ዴሞክራሲ ወይስ የተረኛነት ጥያቄ? የኦሮሞ ፖለቲካ ወዴት? (ብርሃኑ አበጋዝ (ዶ/ር) )

ዴሞክራሲ ወይስ የተረኛነት ጥያቄ?
የኦሮሞ ፖለቲካ ወዴት?
***
ብርሃኑ አበጋዝ (ዶ/ር)
***
ለዚህች አነስተኛ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ የሰሞኑ አክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች አካሄድ ነው፡፡ እነዚህ አካላት ቡራዩና አሸዋ ሜዳ ላይ በንጹሐን ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን ላይ የተፈፀመውን ፍፁም ኢሰብአዊ የሆነ የጥፋት እርምጃ ከማውገዝ ይልቅ፣ ድርጊቱን የፈፀሙት የኦሮሞ ወጣቶች አይደሉም ብለው ለመካድና ነገሩን ለማድበስበስ የሄዱበት ርቀት፣ እንዲሁም በኦሮሞ ሕዝብ ስም የተደራጁ ፓርቲዎች አምስት የፖለቲካ ድርጅቶች መስከረም 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ ቡራዩና አሸዋ ሜዳ ላይ የተፈፀመውን ድርጊትና አዲስ አበባ ከተማን በሚመለከት ያራመዱት አቋም አክራሪው የኦሮሞ ጎራ ለዴሞክራሲ ያለውን ዝግጁነት አጠያያቂ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡

ዝቅ ብየ እንደምገልጸው፣ በእኔ አስተያየት ኢትዮጵያችን ከዚህ በኋላ የአንድ ቡድንም ይሁን የአንድ ሕዝብ የበላይነት የነገሠበት የአፈና አገዛዝ የመሸከም አቅሙ የላትም፡፡ መድኀናችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ ከዴሞክራሲም ሁሉንም ሕዝቦች አካታችና አሳታፊ የሆነው (consociational democracy) ዓይነት ዴሞክራሲ ነው፡፡ በዘውጋዊ ማንነታቸው የተደራጁትም ይሁን በዜግነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊነትን እንከተላለን የሚሉት የፖለቲካ ኀይሎች ሁሉ በነጻነት የሚሳተፉበትና ሁሉም እንደየአቅማቸው የሚሳተፉበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲገነባ ብቻ ነው በአገራችን ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋትና ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው፡፡ አንዳንድ በኦሮሞ ሕዝብ የተደራጁ የፖለቲካ ቡድኖች ከሰሞኑ የሚያራምዱት “የእኛ ተራ ነው” የሚል ከዴሞክራሲ ጋር የሚጋጭ አዝማሚያ ለአገርና ሕዝብ በምንም ዓይነት መንገድ አይበጅም፡፡

ታሪክ፡- የጦርነት አውድማ
***
ታሪክ የዘውጌ ብሔርተኞች ዋና የጦርነት አውድማ ነው፡፡ የትኛውም ዘውጌ ብሔርተኛ ታሪክን እሱን በሚያገለግል መልኩ መጻፍ ዓይነተኛ መለያ ባሕርይው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይ የውጭ አገራት የሥነ-ሰብዕ፣ ታሪክና ቋንቋ ምሁራን እንዲሁም ሚሲዮናዊያን አስተዋጽዖ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ዊሊያም ሀስቲንግስ የተባለው ብሪታኒያዊና ‹ኢስት ኢንዲያ ካምፓኒ› ውስጥ በኀላፊነት ቦታ ላይ ይሠሩ የነበሩ ባልደረቦቹ የቤንጋል ቋንቋን በማሳደግ ለሕንድ ብሔርተኝነት ከፍ ያለ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ የኦሮሞ ዘውጌ ብሔርተኝነትም በአውሮፓ ወንጌላዊ ሚሲዮናዊያን እና እንደ ባርቴልስ (Bartels, L.)፣ ሃበርላንድ (Haberlaned Von, E.)፣ ባክስተር (Baxter, P.T.W.)፣ ሆሎኮምብ፣ (Holocomb,B.K.)፣ አስምሮም ለገሠ ወዘተ. ባሉ የሥነ-ሰብዕና የቋንቋ ምሁራን አማካይነት የተፈጠረ ነው፡፡

በዚህ የታሪክ አውድ ውስጥ ተወለደው የኦሮሞ ዘውጌ ብሔርተኛ የኢትዮጵያ ታሪክ የሁሉንም ሕዝቦች ታሪክ ያካተተ ብሔራዊ ታሪክ አይደለም ብሎ ሲያበቃ እዚያው በዚያው ራሱን በሚጠቅም መልኩ ልዩ ልዩ ድርሳናትን እያዘጋጀ ታሪክን የፖለቲካ መሣሪያነት ሲገለገልባት ከርሟል፡፡ የትናንቱን ኹነት በዛሬ መነጽር በማየት ተመልሶ ከ1983 ዓ.ም. በፊት በታሪክ ውስጥ ስላልነበረችው “ኦሮሚያ” የተባለች አገር የፈጠራ ታሪክ ያስነብበናል፤ የኦሮሞን የገዳ ሥርዓት የገደሉት አባ ጅፋርን ጨምሮ ከራሱ ከኦሮሞ ሕዝብ የወጡት ባህላዊ መሪዎች (አባ ሞቲዎች) መሆናቸው በግልጽ እየታወቀ፣ አክራሪ ዘውጌ ብሔርተኞች የሐበሻ ወረራ የፍትሕ ሥርዓታችንን አወደመ ብለው ሳያፍሩ መጻሕፍት ያሳትማሉ፤ የኦሮሞ ሕዝብ በብዛት በሚኖርባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙት አብያተ-ክርስቲያናት የተሠሩት በአባ ገዳዎች መሰብሰቢያ ላይ ስለመሆኑ ይተርኩልናል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የኦሮምኛ ስያሜ ያላቸው አካባቢዎች የኦሮሞ እንደነበሩ ይገልጹልናል፡፡ አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን ሰፈሮቿም የኦሮምኛ ስያሜ የነበራቸው ስለመሆኑ የሚያብራራ መጽሐፍ ከመጻፍም አልፎ የግል ባንኮችና ዩኒቨርሲቲዎች በእነኝህ ስያሜዎች ቅርንጫዎቻቸውን እንዲሰይሙ በመደረግ ላይ ነው፡፡

በየትኛውም አገር ውስጥ በብሔራዊ ታሪክ ላይ አለመግባባቶችና ክርክሮች አሉ፡፡ በየትኛውም አገር ከዋናው ብሔራዊ/አገራዊ የታሪክ አተያይ (interpretation) የሚለዩ የታሪክ ድርሳናትና አተያዮች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም አንድ ሁሉም ሕዝቦች የእኛ ታሪክ ነው ብለው የሚቀበሉት ብሔራዊ ታሪክ ከሌለ ጠንካራ አገረ-መንግሥት ሊኖር አይችልም፡፡ ታሪክ የዘውጌ ብሔርተኞች የፖለቲካ መሣሪያ ሲሆን ደግሞ መዘዙ ከሁሉም የከፋ ነው፡፡ አዲስ አበባ የኦሮሞ ርስት ናት የሚለው የአክራሪ ዘውጌ ብሔርተኞች ትርክት የሚያሳየው ዘውግ-ተኮር ታሪክ ምን ያህል አገር እንደሚያጠፋ ነው፡፡ የሕወሓት የበላይነት የሰፈነበትን አገዛዝ ያንኮታኮተው ቄሮ ነው እያሉ ለ27 ዓመታት በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የከፈሉትን መስዋዕትነትና ያስገኙትን ፍሬ ለአንድ ቡድን አሳልፎ መስጠት ዘውግ-ተኮር እይታ ምን ያህል አእምሮን እንደሚሸብብ ምስክር ነው፡፡

ማነው ኢትዮጵያዊ?
****
የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ ኀይለማርያም A History Of Nationalism in Ethiopia፡ 1941-2012 በሚል ርዕስ በጻፈው የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ሥራው እንደገለጸው በማርክሳዊ አስተሳሰብ የተቃኘው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ የሚመራበት ርዕዮተዓለም በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አመለካከት ውስጥ በመደባዊና አውራጃዊ ወይም በአውራጃዊና ብሔራዊ ጭቆናዎች፤ በጨቋኝና ተጨቋኝ ብሔረሰቦች፣ በደቡብና በሰሜን ንፍቀ አገራት፣ በባህላዊ ራስ-ገዝነትና በፖለቲካዊ መገንጠል ወዘተ. የተፈረጁ ተቃርኖዎችን ያለቅጥ በማጋነን ትልቅ ጥፋት አድርሷል፡፡ ማነው ኢትዮጵያዊው? የሚለው ውስጠ ወይራ ጥያቄ የአፍለኛው ምሁር የትግል አጀንዳ ሆኖ ብቅ ያለውም በዚህ ግርግር ውስጥ ነበር፡፡

ዶ/ር ቴዎድሮስ እንዳብራራው ይህንን ብዥታና ወላዋይነት ተጣብተው የተፈለፈሉት ጥገኛ አስተሳሰቦች ቀስ በቀስ የብሔረሰቦችን ጥያቄ በማጉላት ገዥ መርህ ሆኖ እንዲወጣ ለማድረግ ቻሉ፡፡ ገና የኢትዮጵያ አብዮት ከመፈንዳቱ ቀደም ብሎ በየአውራጃው በሕዝብ ስም የተቋቋሙ ልዩ ልዩ የባህልና የመረዳጃ ማኅበሮችን በመጠለል ሲንቀሳቀሱ የቆዩት የብሔረሰብ ፖለቲካ አቀንቃኝ ኀይሎች የአብዮቱን ሒደት መቆጣጠር እንዳልቻሉ በተገነዘቡ ጊዜ ወዲያውኑ እውነተኛ ማንነታቸውን በማጋለጥና እነኘህን ማኅበራት በብሔረሰብ ስም ወደተደራጁ አማጺ ቡድኖች በመቀየር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን መዋጋት ቀጠሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ እንደ አብነት የሚጠቀሰው “ሜጫና ቱለማ” (1955 ዓ.ም.) በኋላ ለተመሠረተው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መቀፍቀፊያ በመሆን አገልግሏል፡፡

የኦነግና ሌሎች ዘውጌ ብሔርተኛ ታሪከኞች የዓለም ሁሉ ክፋትና ጥፋት ምንጭ ምኒልክ ነው የሚሉ ትርክቶችን በማድራት፤ በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የቋንቋና የባህል ማኅበረሰቦች መካከል ያሉ የአብሮነት ታሪኮችን፣ የጋራ ዕሴቶችንና ባህሎችን በመካድ፤ ከብዙ ዐሥርት ዓመታት በፊት የተደረጉ ጦርነቶችን እየተቀሱ በአዲስ መልክ የጭቆናና የሰቆቃ ገድሎችን በመፍጠርና በማጉላት፣ ኢትዮጵያውያንን የሚያገናኙ ድልድዮችን ሁሉ ለማፍረስ ያልተጓዙበት ርቀት የለም፡፡

ኢትዮጵያ የሁላችንም እንድትሆን የጋራ ዕሴቶችን ከመፍጠርና ከማጉላት ይልቅ በሕዝቦች መካከል ጥላቻና ግጭትን በሚፈጥሩ አጀንዳዎች ላይ ብዙ ሀብት ፈሰሰ፤ ብዙ ጉልበት ባከነ፡፡

“የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል”
****
በኦሮሞ ፖለቲከኞችና ምሁራን አካባቢ ስለ “ሐበሻ ወረራ” እና ከዚህ ወረራ ነጻ ስለመውጣት ብዙ ተጽፏል፤ ለረዥም ዘመናት ብዙ ተብሏል፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና በገዳ አባ ጃራ ይመራ የነበረው የኦሮሞ እስላማዊ ግንባር ዋና ዓላማ “ፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግል” ማካሄድና ነጻ የኦሮሚያ ሪፐብሊክን መመሥረት እንደነበርም የሚታወቅ ነው፡፡

እንደነ አሰፋ ጃለተና ሲሳይ ኢብሳ ያሉ የኦሮሞ ምሁራን ኢትዮጵያን “ብቸኛዋ የጥቁር ቅኝ ገዥ” ይሏታል፡፡ መፍትሔው ከኢትዮጵያ የቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነጻ መውጣት ነው የሚል ትርክት ለበርካታ ዓመታት ሲራመድ ቆይቷል፡፡ በብዙ አንጃዎች የተከፋፈለው ኦነግ ይህን ነባር ትርክቱን ይቀይር አይቀይር በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

ኦነግ ምንም ይበል ምን የነዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን መያዝ ለረዥም ዘመናት ሲያራምደው የነበረው አጀንዳ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ይበልጥ ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ ጥርጥር የለውም፡፡ እንደ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ያሉ የኦሮሞ ልጆች በበላይነት የሚመሯት ኢትዮጵያ የኦሮሞ ቅኝ ገዥ ናት ቢሉ የሚሰማቸው የለም፡፡ ስለሆነም አክራሪው ጎራ ኦሮሚያን እገነጥላለሁ (በእነሱ አነጋገር ነጻ እናወጣለን) ነባሩን አቋሙን ቀይሮ ተራው የእኛ ነውና አርፋችሁ ተቀመጡ የሚል አጀንዳ ማራመድ የጀመረ ይመስላል፡፡

ዴሞክራሲ ብቻ!
***
በመግቢያዬ እንደገለጽኩት ለኢትዮጵያዊያን መድኅናችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በዚህች አገር የአንድ የፖለቲካ ቡድንም ይሁን የአንድ ሕዝብ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት የሚኖርበት የፖለቲካ ሁኔታ የለም፡፡ ሁሉም አገራችን የፖለቲካ ኀይሎች ይህን መሠረታዊ ሐቅ በሚገባ ተገንዝበው ሁላችንም በእኩልነት የምታስተናገድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በሚያሳዝን መልኩ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚታየው አካሄድ ከዴሞክራሲ በተጻራሪ ቆመ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት ሁኔታዎችን ለማስተካከል ጥረት እያደረገ ቢሆንም በክልሉ የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎች በከፍተኛ ደረጃ ፈርተውና ተሸማቅቀው እንዲኖሩ ሆኗል፡፡ አክራሪ ዘውጌ ብሔርተኞች በሚረጩት የጥላቻ አዋጅ ምክንያት ዜጎች ትልቅ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የአገሬና የሕዝቤ ጉዳይ ይመለከተኛል የምንል ኢትዮጵያዊያን ጠንከር ብለን ለሁላችንም የሚበጀውን ስንናገርና በአክራሪ ዘውጌ ብሔርተኞች ላይ ሂስ ስናቀርብ “የኦሮሞ ጥላቻ” (Oromo phobia) አለብህ/ሽ እያሉ ዜጎችን ለማሸማቀቅና ዝም ለማሰኘት ከመሞከር ተቆጥበን፣ ለሁላችንም የምትሆን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመገንባቱ ላይ እናተኩር፡፡ ብቸኛው መዳኛችን ዴሞክራሲ ብቻ ነው!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች!

Advertisements

Report this ad

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s