘበው ፓለቲካዊ ጽንሰ ሐሳብና ሕዝብን በእኩልነት የመምራትና የማስተዳደር መርህና ሥርዓት ያለው  አልፎም በትንሣኤነትን የሚያሳይ መንፈስና አቋም አልነበረውም።

አሁን በረከት ስምዖን  የሚቀባጥራቸው ፓለቲካዊ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ማስመሰያ ቅዥቶች ሁሉ የግዛት እደሜ ዘመን ማራዘሚያ መድኅኒትና የሰለጠኑ ዓለማትን የማጭበርበሪያና የርዳታ መቀበያ በወረቀት ላይ የሠፈሩ ዲስኩሮች ሆነው የቆዩ ከመሆናቸው በስተቀር ኢሕአዴግ ትክክለኛ ሕጋዊና ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው በለውጥ የሚያምን፣ ትክክለኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚያሳትፍ፣ ለሕግ የሚገዛ፣ በሕዝብ የበላይነት የሚሠራ ሳይሆን በመከፋፈል ሰይፍ የሚቀላ፣ መለያየት መጋዝ የሚቀረድድ፣ በጥላጫ ሾተል የሚወጋ ኢትዮጵያዊ ውድቀትን የሚያበረታታ ሞትን የሚያፋጥን መቃብር የሚቆፈር እንጅ ትንሣዔን  የሚያንጸባርቅ ሕልውና አልታየበትም።

ዛሬ በትግሬ ክልል የታቋቋሙት ከመቶ በላይ የሚደሱ ከፍተኛ በሆነ ካፒታል እየታገዙ የሚንቀሳቀሱ ከባድ ኢንዳስተሪዎች፣ በሥልጣን ላይ ያሉ የትግሬ ተወላጆችና ዘመዶቻቸው የቻይናንና የዱባይ ባንኮችን ያጣበበ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ካፒታል፣ በትግሬ ክልል የተሠሩ የመሠረተ ልማት ተቋማት በሙሉ ከትግሬ ምድር ውስጥ በተገኘ አንጡራ ሀብትና የምርት ውጤት እንዲሁም የውጪ ገበያ አቅርቦት ግብአት የመጣ በተገኘ የገነባው አለመሆኑ  እየታወቀ፤ በተቃራኒው ደግሞ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ምርትም ሆነ ለውጭ ገበያ አቅርቦት የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት የሆኑ ክልልሎች የረባ የዳቦ ማምረቻ ማሽን እንኳን አለመኖራቸው በራሱ የነበረው የሕወሀት አገዛዝ ለማንን  እንደሚሠራ በምን ዓላማ ላይ የተሠማራ መሆኑንን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ አፍንጫ ሥር ያለ ሚዛን ሆኖ ሳለ ይህን የኢትዮጵያ ትንሣኤ ብሎ መዘገብ ፍጹም ቅጥፈት ነው።

ደርግን የለወጠው ሕወሀት ሳይሆን፤ ከስልሳዎች የንጉሠ ነገሥት ምንስትሮች በመረሸኑ የደረሰበት የውስጥና የውጪ ከባድ ነቀፌታን ተከትሎ በሱማሌ ወረራ  በተደረገው ጦርነት መዳከም ጋር ተያይዞ በተለይም «ከአስረኛው አቢዮት በዓል» ማግሥት የኮሚኒዝም ሥርዓት እየወደቀ መምጣት፣ ወጣቱ በማያቋርጥ የጦርነት ጉዞ ማገዶ መሆን የፈጠረው መማረርና መሰላቸት፣ በምዕራቡ ዓለም የፓለቲካ አጋር ማጣት፤ በ1981 ዓ.ም የተደረገው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፍና የተዋቂ ጀነራሎች ያለፍርድ መረሸን ከዚያም አልፎ በምዕራባዊያን የተሳሳተ የፓለቲካ መረዳት፣ በለንደን ከተማ በእነ  አንባሳደር ኽርማንኮን የተመራው የደርደር ስብሰባ የፈጠረው አሻጥር፤በበርሀ የነበረውን የኤርትራ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር እየተጠናከረ በመምጣቱ ሕወሀትም የዚሁ ግንባር የማደጎ ልጅ ስለሆነች በጠበንጃ ኃይል በመደጋገፍ የተቀማ ሥልጣን እንጅ ሕወሀት ከደርግ የተሻለ ሕዝብን ያሳመነ፣ ለሀገር ሉአሏዊነት የቆመ፣ በሕዝብ የደምጽ  ብልጫ የተወከለ የለውጥ አካል አይደለም አልነበረም። ይህም የለውጥ ምዕራፍ ወይም የኢትዮጵያ ትንሣዔ ተብሎ ሊጠቀስ አያስችለውም።  ሕወሀት ሕዝባዊ ድጋፍ ተቀባይነት ያለው ለውጥን ተከትሎ በመርህ በሰለጠነና በበሰለ የፓለቲካዊ ግብአትና ሕዝባዊ አስተዳደር መርህ አመኔታ አግኝቶ በማዕክላዊ መግሥትነት አልተቀመጠም። ተቀምጦም አያውቅም። ሕወሀት የለውጥ አካል  ሳይሆን ያለሕዝብ ፍላጎትና ምርጫ በኃይል ሥልጣን ኮርቻ የተፈናጠጠ  የወረራ ይዘትና ቅርጽ ያለው ነው።

ከማያቋርጠው የሕዛብዊ ተቃሞ በተጨማሪ «እኛ በርሃ ገብተን ደማችን ገበረን ያገኘነው ሥልጣን ነው፤ እንደ እኛ ጠበንጃ ይዛችሁ አሸንፋችሁ ሥልጣኑን ውሰዱ የሚለው የመለስ ዜናዊ የተዘወተረ አነጋገር፤ አሁንም ስልሳ ሺህ  የትግሬ ወጣት ገብረን ነው ሥልጣኑን ያገኘነው የሚለው ዘይቤ ሁሉ ሕወሀትን በለወጥ አራማጅነት ወይም በለውጥ ተቀባይነት በሕዝብ ድጋፍና ምርጫ የቆየ አለመሆኑን ጉልህ ማስረጃ ነው። «……አዲስ መንግሥት እንጅ ለውጥ መቸ መጣ» የሚለው በሕዝብ የተወደደው የቴዎድሮስ ካሣሁን ዜማ ያስተጋባ የነበረው የሕዝብ ብሶስት፤ ሕወሀት ሠራሹ ኢሕአዴግ በለውጥ የመጣ ለውጥንም የማይቀበል አንባገነናዊ  አገዛዝ መሆኑን ለአዲሱ ትውልድ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ደዎል ከመሆኑ በላይ ኢትዮጵያ በሞት ጥላ ውስጥ መሆንዋን እንጅ በትንሣኤ ውስጥ አለመሆንዋን የሚያሳብቅ መልዕከት ነበረው።

የሕወሀት ምልምሎች አንድ የሚያደርጋቸው ያአነጋገር ዘይቤ አለ። ይህም በሰለጠነው ዓለም ለሰዎ ልጆች በጎ ለውጥ የሚያስቡ  የዳበረ የፓለቲካ ጽንሰ ሐሳብ ያላቸው ወይም የሕዝብን የበላይነት የሕግን ሉአሏዊነት ባስቀደሙ በጎ ሕሊና ባላቸው ሰዎች ሲነገር የሰሙትን ሥር የሰደደ የፓለቲካ ሳይንስ፤ ነገር ግን ትክክለኛ ተርጉማቸውን ሳይረዱ እንዲሁም በተግባር የማያውሉትን ቃላቶች ኮርጆ በጣም አጋኖ በማውራትና በማስወራት፤ የፓለቲካ ግብአት ወይም ሕዝብን እያደናገሩ ለመኖር ከሚረዳ በስተቀር ኢትዮጵያ  በእነ በረከት ስምዖን ዘመን የትንሣዔ ሕይዎት አልነበራትም። ተዘውትረው ከሚነገሩት የተጋነኑ ቃላት መካከል «አብዮታዊ ዲሞክራሲ»  የሚለውን ማየቱ በቂ ነው።

አቢዮታዊ ዲሞክራሲ፤ ይህ ቃል በኮሚኒስታዊ ጽንሰ ሐሳብ የተካተተ ቢሆንም በትክክል ሥራ ላይ የሚተረጉመው እና ሥራ ላይ የሚያውለው ቢያገኝ እጅግ የረቀቀና ሰፊ በውስጡ ብዙ ቁሳዊ መርሐ ግብሮችን ሊያሳትፍ የሚችል ዲሞክራሲያዊ መርህ ቢሆንም፤ በማይመጥን የግንዛቤ ጉድለትና መስመር በትንሣዔ ዘኢትዮጵያ የበረከት ስምዖን ቁንጽል አስተሳሰብ እንደተካተተ ከቃለ ምልልሱ ላይ ለመረዳት ችያለሁ።

ለመሆኑ አቢዮታዊ ዲሞክራሲ ምንድን ነው?  ሕወሀት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የመመራት ተፈጥሮ አለውን? አሁን የምናየው ለውጥ በሕውሀት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ፈላጊነት የመጣ ትንሣዔ ነውን? የሚሉትን መጠይቆች በማንሳት ከሕወሀትን የአገዛዝ ዘመን ጋር ባጭር ባጭሩ በማገናዘብ ከሕወሀታዊ ኢትዮጵያ አንጻር በስሌት ስናወራርደው ኢትዮጵያ ሞትን በሕይወት የሚለውጥ ምንም ዓይነት የትሣዔ  ተስፋ ያልታየባት መሆንዋን መረዳት ይቻላል።

«አቢዮታዊ ዲሞክራሲ» የሚለውን ቃል የመስኩ ምሁራን እንዲህ ይገልጹታል፤« Democratic Revolution is a political science term denoting a revolution in which a democracy is instituted, replacing a previous non-democratic government, or in which revolutionary change is brought about through democratic means, usually without violence.» 

«አቢዮታዊ ዲሞክራሲ ማለት የፓለቲካ ሳይንስ አካል ሲሆን ሕገ መንግሥታዊ  ፈላጊነት የሕዝባዊ አቢዮት፣  ሕገ መነግሥታዊ ያልሆነውን/ያልነበረውን የመንግሥት አስተዳደር መተካት ወይም ሕዝባዊ አቢዮትን ተጠቅሞ የሚመጣ ሕዝባዊ አስተዳደር ለውጥ ነው፤ ይህም በአብዛኛው ምንም ኃይል፣ጉልብት፣ ማስገደድ….የመጠቀም  ችግር ሳይኖርበት የሚፈጸም ይሆናል።

ከላይ እንደተገለጸው አቢዮታዊ ዲምክራሲ የሚለውን የፓለቲካ ጥበብ በአግባቡ የሚሠራበትና በትክክል ተግባር ላይ የሚያውለው ቢኖር በውስጡ ሕዝባዊ ድጋፍ የሚሰጥ ሰፊ ድርሻ ያለው በተለይም በኮሚኒስቱ በኩል የሚዘወተር ቢሆንም ከኮሚኒስት ውድቀት በኋላ በምዕራቡ ዓለም ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር አጋዥ የፓለቲካ ቀመር መሆኑ አያጠያይቅም ።

ከዚህ አቢዮታዊ ዲሞክራሲ መገለጫ  ባህሪ አንጻር ሕወሀት/ኢሕዴግ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ሕዝቡንም እንደ ሕዝብ ያገናዘበና የታገለ አይደለም። ሕወሀት በትጥቅ ትግል የታገለው አንድን ክልል ነፃ ለማውጣት ብቻ ሲሆን ነገር ግን በአንድ ትልቅ ሀገር  ያለሕዝብ ምርጫና ፈቃድ መንግሥት ሆኖ በኃይል የተቀመጠ ነው። ይህ ደግሞ  ሕዝባዊነት ለውጥ ፈላጊነት ዲሞክራሲያዊ አቢዮተኝነት ባህሪን ተከትሎ የተተካ መንግሥት አይደለም ሊሆንም አይችልም። ሕወሀት ከመነሻው እስከ መድረሻው ያለው ሕይዎት በሙሉ  ከመስማት ወይም በስያሜ ተጠቃሚ የመሆን ጭንብል ከሚሆነው በስተቀር በጭራሽ አቢዮታዊ ዲምክራሲያዊ ተፍጥሮ የለውም። በዚህ መርህም ያመጣው ለኢትዮጵያ ትንሣኤ አልነበረም።

ሕወሀት በኢትዮጵያ ሃያ ሰባት ዓመት  መንግሥት ሆኖ የቆየው ፀረ አቢዮታዊ ዲሞክራሲ በመሆን ነው። ይህም የሕዝብን ጥያቄ ማፈን፣ያለፍርድ ቤት ወሳኔ ዝብን በጀምላ ማሠር፣ የሕዝብን መሠረታዊ ሰባዊ መብት በመንፈግ፣ የምርጫ ኮሮጆችን በመስረቅና በማጭበርበር ጭርምር በዓለም ታዛቢዎች ዘንድ የሚገለጽ ሲሆን የእነ በረከት ስሞዖን አቢዮታዊ ድሚክራሲያዊ ለውጥ ፍላጊነት ተቀባይነት ቀርቶ በለውጥ የማያምን ለውጥም ለመቀበል የተዘጋጀ ስህተቱንም ለማረም ብቃት ያለው የትንሣዔ ተስፋ ሳይሆ ትንሣዔ እንዳይኖር መቃብሩን አርቆ የሚቆፍር ሕዋስ ነበር።ምናልባትም በቆፈረው ጥልቅ ጉድጓድ እራሱን ለመቅበር ጉድጓዱ ጠርዝ ላይ የቆመ  መስሎ ይታያል።

አሁን የተገኘው ለውጥም በአቢዮታዊ ዲምክራሲ መርህ የመጣ ሳይሆን፤ በፀረ አቢዮታዊ ዲምክራሲነት የታፈነው ኃይል ቁጥጥር ውጭ በመሆኑ፣ በሕዝባዊ አመጹ እጅግ እየበረታና በየአቅጣጫው የሚመሽገው የትጥቅ ትግል አስገዳጅነት የታየበት የለውጥ ሂደት እንጅ የውዴታ በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ፈላጊነት የመጣ ትንሣዔ ባለመሆኑ፤ እነ በረክት ስምዖን የአቢዮታዊ ዲምክራሲያዊ  ግንዛቤ ፍጽሞ የሌላቸው በአንድ የቡድን የአፈና አደረጃጀት የተመሠረቱ  አፋኝና አንባገነናዊ መሆናቸውን ይበልጥ ያረጋግጣል። በአፈና ሥርዓት ውስጥ ሰላማዊ ሕይዎት የሚተነፍስ ትንሣዔ አለ ብሎ ማሰብ ቂልነት ነው።

ከዶክተር ዐቢይ አሕመድ አሻጋሪ አመራር ጋር አብዮታዊ ዶሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊመጣ የሚችለው የኢትዮጵያ ትንሣዔ በሕዝብ ፍላጎት ላይ በተመሠረተ የሚከተሉትን የእስትንፋስ አማራጮች መጠቀም ሲችል ነው ማለትም፤

 • ጠቅላላ የነበረውን ሕገ መንግሥት በመቀየር/Complete change of existing constitution/
 • ያለውን ሕገ መንግሥት በማሻሻልና በማስተካከል /Modification of an existing constitution/

ከላይ በተመሠረቱ ሁለት አማርጮች ብቻ በሕዝብ ሙሉ ምርጫና በሕገ መንግሥታዊ የበላይነት የሚተካው መንግሥት አቢዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ተብሎ መመሥረት ሲቻላል ነው። ይህ ከሆነ ከሃያ ሰባት ዓመት አፈና በኋላ የኢትዮጵያ ትንሣዔ የሚጀምረውም ከዚህ ምዕራፍ ነው። ብዙዎች የሚስማሙበት ያለውን ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል Modification of an existing constitution/ መሸጋገር እወነተኛ ሀገር አቀፋዊ ሕዝባዊ አቢዮታዊ ዲሞክራሲዊ መንግሥት ወይም «ትንሣዔ  ዘኢትዮጵያን» መመሥረት ይቻላል በሚለው ይስማማሉ ።

ከዚህም አንጻር የጠቅላይ ምንስትር ዶክተር ዐቢይ አመራር ከአንባገነናዊ ሥርዓት አላቆ አንድ ኢትዮጵያዊ ሀገር በአንድነት «የተደመረ» ሕዝብ አጋዥነት ወደ አንድ በሕዝብ የተመረጠ ማዕከላዊ መንግሥት ጥላ ሥር የሚያሸጋግረን ሊበራሊዝም ዴሞክራሲያዊ  አመራር  መሆኑን መረዳት አለብን። በዚህ አሻጋሪነት የሚተካው ሕዝባዊ መንግሥት አቢዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ተብሎ ሊጣራ ከሚችል በስተቀር የእነ በረከት ስሞዖን አገዛዝ በፀረ አብዮታዊ ዲምክራሲነት ያለፈ በአንድ ጠባብ ብሔር ሰንሰለታዊ  የአፈና መዋቅር ሃያ ሰባት ዓመት ያለ ምንም ለወጥ አርጅቶ በሕዝብ ተፈንግሎ የወደቀ እንኳን ለኢትዮጵያ ለራሱም ትንሣዔ የማይኖረው ነው።

ይህን በሕዝብ መስዋዕትነትና አስገዳጅነት የተገኘውን ለውጥ ለመቀልበስ፣ በሱማሌ፣ በአማራው ክልል በሱዳን ደንበር በኩል፣ በኦሮሚያ ክልልና በደቡብ ሕዝቦች፣ በመስቀል አደባባይ ሕዝባዊ ድጋፍ በሽብርተኝነት ለማኮላሸትና ከቁጥጥር ውጪ ለማድረግ በሕወሀት ፊታውራሪነት የሚነሳው ብጥብጥ ሁሉ፤ ሕወሀት በሀገሪቱ ላይ ወደ ሕዛባዊ መንንሥት የሚያሸጋግር የተረጋጋ አስተዳደር እንዳይኖር የሚያደርገው ሽብር በመሆኑ፤ ስለ አቢዮታዊ ዲሞክራሲያዊነት የመተረክ ሞራሉም ሆነ ብቃቱ የለውም። በመጨረሻው ስዓት የማያውቁትን ያልነበሩበትን አቢዮታዊ ዲሞክራሲያዊ መናፈቅ እና ወደ ነበርንበት እንመለስ እያሉ ማቅራራት ከአሁን በኋላ አንባሻ እንደ መጋገር ቀላል አይሆንም። ብዙ አሽቶ መለወስ፣ ማቡካት፣ ማቅጠንና ምጣዱን ከእሳቱ ጋር አስማምቶ በጥንቃቄ አስፍቶ እንጀራ የማድረግን ብቃት ያለው ሙያን ይጠይቃል።

የበረከት ጎንደር ተወላጅነት የብአዴን አመራርነት፤ ሰው ከሌሎች እንስሳ ከሚለይባቸው አንዱ ባህሪው አንዱ ጎሳ ከተወልደበት ሀገር ክልል ቀየ በልዮ ልዩ ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ምክንያት ተነስቶ ወደ ሌሎች ጎሳዎች መኖሪያ መፍለስና እንደ አስፈላጊነቱ በአዲስ መልክ የሰፈረበትን ጎሳ ባህል መስሎ፣ ከሕዝቡ ጋር ተግባብቶ፣ መልካ ምድራዊ ሕይዎቱን አገናኝቶ፣ ቋንቋውን ለምዶ ተዛምዶ፣ በኅብረተሰቡ ማኅብራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ውሕደትና መጋራትን ፈጥሮ ተባብሮ የመኖር ብልህነቱ ነው። ይህ ደግሞ በተለይም በሀገራችን ኢትዮጵያ ሺህ ዘመናትን ያስቆጠረ ጥምር፣ ቅይጥ፣ ስብጥር፣ የተዋሐደ፣ሐበሻ ብለን የምጠራው ኅብረተሰብን ያስገኘ የሰው ልጆች ሰው የመሆን የግኙኝነት መስመር ትርጉምና ውጤት ነው።

ከዚህም አንጻር የበረከት ስሞዖን ቤተሰቦች ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ወደ አማራው የሀገራችን ክፍል ፈልሰው በመኖራቸው የመጀምሪያዎቹ ባይሆኑም በዚያው ኅብረተሰብ የቆየው ቀጣይነት ባለው  የሕይዎት ውስጥ ጉዞ በማድረግ በረከትን ወልደዋል። በርከትም የተወልደበትን ማኅብረሰብ መስሎ ማደጉ፣ የማኅበረሰቡ አካል በመሆኑ አማራ ሆኖ መኖሩን የሚከለክለው አንዳችም ነገር የለም። መሆን አትችልም ብሎ የሞገተውም የለም። አማራ ሁን ብሎ ያስገደደውም የለም። አማራ እንዳይሆን የሚከለክል ሕግም አልተሠራም።

በረከት አማራ ያልሆነው ኤርትራዊ  ቤተሰቦቹ በአማራ ምድር ስለወለዱት ሳይሆን፤ ተወልዶ ያደገበትን፣ ባህሉን ቋንቋውን አውቆ በወሃው ተራጭቶ፣ በአፈሩ ፈጭቶ፣ በአማራ ጎረቤቶቹ እቅፍ አድጎ፣ ፊደል ቆጥሮ ያደገበትን የአማራ ማኅበረሰብ ከምደረገ ገጽ ለማጥፋት በረሀ ገብቶ አማራውን በጠላትነት ፈርጆ በተቀረጸ ሕወሀታዊ ማኒፌስቶ ውስጥ ሰልጥኖ አማራውን ማኅበረሰብ መስሎ በሁለት መልኩ የተሳለ መርዘኛ ሰይፉ ሆኖ፤ 1ኛ/ ሕወሀት በቀረጸው ብአዴን ድርጅት ውስጥ የአማራው ክልል ፈላጭ ቆራጭ ከሆኑ የትግሬ ተወላጆች ጋር በማበር በእራሱ አማራው ክልል ውስጥ በነበረው ኃላፊነት፤ 2ኛ/ በማዕከላዊ መንግሥት ከፍተኛ የፓሊት፣ የምንስትር የመረጃና የፓሮፓጋንዳ ቁልፍ የሥልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጦ አማራውን፣ ለችግር፣ ለስደት፣ ለጀምላ እሥራት፣ ለግድያ፣ ለማፈናቀልና ለዝርፊያ ሥር የሰደደ ከፍተኛ ወንጀል እንዲፈጸምበት በአመራር ሰጭነት ደረጃ ከፍተኛውን ሚና በመጫዎቱ በአማራው ኀብሔረሰብ ዘንድ እጅግ የተነቀፈ በጨረሻም ከአማራው ውክልና የተባረረ በመሆኑ ትንሣኤ የለውም።

በረከት ተናገረም አልተናገረም አማራው በኢትዮጵያን እንደ ሀገር በማነጽ፣  በእድገት፣ ሥልጣኔ፣ ከውጭ ወራሪ ከውስጥ መሰሪ በመከላከል በማኅበራዊና ቁሳዊ ትስስሮች ሁሉ ከባድ ቀንበር ተሸክሞ ያለፈ እንደ ውቅያኖስ ጥልቅ የሆነ ተቀድቶ የማያልቅ፣ ተጽፎ የማይጠቃለለል፣ተነቦ የማይቋጭ አኩሪ ታሪክና ባህል ያለው የአንድነት ምሰሶና ማገር መሆኑ የማይጠረጠር ቢሆንም፤ በባህልና በሃይማኖት ተሸፍኖ በከዳተኞች፣ አፍራሽነትና ከፍፋይነትን፣ስርቆትንና ዝርፊያን ባህል ባደረጉ ክፍሎች በመደብ ጠላትነት ፈርጀው እስከ መጨረሻው ደረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከምድረገጽ ለማጥፋት በሙሉ ኃይላቸው ሲወጉት ከመጠን የዘለለ የመታገስ መለኮታዊ ባህሪ አልተሰጠውም። በመሆኑም ለሃያ ሰባት ዓመት አማራውን ያስጨፈጨፈውን በረከት ስሞዖንን በእራሱ በአማራ ትግልና የሕይዎት መሰዋዕትነት ከአማራው ትከሻ ላይ ማስወገዱ ወቅቱ የሚጠይቀው ትክክለኛ ምላሽና የሀገራችን ኢትዮጵያ ትንሣኤ ዋዜማ  ነው።

በረከት አማራ ቁሳዊ፣ማኅበራዊና ባህላዊ እሴት ውስጥ ተወልጀ ያደኩኝ አማራ ነኝ በብአዴን እወክላለሁ ካለ የሚያውቀው የአማራ መሬት ወልቃይት ጠገዴ፣ ሁመራ እና ራያ አዘቦ ከአማራው ክልልና ማኅበረሰብ ነባር ይዞታነት ሲነጠቁ፣ ቢያንስ ሦስት ሚሎዮን አማራ ህዝብ ሲጠፋ፣ እናቶች እንዳይወልዱ ማምከኛ ሲከተቡ፣ በወልቃይት አካባቢ የሚገኙ ዜጎች የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸምባቸው፣ በእሥር ቤት ግፍ የተመላው ደብደባና ሰቆቃ የአባለዘር መኮላሸት ሲደርስባቸው፣ እረጅም ዘመን ያስቆጠሩ በአማራው ክልል የሚገኙ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ የውኃ መጎተቻ ጀነረተሮች ወደ ትግሬ ተዘርፈው ሲጫኑ፣ አማራው እንደ አማራው ከመሠረተ ልማት ሲገለል በቅርብ የሚያውቀው የብአዴን ሥራ አስፈጻሚ የበረከት ስምዖን ድምጽ ሳይሰማ ዛሬ  በሕወሀት ዘመን የሞተችውን ሀገር የኢትዮጵያ ትንሣዔ  ብሎ በደፍረት ያለሀፍረት ሊሰብከን ከቶ ምን ዓይነት የሞራል ብቃት ሊኖረው ይችላል? ይልቁንም ከላይ በተጠቀሱት ወንጀሎች ሁሉ ግንባር ቀደም ተጠያቂ ሆኖ ለፍርድ መቅረብ አለበት።

በረከት በአማራው ማኅበረሰብ ግፍ ሲፈጽምበት በኖረበት በሁለት በኩል ከተሳለ  ከፍተኛ ህወሀታዊ ሥልጣኑ የሕዝብ መራራ ትግል አሽቀንጥሮ ከጣለው በኋላ እንኳን በአማራው ክልል መጠነ ሰፊ ገንዘብ ይዞ እየዞረ በመስዋእትነት የተገኘውን የለውጥ ወጋገን መልሶ ለማጨለም በመጨረሻው ስዓት ያደረገው የተንኮልና የክፋት እሩጫ፣ እንዲሁም  በምሥራቃዊ የሀገራችን ክፍል በጅግጅጋ አማራውና ኦሮሞው ያቀናውን ምድር የጥፋት አውድማ ማድረግና የሰው ልጅ እንደ ማገዶ በእሳት እንዲነድ፣ አቢያተ ክርስቲያናት እንዲቃጠሉ የተቀነባበረ ሴራ ያስፈጸመው ይኸው የሕወሀት ቀኝ ክንድ በረከት ስምዖን የሸረበው ለውጥን የማጨለም ተንኮል ነው።

ይህ ሁሉ ሳይበቃው በውድቀቱ ጠርዝ ላይ ቆሞ በተረፈው አነስተኛ ደቂቃዎች ሳይቀር  ሰይፉ የሚባለውን የቧልት ሚድያ ተገን አድርጎ ትግሬን፣ ሱዳንን እና አፋር በአንድነት በአማራ ላይ በጠላትነት እንዲነሱ ያስተላለፈውን የጦርነት ክተት አዋጅና ቅስቀሳ  እንዲሁም አሽቀንጥረው የጣሉትን በአማራ ክልል ያሉትን የለውጥ አይከኖች አሳንሶ ለማቅረብ የሞከረበት፣ በክልልሉ ያሉትን ወጣቶች በመደለያ አፍኖ ለማያዝ ያደረገው ሙከራ፤ ይህ አልሳካ ሲለው የወደፊት አቅጣጫ ወይም ርዐይ የላቸውም በማለት የተቸበትን በብዙ መልኩ አበጥረንና አንጥረን  ስንመለከት ይህ ሰው የማራውን እንጀራ በልቶ ያደገ ነገር ግን የአማራው ሕዝብ   ትንሣዔ እንዳይኖረው እስከ ዕለተ መቃብሩ ድረስ የከፋና የጠለቀ የጠላነት ድርሻ እንዳለው ማረጋገጡ እጅግ በጣም ቀላል ነው።

በ1997 ዓ.ም በተደረገው ሀገራዊ መርጫ ተከትሎ በውጪ ሀገር የምርጫ ታዛቤዎች ጭምር የሕዝብ ድምጽ ባማጭበርበር ለዓለም ይፋ የሆነውን ዜና የማጭበርበሩ ተግባር በቀዳሚነት ያስፈጸመው በረከት ስምዖን መሆኑ ከመታወቁም በላይ በአዲስ አበባ ከተማ ማጭበርበሩን በመቃወም ሰላማዊ ሰለፍ በወጣው ሕዝብ ላይ በቀጥታ በመተኮስ ከአንድ መቶ ዘጠና በላይ የሆኑ ንጹሐን ዜጎች እንዲገደሉ አስተዋጾዖ ካደረጉት መካከል ግንባር ቀደም ተጠያቂ በመሆኑም ነው።

በተለይም በክብርት አና ጎሚዝ የተመራው የአውሮፓ ኅብረትን የምርጫ ታዛቢ የውጭ ሀገር ልዑካንን እወነተኛ ሪፓርት በሀሰት መርዝ ቀብቶ በማጣጣል ስም በማጠልሸት በሕዝብ ድምጽና በዜጎች ሕይዎት ላይ ቁማር የተጫወተ ወነጀለኞ መሆኑ በእነዚህ ሉዑካን ጭምር የተረጋገጠ ወንጀል ሆኖ ሳለ በእርሱ የሥልጣን ዘመን ኢትዮጵያ ውርደትና ውድቀት የገጠማት ዘመን እንጅ ትንሣኤ አልነበራትም።

የአውሮፓን ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ መሪ አና ጎሚዝ የኢትዮጵያ ሕዝብ የደረሰበትን የምርጫ ማጭበርበር በቅርብ ሆነው ስለተመለከቱ፤ ከዚያን ዕለት ጅመሮ በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ውስጥ  በሕዛባዊ ታላላቅ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ላይ የሀገራችን ኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ በመሆን የእነ በረከት ስምዖንን  የተቀናጀ ወነጀል ለዓለም ያጋለጡ፣ በግፍ ለታሠሩ ኮር የተቃዋሚ የፓለቲካ አባላት የጮኩ ከአንድ  የሀገርና የሕዝብ  ተቆርቋሪ ዜጋ በላይ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉ ትውልደ ፓርቱጋላዊት እመቤት ናቸው።

ታሪክ እንደሚያስረዳን ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ እየቀረቡ የመጡ አውሮፓውያን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባህል፣ ታሪክ ጋር በቀላሉ ተላምደው በፍቅር የመኖር ብቻ ሳይሆ ከአንድ ዜጋ በላይ ሕይዎታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የደረሱ ትውልደ አውሮፓውያንን መጥቀስ የዚህን ጽሑፍ መሠረተ ሐሳብ የታሪክ ድጋፍ የጎላ ያደርገዋል።

በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ለስለላ  በምጽዋና በአሰብ የተላኩት ጆን ቤል፣ ፕላውዴንን ብንመለከት ንጉሡ ለሀገራቸው ያላቸውን የሥልጣኔ መጠማትና የግዛት አንድነት ማስፋት ጠንካራ ዓላማ በቅርብ ሆኖ በመረዳትና የሕዝባችን ባህልና የአኗኗር ዘዴ ተማርከው ለንጉሡ ወግነው  በአውደ ጦርነት ሕይዎታቸውን የገበሩ እንግሊዛዊያንን ስንታስታውስ፣ በጣሊያን ወረራ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል በማጋለጥ ደረጃ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱትን የተከበሩ ሚስስ ፓንክረስትን ስንዘክር እንዲሁም ልጃች ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትም በኢትዮጵያ ሕዝብና ታሪክ ፍቅር ሥር ወድቀው በገናናው የሀገራችን ታሪክ ተማርከው ጥልቅ ምርምር በማድረግ፣ በውጭ ሀገር ወራሪዎች የተዘረፉ ጥንታዊ ቅርሶች እንዲመለሱ ሁሉ ታላቅ አስተጾ በማድረግ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ታግለዋል። ከዚህ በፊት በተደረገ የታሪክ ጎዞ ፤ የዘመናችን የኢትዮጵያ ጠበቃ ፓርቱጋላዊት  ክብርት አና ጎሚዝን ከቀደምት የፓርቱጋልና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ግኙኝነት ጋር አገናዝበን ስንመለከት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከእነ በረከት ስምዖን የተሻለ አስተዋጽዖ ያደርጉ መሆናቸውን እንረዳለን።

ልክ እንደ አሁኑ ሕወሀት እነ በረክት ስምዖን አብዲ ኢሌ የሚባል ጋጠ-ወጥ አስልጥነው በምሥርቁ ክፍል እረጅም ዘመን ያስቆጠሩትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በማፈናቀል፣ አቢያተ ክርስቲያናትን በማቃጠል፤ ሰዎችን ከእነ ሕይዎታቸው ማገዶ በማድረግ ካህናትን በስለት በማረድ ወነጀል እንደፈጸሙ ሁሉ፤ በ12ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ እንደ ቱርክ ባሉ አዳዲስ አክራሪ የእስልምና ተስፋፊ ሀገሮች ግራኝ መሐመድ የሚባል ወራሪ አስነስተው ብዙ ቅርሶችን አቢያተ ክርስቲያናትንና ካህናትን በጀመላ ሲጨፈጭፍ ሀገሪቱን እንዳልነበረች ያደረጓት መሆኑ ዝክረ ታሪክ ዘኢትዮጵያ በግልጽ ያስረዳሉ።

በወቅቱ የነበረው የአና ጎሚዝ  የተውልድ ሀገር የፓርቱጋል መንግሥት የስለጠኑ ወታደሮችን በመላክ  በኢትዮጵያ ላይ የነበረው አስከፊው የግራኝ አሕመድ የወረራና የጥፋት ዘመን እንዲገታ ያደርገውን አስተዋጽዖ ስናስታውስ በተቃራኒው በሃያኛው ክፍለ ዘመን የእነ በረከት ስምዖን አያቶች ፓሻዎች፣ ሹንባሾችና ቃፊሮች የጣልያን ቸላና ዲናሬ ተቀጣሪዎች ሆነው ጣሊያንን መንገድ እየመሩ በአማራው፣ በተለይም በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮ ክርስቲያን ላይ ያደርገው ጭፍጨፋ፣ የብልት ቆረጣ ዛሬ በልጅ ልጆቻቸው በእነ በረከት ስምዖን  አቀነባባሪነት ከሚደረገው ወነጀል  ጋር ደምረን በንጽጽር ስንመለከተው ምንም ልዩነት የለውም።

የክብርት አና ጎሚዝ  እንደ አንድ ዜጋ ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿን በክፉ ቀን መርዳት መተባበር የቆየ ታሪካዊ ትስስር ያለውን አስተዋጽዖ፤ በተቃራኒው የእነ በረከት ስምዖን ኢትዮጵያን የማጥፋትና የመበታተን የታሪክ አሻራ ሁሉ በንጽጽር ተመልክተን በትክክለኛ የዳኝነት  ወንበር ተቀምጠን ፍርድ ብንሰጥ ክብርት አና ጎሚዝ  ከበረከት ስምዖን የተሻለ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ሊኖራቸ የሚስችልና በኢትዮጵያዊያን የወደፊት የታሪክ መዝገብ ውስጥ የማይረሳ ምዕራፍ ያላቸው ተስፋ ለተጣለበት የወደፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ትንሣዔ በክፉ ቀን ጠበቃ የሆኑ ታላቅ ክብር የሚገባቸው እመቤት ናቸው። ከዚህ አንጻር በረከት ስምዖን አና ጎሚዝን ኢትዮጵያዊ ዜግነት አለመኖር የመተቸት ታሪካዊ አሻራውና አሁን ያለው ሞራላዊ ብቃቱ አይፈቅድለትም። በበረከት ስምዖን ዘመን ኢትዮጵያ ትንሣዔ አልነበራትምና።

የበረከት ተቆርቋሪነት የትግሬ ሕዝብ ከጎንደር መፈናቀል፤ ባለፈው ጊዜ «ትግሬና ጎንደር» በሚለውን ንዑስ ርዕስ በሁለቱ ማኅበረሰብ መካከል ያለውን የቀረበ ታሪካዊ ትስስር ጽሕፌ ለንባብ ማብቃቴን አስታውሳለሁ። እርግጥ ነው የትግሬ ሕዝብ ይኑር ከተባለ ሊኖር የሚችለው  ከአማራው በተለይም ከጎንደር ሕዝብ ጋር ብቻ ነው። ለዘመናትም አብረው ኖረዋል። በክፍለ ሀገሩ ብቻ ወደ ሃያ አምስት ሺህ የሚገመቱ ትግሬ ከአማራው ሕዝብ ጋር በእቁብ፣ በእድር፣ በማኅበር፣ በአምልእኮት፣ በሠርግ በጋብቻ ተሣስሮ ዘመናትን አስቆጥሯል። ይህ ሕዝብ ከሕወሀት በፊት ተለያይቶ ጦርነትን ያደረገበት ዘመን አይታውቅም።

አፄ የሐንስም ምንም እንኳን የእንግሊዝ ቃፊር ሆነው በር ከፍተውና በቅሎ ሳቢ ሆነው፣ መንገድ መርተው የንጉሡ ሞት ቢያፋጥኑም፤ እስከ እንግሊዝ ወረራ  ዋዜማ ደረስ «ባላንባራስ ካሣ ምርጫ» እየተባሉ የአፄ ቴዎድሮስ ገባር ሆነው ድምጻቸውን አጥፈተው የኖሩ ሰው ናቸው።  በመካከላኛው የሀገራችን ክፍልም ልጃቸውና የልጅ ልጆቻቸው ከማራ ከኦሮሞ የጋብቻ ትስስር አላቸው። ራስ አርያሥላሴ ዮሐንስ እቴጌ ዘውዲቱ ምንይልክን፣ ባንዳው ኃይለሥላሴ ጉግሳ አርያ ዩሐንስ ልዕልት ዘነበወርቅ ኃይለሥላሴን፣ ራስ መንገሻ ስዮም መንገሻ ዮሐንስ ልዕልት ዐይዳ ኃይለሥላሴን ተጋብተው ተዛምደዋል።

እነ በረከት ስሞዖንም በዚሁ የባህል የታሪክ ተሣሥሮና ተሰባጥሮ በአማራው ክልል በመኖር በአማራው መሬት ላይ የተወለዱ የቀደሞ ተከባብሮና ተሳስቦ የመኖር ወጤቶች ነበሩ። በተለይ በመንፈሳዊ ትምህርቱ በኩል የጎንደርን እንጀራ ለምኖ ያልበላ የትግሬ ተማሪ አይገኝም። ዛሬ እነ ሊቁ መምህር እንደሥራቸው አግማሴን በትግሬ መሬት አሳስረው በቤተ ክህነቱ ውስጥ  እንደ ፈለጉ የሚንደላቀቁት ቀንደኛ የአማራ ጠላት የሆኑት እነ አባ ኤልያስ አብርሃ የጎንደርን እንጀራ እየበሉ ያደጉ ከጎንደር ሊቃውንት  እውቀት የቀሰሙ ነበሩ።

ሆኖም የትግሬ ሕዝብ ሕወሀት ሥልጣን ከያዘ በኋላ፤ ከቁቡም፣ ከደሩም፣ ከማኅበሩም፣ ከጋብቻ ትስስሩም፣ ከቆየ ወዳጅነቱ አፈነገጠ። ከሕወሀት በሚሰጠው መመሪያ አማራውን  በክፍተኛ ጠላትነት ይፈርጀው ጀመር፤ የገንዘብ ባቤት በመሆኑ በአማራ መሬት እየሠራ የሚያገኘውን ንብረት በሙሉ በትግራይ ልማት ማኅበር ማስቀመጥ፣ በተግራይ ባንኮች ማካበት፣ ከትግራይ ባንኮች በሰፊ የጊዜ ገደብ በገፍ በመበደር፤ በብሔራዊ ባንክ በአጭር የጊዜ ገደብ ተበድረው በንግድ ሥራ የተሠማሩ የአማራ ነጋዴ ድርጅቶችን የባንክ ዕዳ ባለመክፈል ምክንያት እያደረጉ በጨረታ ስም  በርካሽ በመግዛት፣ ያለቀረጥ በማስገባት  የአማራ ነጋዴዎችን ማዳከም አበሳጭቶ ከገበያ ውጭ ማድረግ የግፍ ግፍ ተፈጸመ ።

ከዚያም አልፎ የአማራውን ታሪካዊ የጎንደር ክፍለ ሀገር ነባር ይዞታዎች ወደ ትግሬ ከመከለል በተጨማሪ የትግሬ ክልል በእብሪትና በትዕቢት እየተወጠረ እስከ እራስ ደጀን ተራራ ድረስ መጣ። በወሎም እስከ ላሊበላ መቅደስ ድረስ በመገስገስ የአማራው ጥንታዊ ቅርሶች በሙሉ የትግሬ ናቸው የሚል የማስተማሪያ መጽሐፍት ታትመው ለትምህርት ቤቶች ታደሉ። በዚህን ጊዜ ሁሉ እነ በረከት የሚሰማ ጀሮ፣ የሚመለከት ዓይን፣ የሚያስተውል ልቦና የሚያመዛዝን አዕምሮ የላቸውም ነበር። ሕያዋን ሳሉ ሙታን ነበሩ ትንሣኤ አልነበራቸውም። ይልቁንም የአማራውን ግባተ መሬትና ከጎንደር ምድር የማጽዳት ሥራቸውን ያፋጥኑ ነበር። ትንሣኤን ተስፋ እንዳያደርግ ጉድጓዱን አጥልቀው ይቆፈሩ ነበር። ተዛማች ብሽታዎችን በተመሳሳይ መርፌ በመከተብ፣የማምከኛ መዳህኒቶችን በማደልና በመውጋት፣ በመኢሀድ፣በግንቦት 7፣ በአሸባሪነት ስም እየተሰጡ በጀምላ ማሰርና በማንገላታት፣ ተቆጥሮ የማያልቅ ግፍ ተፈጽሞበታል። በአንድ ወቅት ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በመቀሌ በተደረገው ስብሰባ «አሁን በጎንደር ሕዝብ የደረሰው መከራ»በማለት በተሰበረ አንደበት የገለጹት ለአብነት ማስታወሱ ተገቢ ነው።

ጥንት በአማራው ምድር ጎረቤት፣ ዘመድ፣ ቡና አጣጭ፣ እድር አባል፣የጽዋ ማኅበርተኛ ወዳጅና ዘመድ የነበረው ትግሬ ሁሉ የሕወሀት ነጭ ለባሽ ሆኖ አማራውን እየጠቆመ የሚያሳስር የሚያስገድል፣ ለደህነትና ለበሽታ የሚጋልጥ ያልታሠበ ያልተጠበቀ ቀንደኛ ጠላት ሆነ። ጥጋብ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ የግፍ ጽዋ ሞልቶ ፈሰሰ። በዚህን ጊዜ የአማራው ሕዝብ የለም ግፍ በዛብን እንደጥንቱ እንደ ጧዋቱ አብረን መኖር አልቻልንም ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ ቢያንስ ሕይዎቱን ለማቆየት ወዶ ሳይሆን ተገዶ ሰላይ ትግሬዎችን በዓይነ ቁራኛ ይመለከታቸው ጀመር ።

ይህን የተረዳው ሕወሀት መሀል ጎንደር ይኖር የነበረውን ትግሬ ለሊት በአውሮፕላን በማጓጓዝ፣ በጎንደርና በሱዳን ጠረፍ የአማራ  መሬት የሰፈረውን ትግሬ በሰላም አውቶብስ በማጓጓዝ አንድ ላይ ሰብስቦ  ለሚዲያ ፍጆታ ለማዋል በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለአልጃ-ዚራ ቴለቪዝን ከፍሎ በሚያሳዝን ሁኔታ «ጎንደርያን አናሳዎቹን ዳሃ ትግሬዎችን ከጎንደር ምድር አፈናቀሉ» በማለት  አማራው ላይ በዓለም የታወቀ ጥላቻ እንዲፈጠርና የግደያ ዘመቻውን ለማፋጠን በዓለም ዙሪያ ሁሉ ዜናውን ተሰራጨ።

አያይዞም ኃይለማርያም ደሳለኝን ታዛዥ አድርጎ በማስፈረም የሀገሪቱ ጦር ማንኛውንም እርምጃ በአማራ ላይ እንዲወስድ በብሔራዊ ደረጃ በጠቅላይ ምንስትሩ ሥልጣን ልዩ የጭፍጨፋ ትእዛዝ ታወጀበት። የትግሬ ልዩ ኃይል በየጓዳው እየገባ ብዙ ወጣቶችን አሰቃየ ፎቅ ላይ ሆኖ በስናይፐር እያነጣጠረ አናታቸውን አፈረሰ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ደብረ ማርቆስ፣ ወልደያ፣ደሴ በደም ታጠበች። ይህን ሁሉ በደል የሚመለከት ዓይን አልተገኘም። በየጊዜም አማራው ንብረቱ እየተቀማ ከብዙ ክልልሎች እንዲፈናቀል ተፈረደበት።ማንም ዘወር ብሎ ያየው የለም።እነ በረከት ይህን የመቃብርና የጨለማ ዘመን የኢትዮጵያ ትንሣኤ ብለው ይጠሩታል።

ትንሣዔ ባላዋቂዎች ዘንድ ቀላል ቢመስልም፤ በሚያውቁት ዘንድ ግን ተጽፎ የማያልቅ ምስጢር አለው፡፡ አንዱን ነፃ እያውጣህ ሌላውን እየገደልክ፣ አንዱን በላተኛ ሌላውን ፆም አዳሪ፣ አንዱ ተገዳይ ሌላውን ገዳይ እያደረክ፣ የአንድ ክልል ሰዎችን ከላይ አስከታች  በሥልጣን ማማ ላይ አሰማርተህ ህዝብን በግፍ ዱላ እያስቀጠቀጥክ፣ የአንዱን ሕይዎት እያጨለምክ የሌላውን እያበራህ በኖርክበት ዘመን የኢትዮጵያ ትንሣኤ ነበር ማለት ትርፉ በወርደት ላይ ውርደት መጨመር ብቻ ካልሆነ በስተቀር የሚሰማ ጀሮ የለም። የትንሣኤ ብርሃንን ትርጉም ያዛባል ብርሃናዊ መልዕክቱንም ጨለማ ያደርጋል።

ስለዚህ «ትንሣኤ ዘኢትዮጵያ» የሚለው የበረከት ስምዖን ፓሮፓጋንዳ ከማንበባችን በፊት «ከእባብ እንቁላል እርግብ» እንደመጠበቅ ተቆጥሮ ከዚህ በላይ በተሰጠው አጭር መሠረተ ሐሳብ ምላሽነት «መጽሐፉ» ላይ ጊዜ ማጥፋት ተገቢ አይደለም። በበረከት ስምዖን ብቻ ሳይሆን ህወሀታዊ  ርዮተ ዓለም ንክኪ ያላቸው ሰዎች በሙሉ የሚያቀርቡትን ማንኛውንም ነገር ማንበቡ ተገቢ ቢሆንም አሁን ላለንበት የጠቅላይ ምንስትር ዶክተር ዐቢይ አሻጋሪ መንግሥት ግንባታ ከፍተኛ እንቅፋት የሚፈጥር ሥውር ተልዕኮ ያለው መሆኑን ፈጥኖ በመረዳት ከዚህ ቡደን ነባራዊ ሕይዎት ጋር በማገናዘብና  ወዲያውኑ አሽቀንጥሮ መጣል በጥቅሉ በሕወሀት ዘመን ኢትዮጵያ ትንሣኤ አልነበራትም በሚል ቁርጠኛ  ውሳኔ  መድረስ ተገቢ ነው።

ቀጣይ ጽሑፎች፤

 • የዓመተ ምሕረት ሰዎች እንሁን +አዲሱን ዓመትና ለወጡን አስመልክቶ
 • የአንበሳ ሥጋ የበላው የሕወሀት ዶክተር በአንበሳ ግቢ፤
 • ግንቦት ሰባት ማን ነው፤ አርበኞችስ እነማን ናቸው፤ የሚሉትን ጽሑፎች በቅርብ ቀን ማቅረብ ፍላጎት አለኝ ፤

ቸር ይግጠመን። ከመንገሻ መልኬ፤

ጳጉሜን 2 ቀን 2010 ዓ.ም፤ ለንደን ከተማ፤

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s