ምን ለብሳ ነበር…?

 By KALITI

መስቀል አደባባይ በሚገኘው የአዲስ አበባ ሙዚየም አውደ ርዕይ /ኤግዚቢሽን/ እየተካሄደ ነው። ሰኞ ህዳር 17 የጀመረው እና ለ16 ቀናት ቀጥሎ ታህሳስ 1 ቀን የሚጠናቀቀው ይህ አውደ ርዕይ ‘ምን ለብሳ ነበር’? የሚል ርዕስ የተሰጠው ሲሆን የአስገድዶ መድፈር ሰለባ
የሆኑ ሴቶች ጥቃቱ በደረሰባቸው ሰዓት ለብሰውት የነበረው ልብስ ለትዕይንት የሚቀርብበት ነው፡፡ “ሴታዊት” የተባለ በሴቶች መብት ላይ የሚሰራ ንቅናቄ ከተባበሩት መንግስታት የሴቶች ጉዳይ እና በኢትዮጵያ የስዊድን ኤምባሲ ባዘጋጁት በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ከአልባሳቱ በተጨማሪ ጥቃቱ የደረሰባቸው ሴቶች የአስገድዶ መድፈሩ እንዴት እንደተከሰተ በጽሁፍ ቀርቧል። የአውደ ርዕዩ ዓላማ ለሴቶች መደፈር አለባበሳቸውን ምክንያት የማድረግ እና ተጠቂዎቹን የመውቀስ ልማድ ስህተት መሆኑን ለማመላከት ነው ተብሏል፡፡ በአውደ ርዕዩ የቀረቡት ታሪኮች ባለፉት 6 ወራት የተከሰቱ ሲሆን በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር እና አዳማ ነዋሪ የሆኑ ከ7 እስከ 20 ዓመት እድሜ ያላቸው አዳጊ ሴቶች ላይ የደረሰ ነው፡፡ ከአልባሳቱ ጋር አብረው የተፃፉት ታሪኮችን አዘጋጆቹ እንዳስቀመጡት በቀጥታ አቅርበነዋል፡፡
…………
“ኑሮ ሁሉ አስጠልቶኝ ራሴን ለማጥፋት መርዝ ጠጣሁ”
ስም – መክሊት
ዕድሜ 16
የደፈረኝ በቤት ሰራተኝነት እየሰራሁ በነበረበት ቤት ተከራይቶ የሚኖር ሰውዬ ነው፡፡ በወቅቱ እራሴን ስቼ ወድቄ ነበር እና ከዚያ በኋላ ለምን ለብዙ ቀናት ደም ይፈሰኝ እንደነበር ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡ ኑሮ ሁሉ አሰጠልቶኝ ራሴን ለማጥፋት መርዝ ጠጣሁና አሰሪዬ ሆስፒታል ስትወስደኝ የአራት ወር ነፍሰ ጡር እንደሆንኩ ታወቀ፡፡ ልጅ ወልጄ ለማሳደግ ዝግጁ ስላልነበርኩ ጽንሱን ማቋረጥ ፈልጌ ነበር፡፡ ግን እንዴት ማቋረጥ እንደምችል በቂ ግንዛቤ ስላልነበረኝ ብቻዬን ልጄን ወለድኩኝ፡፡ እንደወለድኩ አካባቢ ሳያት በጣም እናደድ ነበር አሁን ግን እየለመድኳት ነው፡፡ ስታድግ አባትሽ ሞቷል ነው የምላት እንጂ አልነግራትም፡፡
…………
“ከዚያ ቀን ጀምሮ በተደጋጋሚ የፆታዊ ጥቃት ያደርስብኛል”
ስም – ጥሩነሽ
እድሜ – 16
እናቴ ሞታለች፤ ከአባቴ ጋር ነበር የምኖረው፣ ያን ቀን ማታ አባቴ ከታናሽ እህቶቼ ጋር ከተኛሁበት ቢላ ይዞ ድምጽ እንዳታሰሚ ብሎ አስነስቶ ደፈረኝ፡፡ ከዚያ ቀን ጀምሮ በተደጋጋሚ የፆታዊ ጥቃት ደርሶብኛል፡፡ እርጉዝ መሆኔን ሲያውቅ ሁለተኛ እንዳላይሽ ብሎ ከባለ መኪና ረዳት ጋር ተነጋግሮ በባዶ እጄ አባረረኝ፡፡
…………
“ፖሊሱ ቢሮው ውስጥ አስገብቶ ደፈረኝ”
ስም – ኮከብ
ዕድሜ 16
ከክፍለ ሃገር ስራ ለመስራት ብዬ ነው ከቤት ጠፍቼ ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት፡፡ መንገድ ላይ ፖሊሶች አገኙኝና ወደ ጣቢያ ወስደው ተረኛ የነበረውን ፖሊስ የሴቶች እስር
ቤት ውስጥ አሳድራትና ሰኞ ጉዳዩን እናያለን ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚያ ግን ፖሊሱ ቢሮው ውስጥ አስገብቶ ደፈረኝ፡፡ ሲነጋ እስረኞቹ ጋር ወስዶ አስገባኝ። ለማንም አልናገርም
ብዬ ነበር፡፡ ግን እዚያ ውስጥ የነበሩት እስረኞች ፖሊሶቹ ሲመጡ ይቺ ልጅ ሲነጋ ነው የመጣችው የት እንዳደረች ጠይቋት ብለዋቸው ሲጠይቁኝ ነገርኳቸው። ጥቃቱን ያደረሰብኝ ፖሊስ መጀመሪያ ታስሮ ነበር ግን በዋስ ተለቀቀና ጠፋ፡፡ እስካሁን አልተያዘም፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ባልሄድ ኖሮ ይህ አይፈፀምም ነበር እያልኩ አንዳንዴ አስባለሁ፡፡
………
“ጥፋቱ የኔ እንደሆነ ተሰማኝ”
ስም – መንበረ
ዕድሜ 19
ከጓደኛዬ ጋር አብሬ እየኖርኩ የቀን ስራ ለመስራት ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት፡፡ ከስራ በኋላ ሁልጊዜ በታክሲ ወደ ቤቴ እገባ ነበር፡፡ አንድ ቀን ታክሲ ስላልነበር ሳይመሽብኝ በእግሬ ብሄድ ይሻለኛል ብዬ እየሄድኩኝ እያለ ሁለት የማላውቃቸው ወንዶች አፍነው መንደር ዳር ወዳለ ጫካ አስገብተው ደፈሩኝ፡፡ የትም አታገኛቸውም ሲሉኝ ወደ ፖሊስም አላመለከትኩም፡፡ ከወራት በኋላ የአምስት ወር ነፍሰ ጡር እንደሆንኩ አወቅኩኝ፡፡ ለሰዎች ስናገር እንዲህ አይነት ነገር እዚህ ያጋጥማል ሲሉኝ ጥፋቱ የኔ እንደሆነ ተሰማኝ፡፡

(ህዳር 20/2011 ዓ.ም.( አዲስ ልሳን ጋዜጣ)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s