መንግሥት ሆይ ቁስልንና መንስኤን ለይ (ምሕረቱ ዘገዬ)

ሁሉም ሰው በግልጽ የሚረዳው በህክምናው ዓለም የሚተገበር አንድ አሠራር አለ፡፡ ይሄውም በአንድ ህመም ውጫዊ የስቃይ ምልክቶችና ውጤታቸው ላይ ብቻ ከማተኮርና የህመም ስሜቶችን ብቻ እየተከታተሉ ስቃይን በማስታገሻ መድሓኒቶች ለተወሰነ ጊዜ ፋታ ከመስጠት በተጓዳኝ የበሽታውን መንስኤ ማጥናትና ህመሙን ከሥር መሠረቱ አክሞ መፈወስ ተመራጭ የመሆኑ እውነታ ነው፡፡ ይህ አሠራር በጤናው ዘርፍ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡

ጥረቴ በፈረንጅኛው አጠራር ‘cause and effect’ የሚለውን ለማስታወስ ነው፡፡ መንስኤና ውጤት – ባማርኛ፡፡ አንድ ችግር የሚያስከትለውን ውጤት ብቻ እያዩ ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት መላ አቅምንና ጊዜን ከማባከን ትኩረትንና ዕውቀትን ሰብሰብ አድርጎ የችግሩን መነሻ ምክንያት በማጥናት ለአንዴና ለመጨረሻ በሚባለው አገላለጽ ሊጠቀስ በሚችል መልኩ ችግሩን እስከወዲያኛው ለማስወገድ ቢሞከር ብልኅነት ነው፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድና ሊጠገን ከማይችል ኪሣራም ያድናል፡፡

የሀገራችንን ለውጥ ተከትሎ ነቀርሣዎቹ ወያኔዎች መቀሌ ላይ መሽገው በ100 ሚሊዮኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ክተት ካወጁ ሰነበቱ፡፡ የለውጡ ኃይልም በነቀርሣዎቹ አማካይነት እዚያና እዚህ የሚቀጣጠሉ እሳቶችን – ከሕዝብ ድጋፍ ጋር – ባለ አቅሙ እየተሯሯጠ ከማጥፋት ውጪ ችግሩን ከመሠረቱ መንቅሎ ለመጣል የጎላ ነገር ሲያከናውን አይታይም – ቢያንስ እስካሁን ባለው ሁኔታ፡፡ ይህንን ስል ግን እጅግ የሚያበረታቱ ፀረ-ነቀርሣ ትግሎችን ማካሄዱንና ብዙ ድሎችን ማስመዝገቡን እንዳልዘነጋሁ ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡  ይሁንና ይህ አሁን የሚታየው መፈራራት የሚስተዋልበት አካሄድ ብዙ መስዋዕትነትን እንዳያስከፍለን እፈራለሁ፡፡ እነሱም ለዘመናት በቀበሩት ፈንጂ ምክንያት እንደምንፈራቸው የተረዱ ይመስላሉ፡፡ ያንንም ሥነ ልቦናዊ ስሜት እስከጥግ ለመጠቀም ሳያቅዱ አልቀሩም፡፡ እርግጥ ነው መሸነፋቸውን ይረዱታል፡፡ እኛ ግን ተስፋ የቆረጠ ሰው የማያደርገው ነገር ስለሌለ ወደማይቀረው ከርሠ መቃብራቸው እስኪገቡ ድረስ ብዙ ነገር እንደሚያደርጉ ማሰብ አለብን፡፡ ባህር ውስጥ እየሰመጠ የሚገኝ ሰው – ለምሣሌ – ገለባና ዐረፋ የሚያድነው እየመሰለው ይጨብጣቸዋል፡፡ መንፈራገጡ ግን የጊዜ ጉዳይ እንጂ መሞቱ በፍጹም አይቀርም፡፡ እባብ አናቱን እስኪመታ ይንፈራገጣል፤ ድመት ዘጠኝ ነፍስ አላት ቢባልም መሞቷ ግን አይቀርም፡፡ የጭንቅላት ሥጋም እንጨት መፍጀቱ ከፋ እንጂ ቢውል አያድርም – ቢያድር አይውልም- ይበስላል፡፡ አራዳዎች “ላታመልጠኝ አታሩጠኝ! “የሚሉት ወደው አይደለም፡፡ ሁሉም በጊዜው ይሆናልና የሚደንቅ አዲስ ነገር የለም፡፡ ቆራጥነትና መግባባት ካለ መቶ ሚሊዮን የተገፋና የተበደለ ሕዝብ በጥቂት መቶ ሽዎች የሚቆጠሩ “ሌቦቼን አትንኩብኝ” ባይ አፈንጋጮችን ማሸነፉ ይቅርና ስድስት ሚሊዮን ጽዮናውያንም 7.5 ቢሊዮን ሕዝብ በፖለቲካና በኢኮኖሚ አንበርክከው አብዛኛው የነሱ ፍላጎት በምድራችን እውን እየሆነ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህ ምሥጢር ነው፡፡…

በአዲስ አበባና በሌሎች ቦታዎች ባልተለመደ ሁኔታ የነዳጅ አቅርቦት እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ይህ ችግር በተለይ አሁን ለምን ሊፈጠር ቻለ? በአንዳንድ አካባቢዎች አንድ ሊትር ቤንዚን እስከ 30 እና 40 ብር በጥቁር ገበያ እንደሚሸጥ እየሰማን ነው፡፡ የዚህ ችግር መንስኤ መታወቅ አለበት፡፡ እርምጃም መወሰድ ይኖርበታል፡፡ በመጠኑም ቢሆን ከደርግ መማር ተገቢ ነው፡፡ ያለመስዋዕትነት ድል ባለመኖሩ አጥፊዎችን እየያዙ ተገቢውን ቅጣት መስጠት ከተጨማሪ ጥፋትና ውድመት ይታደጋል፡፡ እርግጥ ነው – የዘመናችን ከይሲዎች እንደነዚያ የበርበሬ ነጋዴዎች በጥይት ይገደሉ ማለቴ አይደለም፡፡ ግን ቅጣት መኖሩን የማያውቅ ባለጌ ጥፋት ማድረሱን ይቀጥላልና ይታሰብበት ለማለት ነው፡፡ መምከርም፣ ማስተማርም፣ … ተገቢ ነው፡፡

አዲስ አበባ በመንገድ ችግር እየተጨናነቀች ነው፡፡ በተለይ መሀል ከተማ ትልቅ ችግር አለ፡፡ ለ10 ኪሎ ሜትር ጉዞ ሰዓታትን እየፈጀን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ጥቂት ዓመታትን ብንቆይ ከተማዋ  ለይቶላት የምትፈነዳ ይመስለኛል፡፡ አሁን እኮ እሳት ለማጥፋት፣ ወላዶችንና ህሙማንን በወቅቱ ሀኪም ቤት ለማድረስ፣ ሌባንና ቀማኛን በፖሊስና በቀበሌ ቃፊር አባርሮ ለመያዝ፣ ወንጀለኛን በቁጥጥር ሥር ለማዋል፣ ወደ ሥራ በሰዓቱ ለመግባት፣ ቀጠሮን አክብሮ ለመገኘት፣ ትምህርትን ለማስተማርም ሆነ ለመማር፣… አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ነገሮች ለጊዜ ጋር የተገናኙ ናቸውና ጊዜህን የትራፊክ ጭንቅንቁ እንክት አድርጎ ከበላው እዚህ የተጠቀሱትን ጨምሮ ብዙ ነገር ይከሽፍብሃል፡፡ እሳት ጊዜ አይሰጥም፡፡ በሽታ ጊዜ አይሰጥም፡፡ ምጥ ጊዜ አይሰጥም፡፡ ሌባና ወንጀለኛ ጊዜ አይሰጥም፡፡ እነዚህን ጉዳዮች የሚያስተናብሩ የመንግሥትም ሆኑ የግል አካላት መንገድ ላይ ለሰዓታት ተዘግቶባቸው እዚያው ሲድሞነሞኑ ከዋሉ ችግሮች እየተወሳሰቡ እንጂ እየተፈቱ አይሄዱም፡፡ ይታሰብበት፡፡

የሚገርመው ነገር ችግርን ለመፍታት ችግር የሚጨመርበት ሁኔታ ነው፡፡ የመኪና መንገድ ችግር ከተማችንን አስጨንቆ ባለበት ሁኔታ በብዙ ቦታዎች ፍጥነት መቀነሻ በሚል በሚጋደሙ ጉርብርብ ንጣፎች መኪኖች ሲርመሰመሱ ይውላሉ፡፡ ችግርን ማስወገድ ቢያቅት በችግር ላይ ችግር ለምን ይደረባል? የሰው ኃይል መድቦ ህግ ተላላፊን እንደማስተማርና ካልተቻለም እንደመቅጣት መንገድን በዚህ መልክ ማጣበብ ተገቢ አይመስለኝምና ይሄም ጉዳይ በቅጡ ይታሰብበት፤ በስሜትና በወጉ ባልተጠና የይድረስ የሞቅታ ሃሳብ አንመራ – (በመቅጣት እንደማላምን ቢታወቅልኝ ግን ደስ ይለኛል)፡፡ ሰዎች አእምሯቸውን ቢጠቀሙ አንድም ፖሊስ፣ አንድም ዳኛ፣ አንድም ወታደር ሳያስፈልጋቸው መኖር እንደሚችሉ ብዙ ምሣሌዎችን ከዓለማችን አካባቢ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኛ ሀገር ያለው ህግ-አልባነት ግን የሚያሳዝንና የሚገርምም ነው፡፡ ህግ አውጪውና  ህግ አስከባሪው የሚያወጡትን ህግ ለመደፍጠጥ ቀዳሚዎቹ እነሱ ናቸው፤ ህጉ እነሱን የሚያካትት አይመስላቸውም፡፡ ያለብን ችግር እኮ — በስመ አብ!!!!!!!

የተቀጣሪዎች ደመወዝ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ የገንዘባችን የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደጊዜ ተሽመድምዶ እንደሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የጀርመን ማርክ ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡ አላየሁም እንጂ ላጤዎች ግድግዳቸውን በመቶ ብራችን የሚያሰጌጡ ይመስለኛል – ቢያንስ ሌሊቱ እስኪነጋና ልጠው እስኪጠቀሙበት፡፡ በዚህን ሁኔታ ሰውን አትስረቅ ወይም አትሞስን ማለት ታዲያ “ኢ-ሞራላዊ” መሆን ነው፡፡ ሰዎች እንዴት ተንደላቀው እንደሚኖሩ የሚመለከት ባለዝቅተኛ ደሞዝ በወር ሁለት ቀናትን እንኳን ሊያስኖረው የማይችል ደሞዝ ሲከፈለው መናደዱና ገንዘብ ለማግኘት ሲል ወደ ወንጀልና ኃጢኣት መግባቱ አይቀርም፡፡ በዚህን መሰሉ አስጨናቂ ወቅት ለነፍስና ለኅሊና የሚያስቡ ዜጎች ቁጥር እጅግ አናሳ ነው፡፡ የሚዘወተረው የሕይወት መርህ “ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ” የሚለው ይሆንና ሩጫው የጥሎ ማለፍ ይሆናል፡፡ በጥሎ ማለፍ ማኅበረሰብኣዊ የኳስ ዐበደች ጨዋታ ደግሞ ተረጋግጦ የሚሞተው እጅግ ብዙ ነው፡፡ ትግሉ እግር አውጭኝና ነፍስን  አውሎ የማሳደር በመሆኑ ይሉኝታንና ሀፍረትን ሸጦ የበላ ነው፡፡ ይህም ታዲያ ይታሰብበት፡፡ በሰው ከመፍረድ በፊት ቅጥር ሠራተኛው  የሚከፈለው ደሞዝ የኑሮ ውድነቱን ያገናዘበ ነው ወይ? ቢያንስ ቢያንስ ከጎረቤት ሀገራት የማይተናነስ የደሞዝ እስኬል እንከተላለን ወይ? የኬንያ መምህር እንዴት ይኖራል? የታንዛንያ የህክምና ዶክተር እንዴት ይኖራል? የሞዛምቢክ ነርስ እንዴት ይኖራል/ትኖራለች? የናይጄሪያ አንድ የቢሮ ኃላፊ እንዴት ይኖራል? ስንቱ ዜጋ በቤቱ ምን ምን አለው? ምን ምን የለውም? ምን ያህል ዓመታትን በምን የትምህርትና የደሞዝ ደረጃ ሠርቶ ምን ምን ሊኖረው ይገባል? የትና እንዴት ይኖራል? ምን ይበላል? ምን ይጠጣል? ምን ይለብሳል? የንጹሕ ውኃ፣ የመብራት፣ የስልክ፣ የመንገድ፣ የመንግሥታዊ ታህታይና ላዕላይ መዋቅሮች ዝርጋታ በምን መልክ ተደራጅተውለታል? … ተብሎ ይጠና፡፡ መንግሥት ለዜጎቹ ካላሰበ ማን ያስብላቸዋል? ግዴታውን ያልተወጣ መንግሥት ደግሞ የዜጎችን መብትና ግዴታ ሊያስከብር አይችልም፡፡ ማዘዝና መታዘዝ የሚኖረው ሁሉም መብትና ግዴታውን በአግባቡ ሲወጣ ነው፡፡ በሥርዓቱ የማልይዘው ልጅ ዐመፀኛና በዋልፈሰስ ቢሆን ተጠያቂው እኔ እንጂ እርሱ ሊሆን አይችልም፡፡

በየቀኑ ወደሰማያት የሚመጥቀው የኑሮ ውድነት መፍትሔ ይፈለግለት፡፡ የመነገጃና የማትረፊያ ህጎች ይኑሩ፤ ካሉም እንዲከበሩ ቁጥጥር ይደረግ፡፡ ንግዱም ልክ እንደፖለቲካው ሁሉ በስሜት የሚነዳ ከሆነ ሁላችንም ተያይዘን መጥፋታችን አይቀርም፡፡ ይሄ በየቦታው የተገተረ የሀብታም ፎቅና ሕንፃ ደግሞ ሰው ሠራሽ ነውና ቀውጢ ቀን ሲመጣ የዶጋ ዐመድ ይሆናል፡፡ አሌፖንና ደማስቆስን ያዬ በጦርነትና በግጭት አይቀልድም፡፡ ሩዋንዳንና የመንን ያዬ በጎሣና በዘር እሳት አይጫወትም፡፡ ጋዳፊን፣ ሣዳምን፣ መንግሥቱን፣ መለስን፣ …  ያዬ በአምባገነንነት ካርድ አያፌዝም፡፡ ሶማሌንና ዩጎዝላቪያን ያዬ በተመሳሳይ ወይም በተቀራራቢ ቋንቋና ባህል አለኝታነት አይመፃደቅም፡፡ እኔ ተናግሬያለሁ! ዋ! ዛሬን እያማረጥሽ የምትበይና መኪና እንደሸሚዝ እየለዋወጥሽ የምትዘባነኝ ሌባና ሙሰኛ ሁላ ነገ ጉድ ሲዘንብ መግቢያ ቀዳዳ የለሽምና አሁኑኑ ማሰብ ጀምሪ፡፡ ነገ የማሰቢያ ጊዜም ላይኖረን ይችላል፡፡ አምስት ይሁን ስድስት የቤተሰብ አባላቱን ከአየር በወረደ ቦምብ ያጣ ሦርያዊ የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር በአውሮፓ ጎዳናዎች ለማኝ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ የወደፊት የማይቀር ኹነትን ከዛሬ አስቀያሚ ገጠመኞች ተነስቶ ለመተንበይና አስቀድሞ ለመጠንቀቅ በግድ ኢትዮጵያዊውን ሼህ ሁሴን ጂብሪልን ወይም የእንግሊዟን የ16ኛው ክፍለ ዘመን ነቢይት  ማዘርሽፕተንን መሆን አይጠይቅም፡፡ እነስብሃት ነጋና አባይ ፀሐዬ፣ እነጌታቸው አሰፋና ጌታቸው ረዳ የሠሩትን ያን ሁሉ ግም ሥራ በማሰብ መጨረሻቸው እንደማያምር መረዳት ከተሳናቸው በርግጥም በሰው አምሳል የተፈጠሩ ጅቦች እንጂ አእምሮ ያላቸው ሰዎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ኧረ ጅቦች ከወያኔዎች በስንት ጣማቸው! ጅብ እኮ ወንድ ወንዱን አይሰርም፡፡ ጅብ እኮ በህግ ስም አስሮ ወገኑን አያኮላሽም፡፡ ጅብ እኮ ሰውን ከነነፍሱ ወደ ገደል አይጥልም፡፡ ጅብ እኮ ይጠግባል – እንደወያኔ እምብርት-የለሽ አይደለም፡፡ እነዚህ ወያኔዎች እኮ ከሰይጣንም በልጠው ሰይጣን ራሱ ስለነሱ እንዲመሰክር አስገድደውታል – “ወያኔዎች በክፋትና በጭካኔ እኔን ዕጥፍ ድርብ ያስከነዳሉ! እኔ ያላደረኋቸውንና ለተከታዮቼ ያላስተማርኳቸውን አዳዲስ የማሰቃያ ሥልቶችን የፈለሰፉ አለቆቼ ናቸው፡፡…” ሲል ዲያብሎስ ራሱ ምዕመናኑ ፊት ዐውደ-ጥፋት ላይ ቀርቦ በቅርቡ መናገሩን በፌስቡክ አንብቤያለሁ – የማመንና ያለማመን ጉዳይ የግሌ ነው፡፡ ወያኔዎች ዕረፍት የሌላቸውና ዕረፍትም የማይሰጡ የሲዖል ትሎች ናቸው፡፡ …

ወያኔ ቤተ አምልኮቶችንም አጥፍቷቸዋል፡፡ ክህነት የሌላቸው ቀሳውስትን፣ ፅድቅ የሌላቸው ማይም ጳጳሣትን፣ ትምህርት የሌላቸው የደብር አለቆችን… በየአድባራቱና በየሰበካ ጉባኤዎች እየሾመ ምዕመናንን ሲቦጠቡጥ፣ ሲሰልልና ሲያሰልል በመኖሩ ሃይማኖታችን እንዳለች አትቆጠርምና ይህም ይታሰብበት፡፡ በመንግሥት መዋቅሮችና በሃይማኖት ተቋማት በብዛት የተሰገሰጉት ወያኔዎች በቶሎ ካልተመነጠሩና ትክክለኛ ችሎታና ሙያ እንዲሁም የክህነት ሥልጣን ባላቸው ሰዎች ካልተተኩ ታጥቦ ጭቃ ነው፡፡ የዘር ጉዳይ ምኔም አይደለም፡፡ የሚተኩት ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከትግራይ ቢመጡ ጉዳየ አይደለም፤ ነገር ግን ወያኔ አይሁኑ ብቻ፡፡

ድህነትና ጎዳና ተዳደሪነት ከቀን ወደ ቀን እየበዛ ነውና በዚህም ጉዳይ ይታሰብበት፡፡ በተለይ ባለፉት 30 ዓመታት በሀገራችን የነበረው ሸፋፋ የሀብት ክፍፍል የፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ እያስከተለው ያለው ድህነት አሰቃቂ እየሆነ ነው፡፡ ጥቂቶች ተንደላቅቀው በሚኖሩባተ ሀገራችን ሚሊዮኖች በርሀብ አለንጋ እየተገረፉ የሚኖሩበት ሁኔታ በቶሎ መቋጨት አለበት፡፡ ድህነት ለብዙ ነገር ያጋልጣል፡፡ በድህነት ላይ ኳሻርኳራዊው ኢኮኖሚ የፈጠረው አድልዖኣዊው የሀብት ልዩነት ሲጨመርበት ደግሞ አደጋው ቀላል አይደለም፡፡ ብሔራዊ ስሜትን እየናደ፣ ሰብኣዊነትን እየደረማመሰ፣ የሞራልና ግብረ ገብ አጥሮችን እያፈራረሰ፣ የዝምድናንና የወዳጅነትን ድንበሮች ሳይቀር እየጠረማመሰ፣ … ጉድ እየሠራን ያለው ዋነኛ ነገር ድህነት ነውና አሁንም ይታሰብበት፡፡ ቁርሱን እንደምንም ቀምሶ ለምሣው የሚጨነቅ ማኅበረሰብ ይዘን ወዴት እንደርሳለን? ምናልባት ወደ መካከለኛዋ አፍሪካና ወደ የመን፡፡

በሩቅ ስንሰማቸው ይዘገንኑን የነበሩት ኢ-ሞራላዊና ኢ-ሃይማኖታዊ አውሮፓዊ ድርጊቶች እንደሰደድ እሳት እየተስፋፉ መጥተው ሀገር ምድሩን እያጥለቀለቁት ነውና ይህም ይታሰብበት (እርግጥ ነው ዓለም አቀፍ በጀት ተመድቦለት በታላላቅ ወንድሞች የሚተገበር የዘመን ፍጻሜ ምልክት በመሆኑ የትግሉ ከባድነት አይካድም)፡፡ ለማንኛውም እግዚኦ እንበል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሙስና (ጥፋት) ሀገርን በእሳት ቋያ የሚለበልብ ሰማያዊ መርገምት ስለሚያስትል በተለይ አባቶችና እናቶች ሌት ተቀን በርትታችሁ ጸልዩ – እንጸልይ፡፡ ሶዶምና ገሞራ ወደ ኢትዮጵያ እያመሩ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ እርግጥ ነው – በሕይወት ተስፋ መቁረጥና በባዶነት ስሜት መቃተት ለዕኩይ ተግባራት እንደሚዳርጉ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም የዜጎችን የመኖር ተስፋና ጣፋጭ ቤተሰባዊ ኑሮን በማለምለም አኳያ መንግሥትና ጤናማ መያዶች ያላቸው ሚና ቀላል እንዳልሆነ ተገንዝበው በዚህ ዙሪያ ጠንክረው ቢሠሩ ችግሮች ቀስ በቀስ እየተቀረፉ የመሄድ ዕድላቸው የሰፋ ይመስለኛል፡፡ የሆኖ ሆኖ ይህም ይታሰብበት፡፡ በአየር ላይ “ሀገር፣ ሀገር” ማለቱ ፋይዳ የለውም፡፡ “ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል” እንዲሉ ሀገር ያለች እየመሰለች ከእጃችን እያመለጠች እንደሆነ ይታየኛል፡፡….

ጠጭነት፣ ሰካራምነት፣ ሀሽሻምነት፣ ወፈፌነትና ዕብደት፣ ሴተኛ አዳሪነት፣ ሥራ ፈትነት፣ ሥራ አጥነት…. እየተበራከቱ ነው፡፡ እነዚህ ማኅበራዊ ነቀርሣዎች እየቀነሱ እንዲሄዱ የሚደረግበት መፍትሔ ካልተገኘና በተናጠል መክበር ፋሽን እንደሆነ ከተጓዝን የጋራ ሀገር አይኖረንም፤ ሁላችንም እናጣለን እንጂ አንዳችንም ደግ ነገር አናገኝም፡፡ አዲስ አበባን በዋናነት ይዛችሁ ከተሞችን በሥራ ሰዓት ታዘቡ፡፡ መንገዶች ላይና መጠጥ ቤቶች ውስጥ የሚታየው የሰው ብዛት፣ አስፋልቶች ላይ የሚርመሰመሰው የመኪና ብዛት… ሲታይ  “ለመሆኑ በዚህች አገር ሥራ የሚሠራው ሌሊት ነው እንዴ?” ያስብላል፡፡ የውጭ ሰዎች ይህንን ሁኔታችንን ሲታዘቡ ምን እንደሚሉን ባውቅ ደስ ባለኝ፡፡ ደግሞም በአውሮፓ መንገዶች እንደብርቅ የሚታዩ ዘመናዊ አውቶሞቢሎች እዚህ በኛ በድሃዋ ሀገር ያላንዳች ሀፍረት ሽንጣቸውን እያሳዩ እዚያና እዚህ በብዛት ሲታዩ ሀገራችንን የዕንቆቅልሾች መፈልፈያ ዋሻ ማድረጋቸውን እንረዳለን፡፡ ግርምቲ ዓዲ – ማለትም ሀገር፡፡ ይሄኔ እኮ የዚያ መኪና ባለቤት አጎት ለማኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ጉረኞች እኮ ነን!

ስለዚህ የደመወዙ ማነስ፣ የገንዘቡ የመግዛት አቅም ማሽቆልቆል፣ የመንገዱ መጥበብና በየቀኑ ከሚጨምረው የተሸከርካሪና የሰው ብዛት ፈጽም አለመጣጣም፣ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ከፍተኛና ማዘጋጃ ቤት እንዲሁም የትኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ድረስ የሚታየው የሙስናና የዘመድ አዝማድ አሠራር መንሰራፋትና የባህል ያህል መቆጠር፣ የዜግነትና ብሔራዊ ስሜት መጥፋት፣ የሀኪም ቤቱና የሀኪሞቹ ጥራት መጓደል፣ የትምህርቱ ጥራት ወደ ዜሮ መውረድ፣ የህግ አስከባሪው ንቃተ ኅሊና መዝቀጥ፣ ድንበር ያጣው ሆዳምነት፣ ትውልድን እየገደለ ያለው ማይምነት፣….. መንግሥታዊ ትኩረት አግኝቶ ልዩና የተቀናጅ ሥራ እንዲሠራበት ይደረግ፡፡ ምናልባት ያኔ መኖር ብጀምር ማለቴ ብንጀምር …

ይድረስ በተለይ ለተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች (ነፃነት ዘለቀ – አዲስ አበባ)

ነፃነት ዘለቀ (አዲስ አበባ)

Ethiopian PM Abiy Ahmed, discussed with opposition party leaders.

Ethiopian PM Abiy Ahmed, discussed with opposition party leaders.

በሰው የሚጠሉት ወይም እንደሚጠሉት የሚናገሩትን ራስ ሲያደርጉት የማያስጠላ ከሆነ የተሳከረ ስብዕና (MPD) ባለቤት የመሆን ችግር አለ ማለት ነውና በቶሎ መታከም ያስፈልጋል፡፡ እኔ ለምሣሌ በወንድሜ ወይ በጓደኛየ ላይ የማየውንና የምቃወመውን መጥፎ የመሰለኝን ምግባር እኔ ራሴ ባደርግና እንደነውር ባልቆጥር ትክክል አይደለሁም፡፡ ጨለማና ብርሃን ኅብረት እንደሌላቸው ሁሉ በአንድ ሰውነት ውስጥ ሁለትና ከዚያ በላይ ተቃራኒ ሰውነቶች ሊኖሩ አይችልም፡፡ እንደዚያ ያለ ችግር በፖለቲካው መስክ በጉልኅ እያስተዋልን ነው፡፡ ይህ አንቀጽ መግቢያየ መሆኑ ነው፡፡

ትናንት የሀገራችን – በአዲሱ አጠራር – የፖለቲካ ተፎካካሪዎች በጠ/ሚኒስትሩ ተጠርተው ውይይትና የምሣም ግብዣ ማድረጋቸውን በሚዲያ ተከታትለናል፡፡ እጅግ በጎ ጅምር ነው፡፡ በሀገራችን ለዘመናት ስንመኘው የነበረና በነዚህ ባሳለፍናቸው ጥቂት የለውጥ እንቅስቃሴ ጎልቶ በታየባቸው ወራት ውስጥ እናያለን ብለን ያልገመትነው ነገር ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ ከዚህ መልካም ጅማሮ ብዙ ነገር እንደተማሩ መገመት ይቻላል – ለመማር ፈቃደኛ ከሆኑ፡፡ በባህላችን እንካ ያሉት ዳቦ እርካሽ እንደሆነ መኖሩ አውኮን እንጂ በቀደምት አምባገነን ገዢዎች ዘንድ እንደዜጋና እንደሰውም መቆጠር ብርቅ እየሆነባቸው በየማጎሪያ ቤቶች እየታጨቁ ስንትና ስንት ግፍና በደል ይደርስባቸው የነበሩ ተቃዋሚዎች ይህንን የመሰለ ክብር ሲያገኙ ቢያንስ የጌቶች ጌታ የሆነውን ኅያው እግዚአብሔርን – የሚያምኑ ከሆነ ነው እሱም-  ቢበዛ ደግሞ ለዚህ ማዕረግ ያበቃቸውን የሕዝብ ትግልና የወጣቶች መስዋዕትነት ክብር ሊሰጡት በተገባ ነበር፡፡ ይቺ ዕድል እንዲህ በቀላሉ አልተገኘችም፡፡ እንኳንስ ተቃዋሚዎች ጠ/ሚ ዐቢይ ራሱ የንጹሓን ዜጎች ደምና አጥንት ነው ወደላይ አሽቀንጥሮ ለዚህ የታሪክ ኃላፊነት ያበቃው – ኃላፊነቱ ባለው እቶናዊ የሚጋረፍ ሙቀት የተነሣ የሚቀናበት ባይሆንም፡፡ ነገር ግን በሀገራችን የተለመደው ነገር ሌላ ሆነና ተቸገርን፡፡ አንድ ያገሬ የኔ ቢጤ (“ለማኝ” ላለማለት ነው) እንዲህ አለ ይባላል – “ስንቅ ያለቀበት ጌታ ‹ደጅህ ላይ ቆሟል› ብለህ ለጌታህ ንገረው!”፡፡ መግደርደርና መኮፈስ በመንደር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በላይኛው እርከንም መታየቱ እየጎዳን ነው፡፡… እንጂ አሁን “በምድርህና በሕዝብህ መሀል በሰላም ታገል” ተብሎ ተጠርቶ ሲያበቃ ሕዝብን ማመስና ትጥቅ አልፈታም ማለትን ምን ያመጣው ነበር? ለማንኛውም የነፃነትን አየር ገና በጨረፍታው ከመተንፈሳችን ያን ለዘመናት ያንገፈገፈንን የቆሪጥ አገዛዝ እንዳታመጡብን ተቃዋሚዎች አቅል ግዙልን፤ ከራሳችሁም፣ ከመንግሥትም ጋር በቀናነት ተግባቡ፡፡ እናንተስ ሾልካችሁ ብትሄዱ መውጫ መግቢያውን ታውቁታላችሁና ምንም አትሆኑም፡፡  ለኛ ለተገፋነው አስቡልን፡፡ …

የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን ስብሰባ በቲቪ ስመለከት ብዙ የተደበላለቀ ስሜት አደረብኝ፡፡ ጎላ ብሎ የተሰማኝ ግን ሀገራችን በሁሉም ረገድ ዕድለኛ አለመሆኗ ነው፡፡ በርካታዎቹ ፖለቲከኞች ዕድሜያቸው ከመግፋቱ የተነሣ ራሳቸውን ችለው ስለመራመዳቸውም ተጠራጠርኩ፡፡ እንዲህም አልኩና ራሴን ጠየቅሁ “ይሄ ፖለቲካ የሚሉት ነገር ጡረታ የለውም ማለት ነው?” ጥያቄየ ሳላስበው ቀጠለ “እነዚህ ሀፍረትና ይሉኝታ የሚባሉ ነገሮች ከትግራይ – ከወያኔ ትግሬዎች መፈልፈያ ዋሻ –  ብቻ ሣይሆን ከመላው ፖለቲከኞቻችን ጭንቅላት ውስጥም ሙልጭ ብለው ወጥተው ይሆን?” አልኩ፡፡ ነገር በሦስት ሲሆን ይጸናልና እንዲህ ስል ጥያቀየን ሰለስኩ – “በዚህ ሁኔታ የዚህች ሀገር የመኖር ዋስትና ምንድን ነው?” አዎ፣ ከ“ታላላቆች” እንዲህ ያለ ስሜት-አልባነት (insensitivity) ከተስተዋለ ከተራው ዜጋማ ምን ሊጠበቅ? “የዓሣ ግማት ከአናት” መባሉ ትክክል ነው፡፡ ሁላችን ተያይዘን የዝቅጠት ቁልቁለቱን የምንነጉደው አለምክንያት አልነበረም፡፡ ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሲሆን?

አንዱ አንዱን ሲያማ ጀምበር ልትጠልቅ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች በመንግሥት ወንበር ላይ ያሉትን “ሥልጣን ርስተ ጉልት መሰላቸው እንዴ? የሥልጣን ገደብ ተበጅቶለት መሪዎቻችንን በዙር ለምን አንመርጥም?” ለማለት የሚቀድሙት ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡ ይህን የሚሉ ተፎካካሪዎችን በየድርጅታቸው በሚገኙ ወንበሮች አንዳንዶቹ ከ25 ዓመታት በላይ መጎለታቸውንና በፈረንጅኛው አነጋገር እዚያው ወንበር ላይ vegetate ማድረጋቸውን ሳስበው አፈርኩ፡፡ በሀገሬ ዕድልም አዘንኩ፡፡ ከተሰብሳቢዎቹ ውስጥ በጣም ጥቂት ጎልማሦችን ብቻ ነው ያየሁት፡፡ አብዛኛው ያረጀው ያፈጀው የኢህአፓውና በኋሊዮሽ አቆጣጠር ከዚያም የሚያልፈው ትውልድ ነው – አንዳንዶቹ እንዲያውም ከዐቢይ ጋር መግባባት ሊሣናቸው የሚችሉ ጎምቱዎች ናቸው፡፡ ደግነቱ የመድረኩ መሪ – ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ – ወጣት መሆኑ ትንሽ ተስፋ አጫረብኝ እንጂ ዱሮ ወጣት ሳለሁ የፖለቲካ ቡድን መሪ የነበሩ የያኔዎቹ አንጋፋዎች አሁንም በ80 እና በ90ዎቹ ዕድሜያቸው እዚያው ሙጭጭ ብለው ስመለከት በኢትዮጵያ ውስጥ ንግግርና ተግባር እጅግ የተለያዩ መሆናቸውን አስታወስኩ – አወውሮፓ ውስጥ ብሆን ኖሮ – ብቻየንም ብሆን ሠልፍ ወጥቼ “shame on you dear octogenarians and nonagenarians!” እል ነበር – ዕድሜ ፀጋ መሆኑንና በአግባ ከተጠቀሙበት የሚያስከብር መሆኑን አውቃለሁና ትችቴን ከዐውድ ውጪ በሌላ መልክ እንዳትተረጉሙብኝ አደራ፡፡ ይህ ራስን የማምለክና ሌሎችም እንዲያመልኩብን የማስገደድ አባዜ ቤተ መንግሥቱን አልፎ ወደ ተቃዋሚዎች መውረድ ነገንም ከዛሬው በበለጠ እንድንፈራው ቢያስገድደን አይፈረድብንም፡፡ ክፉ ዐመል፡፡

በዚህች የበሬ ግምባር በማታህል ሀገር እንደሚባለው 70 እና 80 የፖለቲካ ኩይሣ ካለ የበሽታ እንጂ የጤና ሊሆን አይችልም፡፡ ከ310 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አሜሪካ እንኳን ሁለት ታላላቅ ፓርቲዎች ናቸው ያሏት፤ ከዚህ አንጻር የኛ በርግጥም አለመታደል ብቻ ሣይሆን ትልቅ እርግማን ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ፓርቲ ደግሞ በጎሣ የተመሠረተ ነው ማለት አንችልም፡፡ ለይምሰል ያህልም ቢሆን የሃሳብና የአመለካከት ልዩነትም አለበት፡፡ ስለዚህ ችግሩ የጎሣና የሃይማኖት ብቻ ሳይሆን እነሱን ሽፋን አድርጎ በሃሳብና በአመለካከት የተለያዩ በማስመሰል የጥቅምና የሥልጣን ፍትጊያ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ከ“ፍቅር እስከመቃብር”  የሚቀጥል “የሥልጣን ጥም እስከ መቃብር” በሚል መጽሐፍ ቢጻፍ ጥሩ ነው፡፡

አንዲት ትል ከመሀል ሸዋ በጧት ተነስታ እየገሠገሠች ስትሄድ እዚያው መሀል ሸዋ አንድ ሰው ያያታል አሉ፡፡ “አንች ትል ወዴት ትሄጃለሽ?” ብሎ ይጠይቃታል፡፡ እርሷም “መተማ!” ብላ ትመልስለታለች፡፡ እሱም ይቀጥልና “ትደርሻለች?”ይላታል፡፡ እርሷም “ልብማ!” ትለውና መንገዷን ትቀጥላለች፡፡ እኛም በነዚህ ጎምቱ የፖለተካ አበጋሮች የዴሞክራሲ ጥማታችን ሊረካ ጫፍ ላይ ደርሰናል፡፡…

የኛም ነገር እንደትሊቱ መሆኑ ነው፡፡ በ1983 እና ከዚያ ወዲህ እንደአሸን የፈላው ይሄ ሁሉ የፖለቲካ ድርጅት ጉዞው ወደ አራት ኪሎ ነው፡፡ ግን የትም ሳይደርስ ዕድሜውን ብቻ በመቁጠር አብዛኛው የድርጅት መሪ አራት ኪሎን በልቡ እንደሰነቀ አረጃና አሁን ጠማማ ጣሳ መስሎ በህልሙ ብቻ ጠ/ሚኒስትርና ፕሬዝደንት እንደሆነ ቀረ – ላልተለመደ ግልጽነቴ ይቅርታ፡፡ እንደሚመስለኝ እንደኛ እንደ ኢትዮጵያውያን ሥልጣንና ሀብት ወዳድ በዓለም ያለ አይመስለኝም፡፡ ለሥልጣን በተለይ ጉጉ ነን፡፡ ለዚያም ስንል አይደለም ሀገርና ሕዝብ ልጃችንንም ቢሆን ሳንሸጥ የማንቀር ብዙዎች ነን፡፡ መጥፎ ተፈጥሮ፡፡ ለዚህ ይመስላል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ትንንሽ ዘውዶችን አናቱ ላይ ጭኖ እንደሚንቀሳቀስ አንዳንድ የፖለቲካና የማኅበረሰብ ሥነ ልቦና ተንታኞች የሚናገሩት፡፡ የሥልጣን ሱሳችንን በስያሜዎች ሳይቀር መገንዘብ እንችላለን፡፡ “የኢዴፓ ፕሬዝደንት፣ የመዐሕድ ፕሬዝደንት፣ የኢመማ ፕሬዝደንት፣ የኢ.ቤ.መ ፕሬዝደንት፣ የአኢወማ ፕሬዝደንት፣ የኢሠማ ፕሬዝደንት፣ የ‹መኢጠማ› ፕሬዝደንት…” የብዙ ተቋማትን ኃላፊዎች ወይም ሊቃነ መናብርት ስያሜ ስንመለከት “ፕሬዝደንት” ነው የሚለው፡፡… እንዲህ ከሆነ እኔም የስድስቱ ቤተሰቤ ፕሬዝደንት ሆኜ ራሴን በራሴ መሾሜን በዚህ አጋጣሚ ሳልገልጽ ባልፍ ይቆጨኛል፡፡ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ደግሞ በምክትል ፕሬዝደንትነት ተሰይማ የቤት እመቤትነት ሥራዋን እንድትቀጥል ዛሬ ማታውን የሹመት ደብዳቤዋን እሰጣታለሁ – በልጆቻችን ፊት፡፡ ከጊዜው የሴቶች ሀገራዊ የሥልጣን ክፍፍል አኳያ ግን ይህ ሹመት መመርመር ሳይኖርበት አይቀርም፡፡ ቢሆንም እኔ ግን ሞቼ እገኛታለሁ እንጂ የፕሬዝደንትነቷን ሥልጣን  አልለቅም፡፡ … ይሁን፡፡ ፈገግታም የሕይወት ቅመም ናት፡፡

እባካችሁ እናንት አረጋውያን የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች!

አንጀቴ እያረረ በራሴ እስከመቀለድ የበቃሁት በናንተ ሁኔታ ስለተበሳጨሁ ነው፡፡ አላስፈላጊ ብዛታችሁን በተመለከተ እንደተመከራችሁት ቢቻል ወደ ሁለት አለበለዚያም ወደ ሦስትና አራት ውረዱ፡፡ ሰባና ሰማንያ ፓርቲ ሕዝብን ያወናብዳል፣ የሀብት ምንጭንም ያራቁታል እንጂ ለሀገር አይጠቅምም፡፡ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ሊይዝ የሚችለው የጠ/ሚኒስትር ብዛትም አንድ ብቻ ነው፡፡ በመቶና ሁለት መቶ ሥፍራ ተቧድኖ ለአንድ ቦታ መወዳደር ደግሞ አላዋቂነት ነው፤ ሕዝብ ይታዘባችኋል፡፡ ስለዚህ የዚህ ሁሉ ጎራ ዋናው ልዩነት የሥልጣን ጉዳይ እንጂ ሌላ ባለመሆኑ በቶሎ ንቁና ተሰባሰቡ፡፡ በዘርና በሃይማኖት ፓርቲ መመሥረት ደግሞ የስብዕና ክስረት ነው፡፡ ይህን ከሌላው ዓለም ተማሩ፡፡ በተለይ በዚህ በሰለጠነ ዘመን በጎሣና በሃይማኖት መሰባሰብ ከእንስሳም መውረድ ነው፡፡ ለአንዲት ቦታ አትራኮቱ፡፡ ሕዝቡን አድምጡት፡፡ ሕዝቡ ከእናንተ በላይ የነቃ ነው፡፡ የዝምብ ልጃገረድንና የቁንጫ ጠንጋራን የሚለየውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ማታለል በፍጹም አይቻልም፡፡ በበቀደሙ ስብሰባችሁ ለምሣሌ ብዙ ሰው ሆዱን ይዞ ሲስቅባችሁ ተመልክቻለሁ፡፡ እኔም ፍርፍር ብዬ ስቄያለሁ፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ካሙዙ ባንዳንና ሮበርት ሙጋቤን በተቃውሞው ጎራ ተጎልተው እንደማየት ምን እሚያስቅ ነገር አለ?

የዚህችን ሀገር ፖለቲካ እያበለሻሸ ያለው ትውልድ እንደሚመስለኝ ከ60 እስ 90 አካባቢ ያለው የቀደመው ትውልድ ነው፡፡ እናንተ ቢቻል ዕረፉ፤ ባይቻላችሁና የመታየትና የመወደስ እንዲሁም የዝነኝነትና የታዋቂነት አባዜ ናላችሁን እያዞረ የሚያስቸግራችሁ ከሆነ በወጣቶች ጀርባ አማካሪ ሆናችሁ ለሕዝቡ ታዩት፡፡ በእናንተ ቦታ ግን የተማሩ ወጣቶችን ተኩና ከድካማችሁ ዐረፍ በሉ፡፡ ይሄ “ያለ እኔ ሀገር ትጠፋለች” የሚለው የምትክ-የለሽነት አስተሳሰብ (sense of indispensability – which is, to me, a psychopathic problem))  አሳውሯችሁ እንዳይቀር ወደ ኅሊናችሁ ተመለሱና ከእናንተ የተሻሉ ወጣት ዜጎችን በመተካት ሕዝቡን ካሱት፡፡ አሪስቶትል ይሁን ፕሌቶ እንዲህ ብሏል አሉ “ተማሪ ከመምህሩ ካልበለጠ መምህሩ ደከመ እንጂ ዘር አልተካም፡፡” ግሩም አባባል ነው፡፡ እኛ ግን የፈዘዘ ቅጂ (ኮፒ) እየተውንና ራሳችንን እምሰማየ ሰማያት እየሰቅልን መሥራት የሚገባንን ሣንሠራ ሀገሪቱን ሰው-አልባ አድርገን አስቀረናት፡፡ ዶ/ር ዐቢይን ተመልከቱ፡፡ ይህ ብላቴና ትናንት ማንም የማያውቀው ፈጣሪ ከሰማይ ዱብ ያደረገው የሚመስል የሀገር አለኝታ ነው፡፡ እግዜር ቢፈልግ ኖሮ ብዙ የደከሙትን ኢንጂኔር ግዛቸውን ወይም ፕሮፌስር በየነን ያስነሳ ነበር፡፡ ያ አቅቶት አይመስለኝም፡፡ ግን የሁሉንም ልብና ኩላሊት የሚመረምር ፈጣሪ እነጎልያድን ትቶ ትንሹን ዳዊት አስነሳ፤ ምናልባት ጎልያዶችን በጎልያዶች ማጥፋት አልፈለገ ይሆናል – የፈጣሪ ሥራ እንደዚህ ነው፡፡ ከዚህ እንኳን ብዙ መማር በተገባ፡፡

በመሠረቱ በዚህች ዓለም ሁላችንም ነቁጥ ነን፡፡ ምንም ያህል እንማር፣ ምንም ያህል ሀብትና ገንዘብ ይረን፣ ምንም ያህል ዝነኞችና ታዋቂዎች እንሁን፣ በሕይወት ዘመናችን ምንም ዓይነት ተዓምር እንሥራ …  ዕድሜያችን ግን ውሱን ናት – ይህን ሌጣ እውነት ከተፎካካሪ ፖለቲከኞች ስብሰባ በጣም ተገንዝቤያለሁ፡፡ በሽታ ባያውቀን፣ ማጣት ባይደፍረን፣ ፍቅር ሞልቶ ቢፈሰን … እርጅናን ግን ልናስቀራት አንችልም፡፡ ታዲያ ለዚህች  ዕድሜ ብለን ለምን በሥልጣንና በሀብት ሱስ እንጠመዳለን? ለዚህች ከንቱ ዓለም ለምን የወገኖቻችንን ቁስል እያነፈረቅን በፖለቲካ ቁርቋሶ ሰበብ የሕዝብን ዕንባ በከንቱ እናፈሳለን? መንግሥቱና መለስ ኢትዮጵያን ልክ እንደእጅ ሥራ ዳንቴላቸው ቆጥረው ሲጫወቱብን፣ “እኔ ከሌለሁ ሁሉም የለም” ከሚል ዕብሪትና ትምክህት ያለነሱ ኢትዮጵያ አንድም መሪ ሊሆን የሚችል ዜጋ እንደማታፈራ አስበው ብዙ ተጫወቱብን፡፡ መጨረሻቸውን ስለምናውቀው አናነሳውም፡፡ ከንቱ ሰው መጨረሻውም ከንቱ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የወላድ መካን አይደለችም፡፡ አይሳካልንም እንጂ የወላድ መካን ልናደርጋት የምንፋጭረው እኛው ነን – በተለይ ትልልቆቹ፡፡ ሰውን እንንቃለን፤ ወጣቱን በተለይ አናስጠጋውም – ልክ እንደዝንጀሮ አባት – ዐቢይ አህመድ ከዝንጀሮ አባቶች እንዴት እንዳመለጠ ይገርመኛል – ለነገሩ እንዴት እንዳመለጠ እርሱ ራሱ በአንድ ወቅት ተናግሮታል – ክፋታችን እኮ ወደር የለውም፡፡ ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ከሀገራችን ይልቅ ለሥልጣናችን ቀናኢ መሆናችን ነው፤ ለሀብትና ለገንዘብ ስሱ ነን፡፡ እንጂ ብዙ የተማሩ ሰዎች አሉ፡፡ እነሱን እየመከርንና እያቃናን ወደ ኃላፊነት ብናስገባቸው በአዲስ አስተሳሰብ አዲስና ለሁሉም የምትመች ሀገር መሥራት በተቻለን፡፡ አሮጌ ምን ጊዜም አሮጌ ነው፡፡ በ83 የፖለቲካ ቅኝት 2011ን ልንመራው አንችልም፡፡ ዝንታለማችንን ዳውድ ኢብሳ ወይም በየነ ጴጥሮስ ወይም አረጋዊ በርሃ ወይም መርሻ ዮሴፍ እያልን መኖር አልነበረብንም፡፡ አሜሪካኖች የአንድን ሰው ፊት ከስምንት ዓመታት በላይ እንዳያዩ በህጋቸው የወሰኑት ወደው አይደለም፡፡ የመንግሥት ጥውርስ ጠበንጃ ስላለው – ታንክና መትረየስ ስላለው – ይሁን ግዴለም፤ የአንድን የፖለቲካ ተፎካካሪ መሪ ማለቴ “ፕሬዝደንት” ግን እንዴት ለ30 ዓመታት እንድመለከት ዕድሜ ይፍታህ ይበየንብኛል? ይችም ዕድል ሆና? እነዚህ ሰዎች ዛሬ ወይም ነገ ወደማይቀሩበት ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ እነሱ ሄዱ ማለት ደግሞ ቢያንስ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ኢትዮጵያም ሄደች – እስከወዲያኛው ነጎደች ማለት ነው፡፡ ይብላኝ ለነሱ እንጂ ኢትዮጵያ ግን ትኖራለች፡፡ ዐፄዎቹ ሄዱ፤ መንግሥቱም ሄደ፤ መለስም ተጓዘ፣ “ኃይለ ማርያም”ም ከ“ሥልጣን” ወረደ – ኢትዮጵያና ሕዝቧ ግን አሁንም አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ – እንዲያውም ከአሁኑ በተለዬ አምሮባቸውና በዓለም ላይ ደምቀው፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን የፖለቲከኞቻችን ነገር መስተካከል ያለበት ነገር አለ፡፡ አስተሳሰባችን ካልተቀየረ የሀዘንና የልቅሶ ዘመናችን በአጭር ላይቋጭ ይችላል፡፡

እናም ውድ ወንድሞቼና አባቶቼ!

እባካችሁን ልቀቁን! የተሸከማችሁትን ታሪካዊ ኃላፊነት ለወጣቱ አስረክቡ፡፡ ወደ ፍቅርና መተሳሰብ ማዕድም ቅረቡ፡፡ የቆዬ ቂማችሁንና ጥላቻችሁን ትታችሁ መጀመሪያ እርስ በርሳችሁ ዕርቅ አውርዱ – የጎሪጥ መተያየታችሁን ተውት፤ ለወጣቱ ትውልድ አርአያ ሁኑ፡፡ ብታዩት የአሁኑ ትውልድ ከእናንተ ቂምና በቀልን እንጂ ሌላ ነገርን ስላልተማረ ትቷችሁ የራሱን ኑሮ በራሱ ዓለም እየኖረ ነው፡፡ እናንተ ግን በዱሮው በሬ እያረሳችሁ በ “ማን አባት ገደል ገባ” የልጆች ጨዋታ ትቆራቆሳላቸሁ፡፡ በመሀሉ  ሀገርን ለማፍረስ ቀን የሚጠብቁ ወገኖች የእናንተን አለመስማማት እንደወርቃማ ዕድል ይጠቀማሉ፡፡

ዕድሜ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከሚጻፈው፣ ከሚነገረው፣ ከሚታየው፣ በራስ ላይ ከሚደርሰው የሕይወት ተሞክሮ  መማር ካልተቻለ ከምን ይማሯል? በራስ ዓለም ብቻ በምናብ እንደተመላለሱ ማርጀት ለአወንታዊ የካርማ መዝገብ (Karmatic Record) ጠቃሚ አይመስለኝም፡፡ ከፀጉር መሸበት ጋር የሚመጡ ብዙ ነገሮች አሉ፤ እነዚያን አለመገንዘብ ሽበትን ማስወቀስ ይሆናል – ድንጋይና እንጨትም ይሸብታሉና፡፡ እናም ነገ ዛሬ ሳትሉ እናንተ ታረቁና በትረ መኮንናችሁን ለወጣቱ ስጡ፡፡ ስታስረክቡም 70 እና 80 ኢትዮጵያን ሳይሆን አንዲት ኢትዮጵያን አስረክቡ፡፡ በቃ፡፡ ለመማር በጣም ዝግጁ ነኝ፤ ባጠፋሁ ይቅርታ፡፡ netsanetz28@gmail.com

በሃምሳ ዘጠኝ ሚሲዮኖች እና በዋናው መስሪያ ቤት የሰራተኛ ድልድል ስራ ተካሄደ

 By KALITI PRESS  

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሃምሳ ዘጠኝ ሚሲዮኖች እና በዋናው መስሪያ ቤት የሰራተኛ ድልድል ስራ አካሂዷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጀመረው የሪፎርም ስራ የአገራችንን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስከብር እና ኢትዮጵያውያን የሚኮሩበት ተቋም እንዲሆንና ተቋሙን ወደ እምርታዊ ለውጥ የሚያሸጋግር (Major Departure) መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ዛሬ ለአገር ውስጥ እና ለውጭ የመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ከሰራተኞች ድልድል በተጨማሪ አዲስ የአምባሳደሮቸ ሹመት በቅርቡ እንደሚካሄድና የምደባው ዋነኛ መመዘኛው እና ማቅኛው ሙያ ወይም ፕሮፌሽናሊዝም፣ ዕውቀትና ክህሎትን ያማካለ እንደሆነና በመስሪያ ቤቱ የሚሰሩትን ዲፕሎማቶች የሚያበረታታ ከመሆኑም በተጨማሪ ከውጭም ምሁራንና የአካዳሚክ ባለሙያዎች እና ታዋቂ ግለሰቦችን እንዲያካትት ይደረጋል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በውጭ ጉዳይና አገራዊ ደህንነት ፖሊስና ስትራቴጂ መሰረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልምድ እና የተሻለ ብቃት ያላቸው አንጋፋ ዲፕሎማቶችን (Senior Diplomats) ከሌላ አካባቢ ይልቅ በጎረቤት አገራት ይሰማራሉ፤ ከጎረቤቶቻችን ጋር “የዜሮ ውጥረት” (Zero Discord) ፖሊሲ እንከተላለን ብለዋል፡፡

በተለያዩ አገራት የሚገኙ 59 ሚስዮኖችን (አስራ አንዱ የቆንስላ ጄኔራል) በአራት የትኩረት መስኮች ማለትም ለኢትዮጵያ የክፉ ቀን ወዳጅ እና አጋርነት ማፍራት እና ማጠናከር፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ በውጭ የሚገኙ ወገኖቻችን በአገራቸው ጉዳይ ባይተዋር እንዳይሆኑ ተሳታፊ ማድረግ እና ለዜጎቻችን እና ሌሎች አካላት የተሻለ የቆንስላ አገልግሎት በመስጠት በመከፋፈል በትኩረት የሚሰራባቸውን መስኮች ለይቶ እንደሚሰራ ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰው ኃብት ልማት ሪዕይ በስፔሻላይዜሽን ላይ ያተኮረ፣ በሁሉም መስኮች የነበሩ እና የተሻሉ ዲፕሎማቶች ማፍራትና ከሌሎች አገሮች ጋር ተደራድረው የሚያሸንፉ፣ ተናግረው የሚያሳምኑ ለአገር ኩራት የሆኑ ዲፕሎማቶች በቻ ሳይሆን የሌሎች ሙያዎች ባለቤት (Generalist) እንዲሆኑ በማድረግ ተለዋዋጭ ከሆነው የዲፕሎማሲ ዓለም ጋር በቀጣይ እና በሂደት ስፔሻሊስት ማፍራት ነው፡፡

በተቋሙ አዲስ መዋቅርና ድልድል ማካሄድ ዋና እምርታ ታሪክ የሚናገር ብቻ ሳይሆን ታሪክ የሚሰራ፣ የኢትዮጵያን ውድቀት ሳይሆን ዕድገትን የሚደግፉ ወዳጅ መፍጠር፣ ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ባለሃብቶችን ወደ አገራችን መሳብ እና በውጭ ያሉ ኢትዮጵውያንና የአገራቸው ዋነኛ አምባሳደሮችን ያካተተ፣ የተሟላ ዲፕሎማሲ ስራ መስራት ነው ሲሉ አቶ መለስ በመግለጫቸው አውስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዋነኞቹ አምባሳደሮች በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ኤምባሲዎች በራቸውን ከፍተው የማገልገል ኃላፊነት እንዳለባቸውም አቶ መለስ ጠቅሰው፤ እነሱን ያልያዘ ዲፕሎማሲ ምን ተይዞ ጉዞ ነው፡፡ ከወገን ተነጥሎ፣ በርን ክርችም አድርጎ ዘግቶ የተሟላ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወን እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ ከውጭ ግንኙነት አንፃር የተቀመጠለትን ራዕይ እንዲያሳካ፣ ያሉበትን ጉድለቶች እንዲያስተካክልና ፈተናዎች እንዲወጣ የተዘጋጀው መዋቅር ስራ ላይ ውሏል፤ የበላይ አመራሩ በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች እንዲያተኩር እንዲሁም የመሰሪያ ቤቱ የትውስታ አቅም (Institutional Memory) መጠበቅ የሚያስችሉ አምስት ቋሚ ተጠሪዎች ወደ ስራ ገብተዋል፡፡

ያለ ሕገመንግስት ማሻሻያ የተሳካ ምርጫ ማድረግ ይቻለናል?

 By KALITI PRESS  

በኢትዮጵያ ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ጭምር የሚያስፈልጋቸው እርምጃዎች መወሰድ አለበት። ምርጫው የቀረው ጊዜ አስራ ሰባት ወራት ነው። አዳዲስ ክልሎች እውቅና ይሰጠን ብለው አሰፍስፈዋል። ህዝበ ውሳኔ የሚጠብቁና የማንነት ጥያቄ ያላቸውም አሉ። ምርጫ ቦርድ እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች ማስተናገድ ይጠበቅበታል። ታዲያ የፖለቲካ ፓርቲዎቹና መንግስት የታለመውን ተዓማኒ ምርጫ ማድረግ ይቻላቸዋል? ቻላቸው ታደሰ ይህን ዘገባ አዘጋጅቷል

ዜግነት

በተለይ ከውጭ የመጡት የፖለቲካ ድርጅቶቹ ድርብ ዜግነትን የሚከለክለው አዋጅ ትልቅ መሰናክል እንደሆነባቸው ደጋግመው አንስተዋል፡፡ አሁን በውይይቱ ከሚሳተፉት የፖለቲካ ቡድን መሪዎች ውስጥም ድርብ ዜግነት ያላቸው እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡

እዚህ ላይ እንግዲህ አሁን ሕገ መንግሥቱ ባልተሻሻለበት ሁኔታ የውጭ ዜግነት ያላቸው ፖለቲከኞች በተገኙባቸው መድረኮች የሚተላለፉ የውሳኔ ሃሳቦች እንደምን ቅቡል እና ሕጋዊ ሊሆኑ ይችላሉ? በሕጋዊነት በምርጫ ቦርድ ያልተመዘገቡ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም የምርጫ አዋጅ እና ሕገ መንግሥት ስለማሻሻል መነጋገራቸውስ አግባብነቱ እንዴት ይታያል? ትጥቁን በይፋ ያልፈታው ኦነግስ ተሳታፊ መሆኑ ጥያቄ አያስነሳም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳት ያላባቸው ናቸው፡፡ የኦነግን ጉዳይ ወረድ ብለን እናነሰዋለን፡፡

አንዳንዶቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ሕጋዊ ሆነው መመዝገብ ቢፈልጉ ምርጫ ቦርድ ቢያንስ አመራሮቹ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ብቻ ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ቦርዱ ድርብ ዜግነት መያዝ አለመያዛቸውን በምን ዘዴ ያጣራዋል? የሚለው ግን ሌላ ፈተና ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚችለው ራሱ መንግሥት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ አማራጭ አድርገው ያቀረቡት ፖለቲከኞቹ የውጭ ዜግታቸውን ይተውት የሚል ነው፡፡ ይሄ ደሞ እንደየግለሰቡ የሚለያይ የግል ውሳኔ እንጅ በፖለቲካ ድርድር የሚፈታ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ብዙዎቹ የድርጅት አመራሮች የዜግነትን ጉዳይ ደጋግመው የሚያነሱት ራሳቸው የድርጅቶቻቸው አመራር ሆነው ለመቀጠል፣ ለምርጫም ራሳቸውን ዕጩ ተወዳዳሪ አድርገው ለማቅረብ ጽኑ ፍላጎት ስላላቸው መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

አሁን ለምሳሌ ለዜግነት ሕጉ ሲባል ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግ ለኢሕአዴግ በቀላሉ የሚሞከር አይደለም፡፡ በርግጥ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይም ስለ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ተስፋ አልሰጡም፡፡ ኢሕአዴግ ቢሞክረው እንኳ ለየትኛውም ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የአባል ድርጅቶቹንም ይሁን የክልሎችን ድጋፍ ለማግኘቱ አስተማማኝ ዋስትና ሊኖረው አይችልም፡፡ እናም የዜግነት አዋጁ ጥቂት የማይባሉ ፖለቲከኞችን ከምርጫ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ውጭ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ከወዲሁ ይገመታል፡፡ ይሄም ታዲያ በምህረት መግባታችን ጥቅሙ ምንድን ነው? የሚል ቅሬታ ሊፈጥርባቸው ይችላል፡፡

በሌሎች መለስተኛ የምርጫ ደንቦች እና መመሪያዎች የተካተቱ ገደቦችን እንኳ በቀላሉ ማሻሻል ይቻል ይሆናል፡፡ ራሱ ምርጫ ቦርድ ሊያሻሽላቸው የሚችላቸውም ይኖራሉ፡፡

የፓርቲዎች ቁጥር

የፖለቲካ ድርጅቶችን ቁጥር ሰለመቀነስ ከተቃዋሚዎችም ከጠቅላይ ሚንስትሩም በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሦስት አራት ድርጅቶች ብትሆኑ እገዛ ለመስጠት ያመቸናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ይሄ አባባላቸው ባንድ በኩል ግን የተለመደውን የኢሕአዴግን የጌታ እና ሎሌነት ባሕሪ መልሶ የሚያመጣ ይመስላል፡፡ የፖለቲካ ቡድኖቹ አመራሮችም ይሉኝታ የያዛቸው ነው የሚመስሉት፡፡ መቸም ተቃዋሚ ድርጅት ሆነው በጠቅላላው የለውጥ ሃይሉን እና የለውጡን ሂደት ላለመተቸት የተማማሉ መስለው መታየታቸው ሳያስገምታቸው አይቀርም፡፡

በሌላ በኩል ድርጅቶቹ የመንግሥትን እገዛ ስላገኙ ብቻ ይወሃዳሉ ብሎ መጠበቅም የዋህነት ነው፡፡ አዳዲስ ብሄረሰብን መሠረት ያደረጉ የክልልነት እና ዞን ጥያቄዎች እየመጡ ባለበት ሰዓት እና የብሄር ፖሊቲካው እንደገና እየጦዘ ባለበት ወቅት ውህደት ይሳካል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ክልልነት ደሞ አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶችን ይወልዳል፡፡ የብሄር ፖለቲካው እስካለ ድረስ የብሄረሰብ ነጋዴዎች እና ጥቅመኞች የፖለቲካ ድርጅቶችን እየፈለፈሉ መቀጠላቸው የማይቀር ነው፡፡ ምናልባት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ከተገታ ግን ጥቆቶቹ የመዋሃድ ተስፋ ይኖራቸው ይሆናል፡፡

ላሁኑ ግን የሚጠብቅባቸውን ሕጋዊ ግዴታ መወጣት ያልቻሉትን ጥቃቅን ቡድኖች ምርጫ ቦርድ በሕጋዊ አሠራሩ እንዲሰርዛቸው ማድረግ አንዱ ተመራጭ አስተዳደራዊ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡

አሁን ሊሳካ የማይችለውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያን እንተወውና መንግሥት ግን አሁንም ለተቋም ግንባታ በቂ ጊዜ እና ዝግጅት ያለው አይመስልም፡፡ የምርጫ ቦርዱ አዋጅ እና ሌሎች የምርጫ ሕጎች እና ደንቦች ማሻሻያ ገና አላለቀም፡፡ ከፖለቲካዊ ቀውስ የወጡ እና ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ማድረግ የሚፈልጉ ሀገሮች ደሞ የተራዘመ ሂደትን፣ ጥልቅ ጥናት እና ድርድርን የሚጠይቅ የምርጫ ሕግ እና ሥርዓት ማበጀት እንዳለባቸው የሌሎች ሀገሮች ልምድ ያሳያል፡፡ ይሄ በእኛ ሀገር እየሆነ አይመስልም፡፡ ምርጫ ቦርዱ ራሱ ሥልጣኑ እና ነጻነቱ ተጨምሮለት ወደ ኮሚሽንነት ከፍ ይላል ወይስ በዚያው ስያሜው እና አወቃቀሩ ይቀጥላል? የሚለው ጉዳይም ገና ምላሽ አላገኘም፡፡ ገና አዋጁ ከጸደቀለት በኋላ ነው ራሱን እስከታች ድረስ እንደገና ማዋቀር የሚጀምረው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅም በመሻሻል ሂደት ላይ ነው ገና፡፡ ለነጻ እና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ደጋፊ የሆኑት የሲቪል ማህበራት እና የፕሬስ ሕጎችም እንዲሁ በመሻሻል ሂደት ላይ ናቸው፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃንን መልሶ በገለልተኛነት የማዋቀሩ ነገር ጨርሶ አልተጀመረም፤ የማሻሻያ ሃሳቡም በይፋ አልቀረበም፡፡
የኦነግ ፈተና

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከቀድሞው አቋማቸው ለዘብ ብለው ቀጣዩ ምርጫ መቸ ይካሄድ? የሚለውን በውይይት ለመፍታት ሃሳብ ማቅረባቸው ግን አንድ ተስፋ ሰጭ ነገር ነው፡፡

በጠቅላላው ስለ ሁሉም ድርጅቶች ፈተና ይህን ካልን እስኪ ደሞ ኦነግን በተናጥል እንየው፡፡

ኦነግ ሰሞኑን “ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሆነህ ተመዝገብ አለኝ፣ እኔም የለም፣ አልመዘገብም” አልኩ ብሎ አቋሙን ገልጧል፡፡ እንደ ምክንያት ያስቀመጠው ደሞ “በ1983/84 ሕጋዊ ነበርኩ፤ በዚያው ይያዝልኝ” የሚል ነው፡፡ ቦርዱ ደሞ አልተቀበለውም፤ እንዲቀበለውም ሕጉ አይፈቅድለትም፡፡ ኦነግ ይህን አቋም ሊያንጸባርቅ እንደሚችል እና ከምርጫ ቦርድ ጋር ሊወዛገብ እንደሚችል ዋዜማ ቀደም ሲሉ ግምቷን አስቀምጣ ነበር፡፡

አሁን ይሄ እሰጣገባ የተነሳው ምናልባት ኦነግ ከምርጫ ቦርድ የሕጋዊነት ሰርትፍኬት ለማግኘት ጠይቆ “መጀመሪያ ሕጋዊ ፓርቲ ሆነህ ተመዝገብ” የሚል ምላሽ ስለተሰጠው ይመስላል፡፡ በርግጥ ከውጭ ከመጡት ድርጅቶች እስካሁን በቦርዱ የተመዘገበ እንደሌለ ነው የሚታወቀው፡፡ ምናልባትም የምርጫ አዋጁ ማሻሻያ አንድ በጎ ነገር ይዞልን ይመጣ ይሆናል የሚል ተስፋ ያላቸው ይመስላል፡፡ ኦነግን ልዩ የሚደርገው ግን ከቦርዱ ጋር አተካራ በመግጠም የመጀመሪያው መሆኑ እና ጠመንጃውን በይፋ ያላስቀመጠ ብቸኛው ድርጅት መሆኑ ነው፡፡

ኦነግ “ከመንግሥት ጋር ትጥቅ ስለመፍታት ውል አልገባሁም፤ በኦሮሚያ ክልል አሁንም ታጣቂዎች አሉኝ” እያለ በአደባባይ ሲለፍፍ ከኖረ በኋላ በቅርቡ ከመንግሥት ጋር አዲስ ስምምነት እንደደረሰ ተነግሯል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ እና አቶ ዳውድ ኢብሳም ተስማምተናል ብለው ሲጨባበጡ አይተናል፡፡

እዚህ ላይ እንግዲህ ኦነግንም ሆነ ሌሎችን ድርጅቶች ከኤርትራም ይሆን ከሌላ ሀገር ጋብዞ ያመጣቸው ፌደራል መንግሥቱ ነው፡፡ በዚያ ላይ ደሞ ኦነግ ታጣቂ ድርጅት ነው፡፡ እናም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በምን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኑ ነው ከኦነግ ጋር የሚነጋገረው? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ተዳፍኖ ቀርቷል፡፡ ስምምነቱም ልክ እንደ አሥመራው ስምምነት ያልተብራሩት ነገሮች አሉት፡፡ ስምምነቱ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና ኦነግ መካከል ነው? በኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና በኦነግ መካከል ነው? ወይንስ በፌደራል መንግሥቱ እና ኦነግ መካከል ነው? የሚለው ጥያቄ በጊዜው ብዥታ ፈትሮ ነበር፡፡ የመንግስት መገናኛ ብዙሃንም ርስበርሱ የሚጣረሱ ዜና ነበር ያስተላለፉት፡፡

ሌላው ግርታ የፈጠረው ነገር “ኦነግ እና ሠራዊቱ ከመንግሥት ጋር ተባብረው ለመስራት ተስማምተዋል” የሚለው የመንግሥት አገላለጽ ነው፡፡ እንዴት በመንግሥት መገናኛ ብዙኻን ኦነግ እና ሠራዊቱ ተብሎ ሊገለጽ እንደቻለ ለሰሚው ግራ ነበር፡፡ መንግሥት “የትጥቅን ነገር አሥመራ ላይ ጨርሰነዋል” ባለበት አፉ መልሶ ለኦነግ ሠራዊት በተዘዋዋሪ እውቅና መስጠቱ አስተዛዛቢ ሆኖል፡፡

ለመሆኑ ኦነግ ለምንድን ነው ድጋሚ መዝገብ ያልፈለገው? ቢመዘገብስ ምን ይጎልበታል? የሚለውን ጥያቄ እናንሳው፡፡ መቸም ኦነግ ምዝገባውን ያልፈለገበትን ስውር ምክንያት እንዳለው ለእውነታ የቀረበ ግምት መያዝ ይቻላል፡፡ ድጋሚ የሚመዘገብ ከሆነ በሕጉ መሰረት ትጥቅ የፈታ መሆኑን እና በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የወሰነ መሆኑን በይፋ በምርጫ ቦርድ ሰነድ ላይ መፈረም ያለበት መሆኑ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚያስገባው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህን ሳያደርግ ደሞ ሕጋዊ የሕልውና ሰርትፍኬት ሊያገኝ እንደማይችል ያውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የኦነግ አቋም የአሥመራው ስምምነት ድጋሚ ሕጋዊ ሆኖ ስለመመዝገብ ምንም የሚገልጸው ነገር የለም ወይ? ወደሚል ጥያቄ ይወስደናል፡፡ መንግሥት የስምምነቱን ዝርዝር እስካላሳወቀ ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ መላ ምት ብቻ እየሰጠን ለመቆየት መገደዳችን አይቀርም፡፡

ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምርጫ ቦርድ ከኦነግ ጋር ምን ዐይነት የሥራ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል? ትጥቁን በይፋ ካልፈታ ድርጅት ጋር ለመነጋገር፣ የቃል ወይም የደብዳቤ ልውውጥ ለማድረግ ምን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን አለው? ብለን ብናነሳ ስህተት አንሆንም፡፡ ይልቅስ ቦርዱ ከኦነግ ጋር የሥራ ግንኙነት ከማድረጉ በፊት ለመንግሥት አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ማንሳት ያለበት ይመስለናል፡፡ ኦነግ ትጥቅ ስለመፍታቱ እና በሀገሪቱ አንድም ታጣቂ ሠራዊት የሌለው ሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅት ስለመሆኑ መንግሥት ይፋዊ ማረጋገጫ እንዲሰጠው መጠየቅ… ቦርዱ ይህን የመጠየቅ መብት አለው፤ መንግሥትም ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ቦርዱ ሙሉ ነጻነት ኖሮት እንዲሰራ እፈልጋለሁ ብሎ የድሮ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩትን ብርቱካን ሚደቅሳን ለቦርዱ የሾመ መንግሥት ይህን ግዴታውን ለመወጣት ፈጽሞ ሊሳነው አይገባም፡፡

መንግሥት የድሮውን ጽሕፈት ቤቱን ለኦነግ በቅርቡ የመለሰው አሥመራ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሠረት መሆኑን ኦነግ ራሱ ገልጧል፡፡ ምንም እንኳ ጎለሌ የሚገኘው ጸሕፈት ቤቱ ከጅምሩ የማን ንብረት እንደነበር ባይገለጽም ቅሉ… ችግሩ ግን ይሄ ሳይሆን ኦነግ “የድሮ ጽሕፈት ቤቴ ከተመለሰልኝ በዚያውም የድሮው ሕጋዊ ሰውነቴ እንዳለ መቀጠል አለበት” የሚል አቋም የያዘ መስሎ መታየቱ ነው፡፡ ሁለቱ ነገሮች ግን ሰፊ ልዩነት ያላቸው ናቸው፤ ጽሕፈት ቤት መመለስ ወይም አለመመለስ ተራ አስተዳደራዊ ጉዳይ ሲሆን ባንጻሩ ሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ መሆኑን ቃል ገብቶ መመዝገብ ወይም አለመመዝገብ ግን ግዙፍ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ነው፡፡

ኦነግ በዚህ አካሄዱ ድሮ “በሽግግሩ ካቢኔ የነበሩኝ የሥልጣን ቦታዎች ይመለሱልኝ፤ ከሽግግሩ መንግሥት ምክር ቤት በሃይል ተገፍቼ ስለወጣሁ አሁን ባለው ምክር ቤትም ተመጣጣኝ መቀመጫ እንዳገኝ በልዩ ሁኔታ ይታይልኝ” ላለማለቱ ምንም ዋስትና አለ? እስካሁን ከታዘብነው ተነስተን ስናየው ምንም ዋስትና የለም ማለት ይቻላል፡፡

ባጠቃላይ አሁን ሁሉም ያገባኛል የሚሉ ወገኖች ሀገር ውስጥ ጠቅልለው መገኘታቸው አንድ ጥሩ ዕድል ነው፡፡ መንግሥት የውይይት መድረኩን ማዘጋጀቱን ትልቅ ርምጃ ነው፡፡ መንግሥትም ውጭ የነበሩትን ድርጅቶች ስላስመጣ፣ ሀገር ውስጥ ላሉትም የሕወሃትን ፈላጭ ቆራጭነት ያስወገደ ለውጥ ስለጀመረ መድረኮቹ ግን ያው እንደ ድሮው መንግሥት-መር እየሆኑ እንዳይሆን ስጋት አለ፡፡

መንግሥት አሁን የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ አዋጅ በቶሎ አሻሽሎ ካልጨረሰ ምርጫ ቦርድ ሥራውን ለመስራት ይቸገራል፡፡ ብዙ ግዙፍ ነገሮችም ባጭር ጊዜ ውስጥ እንዲከናወኑ የተፈለገ ይመስላል፡፡ በዚያ ላይ የክልልነት ሕዝበ ውሳኔዎች እና የሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ ሥራዎች ተደርበው መጥተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ቅቡልነት ያላቸው፣ ሀገሪቱን ወደፊት የሚያሻግሩ የምርጫ ተቋማት እና ሕግጋት እንደምን መዘርጋት እንደሚቻል በጣም በጣም አጠራጣሪ ነው፡፡ [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

(ዋዜማ ራዲዮ)

ምን ለብሳ ነበር…?

 By KALITI

መስቀል አደባባይ በሚገኘው የአዲስ አበባ ሙዚየም አውደ ርዕይ /ኤግዚቢሽን/ እየተካሄደ ነው። ሰኞ ህዳር 17 የጀመረው እና ለ16 ቀናት ቀጥሎ ታህሳስ 1 ቀን የሚጠናቀቀው ይህ አውደ ርዕይ ‘ምን ለብሳ ነበር’? የሚል ርዕስ የተሰጠው ሲሆን የአስገድዶ መድፈር ሰለባ
የሆኑ ሴቶች ጥቃቱ በደረሰባቸው ሰዓት ለብሰውት የነበረው ልብስ ለትዕይንት የሚቀርብበት ነው፡፡ “ሴታዊት” የተባለ በሴቶች መብት ላይ የሚሰራ ንቅናቄ ከተባበሩት መንግስታት የሴቶች ጉዳይ እና በኢትዮጵያ የስዊድን ኤምባሲ ባዘጋጁት በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ከአልባሳቱ በተጨማሪ ጥቃቱ የደረሰባቸው ሴቶች የአስገድዶ መድፈሩ እንዴት እንደተከሰተ በጽሁፍ ቀርቧል። የአውደ ርዕዩ ዓላማ ለሴቶች መደፈር አለባበሳቸውን ምክንያት የማድረግ እና ተጠቂዎቹን የመውቀስ ልማድ ስህተት መሆኑን ለማመላከት ነው ተብሏል፡፡ በአውደ ርዕዩ የቀረቡት ታሪኮች ባለፉት 6 ወራት የተከሰቱ ሲሆን በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር እና አዳማ ነዋሪ የሆኑ ከ7 እስከ 20 ዓመት እድሜ ያላቸው አዳጊ ሴቶች ላይ የደረሰ ነው፡፡ ከአልባሳቱ ጋር አብረው የተፃፉት ታሪኮችን አዘጋጆቹ እንዳስቀመጡት በቀጥታ አቅርበነዋል፡፡
…………
“ኑሮ ሁሉ አስጠልቶኝ ራሴን ለማጥፋት መርዝ ጠጣሁ”
ስም – መክሊት
ዕድሜ 16
የደፈረኝ በቤት ሰራተኝነት እየሰራሁ በነበረበት ቤት ተከራይቶ የሚኖር ሰውዬ ነው፡፡ በወቅቱ እራሴን ስቼ ወድቄ ነበር እና ከዚያ በኋላ ለምን ለብዙ ቀናት ደም ይፈሰኝ እንደነበር ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡ ኑሮ ሁሉ አሰጠልቶኝ ራሴን ለማጥፋት መርዝ ጠጣሁና አሰሪዬ ሆስፒታል ስትወስደኝ የአራት ወር ነፍሰ ጡር እንደሆንኩ ታወቀ፡፡ ልጅ ወልጄ ለማሳደግ ዝግጁ ስላልነበርኩ ጽንሱን ማቋረጥ ፈልጌ ነበር፡፡ ግን እንዴት ማቋረጥ እንደምችል በቂ ግንዛቤ ስላልነበረኝ ብቻዬን ልጄን ወለድኩኝ፡፡ እንደወለድኩ አካባቢ ሳያት በጣም እናደድ ነበር አሁን ግን እየለመድኳት ነው፡፡ ስታድግ አባትሽ ሞቷል ነው የምላት እንጂ አልነግራትም፡፡
…………
“ከዚያ ቀን ጀምሮ በተደጋጋሚ የፆታዊ ጥቃት ያደርስብኛል”
ስም – ጥሩነሽ
እድሜ – 16
እናቴ ሞታለች፤ ከአባቴ ጋር ነበር የምኖረው፣ ያን ቀን ማታ አባቴ ከታናሽ እህቶቼ ጋር ከተኛሁበት ቢላ ይዞ ድምጽ እንዳታሰሚ ብሎ አስነስቶ ደፈረኝ፡፡ ከዚያ ቀን ጀምሮ በተደጋጋሚ የፆታዊ ጥቃት ደርሶብኛል፡፡ እርጉዝ መሆኔን ሲያውቅ ሁለተኛ እንዳላይሽ ብሎ ከባለ መኪና ረዳት ጋር ተነጋግሮ በባዶ እጄ አባረረኝ፡፡
…………
“ፖሊሱ ቢሮው ውስጥ አስገብቶ ደፈረኝ”
ስም – ኮከብ
ዕድሜ 16
ከክፍለ ሃገር ስራ ለመስራት ብዬ ነው ከቤት ጠፍቼ ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት፡፡ መንገድ ላይ ፖሊሶች አገኙኝና ወደ ጣቢያ ወስደው ተረኛ የነበረውን ፖሊስ የሴቶች እስር
ቤት ውስጥ አሳድራትና ሰኞ ጉዳዩን እናያለን ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚያ ግን ፖሊሱ ቢሮው ውስጥ አስገብቶ ደፈረኝ፡፡ ሲነጋ እስረኞቹ ጋር ወስዶ አስገባኝ። ለማንም አልናገርም
ብዬ ነበር፡፡ ግን እዚያ ውስጥ የነበሩት እስረኞች ፖሊሶቹ ሲመጡ ይቺ ልጅ ሲነጋ ነው የመጣችው የት እንዳደረች ጠይቋት ብለዋቸው ሲጠይቁኝ ነገርኳቸው። ጥቃቱን ያደረሰብኝ ፖሊስ መጀመሪያ ታስሮ ነበር ግን በዋስ ተለቀቀና ጠፋ፡፡ እስካሁን አልተያዘም፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ባልሄድ ኖሮ ይህ አይፈፀምም ነበር እያልኩ አንዳንዴ አስባለሁ፡፡
………
“ጥፋቱ የኔ እንደሆነ ተሰማኝ”
ስም – መንበረ
ዕድሜ 19
ከጓደኛዬ ጋር አብሬ እየኖርኩ የቀን ስራ ለመስራት ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት፡፡ ከስራ በኋላ ሁልጊዜ በታክሲ ወደ ቤቴ እገባ ነበር፡፡ አንድ ቀን ታክሲ ስላልነበር ሳይመሽብኝ በእግሬ ብሄድ ይሻለኛል ብዬ እየሄድኩኝ እያለ ሁለት የማላውቃቸው ወንዶች አፍነው መንደር ዳር ወዳለ ጫካ አስገብተው ደፈሩኝ፡፡ የትም አታገኛቸውም ሲሉኝ ወደ ፖሊስም አላመለከትኩም፡፡ ከወራት በኋላ የአምስት ወር ነፍሰ ጡር እንደሆንኩ አወቅኩኝ፡፡ ለሰዎች ስናገር እንዲህ አይነት ነገር እዚህ ያጋጥማል ሲሉኝ ጥፋቱ የኔ እንደሆነ ተሰማኝ፡፡

(ህዳር 20/2011 ዓ.ም.( አዲስ ልሳን ጋዜጣ)

አትዮጵያዊነት ከዘር በላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለሁላችንም በቂ ናት! እንወዳድ በፍቅር እንኑር – (ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ)

N

ሁላችንም ዘር አለን፡፡ዘሩ ግን እኛ አይደለንም ! እኛ ሰዎች ነን፡፡ሰውነት ከመፈጠር እንጂ ከመወለድ አይጀምርምና ፈጣሪ ዘራችንን ኢትዮጲያ በምትባል ምድር ላይ ዘራው፡፡ ሲዘራው ኢትዮጲያ ማለት ሰዎች መሆኗን አወቅን፡፡ መነጣጠል እስከማንችል ተዋሃድን፡፡ ትናንት የሆነ የሰው ዲስኩር አንዳችንን ካንዳችን ካልለየሁ እያለ ሥያሜ አበጀልን፡፡ ፈጣሪን ለማረም ይመስል እኛም ሆሆሆ ብለን ተቀበልን፡፡

በሕንድ 2032 ብሔረሰብ በሠላም እየኖረ በቻይና 499 ብሔረሰብ በሠላም እየኖረ ምነው እኛ (ሰማኒያዋን) መሸከም አቃተን?ተራ በተራ መግዛታችንን ለበላይነት ተጠቀምንበት?

ማንም ከማንም ጋር የሰውነት ጥል ሊኖረው አይችልም የዕውቀት ጥል እንጂ፡፡ገና ስንወለድ ዘር ምን ይሁን ቋንቋ ምን ይሁን የምናውቀው ነገር አልነበረም፡፡የዕውቀት ጥል ደግሞ በጠረጴዛ ዙሪያ እንጂ በጦር ሜዳ አይፈታም፡፡ምክንያቱም ይቅርታ እንጂ በቀል ታሪክን አያርምምና፡፡

ቋንቋ የሚባልን ነገር ከመካከላችን አውጥተን ማሰብ ብንጀምር ዘረኝነት ሃሳብ ላይ እንጂ ደም ላይ እንደሌለ እንረዳለን፡፡እየጨፈርን የናድነውን ቤት እያለቀስን አንሠራውም፡፡ ሁልጊዜ ጥፋት ካደረስን በኀላ እንዳጠፋን ምንረዳ ከሆነ ዞሮ መልሶ አለማወቅ ይሆንብናል፡፡ በመቻቻል ሳይሆን በፍቅር እንኑር መቻቻል አንድ ቀን ያሰለቸናል፡፡ታገስኩህ ቻልኩህን ያመጣል፡፡ ፍቅር ግን እስከዖሜጋ ይሸከማል፡፡

ከሰውነት በላይ ምን ማንነት ኖሮ የሁሉም መገኛ ያው አዳም ነው ዞሮ የማይሻር ሽረን አይሆኑሽ ሆነናል የማይድን ስናክም የማይሞት ገለናል፡፡

አትዮጵያዊነት ከዘር በላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለሁላችንም በቂ ናት! እንወዳድ በፍቅር እንኑር፡፡

ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ

ከብዕር ይልቅ ዱላ የቀለለውን የዩንቨርሲቲ ተማሪ እና የነገዋ ኢትዮጵያ ሳስብ


ከያሬድ ኃይለማርያም

ጋብ ብሎ የነበረው በዩንቨርሲቲዎች ውስጥ የሚታየው ተማሪዎች በጎጥ እየተደራጁ የመቧቀስ የኋላ ቀርነት አዙሪት ይህን ሳምንት ደግሞ እንደ አዲስ አገርሽቶ መታየቱ እጅግ አሳዛኝም፤ አሳሳቢም ነው።

ያሬድ ኃይለማርያም ለ7 ዓመታት ያህል ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ካውንስል ጋር አብሮ የሠራና የኖቬምበር 1 እማ 2ቱን ጭፍጨፋ ተከትሎ ከሃገር ብዙ ምስጢሮችን ይዞ በመውጣት ለአውሮፓ ሕብረት ያቀረበ ነው።

ዩንቨርሲቲዎች የምርምር፣ የእውቀት፣ የጥበብ እና የመፈላሰፊያ መንደሮች ናቸው። የዩንቨርሲቲው ማህበረሰብም አቅሙ የሚለካው በሰነቀው እውቀቱ፣ ባደረገው ምርምር እና የምርምር ውጤት ወይም ግኝት፣ በሃሳቦች ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች እና ሙግቶች እና ታትመው በሚወጡ ጽሁፎች ነው። የአንድን አገር እጣ ፈንታ የሚወስነው፣ የአገርን እድገት የሚመትረው፣ ትውልድ ቀራጭ የሆነው፣ የአገርን ሁለተናዊ ጉዞ እና አቅጣጫ የሚያሰምረው የህብረተሰብ ክፍል የሚወጣው ከእነዚህ ተቋማት ነው። እነዚህ ተቋማት የሚያፈልቁት የህብረተሰብ ክፍል ጠናማ መሆን የአገሪቱን ጤናማ ሆኖ መቀጠል ያመላክታል። በዛው ልክ የታወከ ምሁር ካፈለቁም የአገሪቱ እጣ ፈንታም እንዲሁ የሁከት ይሆናል።

እንዴት በዩንቨርሲቲ ደረጃ ያሉ ሰዎች በሃሳቦች ዙሪያ ሳይሆን በዘር ይቧደናሉ? እሺ መቧደናቸውስ ባልከፋ ያላቸውን ልዩነት በሰለጠነ የውይይት መድረክ ለመፍታት ለምን ድፍረት እና ብልሃቱን አጡት? እንዴትስ በአንድ ገበታ አብሯቸው ተቀምጦ እውቀት የሚገበይ ወንድማቸውን እና እህታቸውን መጤ ብለው ፈርጀው ለማጥቃት ተነሱ? በእውነት ይህ እንደ ሃገር ጠልቀን የገባንበትን ዝቅጠት ነው የሚያመላክተው።
ዛሬ በዩንቨሪስቲ ውስጥ ተማሪ የሆኑ ወጣቶች ይህ ሥርዓት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የተወለዱ ናቸው። አንዳንዶቹ ወጣቶች ሲናገሩ አገራችን ብለው የሚያስቡት ተወልደው ያደጉበትን ክልል ነው። ትልቋን ኢትዮጵያን በቅጡ አያቋትም። እንዲያውቋት ተደርገውም አላደጉም። ክልላቸውን ከኢትዮጵያ አግዝፈው እና አተልቀው የሚያዩ ይመስለኛል።

የሚገርመው አጥቂዎቹ ተማሪዎች መፈክራቸው ‘ከሃገራችን ውጡ’ ነው። አንዳንድ ጥቃት የደረሰባቸው ተማሪዎችም በመንግስት መገናኛ ጣቢያዎች ሳይቀር ሲናገሩ እንደሰማሁት ጥያቄያቸው ‘ወደ አገራችን መልሱን’ የሚል ነው። በሁለቱም ወገኖች በኩል በግልጽ የሚታየው እነሱ ከተወለዱበት ክልል ውጭ ያለው ሥፍራ አገራቸው አይደለም ወይም እነሱ የተወለዱበት ክልል የሌላው አገር አይደለም።

ለነገሩ የወያኔ የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ውስጥ በዙ አገሮችን ፈጥሯል። ተማሪዎቹ ብቻ ሳይሆኑ ፖለቲከኞችም ክልላቸውን እራሱን እንደቻለ እንደ አንድ ሉዐላዊ አገር አድርገው ሲገልጹ መስማት የተለመደ ሆኗል። ክልሎች እራሳቸውን ማስተዳደራቸው መልካም ሆኖ ሳለ በዘርና በቋንቋ ላይ መዋቀራቸው ግን ሌላ ገጽታ ሰጥቷቸዋል። ለዚህም ጥሩ ማሳያው በተለያዩ የክልል መንግስታት መካከል በአደባባይ ፈጦ የሚታየው ግጭት እና ንቁሪያ በሁለት ሉዐላዊ አገሮች መካከል የሚደረግ እንጂ በአንድ አገር ውስጥ በፌደራል አወቃቀር በተሳሰሩ ክልሎች መካከል ያለ አለመግባባት አይመስልም። ከዛም አልፎ አንዳንድ ክልሎች የፌደራል መንግስቱንም ጭምር እየተገዳደሩ ያለበት ሁኔታ በግልጽ እየታየ ነው። የትግራይ ክልላዊ መንግስት ወንጀለኞችን አሳልፌ ለፌደራል መንግስቱ አልሰጥም ማለቱ፣ ታሳሪዎችን አልፈታም ማለቱ እና አንዳን እያሳያቸው ያሉት ባህሪያት ትግራይ እራሷን የቻለች ሉዐላዊት አገር አስመስሏታል። በክልሎች መካከል ያለው የወሰን ግጭትም እንዲሁ የሁለት አገር የድንበር ግጭት ነው የሚመስለው።
ለማንኛውም እነኚህ በዩንቨርሲቲዎች ውስጥ የሚታዩት መናቆሮች እና በቡድን የሚደረጉ ዘር ተኮር ግጭቶች የጠቅላላ ፖለቲካው ነጸብራቅ ስለሆኑ በቅጡ ሊያዙ እና አፋጣኝ መፍትሔ ሊያገኙ ይገባል። የዚህ ዘር ተማሪዎች ወደዚህ ክልል አትሂዱ እየተባለ በአደባባይ የሚነገርበት እና ቅስቀሳ የሚደረግበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ከዚህ በኋላ የቀረን ምን ሊሆን እንደሚችል መገመቱ ከባድ አይሆንም።

ተማሪ ከመንግስት ጋር በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ወይም በነጻነት ጉዳይ ሲጋጭ እና እርስ በርሱ በዘር ሲጋጭ እንድምታው ለየቅል ነው።
ተሜ በጋራ ቆማ ለአካዳሚክ ነጻነት፣ ለፍትሕ፣ ለማህበተሰብ እኩልነት እና ጥቅም ከሥርዓት ጋር ስትታገል ሰው ሰው፣ ሙሁር ምሁር ትሸታለች። ተሜ በዘር ተቧድና ወንድም እና እህቶቿን መጤ እያለች ዱላና ድንጋይ ተሸክማ እርስ በርስ መፋለጥ እና እስከ እልፈተ ህይወት የሚያደርስ ጥቃት መሰንዘር ከጀመረች ግን ምሁርነቱም ቀርቶ ከሰው ተራም ትወርዳለች። ያ ማለት ደግሞ የነገዋ ኢትዮጵያ ከሰውም ተራ በወረዱ ሰዎች እጅ ትወድቃለች ማለት ነው። ሊነጋ የሚመስለውም ጨለማ ጭርሱኑ ድቅድቅ ይሆናል።

የነገ ብርሃኖቻችን ገና በጠዋቱ መጨላለም ከጀመሩ የመከራ ዘመናችን ይራዘማል። እንደ ማለዳ ጸሃይ እየፈኩና እያንጸባረቁ ከመመጡም መንገዳችን ሁሉ ከተጀመረው ለውጥ ጋር ተዳምሮ ከትውልድ ትውልድ የሚዘልቅ እና ጽልመት የማያሸንፈው የብርሃን መንገድ ይሆናል።

እባካችሁ በልዩነታቸው ዙሪያ ተወያዩ፣ ተጨቃጨቁ፣ ተከራከሩ፣ ጻፉ፣ አንብቡ እንጂ ዱላ አታንሱ። ወገኑን ለመጉዳት ዱላ የሚያነሳ ሰው ከተሸከመው ዱላም ይሁን ድንጋይ የተሻለ ዋጋ አይኖረውም። በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ሰው እና ጥሩ ተመራማሪ ምሁር መሆን በቂ ነው።
ለማንኛውም ልቦናውን ይስጣችሁ!