ከህወሓት ጋር ተናንቆ የተሰዋው የኢህዴን ታጋይ አስደማሚ ታሪክ! (ጓዶቹ እንደፃፉት)

(ጓዶቹ እንደፃፉት)

~”እኔ እኮ የምታገለው የኢትዮጵያን ህዝብ ከደርግ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት እንጅ ህወሓትን ለማገዝ አይደለም”

ይርጋ አበበ በትግል ስሙ ሀው ጃኖ/ ይባላል። ስለ ጀግንነቱ ደግሞ የራያው መብረቅ ይሰኛል

በ1975 ዓ/ም ትግሉን ከኢህዴን ጋር ተቀላቀለ፡፡ ጎበዝ ተዋጊ እና አዋጊ ጀግና ስለነበር የኢህዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ለመሆን ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል መሆኑ በሰራዊቱ ውስጥ የሚደረግ አድሎአዊ አሰራርን ለመቃወም አስችሎታል፡፡ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ ወቅትም ሆነ በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲሁም በኢህዴን ጦር መካከል በሚደረግ ስብስባ ህወሓት በኢህዴን ላይ የሚያደርገውን የቀጥታ ጣልቃ ገብነት በጽኑ ያወግዝ ነበር፡፡ ይህን በማድረጉም በአድር ባዩ ኢህዴን/ብአዴን አድር ባይ ዓመራሮች አልተወደደለትም ነበር።

ሓው ጀኖ ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ የኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኖ የተመረጠ ሲሆን ብዙ ጦርነቶችንም በአዛዥነት ተዋግቶ አዋግቷል። በተለይም በጉናና ደብረታቦር አካባቢዎች በተደረጉ ጦርነቶች የተሰጠውን ግዳጅ በጀግንነት ተወጥቷል።

ይህ ታጋይ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከደርግ ሰራዊት ጋር በሚደረገው የጦርነት ወሎ ግምገማ ላይ በህወሃት አመራሮች የሚነሳውን “ኢህዴን ፈሪ ነው፣ በቀላል የውጊያ ስልት የተሰጠውን ግንባር አሸንፎ ብዙ ንብረት መማረክ እየቻለ መስዋትነት ስለምትፈሩ አውዳሚ የጦር ስልት ትከተላላችሁ፣ … ከደርግ የተማረኩ ወታደሮችንም በታጋይነት በኢህዴን ውስጥ እየገቡ እንዲታገሉ አድርጉ ሲባል ፍላጎቱ የላችሁም፣.. ህወሓት ለትግራይ ህዝብ ብቻ የሚታገል ብሄርተኛ ድርጅት መሆኑን እያወቃችሁ ለምን ምርኮኛ ወታደሮች በህወሓት ስር ጭምር ተደራጅተው እንዲታገሉ አይደረግም የሚል ማዕከላዊነትን ያላከበረ ጥያቄ ታነሳላችሁ፣… በትግሉ ወቅት የሚማረኩ ከቀላል እስከ ከባድ መሳሪያዎችንም ህወሓት ብቻውን ለምን ይወስዳል የሚል ጥያቄ ታነሳለችሁ” የሚል ሂስ በሰፊው ይቀርብ ነበር።

ይህ ጀግና ደግሞ፣ “እኔ እኮ የምታገለው የኢትዮጵያን ህዝብ ከደርግ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት እንጅ ህወሓትን ለማገዝ አይደለም። ድርጅታዊ የትግል እኩልነት የለም።” የሚል ጠንካራ ትችት ያቀርብ እንደነበር በወቅቱ በትግሉ የነበሩ አሁንም በህይወት ያሉ ታጋዮች ህያው ምስክሮች ናቸው። በዚህ ሃገራዊ አቋሙ ምክንያት በህውሃት ከፍተኛ አመራሮች ጥርስ የተነከሰበት ሀወጀኖ መለስ ለታምራት “ከኢህዴን አመራርነት አሰናብቱ እና ገለል ይበል…” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ያስተላልፋል።

እነ ታምራት ላይኔም የመለስን ትዕዛዝ ተቀብለው ከአዋጊነቱ ተነስቶ የሎጅስቲክስ አመራር እንዲሆን ያደርጉታል። በዚህ ሃላፊነቱም ቢሆን የኢህዴን ሰራዊት አባላትና ክፍለ ህዝቦች ለስራ የሚያስፈልጋቸውን ከምግብ እስከ አልባሳት ድረስ እንዳያገኙ እና ትግሉን እንዲጠሉ ሲደረግ በተቃራኒው ከደርግ የተማረኩ ብርድልብሶችና ዮኒፎርሞች ግን ለህወሓት ሰልጣኞች ይሰጥ የነበረ መሆኑን አሁንም ለግምገማ ያቀርባል። በተለይም ህወሓት ሃገረ ሰላም ላይ በነፃ መሬት ወደ ትግሉ የተቀላቀሉ ወጣቶችን ትምህርት ቤት ከፍታ በራሷ ካሪኩለም ቀርፃ ስታስተምር ነባር የጎንደር እና የወሎ ራያ አማራ መሬቶችን በትግራይ ስር እንደሚተዳደሩ እና የትግራይ መሬቶች እንደሆኑ የምታስተምር መሆኑን የተረዳው ሀወጀኖ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ሲል ለማዕከላዊ ኮሚቴ ጥያቄውን አቅርቦ ሲሟገት “…እኛ ኮሚኒስቶች ስለሆንን ሃገር የለንም። ደርግን ከጣልን በኋላ ህዝቡ እራሱ ይወስናል እናስተካክላለን…” እስከማለት ደርሰው እንደነበር የትግል ጓዱ አጫውቶኛል።

በዚህ ወቅት ታዲያ ህወሓት “ይች ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም” የሚል ሴራ ተሴረበት። በኢህዴን አመራር በኩል ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነቱ እንዲታገድና ከሎጅስቲክስ ሃላፊነቱም ተነስቶ በወቅቱ ኢህዴን ወታደር ያሰለጥንበት ወደነበረው አዲስ ዘመን አካባቢ እንዲዛወር አደረጉ። ይህን ጊዜ ሁኔታው አላምር ያለው ሀወጀኖ በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ የተያዘውን ይህንን ምስጢር ዘክዝኮ በመፃፍ ለተወሰኑ የድርጅት አባላት በድብቅ አሰራጨ። በውጤቱም እኛ ፈሪ ከሆንን ህወሓት እራሱ ይወጣው ሲል የኢህዴን ታጋይ ይመክር እና ጋሳይ አካባቢ በተደረገው ጦርነት የህወሓት አንዲት ሃይል ሰብራ ገብታ የኢህዴን ሃይሎች ደግሞ ግራና ቀኝ ከበባ እንዲያደርጉ የተሰጠውን ትዕዛዝ አልቀበልም በማለት ሰብራ የገባችው የህውሃት ሃይል በደርግ የቀለበት ውጊያ እንድትጠቃ በመደረጉ የህወሃት ሰራዊት ወደ ኋላ ለማፈግፈግ እንደተገደደ አጫውቶኛል።

ከዚህ ሽንፈት በኋላ ህወሓት የለመደችውን ስለላ እና አደናጋሪ ግምገማ መሰረት አድርጋ “ሀወጀኖ ከጀርባ ሁኖ ወግቶናል ስለዚህ ባለበት መታሰር አለበት” ስትል ኢህዴን ሀው ጃኖን እንዲያስር ትዕዛዝ ተሰጠው። ለዚህ ተልዕኮም ህላዊ ዮሴፍ፣ ታደሰ ካሳ እና ንጉሴ ጺሞ ወደ አዲስዘመን ተላኩ። ስብሰባም ጠሩ። ይህንን ስብሰባ በጥርጣሬ ያየው ሀወጀኖ ወደስብሰባው ከመግባቱ በፊት ሙሉ ትጥቅ ታጥቆ ሲገባ የተመለከተው ፀሃየ የተባለ ታጋይ “የት ልትሄድ ነው…?” ብሎ ሲጠይቀው “ወደ ሰማይ ቤት” ብሎ እንደመለሰለት ታሪኩን ያጫወተኝ ታጋይ ፀሃየ ነገረኝ ሲል አጫውቶኛል።

ሚያዚያ 20 ቀን 1983 ዓ.ም ረፋድ 5፡00 ሰዓት አካባቢ አይቀሬው ስብሰባ ተጀምሮ ሀው ጀኖ “ከድርጅቱ መርህ ውጭ የማዕከላዊ ኮሚቴ ምስጢር ለታጋዮ አውጥተሃል” የሚል ግምገማ ከላይ በጠቀስኳቸው ሰዎች ሲቀርብ ደሙ የፈላው ሀው ጀኖ የያዘውን ክላሽንኮብ አቀባብሎ ወደ ታደሰ ካሳ ሲተኩስ ታደሰ ጥንቅሹ እና ህላዊ ዮሴፍ በመስኮት ዘለው እንዳመለጡና ንጉሴ ፂሞ ተቀምጦ እንደቀረ እና ሀወጀኖም በብስጭት ውስጥ ሆኖ ተኩሶ እንደገደለው አጫውቶኛል። ከዘ በኋላ ከነ ህላዊ ዮሴፍና ታደሰ ጥንቅሹ ጠባቂዎች ጋር ተታኩሶ እንደተገደለ እና በአዲስ ዘመን ቅድስተ ሃና በተክርስቲያን እንደተቀበረ በእልክና በቁጭት እየተናጠ ይህ የአይን ምስክር ታጋይ አጫወተኝ።

(የዚህ ጀግና ታጋይ አፅም ከአዲስ ዘመን ተወስዶ ነገ ራያ አላማጣ ላይ ያርፋል)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s