ፖለቲካዊ ለውጡን ተቋማዊ መሰረት ማስያዝ እንደሚገባ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ

ፖለቲካዊ ለውጡን ተቋማዊ መሰረት ማስያዝ እንደሚገባ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ

በአገሪቱ የፖለቲካ ምሕዳር እየታየ ያለው መሻሻል ዘላቂነት ኖሮት ይበልጥ እንዲጠናከር ከተፈለገ ለውጡን አስተማማኝ፣ ሕጋዊና ተቋማዊ መሰረት እንዲኖረው ማድረግ እንደሚጠይቅ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ትናንት በሃዋሳ ሲጀመር 18 ፓርቲዎች በተወካያቸው አማካይነት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ፓርቲዎቹን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፤ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በሰላማዊ የለውጥ ሂደት ወደጠንካራና የማይታጠፍ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሸጋገሯን በተጨባጭና በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡ በጠላትነት ከመተያየትና ሁላችንንም አውዳሚ ከሆነው የመፈራረጅ ፖለቲካ ወጥተን ዛሬ አንዳችን ለሌላችን ያለንን መልካም ምኞት ለመግለጽ ወደምንችልበት ሁኔታ ላይ በመብቃታችን ደስታ ተሰምቶናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ በአንድ በኩል ኢህአዴግ ራሱን አርሞ ከውስጡ የለውጥ ኃይል እንዲፈጠር ማድረጉ የገለጹት ፓርቲዎቹ፤ የሕዝቡ ጨዋነትና አብሮ የመኖር የቆየ ባህል ተጨምሮበት ወደ አንፃራዊ ሰላም ሊሸጋገር ችሏል፡፡ ለለውጡ ብዙዎች መስዋዕት መሆናቸውን የጠቀሱት ፓርቲዎቹ፤ ጅምሩ ለውጥ ዘላቂና የተሳካ እንዲሆን በፖለቲከኞች መካከል የነበረው የጥላቻና የመፈራረጅ ሂደት ተወግዶ የለውጥ እንቅስቃሴው እስከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ በተቋማዊ ቁመና ተግባራዊ እንዲሆን መሥራት ይገባል፡፡
ከ11ኛው ጉባኤ የሚጠብቋቸውን አቅጣጫና ውሳኔዎች በተመለከተም ፓርቲዎቹ አራት ነጥቦችን አስቀምጠዋል፡፡ አገራዊ ለውጡ በአስተማማኝ ሁኔታ በዘላቂነት እንዲቀጥል ከተፈለገ በቀዳሚነት የሕግ የበላይነትን ማስከበር ከምንም በላይ አስፈላጊነት በመሆኑ ጉባኤው ተጨባጭ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ የጠየቁት ፓርቲዎቹ፤ መንግሥት የዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢዎች ያለልዩነት ተዘዋውረው የመሥራት ሕጋዊና ሰብዓዊ መብታቸውን በማያሻማ መልኩ እንዲያስከብርም ጠይቀዋል፡፡
አያይዘውም በየአካባቢው የሚስተዋሉ የአስተዳደራዊ ወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችን አግባብ ካላቸው ሕጎች ጋር በማገናዘብ በሰለጠነና በዴሞክራሲዊ መንገድ ተወያይቶ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚሰጥ ፓርቲዎቹ ያላቸውንም እምነት ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ የተነሱ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች በተሟላ ሁኔታና በዘላቂነት እንዲፈታ ገለልተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡

አዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 24 ቀን 2011 ዓ.ም

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s