የሕዝብ ጎርፍ ከወደ ኤርትራ! ( በሪሁን አዳነ )

የሕዝብ ጎርፍ ከወደ ኤርትራ!
***
በሪሁን አዳነ
***
ሊ ኩዋን ዩ (Lee Kuan Yew) ግሩም መሪ ነበሩ፡፡ እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ሕግ አጥንተዋል፡፡ እንደ አውሮፓዊያን የዘመን አቆጣጠር ከ1959-1990 አገራቸውን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መርተዋል፡፡ From Third World To First በሚል ርዕስ ባሳተሙት ዳጎስ ያለ መጽሐፋቸው ስለ ሲንጋፖር ሪፐብሊክ አመሠራረት፣ አገረ-መንግሥት ግንባታና ሁለንተናዊ ልማት በስፋት ያብራራሉ፡፡

በተለምዶ “የኢሲያ ነብሮች” እየተባሉ ከሚጠሩት አገሮች መሀከል አንዷ የሆነችው ሲንጋፖር፣ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛትነት ነጻ በውጣች ማግስት ከማላያ ጋር በመሆን የማሌዢያ ፌደሬሽንን መሥርታ ነበር፡፡ ሆኖም በማላይና ቻይና ማኅበረሰቦች መሀከል ከፍ ያለ ቅራኔና ግጭት እየተፈጠረ በመምጣቱ እና ፌደሬሽኑ ከሁለት ዓመት በላይ መቆየት ባለመቻሉ እ.ኤ.አ. በ1965 ሲንጋፖር ተነጥላ ልትወጣ ችላለች፡፡ ትልቁ የዚያች አገር የስኬት ታሪክ የሚጀምረው ከዚህ በኋላ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ እንደሚያስረዱት ከስኬታቸው ቁልፍ ምስጢሮች መሀከል፣ የሲንጋፖርን ልዩ ሁኔታ (አነስተኛ የቆዳ ስፋትና የተፈጥሮ ሀብት፣ ውስን ቁጥር ያለው ሕዝብ ወዘተ.) በሚገባ ተረድተው ወዳጅ/አጋር ማብዛታቸውና ጠላት መቀነሳቸው፣ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ሊያቀርብ የሚችል ጠንካራ መንግሥታዊ መዋቅር መፍጠራቸው፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጅ ልዩ ትኩረት መስጠታቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እዚህ ግባ የሚባል የተፈጥሮ ሀብት ሳይኖራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዓምራዊ ሊባል የሚችል ዕድገት አስመዝግባ ዓለምን ጉድ ያሰኘችው ሲንጋፖር፣ ኢትዮጵያንና ኤርትራን ጨምሮ ለርካታ አገሮች የልማት አብነት ለመሆን በቅታለች፡፡

“የአፍሪካ ሲንጋፖር”
***
የኤርትራ መሪዎች ከትጥቅ ትግል ጊዜ ጀምሮ ኤርትራ ከኢትዮጵያ “ቅኝ አገዛዝ” ነጻ ከወጣች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዓምራዊ ዕድገት እንደምታስመዘግብ በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ሲገልጹ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የአፍሪካ ሲንጋፖር እንደሆናለን የሚል ሕልም ነበራቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሲንጋፖር መሪዎች እንዳደረጉት የኤርትራን አቅም በሚገባ ገምግመው ጠንካራ አገረ-መንግሥት በመገንባት፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ሰላማዊ ግንኙነትና ስትራቴጅክ አጋርነት በመፍጠር፣ ወደቦቻቸውን ዘመኑ በሚጠይቀው የጥራት ደረጃ በማሳደግና ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ወዘተ. የኤርትራን ሁለንተናዊ ልማት ማረጋገጥ አልቻሉም፡፡ ይልቁንም የሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ፍትሕ (ሕግዴፍ) መሪዎች ገና ከኢትዮጵያ በተነጠሉ ማግስት ከሁሉም ጎረቤት አገሮች ጋር አላስፈላጊ ግጭትና ጦርነት ውስጥ ነው የገቡት፡፡ ዋናው የግጭት ምክንያት የመሬት/ወሰን ጉዳይ ባይሆንም ከየመን ጋር በሐኒሽ ደሴቶች፣ ከጅቡቲ ጋር በራስ ዱሜራ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በባድመ ምክንያት ግጭትና ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ከሱዳን ሪፐብሊክ ጋርም ይህን ያህል የሚያወላዳ ወዳጅነት የላቸውም፡፡

የኤርትራ መሪዎች እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ብዙ ሕዝብና የመልማት አቅም ያላቸውን አገሮች በልዩ ሁኔታ፣ በመልካም ጉርብትና ተንከባክቦ መያዝና የገበያው ተጠቃሚ መሆን ሲገባቸው አውዳሚ የሆነውን ጦርነት መርጠው ሁለቱም አገሮች ውድ ዋጋ ከፈሉ፡፡ በጦርነቱ አስከፊ በሆነ መልኩ የተሸነፉት እነ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደ አሜሪካ ካሉ ኀያላን አገሮች ጋር ጭምር በመነጠላቸውና የማዕቀብ ሰለባ በመሆናቸው፣ የአፍሪካ ሲንጋፖር ትሆናለች የተባለችው ኤርትራ ወጣቶቿ በየዕለቱ የሚሰደዱባት፣ ሥርዓቱን የሚተቹ አካላት (ዐሥራ አምስቱን ከፍተኛ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጨምሮ) ጨለማ ቤት ታስረው የሚሰቃዩባት፣ በሰብአዊ መብት ጥሰት ከመጀመሪያዎቹ ተርታ የምትመደብ አገር ሆና ቆይታለች፡፡
አሁን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በሚመለከት ብዙ ነገሮች ተቀይረዋል፡፡ የወደፊቱ ሁኔታ ባይታወቅም ሰላም ወርዷል፡፡ ጥያቄው የኤርትራ መሪዎች ካለፈው ስህተታቸው ተምረው ጠንካራ አገረ-መንግሥት በመገንባት፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት በማስፈን እና ወደቦቻቸውን ዘመኑ በሚጠይቀው ደረጃ አዘምነው ጥራት ያለው ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የኢትዮጵያን ሰፊ ገበያ ለመጠቀም ተዘጋጅዋል ወይስ አሁንም እንደ ቀደመው ጊዜ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በሚዳፈርና ብሔራዊ ጥቅሟን በሚጎዳ መልኩ የመንቀሳቀስ ፍላጎት አላቸው? የሚለው ነው፡፡

ቤተሰብም ባላንጣም
***
“ምንም እንኳ የመረብ ባሻገር ክልል አስተዳደር በባዕድ እጅ ይግባ እንጅ ለአካባቢው ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ስሜቱም ሆነ መብቱ ላይ ያመጣው ለውጥ እጅግም አለመሆኑ አንዱ ማስረጃ በኢትዮጵያ መንግሥት ከተራ ጸሐፊነት እስከ ሚኒስትርነት ማዕረግ ባሉት ደረጃዎች ያገለግሉ የነበሩት የኤርትራ ተወላጆች ብዛት ነው፡፡ ከነዚህም መካከል በፋሽስት ወረራ ጊዜ ኢትዮጵያን ወክለው በግምባር ቀደምትነት በጄኔቫ ይሟገቱ የነበሩት ብላቴን ጌታ ሎሬንዞ ታዕዛዝ (የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና በኋላ በሶቬዬት ኅብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር)፣ ብላታ ኤፍሬም ተወልደመድኅን (በኋላ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር)፣ ብላታ ዳዊት እቁባዝጊ (ምክትል ሚኒስትር)፣ አቶ ገብረመስቀል ሀብተማርያም (ታዋቂ አርበኛና በኋላ የፖስታና ቴ.ቴ. ዋና ዲሬክተር)፣ አቶ ገብረመስቀል ክፍለዝጊ (የአገር ውስጥ ሚኒስትር ጠቅላይ ጸሐፊ)፣ አቶ መለስ አንዶም (በሕንድ የኢትዮጵያ መንግሥት አንደኛ ጸሐፊ)፣ አባ ገብረመስቀል (በኋላ አቡነ ዮሐንስ)፣ ይገኙባቸዋል፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ለንደን ላይ ለተሰበሰበው የአራቱ ኀያላን መንግሥታት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ ባቀረበው ሰነድ ውስጥ ከ1600 በላይ የኤርትራ ተወላጆች የሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የጦርና የሲቪል ሹማምንት ዝርዝር ይገኛል፡፡ ምናልባት ከሌሎች ክፍለ አገሮች ድርሻ ጋር ብናነጻጽረው ይህ ቁጥር ከሸዋ ቀጥሎ ከፍተኛው ሳይሆን አይቀርም፡፡” (ሹመት ሲሻኝ፣ ውይይት ቅጽ-3፣ ቁጥር-2፣ 1984 ዓ.ም.)

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከየትኛውም የአፍሪካ ቀንድ አገሮች በላይ ጥብቅ ትስስር አላቸው፡፡ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በዘርና በታሪክ ከፍ ያለ አንድነት ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ በርካታ የኤርትራ ተወላጆች ኢትዮጵያን እናታችን፣ ኢትዮጵያዊያንን ደግሞ ወንድምና እህቶቻችን ብለው ኢትየጵያን አገልግለዋል፤ ከወራሪ ጠላት በጀግንነት ተከላክለዋል፡፡ ኢትዮጵያም ቀን በከፋ ጊዜ አቅፋ ደግፋ ይዛቸው ኖራለች፡፡
ይሁን እንጂ ግንኙነታችን ሁልጊዜም ቤተሰባዊና በፍቅር ላይ የተመሠረተ ነበር ማለት አይደለም፡፡ በጣም ብዙ ኤርትራዊያን ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ቤተሰባዊ ዕይታ ቢኖራቸውም የዚያኑ ያህል ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በባላንጣነት የሚያዩ ብዙ የኤርትራ ተወላጆች ነበሩ፤ አሉም፡፡ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ተወላጆች ከኢትዮጵያ ነጻ ለመውጣት በልዩ ልዩ ድርጅቶች ተደራጅተው አገራችን ከሠላሳ ዓመታት በላይ ወግተዋል፡፡ በዚህ የተራዘመ የጦርነት ዘመን በሁለቱም ወገን በኩል በደረሰው ጉዳት ምክንያት በመሀከላችን ያለው መስተጋብር በጥርጣሬና ጥላቻ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በ1992 ዓ.ም. ሁለቱ አገሮች ያደረጉት ትርጉም አልባ ጦርነት የፈጠረው ጠባሳም ከፍተኛ ነው፡፡

በቅርቡ የተጀመረው የሁለቱ አገሮች የሰላም ግንኙነት ዘላቂነት ሊኖረው የሚችለው በአገሮች መሀከል የተፈጠሩትን የታሪክ ጠባሳዎች በሚገባ ለይቶ ዳግም ወደ ግጭት እንዳንገባ ሥርዓት ያለው [ሕጋዊ] ግንኙነት የተመሠረተ እንደሆነ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት በመርህ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ስላልበረ ነው ሁለቱ አገሮች በ1992 ዓ.ም. አላስፈላጊና አውዳሚ ጦርነት ውስጥ የገቡት፡፡ ሁለት አገሮች ነንና ግንኙነታችን የሁለት ሉዓላዊ አገሮች ግንኙነት እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ከሆነ ቤተሰባዊነታችን እየተጠናከረ፣ በመሀከላችን የግጭት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችም ከሥር ከሥር እየተቀረፉና መልክ እየያዙ ይሄዳሉ፡፡

ኀላፊነት የጎደለው ግንኙነት
***
አቶ ገብሩ ዐሥራት “ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደገለጹት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተነጠለችበት ጊዜ ጀምሮ ጦርነቱ እስከተጀመረበት በነበሩት ዓመታት፣ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በሚመለከት የተካሄዱት ውይይቶች፣ ድርድሮች እና የተፈፀሙት ውሎች በሕወሓትና ሻዕብያ አማካይነት የተደረጉ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያና ኤርትራን ግንኙነት በሚመለከት ከሕወሓት ውጪ ያሉት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም ሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙያተኞች የሚውቁት ነገር አልነበረም፡፡ አቶ ገብሩ በመጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ራሳቸው መኪና እያሽከረከሩ መቀሌ ጎራ እያሉ ከሕወሓት አመራሮችና እንደ አቶ ዜናዊ አስረስ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ የትግራይ ሽማግሌዎች ጋር ይወያዩ ነበር፡፡

የኤርትራ መሪዎችና እነሱን የተማመነው የንግድ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በሚዳፈርና የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በሚጎዳ መልኩ በኮንትሮባንድ፣ በጥቁር ገበያና በልዩ ልዩ ሕገ-ወጥ ተግባር ተሰማርቶ ነበር፡፡ በሁለቱ አገሮች መሀከል የተካሄደው አውዳሚ ጦርነት የተቀሰቀሰው [በኋላ ከሕወሓት ተነጥሎ በወጣው አመራር ትግል] የኢትዮጵያ መንግሥት መረን የለቀቀውን የኤርትራ መሪዎችና የንግድ ማኅበረሰቡን አካሄድ እንዲገታ በማድረጉና የኤርትራ መሪዎች እንደለመዱት በኢትዮጵያ ላይ ፊታውራሪ ሆነን እንቀጥላለብ ብለው አሻፈረኝ በማለታቸው ነው፡፡
በቅርቡ የሚታየው አዝማሚያ እንደሚያሳየው የኤርትራ መሪዎች አሁንም ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና ክልሎች ጋር በተናጠል መገናኘት ጀምረዋል፡፡ ከሕዝባዊ ግንባር (ሕግዴፍ) መሪዎች አካሄድና የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የነ ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ድጋፍ ለማግኘት ከሚያደርጉት የተናጠል ሽኩቻ መረዳት እንደሚቻለው አሁንም ግንኙነቶች የሁለቱን አገሮች ዘላቂ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እየተካሄዱ አይደለም፡፡ እነ አቶ ኢሳያስ የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረቦችና አምባሳደሮችን ሳይቀር ከሥራ እስከማስነሳት ደርሰዋል ነው የሚባለው፡፡ ይህ አደገኛ አዝማሚያ ከወዲሁ ካልተቀጨ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ላይ ከፍ ያለ ጉዳት እንደሚያስከትል ጥርጥር የለውም፡፡

ሌላ የግጭት ምንጭ?
***
ሰላም ከተመለሰ ወዲህ በርካታ ኤርትራዊያን ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነው፡፡ የኤርትራ ተሸከርካሪዎች መቀሌ፣ ጎንደርና ባሕር ዳር ላይ በስፋት ይታያሉ፡፡ የትግራይ ክልል የንግድ ማኅበረሰብም በገፍ ወደ አስመራ እየተመመ ነው፡፡ ሕዝቡ በነጻነት መገናኘቱና መገበያየቱ መልካም ቢሆንም የግንኙነቱ ፍጥነትና ሥርዓት አልባነት ግን በጣም አስፈሪ ነው፡፡ ትልቁ አደጋ ግን ይህ አይደለም፡፡ ትልቁ አደጋ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ወጣቶች በየዕለቱ ወደ ኢትዮጵያ መጉረፋቸው ነው፡፡ በገጠርም በከተማም የሚኖረው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ ወጣት በሥራ ማጣትና ተስፋ መቁርጥ ውስጥ ባለበት ሁኔታ የኤርትራ ወጣቶች መምጣት መልካም ዜና ሊሆን አይችልም፡፡ እንደ ደቡብ አፍሪካ ባሉ አገሮች ውስጥ በአገሬውና በስደተኛው መሀከል በየጊዜው ግጭት እየተነሳ የሚፈጠረውን ውድመት ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ በሥራ ማጣት ምክንያት ልጆቿ የባሕርና በረሃ ሲሳይ በሚሆኑባት ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ከነ ደቡብ አፍሪካም የከፋ አደጋ ሊከሰት የሚችልበት ሰፊ ዕድል አለ፡፡ የራሷ ዜጎች ከክልል ክልል ተንቀሳቅሰው ለመሥራት የተቸገሩባት ኢትዮጵያ ከውጭ የሚመጡ ስደተኞችን ሊያስተናገድ የሚችል ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አቅም የላትም፡፡

ቀደም ሲል በሁለቱ አገሮች መሀከል ለተከሰተው ግጭት መንስኤ የሆኑ ነገሮች በዝርዝር ተለይተውና ውይይት ተደርጎባቸው ስምምነት ባልተደረሰበትና ጠንካራ ውሎች ባልተፈረሙበት ሁኔታ የሚደረጉት ግንኙነቶች፣ የሕዝብ ዝውውሮችና የንግድ ልውውጦች መልካም ውጤት አያስገኙም፡፡ ስለሆነም ከሁሉም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የሁለቱን ሉዓላዊ ጎረቤት አገሮች ግንኙነት ሊገዙ የሚችሉ ዝርዝር ውሎችን ለማዘጋጀትና በውሎቹ ላይ ጊዜ ወስዶ ለመምከር መሆን ይገባዋል፡፡ አሁን የሚታየው አዝማሚያ ከፈረሱ ጋሪው ዓይነት ነው፡፡ መስመር ሳይስት በጊዜ መስተካከል ይኖርበታል፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s