መንግሥት ሆይ ቁስልንና መንስኤን ለይ (ምሕረቱ ዘገዬ)

ሁሉም ሰው በግልጽ የሚረዳው በህክምናው ዓለም የሚተገበር አንድ አሠራር አለ፡፡ ይሄውም በአንድ ህመም ውጫዊ የስቃይ ምልክቶችና ውጤታቸው ላይ ብቻ ከማተኮርና የህመም ስሜቶችን ብቻ እየተከታተሉ ስቃይን በማስታገሻ መድሓኒቶች ለተወሰነ ጊዜ ፋታ ከመስጠት በተጓዳኝ የበሽታውን መንስኤ ማጥናትና ህመሙን ከሥር መሠረቱ አክሞ መፈወስ ተመራጭ የመሆኑ እውነታ ነው፡፡ ይህ አሠራር በጤናው ዘርፍ ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡

ጥረቴ በፈረንጅኛው አጠራር ‘cause and effect’ የሚለውን ለማስታወስ ነው፡፡ መንስኤና ውጤት – ባማርኛ፡፡ አንድ ችግር የሚያስከትለውን ውጤት ብቻ እያዩ ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት መላ አቅምንና ጊዜን ከማባከን ትኩረትንና ዕውቀትን ሰብሰብ አድርጎ የችግሩን መነሻ ምክንያት በማጥናት ለአንዴና ለመጨረሻ በሚባለው አገላለጽ ሊጠቀስ በሚችል መልኩ ችግሩን እስከወዲያኛው ለማስወገድ ቢሞከር ብልኅነት ነው፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድና ሊጠገን ከማይችል ኪሣራም ያድናል፡፡

የሀገራችንን ለውጥ ተከትሎ ነቀርሣዎቹ ወያኔዎች መቀሌ ላይ መሽገው በ100 ሚሊዮኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ክተት ካወጁ ሰነበቱ፡፡ የለውጡ ኃይልም በነቀርሣዎቹ አማካይነት እዚያና እዚህ የሚቀጣጠሉ እሳቶችን – ከሕዝብ ድጋፍ ጋር – ባለ አቅሙ እየተሯሯጠ ከማጥፋት ውጪ ችግሩን ከመሠረቱ መንቅሎ ለመጣል የጎላ ነገር ሲያከናውን አይታይም – ቢያንስ እስካሁን ባለው ሁኔታ፡፡ ይህንን ስል ግን እጅግ የሚያበረታቱ ፀረ-ነቀርሣ ትግሎችን ማካሄዱንና ብዙ ድሎችን ማስመዝገቡን እንዳልዘነጋሁ ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡  ይሁንና ይህ አሁን የሚታየው መፈራራት የሚስተዋልበት አካሄድ ብዙ መስዋዕትነትን እንዳያስከፍለን እፈራለሁ፡፡ እነሱም ለዘመናት በቀበሩት ፈንጂ ምክንያት እንደምንፈራቸው የተረዱ ይመስላሉ፡፡ ያንንም ሥነ ልቦናዊ ስሜት እስከጥግ ለመጠቀም ሳያቅዱ አልቀሩም፡፡ እርግጥ ነው መሸነፋቸውን ይረዱታል፡፡ እኛ ግን ተስፋ የቆረጠ ሰው የማያደርገው ነገር ስለሌለ ወደማይቀረው ከርሠ መቃብራቸው እስኪገቡ ድረስ ብዙ ነገር እንደሚያደርጉ ማሰብ አለብን፡፡ ባህር ውስጥ እየሰመጠ የሚገኝ ሰው – ለምሣሌ – ገለባና ዐረፋ የሚያድነው እየመሰለው ይጨብጣቸዋል፡፡ መንፈራገጡ ግን የጊዜ ጉዳይ እንጂ መሞቱ በፍጹም አይቀርም፡፡ እባብ አናቱን እስኪመታ ይንፈራገጣል፤ ድመት ዘጠኝ ነፍስ አላት ቢባልም መሞቷ ግን አይቀርም፡፡ የጭንቅላት ሥጋም እንጨት መፍጀቱ ከፋ እንጂ ቢውል አያድርም – ቢያድር አይውልም- ይበስላል፡፡ አራዳዎች “ላታመልጠኝ አታሩጠኝ! “የሚሉት ወደው አይደለም፡፡ ሁሉም በጊዜው ይሆናልና የሚደንቅ አዲስ ነገር የለም፡፡ ቆራጥነትና መግባባት ካለ መቶ ሚሊዮን የተገፋና የተበደለ ሕዝብ በጥቂት መቶ ሽዎች የሚቆጠሩ “ሌቦቼን አትንኩብኝ” ባይ አፈንጋጮችን ማሸነፉ ይቅርና ስድስት ሚሊዮን ጽዮናውያንም 7.5 ቢሊዮን ሕዝብ በፖለቲካና በኢኮኖሚ አንበርክከው አብዛኛው የነሱ ፍላጎት በምድራችን እውን እየሆነ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህ ምሥጢር ነው፡፡…

በአዲስ አበባና በሌሎች ቦታዎች ባልተለመደ ሁኔታ የነዳጅ አቅርቦት እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ይህ ችግር በተለይ አሁን ለምን ሊፈጠር ቻለ? በአንዳንድ አካባቢዎች አንድ ሊትር ቤንዚን እስከ 30 እና 40 ብር በጥቁር ገበያ እንደሚሸጥ እየሰማን ነው፡፡ የዚህ ችግር መንስኤ መታወቅ አለበት፡፡ እርምጃም መወሰድ ይኖርበታል፡፡ በመጠኑም ቢሆን ከደርግ መማር ተገቢ ነው፡፡ ያለመስዋዕትነት ድል ባለመኖሩ አጥፊዎችን እየያዙ ተገቢውን ቅጣት መስጠት ከተጨማሪ ጥፋትና ውድመት ይታደጋል፡፡ እርግጥ ነው – የዘመናችን ከይሲዎች እንደነዚያ የበርበሬ ነጋዴዎች በጥይት ይገደሉ ማለቴ አይደለም፡፡ ግን ቅጣት መኖሩን የማያውቅ ባለጌ ጥፋት ማድረሱን ይቀጥላልና ይታሰብበት ለማለት ነው፡፡ መምከርም፣ ማስተማርም፣ … ተገቢ ነው፡፡

አዲስ አበባ በመንገድ ችግር እየተጨናነቀች ነው፡፡ በተለይ መሀል ከተማ ትልቅ ችግር አለ፡፡ ለ10 ኪሎ ሜትር ጉዞ ሰዓታትን እየፈጀን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ጥቂት ዓመታትን ብንቆይ ከተማዋ  ለይቶላት የምትፈነዳ ይመስለኛል፡፡ አሁን እኮ እሳት ለማጥፋት፣ ወላዶችንና ህሙማንን በወቅቱ ሀኪም ቤት ለማድረስ፣ ሌባንና ቀማኛን በፖሊስና በቀበሌ ቃፊር አባርሮ ለመያዝ፣ ወንጀለኛን በቁጥጥር ሥር ለማዋል፣ ወደ ሥራ በሰዓቱ ለመግባት፣ ቀጠሮን አክብሮ ለመገኘት፣ ትምህርትን ለማስተማርም ሆነ ለመማር፣… አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ነገሮች ለጊዜ ጋር የተገናኙ ናቸውና ጊዜህን የትራፊክ ጭንቅንቁ እንክት አድርጎ ከበላው እዚህ የተጠቀሱትን ጨምሮ ብዙ ነገር ይከሽፍብሃል፡፡ እሳት ጊዜ አይሰጥም፡፡ በሽታ ጊዜ አይሰጥም፡፡ ምጥ ጊዜ አይሰጥም፡፡ ሌባና ወንጀለኛ ጊዜ አይሰጥም፡፡ እነዚህን ጉዳዮች የሚያስተናብሩ የመንግሥትም ሆኑ የግል አካላት መንገድ ላይ ለሰዓታት ተዘግቶባቸው እዚያው ሲድሞነሞኑ ከዋሉ ችግሮች እየተወሳሰቡ እንጂ እየተፈቱ አይሄዱም፡፡ ይታሰብበት፡፡

የሚገርመው ነገር ችግርን ለመፍታት ችግር የሚጨመርበት ሁኔታ ነው፡፡ የመኪና መንገድ ችግር ከተማችንን አስጨንቆ ባለበት ሁኔታ በብዙ ቦታዎች ፍጥነት መቀነሻ በሚል በሚጋደሙ ጉርብርብ ንጣፎች መኪኖች ሲርመሰመሱ ይውላሉ፡፡ ችግርን ማስወገድ ቢያቅት በችግር ላይ ችግር ለምን ይደረባል? የሰው ኃይል መድቦ ህግ ተላላፊን እንደማስተማርና ካልተቻለም እንደመቅጣት መንገድን በዚህ መልክ ማጣበብ ተገቢ አይመስለኝምና ይሄም ጉዳይ በቅጡ ይታሰብበት፤ በስሜትና በወጉ ባልተጠና የይድረስ የሞቅታ ሃሳብ አንመራ – (በመቅጣት እንደማላምን ቢታወቅልኝ ግን ደስ ይለኛል)፡፡ ሰዎች አእምሯቸውን ቢጠቀሙ አንድም ፖሊስ፣ አንድም ዳኛ፣ አንድም ወታደር ሳያስፈልጋቸው መኖር እንደሚችሉ ብዙ ምሣሌዎችን ከዓለማችን አካባቢ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኛ ሀገር ያለው ህግ-አልባነት ግን የሚያሳዝንና የሚገርምም ነው፡፡ ህግ አውጪውና  ህግ አስከባሪው የሚያወጡትን ህግ ለመደፍጠጥ ቀዳሚዎቹ እነሱ ናቸው፤ ህጉ እነሱን የሚያካትት አይመስላቸውም፡፡ ያለብን ችግር እኮ — በስመ አብ!!!!!!!

የተቀጣሪዎች ደመወዝ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ የገንዘባችን የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደጊዜ ተሽመድምዶ እንደሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የጀርመን ማርክ ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡ አላየሁም እንጂ ላጤዎች ግድግዳቸውን በመቶ ብራችን የሚያሰጌጡ ይመስለኛል – ቢያንስ ሌሊቱ እስኪነጋና ልጠው እስኪጠቀሙበት፡፡ በዚህን ሁኔታ ሰውን አትስረቅ ወይም አትሞስን ማለት ታዲያ “ኢ-ሞራላዊ” መሆን ነው፡፡ ሰዎች እንዴት ተንደላቀው እንደሚኖሩ የሚመለከት ባለዝቅተኛ ደሞዝ በወር ሁለት ቀናትን እንኳን ሊያስኖረው የማይችል ደሞዝ ሲከፈለው መናደዱና ገንዘብ ለማግኘት ሲል ወደ ወንጀልና ኃጢኣት መግባቱ አይቀርም፡፡ በዚህን መሰሉ አስጨናቂ ወቅት ለነፍስና ለኅሊና የሚያስቡ ዜጎች ቁጥር እጅግ አናሳ ነው፡፡ የሚዘወተረው የሕይወት መርህ “ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ” የሚለው ይሆንና ሩጫው የጥሎ ማለፍ ይሆናል፡፡ በጥሎ ማለፍ ማኅበረሰብኣዊ የኳስ ዐበደች ጨዋታ ደግሞ ተረጋግጦ የሚሞተው እጅግ ብዙ ነው፡፡ ትግሉ እግር አውጭኝና ነፍስን  አውሎ የማሳደር በመሆኑ ይሉኝታንና ሀፍረትን ሸጦ የበላ ነው፡፡ ይህም ታዲያ ይታሰብበት፡፡ በሰው ከመፍረድ በፊት ቅጥር ሠራተኛው  የሚከፈለው ደሞዝ የኑሮ ውድነቱን ያገናዘበ ነው ወይ? ቢያንስ ቢያንስ ከጎረቤት ሀገራት የማይተናነስ የደሞዝ እስኬል እንከተላለን ወይ? የኬንያ መምህር እንዴት ይኖራል? የታንዛንያ የህክምና ዶክተር እንዴት ይኖራል? የሞዛምቢክ ነርስ እንዴት ይኖራል/ትኖራለች? የናይጄሪያ አንድ የቢሮ ኃላፊ እንዴት ይኖራል? ስንቱ ዜጋ በቤቱ ምን ምን አለው? ምን ምን የለውም? ምን ያህል ዓመታትን በምን የትምህርትና የደሞዝ ደረጃ ሠርቶ ምን ምን ሊኖረው ይገባል? የትና እንዴት ይኖራል? ምን ይበላል? ምን ይጠጣል? ምን ይለብሳል? የንጹሕ ውኃ፣ የመብራት፣ የስልክ፣ የመንገድ፣ የመንግሥታዊ ታህታይና ላዕላይ መዋቅሮች ዝርጋታ በምን መልክ ተደራጅተውለታል? … ተብሎ ይጠና፡፡ መንግሥት ለዜጎቹ ካላሰበ ማን ያስብላቸዋል? ግዴታውን ያልተወጣ መንግሥት ደግሞ የዜጎችን መብትና ግዴታ ሊያስከብር አይችልም፡፡ ማዘዝና መታዘዝ የሚኖረው ሁሉም መብትና ግዴታውን በአግባቡ ሲወጣ ነው፡፡ በሥርዓቱ የማልይዘው ልጅ ዐመፀኛና በዋልፈሰስ ቢሆን ተጠያቂው እኔ እንጂ እርሱ ሊሆን አይችልም፡፡

በየቀኑ ወደሰማያት የሚመጥቀው የኑሮ ውድነት መፍትሔ ይፈለግለት፡፡ የመነገጃና የማትረፊያ ህጎች ይኑሩ፤ ካሉም እንዲከበሩ ቁጥጥር ይደረግ፡፡ ንግዱም ልክ እንደፖለቲካው ሁሉ በስሜት የሚነዳ ከሆነ ሁላችንም ተያይዘን መጥፋታችን አይቀርም፡፡ ይሄ በየቦታው የተገተረ የሀብታም ፎቅና ሕንፃ ደግሞ ሰው ሠራሽ ነውና ቀውጢ ቀን ሲመጣ የዶጋ ዐመድ ይሆናል፡፡ አሌፖንና ደማስቆስን ያዬ በጦርነትና በግጭት አይቀልድም፡፡ ሩዋንዳንና የመንን ያዬ በጎሣና በዘር እሳት አይጫወትም፡፡ ጋዳፊን፣ ሣዳምን፣ መንግሥቱን፣ መለስን፣ …  ያዬ በአምባገነንነት ካርድ አያፌዝም፡፡ ሶማሌንና ዩጎዝላቪያን ያዬ በተመሳሳይ ወይም በተቀራራቢ ቋንቋና ባህል አለኝታነት አይመፃደቅም፡፡ እኔ ተናግሬያለሁ! ዋ! ዛሬን እያማረጥሽ የምትበይና መኪና እንደሸሚዝ እየለዋወጥሽ የምትዘባነኝ ሌባና ሙሰኛ ሁላ ነገ ጉድ ሲዘንብ መግቢያ ቀዳዳ የለሽምና አሁኑኑ ማሰብ ጀምሪ፡፡ ነገ የማሰቢያ ጊዜም ላይኖረን ይችላል፡፡ አምስት ይሁን ስድስት የቤተሰብ አባላቱን ከአየር በወረደ ቦምብ ያጣ ሦርያዊ የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር በአውሮፓ ጎዳናዎች ለማኝ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ የወደፊት የማይቀር ኹነትን ከዛሬ አስቀያሚ ገጠመኞች ተነስቶ ለመተንበይና አስቀድሞ ለመጠንቀቅ በግድ ኢትዮጵያዊውን ሼህ ሁሴን ጂብሪልን ወይም የእንግሊዟን የ16ኛው ክፍለ ዘመን ነቢይት  ማዘርሽፕተንን መሆን አይጠይቅም፡፡ እነስብሃት ነጋና አባይ ፀሐዬ፣ እነጌታቸው አሰፋና ጌታቸው ረዳ የሠሩትን ያን ሁሉ ግም ሥራ በማሰብ መጨረሻቸው እንደማያምር መረዳት ከተሳናቸው በርግጥም በሰው አምሳል የተፈጠሩ ጅቦች እንጂ አእምሮ ያላቸው ሰዎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ኧረ ጅቦች ከወያኔዎች በስንት ጣማቸው! ጅብ እኮ ወንድ ወንዱን አይሰርም፡፡ ጅብ እኮ በህግ ስም አስሮ ወገኑን አያኮላሽም፡፡ ጅብ እኮ ሰውን ከነነፍሱ ወደ ገደል አይጥልም፡፡ ጅብ እኮ ይጠግባል – እንደወያኔ እምብርት-የለሽ አይደለም፡፡ እነዚህ ወያኔዎች እኮ ከሰይጣንም በልጠው ሰይጣን ራሱ ስለነሱ እንዲመሰክር አስገድደውታል – “ወያኔዎች በክፋትና በጭካኔ እኔን ዕጥፍ ድርብ ያስከነዳሉ! እኔ ያላደረኋቸውንና ለተከታዮቼ ያላስተማርኳቸውን አዳዲስ የማሰቃያ ሥልቶችን የፈለሰፉ አለቆቼ ናቸው፡፡…” ሲል ዲያብሎስ ራሱ ምዕመናኑ ፊት ዐውደ-ጥፋት ላይ ቀርቦ በቅርቡ መናገሩን በፌስቡክ አንብቤያለሁ – የማመንና ያለማመን ጉዳይ የግሌ ነው፡፡ ወያኔዎች ዕረፍት የሌላቸውና ዕረፍትም የማይሰጡ የሲዖል ትሎች ናቸው፡፡ …

ወያኔ ቤተ አምልኮቶችንም አጥፍቷቸዋል፡፡ ክህነት የሌላቸው ቀሳውስትን፣ ፅድቅ የሌላቸው ማይም ጳጳሣትን፣ ትምህርት የሌላቸው የደብር አለቆችን… በየአድባራቱና በየሰበካ ጉባኤዎች እየሾመ ምዕመናንን ሲቦጠቡጥ፣ ሲሰልልና ሲያሰልል በመኖሩ ሃይማኖታችን እንዳለች አትቆጠርምና ይህም ይታሰብበት፡፡ በመንግሥት መዋቅሮችና በሃይማኖት ተቋማት በብዛት የተሰገሰጉት ወያኔዎች በቶሎ ካልተመነጠሩና ትክክለኛ ችሎታና ሙያ እንዲሁም የክህነት ሥልጣን ባላቸው ሰዎች ካልተተኩ ታጥቦ ጭቃ ነው፡፡ የዘር ጉዳይ ምኔም አይደለም፡፡ የሚተኩት ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከትግራይ ቢመጡ ጉዳየ አይደለም፤ ነገር ግን ወያኔ አይሁኑ ብቻ፡፡

ድህነትና ጎዳና ተዳደሪነት ከቀን ወደ ቀን እየበዛ ነውና በዚህም ጉዳይ ይታሰብበት፡፡ በተለይ ባለፉት 30 ዓመታት በሀገራችን የነበረው ሸፋፋ የሀብት ክፍፍል የፈጠረው የኢኮኖሚ ቀውስ እያስከተለው ያለው ድህነት አሰቃቂ እየሆነ ነው፡፡ ጥቂቶች ተንደላቅቀው በሚኖሩባተ ሀገራችን ሚሊዮኖች በርሀብ አለንጋ እየተገረፉ የሚኖሩበት ሁኔታ በቶሎ መቋጨት አለበት፡፡ ድህነት ለብዙ ነገር ያጋልጣል፡፡ በድህነት ላይ ኳሻርኳራዊው ኢኮኖሚ የፈጠረው አድልዖኣዊው የሀብት ልዩነት ሲጨመርበት ደግሞ አደጋው ቀላል አይደለም፡፡ ብሔራዊ ስሜትን እየናደ፣ ሰብኣዊነትን እየደረማመሰ፣ የሞራልና ግብረ ገብ አጥሮችን እያፈራረሰ፣ የዝምድናንና የወዳጅነትን ድንበሮች ሳይቀር እየጠረማመሰ፣ … ጉድ እየሠራን ያለው ዋነኛ ነገር ድህነት ነውና አሁንም ይታሰብበት፡፡ ቁርሱን እንደምንም ቀምሶ ለምሣው የሚጨነቅ ማኅበረሰብ ይዘን ወዴት እንደርሳለን? ምናልባት ወደ መካከለኛዋ አፍሪካና ወደ የመን፡፡

በሩቅ ስንሰማቸው ይዘገንኑን የነበሩት ኢ-ሞራላዊና ኢ-ሃይማኖታዊ አውሮፓዊ ድርጊቶች እንደሰደድ እሳት እየተስፋፉ መጥተው ሀገር ምድሩን እያጥለቀለቁት ነውና ይህም ይታሰብበት (እርግጥ ነው ዓለም አቀፍ በጀት ተመድቦለት በታላላቅ ወንድሞች የሚተገበር የዘመን ፍጻሜ ምልክት በመሆኑ የትግሉ ከባድነት አይካድም)፡፡ ለማንኛውም እግዚኦ እንበል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሙስና (ጥፋት) ሀገርን በእሳት ቋያ የሚለበልብ ሰማያዊ መርገምት ስለሚያስትል በተለይ አባቶችና እናቶች ሌት ተቀን በርትታችሁ ጸልዩ – እንጸልይ፡፡ ሶዶምና ገሞራ ወደ ኢትዮጵያ እያመሩ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ እርግጥ ነው – በሕይወት ተስፋ መቁረጥና በባዶነት ስሜት መቃተት ለዕኩይ ተግባራት እንደሚዳርጉ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም የዜጎችን የመኖር ተስፋና ጣፋጭ ቤተሰባዊ ኑሮን በማለምለም አኳያ መንግሥትና ጤናማ መያዶች ያላቸው ሚና ቀላል እንዳልሆነ ተገንዝበው በዚህ ዙሪያ ጠንክረው ቢሠሩ ችግሮች ቀስ በቀስ እየተቀረፉ የመሄድ ዕድላቸው የሰፋ ይመስለኛል፡፡ የሆኖ ሆኖ ይህም ይታሰብበት፡፡ በአየር ላይ “ሀገር፣ ሀገር” ማለቱ ፋይዳ የለውም፡፡ “ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል” እንዲሉ ሀገር ያለች እየመሰለች ከእጃችን እያመለጠች እንደሆነ ይታየኛል፡፡….

ጠጭነት፣ ሰካራምነት፣ ሀሽሻምነት፣ ወፈፌነትና ዕብደት፣ ሴተኛ አዳሪነት፣ ሥራ ፈትነት፣ ሥራ አጥነት…. እየተበራከቱ ነው፡፡ እነዚህ ማኅበራዊ ነቀርሣዎች እየቀነሱ እንዲሄዱ የሚደረግበት መፍትሔ ካልተገኘና በተናጠል መክበር ፋሽን እንደሆነ ከተጓዝን የጋራ ሀገር አይኖረንም፤ ሁላችንም እናጣለን እንጂ አንዳችንም ደግ ነገር አናገኝም፡፡ አዲስ አበባን በዋናነት ይዛችሁ ከተሞችን በሥራ ሰዓት ታዘቡ፡፡ መንገዶች ላይና መጠጥ ቤቶች ውስጥ የሚታየው የሰው ብዛት፣ አስፋልቶች ላይ የሚርመሰመሰው የመኪና ብዛት… ሲታይ  “ለመሆኑ በዚህች አገር ሥራ የሚሠራው ሌሊት ነው እንዴ?” ያስብላል፡፡ የውጭ ሰዎች ይህንን ሁኔታችንን ሲታዘቡ ምን እንደሚሉን ባውቅ ደስ ባለኝ፡፡ ደግሞም በአውሮፓ መንገዶች እንደብርቅ የሚታዩ ዘመናዊ አውቶሞቢሎች እዚህ በኛ በድሃዋ ሀገር ያላንዳች ሀፍረት ሽንጣቸውን እያሳዩ እዚያና እዚህ በብዛት ሲታዩ ሀገራችንን የዕንቆቅልሾች መፈልፈያ ዋሻ ማድረጋቸውን እንረዳለን፡፡ ግርምቲ ዓዲ – ማለትም ሀገር፡፡ ይሄኔ እኮ የዚያ መኪና ባለቤት አጎት ለማኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ጉረኞች እኮ ነን!

ስለዚህ የደመወዙ ማነስ፣ የገንዘቡ የመግዛት አቅም ማሽቆልቆል፣ የመንገዱ መጥበብና በየቀኑ ከሚጨምረው የተሸከርካሪና የሰው ብዛት ፈጽም አለመጣጣም፣ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ከፍተኛና ማዘጋጃ ቤት እንዲሁም የትኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ድረስ የሚታየው የሙስናና የዘመድ አዝማድ አሠራር መንሰራፋትና የባህል ያህል መቆጠር፣ የዜግነትና ብሔራዊ ስሜት መጥፋት፣ የሀኪም ቤቱና የሀኪሞቹ ጥራት መጓደል፣ የትምህርቱ ጥራት ወደ ዜሮ መውረድ፣ የህግ አስከባሪው ንቃተ ኅሊና መዝቀጥ፣ ድንበር ያጣው ሆዳምነት፣ ትውልድን እየገደለ ያለው ማይምነት፣….. መንግሥታዊ ትኩረት አግኝቶ ልዩና የተቀናጅ ሥራ እንዲሠራበት ይደረግ፡፡ ምናልባት ያኔ መኖር ብጀምር ማለቴ ብንጀምር …

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s