ህወሀት በጋምቤላ እጁ ተቆረጠ በአፋርም እየተገዘገዘ ነው!!! (መሳይ መኮንን)

አፋሮችና ጋምቤላዎች የመንግስት ያለህ ጩሀት ማሰማት ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል። በዶ/ር አብይ አህመድ የተጀመረው የለውጥ ሂደት እኛ ዘንድ አልደረሰም የሚለው የህዝብ ድምጽ በተለይ ከአፋርና ከጋምቤላ ያለማቋረጥ ይሰማ ነበር። የለውጥ ሽታ ይድረሰን፡ አመራሮቹ ከህወህት እቅፍ አልወጡም፡ ለሌላው ኢትዮጵያዊ የደረሰው ተስፋ ለእኛ ለምን ይነፈገናል የሚለው መልዕክት ለአራት ኪሎው ቤተመንግስት ምነው ራቀ አሰኝቶ ነበር የሰነበተው። በሁለቱ ክልሎች ህዝቡ ላለፉት አራት ወራት በተቃውሞ ቆይቷል።

በእርግጥ በሁለቱ ክልሎች የህወሀት እጅ አልተቆረጠም። ህወሀት ማዕከላዊ መንግስቱን ከተነጠቀ በኋላ ጓዙን ጠቅልሎ መቀሌ ቢገባም በአራቱ ታዳጊና ወደኋላ የቀሩ ክልሎች ላይ የበላይነቱን የሚነጥቀው አልነበረም። መቀሌ ከዮሀንስ ቤተመንግስት ተቀምጦ የጥፋት ተልዕኮውን ያለአንዳች ከልካይ ማስፈጸም የቀጠለባቸው በተለይ በአራቱ ክልሎች ነው። በሶማሌ፡ በአፋር፡ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል።

በሌሎች ክልሎች አንጻራዊ በሆነ መልኩ የለውጥ ሂደት ተጀምሯል። የህወሀት የበላይነትን ቀብረዋል። በሌሎች አዳዲስ ከለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ቢከሰቱም የ27 ዓመቱ የህወሀት ዘረኛ አገዛዝ ከነሰንኮፉ ተነቅሎላቸዋል። በአራቱ ክልሎች ግን ህወሀት አልሞተም ነበር። ከነመርዙ እየተናደፈ ቀጥሏል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ላይ ከሚቀርቡ ወቀሳዎች አንዱ በእነዚህም ክልሎች ላይ ምነው አቅም አጡ የሚል ነበር።

አብዲ ዒሌ የሶማሌ ህዝብ ከለውጡ ጋ እንዳይገናኝ እንቅፋት ሆኖ ለአራት ወራት ተንገታገተ። የሶማሌ ኢትዮጵያዊው ለሁለት ወራት ሲተናነቅ፡ እስከአዲስ አበባ የተዘረጋ ተቃውሞ ሲያሰማ ቆየ። ቢዘገይም መልስ ማግኘቱ አልቀረም። የጠ/ሚር አብይ አስተዳደር በብልሃትና ጥበብ የህወሀትን እጅ በመቁረጥ፡ አብዲ ዒሌን እጆቹ በሰንሰለት ታስረው ወደ ከርቸሌ እንዲገባ አደረገው። የሶማሌ ክልል ህዝብ እፎይ አለ። አዲሱ የክልሉ ፕሬዝዳንት ከዘር ቆጠራ ወጥተው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አመራር ከጀመሩ ሁለተኛ ወራቸውን ይዘዋል።አሁን ጂጂጋ ላይ ” ሶማሌነቴ ከኢትዮጵያዊነቴ ጋር አይጋጭብኝም” የሚል አመራር ተቀምጧል።

የእኛም ጩሀት የነበረው ጠ/ሚር አብይ እንደሶማሌ ክልል ሁሉ ለአፋሮች እሮሮና ከጋምቤላ ለሚሰማው የድረሱልን ጥሪ መልስ እንዲሰጥ ነበር። ያልተረጋጋ አስተዳደር፡ ሙሉ በሙሉ ስልጣኑን ያልጨበጠ አመራር፡ በሽግግር ላይ ያለ ስርዓት መሆኑ ባይጠፋንም ባለች ውሱን አቅምም ቢሆን የሆነ መፍትሔ እንዲፈለግ ከአፋሮችና ጋምቤላዎች ጋር አብረን ስንጮህ ቆይተናል። ህወሀት ከጂጂጋ እጁ ሲቆረጥ አፋር፡ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ላይ ግን ስር ይዞ ቀጥሏል። የእነዚህ ክልሎችን አመራሮች በመቆጣጠር ከመቀሌ በሪሞት ኮንትሮል እንዳሻው መጠምዘዙን አላቆመም። ሀብትና መሬታቸው ላይ ተቀምጦ መቦጥቦጡን የሚያስጥለው ሊገኝ አልቻለም ነበር። የህዝብ ተቃውሞ ሳይቋረጥ እየተሰማ ነው። ዶ/ር አብይ ከወዴት አሉ?

ትላንት ስለሁለቱ ክልሎች የሰማነው ተስፋ የሚሰጥ ነገር ነው። ይዘገያል እንጂ አይቀርም። ጋምቤላ ላይ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረው፡ ለውጡን ሲያደናቅፍ የሰነበተው፡ ከህወሀት እቅፍ መውጣት ያልቻለው የጋትሉዋክ ቱት አመራር ከስልጣን መልቀቁ ተነገር። ጠ/ሚር አብይ አህመድ በተገኙበት በአዲስ አበባ በተደረገ ግምገማ የጋት ሉዋክ አመራር በገዛ ፍቃዱ ስልጣን መልቀቁ ታውቋል። ለጋምቤላዎች ትልቅ ዜና ነው። ጩሀታቸው ተሰምቷል። ዘግይቶም ቢሆን መልስ አግኝቷል። ህወሀት በጋምቤላም እጁ ይቆረጥ ዘንድ ውሳኔ አግኝቷል።

በአፋርም ሂደቱ ተጀምሯል። የክልሉ ገዢ ፓርቲ ለሁለት ተሰንጥቋል። ለውጡን የሚደግፉ ሃይሎች ዝምታውን ሰብረዋል። የአቶ ስዩም አወል አመራር ክሀወህት ጋር መቆየትን በመምረጥ ለውጥ በጠየቁ የፓርቲው አመራሮች ላይ እገዳ አስተላልፈዋል። የአፋር ህዝብ ከለውጥ ፈላጊ አመራሮች ጎን በመሆኑ የአቶ ስዩም እገዳ ዋጋ እንደማይኖረው ይታመናል። ከመቀሌ ትዕዛዝ እየተቀበሉ አፋርን የሚመሩት አቶ ስዩም የመጨረሻ ሙከራቸውን ለማድረግ ከህወሀት ጋር እየመከሩ እንዳለ ይሰማል። የዶ/ር አብይ መንግስት በብልሃት የህወሀትን እጅ ከአፋር ላይ ለመቁረጥ መንገዱን ተያዞታል። በቅርቡ የለውጥ እንቅፋት የሆነው የአቶ ስዩም አወል አመራር እንደጋትሉዋክ ቱት በገዛ ፈቃዱ ስልጣኑን ይለቃል አልያም እንደአብዲ ዒሌ መጨረሻው ከርቸሌ ሆኖ ያበቃለታል።

ሁሉም በጊዜው መሆኑ አይቀርም። ጂጂጋ፡ ጋምቤላና ሰመራ ላይ አቅሙን ያሳየው የጠ/ሚር አብይ መንግስት መቀሌ ላይም እንደሚመሰከር እንጠብቃለን። ጠ/ሚር አብይ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው ሳምንታት ቀደም ብሎ ለውጡ አይቀሬ መሆኑን የተረዱት ህወሀቶች በድብቅ ባደረጉት ስብሰባ፡ አዲስ አበባን ብንነጠቅ፡ ትግራይን ግን አናስነካም፡ የሚል አቋም ላይ ደርሰው ተማምለው ነበር። ባለፉት ስድስት ወራት መሀላቸውን ጠብቀው ቆይተዋል። ሆኖ ትግራይን ከተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ለይተው ለብቻቸው እንደዘመነ መሳፍንት ሊያቆዩ አይችሉም። በሂደት የመቀሌውንም ቁልፍ ይነጠቃሉ። የጠ/ሚር አብይ አህመድ የብልሃት አካሄድ ጊዜ ሊወስድ ይችል ይሆናል እንጂ መቀሌም የለውጡ ሂደት አካል መሆኗ አይቀርም።
@መሳይ መኮንን

የሀገሪቱ ባንኮች ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ ሊያዋጡ ነው

ዋዜማ ራዲዮ- የሀገሪቱ ባንኮች ከአመታዊ ትርፋቸው 0.5 በመቶ የሚሆነውን በሀገሪቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ ሊያዋጡ ነው። ዋዜማ ባገኘችው መረጃ መሰረት በሀገሪቱ ያሉ ሁለት ሚሊየን የሚጠጉ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም መንግስት አቅም አንሶታል፣ ከለጋሾችም የሚፈለገው ድጋፍ ሊገኝ አልቻለም።

ተፈናቃይ ዜጎች በብዛት ያሉባቸው ክልል አስተዳደሮች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ነው ልገሳው የተጀመረው።
በአሁን ሰአት በኢትጵያ ውስጥ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች 1.8 ሚሊዮን እንደደረሰ የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መረጃ ያሳያል።ይህም ኢትዮጵያን የሀገር ውስጥ መፈናቀል ካሉባቸው ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ አሰልፏታል።
እነዚህን ተፈናቃዮችንና ሌሎች በተፈጥሮ አደጋ ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለማቋቋም መንግስት 1.4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልገው ኮሚሽኑ ይገልጻል።

ይህን ያክል መጠን ያለውን ገንዘብ መንግስት ከራሱ ካዝና ማግኘት እንደቸገረው ታውቋል። መንግስት የዚህን ሰባ በመቶ ለመሸፈንና 30 በመቶውን ከለጋሾች ለማግኘት ነው ያቀደው ። ሆኖም ገንዘቡ የመንግስትን ካዝና በመፈታተኑ የክልል አስተዳደሮች በሀገሪቱ በአንጻሩ አትራፊ ስራ ላይ ናቸው ወደተባሉት የባንክ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ፊቱን አዙሯል።
በሀገሪቱ ያሉ የንግድ ባንኮች ባደረጉት ውይይትም ከአመታዊ ትርፋቸው 0.5 በመቶ የሆነውን ገንዘብ ለዚሁ አላማ ለመለገስ ወስነው የሰጡም አሉ። ለመስጠት ውሳኔን የማጸደቅ ሂደት ላይ ያሉ ባንኮች መኖራቸውንም ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ያገኘችው መረጃ ያሳያል። እስካሁንም ከአንድ ባንክ 20 ሚሊየን ብር እንደተለገሰም ማወቅ ችለናል።
ባለፉት ወራት በኢትዮጵያ በተለያዩ ስፍራዎች ብሄር ተኮር ግጭቶች ተነስተው በርካቶች መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው።በጌዲዮና ጉጂ አካባቢ በተፈጠረው ብሄር ተኮር ግጭት አንድ ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮምያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ በተነሳው ግጭትም በርካቶችን ለመፈናቀል አብቅቷል።መስከረም ወር ላይ በቡራዩ ላይ በደረሰ አደጋ በሺዎች ተፈናቅለው ነበር።ቀደም ብለው ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን የማቋቋሙ ስራ አልተጠናቀቀም ።

እነዚህ ሁሉ ጫናዎች በየአመቱ በሴፍትኔት ዕርዳታ ከሚያስፈጋቸው ዜጎች ጋር ተዳምሮ ከባድ የበጀት ጫና እየፈጠረ መሆኑን ከመንግስት ባለስልጣናት በኩል እየተነሳ በመሆኑም ነው የባንኮቹ ድጋፍ ያስፈለገው።

ለወራት በውሃ ጥም ስትቃጠል የከረመችው ሐረር በፈረቃ ውሃ ማግኘት መጀመሯ ተሰምቷል

ለወራት በውሃ ጥም ስትቃጠል የከረመችው ሐረር በፈረቃም ቢሆን ውሃ ማግኘት መጀመሯ ተሰምቷል።

ባለፈው ሳምንት ሐረር ከተማ ያሉ ሰፈሮች እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ ውሃ ሳያገኙ እንደቆዩ መዘገባችን ይታወሳል፤ የሐረር ከተማ ሰዎችም የድረሱልን ጥሪ አቅርበው ነበር።

የሐረሪ ክልል ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የከተማዋ አንድ ሦስተኛ ክፍል የቧንቧ ውሃ ማግኘት ጀምሯል።

«የችግሩ ዋነኛ ምንጭ የነበረው የዓለማያ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ከኦሮሚያ መስተዳድር እና ከዓለማያ እና አወዳይ አስተዳደር ጋር በመነጋገር ጣቢያው አገልግሎት መስጠት እንዲቀጥል ተደርጓል» ይላሉ ባለስልጣኑ።

አክለውም «ከዓለማያ የሚመጣውን ውሃ ከድሬዳዋ ከሚመጣው ጋር በማጣመር ቢያንስ የከተማዋን አንድ ሦስተኛ ክፍል በማዳረስ ለማረጋጋት እየጣርን ነው» ብለዋል አቶ ተወለዳ።

በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ደግሞ ሌሎች ውሃ ያልደረሳቸውን ቦታዎች በፈረቃ የማዳረስ ዕቅድ እንዳላቸው ባለሥልጣኑ አሳውቀዋል።

የኤረር የውሃ መስመር ችግር እስካሁን እንዳልተፈታ የጠቆሙት አቶ ተወለዳ በሚቀጥሉት ሁለት ሦስት ቀናት ችግሩ እንደሚቀረፍ እምነት አላቸው።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያሰቡት ነገር እንዳለ የተጠየቁት ሥራ አስኪያጁ «ሌሎች ውሃ አመንጪ ጉድጓዶች ቆፍረን መስመር ለመዘርጋት ዝግጅት ላይ ነን» ብለው፤ ወደ ሐረር ከተማ ውሃ የሚያሰራጩ መስመሮችን በማብዛት ሥራ መጠመዳቸውን ጠቁመዋል።

አክለውም «ለሚቀጥሉት አምስትና አስር ዓመታት ከተማዋ ምን ያህል ውሃ ያስፈልጋታል የሚል ጥናት ልናካሂድም ነው» ብለዋል።

አቶ ዳንኤል በርሄ በሐረር ከተማ የሆቴል ባለቤት ናቸው። ላለፈው አንድ ወር በሳምንት ከግለሰብ ከቦቴ ውሀ በ2000 ብር እንደገዙ ያስታውሳሉ።

አሁን ግን ውሃ መጥቶ «ትልልቅ ማጠራቀሚያቸውንም ባሊውንም ሞልተናል» ይላሉ፤ ሌሎች ከእርሳቸው ሰፈር በከፋ ለአራት ወራት ያክል ውሃ ያላገኙ ሥፍራዎች እንዳሉ በመጠቆም።

ችግሩ ፀንቶባቸው የቆዩ ቦታዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የውሃ አቅርቦት እንዲኖራቸው መደረጉን ባለሥልጣኑ አክለው ነግረውናል።

«ቅድሚያ የሰጠናቸው ለረዥም ወራት ውሃ የሚባል ያላገኙ አካባቢዎችን ነው፤ ለምሳሌ በተለምዶ ጊዮርጊስ ጋራ እና ከራስ ሆቴል በላይ ያሉ አካባቢዎችን ነው። ከራስ ሆቴል በታች ያሉትም ቢበዛ በአራት ቀናት ውስጥ ውሃ እንደሚያገኙ እምነቴ ነው» ብለዋል አቶ ተወለዳ።

ባለስልጣኑ አክለውም «10 ሚሊዮን ብር ካልተሰጠን የዓለማያ ውሃ ጣቢያ አግልግሎት እንዲሰጥ አንፈቅድም ያሉ ሰዎችን አደብ በማስያዝ የኦሮሚያ ክልል አስተዋፅኦ አበርክቷል» ይላሉ።

የሐረር ከተማ ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ ችግራቸውን ለማስታገስ የታሸገ ውሃ በመግዛት ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ገልፀውልን እንደነበር አይዘነጋም።

ውሃ ሲጠፋ 55 ኪሎ ሜትር ድረስ ተጉዘው የሚቀዱ እንዳሉ እና ይህንን ማድረግ የሚችሉት መኪና ያላቸው እንደሆኑም የችግሩን ግዝፈት እንደሚያሳይ ተነግሮ ነበር።

የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ በጥድፊያ?! – ሌላ ትውልድ “እንዳንገድል!” (ከአብዱራህማን አህመዲን)

የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ በጥድፊያ?! – ሌላ ትውልድ “እንዳንገድል!”

(ከአብዱራህማን አህመዲን – የቀድሞ የፓርላማ አባል)  Addis Admass

የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል ገደማ “ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወይስ ከፍተኛ የዝርፊያ ተቋማት?” በሚል ርእስ አንዲት ጽሁፍ አዘጋጅቼ በጋዜጣም በኢንተርኔትም አሰራጭቻት ነበር፡፡ ጽሁፉን የተመለከተ አንድ የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ወንድሜ፤ “የትምህር ነገር አሳሳቢ ነው፤ አንተም የበኩልህን አስተያየት ሰንዝር” ከሚል መልእክት ጋር የትምሕርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ ጨመቅ (Executive Summary) ቅጅ ላከልኝ፡፡ ሰነዱ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል በ“ከላይ ወደ ታች ዘይቤ” (top-down approach) ወርዶ፣ሰሞኑን በከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት መምሕራን “ውይይት” እየተደረገበት መሆኑ ይታወቃል፡፡
ፍኖተ ካርታውን እያነበብኩ ባለሁበት ወቅት ዮሐንስ ሰ. የተባለ ጸሐፊ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የመስከረም 19 ቀን 2011 እትም ላይ “ለተሳከረው የአገራችን ትምህርት መፍትሄው፣… ‘ከእውቀት የራቀ ትምህርት’ ነው?” በሚል ርእስ ያቀረበውን ጽሁፍ አየሁና እውነትም ይሄ ነገር ዝም ሊባል እንደማይገባው በማመን፣ይህቺን አስተያየት ለመከተብ ተነሳሁ፡፡
የዮሐንስ ሰ. ጽሁፍ ያተኮረው በፍኖተ ካርታው ላይ በቀረቡት ፍሬ ሃሳቦች ዙሪያ ነው፡፡ የእኔ ጽሁፍ ትኩረት የሚያደርገው ግን በፍኖተ ካርታው አዘገጃጀት፣ የቀረበበት ወቅት፣ በጥናቱ ተሳታፊዎችና አጠናኑ ላይ ያለውን አንደምታ በተመለከተ ይሆናል፡፡ለመንደርደሪያ ይሆን ዘንድ ከዮሐንስ ጽሑፍ የተወሰኑ ነጥቦችን ልጥቀስ፡፡
“ለተሳከረው የአገራችን ትምህርት መፍትሄው ‘ከእውቀት የራቀ ትምህርት’ ነው?” የሚለው ርእስ ግራ እንደሚያጋባ የተረዳው የአዲስ አድማሱ ጸሐፊ ዮሐንስ ሰ.፤ አእምሯችን መልስ ፍለጋ እንዳይባዝን በማሰብ፤ “ከሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል፣ ግማሽ ያህሉ (ማለትም 50%)፣ አንዲት አጭር ዓረፍተ ነገር አንብበው ለመገንዘብ የሚያስችል እውቀት የላቸውም። ሩብ (25%) ያህሉ ደግሞ አንዲትም ቃል ማንበብ አይችሉም። [ይህ] ውድቀት… በእጣ ፋንታ ሰበብ የወረደ ክፉ መዓት፣ ባልታወቀ ፍጡር የተወረወረ እርግማን አይደለም… ‘ከእውቀት የራቀ የማወቅ ክህሎትን እናስተምራለን’ በሚል የተሳከረ አስተሳሰብ የተቃኘ ትምህርት… ” ውጤት መሆኑን ይነግረናል፡፡
ዝቅ ብሎ ደግሞ “እውቀትን ማስጨበጥ ሳይሆን ሙያን ማስተማር… ነው የትምህርት ዓላማ… [ይላል ፖሊሲው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ] ያለ እውቀት የህክምና ሙያ፣ ያለ እውቀት የምህንድስናም ሆነ የአናፂነት ሙያ… [እንደሚኖር ማሰብ ነው]…” በማለት በአጥኚዎቹ ላይ ይሳለቃል ዮሐንስ፡፡
የአዲስ አድማስ ጸሐፊ ዮሐንስ ሰ. ቀዳሚው የትምህርት ፖሊሲ፤ተማሪዎች ማንበብና መጻፍ፣ መደመርና ማባዛት… እንደማይችሉ አዲሱ ፍኖተ ካርታ በጥናት ማረጋገጡን በ“ፀፀት” ከነገረን በኋላ፤ የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ራሱ የቋንቋ ሰዋሰው መፋለስ የታጨቀበት መሆኑን በ“ስላቅ” ያመላክተናል፡፡ ዮሐንስ ሰ. ያልነገረን በሰዋሰው ስህተቶች የተሞላውን ሰነድ ካዘጋጁት “አጥኝዎች” ውስጥ ማንበብና መጻፍ፣ መደመርና ማባዛት… “የማይችሉት” የአዲሱ ትምህርት ፖሊሲ ውጤቶች መሳተፍ አለመሳተፋቸውን ነው፡፡
ላለፉት 25 ዓመታት አገልግሎት ላይ የዋለው የሀገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ፤ ሀገሪቱ ህገ መንግስት እንኳ ሳይኖራት፣ የምትመራበት ርዕዮተ-ዓለም ምን እንደሆነ በቅጡ ሳይታወቅ፣ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላትና በወቅቱ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች በአግባቡ ሳይመክሩበትና ምርጫ ተካሂዶ ቋሚ መንግስት ሳይመሰረት በይድረስ ይድረስ፣ የአንድን የፖለቲካ ቡድን ፍላጎት ማዕከል አድርጎ፣ ይሁንታ (mandate) በሌለው አካል የተዘጋጀ ነበር፡፡
ሰሞኑን የትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ፍኖተ ካርታም ከቀዳሚው የተለየ ሆኖ የቀረበ አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህ ወቅት ህገ መንግስትና በምርጫ የቆመ መንግስት ቢኖርም፤“ታሪክ ራሱን ይደግማል” እንዲሉ ሀገሪቱ በቄሮና በፋኖ በምትታመስበት፣ በለውጥ ማዕበል በምትናጥበት፣ የፌስቡክ ቱማታ በጦፈበት፣ እዚህም እዚያም ህዝብ በሚፈናቀልበት፣ አሁን ያለው ህገ መንግስት እጣ ፋንታ ከመጪው ምርጫ በኋላ ምን ሊሆን እንደሚችል ባልታወቀበት፣ ዜጎች ተረጋግተው በማያስቡበት… በዚህ ወቅት የመጪውን ትውልድ መፃዒ ዕድል የሚወስን የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ አዘጋጅቶ፤ የይስሙላ ውይይት አድርጎ በማጽደቅ ለትግበራ መቻኮል ፋይዳውንም ሆነ ዓላማውን የሚያውቁት ትምህርት ሚኒስቴርና የሰነዱ አዘጋጆች ብቻ ናቸው፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት ትምህርት ለሁሉም የሀገሪቱ ህፃናት ተደራሽ ባለመሆኑና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ባለመቻሉ አራት ክፍሎች ያሉት “የትምህርትና የስልጠና ችግሮችንና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን…” የያዘ 84 ገፆች ያሉት ፍኖተ ካርታ በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ስትራቴጂክ ማዕከል መሰናዳቱን አዲሱ ሰነድ መግቢያው ላይ ይነግረናል፡፡
ይህ ሰነድ የሃሳብ መጣረሱን የሚጀምረው ገና መግቢያው ላይ “… በሁሉም ዘርፎች… በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ አመርቂ ውጤቶችም ተመዝግበዋል…” በማለት ነው፡፡ ይህ አባባል “ታዲያ አመርቂ ውጤት ያስገኘ ፖሊሲ ተቀዶ ተጥሎ በሌላ እንዲተካ ለምን ጊዜና ጉልበት፣ ሀብትና ንብረት ይባክናል?” የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡
በነባሩ የትምህርት ፖሊሲ ተምረው ከሚመረቁ ወጣቶች ብዙዎቹ “garbage in garbage out” ዓይነት የመከኑ፣ እውቀት አልባ፣ ስማቸውን እንኳ በትክክለኛ ፊደል አስተካክለው መጻፍ የተሳናቸው መሆናቸውን ያስተዋሉ ሰዎችንና ከጅምሩ “ፖሊሲው ትውልድ ገዳይ ነው” በማለት ሲናገሩ ጆሮውን በጥጥ ደፍኖ አስተያየቱን እንደ “ሟርት”፣ ትችቱን እንደ “የጠላት ወሬ” ሲቆጥር የነበረው ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ እንደ አዲስ ግኝት የፖሊሲውን የድክመት መርዶ ሊነግረን መነሳቱ ቢያስገርመንም ከዚህም በላይ አለመዘግየቱ ያስመሰግነዋል ባይ ነኝ፡፡
ፍኖተ ካርታው ለሦስት ዓመታት፣ በ36 “ዋና አጥኝዎች” እና በ73 “ረዳት አጥኝዎች” 15 ሺህ ሰዎች መረጃ በመስጠት ተሳትፈውበት የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ፤ ጥናቱን ያካሄዱት ሰዎች እነማን ናቸው? ከትምህርት ጋር ተያያዥነት ያለው ሙያዊ ብቃት አላቸው? ለጥናቱ መረጃ እንዲሰጡ የተመረጡት ሰዎች (የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርስቲ ኘሬዝዳንቶች፣ የዞንና የወረዳ የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣…) ምን ያህል ተዓማኒነት ያለው መረጃ ይሰጣሉ? 100 ሚሊዮን ህዝብ ባላት ሀገር የ15 ሺህ ሰዎችን አስተያየት ወስዶ ጥናት ማካሄድስ ፖሊሲ ለመቅረጽ የሚያስችል ወካይ ናሙና ሊሆን ይችላል? “ፖሊሲው ትውልድ ገዳይ ነው” ይሉ የነበሩት ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎችስ የጥናቱ አካል ነበሩ? የሚሉት ጥያቄዎች በቂ ማብራሪያ ይፈልጋሉ፡፡
እንደኔ እንደኔ ቁም ነገሩ “ምርጥ” ፍኖተ ካርታና “ምርጥ” ፖሊሲ ማውጣት ብቻ አይደለም፡፡ የተማሪ ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን የተሻለ መሆኑ የተነገረለትን “ምርጥ” ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የሚሆን እውቀትና ይህንን መሸከም የሚችል የፋይናንስ አቅም አለ? ቴክኒካዊ አቅምስ ማሟላት ይቻላል?
የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ “ጥራት ያለው ፖሊሲ” ማዘጋጀት አንዱ ግብዓት ይሆናል እንጂ ብቻውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም፡፡ ስለ ትምህርት ጥራት ስናወራ ቀዳሚውና ዋነኛው ግብዓት ደግሞ ጥራትና ብቃት ያለው መምህር ነው፡፡ እስከዛሬ የመጣንበት የመምህራን የቅጥር ሁኔታ በብቃት ሳይሆን ለገዢው ፓርቲ ባለው አመለካከትና ታማኝነት ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሁን በሥራ ላይ ያለው የትምህርት ባለሙያ፤ አይረቤነቱ በተነገረለት ፖሊሲ ተምሮ ወደ ስራ የተሰማራ ነው፡፡ እናም እነዚህ የመከነው ፖሊሲ ውጤቶች፣ አዲስ እየተዘጋጀ ያለውን ፖሊሲ የማስፈጸም ብቃት አላቸው ብሎ ለመውሰድ ያስቸግራል፡፡
በተሽመደመደ ፖሊሲ ተምሮ፣ በወገንተኛ የቅጥር ስርዓት ተቀጥሮ “garbage in garbage out” ዓይነት ስማቸውን አስተካክለው መጻፍ የማይችሉ ተማሪዎችን ሲያመርት የነበረ፣ ራሱ የመከነ የመምህራን ሰራዊት ሀገሪቱን ወደ 22ኛው ክፍለ ዘመን ማሸጋገር የሚችል ትውልድ ማፍራት ይችላል ብሎ ማሰብ ራሱ ከንቱነት ነው፡፡ ያልበቃ አብቂ፣ ያልሰለጠነ አሰልጣኝ ከመሰኘት የዘለለ ፋይዳ ያለው ሆኖ አይታየኝም፡፡
ይህቺን አስተያየት ለመጻፍ ስነሳ ያነጋገርኳቸው በትምህርት ሙያ መስክ ለረዥም ዓመታት፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማለትም በዩኒቨርሲቲ ከ30 ዓመት በላይ ያስተማሩ ምሁራን “ለመሆኑ ሀገሪቱ የትምህርት ፍልስፍና አላት ወይ? ካለ ፍልስፍናችን ምን ነበር?” የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት ምን ዓይነት የትምህርት ፍልስፍና እንደነበር አላውቅም፡፡ በአዲሱ ፍኖተ ካርታ ላይ ግን “(1) ዜጐች በራሳቸው የሚተማመኑ፥ ብቁና በምክንያታዊ ትንተና የሚያምኑ፥ በሙያቸው ብቃት ያላቸው በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ አድርጐ አጠቃላይ ሰብእናቸውን መገንባት፤ (2) ሥራ ፈጣሪዎች፥ አዳዲስ ግኝቶችን አፍላቂዎች፥ ጠንካራ የሥነ ምግባርና ግብረ ገባዊ እሴቶችን የተላበሱና ለሕግ ዘብ የቆሙ ዜጐችን ማፍራት (3) ብዝሃነትን ላካተተው አገራዊ አንድነትና ሠላም ዘብ እንዲቆሙ ማድረግ” የሚሉ ሦስት የትምህርት ፍልስፍናዎችን ያስቀምጣል፡፡
እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ጥያቄ “ይህ የትምህርት ፍልስፍና ከአጠቃላይ ሀገራዊ ራዕያችንና ከህገ መንግስታዊ ግባችን ጋር አብሮ ይሄዳል ወይ?” የሚል ነው፡፡ እኔ እንደሚገባኝ (በህገ መንግስታችን ላይ እንደተቀመጠው) ሀገራዊ ግባችን “አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር” ይመስለኛል። ታዲያ በፍኖተ ካርታው ላይ የተቀመጡት፣ ከፍ ሲል የጠቀስኳቸው የትምህርት ፍልስፍናዎች ሀገራዊ ግባችንን እውን ከማድረግ አኳያ የተቃኙ ናቸው? ይህም መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡
የሀገራችን የትምህርት ስርዓት በየወቅቱ የነበሩ መሪዎችን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የእነርሱን ወዳጅ ሀገራት ፖሊሲዎች በአርኣያነት በመውሰድ የተቀረፁ መሆናቸውን ወደ ኋላ ተመልሶ ማየት ይቻላል። በምኒልክ ዘመን የተጀመረው ዘመናዊ ትምህርት የአውሮፓን የትምህርት ስርዓት የተከተለ ነበር፡፡ ብዙዎቹ መምህራንና የማስተማሪያ መጽሐፍት ጭምር ከአውሮፓ የመጡ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በአምስቱ ዓመት የወረራ ዘመን ደግሞ የጣሊያኖቹን አስኮላ የሚመስል የትምህርት አሰጣጥ ተጀምሮ ነበር፡፡
የጣሊያን ወረራ በሀገሪቱ ማቆጥቆጥ ጀምሮ የነበረውን ዘመናዊ ትምሕርት ሙሉ በሙሉ አዳፍኖት ነበር፡፡ በጣሊያን ወረራ ወቅት ትምሕርት ቤቶችና የትምሕርት መሣሪያዎች በመውደማቸው፣ በጊዜው የነበሩ ጥቂት መምሕራን በጦርነቱ ምክንያት በመሰደዳቸውና በመሞታቸው 4,200 ያህል ተማሪዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲበተኑ በመደረጉ በጥቂቱም ቢሆን የነበረው የዘመናዊ ትምሕርት ጭላንጭል ሙሉ በሙሉ በመጨለሙ ከድል በኋላ ከባዶ መጀመር ግድ ሆኖ ነበር፡፡
የጣሊያን ወራሪ ኃይል ተወግዶ በአዲስ መልክ የተዋቀረው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የትምሕርት ስርዓት እንደ ቀድሞው ሁሉ ከምዕራባዊያን ተጽዕኖ ነጻ አልነበረም:: የየካቲቱን ሕዝባዊ አብዮት ተከትሎ የአብዮቱ የእንግዴ ልጅ የነበረው ግራ ዘመሙ ወታደራዊ ጁንታ መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ የትምሕርት ዘርፉ ማርክሲስት ሌኒኒስት መሽተት ጀመረ:: በዚያ ወቅት በትምህርት ስርዓቱ አማካይነት “ሶሻሊስት አርበኞችን” ለማፍራት ብዙ የተደከመ ይመስለኛል፡፡ እኔም የዚያ ፖሊሲ ውጤት ነኝ፡፡
ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ስልጣን ሲጨብጥ (ገና በሽግግሩ ዘመን) ኢህአዴግ ከዘመተባቸው ተቋማት አንዱ የትምህርት ሴክተር ነው፡፡ ገና ህገ መንግስት ሳይረቀቅ፣ ምርጫ ተካሂዶ ቋሚ መንግስት ሳይመሰረት ያገባናል የሚሉ ኃይሎች ጥሪ ተደርጎላቸው ሳይመክሩበት በጥድፊያ አዲስ የትምህርት ፖሊሲ ወጥቶ ሥራ ላይ ዋለ፡፡
በወቅቱ 120 ሺህ መምህራን የመረጡት እድሜ ጠገብ የመምህራን ማህበር ፈርሶ ለስርዓቱ ታዛዥ የሆነ የመምህራን ማህበር ተቋቁሞ፣ ከትምሕርት ሚኒስቴርና መሰል የመንግሥት ተቋማት ጋር በመቀናጀት የፖሊሲው መሀንዲስ ሲሆን፤ ያኔውኑ “ይህ ፖሊሲ ትውልድ ገዳይ ነው” የሚሉ ኃይሎች ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ፡፡ አሁን ደግሞ ያ ፖሊሲ ጉድለት እንዳለው ታምኖ አዲስ ሰነድ ተዘጋጀ፡፡
የያኔውን ፖሊሲ አሁን እየተዘጋጀ ካለው ጋር የሚያመሳስላቸው መሰረታዊ ነገር፣ የያኔው ቋሚ መንግስት ሳይመሰረት በሽግግር ወቅት ተዘጋጀ፡፡ አሁንም የሰከነ አእምሮ በሌለበት፣ የፖለቲካ መረጋጋት ባልተፈጠረበት፣ ህዝብ በሰፊው በሚፈናቀልበት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች መማር ማስተማር ባልተጀመረበት የለውጥ ሂደት ላይ እያለን ነው ይህ ሰነድ ብቅ ያለው፡፡
እዚህ ላይ ቀዳሚው ጥያቄዬ፣ ይህ ያልተረጋጋ ወቅት አዲስ የትምህርት ፖሊሲ ለማውጣት ለምን ተመረጠ? የሚል ነው፡፡ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ምርጫ ተካሂዶ አዲስ መንግስት እንደሚመሰረት በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት በስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ፍላጎትና ራዕይ ብቻ የሚያንጸባርቅ የትምህርት ፖሊሲ ማውጣት ለምን አስፈለገ? የሚል ተጨማሪ ጥያቄም ማንሳት ይቻላል፡፡
የትምህርት ፖሊሲ የአንድን ሀገር ዜጎች ሁሉ የሚመለከት፣ ለሀገሪቱ ውድቀትም ሆነ እድገት ወሳኝነት ያለው ጉዳይ በመሆኑ የሚመለከታቸው ሁሉ ሊመክሩበትና ሊዘክሩበት ይገባል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ መምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ በመምሕራን ለመምሕራን የቆመ የመምህራን ማህበርና ሌሎች የሙያ ማህበራት፣ ተማሪዎችና ወላጆች በዋናነት ሊወያዩበት ይገባል፡፡
አዲሱ የትምሕርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ፤ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ሁሉ የተወያዩበትና ያዳበሩት ካልሆነ፣ እንዳለፉት 25 ዓመታት ማዶ ለማዶ እየተያዩ አንዱ “ትውልድ ገዳይ ነው” ሲል፣ ሌላው “ለብሔር ብሔረሰቦች ተደራሽ የሆነ የሊቃውንት ማፍሪያ ነው” እያለ ሲመጻደቅ ተጨማሪ ፍሬ-አልባ ዓመታት ይቆጠራሉ የሚል ስጋት አድሮብኛል፡፡ እናም ጥድፊያውን እናቁም – ሌላ ትውልድ እንዳንገድል እላለሁ፡፡

አቤቱታ!! ለክቡር የኢትዮጵያ ህዝብ !! ለክቡር የኢትዮጵያ ፌድራላዊ መንግሥት ጠ/ሚር አብይ አህመድ፡ ጉዳዩ፦ የህ.ወ.ሓ.ት.መስፋፋትና መሬት ነጠቃ!! | ገብረመድህን አርአያ

አቤቱታ!! ለክቡር የኢትዮጵያ ህዝብ !!

ለክቡር የኢትዮጵያ ፌድራላዊ መንግሥት ጠ/ሚር አብይ አህመድ፡ ጉዳዩ፦ የህ.ወ.ሓ.ት.መስፋፋትና መሬት ነጠቃ!!

ገብረመድህን አርአያ

(PDF) ክቡር የእትዮጵያ ህዝብ ሆይ ፤ ክቡር የእትዮጵያ ጠ/ሚር ዶ/ር አብይ አህመድ ፡ የማቀርበው አብዮቱታየ በኢትዩጵያ ህዝብና በርሶው አስተዋይ መሪነት የእልባት መፍትሄ እንደሚያገኝ በመተማመን ነው ።

ክቡራን!! ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ፡በየካቲት ወር 1967 ዓ.ም ደደቢት በረሃ ከመውረዱ ጥቂት ቀደም ብሎ አዲስ አበባ ውስጥ ሆኖ በንድፈ ሃሳብ ያዘጋጀው ማኒፈስቶው ( የትግል ፕሮግራሙ ) ጥር ወር 1967 ዓ.ም. ኤርትራ ሳሕል በረሃ ወርደው የአንድ ወር ወታደራዊ ትምህርታቸው ያጠናቀቁ ቁልፍ አመራረቹ የሚሰጣቸው ትምህርት ጨርሰው የካቲት ወር 1967 ዓ.ም. ደደቢት በረሃ እንደገቡ ፡ተሰባስበው የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት በሚል የዛሬው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ መሰረቱ ።በዚሁ እንዳሉም ይዘዉት የመጡ ፀረ ኢትይዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ፤ ፀረ ኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት ፕሮግራማቸው እጅግ አጠናክረው በመፃፍ አዘጋጅተው ጨረሱ።ይህ የአቋም ፖሊሲ ፕሮግራም፤በወቅቱ የነበሩ አመራሮች የማ.ገ.ብ.ት ወይም የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት የዛሬው ህ.ወ.ሓ.ት. ፕሮግራሙ ኢትዮጵያ ዳግም ተመልሳ ሂወት እንዳትዘራ ሃገራዊ አንድነትዋ ፤የህዝብዋ አንድነትና ኢትዮጵያዊነቱ እንዲከስም እንዲጠፋ ተደርጎ የተዘጋጀ ፕሮግራም ፤ከየካቲት ወር 1967 ዓ.ም. እስከ ጥር ወር 1968 ዓ.ም.ጊዜ በመውሰድ የአንድ ዓመት ጥናትና እርምት ፈጀ ፤ተጠናቆ በመዝጋጀት በመጨረሻ በመፅሓፍ መልክ ተሰናድቶ ፤የካቲት ወር 1968 ዓ.ም 1 በትግርኛ 2 በአማርኛ 3በእንግሊዝኛ ተባዝቶ ተጠርዞ በየአስፈላጊነቱ ተሰራጨ።ይህ የህ.ወ.ሓ.ት. ፕሮግራም በብዙ ኢትዮጵያዊ እጅ ስለሚገኝ ዝርዝር መረጃው አላነሳውም ፤ለአብዮቱታየ መነሻ ሁለት ነጥቦች አቀርባለሁ ።

1ኛ ትግራይ ነፃ ሃገር ከአፄ ዮሓንስ 4ኛ ሞት በኋላ በተስፋፊውና ወራሪው ዳግማዊ ምኒሊክ መሪነት ነፃ ሃገር የነበረችው ትግራይ በአማራው ቅኝ ግዛት ሥር ወደቀች::ህዝብዋም ለመክራና ችግር ለስደት ለድንቁርና ወ.ዘ.ተ.ተዳረገ ይላል ።

2ኛ የዳግማዊ ምኒሊክ ወራርና መስፋፋት ትግራይና ህዝብዋ በቅኝ ግዛቱ ሥር እንደተቆጣጠረ ፤ዘመቻውን በማስፋት ዛሬ ኢትዮጵያ ተብላ በምትጠራው ሃገር አካባቢ የሚገኙ ነፃ ሃገር ሆነው ራሳቸውን ችለው ህዝባቸው የሚመሩ የነበሩ የተለያዩ ብሄር፤ ብሄረ ሰቦች፤ በአማራው ነፍጠኛ ሠራዊቱ ጥቃት ተፈፅሞባቸው፤እነዚህንም በአማራው ስርአት ቅኝ አገዛዝ ሥር ከወደቁ በኋላ ኢትዮጵያ ተብላ የምትጠራው ሃገር በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ምኒሊክ የመሰረታት ሃገር ይህች የዛሬዋ ኢትዮጵያ ናት ። ትግራይም ከአማራው ቅኝ አገዛዝ ስርአት በብረት ሃይል ትግል ነፃ ወጥታ የቀድሞው ሃገራዊን ነፃነትዋ ታስመልሳለች ።የራስዋንም መንግሥት ትመሰርታለች ።በዚሁ የህ.ወ.ሓ.ት. ፕሮግራም የተካተተው የትግራይ መንግሥት ሲመሰረት ለሚመሰረተው የትግራይ መንግሥት ድንበሩን ማስፋት ከሱዳን ሃገር በድንበር ማገናኘት የድርጅታችን ተግባር ነው።የትግራይ መንግሥት ሰፋፊ የእርሻ መሬት በሌለበት ብቁ ሃገር ለመሆን ስለማይቻል ከጎንደር ጠ/ግዛት ሰሜን ጎንደር ወይም በቅድሞ አጠራሩ ሰሜን ቤጌምድር ፤ ወልቃይት ፤ጠገዴ፤ጠለምት፡ቃፍታ ሁመራ (ሰቲት ሁመር) ወደ ትግራይ በማጠቃለል ከሱዳን ድንበር በቀጥታ ትግራይ ትገናኛለች ባለ ሰፊ የእርሻ መሬትም እንሆናለን ከዚሁ በማይለይ ከወሎ ጠ/ግዛት ከአለዋሃ ምላሽ እስከ ራያና ቆቦን በማካለል በትግራይ ግዛት ውስጥ ይሆናል ። የህ.ወ.ሓ.ት. መሪዎች ይህን እቅድና ፖሊሲ ያዘጋጁት 1 አረጋዊ በርሄ 2ግደይ ዘርአፅዮን 3 ስብሃት ነጋ 4 አባይ ፀሃየ 5 ሥዩም መስፍን 6 መለስ ዜናዊ ሲሆኑ ፤ በፕሮግራሙ እንደ ዋና የትግሉ አቋም አስገብተው ትግሉን ቀጠለ።ይህም በተግባር ለመፈፀም በተለይ በሰሜን ጎንደር እነዚህ የህ.ወ.ሓ.ት. መሪዎች ሙሉ በታጠቀ ኋይላቸው አሰማርተው የሰሜን ጎንደር ነዋሪው አማራው ግፍ ተፈፅሞበታል፤ገደሉት ዘሩን ለማጥፋት ለዓምታት ሰፊ እንቅስቃሴ አካሂደዋል ፤ገደሉት ፤ አፈናቀሉት ፤ቀሪዉም በስደት ተበታተነ ። በወሎ ጠ/ግዛትም ተመሳሳይ ድርጊት ህ.ወ.ሓ.ት. ፈፅመዋል።ድንበር ዘለል የመሬት መስፋፋት ሕገ ወጥ ወራር ነው ። የመስፋፋት ፖሊሲ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በህ.ወ.ሓ.ት.መሪዎች ተባራዊ ተደረገ፤አሁንም አልቆመም ህ.ወ.ሓ.ት.የመስፋፋት ፖሊሲው አጠናክሮ እየቀጠለበት ይገኛል።ይህ ፀረ ኢትዮጵያ አንድነት ፀረ ህዝብ ፤ደም አፋሳሽ ሃገር አፍራሽ ፤ አደገኛ ፋሽሽታዊ ፖሊሲም ነው ። ህ.ወ.ሓ.ት. ያዘጋጀው ፕሮግራም ወደ ህዝብ ባሰራጨው ወቅት፤ለመጀመሪያ ተቃውሞ የገጠመው፤ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ የትግራይ ህዝብ ነበር ፕሮግራሙን በማውገዝ ጭምር አልተቀበለዉም፤ የከተማውና የገጠሩ ነዋሪ ህዝብ ሁሉ ለማለት ይቻላል እሳት ውስጥ ከቶ አቃጠለው ። ወያኔ የትግራይ ሃገር ከአማራው ቅኝ አገዛዝ ስርአት ነፃ ለማውጣት ትግሌን ጀምሬ አለሁ ብሎ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ ለ5 ዓመታት .በፅናትና በጥንካሬ ወያኔን የታገለው ግልፅና ስውር ጥቃቶች አድናቆት በሚሰጥበት የትግል ዘዴ የትግራይ ህዝብ ነው። ቢታገለዉም አልተሳካለትም ፤በወያኔ ሃብት ንብረቱ እየተወረሰ ቤቱ ፈረሰ፤ እሱም እየታፈሰ ወንድ ሴት ወጣት ሽማግሌ፤ በቀንና ለሊት ከያለበት እየተያዘ እየታፈነ 06 –ሓለዋ ወያነ አስገብተው ጭካኔ በተሟላበት በማሰቃየት የሚቀብርበት ሰፊ ጉድጓድ ራሱን በመቆፈር ፤በቆፈረው ጉድጓድ በጅምላ እያስገቡ በጥይት ረሽነው ገድለው ጨረሱት ።ከላይ የተጠቀሱ አመራሮች። ኢትዮጵያና ህዝብዋም ጭምር አሁን ያሉበት ምስቅልቅልና ችግርም ያደረሱት እነዚህ ሰዎች ናቸው ፤የአማራው የዘር ማጥፋት ወንጀልም ፈፅመዋል ።የኢትዮጵያ ሃገር ሉአላዊነት አፍርሰዋል።

ዛሬ በኢትዮጵያ ሃገራችን በህ.ወ.ሓ.ት. እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ እንዳይደርስ ብሎ አስቀድሞ የተከላከለው የትግራይ ህዝብ የሂወቱ ቤዛ መስዋእትነት ከፍሎ ሂወቱ የገበረው ኢትዮጵያዊ ነው። ኢትዮጵያ ሃገሬ በወያኔዎች ትፈርሳለች ህዝብዋም ለክፉ የመበታተን አደጋ ይደርስበታል ብሎ ስላመነ ስለ ተነበየ ነበር የመጀመሪያ የወያኔ ግፍ ቀማሽ ያደረገው ። ያ የትግራይ ህዝብ ዛሬ የለም፤ኢትዮጵያዊ ግዳጁ ፈፅሞ በወያኔዎቹ ተገድሎ ከዚች ዓለም ተሰናብቶዋል።የከፈለው ከባድ መስዋእትነት ግን በታሪክ ማህደር ውስጥ መዝገብ ተዘግቦ ይገኛል።የኢትዮጵያ ህዝብም ወንድሙ ለሆነው የትግራይ ህዝብ የከፈለው መስዋእትነት ሰሜን ጎንደር ፤አለዋሃ ምላሽ እስከ ራያቆቦ ያንተ የትግራይ ህዝብ መሬት ነው ሲሉት የኔ አይደለም፡ ይህ መሬት ግዛቱ የጎንደር አማራ፤የወሎ ግዛት እንጂ ፡የትግራይ ግዛት ሆኖም አያውቅም የትግራይም አይደለም የትግራይ ህዝብ አማራ መሬቴን ቀማኝ ብሎ አያውቅም፤ የሚልበትም ምክንያት የለውም ፡ የህ.ወ.ሓ.ት. ፕሮግራም ትልቁ የስህተት ጥፋቱ እዚህ ላይ ነው ። በማለት አጥብቆ በመቃወሙ ከባድ መስዋእትነት ከፍሎ ያለፈ ኢትዮጵያዊ ነው።ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ በፀሎት ሊዘክረው ይገባል ።

በሃገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለውን በጣም አደገኛ የህ.ወ.ሓ.ት.የመሬት መስፋፋት ፖሊሲው የኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላምና የሃገር አንድነትና ለክፉ አደጋ የሚዳርግ ነው።ይበልጥ የሚጎዳ ደግሞ ንፅሁ ኢትዮጵያዊው የትግራይ ህዝብ ነው።የህ.ወ.ሓ.ት. መሪዎች የትግራይ ህዝብ ባላቸው የሃይል ጉልበት አፍነው በመያዝ የራሳቸው ፍላጎት መጠቀሚያ ፖሊሲ በማድረግ በስሙ እየነገዱበት እንደሸቀጥ ዕቃ መጠቀም የጀመሩት ደደቢት በረሃ ከወጡ ጀምሮ እንሆ እስከ ዛሬ ድረስ 43 ዓመት አስቆጥረዋል ።ይህ ኢትዮጵያዊ የትግራይ ህዝብ ከባርነት ወለል በታች ሆኖ ፤በባሪያ ስርአት አገዛዝ የህ.ወ.ሓ.ት. ፖሊሲ መጠቀሚያና መነገጃ እያደረጉት ነው ።በማያምንበት በማይፈልገው በሰላማዊ ኑሮው በሂወቱ ከባድ እንቅፋቶች እየፈጠሩበት ነው።የትግራይ ህዝብ ህ.ወ.ሓ.ት በተስፋፊ ፖሊሲው በጉልበቱ ከጎንደር፤ ከወሎ፤ ከአፋር፤ወ.ዘ.ተ. በመስፋፋት ፖሊሲው በወረራ ወደ ትግራይ ያካለላቸው መሬቶች አያምንበትም አይቀበለዉም ።የህ.ወ.ሓ.ት. መንገድ በኢትዮጵያውያን ወንድማሞች የአንዲት ሃገር ልጆች መካከል ብጥብጥና ህውከት ፈጥሮ ፤የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነት የመበታተነ እቅድና የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት የሚንድ ፖሊሲ ነው።ስለሆነም የጥቃቱ ሰለባ የትግራይ ህዝብ ይሆናል። የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ፤ክቡር ጠ/ሚር ዶ/ር አብይ አህመድ የትግራይን ህዝብ ከዚሁ አረሜኔ ፋሽሽት ወያኔ አድኑት ።ህ.ወ.ሓ.ት.እና ካድሬዎቹ፤ ደጋፊ አባሎቹ፤ ልዩ ፖሊሶቹ፤ የወያኔ ምልሻ፤ በኢትዮጵያ ህዝብ በሚፈጥሩት ችግርና እየፈፀሙት ያለውን ግፍ በተለይ በአማራው በጎንደር ጠ/ግዛት በወሎ ጥ/ግዛት በአፋር ወረዳዎች ፤ ግድያ እስራት ብዙ ነው ።ህ.ወ.ሓ.ት. ወያኔ በመስፋፋት ፖሊሲው የሚፈፅማቸው ያለውን ኢ-ሰብአዊ ተግባሩ በትግራይ ህዝብ ፍላጎት እየፈፀምኩት ነኝ በማለት ፋሽሽታዊ ድርጊቱን ፤ንፁህ በሆነው ኢትዮጵያዊ በትግራይ ህዝብ እያላከከ ይገኛል።የትግራይ ህዝብ ግን በዚሁ ድርጊት ውስጥ የለበትም ፤እንዲያውም አያውቀዉም ጭምር። ክቡር የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ /// ክቡር የኢትዮጵያ ጠ/ሚር ዶ/ር አብይ አህመድ/// ከዚህ በታች የሚታየው ካርታ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ የድርጅቱ የቀድሞው አመራርና የአሁኖቹ መሪዎች ተሰባስበው የትግራይ ግዛት ይህ ነው፡ብለው አምነዉበት ያፀደቁት ነው። ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ያለ የተስፋፊ ፖሊሲ እቅድም ይህ ነው። ይህ የወያኔ ህ.ወ.ሓት.የተስፋፊነት ወረራ በይፋ ያወጁት በድርጅቱ ልሳን በሆነው Tigrai On line sep 6 2018 የመስፋፋት ፖሊሳቸው ግልፅ አድርገዉታል ፤ ካርታውን እንመልከት ወይኔ ቀደም ብሎ በወረራ ከይዘው በጎንደር ጠ/ግዛት ወልቃይት፤ጠገዴ፤ቃፍታ

ሑመራ፤ጠለምት ከወሎ ጠ/ግዛት ከላይ አለውሃ ምላሽ እስከ ራያና ቆቦ ፡ በተጨማሪ በሰሜን በኩል የአፋር ወረዳዎች እንደነ በራሕሌ፤ ዳሉል ወ.ዘ.ተ ፤በጎንደር ከላይ አርማጮህ እስከ ታች አርማጮህ፤ ዓብድራፈዕ፤መተማ፤አብርሃ ጅራ፡ወሎ ጠ/ግዛት ደቡቡ ሁሉ ያጠቃለለ ነው ፡እነዚህ ሁሉ የትግራይ ግዛት ናቸው ብሎ የህ.ወ.ሓ.ት. የቀድሞውና የዛሬ መሪዎች የመስፋፋት የሃይል ወራራ በመፈፀምና ለመፈፀም እየተዘጋጁ ናቸው ።ህዝብና መንግሥት ትክረት በመስጠት ይህ ወራሪው የወያኔ ሕገ ወጥ ተስፋፊነት ማስቆም ግዴታ ነው ።በስንት ሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ ከትውልድ ቦታው ተፈናቅሎ ተሰዶስ የት ሊገባ ነው ?

ክቡራን ሆይ ፤የተስፋፊነት ወረራ ሃገርና ህዝብ ያጠፋል፤ ሃገር ያፈርሳል ፤ሃገር ስርአተ አልበኝነት ያደርጋል፤ይህ ከተከሰተ ደግም ሃገር ይፈርሳል ህዝብ ይበታተናል ሃገር የለም ። የወያኔ የአሁኑ መስፋፋት የወረራው ፖሊሲም የሚፈፀምባቸው፤ተፈፅሞባቸው የሚገኙ 1ኛ የጎንደር አማራው ህዝብ2ኛ የወሎ አማራ ህዝብ 3ኛ የአፋር ህዝብ ዋናዎቹ በሰለባው የተጠቁ ናቸው ። ይህ የመስፋፋት ወረራ ፤ ፀረ ማንነት መብት ፖሊሲ ነው ፡ወያኔ ህ.ወ.ሓ.ት. በማን አለብኝ ትእቢቱ የኢትዮጵያውያን መብትና ነፃነት በሃገራቸው ውስጥ በጠራራ ፅሓይ እየገፈፈ ነው ።የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ይህ የቅኝ ግዛት መስፋፋት ማቆም አለበት ፡ይህ ካልተደረገ ኢትዮጵያና ህዝብዋ ወደ ክፉ አደጋ ይወድቃሉ ። የወያኔው ፋሽሽት የማፍያ ጥርቅም በኢትዮጵያ ሕግም በዓለም ሕግም ተገዶ ማቆም ይገባል፡ከዚሁ በፊትም በተስፋፊ ፖሊሲው የወረራቸው ቦታዎች ሁሉ የጎንደር ፤የወሎ፤ የአፋር መመለስ ግዴታው ነው ።ወያኔ ህ.ወ.ሓ.ት. የኢትዮጵያ ሉአላዊነት እያፈረሰ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት እየበጠበጠ ፀረ ሰላም ግፈኛ ፋሽሽት ድርጅት መቀሌ መሽጎ መኖር የለበትም ። ይህ ከታች ካርታ የሚያመልክተው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ለመውረር የተዘጋጀበት የአማራ፤የወሎ፤የአፋር፤ መሬት፤ወያኔ የራሱ በሆነው ልሳን( ትግራይ ኦን ላይን) በግልፅ ያወጀው የመስፋፋት ወራር ነው። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ይህ ደም አፋሳሽ ፤ሃገር አፍራሽ ፤የህ.ወ.ሓ.ት.የመስፋፋት የሤራ እቅድ ከአሁኑ በሕግ ማቆም አለበት ።

በጦላይ ቆይታዬ የተማርኩት፣ የታዘብኩት፣ የተገነዘብኩት… (በናፍቆት ዮሴፍ)

Addis Admass

አፈወርቅ አምበሌ ተወልዶ ያደገው እዚሁ አዲስ አበባ ፍልውሃ አካባቢ ነው፡፡ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በጅማ ዩኒቨርሲቲ በሜዲካልላብራቶሪ ዲፕሎማውን እንዳገኘ ይናገራል፡፡ በተመረቀበት ሙያ ለአንድ ዓመት ያህል በቦንጋ አካባቢ ከሰራ በኋላ ከወንድሙ ጋር ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደሩሲያ ያቀኑ ሲሆን በሩሲያ የ6 ወር ቆይታቸው ነገሮች እንደጠበቋቸው ባለመሆናቸው ወደ ሆላንድ ይሻገራሉ፡፡ ከሦስት ዓመት የስደት ቆይታ በኋላ ወንድሙ እዚያው ሲቀር እሱ ግን ወደ አገሩ መመለሱን ይገልጻል፡፡ የ36 ዓመቱ አፈወርቅ አምበሌ በቅርቡ ከአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ተይዘው ወደ ጦላይ ከተወሰዱትና ባለፈው ጥቅምት 9 ቀን 2011 ዓ.ም ከተለቀቁት 1700 በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ ይሄ ቃለ ምልልስም ከሌላው ህይወቱ ይልቅ በጦላይ ቆይታው ላይ ያተኩራል፡፡ እንዴትና ከየት ተያዘ? በጦላይ የነበረው አያያዝና ሥልጠና ምን ይመስላል? በአንድ ወር ቆይታው የታዘበውንና የተገነዘበውን ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ እንዲህ አጫውቷታል፡፡

ከወንድምህ ጋር ሆላንድ ከገባህ በኋላ አንተ እንዴት ለመምጣት ወሰንክ?
ነገሮች እንደምጠብቃቸው አልሆኑልኝም። ውጭ አገር አውሮፓ ሲባል የምትገምቺውና የምትጠብቂው ነገር አለ አይደል፡፡ አልሆነም። እኔ እንደውም ለመመለስ ያን ያህል ጊዜ አይወስድብኝም ነበር፡፡ ነገር ግን ማቄን ጨርቄን የምትይው ነገር አለ፡፡ በዚያ ላይ የወንድሜና የእኔ ጉዳይ አንድ ላይ ስለነበር ቆየሁ እንጂ ወዲያው ነበር የምመለሰው፡፡ የሁለታችን ኬዝ አንድ ላይ ሆኖ እኔ በመመለሴ ምክንያት ወንድሜ እስካሁን የመኖሪያ ፈቃድ አላገኘም፡፡ ያኛው ከተመለሰ ይሄኛውም ወደ አገሩ መግባት ይችላል በሚል፡፡ የወጣው ወጪ፣ የቤተሰብ ጉዳይና መሰል ነገሮች ከአገሬ ወጥቼ ሶስት ዓመት እንድቆይ አገዱኝ እንጂ ወዲያው እመለስ ነበር፡፡
አገር ቤት ከተመለስክ በኋላ ምን መስራት ጀመርክ?
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማታው የትምህርት ክፍል፣ ሜዲካል ላብራቶሪ ለዲግሪ እየተማርኩ ቀን ደግሞ በቅድስተ ማሪያም ዩኒቨርሲቲ ኮምፒዩተር ሳይንስ እማር ነበር፡፡ በርቀት ትምህርት ደግሞ ሂስትሪ ስማር ነበር፡፡
ሶስት ትምህርቶችን በአንድ ጊዜ መማር አይከብድም?
ጊዜሽን በደንብ ከተጠቀምሽበት የሚከብድ ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን በቤተሰብ በኩል የሆነ ቀውስ ሲመጣ፣ ሁለቱን አቁሜ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲውን ሜዲካል ላብራቶሪ ጨርሼ ዲግሪዬን ያዝኩኝ፡፡ ቆይቼ ደግሞ አቅሜን አሰባስቤ ማስተርሴን ጀመርኩኝ፡፡ በመሃል አባቴም እናቴም ተከታትለው ሲሞቱ፣ ብዙ ነገሬ ተበለሻሸና አቆምኩት፡፡ አሁን መማር ካቆምኩኝ አራት አመት አካባቢ ሆነኝ፡፡
ምን እየሰራህ ነበር የምትተዳደረው?
አንድ ኢንጂነር ጓደኛ አለኝ፤ አብሮኝ የተማረ። ኮንትራክተር ነው፡፡ ከእሱ ጋር ነው የምሰራው፡፡ እርግጥ ጓደኛዬ ስለሆነ ባህሪዬን ያውቃል፡፡ እንግባባለን። ነገር ግን አገሪቱ ላይ ያለው አጠቃላይ ቢሮክራሲ– የቀጣሪ ቢሮክራሲ ስለማይመቸኝ ተቀጥሮ መስራት አልችልም፡፡
በሙያህ ለምንድነው የማትሰራው?
ቦንጋ ሰርቻለሁ፡፡ በተለያዩ ነገሮች ምክንያት ከሙያዬ ተራርቄያለሁ፡፡ በጤና ጥበቃ ህግ መሰረት ለረጅም ጊዜ ከሙያው ርቀሽ ቆይተሽ እንደገና መጀመር አትችይም፡፡ ሙያው ከጤና ጋር የተገናኘና ሪስክ ያለው ከመሆኑና የመረሳት ባህሪ ያለው ከመሆኑ አንፃር፣ ህጉ ትክክለኛ ቢሆንም፣ እኔ ግን ሲከፋኝ የምፅናናበትን ስራዬን እንዳልቀጥል አድርጎኛል፡፡ በዚህ መስከረም እንደ ምንም ብዬ ያቋረጥኩትን የማስተርስ ትምህርቴን እቀጥላለሁ ብዬ ነበር፣ ሌላ እክል ገጠመኝ፡፡
ከተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ተይዘው ጦላይ ማሰልጠኛ ከገቡት ወጣቶች አንዱ ነህ፡፡ እስኪ የትና እንዴት እንደተያዝክ ንገረኝ?
የተያዝነው ሺሻ ቤት ነው፡፡ እኔ መጠጥ ቤት ማምሸት ትቻለሁ፡፡ የምጠጣውን በውሃ ፕላስቲክ ይዤ ሺሻ ቤት ነው የምሆነው፡፡ መስከረም 8 ቀን 2011 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 ላይ ነው መጥተው ጠራርገው የወሰዱን፡፡
ለምንና የት እንደሚወስዷችሁ ለመጠየቅ ወይም ለመከራከር አሊያም ለማስረዳት አልሞከራችሁም?
እኔ ምንም አላልኩም፡፡ ለመከላከል ለመደባደብ የሞከሩ ነበሩ፡፡ እኔ ትፈለጋለህ ከተባልኩ ፖሊስ ጣቢያ ድረስ ራሴ ነኝ የምሄደው፤ ፈልጋችሁኛል ወይ እላለሁ፡፡ ደግሞም ነፃነቴ ታውቆ እስከምትለቁኝ ድረስ ለማምለጥ እንኳን አልሞክርም፤ ራሴን የማውቅ ሰው ነኝ ብያቸዋለሁ፡፡
ለማምለጥ የሚሞክሩ ነበሩ እንዴ?
ከተለያየ ቦታ ታፍሰው ከመጡ ልጆች ውስጥ ለማምለጥ፣ ፖሊስ ለመደብደብ ሁሉ የሞከሩ እንደነበሩ ሰምቻለሁ፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያ አያያዛቸው ያስፈራ ነበር፤ በኋላ መለየት ጀመሩ እንጂ፡፡ ለምሳሌ አንዷን ከእኛ ጋር ያዟትና የ10 ወር ህፃን ልጅ አለኝ አለቻቸው፤ ወደ ቤቷ ይዘዋት ሄዱ፡፡ ልጅዋን ሲያዩ፣ ይለቋታል ስንል፣ ከእነ ልጇ ይዘዋት ተመለሱ፤ ልጇን እዚያው ስታጠባ አደረች፡፡ በነጋታው ግን ሴቶችን መፍታት ጀመሩ፡፡
ወደ ጦላይ ማሰልጠኛ ካምፕ የተወሰዳችሁት በስንተኛው ቀን ነበር?
ማክሰኞ ተያዝን፣ አርብ ቀን ተወሰድን፡፡ ማክሰኞ የተያዘ አለ፣ ረቡዕ የተያዘ፣ ሐሙስም አርብም የተያዘ አለ፡፡ ሁሉም በአንድ ቀን አልተያዘም፡፡ ከተለያየ ቦታ በተለያየ ቀን ነው ያንን ሁሉ ወጣት የያዙት፡፡ ብቻ አልሞላ ብሏቸው መከራቸውን ሲበሉ ነበር፡፡
አልሞላ ብሏቸው ስትል ምን ማለትህ ነው?
እኔ እጃ ከየአካባቢው ኮታ አለ ማለት ነው፡፡ ከእኛ ክፍለ ከተማም ብዙ ነው የያዙት፤ ከቂርቆስ ማለት ነው። እኔ አሁን የተያዝኩት ሳር ቤት አካባቢ ነው፡፡
ጦላይ ማሰልጠኛ ካምፕ ስትገባ ምን ተሰማህ —- አልፈራህም?
ብዙዎች ፈርተው ነበር፡፡ ኡኡ ብለን እንጩህ፣ ህዝብ ይስማ እንለቀቃለን የሚል ሀሳብም ተነስቶ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ በዚህ መጠን የመንግስት አስተሳሰብ ይወርዳል ብዬ ስላልገመትኩ፣ በግርምት ነበር የምጓዘው እንጂ አልፈራሁም፡፡ እንደውም ለመጀመሪያ ጊዜ የምኖርበትም የምሞትበትም ምክንያት የሰጡኝ ይመስለኛል፡፡
እንዴት ማለት — አልገባኝም?
ምን ለማለት ነው? ከዚያ በፊት የምታወሪው በየመንደሩ ነው፡፡ የምታወሪው በመላምት ነው፡፡ ሁሉ ነገር በግምት ነው፡፡ አንደኛ ስለ መንግስት ችግር፣ በሰው ላይ ስለደረሰ ነገር ሳይሆን ያለ ምንም ጥፋት ታፍሼ ስሄድ በራሴ ላይ በደረሰ በደል ነው የማወራው፤ የሆንኩትን ያየሁትን ነው የምናገረው፡፡ በሌላ በኩል፤ አዋቂም ይሁኑ አይሁኑ፣ ከመንግስት ተወክለው ለመጡ ሰዎች፣ አገሪቱ ላይ ያለውን አጠቃላይ ችግር በቀጥታ ለራሳቸው እንድናገር መድረክ አግኝቻለሁ፡፡ በእርግጥ በፊትም የሚሰማኝን ነገር በማንኛውም ቦታና ሁኔታ የመናገር፣ የመግለፅ ችግር የለብኝም፤ ግን እንደዚህ ለሚመለከተው አካል ፊት ለፊት መናገር ደግሞ ሌላ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡
በማሰልጠኛው ውስጥ ሆናችሁ የሚጎበኟችሁ የመንግስት ባለሥልጣናት ነበሩ?
ትልልቅ የምትያቸው የፖሊስ ኮሚሽነሮች በክፍለ ከተማ ደረጃም ከዚያም በላይ ያሉት ይመጡ ነበር፡፡ እንግዲህ ከሰሙን ብዙ ተናግረናል፡፡
በካምፑ ውስጥ አያያዛችሁ እንዴት ነበር? እስኪ ንረገኝ —
ስልጠና የጀመርነው ከ10 ወይም ከ11 ቀን በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ጠዋት ለቁርስ ትወጫለሽ፣ ከዚያ ሽንት ቤት ከዚያ ወደ ቤት፡፡ ምሳ ሰዓትም ሆነ ራት ላይ እንደዚያው ነው፡፡ ውሃ ሲመጣ ገላ ለመታጠብ ወይ ልብስ ለማጠብ ብቻ የተወሰነ ሰዓት ትወጫለሽ፤ በቃ!
ቅያሪ ልብስ አልያዛችሁም— ምኑን ነበር የምታጥቡት? ወይስ ልብስ ሰጧችሁ?
እስከነገርኩሽ ቀን ድረስ ልብስ አልነበረንም፤ ከዚያ በኋላ ከየት እንደመጣ አናውቅም፣ ኖርማል ቱታና ማሊያ ቲ-ሸርት ቁምጣ ሰጡን፡፡ እንደየ እድልሽ ቁምጣም ቱታም ሊደርስሽ ይችላል፡፡ እኔ ቱታ ነበር የደረሰኝ፤ በግድ ልበሱ ተባለ ለበስን፤ 15ኛው ቀን ላይ ብርድ ልብስ ተሰጠን፤ ፍራሽ ላይ ትተኛለሽ፡፡
አመጋገባችሁ ምን ይመስል ነበር? የሰብአዊ መብት ጥሰት?
ምግብ ጠዋት ዳቦ በሻይ፣ ምሳ ዳቦ በወጥ፣ ራት ዳቦ በወጥ፤ አለቀ! ከዚህ ውጭ እንጀራ ምናምን ሌላ ነገር የለም፡፡ ሰብዓዊ መብት ላልሺው፣ እነሱ እንደውም በዋናነት እሱ ርዕስ ላይ ነው ማውራት የሚፈልጉት። መብታችሁን የነካ፣ የሰደባችሁ ካለ ተናገሩ ይላሉ፡፡ የእኔ ጥያቄ ግን ይሄ አይደለም፡፡ አውሮፓም ኖሬያለሁ፤ ጫፌን ነክቶኝ የሚያውቅ የለም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እኔ ጦላይ በዚያ ሁኔታ የተገኘሁት፣ ሰብአዊ መብቴን ተነጥቄ ነው የሚለው ነው፤ ጥያቄዬ፡፡ ለምንድን ነው ከእድሜዬ ላይ አንዲትስ ሰከንድ ብትሆን፣ በሌላ ሰው የሚወሰነው? ነው ጥያቄዬ፡፡ እዚያ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩ፤ ብዙዎችም የሚጠየቁ፡፡ ምግቡ እንዲህ ቢሆን፣ ውሃ እንደዚህ ቢደረግ፣ ብርድ ልብስ ቢሰጠን ሌላም ሌላም ጥያቄዎች … የእኔ ጥያቄ ግን ለምን እዚያ ቦታ ላይ ተገኘሁ ነበር፡፡ መሰረታዊው ጥያቄ ደግሞ ይሄ ይመስለኛል፡፡ የመለሰልኝ ግን አልነበረም፤ ከዕድሜዬ ላይ 30 ቀናት ያለ ፍላጎቴ ተቀንሶ፣ በሰው ቁጥጥር ውስጥ ሆኜ ነው የከረምኩት፡፡ ይሄ ያለ ምንም ጥፋትና ወንጀል ሲሆን ደግሞ ያሳምማል፡፡ እርግጥ የሚሰደቡም የሚመቱም ልጆች ነበሩ፡፡ እኔን ማንም ነክቶኝ አያውቅም፤ ሁሌም ለፖሊሶቹ እነግራቸዋለሁ፤ እኔ ትዳር የለኝም፤ ልጅም የባንክ አካውንትም የለኝም፡፡ ያለኝ ስሜና ሰብዕናዬ ብቻ ነው፤ እሱ ላይ አልደራደርም፡፡ ይሄንን አስጠብቄ የወጣሁ ይመስለኛል፡፡
ስልጠናና ትምህርት በሚሰጣችሁ ጊዜ አጥብቀህ ትከራከርና ትሞግታቸው እንደነበር ሰምቻለሁ ለመሆኑ ትምህርትና ስልጠናው ምን ምን ያካተተ ነበር ስለመብት ስለ ህግ የበላይነት ስትሟገትስ የተለየ ጫና አያሳድሩብህም?
ስልጠናው በዋናነት በህገ መንግስቱና በህግ የበላይነት ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡ አንዳንዱ ትምህርት እንደሚገልፀው ከሆነ፤ እኛ እዚያ ቦታ ላይ መገኘት አልነበረብንም፤ ማለቴ እኛን የሚመለከት አይደለም፡፡ እንደው እንዲህ አሰለጠንን፣ እንዲህ አደረግን ለማለትና ከህገ መንግስትና ከህግ የበላይነት ውጭ የሚያሰለጥኑት ነገር ስለሌለ እንጂ ያንን ስልጠና ለእኛ መስጠት አልነበረባቸውም፡፡ እኔ ይሄንንም አልቀበልም ነበር፡፡ ምንድነው የምላቸው፤ የሰውን ልጅ በግድ በጉልበት ይዞ አካላዊና ወታደራዊ ስልጠና መስጠት ይቻል ይሆናል፣ እንዴት አዕምሮውን እናሰለጥናለን ትላላችሁ፣ ያውም ይሄን ያህል የኖረ ሰው፣ በዚያ ላይ ያለ ፍላጎቱ እንዴት ይሆናል? ለመሆኑ ምን እያደረጋችሁ እንደሆነ ታውቁታላችሁ ወይ?— እላቸው ነበር፡፡ እነሱ ደግሞ ከላይ ታዘን፣ ይህን ለማስተማር ነው የመጣነው፣ ለጥያቄያችሁ መልስ የለንም ይሉናል፡፡
አንድ ሰው እኔን ሊያስተምር ሲመጣ፣ ማንን ነው የማስተምረው፣ አቅሙ ምን ያህል ነው ማለትና እኔን ማወቅ አለበት፡፡ ህይወት አጭር ነው፤ ትምህርት ሰፊ ነው፤ እኔ 1ኛ ክፍልን 12 ዓመት መማር የለብኝም፤ በአንድ አመት ጨርሼ ወደ ቀጣዩ ትምህርት ማለፍ አለብኝ፡፡ ይህቺ አገርም እኔም መማርና መለወጥ ካለብን፣ በማይረባ ነገር ጊዜ ገንዘብና ጉልበት መባከን የለበትም፡፡ ይሄን እላለሁ እጠይቃለሁ፣ እሟገታለሁ። የሚገባቸው ፖሊሶች ሀሳቤን ይረዳሉ፣ ያልገባቸው ደግሞ አንተ ምንድነው እዚህም እዛም የምትናከሰው ይላሉ፡፡ ከዚህ ያለፈ ግን የተለየ ጫናም ድብደባም ስድም ደርሶብኝ አያውቅም፡፡
ገና ስትወሰዱ በምን ጥፋት ተከሰሳችሁ?
ምንም ዓይነት ክስ አልነበረም፡፡ የብዙዎች ፍርሃትም በምን እንከሰስ ይሆን የሚለው ነበር፡፡ እንደውም ወደ ጦላይ የተጋዘው ሰው አንዱ የተነጠቀው መብት ይሄ ነበር፡፡ ከሳሹንም በምን እንደተከሰስም አያውቅም ነበር፡፡ ልንለለቅ ሶስት ወይም አራት ቀን ሲቀረን፣ መርማሪዎች መጥተው የክስ ቻርጅ አቀረቡ። በሶስት ወንጀል ክስ አለባችሁ አሉን፡፡
ምን ምን ነበሩ ሶስቱ ክሶች?
አንዱ የብሄር ብሄረሰቦችን እኩልነት የሚያንፀባርቀውን፣ አርማ ያለውን ባንዲራ ትታችሁ አርማ የሌለውን ይዛችኋል ይላል፡፡ ይሄ ማንንም የሚያስቅ ነው፡፡ ራሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለበት ነበር፣ አገር ምድሩ አርማ የሌለው ባንዲራ በየአካባቢው፣ በየሰላማዊ ሰልፉ፣ በየአደባባዩ ሲጠቀም የነበረው፡፡ ሁለተኛው ህዝባዊና መንግስታዊ ተቋማትን በኃይል በማፍረስና በማውደም እንዲሁም ከፀጥታ ኃይሎች ጋር እሰጥ አገባ በመፍጠርና ሁከት በመቀስቀስ ይላል። ይሄ ለእኔ ድራማ ነው፡፡ መጀመሪያ ክስ ይመጣብናል ብለን ያሰብነው ከሺሻ ቤት ጋር በተያያዘ ነበር፡፡ የጦላይ ወሬ ሲነሳ በሺሻ ቤት እንዳልሆነ ገባን፡፡ ከመካከላችን ነፍሰ ገዳይ፣ አስገድዶ ደፋሪም — የለም፡፡ ፍርድ ቤት ሳንቀርብ ከህግ አግባብ ውጭ ነው የቆየነው፡፡
ቤተሰብ ይጠይቃችሁ ነበር? በስልክ በፌስቡክ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ትገናኙ ነበር? ቴሌቪዥንስ ማየት ይፈቀዳል?
በፍፁም! ቤተሰብ መጥቶ ሳያየን ተመልሷል፤ ስልክም ኢንተርኔትም — አልነበረም፡፡ ቴሌቪዥንም አይተን አናውቅም፡፡ ምንም ዓይነት መረጃ ከማንም ጋር ተለዋውጠን አናውቅም፡፡
ታዲያ ከምን ተነስታችሁ ነው “ስለ እኛ በፌስ ቡክና በተለያዩ መንገዶች የሚነገረው እኛን አይወክልም” የሚል የአቋም መግለጫ አውጥታችሁ በቴሌቪዥን የተላለፈው?
ይሄን ስንሰማ አብረን ነው የሳቅነው፡፡ እኔ በበኩሌ እዚህች አዲስ አበባ እስክደርስ ምንም አይነት ግንኙነት አልነበረኝም፡፡ ከጦላይ መጥተን አዲስ አበባ ስንደርስ አንዳንድ ፖሊሶች ስልክ ለቤተሰብ እንድንደውል ተባብረውናል፡፡ የአቋም መግለጫው በጣም ያስቃል፤ በፌስ ቡክ የሚወራው እኛን አይወክልም ብቻ አይደለም፣ የተከሰስንባቸው ቀደም ብዬ የነገርኩሽ ጉዳዮች አሉ አይደለ መንግስት አልተሳሳተም፣ መታደስ ያለባቸውን ልጆች ነው የያዘው፣ በትክክል አድሷል፣ ተፀፅተን ህብረተሰቡን ለመካስ ነው የመጣነው ምናምን ይላል …. ይሄ እስካሁን በጣም በጣም ያስቀኛል፡፡
ይሄን ነገር ስትሰማ አልተቃወምክም?
ሲነበብ ሳይሆን ገና ሲፃፍ ጀምሮ ነው የተቃወምኩት። እኔ አወያይ ነበርኩኝ፡፡ የሄድነው ከ1270 በላይ ነን፡፡ በሶስት ሻምበል ተከፍለናል፡፡ አንድ ሻምበል 320 ገደማ ታራሚዎችን ይይዛል፡፡ የዚያ ሻምበል አወያይ ነበርኩኝ፡፡ ስለምናገር እኔን መረጡኝ፡፡
ከዚያስ?
አንድ ቀን አስተምረውን ሲጨርሱ ጥያቄ ካላችሁ ሲሉ እጄን አወጣሁና፣ እኔ እዚህ ቦታ ላይ እንደ ሰብሰዊ ፍጡር ከተቆጠርኩ መብቴን ጠብቁ፤ ስትፈልጉ የምታነሱኝ ስትፈልጉ የምትጥሉኝ አይነት ድንጋይ አድርጋችሁ ካሰባችሁኝ ተሳስታችኋል፡፡ ከአገርና ከመንግስት አለመረጋጋት አንፃር፣ እስከሆነች ቀን እጠብቃችኋለሁ፡፡ ከዚያ አልፋችሁ ያለ ጥፋቴ እዚህ የምታስቀምጡኝና ጊዜዬን የምታባክኑ ከሆነ፣ በግሌ ማንንም ሳልወክል እርምጃ እወስዳለሁ፤ ቢያንስ ያለ ጥፋቴ ልታስቀምጡኝ እንደማትችሉ ለማሳየት ራሴን አጠፋለሁ፡፡ ምን እንዳጠፋሁ ማን እንደከሰሰኝ፣ ለምን እንደተከሰስኩ የማወቅ መብት አለኝ፡፡ የአገሪቱን ህግ አክብሬ የትኛውም ቦታ የመኖር መብት አለኝ ስላቸው፤ ይሄው ግቢው ውስጥ ከዚህ እስከዚህ እንድትንቀሳቀሱ ፈቀድንላችሁ ይሉኛል፤ አንተ ማን ስለሆንክ ነው የምትፈቅድልኝ? እንኳን እዚህ በየትኛውም አለም ተዘዋውሬ እንድኖር ነው የተፈጠርኩት፤ ይህን የማታውቁና የማታከብሩ ከሆነ ራሴን በማጥፋት መብቴን አሳያለሁ እንጂ ለወራት እዚህ አልታሽም አልኳቸው፡፡ ከዚህ ንግግር በኋላ ስብሰባዎች ተደረጉ፤ ስልጠና መቼ እንደምንጀምር ተነገረን፡፡ እዛ ሻምበል ውስጥ ታውቄ ነው አወያይ የሆንኩት፡፡ ጠዋት ጠዋት እንማራለን፤ከሰዓት እኔና ሄኖክ የሚባል ልጅ አወያይተን ያንን ስልጠና ምን ያህል ተረድተውታል፣ ምን ያህሉ ተቃውመውታል የሚለውን እናቀርባለን፡፡ ትምህርቱ ከህገ መንግስቱ አንቀፅ አንድ ጀምረሽ እስከ መጨረሻው፣ ከዚያ ስለ ሰብአዊ መብት ነው የምንማር የነበረው፡፡ በእነሱ ቤት ህገ መንግስት፣ የህግ የበላይነት፣ ሰብዓዊ መብት የማናውቅ መሃይሞች ተደርገን ነበር የምንታየው፡፡ ይሄ እንዳልሆነ እንዲገባቸው እንነግራቸው ነበር፡፡ ዝምታ በብዙ ነገር ይጎዳል፡፡ ለምሳሌ ምርጫ ሲመጣ በቀበሌ በክ/ከተማ የእኔ ድምፅ ተቆጠረ አልተቆጠረ ብለን ዝም ስንል ነው ያልመረጥናቸው ተሹመው መከራ የሚያበሉን፤ ቢያንስ የእኔ ድምፅ ለምደግፈው ለአንድ እጩ ቢሰጥ የማልፈልገው ሰው እንዳይመረጥ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ ዝምታ እንደሚጎዳ ስለማውቅ፣ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ሀሳቤን እገልፅ ነበር፡፡
በጦላይ ቆይታህ ምን የተማርከው ነገር አለ?
እንግዲህ ትምህርት ሂደት ነው እንጂ አንድ ቦታ የሚቆም አይደለም፡፡ ከዚህ ቆይታዬ አልተማርኩም ማለት ተፈጥሮን መካድ ነው፡፡ በጦላይ ቆይታዬ ያለ ፍላጎት አንድ ቦታ መታገት ምን ማለት እንደሆነ፣ያንንም እንዴት ማለፍ እንዳለብኝ ተምሬያለሁ፡፡ ብዙ ጓደኞች ከፖሊሶችም ከታሳሪዎችም በኩል አፍርቻለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች አውቀውኛል፡፡ የሚመለከታቸው ለሚመስሉ አካላት ሀሳቤን አንፀባርቄያለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ህዝብና መንግስት ማን እንደሆኑ በደንብ አውቄያለሁ። ከሚዲያ የምትሰሚው ነገር ሁሉ ሃቅ ነው ማለት አይቻልም፡፡ የመንግስትም የግልም የምትያቸው ሚዲያዎች ውሸታሞች ናቸው፡፡
ከምን ተነስተህ ነው እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረስከው?
ለምን እንደዛ እንዳልኩ ልንገርሽ፡፡ ብዙ ሰው እኔ የመንግስት ተቃዋሚ እንደሆንኩ ነው የሚያስበው። እኔ ግን ትክክለኛ ያልሆነ ሀሳብ ተቃዋሚ ነኝ፡፡ ለምሳሌ አፍንጫሽ አያምርም ብዬ፣ አይንሽ ቆንጆ ነው ብል ምንድነው ችግሩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሰው ከጠላ ጠላ ነው፣ ከወደደም በጭፍን ነው የሚወደው፡፡ እኔ ይሄን ዓይነት የመንጋ አስተሳሰብ አልቀበልም፡፡ አሁን ጦላይ እያለን ዶ/ር ዐቢይን ላለመኮነንና ላለመጥላት ምን ይላሉ መሰለሽ … “ዶ/ር ዐቢይ እኛ መታሰራችንን አያውቅም፤ ቢያውቅ ያስለቅቀን ነበር” የሚሉ የዋሆች አሉ፡፡ “በዐቢይ ጊዜ የለም ትካዜ” ሲሉ፣ እኔ ደግሞ “በጃንሆይ ጊዜ ነው እንዴ እዚህ ተክዛችሁ ያላችሁት” እላቸዋለሁ፡፡ ይሄ አስተሳሰብ የሚዲያዎች ተፅዕኖ ነው፡፡ የመንግስት ሚዲያዎች፤ መንግስት ምንም እከን እንደሌለው አድርገው ያቀርቡልሻል፡፡ አንዳንድ የግል ሚዲያ ደግሞ ስለ መንግስት ጥላቻና ማንቋሸሽ በቀር አንዷን ጥሩ የሰራትን እንኳን ገልፀው፣ 99ኙን ስህተቱን አይነግሩሽም፡፡ ድሮ ተገነባ ተመረቀ ለምቷል ሲልሽ የከረመ የመንግስት ጋዜጠኛ፤አንድ የፈረሰ ነገር እንዳለ ሳይነግርሽ፣ ታደሱ ታድሰናል ይልሻል፡፡ ታዲያ ህዝቡ በጭፍን ቢወድና በጭፍን ቢጠላ እንዴት ይፈረድበታል፡፡ መሃሉን ይዞ በሀቅ ላይ ተመርኩዞ የሚሰራ ሚዲያ በሌለበት ሁኔታ አስተሳሰብ እንዴት ይቀናል፡፡
አገር ከግጭትና ቀውስ ወጥታ ሰላምና እርጋታ የሰፈነባት እንድትሆን ምን መደረግ አለበት?
እኔ በመንግሥትም በህዝብም በኩል የሚታዩኝን ክፍተቶች ከሙያዬ አንፃር ልንገርሽ፡፡ በህክምና ሙያ ከኪዩር ፕሪቬንሽን ርካሽ ነው፡፡ ከማከምና ከማዳን ይልቅ ቅድመ መከላከል በእጅጉ ርካሽ ነው፡፡ ህክምናው የሚደረገው በሽታው ስር ከሰደደና ከአቅም በላይ ከሆነ በኋላ ነው፡፡ ለመድኃኒት—ለሁሉ ነገር ወጪ አውጥተሽም ሰው ላይድን ይችላል፡፡ ቀድሞ መከላከል ግን ወጪ እንኳን ቢኖረው ለምርመራ ይሆናል፡፡ መንግስት ሥራ አጥ ሱሰኛና አልባሌ ቦታ የሚውል ትውልድ ከማፍራቱ በፊት ስራ በመፍጠር፣ ዜጎችን እኩል በማቀፍ እኩል ተጠቃሚ ማድረግና አዕምሮ ልማት ላይ ቢሰራ ያተርፋል፡፡ ሥራውም ይቀላል። አንዱ እየበላ አንዱ ጦም የሚያድር ከሆነ፣ አንድ የአገሪቱ አካል ታመመ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የሰውነት አካል ከታመመ ሌላውን ሰውነት ይረብሻል፡፡ ከማህበረሰቡ አንድ የተገፋ አካል ካለም እንደዛው ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያን ፈጣሪ ይባርክ እንላለን፡፡ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን– ካልተባረኩ ህመማቸው ኢትዮጵያን ይነካል፡፡ ሞቃዲሾ ስትታመም አዲስ አበባ ትነካለች፡፡ ስለዚህ በሁሉም ረገድ የተስተካከለ አካሄድ በመንግስት በኩል መኖር አለበት፡፡ ወደ ህዝብ ስመጣ፣ አምስት የማይገናኝ ቲ-ሸርት የሚለብሱ አንድ ዓይነት ሰዎች አውቃለሁ፡፡
ኧረ … አልገባኝም?
ለምሳሌ አንድ ሰው ሆኖ፤ የቅንጅት ቲ-ሸርት፣ ንብ ያለበት የኢህአዴግ ቲ-ሸርት፣ አቶ መለስ ሲሞቱ ፎቷቸው ያለበት ቲ-ሸርት፣ የዶ/ር ዐቢይን ቲ-ሸርት፣ የግንቦት ሰባትን ቲ-ሸርት–ብቻ ምን አለፋሽ ለመጣ ለሄደው ሁሉ ቲ-ሸርት መልበስ የሚወድ አለ፡፡ ይሄ ደስ አይልም፡፡ ምን ለማለት ነው? ህዝቡ አቋሙን፣ ሚናውን መለየትና የሚያደርገውን ቆም ብሎ ማሰብ አለበት፡፡ ያለበለዚያ እንዳደረጉት የሚሆን ከሆነ፣ ነጂው ይበዛል፡፡ እንትን ነፃ አውጭ፣ እከሌ ነፃ አውጭ እያሉ እየመጡ—ህዝቡን ማመስ ለሚፈልጉና አጀንዳቸውን ለሚያስፈፅሙ ጥቂት አካላት መሳሪያ ይሆናል፡፡ እነዚህ ነገሮች ባልተስተካከሉበት ሁኔታ መረጋጋትና ሰላም ይፈጠራል ብዬ አላስብም፡፡ በተረፈ ያለ ጥፋታችን ታስረን ጦላይ ስንቀመጥ እንድንፈታ ህዝቡ ላደረገልን ትብብርና ለያዘው አቋም ማመስገን እወዳለሁ፡፡

በራያ እና አካባቢው የሰላም ጉዳይ ላይ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ መሪነት ውይይት ተደርጏል

አቶ ፍፁም አረጋ እንደገለፁት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በዛሬው ዕለት ከክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ከአቶ ደመቅ መኮንን: ከኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች እንዲሁም ከሁለቱ ክልሎች የበላይ አመራሮች እና ከሰላም ሚንስትር ጋር በጋራ በመሆን በራያና አካባቢው የሰላም ጉዳይ ውይይት አካሄዱ::

በውይይታቸውም ማንኛውም አይነት ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲቀርብና እንዲስተናገድ ስምምነት ላይ ደርሰዋል::

በዚህም መሰረት በራያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ከማንነትም ሆነ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚነሳ ጥያቄ ሕገ-መንግስቱንና ህዝቡን ማዕከል ባደረገ መንገድ ሊፈታ እንደሚገባው: ከዚህ ውጪ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው አመራሮቹ አስምረውበታል::

በፌዴራልም ሆነ በክልል የሚገኙ የመንግስትም ሆነ የግል የመገናኛ ብዙሀን በሁለቱ ክልሎች መካከል ይበልጥ መግባባትና መቀራረብ እንዲፈጠር በኃላፊነት መንፈስ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል::

በነገው ዕለት በተለያዩ የክልላችን ልዩ ልዩ ከተሞች የማንነት ጥያቄዎች ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ ላሊበላን እና ጣናን መታደግ እንደሚገባ መልዕክት ለማስተላለፍ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቷል::

በዚህ አጋጣሚ ሰልፎቹ ሰላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ ለሁሉም ወገኖች የጥንቃቄ መልዕክት እናስተላልፋለን ::

አቶ Nigussu Tilahun

የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከ108 ሚሊዮን በላይ ደረሠ


(ዘ-ሐበሻ) በአለም ባንክና መሠል አለም አቀፍ ተቋማት በዚህ ሳምንት ይፋ የሆነው መረጃ የኢትዮጵያን ህዝብ ብዛት ከ108 ሚሊዮን በላይ አድርሶታል። በዚህ መሠረት ኦክቶበር 22 ቀን የህዝቡ ብዛት 108,354,282 መሆኑ ተገልፇል። ይኸው መረጃ በብሄሮችም ደረጃ ያለውን የህዝብ ስብጥር ዘርዝሯል። በመሆኑም የኦሮሚያ ህዝብ 34.4 ሚሊዮን በመሆኑ በቀዳሚነት የተቀመጠ ሲሆን ቀጣዩ የአማራ ህዝብ ደግሞ 27 ሚሊዮን መሆኑን መረጃው አስረድቷል። ከኢትዮጵያ ህዝብ በቁጥር ሶስተኛ እንደሆነ የተገለፀው ደግሞ 6.2 ሚሊዮን ነው የተባለው ሡማሌ ነው፡፡ መረጃው ትግራይን በ6.1 ሚሊዮን አራተኛ፣ ሲዳማን በ4 ሚሊዮን አምስተኛ፣ ጉራጌን በ2.5 ስድስተኛ፣ ወላይታን በ2.3 ሠባተኛ፣ ሐዲያን በ1.7 ስምንተኛ፣ አፋርን በ1.7 ዘጠነኛ እንዲሁም ጋሞን በ1.5 አስረኛ አድርጏቸዋል።

በከተሞች ያለውን የህዝብ ቁጥር ካየን በግንባር ቀደምነት አዲስ አበባ ሲመራ፡ ጎንደርና መቀሌ ተከታዩን ደረጃ መያዛቸውን መረጃው ጠቁሟል። በዚህ መሠረት የአዲስ አበባ ህዝብ 3,434,000 እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን የጎንደር ህዝብ ደግሞ 360,600 መሆኑን አስረድቷል። በቀጣይነት የመቀሌን ህዝብ 358,529 ያደረሠው መረጃው፣ የአዳማን 355,475 እንዲሁም የሀዋሳን 335,508 በማድረግ ደረጃ ሠጥቷቸዋል። በስድስተኛነት 313,997 ህዝብ ያላት ባህር ዳር፣ በሠባተኛነት 293,000 ህዝብ ያላት ድሬዳዋ፣ በስምንተኝነት 209,226 ህዝብ ያላት ደሴ፣ በዘጠነኛነት 195,228 ህዝብ ያላት ጅማን እንዲሁም በአስረኛ ደረጃ ጅግጅጋን 169,390 ህዝብ በመያዝ ዘርዝሯቸዋል።

እንደዚሁ መረጃ ባለፈው የፈረንጆች አመት የኢትዮጵያ ህዝብ 104 ሚሊዮን 957 ሺህ 438 የነበረ ሲሆን፣ ካቻምና ደግሞ 102 ሚሊዮን 403 ሺህ 196 ነበር፡፡ መንግስት በ10 አመቱ የህዝብ ቆጠራ ማድረግ የነበረበት ቢሆንም በአገሪቱ በተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት ቆጠራው ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይታወቃል፡፡