አብዮታዊ ዴሞክራሲን› ምን ይተካዋል?

​​​​​​​“አብዮታዊ ዴሞክራሲ” በፖለቲካ ሳይንስ ርዕዮተ ዓለሞች ዝርዝር ውስጥ የለም፤ ነገር ግን ኢሕአዴግ የፖለቲካ መሥመር አድርጎ ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን መርቶበታል፡፡ ይሁን እንጂ ማንም በግልጽ ተንትኖት አያውቅም፡፡

    
180621 Kolumne BefeQadu Z Hailu

ሌላው ቀርቶ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምን እንደሆነ አላውቅም” የሚሉ የኢሕአዴግ አመራሮች አሉ፡፡ አሁን ደግሞ ይህንን የግንባሩን ‹የፖለቲካ መሥመር ለመቀየር እታገላለሁ› የሚሉ እና በተቃራኒው ደግሞ ‹የለም፣ ወደመሥመራችን መመለስ አለብን› ድምፆች ከዚያው ከድርጅቱ ውስጥ እየወጡ ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሌላ ይተካ ይሆን? ከሆነስ በምን?

አብዮታዊ ዴሞክራሲ ያልሆነው ነገር የለም፤ “ከነጭ ካፒታሊዝም” እስከ “ልማታዊ አገረ-መንግሥት” ድረስ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሥም ተሞክሯል ወይም ደግሞ ቢያንስ ‹እየተሞከረ ነው› ተብሎ ተነግሯል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በተመቸው መንገድ እየተጣጠፉ መሔድ ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካ ኩነቶች በተቀያየሩ ቁጥር ከበፊቱ የተቃረነ አካሔድ ቢሆንም እንኳን አዲስ ነገር በሥሙ ሲፈፀም በመክረሙ ነው፡፡ ከምርጫ 1997 በፊት የነበረው አንፃራዊ ሰፊ የፖለቲካ ምኅዳርም ይሁን ከዚያ በኋላ የተከተለው ዝግ የፖለቲካ ምኅዳር በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሥም ነው የተፈፀሙት፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “አገር በቀል ርዕዮተ ዓለም ነው” ብለውትም ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሁለት አብረው የማይሔዱ ቃላት ጥምረት የፈጠረው እንቆቅልሻዊ አስተሳሰብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ይመስላል የኢሕአዴግ አባላት እና ሌሎች ሲመለከቱት የተለያዩ ትርጉም የሚሰጠው፡፡ እንዲሁም አሁን ደግሞ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ሳይቀሩ በዚህ የፖለቲካ መሥመር መስማማት እንዳልቻሉ እየተመለከትን ነው፡፡

በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ግለሰቦች አመለካከት፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የአፈና ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ ተቃዋሚዎች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከግለሰቡ ሕይወት ጀምሮ እስከ ማክሮ-ኢኮኖሚ ድረስ በመንግሥት ቁጥጥር እና መልካም ፈቃድ የሚንቀሳቀሱበት ስርዓተ ፖለቲካ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በፊት ጀምሮም ቢሆን በፍፁም ለግሉ ዘርፍ ከማይፈቅዳቸው የቴሌኮም እና የባንክ አገልግሎት የመሳሰሉ ግዙፍ የንግድ ዘርፎች ነበሩ፤ ይሁን እንጂ ምርጫ 97 በፖለቲካ ግጭት ከተቋጨ በኋላ የተለያዩ የአባላት ሊጎችን እና የኢሕአዴግ ደጋፊ ሊጎችን በመመሥረት ንግድ እና ነጋዴዎችን ሳይቀር በስርዓቱ አስተሳሰብ ለማጥመቅ በመሞከር ከላይ የተጠቀሰውን ስለአብዮታዊ ዴሞክራሲ የተነገረ አሉታዊ አመለካከት አጠናክሮታል፡፡

ሆኖም በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ የታየውን መጠነኛ የኢኮኖሚ እመርታ በማስታከክ “ልማታዊ አገረ-መንግሥት” የሚለው ቃል ስርዓቱን ተቀላቅሏል፡፡ ኢሕአዴግ “ልማታዊ ዴሞክራሲ” የሚለውን ቃል አንዳንዴ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጎን ለጎን፣ ሌላ ግዜ ደግሞ በምትኩ መጠቀም ጀምሯል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የልማት ፕሮጀክቶች ሕዝብን ያሳተፉ ባለመሆናቸው – የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን ማስታወስ ይቻላል – የግጭት መንስዔ እየሆኑ ስለሆነ፣ “ዴሞክራሲያዊ ልማት” የሚል አስተሳሰብም እየተነገረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በግልጽ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከሚባለው ምንነቱ በውል ካልተለየ ርዕዮተ ዓለም ማፈግፈግ የተጀመረው ግን የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ራሳቸውን እንደ አዲስ መቅረፅ ሲጀምሩ ነው፡፡

የቀድሞዎቹ ኦሕዴድ (የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት) እና ብአዴን (ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) አሁን ኦዴፓ (የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) እና አዴፓ (የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) ሆነው መጥተዋል፡፡ ከሥም እስከ አርማ የዘለቀ ለውጥ ሲያደርጉ በርዕዮተ ዓለም ጉዳይም መወያየታቸው አልቀረም፡፡ በተለይ አዴፓ ከዚህ በኋላ በኢሕአዴግ ውስጥ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሌላ የተሻለ ርዕዮተ ዓለም እንዲተካ እንደሚታገል አሳውቋል፡፡ ይህም በግንባሩ ውስጥ የፖለቲካ መሥመር ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ተጨማሪ ማመላከቻ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሕወሓት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ ትክክለኛው የፖለቲካ መሥመር ነው የሚል ግትር አቋም እንደያዘ እስከዛሬ ዘልቋል፡፡ የኢሕአዴግ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊዋ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ከዚህ ቀደም ለሚዲያ እንደተናገሩት፣ “በየቦታው እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች መንስዔ ግንባሩ የፖለቲካ መሥመሩን ባለመከተሉ የተፈጠረ ነው”፡፡

የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በፖለቲካ መሥመሩ ለውጥ መስማማት መቻል አለመቻላቸው እንዳለ ሆኖ፣ በአሁኑ ወቅት አገሪቷ እየተዳደረች ያለው በርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ አይደለም ብለው የሚከራከሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣነ መንበሩ ከመጡ ወዲህ የሊበራል ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች ገንነው መውጣታቸው ብዙዎችን አያጠያይቅም፡፡ በሌላ በኩል አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከሊበራል አስተሳሰብ ይልቅ ለሶሻሊስታዊ አስተሳሰብ የቀረበ ስለሆነ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በሊበራሊዝም ሊተካ አይችልም፣ ምናልባት በሶሻል ዴሞክራሲ ሊተካ ይችላል ብለው የሚሟገቱም አሉ፡፡ የማይታበለው ሐቅ ግን አሁን ከተጀመረው እና ለረዥም ጊዜ በጉጉት ሲጠበቅ ከነበረው የኢሕአዴግ ጉባዔ በኋላ ግራ ከተጋባው እና ለመተንበይ ከሚቸግረው የፖለቲካ ሒደት እና አዙሪት ለመውጣት ግልጽ የፖለቲካ መሥመር ይዘው እንዲወጡ በሁሉም ወገን እየተጠበቀ መሆኑ ነው፡፡

በዚህ አምድ የቀረበው አስተያየት የጸሀፊው እንጂ የ « DW»ን አቋም አያንጸባርቅም።

በፍቃዱ ኃይሉ

 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s