የቤት እድሳቱ ላይ ላዩን ከሆነ የዉሸት እድሳት ነው (ግርማ ካሳ)

“ዛሬ በየቦታው የሞትና የመፈናቀል ዜና እየሰማችሁ ይሆናል። ሊታደስ እየፈረሰ ያለ ቤት ፍርስራሽ ስለሚበዛው በአከባቢው አቧራና የሚያውክ ነገር መኖሩ አይቀርም። እናንተ ግን ማወቅ ያለባችሁ ይህ እድሳት ተጠናቆ ውብ የሆነ ቤትና ውብ የሆነች ኢትዮጵያን የሚናስረክባችሁ መሆኑን ነው”

ይሄን ያለው ዶ/ር አብይ ነው። የሚሞቱትንና የሚፈናቀሉትን እንደ “ፍርስራሽ” ማስመሰሉ አልተመቸኝም። ሆኖም ግን ያለዉን በተግባር የሚያሳየን ከሆነ እሰየው ነው። ግን ይሄ ንግግሩ ከንግግር ያለፈ ይሆናል ብዬ አላስብም። በአንድ ትልቅ ዋና ምክንያት።

ቤት ከሚያፈርሱ ነገሮች አንዱ ምስጥ ነው። ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ያለው ነገር፣ የኢትዮጵያ ምስጦች፡

– የጎሳና የዘር ፖለቲካው፣ 
– ዜግነትን ኢትዮጵያዊነትን ሳይሆን የብሄር ብሄረሰባ ሕዝብ የሚሉትን ወይም ዘርን ያንጸባረቀው ሕግ መንግስትና 
– ይሄ መሬት የትግሬ፣ ያ መሬት የኦሮሞ፣ እዚያ ማዶ የጉራጌ….በሚል፣ ዜጎች የከፋፈለው የጎሳና የዘር አወቃቀሩ 

ናቸው።

ዶ/ር አብይ እነዚህ ምስጦች ላይ ሳያነጣጥር፣ እንዴት አድርጎ ዜጎች በሁሉም የአገሪቷ ክፍለ በሰላም የሚኖሩባትን ዉብ ኢትዮጵያ እንደሚያስረከብን አላውቅም። እስክ አሁን ባለው ሁኔታ እነዚህን ምስጦችን ለማስወገድ፣ የዶ/ር አብይ አስተዳደር መሰረታዊ የሆኑ ለውጦችን ሊያሳይ እንደሚችል የሚያሳይ ምልክት አላየሁም። አዎን የአስተዳደር፣ የማንነትና የአከላለል ወሰኖችን የሚመለከት ኮሚሽን ተቋቁሟል።፡ሆኖም ይህ ኮሚሽን ሕገ መንግስቱን የሚያሻሻል ሳይሆን ለዜግነት ቦታ በማይሰጠው ሕገ መንግስት ላይ መሰረት በማድረግ አንዳንድ የአከላለል ማሻሻያዎችን ሊያደርጉ ይችላሉ። እንደዚያም ሆኖም አሁንም አከላለሉ የዘር ሆኖ ነው የሚቀጥለው። ያ ብቻ አይደለም፣ ኮሚሽኑ የሚያቀርበው ሪፖርት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚባለው ጸረ-ሕዝብና ጸረ-ዲሞክራሲያዊ አካል በኩል ነው የሚፈጸመው።

ብዙ ጊዜ በተለያዩ ጦማሮች እንደጠቀስኩት፣ አሁን ያለው ዘርን መሰረት ያደረገው ሕግ መንግስት ካልተሻሻለ፣ አሁን ያለው የጎሳ አወቃቀር ፈርሶ፣ ለአስተዳደር አመች የሆኑ፣ ዘርና ጎሳ ላይ ያላተኮሩ፣ ማንም ኢትዮጵያዊ ዘሩ፣ ሃይማኖቱ ሳይጠየቅ በሰላም መኖር፣ መማር፣ መነገድ፣ ኢንቨስት ማድረግ፣ ፣ መምረጥ፣ መመረጥ የሚችልበት ፌዴራል መስተዳድሮች እንዲፈጠሩና ዘር ክፖለቲካና ከአስተዳደር ከሕገ መንግስቱ እንዲወጣ ካልተደረገ ዉቢቷን ኢትዮጵያ አናያትም። 

የፈረሰውን ወይንም ሊፈርስ ያለውን ማደስ የተቀደሰ ተግባር ነው። ግን ለቤቱ መፈራራስ ምክንያት የሆነውን ሳይነኩ እድሳቱ ላይ ላዩ ከሆነ ግን እድሳቱ የዉሸት ነው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s