የብሔር ፖለቲካ ሁልጊዜ ጥርጣሬን እንጂ መተማመንን አያመጣም – አቶ ኦባንግ ሜቶ

“ሃገሩም፣ ሕዝቡም፣ መሬቱም አየሩም እርቅ ይፈልጋል”

• የብሔር ፖለቲካ ሁልጊዜ ጥርጣሬን እንጂ መተማመንን አያመጣም
• ሁላችንም የምንመኛትን ኢትዮጵያ፣በተናጠል በመሯሯጥ አንፈጥራትም
• እርቁ ለወጣቶቻችን የሞራል ልዕልናን የሚያመጣ መሆን አለበት
• እርቅ ለከባድ ወንጀል አቋራጭ ማምለጫ መሆን የለበትም

የኢትዮጵያ መንግስት የብሔራዊ እርቅና መግባባት ጥያቄ በተነሳ ቁጥር “የተጣላ የለም” እያለ ጉዳዩን ውድቅ ሲያደርገው ቆይቷል፡፡ አሁን ግን የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስት፤ የእርቅን አስፈላጊነትን አምኖበት ተነሳሽነቱን በመውሰድ
ብሔራዊ የእርቅ ኮሚሽን አቋቁሟል፡፡ “የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ” መስራችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ የእርቅ ኮሚሽን መቋቋሙን በእጅጉ ይደግፉታል – እርቅ ለሃገሪቱ ፈውስን ያመጣል በማለት። ዶ/ር ዐቢይ የእርቅ ኮሚሽን ማቋቋማቸው አርቆ
አሳቢነታቸውን ያሳያል ሲሉም አድንቀዋል። ለመሆኑ የእርቅ ኮሚሽን ፋይዳው ምንድን ነው? በእርቅ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉት
እነማን ናቸው? እርቅ እንዴት ይፈጸማል? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ አቶ ኦባንግ ሜቶን አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

መንግስት ብሔራዊ የእርቅ ኮሚሽን አቋቁሟል፡፡ በአሁኑ ወቅት የእርቅ ኮሚሽኑ ለአገሪቱ ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?
የእርቅ ጉዳይ በጣም ዘግይቷል፡፡ ብዙ ስንጠብቀው የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ እርቅ ማድረግ ለሃገሪቱ ፈውስን ያመጣል፡፡ አሁን መታሰቡ በራሱ መልካም ነው። ሃገሪቱ ለውጡን ወደፊት እንድታሻግርና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ እርቅ ትልቁን ድርሻ ይይዛል። እርቅና ብሔራዊ መግባባት የተለየ ትርጉም የለውም፤ ሰላም መፍጠር ነው ትርጉሙ፡፡ እርቅን አልፈልግም ሲል የነበረ፣ ሰላምን አልፈልግም ማለቱ ነው፡፡ እርቅን እፈልጋለሁ የሚል ደግሞ ሰላምን አብዝቶ የሚሻ ነው። የአንድነት ምንጩ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባት ደግሞ የሚመጣው በእርቅ ነው። አሁን ሃገሩም፣ ሕዝቡም፣ መሬቱም አየሩም እርቅ ይፈልጋል፡፡ ሁላችንም ደምተናል፣ ብዙ ቁስል አለን፣ መአት ግፍን ተቀብለናል፡፡ ይሄን መሻር የሚቻለው በእርቅ ብቻ ነው፡፡ እርቅም ብሔራዊ መግባባትን ያመጣል፡፡ የኛ ድርጅት አንዱ አላማ “ለመተማመን እንነጋገር” የሚል ነው፡፡ የሃገራችን አንዱ ችግር መተማመን ማጣት ነው፡፡ የብሔር ፖለቲካ ነው የተጫነብን፡፡ የብሔር ፖለቲካ ሁልጊዜ ጥርጣሬን እንጂ መተማመንን አያመጣም፡፡ ባለፉት 13 ዓመታት የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ በራሱ ያለመተማመናችን ውጤት ነው፡፡ አንድነት የሚል ቃል በዚህ የብሔር ብሔረሰቦች በአል ላይ ብዙም ሲነገር አይስተዋልም። አሁን ያለፉትን 27 ዓመታት ያለመተማመን ምዕራፍ ዘግተን፣ ቁስሎችን በእርቅ አክመን ወደፊት መሻገር፣ ከፊት ለፊታችን ያለ መልካም ዕድል ሆኖ ይታየኛል፡፡
የእርቅ ኮሚሽን የሚያስፈልጋቸው እንደኛ ዓይነት አገራት ብቻ ናቸው ወይስ–?
በርካታ አገራት የእርቅ ኮሚሽን አላቸው፡፡ በቋሚነት ነው የሚሰራው፡፡ እኔ በምኖርበት ካናዳ የእርቅ ኮሚሽን አለ፡፡ በአውስትራሊያና በሌሎች አገራትም አለ፡፡ እኛ ብዙ ችግር አለብን፤ በዚያው ልክ የዳበረ የእርቅ ባህላዊ ስርአት አለን፤ ነገር ግን የእርቅ ኮሚሽን የለንም፡፡ ብዙም ችግር የሌለባቸው አገራት በቋሚነት የእርቅ ኮሚሽን ካላቸው፣ እኛ ብዙ ችግር ያለብን እንዴት አይኖረንም? ከአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግስት ከስልጣን መነሳት ጀምሮ በደርግ፣ በኢህአዴግ ዘመን—እስካሁን ብዙ ቅራኔዎች ናቸው በሀገሪቱ ያሉት፡፡ በቀይ ሽብር እርስበርሳችን ተጨራርሰናል፡፡ ከቀይ ሽብር ጎን ለጎን የእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ነበርን፡፡ ኢህአዴግ ከገባ በኋላ ስለ ሃገር አንድነት የተወራበት አጋጣሚ የለም፡፡ አንድ ህዝብ፣ አንድ ቤተሰብ እንደሆንን ሳይሆን የተለያየን እንደሆንን ነው ሲነገር የኖረው፡፡ ይሄ የህዝባችንን ስነ ልቦና ገዝግዞታል፡፡ ለዚህ ሁሉ እርቅ ያስፈልገናል፡፡ ከገጠር እስከ ከተማ – በእያንዳንዱ ቀበሌና ጎጥ እርቅ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ከዚህ ቀደም ያቋቋምነው ድርጅት በዋናነት እርቅ ላይ አተኩሮ መሥራት ነበር ዓላማው። በወቅቱ ብዙ ነገር ሞክረን አልተሳካም፡፡
ምን ነበር የሞከራችሁት?
በሃገራችን እርቅ ለማምጣት ነበር የሞከርነው። ነገር ግን ባለው መንግስት ተቀባይነት ባለማግኘቱ አልተሳካም፡፡ አሁን ዶ/ር ዐቢይ የእርቅ ኮሚሽን ማቋቋማቸው፣ አርቆ አሳቢነታቸውን ያሳያል፡፡ እርቅ ቋሚ ነው መሆን ያለበት፡፡ እኛ የራሳችን አገራዊ ባህልና ወግ አለን፡፡ በሱ መሰረት የሽምግልና ባህላችንን ተጠቅመን ነው እርቅ ውስጥ መግባት ያለብን፡፡ በዚህ ሃገር እኮ እንደ ህዝብ፣ እንደ ሃገር እስከ ዛሬ ያቆየን የመንግስት መኖር አይደለም፤ ባህላችንና የሽምግልና ጥልቅ መሰረታችን ነው፡፡ እኛን እንደ ኢትዮጵያ ያቆየን የቤተ-መንግስት ህግና አዋጅ ሳይሆን የባህላዊ እርቅና ሽምግልና ስርአታችን ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ የኛ ሃገር ችግሮች በሙሉ የተፈቱት በዛፍ ጥላ ስር እንጂ በመስታወት በተንቆጠቆጠ ዘመናዊ ህንፃ ውስጥ አይደለም፡፡ አሁንም እርቅ ስንል ህገ መንግስቱ የውጪ ሃገር “ኮፒ” ነው እንደሚባለው ሁሉ፣ የእርቅ ስርአቱ “ኮፒ” እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን፡፡ “ቅጂ” ያው “ቅጂ” ነው፤ ኦርጂናል አይሆንም፡፡ እኛ የራሳችን የእርቅ ባህል አለን፡፡ ይሄን አውጥተን መጠቀም አለብን፡፡ እኔ ወደዚህ ከመጣሁ በኋላ በኦሮሚያ፣ ጉራጌ፣ አማራና ሌሎችም አካባቢዎች ያሉ የሽምግልና ስርአቶችን ስመለከት ነበር የቆየሁት፡፡ አስደናቂ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ለዚህ ነው ሀገሪቱ በቤተ-መንግስት ህግ ሳይሆን በሃገር ሽምግልና ነበር የቆመችው ያልኩት፡፡
አገራዊ እርቅ እንዴት ነው የሚፈጸመው?
እርቅ ማለት ያበጠ ቁስልን ማዳን ነው፡፡ ያበጠ ቁስል የሚድነው ውስጡ ያለው ቆሻሻ ሲወጣ ብቻ ነው፡፡ በቁስል ላይ የሚያደርቅ መድሃኒት ከማድረጋችን በፊት ቆሻሻውን እንደምናወጣ ሁሉ በደልንና መገፋፋትን በእርቅ ለማዳን ከፈለግን፣ በመጀመሪያ ያበጠው ቁስል ፈንድቶ ቆሻሻው መፅዳት አለበት፡፡ ይሄን ክፉ ነገር ከእያንዳንዳችን ውስጥ የምናወጣው በውይይት ነው፡፡ በመነጋገር ነው፡፡ ሃገራችን እኮ ባለፉት 27 ዓመታት ጨለማ ውስጥ ነበረች፡፡ አሁን ዶ/ር ዐቢይ ከመጡ በኋላ ትንሽ ብርሃን አግኝተናል፡፡ በብርሃን ውስጥ እውነትን መፈለግ ይቻላል፡፡ እውነት ብርሃን ነው፡፡ ጨለማ ብርሃንን እንደሚሸሽ ሁሉ ውሸት እውነትን ይሸሸዋል፡፡ ፊት ለፊት አይጋፈጠውም፡፡ ዛሬ ብርሃን ሲመጣ ሌቦቹ፣ ነፍሰ ገዳዮቹ ሸሽተዋል፡፡ እርቅን ስንጀምር ከጨለማው ሳይሆን ከብርሃኑ ነው። ከብርሃን ስንጀምር በኃይል እያበራን፣ ጨለማውን እየገፈፍን እናበራዋለን፡፡ ለዚህ ደግሞ እውነተኛ እርቅን የሚፈልጉ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሞልተዋል። እነሱን ፊት አውራሪ ማድረግ ይቻላል፡፡ ዶ/ር ዐቢይ የጀመረው ጥሩ ስራ አለ፡፡ ያንን ሁላችንም ጉልበት ሆነን የበለጠ ልናሰፋው ይገባል፡፡ በሃገራችን ቁርሾዎችን በእርቅ ዘግተን መሻገር የምንችልባቸው እድሎች በርካታ ነበሩ፤ ግን አልተጠቀምንባቸውም። አሁን ከንቀት ባህሪ ወጥተን እያንዳንዱን መልካም ነገር መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የትም አይደርሱም የሚለው ንቀት አይሰራም፡፡ ወያኔዎች ከጫካ ሲመጡ “እነዚህ የትም አይደርሱም” ተብለው ነበር፤ ነገር ግን ባለፉት 27 ዓመታት የት እንደደረሱ በሚገባ አሳይተውናል። ይሄን መልካም አጋጣሚ እንዳናባክነው ሁላችንም የየድርሻችንን መወጣት አለብን፡፡ ሁላችንም የምንመኛትን ኢትዮጵያ፣ በየፊናችን በተናጠል በመሯሯጥ አንፈጥራትም፡፡ እየተደማመጥን የበራውን ጥቂት ብርሃን እየተከተልን፣ በየመንገዳችን አብሪዎችን እየጨመርን ስንጓዝ ነው፣ ሁላችንም የምንመኛትን ብሩህ ኢትዮጵያን ልናገኝ የምንችለው፡፡ ለዚህም ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ሁልጊዜም ስለ እርቅ ሲነሳ፣ ማን ከማን ጋር ነው የሚታረቀው? የሚል ጥያቄ ይሰነዘራል፡፡ በእርቁ የሚካተቱት እነማን ናቸው?
ማን ከማን ጋር ነው የሚታረቀው? የሚለው ጥያቄ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ማን ያልተጣላ አለና ነው ይሄን የምንለው? ከራሳችን ጋር እንኳ ሳይቀር ተጣልተናል እኮ! በብሔር ተከፋፍለን፣ በፖለቲካ ተከፋፍለን ተጣልተናል፤ ተቋስለናል፡፡ በምድራችን ላይ ያልተጣላ ሰው የለም፡፡ ስለዚህ እርቁ መንፈሳዊ ነው። እርቁ ከራስ ይጀምራል፡፡ ከራሳችን ጋር ስለተጣላን ሁላችንም በቅድሚያ ከራሳችን ጋር ታርቀን፣ ክፉ ሃሳብን ከልባችን አንቅረን አውጥተን ጥለን፣ አዲስ የይቅርባይነት ልብን ማግኘት አለብን፡፡ ከዚያ ወደ እርስበርስ እርቅ መሄድ እንችላለን፡፡ እንደሚታወቀው በሃገራችን አንድም በብሔራዊ መልኩ የተቋቋመ የፖለቲካ ድርጅት የለንም። ፓርቲዎች በየብሔራቸው የተሰፉ ናቸው። ኢህአዴግ የነፃ አውጪዎች ስብስብ ሆኖ ነው ሀገር ሲመራ የቆየው እንጂ ብሔራዊ የአንድነት ሃይል ሆኖ አልነበረም፡፡ ነፃ አውጪነት በራሱ እርቅ ያስፈልገዋል። እኛ በብሔር፣ በጎጥ የተከፋፈልን ነን። በዚህ ብዙ ተጎዳድተናል፡፡ እርቅ ያስፈልገናል። በሀገራችን ያልተጣላ ሰው የለም፡፡ ብሔራዊ (ህብረ ብሔራዊ) ተቋም የለንም፡፡ ሁሉም ጎጡን እያሰበ ነው የሚጓዘው። በዚህ ሁላችንም ተጣልተናል፡፡ ኢትዮጵያን (ምድራችንን) ማሰብ የተውነው ለዚህ ነው፡፡ ባንጣላ ኖሮ 1.8 ሚሊዮን ዜጎች አይፈናቀሉም ነበር፡፡ የተጣላ ባይኖር ኖሮ፣ አሁን እኔና አንተም የእርቅን ጉዳይ መነጋገር አያስፈልገንም ነበር፡፡ አንዱ አንዱን ሲበድል ኖሯል፤ በሁሉም መንገድ በደሉ ደርሷል፡፡ ድሮ መሬት ላራሹ ነበር ትግሉ፤ ነገር ግን በኋላ ይሄ ተቀይሮ መሬት ለብሔሩ፣ መሬት ለጎሳው እያልን ሌላውን ወደ መግፋት ነው የተገባው፡፡ በብሔራዊ ደረጃ ማሰብ እየቻልን፣ ወደ ጎጠኝነት ነው የወረድነው፡፡ ከመሬት ላራሹ ሰፊ ፅንሰ ሃሳብ ወርደን፣ ወደ መሬት ለብሔሬ ነው የገባነው። ብዙ በደል ደርሷል፡፡ ብዙ ተበዳድለናል፡፡ ስለዚህ እርቅ በእነዚህ ሁሉ አካላት ዘንድ ያስፈልጋል፡፡
ከአገራዊ እርቁ የሚጠበቀው ውጤት ምንድን ነው?
እርቁ እንደገና ባለሙሉ ሰብዕና አድርጎ እንዲሰራን ነው የሚያስፈልገው፡፡ እንደገና ኢትዮጵያዊነትን እንድንገነባ፣ እንደገና አዲስ የሰብዕና ማንነት እንድንላበስ ነው የሚፈለገው፡፡ አንድን ሰው በሰውነቱ እንጂ በዘሩ፣ በብሔሩ፣ በመልኩ፣ በቋንቋው ሳይሆን በሰብዕናው ብቻ እንድንመለከተው የሚያደርግ እርቅ ነው የሚያስፈልገው፡፡ እርቁ መደማመጥን መከባበርን፣ መዋደድን፣ ቅንነትን፣ የይቅርታ ልማድን የሚያመጣ እንዲሆን ነው መሰራት ያለበት፡፡ ለወጣቶቻችን የሞራል ልዕልናን የሚያመጣ እርቅ እንዲሆን ነው መሰራት ያለበት፡፡ ዛሬ እናቶቻችን ቃና ቴሌቪዥን ተመልካች ሆነዋል። ስለዚህ እናቶቻችን ከቃና፣ ወጣቶቻችን ከምርቃና ወጥተው፣ የሞራል ልዕልናን ተላብሰው፣ ሀገራቸውን ወደፊት እንዲያሻግሩ የሚያግዝ እርቅ ነው መሆን ያለበት፡፡ ኢትዮጵያን በሞራል ልዕልና መገንባት መቻል አለብን፡፡ ሰብአዊነትን የሚገነባ እርቅ ነው የሚፈለገው፡፡
በዚህ እርቅ እነማን ናቸው በዋናነት ተሳታፊ መሆን ያለባቸው?
በትክክል የሃገር ፍቅር ያላቸው ሰዎች በዋናነት እንዲሳተፉ መደረግ አለበት፡፡ በእርቅ ጉዳይ ሰፊ ልምድ ያላቸው አሉ፡፡ እነሱ ተሳታፊ መሆን አለባቸው። የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች አሉን፡፡ በርካታ ስነ ምግባር ያላቸው ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ከዶ/ር ዐቢይ የሚጠበቀው እነዚህን ኢትዮጵያውያን በባትሪ መብራት አፈላልጎ ማግኘት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከተሰበሰቡ ከእነሱ ብዙ ማትረፍ እንችላለን፡፡ እርቁ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም፤ ኢትዮጵያን እንደ ኢትዮጵያ የማቆየት ጉዳይ ነው፡፡
የእርቅ ባህላችን ተሸርሽሯል፤ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ተአማኒነት ቀንሷል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር እርቁ ስኬታማ የሚሆን ይመስልዎታል?
ይሄን ከሚሉ ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ፡፡ የሃይማኖት አባቶች እኮ የሃይማኖት አባቶች ሳይሆን የፖለቲካ አባቶች ነው የነበሩት፡፡ የሃይማኖት አባቶች እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሳይሆን መንግስትን የሚፈሩ ነበሩ፡፡ ሽማግሌዎችም የሃገር ሽማግሌዎች ሳይሆን የመንግስት ሽማግሌዎች ሆነው ነው የቆዩት። በዚያው ልክ ለእውነት፣ ለእምነት፣ ለምድራዊና ሰማያዊ ፍትህ የታገሉ የሞቱ የሃይማኖት አባቶች አሉን፣ ነበሩን። እነዚህ ጥቂቶች ናቸው። እነዚህን እግዚአብሔርን የሚፈሩ ትክክለኛ የሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች በባትሪ መፈለግ ነው ያለብን፡፡ እነዚህን ነው የምንፈልገው እንጂ ትናንት በሌላ ጉዳይ ውስጥ የነበሩትን አይደለም። እነዚህን በመምረጥ በኩል ዶ/ር ዐቢይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ ከቀጣፊ ምሁር ይልቅ ያልተማረ፣ ፈጣሪውን የሚፈራ ሰው ይሻለናል። እንደዚህ ዓይነት ሰዎችን ነው በዚህ መድረክ ፊት አውራሪ አድርጎ ማቅረብ፡፡
ከእርቁ በፊት የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ተቋቁሞ፣ የተፈፀሙ ግፎችና በደሎች መነገር አለባቸው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
አንዱ መሰራት ያለበት በዚህ ጉዳይ ላይ ነው። እውነትን ከስሩ መፈለግና ማጥራትማ አስፈላጊ ነው። አለበለዚያ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ነው የሚሆነው፡፡ ገለልተኛ አካል መቋቋም አለበት፡፡ ነፃና ገለልተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተቋቁሞ እውነቱ መጣራት ይኖርበታል፡፡ ገለልተኛ የሆነ መርማሪ መቋቋምና ከደርግ ዘመን ጀምሮ በግፍ የሞቱ ሰዎች እውነት መውጣት አለበት፡፡ ይሄ መሆኑ አንድም መማሪያ ይሆናል። ከስህተታችን መማር እንድንችል ስህተቱ በግልጽ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ እንደውም በተሰሩ ስህተቶች መግባባት ላይ ከደረስን በኋላ ሃገሪቱ ዲሞክራሲን ለመውለድ ስታምጥ በቆየችባቸው ያለፉት 40 እና 50 ዓመታት የተፈፀሙ ስህተቶችን የሚዘክር ሙዚየም መቋቋም አለበት፡፡ ሙዚየሙ የበቀል ማስታወሻ ሳይሆን የመማሪያ መሆን አለበት። በዚህ ጉዳይ ላይ እኔም እያነጋገርኳቸው ያሉ አካላት አሉ። የሚቋቋመው ሙዚየም የበቀል ማስታወሻ ሳይሆን ታዳጊዎች ኢትዮጵያ ምን እንደነበረች የሚማሩበት መሆን አለበት፡፡ ይሄ እንዲሆን ደግሞ የእውነት አፈላላጊ አካል መቋቋምና ያለ ቂም በቀል በሁሉም ወገን የደረሱ ጉዳቶችን ማፈላለግ አለበት፡፡ ያለፈውን ምዕራፍ የምንዘጋበት የማስታወሻ ሙዚየም ነው መቋቋም ያለበት፡፡
በአንድ በኩል ወንጀል ፈፅመዋል የተባሉ ግለሰቦችን ለህግ የማቅረብ ተግባር እየተከናወነ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የእርቅ ኮሚሽን እየተቋቋመ ነው። እነዚህን ሁለት መንገዶች እንዴት ነው አስታርቆ መጓዝ የሚቻለው?
ብዙ በደል የፈፀሙና ሰውን የገደሉ ለህግ መቅረብ እንደሚገባቸው ጥርጥር የለውም፤ ፍትህ መኖር አለበት። ወንጀል የሰሩ ሁሉ በሰሩት ወንጀል በህግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ የከፋ ወንጀል በእርቅ መሸፈን የለበትም፡፡ ብዙ ሰው የገደለ፣ የገረፈ፣ ያሰቃየ፣ ሃገር የዘረፈ ይቅርታና እርቅ አያሻውም፡፡ እርቅ ለከባድ ወንጀል አቋራጭ ማምለጫ መሆን የለበትም፡፡ በዚህ የእርቅ ሂደት አንዱ ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ ይሄ ነው።
ወደ ሃገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በበርካታ የሃገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውረዋል፡፡ በተጓዙባቸው አካባቢዎች ምን ታዘቡ? የህብረተሰቡን ሥነ ልቦናስ እንዴት አገኙት?
ያየሁት ትልቁ ነገር፣ ህዝባችን ከጠበቅሁት በላይ ጥሩ ህዝብ መሆኑን ነው፡፡ በየሄድኩባቸው ቦታዎች ሁሉ ከገበሬውም ከሃገር ሽማግሌዎችም ከሃይማኖት አባቶችም ከወጣቶችም ጋር ለመገናኘት ሞክሬያለሁ። ከበርካቶቹ ጋር ተወያይቻለሁ፡፡ ከእነዚህ ውይይቶች የተገነዘብኩት ፖለቲከኞቹ እንጂ ህዝባችን አሁንም ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚጨነቅ መሆኑን ነው። ግን ባለፉት 27 ዓመታት የተረጨው የዘር መርዝ ፖለቲካ አመራሩን አበላሽቶታል፡፡ ደግነቱ መርዙ ህዝቡ ጋ ያን ያህል አልደረሰም፡፡ ህዝቡ አሁንም አብሮ በመኖር ስሜት ውስጥ ነው፡፡ አሁንም ህዝባችንን አንድ ለማድረግ የመርዙን ኃይል ማርከስ ይቻላል፡፡ በየቦታው ግጭት የሚፈጥሩት ቡድኖች እንጂ ህዝቡ አይደለም፡፡ ህዝባችን ጤናማ ነው፤ በሽታው ያለው ፖለቲከኞቹ ጋ ነው፡፡ ህዝባችን ሃገር ወዳድ እንደሆነ ታዝቤያለሁ፤ ነገር ግን አርአያዎቹን ፍለጋ ላይ ነው፡፡ ህዝቡ እግዚአብሔርን ይፈራል፤ ፖለቲከኞቻችን ግን በተቃራኒው ናቸው። ውስጣቸው የጥላቻ፣ የቂም በቀል ፖለቲካ ነው ያለው፡፡ እኔ በህዝባችን ተስፋ ስለማደርግ፣ በቀላሉ ከጥፋት መንገድ መመለስ እንችላለን ብዬ አምናለሁ። እኛን አንድ ያደረገን ኢትዮጵያዊነታችን ነው፡፡ ከዘር የበላይነት ወደ ኢትዮጵያዊነት የበላይነት የሚደረገው ትግል እንደሚሳካ አልጠራጠርም፡፡ ጥላቻን በህዝቡ በጎነት መፈወስ እንችላለን፡፡
እውነት ማለት ብርሃን ነው፡፡ በእውነት ጥላቻን ማሸነፍ፣ ጨለማን መግፈፍ እንደምንችል ባደረግኋቸው ጉብኝቶች ታዝቤያለሁ። ሰውን እንደ ሰውነቱ የሚያከብር ህዝብ አለን፡፡ በዚህ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ጥቂት የእውነት ብርሃን በሁላችንም ሰፍቶ ጨለማውን ሁሉ መግፈፍ እንደምንችል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ለዚህ እያንዳንዳችን ኃላፊነት አለብን።

Addis Admass Newspaper

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s